www.maledatimes.com መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፤ (“ነፍስ ካለ፣ መፍጨርጨር አይቀርም!”) በሰሎሞን ተሰማ ጂ. (SEMNAWOREQ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፤ (“ነፍስ ካለ፣ መፍጨርጨር አይቀርም!”) በሰሎሞን ተሰማ ጂ. (SEMNAWOREQ)

By   /   January 14, 2013  /   Comments Off on መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፤ (“ነፍስ ካለ፣ መፍጨርጨር አይቀርም!”) በሰሎሞን ተሰማ ጂ. (SEMNAWOREQ)

    Print       Email
0 0
Read Time:36 Minute, 32 Second

prof mesfin bookበሐምሌ 1955á‹“.ም የወጣው መነን መጽሔት፣ (7ኛ ዓመት፣ ቁ.10 ዕትም፣ በገጽ 27) ላይ እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፤ “እኚህ የ33 ዓመት ወጣት በአባታቸው ጎንደሬ፣ በእናታቸውም ይፋቴ ሲሆኑ፣ በአማርኛ የበሰሉ በመሆናቸው የመናገርና የማስረዳት ስጦታ ያላቸው ትሁት ወጣት ናቸው፤” ሲል ይገለጻቸዋል፡፡ ለጥቆም የወጣቱን መስፍን ወልደ ማርያም ሦስት ሐሳቦች እንደሚከተለው አስፍሮት ይገኛል፡፡ “ማናችንም በዘመኑ የምንገኝ ትውልዶች በምናውቀውና በተማርነው ችሎታችን ተሽለን ተገኝተን፣ የዚህ ዕድል ተሣታፊ ለመሆን የሚጓጉ ወንድሞቻችንን ለመርዳት የምንቦዝንበት ትርፍ ጊዜ እንዲኖረን አያሻም፡፡ …. እኔ ካወቅሁ ሌላው እንዲያውቅ መድከም የለብኝም ማለት፤ በዚህ ዓለም ላይ ብቻዬን በአንድ እግሬ ቆሜ እኖራለሁ ብሎ እንደማሰብ የሚቆጠር ነው፡፡….የሰው ሁሉ የተፈጥሮ ባሕርዩ ለየቅል መሆኑ ሲታመን፤ ይህን የየግል የነበረውን መንፈስ ሰብስቦ ለማስተማር ያለው የመምህሮች ድካም በቀላሉ የሚገመት ባይሆንም፣ ይህን ከመሰለው ጋር መሰለፍም ለመምህራኖች የታሪክ ክብር ነው፡፡” ልብ በሉ ይህ ንግግር የታተመው የዛሬ ሃምሳ ዓመት ገደማ ነው፡፡ ወጣቱ መስፍንም የገባውን ቃል ለመፈጸምና ለዕውቀት “የሚጓጉትን ወንድሞቻችንን ለመርዳትና ለማስተማር” በወሰነውም መሠረት፣ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ቃልና ተግባር ተስማምተው ሲገኙ ሁሌም ያስመሰግናሉ፤ ያስከብራሉም፡፡

ከመጋቢት 2002 ዓመተ ምህረት ጀምሮ፣ ይኼንን መጽሐፍ ሲያሳትሙ አራተኛ ሥራቸው/መጽሐፋቸው ነው፡፡ በሠላሳ ሦስት/አራት ወራት ውስጥ አራት ደህና-ደህና መጽሐፍትን ጽፎ ማሳተም ከባድ ተግባር ነው፡፡ በተለይም ሩጫው ከዕድሜና እርጅና ይዞት ከሚመጣው ጫና ጋር ሲታሰብ ከባድ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡ ኧረ ለመሆኑ፣ ሰማኒያ ሲደመር (80+)….ምናምን ሆኖ በሣምንታዊ ወይም በየሁለት ሳምንቱ የሚወጣ ጋዜጣና መጽሔት ላይ የሚጽፍ ኢትዮጵያዊ ማነው?  ማነው ወቅታዊ ሁኔታዎችን ዕለት-በዕለት ተከታትሎ ከዕድሜና ከኑሮው/ከተሞክሮው እንዲሁም ከተማረው ትምህርት ጋር መርምሮና ፈትሾ ለሕዝብ እምነቱንና እውነቱን ባደባባይ የሚጽፈው? ማነውስ በጡረታ ዘመኑ፣ “አገዛዝን አልፈራም” ብሎ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጉባኤ/ድርጅት ከተባባሪዎቹ ጋር አቋቁሞ ገዢዎችን የሚሞግተው? ብዙዎች፣ ገዢዎችን ፈርተው፣  በፍርሐትም ተሸብበውና በተስፋ መቁረጥ ተሰንገው ዳር ቆመው ሲመለከቱ (ይሳካም-አይሳካም) ከሕዝብ ጎን/ጋር ተሰልፎ በሦስቱም ሥርዓቶች የተገኘው ሊቅ ማነው?(á‹« ሰው በሚያዝያ 16 ቀን 1922á‹“.ም እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ የተወለደው-ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ነው፡፡)
ፕሮፌሰር መስፍን ዋናው የጥናት መስካቸው ጂኦግራፊ ነው፡፡ በ1945ዓ.ም ወደ ሕንድ ሀገር ሔደው ከፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍናና በጂኦግራፊ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በ1948ዓ.ም ወደኢትዮጵያ ተመልሰው በትምህርት ሚኒስቴር-በጆኦግራፊና በካርታ አነሣሥ ኢንስቲቱት ውስጥ ለጥቂት ወራት ሢሠሩ እንደቆዩ፤ በዚያው ዓመት አሜሪካን አገር በሚገኘው የክላርክ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመታት ያህል በጂኦግራፊ ትምህርት የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በ1950ዓ.ም ወደኢትዮጵያም ተመልሰው፣ ወደአሜሪካን ከመሔዳቸው በፊት ይሠሩበት በነበሩበት መሥሪያ ቤት ተመድበው ለሁለት ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ ከዚያም፣ በ1952ዓ.ም ወደቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተዛውረው የጂኦግራፊና የካርታ አነሣሥ ትምህርን በማስተማርና በዚሁ ክፍል ኃላፊ በመሆንም እያገለገሉ ናቸው፤” ሲል ጅማሯቸውን ያትታል፡፡ በጣም ውሱን በሆነ አኳኋን የጻፉትንና መጠነኛ ማሳያ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችለውን “አገቱኒ፡- ተምረን ወጣን (መጋቢት 2002ዓ.ም) የጻፉትን የራሳቸውን መጽሐፍ ማንበቡ የተሻለ መረጃ ስለሚሠጥ አንባቢያን እርሱን እንዲያነቡት ይመከራሉ፡፡
ወደዋናው ጉዳያችን እንመለስ፤ ይኼኛው የፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም መጽሐፍ፣ “እንጉርጉሮ” ብለው (1967ዓ.ም) ያሳተሙትን የግጥም መጽሐፍ ሳይጨምር፣ በአማርኛ ከጻፏቸው መጽሐፍት ውስጥ ሰባተኛው ነው፡፡  በተመሳሳይም፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሰባት መጽሐፍትን በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ጽፈዋል፡፡ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ አገር ጥናታዊ መጽሔቶች ላይ የታተሙ ከሃያ በላይ ጥናቶችን አሳትመዋል፡፡ እጅግ ብርቱ፣ ከማጥናትና ከመመራመር የማይታቀቡ አዛውንት ናቸው፡፡ በቀጥታ፣ ለግምገማ ወደመረጥነው እርዕሰ ጉዳይ እንግባ፡፡ “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፤ (ኢትዮጵያ ሀገሬ፣ ሞኝ ነሽ ተላላ፤ የሞተልሽ ቀርቶ፣ የገደለሽ በላ!) ይሰኛል፡፡ በታኅሣሥ 2005ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሟል፡፡ ጠይቄ እንደተረዳሁት ከሆነ፣ መጽሐፉ በደርግ ዘመን ተጀምሮ በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች ሲደረጉበት የቆየ መጽሐፍ ነው፡፡ ዋጋው ብዙ አይደለም፤ በ45.00 የኢትዮጵያ ብር ገዝቶ ቁምነገር መዝረፍ ያጓጓል፡፡ መጽሐፉ-ካርታዎችን፣ ፎቶዎችንና አባሪዎችን አጠቃሎ 238 ገጾች አሉት፡፡ ገጽ በገጽ ሲገልጡት በአዳዲስ ሃተታዎች የታጨቀ ነው፡፡ የተለየ ጥልቀትም አለው፡፡ (ምናልባትም፣ ይህንን መጽሐፍ በአንድ ክፍል ብቻ መገምገሙ በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ እንዲያውም “ንፉግነት ነው!” ቢባል አያስገርምም፡፡)
ያም ሆኖ፣ የምንገመግመው መጽሐፍ እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠው፤ የፖለቲካ-ጂኦግራፊ፣ የታሪክ፣ የትምህርት፣ የማህበራዊ ሳይንስና የባህል/ስነ-ሰብዕ ይዘት ያለው ሥራ ነው፡፡ስመ-ጥር የጂኦ-ፖለቲካ ሊቅነታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በተደጋጋሚ ያሳዩት አገዛዞችን የመዳፈር ችሎታቸው በዚህም መጽሐፍ ውስጥ ተንፀባርቋል፡፡ ስም እየጠሩና ማስረጃ እያጣቀሱ ብዙዎቹን የታሪክ “ሊቃውንት” እና “ታሪክ ሠሪዎች” ተችተዋል፡፡ ከታሪክ ሊቃውንቱ መካከል፣ ከፕሮፌሰር ስርግው ሐብለ ሥላሴ በስተቀር ከሠላ ትችታቸው ያመለጠ የለም፡፡ ፕ/ር ስርግውን ግን፣ “የኢትዮጵያን ታሪክ በዘመናዊ መልክ በኢትዮጵያዊ መሠረት ላይ ለመትከል ብዙ የሠራና እጅግ የሚጥርም ሰው ነበር፤” ሲሉ ያመሰግኗቸዋል (ገጽ 89)፡፡
ከታሪክ ሠሪዎቹም ነገሥታት መካከል በተራ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስና አፄ ምኒልክ ሚዛን አንስተዋል፡፡ አፄ ቴዎድሮስን “መድፍ የሠራ” ብቸኛ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ ካሉ በኋላ፣ “ያንንም መድፍ መቅደላ ተራራ ላይ ማውጣቱም ራሱ ሌላ ትልቅ ሥራ ነው፤” ሲሉ ይገልጧቸዋል(ገጽ 165)፡፡ አፄ ዮሐንስንም በተመለተ፣ “የቴዎድሮስን ፈለግ ተከትለው፣ ከውስጥ አምባ-ገነኖችና ከውጭ ወራሪዎች ጋር የመረረ ትግል እያካሔዱ፣ ከአፄ ቴዎድሮስ የተሻለ ውጤት አሳይተዋል፤” ሲሉ ተገቢውን ክብር ይሠጧቸዋል(ገጽ 166)፡፡ ስለአፄ ምኒልክም ሲያወሱ፣ ቄሣራዊያን ኃይሎች ኢትዮጵያን ሊቃረጧት ባሰፈሰፉበት በዚያን የመከራ ወቅት፣ የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግሥት ከመደምሰስ “የረዳው የአፄ ምኒልክ አመራርና የዘመኑ የኢትዮጰያ ሕዝብ የመንፈስ ወኔና አልበገር ባይነት የሰጣቸው ኃይል ነው” ብለዋል(ገጽ 168)፡፡ አክለውም፣ “አፄ ምኒልክ በንጉሠ ነገሥትነት ዘመናቸው ሁለት ጠባዮችን በጉልኅ አሳይተዋል፡፡ አንደኛ፣ ለጎበዝና ለጀግና ክብርን የሚሰጡ በመሆናቸው ሁልጊዜም በጀግኖችና በታላላቅ ሰዎች የተከበቡ” መሪ ነበሩ-ይሏቸዋል፡፡ “ሁለተኛም፣ ከመቅደላ ወደሸዋ ሰመለሡ ከወጋቸው ከአቶ በዛብህ ጀምሮ እስከ እምባቦ ጦርነት ላይ ለንጉሥ ተክለ ሃይማኖት እስካሳዩት” የመንፈስ ልዕልና ድረስ፣ “የወጋቸውንም እንኳን በክብር የመያዝና በእርሳቸው አመራር አምኖ ጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል የመስጠት ችሎታ ነበራቸው፤” በማለት ከፍ-ያለ ዋጋ ይሠጧቸዋል(ገጽ 166-7)፡፡
“አፄ ምኒልክ አጠፏቸው የሚባሉት ነገሮች በብዛት፣ አፄ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት ሳሉ በአፄ ዮሐንስ ትዕዛዝና አውቅና የተፈፀሙ እንጂ በአፄ ምኒሊክ ጉልበተኛነት ወይም ግፈኝነት የተፈፀሙ አይደሉም!” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ “የደቡቡ፣ የምስራቁም ሆነ የምዕራቡ የአፄ ምኒሊክ ዘመቻዎች ያለአፄ ዮሐንስ እውቅናና ትዕዛዝ የተደረጉ አልነበሩም፡፡ ሆኖም ግን፣ ታሪክ ያላነበቡት ወያኔዎችና ሻዕቢያዎች፣ እንዲሁም የቄሣራዊያን የታሪክ ቅጥረኞች ሆን ብለው ታሪካችንን ለማክሸፍና ዋጋ ለማሳጣት ሲሉ፤ እየተቀባበሉ የደንቆሮ ለቅሷቸውንና ሙሾአቸውን ያወርወዳሉ፡፡” ይህንን የመሠለ መሰሪ የተቀነባበረ የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱ ሁሉም፣ ዞሮ-ዞሮ አንድ ዓላማና ግብ ያላቸው ኃይሎች ናቸው፤ እርነሱም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ለዘመናት የተገነባ የሕዝቦች ሕንፃ ለማፍረስ የሚፈልጉ-ከሐዲዎች ናቸው-ብለዋል (164-169)፡፡ጀግናውን ራስ አሉላ አባነጋንም አውስተው፤ “የሥራቸውን ዋጋ ሳያገኙ ሞቱ፤” ሲሉ ይቆጫሉ(ገጽ 114)፡፡
ከነዚህ የታሪክ ሠሪዎችና ከፕ/ር ስርግው በስተቀር፣ ብዙዎቹን ኢትዮጵያዊያን በአራት ዓምዶች ስር ሰድረው ይተቿቸዋል፡፡ የመተቻ መስፈርቶቹንም ተጠቅመው የአንባቢያንን ሕሊና ለማንቃት ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ እዚህም እዚያም ተሰባጥረው የሚገኙትን ነጥቦች“መክሸፍ፣” “ታሪክ”፣“ድንበርና-ወሰን”፣ እንዲሁም “ቄሣራዊ ኃይሎች” ባሏቸው አኃዞች አደላዳይነት “የኢትዮጵያን ታሪክና ደንቃራዎቹን”፣ በፈርጅ-በፈርጁ ሊያደራጁ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሙከራቸውም ፈሩን ያለቀቀ ነበር፡፡….  የአንድ ትምህርት ዘርፍ ጥገኛ ለመሆን ስላልፈለጉም፤ ከታሪክም፣ ከፖለቲካም፣ ከስነ-ቃልና ከባሕላችንም ውስጥ ጠቃሚ የሆኑትን ሃሳቦችና ነጥቦች ተፈላልገው በማጠናቀር ከመጀመሪያው አስከ መጨረሻው የአንባቢን ቀልብ ለመግዛት ተፍጨርጭረዋል፡፡
ይሁንና፣ ምንም እንኳን የገለልተኛነት መንገድን ለመውሰድ ቢጥሩም፣ የስሜታቸው ተከታይ ከመሆን አላመለጡም፡፡ በገጽ-64 ላይ እንደጠቀሱትና ለስቬን ሩቢንሰን በ1969á‹“.ም እንደነገሩት፣ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው “ኢትዮጵያ ስትደማ አብሬ እየደማሁ፤ እንዴትስ ስሜት አይኖረኝም?” በማለት ራሳቸውን ያጋልጣሉ፡፡ “የኢትዮጵያ ታሪክና ቄሣራውያን ምሁራን” የሚለው ምዕራፍ ሥርም፣ የደራሲውን የሃሳብ አካሄድና የአስተሳሰብ ፈለግ በይበልጥ የሚመሰክር ነው፡፡ “ታሪክ የሁነቶች ድርደራ አይደለም፤ የተዋናዮቹን ‘አስተሳሰብና ስሜት፤ ጨዋነትና ብልግና’ የሚሉትን፤ ‘ክብርና ውርደት’ የሚሆንባቸውንም የጨምራል፤” ይላሉ(ገጽ-63)፡፡ አያይዘውም፣ ታሪክ የሁነቶች ገለፃ/Descriptive/ ብቻ አይደለም፤ ስነ-ሰብዕ/Ethnographic/ ጭምርም መሆን አለበት-የሚሉ ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ከውጭ ሆነው የሚያጠኑት የውጭ አገር ዜጎችም ሆኑ በውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች መሽገው የሚያጠኑት ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን የታሪክ “ሊቆች!” – “ስለኢትዮጵያ ምንም ስሜት የላቸውም፡፡ ስለሆነም፣ ኢትየጵያ ስትደማ አብረው አይደሙም፡፡” በተለይ-በተለይ፣ “በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካን የሠለጠኑት የታሪክ ባለሙያዎች፣ ለኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን ቋንቋ ከመጻፍ ይልቅ፣ በባዕዳን ቋንቋዎች ለባዕዳን ነው የሚጽፉት” ብለዋል(ገጽ-65)፡፡ በዚህም አተያይ፣ እንደፕ/ር “ባሕሩ ዘውዴ ያለው፣ አንድ አስተማሪው ያስታጠቀውን ጉዳይ” á‹­á‹ž “የማያውቀውን ነገር ይጽፋል” ሲሉ አብጠልጥለዋል(ገጽ-8/9)፡፡ ቀጥለውም፣ “ዱሮም ሆነ ዛሬ የታሪክ ጸሐፊዎቻችን ትኩረታቸው በእንጀራቸው ላይ ነው፤” ሲሉ ዜና መዋዕል ጸሐፊዎቹንም ሆነ ዘመናዊዎቹን የታሪክ “ጸሐፊዎች” ያለርሕራሔ ተችተዋል (ገጽ-76)፡፡
ዘመናዊዎቹ ታሪክ ጸሐፊዎችና አስተማሪዎቻቸው የፈለጉትን ያህል ቢሳሳቱም እንኳን፤ በገጽ 54 እና 56 ላይ እንደገለጹት፤ “የኢትዮጵያ ታሪክ እየተጠናከረ መሔድ የጀመረው፣ ዋናዎቹ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎችና አስተማሪዎች የውጭ አገር ሰዎች” መሆን ከጀመሩ በኋላ ነው-በማለት እውቅና ይሰጣሉ፡፡ ሆኖም ይላሉ መስፍን፣ “ለምን ነጮቹ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርጉት ጥናት ስለዘር፣ ስለቋንቋና ስለባህል ብቻ ሊሆን ቻለ?” በማለት ይጠይቁና፣ ምክንያቱም ግልጽ ነው-ይላሉ፡፡ “እኛን እንደፈለጉ አድርገው ሊቀርጹን የሚያደርጉት” ቄሣራዊ ሙከራቸው አካል ነው፤ ሲሉ በአጽንዖት ይገልፃሉ፡፡ “እኛን እንደጥቁር ሰሌዳ፣ እነርሱንም እንደነጭ ጠመኔ ያለ ባሕርይ ሠጥተን መቀበላችንንም፤” በብርቱ ይቃወማሉ፡፡ ትልቆቹን ቄሣራውያን ምሁራን፣ ለምሳሌ እንደትሪንግሃምና ዶናልድ ሌቪን የመሳሱትን በስም ጠቅሰው፣ “ብዙ የመረጃ ምንጮቻቸውን ሳይመረምሩ፣ የፋሺስቶችን ትምህርትና ልዩ ቄሣራዊ ዓላማ አነግበው/ስላላቸው፤” የኢትዮጵያን ታሪክ አጎደፉ፤ ሲሉ አማረዋል(ገጽ-59-60)፡፡ በሶማልያና በቄሣራዊ ፓስፖርትና ቪዛ የሚምነሸነሹት እነበረከት-አብ ሀብተ ሥላሴም ኢትዮጵያን መካዳታቸው ሣያንስ፣ የሀሰት ታሪክ መጻፍን “የእንጀራቸው” መብያ አድርገውታል ሲሉ ይንገበገባሉ(ገጽ-179)፡፡
የፕ/ር ታደሰ ታምራትንና የፕ/ር መርድ ወልደ አረጋይንም ጥናቶች አንድ ባንድ አያወሱ፣ ከገጽ 90-103 ባሉት ሃተታዎች ውስጥ በእጅጉ ይሞግቷቸዋል፡፡ “ለኢትዮጵያ ልዩ ተፈጥሮና ባሕል፤ በተለይም የኢኮኖሚውና የኑሮው ሁኔታ የፈጠረውን የፖለቲካና የአስተዳደር ሥርዓት በመመርመር-ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ታሪክ የሚያገኙአቸውን የፖለቲካ ሁነቶች መሠረት አድርገው ባለመነሳታቸው፤ ስሕተት ላይ ወደቁ” ብለዋል(ገጽ-88)፡፡  በተለይም፣ ታደሰ ታምራት “ስቴትና ኢምፓየር (State and Empire) የሚሉትን ከአውሮፓ ባሕልና ታሪክ መድረክ የፈለቁ፣ ተለዋዋጭና የተወሳሰበ ታሪክ ያላቸው ሐሳቦች” ለኢትዮጵያ ተጠቅመው፣ ለቄሣራውያን አስተሳሰብ መሣሪያ ሆኑ-ብለው ተከራክረዋል(ገጽ-90)፡፡ በተጨማሪም፣ ፕ/ር ታደሰ መጽሐፍ “ከሣርና ከቅጠሉ በስተቀር፣ የኢትዮጵያን ሁኔታ ሁሉ በሃይማኖት ሚዛን ይለካል፤” ያም ስሕተት እንደሆነ አሳይተዋል(ገጽ-91)፡፡ ፕ/ር መርድንም አንስተው፣ ስለኢትዮጵያ ወሰንና ዳር-ድንበር ሲያጠና “አልቫሬዝ ስለደጋው የኢትዮጵያ ወሰን የጻፈውን “ተረት ነው” ብሎ አጣጥሎ፣ ለቆላማው ኢትዮጵያ ሲሆን ግን ያለማመንታት ይቀበለዋል፡፡ ያንንም የተዋሰው ከማርጀሪ ፐርሃም ሀሳብ ነው፡፡” በመሆኑም፣ ‘መርድ ሳያውቀው፣ ለቄሣራውያን ተንኮል የድምጽ ማጉያ ሆነ!’ ለማለት ይቃጣቸዋል(ገጽ-101/2)፡፡
ወደ“መክሸፍ”ና ስለኢትዮጵያ ታሪክ አከሻሸፍ ያወሱትን ለማጤን እንሞክር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን “ከሻፋ” ነገሮች በሦስት ከፋፍለዋቸዋል፡፡ እነርሱም፤ ጨርሰው የከሸፉ(ገጽ-19)፣ በመክሸፍ ላይ-ያሉ(ገጽ 11-18)፣ እና እስከዘመናችን ድረስ ያለከሸፈ(ገጽ-10) በማለት፡፡ ያለከሸፈው “ለነፃነትና ለክብር በመስዋዕት” መሆኑ ብቻ ነው፡፡  በተረፈ፣ በገጽ-26 ላይ እንዲህ ይላሉ፤ “በኢትዮጵያ በኳስ ጨዋታው ሳይቀር መክሸፍ ጎልቶ ይታያል፤ በረጅም ርቀት ሩጫም ቁልቁለቱን የጀመርነው ይመስላል፡፡ ከባሕር ጠለል አካባቢ የሔደው ሶማሊያዊው ሞ ፋራህ፣ ደገኞቹን (ከደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል የሔዱትን ሯጮች) ቀደማቸው፡፡ መክሸፍ ባህላችን መሆኑ ግዴታ ነው እንዴ?!” ለነገሩማ፣ “ከሸፈ ወይም እከሌ አከሸፈው እንላለን እንጂ፣ እኛ ራሳችን ከሽፈን-አከሸፍነው አንልም!” ሲሉ ይገሥፃሉ(ገጽ 29-31)፡፡ 
በመጨረሻም፣ ከበድ ያለና ተገቢ ማሳሰቢያ ለአንባቢያኑ ያቀርባሉ፡፡ በገጽ 104 ላይ ስለሦስቱ የቄሣራውያን ኃይሎች ግዛት ለማስፋፋት የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች ተንትነው ሲያበቁ፤ በገጽ 145 ላይ ደግሞ ለምን ቄሣራውያን የኢትዮጵያን ለመግፋትና ወሰኗን ለመማጥበብም እንደፈለጉ የሚያሳዩ “ሦስት መሠረታዊ ጥቅሞቻቸውን” ከበቂ ማብራሪያና ማስረጃዎች ጋር ያቀርባሉ፡፡ እነዚህንም፣ የቄሣራውያንን ሴራዎችና ተንኮሎች ሳንረዳ የምንቀር ከሆነ፣ በውጫዊው የቄሣራውያን ግፊትና ሴራ መክሸፋችን እንደማይቀር ያስገነዝባሉ፡፡ “በመሆኑም፤” ይላሉ ፕ/ር መስፍን፣ “በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መክሸፍ ለብዙ ምዕተ-ዓመታት” ቦታ የያዘ መሆኑን ገልጸው(ገጽ-8)፤ “ከ1928ዓ.ም ወዲህ ግን፣ የክሽፈቱ ዓይነት የተለየ ሆኗል፡፡ ስለዚህም፣ ማኅበረሰባዊ ችግሮችንና ለሥልጣን የመስገብገብ ጉዳዩንም አስከፊ አድርጎታል”(ገጽ-12) ይላሉ፡፡ ስለሆነም፣ “የሥልጣን ምንጭ ሙሉ-ለሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆኖ፣ ሰው ለሰው የሚገዛበት ሥርዓት እስካልፈረሰና፣ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መብትና እኩል ግዴታ ያለባቸው መሆኑ በተግባር እስካልተረጋገጠ ድረስ” መክሸፋችን አይቀሬ መሆኑን ጠቁመዋል(ገጽ-201)፡፡
እስቲ ደግሞ ስለመጽሐፉ የቋንቋ አጠቃቀም ጥቂት ነጥቦችን እናንሳ! “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፤”፣ በቃላት አሰካክና አደራደሩ ስርዓትን የተከተለ ነው፡፡ ቃላቱ፣ ለአጫፋሪነትና ለአዳማቂነት ፈፅሞ ልሰፈሩም፡፡ ቀልብን ገዝተው መደመጽሐፉ ማብቂያ ያንደረድራሉ፡፡ ሆኖም፣ እዚህም-እዚያም የፊደል ግድፈቶች ታይተዋል፡፡ ለምሳሌም ያህል፣ በገጽ-53 ላይ “ሲጀምር” የሚለውን “ሺጀምር”፤ በገጽ-78 ላይ “ያተረፉ” የሚለውን “ያተረፋ”፤ በገጽ-88ም ላይ “ሁነቶች” የሚለውን “ሁነትች”፤ በገጽ-93 ላይም “አማርኛው” የሚለውን “አማራኛው”፤ በገጽ-127 ላይም “መሀከል” መሆን ሲገባው “በሀከል”፤ በገጽ-168ም ላይ “ኢትዮጵያ” የሚለውን “ኢጥዮጵያ”፤ እና በገጽ-194 ላይ ደግሞ “የሚተላለፍ” ለማለት “የሚታላለፍ” የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከሁሉም-ከሁሉም ግን፣ በገጽ-9 ላይ የወጣው ስም ስህተት ሊታለፍ አይገባውም፡፡ ፊታውራሪ “ተክለ ሐዋሪያት ተክለ ማርያም” መባል ሲገባው፣ ልጅየው “ግርማቸው” ያለቦታቸው ተተክተዋል፡፡ ከገጽ-12 እስከ 14 ባሉት አንቀጾችም ውስጥ፣ á‹“.ም(ዓመተ-ምህረት)ና ምዕተ-ዓመት(ም.á‹“ – የሚባል አጠቃቀም ካለም ነው፣) ተዛንቀዋል፡፡ መጽሐፉ በድጋሚ ሲታተምም፣ እነዚህን የፊደልና የስም ግድፈቶች አርሞ እንደሚወጣም እምነቴ ነው፡፡
ማጠቃለያ፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት ላሉት አንባቢያን፣ መጽሐፉ እንደልብ ገበያ ላይ ይገኛል፡፡ ዋጋ የሚፍቁና የሚደልዙ ወገኖች እንዳያጭበረብሯችሁ፣ ዋጋው አርባ አምስት/45/ ብር ብቻ መሆኑን በድጋሚ ልናስታውሳችሁ እንወዳለን፡፡ በውጭ አገራትም ያላችሁ፣ በሃያ/20/ ዶላር ገዝታችሁ ለማንበብ ወደ ኢሳት-ስቶር http://ethsat.com/store/ ጎራ በሉ፤ ታገኙታላችሁ፡፡ መጽሐፉን “ይፋ ባልሆነው ማተሚያ ቤት” ያሳተሙትን, ፕ/ር መስፍንና ተባባሪዎቻቸውን በሙሉ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ እንዲሁም፣ መጽሐፉን በመተየብና የአርትኦቱም ስራ ያገዙትን ሁሉ፣ በአንባቢያኑ ስም “ክብረት ይስጥልን!” ልላቸው እመዳለሁ፡፡ (የሳምንት ሰዎች ይበለን!)
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on January 14, 2013
  • By:
  • Last Modified: January 14, 2013 @ 7:27 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar