www.maledatimes.com አማራውን በሁለንተናዊ መልኩ አዳክሞ መግዛት ወይም ማጥፋት፦ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

አማራውን በሁለንተናዊ መልኩ አዳክሞ መግዛት ወይም ማጥፋት፦

By   /   May 22, 2014  /   Comments Off on አማራውን በሁለንተናዊ መልኩ አዳክሞ መግዛት ወይም ማጥፋት፦

    Print       Email
0 0
Read Time:43 Minute, 31 Second

(በጌታቸው ፏፏቴ)
ራስ ስሁል(ራስ ስዑል) ሚካኤል መቀመጫውን በጐንደሩ ቤተ-መንግሥት በማድረግ በሥሩ ንጉሶችን በማንገስ ከላይ ሆኖ የሚቆጣጠራት በመሳፍንቶች
የምትመራና አንድ ማዕከላዊ የሆነ ግዛቷ ለተወሰነ ጊዜ ተዳክሞ የነበረች ኢትዮጵያችን ይገዛ ነበር። በኋላ በመይሳው ካሣ(አፄ ቴዎድሮስ) የተገነባ ማዕከላዊ
መንግሥት ተመስርቶ እነሆ እኛ እስካለንበት ዘመን ደርሷል። የኛው ሞራልና ኢትዮጵያዊነት ወኔ ደግሞ የት እንደሚያደርሰን እናየዋለን።ወደ ራስ ስሁል ልመለስና
ራስ ስሁል ሚካኤል ጨካኝና ተንኮለኛ መሆናቸውን የሚያሳይ አንዱን ንጉሥ ከምግብ ጋር መርዝ በመጨመር አንደኛውን ንጉሥ በሻሽ አሳንቀው መግደላቸውን
የሚገልጽ አንድ ጹሑፍ አንብቤ ስለነበር የህወሃት ድርጅታዊ ፕሮግራም ከዚህ የተቀዳ ይሆን ? በማለት አንዳንድ የቀደምት ጸሓፍትን መመልከት እንዳለብኝ
የግድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።ራስ እየተባሉ ንጉሶችን ይገዙ የነበሩት ራስ ስሁል ሚካኤልና ዛሬ ህወሃት ብዙ የክልል ንጉሶችን አንግሶ የክልል ንጉሶችን እየገዛ ሕዝባችን
በጭቆና መዳፍ ሥር ወድቆ መተናፈሻ ተነፍጎት ሳይ ይህን ችግር ቶሎ ነቅለን ካልጣልን እስከ ወዲያኛው ትውልዳችን መክኖ እንደሚቀር ግልጽ ማሳያ መስሎ
ይታየኛል።የዘመኑ የክልል ገዥዎች ወይም መሪዎች ከህወሃት መንገድ ትንሽ ሲያፈነግጡ ምን እንደሚከተላቸው ግልጽ ሲሆን ውክልናቸው ወይም ታማኝነታቸው
ላሉበት ክልልና ህዝብ ሳይሆን ለህወሃት ብቻ እንደሆነ ማሳመኛ የሚያስፈልገው አይመስለኝም።በቅርብ ወራት የሞተውን የኦሮሞ ክልል ፕሬዘዳንት ዓለማየሁ
አቶምሳን ህመም ምንጭ ምን እንደሆነ በተለያየ መንገድ ያፈተለኩት ወሬዎች እንደሚነግሩን ህወሃት የራስ ስሁልን ታሪክ እንደደገመ ነው።የኢትዮጵያ ሶማሌ
ክልል ፕሬዘዳንት ከህወሃት የተቀሰረበትን ጣት ለማስነሳት ተገንጥየ ወደ ሶማሌ ሄጀ እቀላቀላለሁ ብሎ ለጊዜው ቢያስፈራራም ነገ የሚገጥመውን በጋራ የምናየው
ይሆናል። እንግዲህ ይህን ያህል ካልኩ አቅሙና ጊዜው እንዲሁም መረጃው ያላችሁ ይህን መነሻ በማድረግ ጠንከር ያለ ጹሑፍ ታስነብቡን ይሆናል ብየ ተስፋ
አደርጋለሁ።
ህወሃት የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም ማናቸውንም አይነት ጸረ ህወሃት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ለማፈን ያለ የሌለ አቅሙን አሟጦ እየተጠቀመ መሆኑን በግልጽ
የምናውቀው ቢሆንም እንደ ድርጅት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን በፕሮግራሙ ቀርጾ የያዘው ትልቁ ዓላማው ግን አማራውን አዳክሞ መግዛት ወይም
ማጥፋት እንደሆነ ይታወቃል። ከነዚህም ዋና ዋናዎቹ
1ኛ/ ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዳይኖረው ማድረግ፦
ይህን አንጋፋ የአማራ ነገድ በኢኮኖሚ ለማዳከም መጀመሪያ የአርሶ አደሩን መሬት በመንጠቅ አርሶ አደሩን ማፈናቀል ነው። ለዚህ ማስረጃው ከሰሜን ወሎና
ሰሜን ጎንደር ወደ ትግራይ የተወሰው መሬት ላይ የነበሩ የአማራ አርሶ አደሮች የት ደረሱ? ብሎ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል።ሌላው የሰሜን ምዕራብ ጎንደር ለም
መሬት ለሱዳንና ለግል ባለሀብቶች ሲሰጥ እዛ ላይ የነበሩ አርሶ አደሮች የት ደረሱ? የሚለው ነው።በስኳር ፋብሪካ ሰበብ ጣና በለስ በሚገነባው ላይ የአለፋ ወረዳ
27 ቀበሌዎች ከጎንደር ተነስተው ወደ አዊ ዞን ማካለል ከታች አርማጭሆ የተወሰኑ ቀበሌዎችን አንስቶ ወደ መተማ በማካለል ሁሉም የትውልድ አጥቢያቸውን(መንደራቸውን) ጥለው እንዲሰደዱ ነው የተደረገው።ዛሬ ከየትኛውም አካባቢ እንዳናይህ ተብሎ እንደ የተለከፈ ውሻ ውጣ የሚባለው ነገደ አማራ
በቤኒሻንጉል፤በጉራ ፈርዳ በወተር አርባጉጉ …ወዘተ የደረሰበትንና የሚደርስበትን ግፍና በደል ማንም ቢሁን የሚረሳው አይደለም። ይህ እንግዲህ ከሞቀ ቤቱ
አውጥቶ ሀብት ንብረቱን እንዳያነሳ ከልክሎ በማሰደድ በስደት ኑሮውም ደግሞ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ሰርቶ እንዳይበላ፤ ልጅ ወልዶ እንዳይስም፤ አግብቶ
ትዳር እንዳይኖረው በማድረግ ተገዶ እንዲገዛና የውጭ እርዳታ መለመኛ ለማድረግ በአማራው ላይ የተወሰደ እርምጃ ነው።ሁለተኛው ደግሞ በንግድ ሥራ ላይ
የተሰማራውን ነገደ አማራ የባንክ ብድር እንዳያገኝ ማድረግ የንግድ ፈቃዱን መከልከልና ከፍተኛ የንግድ ሥራ ግብር በማስከፈል ተስፋ ማስቆረጥ፤አብዛኛውን
ደህና ትርፍ የሚያስገኝ የንግድ ሥራ አስቀድሞ በሌሎች እንዲያዝ በማድረግ ያኛው ተይዟል ይህኛው ተይዟል በማለት ቢሮክራሲ እየፈጠሩ የያዛትን ገንዘብ
በውጣ ውረድና በጉቦ አባክኖ ተስፋ ቆርጦ እንዲቀመጥ ማድረግ የመሳሰሉት ይፈጸሙበታል።አንድ ምሳሌ ወስደን እንመልከት የአማራ ክልል የሚባለውን
የህወሃቱ ኤፈርት የተቆጣጠረው መሆኑ ይታወቃል በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ አምባሰል የሚባል የንግድ ድርጅት የበረከትና አዲሱ የገንዘብ ማመንጫ
ኩባንያ ሰሊጥ ፤ ጥጥና ማሽላ ግዥን ጨምሮ በአማራው ክልል የንግድ ሥራን ይሰራል። የሰሊጥና የጥጥ ግዥ የተወሰነ ወቅት ሲኖረው በዚህ ወቅት በአማራ
ክልል ከአምባሰል ውጭ ማንም ነጋዴ ጥጥና ሰሊጥ እንዳይገዛ በአስተዳደር ተብየው ቀጭን ትእዛዝ በሰርኩላር ይተላለፋል ከካድሬው እጅ ከደረሰ በኋላ ሕጋዊ
የንግድ ፈቃድ የያዘው ሰው መግዛት እንደማይችል ይነገረዋል።ይህንና እነዚህን በመሳሰሉት ሞራሉን እየገደሉ ሲደክመው እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥና
እንዲተወው ማድረግ ነው።
2ኛ/በፖለቲካው ጉዳይ ላይ አማራውን እንዳይሳተፍ ማግለል፦
ለዚህ ጉዳይ በቀላሉ ማሳያ የሚሆነን በአማራ ክልል በአማራው ስም፦ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የሚለውን እንመልከት ይህ ድርጅት
የሚመራው ከላይ የህወሃት መሳፍንቶች ዝቅ ሲል ደግሞ በአዲሱ ለገሰ፤ በረከት ስምኦን፤ህላዊ ዮሰፍ፤ታደሰ ካሳ፤ካሳ ተክለብርሃን፤መለስ ጥላሁን፤ተሰማ
ገ/ሕይወት አሁን ተፈራ ዋልዋ ይኑር አይኑር አላውቅም ዋናዎቹ እነዚህ ሲሆኑ የድርጅቱ ኃላፊ ብለው የጎለቱትን ዓለምነው መኮንን በቅርቡ የፈጸመውን
ሁላችንም የምናስታውሰው ነው። ሌሎች ከዓለምነው ተለይተው የማይታዩ ነገደ አማራዎች ቢኖሩበትም እነዚህ ኃይሎች እውን የአማራውን ነገድ ሕዝብ
ይወክላሉን? የአማራውን ነገድ ሕዝብስ እውን ያውቁታልን? አያውቁትም ሊወክሉትም በፍጹም አይችሉም ቢችሉማ ኖሮ በአማራው ነገድ ሕዝብ ላይ
የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን አስከፊ ከኢትዮጵያዊ ዜግነት በጣም ዝቅ የሚያደርግ ጥቃት በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግሮች ተጠምዶ ሲያዝ መከላከል በተቻለ
ነበር።ዓለምነው መኮንን ለአማራ ሕዝብ ያለውን ንቀት ስብሰባው ውስጥ የነበረው ታዳሚ ጥቂት የህወሃት ጌቶቻቸው ቢኖሩበትም አብዛኛው ከዚህ የአማራ ነገድ
ሕዝብ አብራክ የተፈጠሩ ናቸው ብሎ መደምደም ይቻላል። ዳሩ ግን የተስተዋለው በዓለምነው መኮንን ንግግር ሲስቁ ነው የምንሰማው በርግጥ ይህን ትራጀዲ
ያጋለጡ በግለሰብ ደረጃ የሕዝብን መዋረድና መሳለቂያ መሆን አልዋጥህ ያላቸው ነገር ግን ሌላ መታጠፊያ ያጡ ከስብስቡ ውስጥ አልነበሩም ማለት አንችልም።
እመራዋለሁ ያለውን ሕዝብ እስከ አፉ ጢም በሞላ አዳራሽ ውስጥ ምንም ዓይነት ሕሊናዊ ሀፍረት ሳይሰማው ሕዝብን ያዋረደ ፤ የዘለፈ ስድና መደዴ ላይ
እርምጃ ያልወሰደ ብአዴን እንዴት ብሎ ነው ሰፊውን የአማራ ነገድ ሕዝብ ሊወክል የሚችለው? በአማራ ክልል ቢሮክራሲን ማፈራረስና ትጥቅ ማስፈታት፤
ማንኛውም ሀብትና ንብረት መሰብሰብና ወደ ትግራይ ማጓጓዝ በሚል ቋሚ ፕሮግራም አውጥቶ አማራውን የማስወገድ ዘመቻ ተካሂዷል። አንገታቸውን ቀና ያደረጉና የአማራውም ሕዝብ መብት ሊከበር ይገባል ያሉትን ምን እንደተፈፀመባቸው ትንሽ ማገናዘቢያ የሚሆን አስቀድሞ ከተሰሩት ሥራዎች የተወሰኑትን
እንጥቀስ፦
1ኛ/ ዘለቀ የትውልድ ቦታው ጋይንት አውራጃ ነገዱ አማራ የሥራ ኃላፊነቱ የኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴና ወታደራዊ አዛዥ ሲሆን ብዙ ጊዜ አርማጭሆ ማሰሮ
ደንብ የቆየና ሕዝቡ ባሕታዊ የሚል ቅጽል ስም አውጥቶ የሚጠራው ደፋርና ጀግና በኢህዴን ሠራዊትም ሆነ ከደርግ ነፃ በነበረው አካባቢ በሕዝብ ተወዳጅነትን
ያተረፈ ህወሃትን እያሰጋ በመምጣቱ በ1981 ዓ/ም አምደወርቅ ላይ ገደል ገፍተው በመጣል ሲገድሉት ምክንያቱን የመኪና አደጋ ብለው አሳበቡ።እዚህ ላይ በጣም
የሚያሳዝነው ጉዳይ ገዳዮቹ ታምራት ላይኔና መለስ ዜናዊ አንድ አይነት ጃኬት አንድ አይነት ሱሪ አንድ አይነት ቆብ በማድረግ ለጉባኤተኛው ንግግር ሲያደርጉ
የስካር ምልክትና የፈካ ፊት ይታይባቸው የነበረ ሲሆን በመንተባተብ አፋቸው ተይዞ «እንኳን ሞት እርጅናም አለ። አለ አንበሳ ብሎ የተረተውን የዘለቀን የአንድ
አፍታ ወግ በማውሳት ተራ በተራ ወደ መድረክ እየወጡ ራሳቸው ለቅሶውን ሲያቀልጡት እኛንም እንድናለቀስ መጋበዛቸው ትዝ ይለኛል። የገባንበት አዳራሽ
ጮፌ የተነሰነሰበትና ሽቶ የተረጨ እንደነበርና ወደ አዳራሹ ስንገባም አንድ የሻምበል ጦር በማስመጣት ትጥቃችን እንድንፈታ ተደርጎ ነበር የገባነው።
2ኛ/ ጌጡ አሸኔ (ኡስማን) ትውልዱ ጎንደር አውራጃ ደንቀዝ ነገዱ አማራ የሥራ ኃላፊነቱ የኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የኢህዴን ሠራዊት አዛዥ የነበረ
የኢህዴን ሠራዊትና አባሉ በቅጽል ስሙ ኡስማን-ግርግር እያለ የሚጠራው ፍጹም ተወዳጅ የነበረ ሰሜን ወሎ ወልድያ የማ/ኮ ስብሰባ ቆይቶ ትንሽ ልናፈስ ብሎ
ሄደ በማለት ነገር ግን በመኪና ገጭተው የገደሉት።ህወሃትን ያሰጋና በኢህዴን ማ/ኮ የግድያ ግፍ የተፈፀመበት።
3ኛ/ ንጉሤ ጢሞ ትውልዱ ጎንደር አዲሰላም ነገዱ አማራ የሥራ ኃላፊነቱ የኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሲሆን ጎንደር አዲስ ዘመን አውጃኖ ሕላዊና ንጉሤ
ስብሰባ ላይ እያሉ በሃሳብ አለመግባባት አውጃኖ በንጉሤ ላይ ተኩሶ ይገድለዋል ከዚያም ፀጉሩን በእሳት አቃጥሎ ሕላዊ ሮጦ ሲያመልጥ መጨረሻ ራሱን ገደለ
የሚል መረጃ ነበረኝ። በሌላ በኩል ደግሞ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ከአዲስ አበባ በሚል በፃፈው «እንዲህ የሚል ይገኝበታል ጀግናው ታዋቂው የጦር መሪ የወሎ
አውጃኖ የህወሃት ሰለባ ከሆኑት አንዱ ነው ይልና አውጃኖ የኢህዴን የሥራ አስፈጽሳሚ ኮሚቴ አባልና የጦር አዛዥ ሲሆን የህወሃትን ሴራ በጥብቅ የሚቃወምና
በመጨረሻም ለመላው የኢህዴን አባላትና ለማ/ኮው “የህወሃት የተሳሳተ መንገድና የኢህዴን እጣ ፈንታ” በሚል ርእስ የጻፈውን 18 ገጽ ሪፖርት ለኢህዴን
አመራርና አባላት በመበተን አስቸኳይ መፍትሔ ላይ እንዲደረስ በጥብቅ በማሳሰብ ከፈተኛ የመነሳሳት ሞራል ፈጥሮ ነበር።በዚህና በመሳሰሉት ጉዳዮች ከህወሃቱ
የወታደራዊ ጉዳይ አዛዥ ከነበረው ከጻድቃን ወልደትንሳኤ/አሁን ሜጀር ጀኔራል/ በጡረታ የተገለለ ጋር በጉናና በሀይቅ በነበረው አውደ ውጊያ ባለመግባባታቸው
የተነሳ አውጃኖ ለጻድቃን ደደብ ነህ ። ከዚህ በኋላ አንተ አትመራኝም ብሎ ስለሰደበውና አካሄዱ ስለ-አላማራቸው አዲስ ዘመን ላይ ስብሰባ ብለው በ1983 ዓ/ም
በጥይት ደብድበው ገደሉት።የሚለውን እናገኛለን።ቆላም ነፈሰ ደጋ አውጃኖን እኔም ስለማውቀው ለህወሃት አሜን ብሎ የሚገዛ አልነበረምና ቀደሙት።
4ኛ/ አውጃኖ ትውልዱ ወሎ ነገዱ አማራ የሥራ ኃላፊነቱ የኢህዴን ማ/ኮና የኢህዴን ሠራዊት አዛዥ የነበረ ሲሆን እኔ እስከማውቀው ድረስ አውጃኖ የተዋጣለት
የጦር ሜዳ ሰው ነበር። ነገር ግን ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ ሪፖርቱ የህወሃት ተደርጎ ስለሚቀርብ ጀግንነቱን አፍነውት ነበር። 5ኛ/ አገኘሁ ትውልዱ ወሎ ነገዱ አማራ የሥራ ኃላፊነቱ ከዝቅተኛ እስከ ከፈተኛ ደረጃ ባሉ የኢህዴን ሠራዊት ውስጥ አመራር የነበረ የኢህዴን ማ/ኮ አባል
የተገደለበት ቦታ ደሴ ምክንያቱ ለህወሃት የሚያሰጋ ስለነበረና ሰበቡ የአውጃኖ ደጋፊ ነህ በሚል በህወሃት ገዳይ ኃይል በጥይት የተገደለ።
6ኛ/ አሞራ እየተባለ የሚጠራ ትውልዱ አዲስ አበባ ነገዱ አማራ የሥራ ኃላፊነቱ የኢህዴን ማ/ኮሚቴ አባል የነበረ በ1981 በወልቃይት ጉዳይ ፀረ-ህወሃት አቋም
ይዘሃል በሚል ሰቆጣ ውስጥ አሪ ከተባለ ቦታ በጥይት የተገደ።
7ኛ/ ሙሉዓለም አበበ ትውልዱ ጎንደር ጠዳ (አምቦ) ነገዱ አማራና የቤተ-እሥራኤል ደም ያለው የሥራ ኃላፊነቱ የኢህዴን ማ/ኮሚቴ አባል አንድ ወቅት ላይ
ደግሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበረ የተገደለው በፈንጅ ቦታው ደብረማርቆስ ሲሆን የኢህዴንን ካድሬ ግምገማ ሲመራ ቆይቶ ለበረከት ሪፖርት እያደረገ እያለ
ከጠረጴዛ ሥር በሰአት እንዲፈነዳ ተደርጎ የተጠመደ ፈንጅ ገደለው የተባለ።በቀብሩ ሥነ-ሥርዓት እዛው ከትውልድ ቦታው አምቦ ድረስ ሄዶ እንዲቀበር የተደረገ
ሲሆን በቀብሩ በረከት አልተገኘም። አዲሱና ታደሰ ካሳ መቸም ገድሎ ማርዳትና መቅበር ይሆንላቸውል ተገኝተው ነበር።
8ኛ/ አበበ አንዳርጌ ትውልዱ ጎጃም ሞጣ ነገዱ አማራ የሥራ ኃላፊነቱ የኢህዴን ማ/ኮሚቴ አባል ሲሆን ምሥራቅ ጎጃም በኃላፊነት እየሰራ በነበረበት ወቅት
ከሙሉዓለም ሞት ጋር በተያያዘ ገድለውታል በአንድ በኩል በሌላ በኩል ደግሞ ለጊዜው አስረውት ነበር ወዲያውኑ ነው የፈቱት የሚባልና ከታሰረ በኋላ የት
እንዳገቡት አይታወቅም እየተባለ ያለ ጉዳዩ እስከ አሁን መሬት ያልነካ ሆኖ ይገኛል።
9ኛ/ዘርጋው ፤ ኮበል፤አስራደ፤ ዮርዳኖስ የሚባሉ የኢህዴን ማ/ኮሚቴ አባላት የነበሩ ትውልደ ጎንደር ነገደ አማራ የሆኑ ፀረ-ሕወሃት የሆነ አቋም አላቸው
የወልቃይትን ወደ ትግራይ ማካለል ይቃወማሉ በሚል በህወሃት ተገድለዋል።
10ኛ/ በ1978 አንገረብ ላይ በነበረው ስብሰባ የወልቃይትን መሬት ወደ ትግራይ ማካለል በሚለው ጉዳይ ላይ እንዴት ሊሆን ይችላል በማለት አጥብቀው
የተከራከሩ 3 በሕክምና ሙያ ሲያገለግሉ የነበሩ ሐኪሞች ትውልዳቸው ጎንደር ነገዳቸው አማራ የሆኑ ተገድለው አንገረብ ወንዝ የተጣሉ መሆኑን ዳግማዊ
ቴዎድሮስ ከዚህ በፊት ያስነበበን ሲሆን ይህን ጉዳይ እኔም አቅርቤው ነበር በድጋሚ ለመጥቀስ የተገደድኩት የዛሬው ትኩረቴ ጋር አብሮ ስለሚሄድና በአጠቃላይ
አማራው በፖለቲካው ዙሪያ ያለውን” አማራ ገለል በል የሚለውን ለማሳየት ነው” አንድ አስማረ ኮበሌው እየተባለ የሚጠራ የኢህዴን የማ/ኮሚቴ አባል የነበረም
እንዲሁ የተገደለ መሆኑን ከኢህዴን ቀደምት ታጋዮች ይነገር ነበር። የህወሃት የፖለቲካ ምሕዳርና የአማራው በፖለቲካው ዙሪያ ያለው ተሳትፎ በፍጹም የመከነና
ከፖለቲካው ውጭ መደረጉን እንዲሁ ለመነካካት እንጅ ተዘርዝሮ ያበቃል ማለት የማይታሰብ ነው። ህወሃት አርባ ዓመት የፈጀበትን የአማራን አዳክሞ መግዛት
ወይም ማጥፋት የሚል የፖለቲካ ዳካር ውስጥ ከመግባት ተደራጅቶ ይህን እኩይ ከፋፋይና ዘረኛ ድርጅት ዳግም እንዳይነሳ አድርጎ ከመቅበር ውጭ ምንም
ዓይነት አማራጭ አይገኝም።በመጨረሻ አንዱዓለም አራጌ የታሰረበትና የተበየነበት የፍርድ ብይን በየት አገር ዳኛ እንደተወሰነ ኢትዮጵያዊ ዳኛም ከሆነም
የአንዱዓለም አራጌን ንግግሮች ህወሃትን የሞገተበትን ምርጥ የፖለቲካ ቃላት ዩቱቢ ላይ ገብቶ በነፃና ኢትዮጵያዊ በሆነ መንፈስ እንዲመለከትውና አማራ በመሆኑ ብቻ እንዲጠቃ መደረጉን እንዲያስብ ወይም እንዲያስቡ እመክራቸዋለሁ ውሃው ሂያጅ ድንጋዩ ቀሪ እንደሚባለው ነገ በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ክብርን እንድታገኙ
ዛሬ ለሀቁ መቆም ግድ ይላችኋልና።
3ኛ/ አማራው በማህበራዊ ጉዳዮች ዘሪያ፦
ሀ/የትምህርት አሰጣጡና ካሪኩለሙ -አማራው ክልል ላይ ሲደርስ የተለየ ነው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና የሚሰጠው 10ኛ ክፍል ላይ ሲሆን ሚኒስትሪ
የሚባለው ፈተና 4ኛ ክፍል ፤6ኛ ክፍልና ፤8ኛ ክፍል ይሰጣል ስለሚደረድሩት የነገር ድሪቶ አሁን ማንሳት አልፈልግም በአጠቃላይ ግን የተማራ የአማራ ነገድ
እንዲኖር ስለማይፈለግ በንቃትና ታስቦበት የተፈፀመ ድርጊት ነው። ለነገሩ ያልተማሩ መሪዎች ስለትምህርት ምኑንስ አውቀውት ነው የጠለቀ ሥልጡን ሕብረተ-
ሰብ እንዲኖር የሚያስቡት። ሚንስቴር የነበረውን ደመቀ መኮንን በጣም አውቀዋለሁ። አዲሱ እንደ በክር ልጁ በመንከባከብ እዚህ ደረጃ እንዳደረሰውም
አውቃለሁ ምክንያቱም እጅግ በጣም አድርባይ ነው፡፤ ወደዚህ ድርጅት ሲመጣ ቡሬ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የነበረ ሲሆን በዚያ ሰአት
የመጀመሪያ ዲግሪ እንደነበረው አውቃለሁ በራሱ ሴክተር መ/ቤት የሚያገኘው ገቢ ሊበቃው ስለ አልቻለ እንደማንም ተባጥሶ ከዘራፊዎቹ መንደር ተቀላቀለ
ምክ/ጠቅላይ ሚንስርነትንም በእጁ አስገባት ነገር ግን እነ አዲሱ እየዛሉ ሲሄዱ” ወጣ ወጣና እንደ ሸምበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ” እንደሚሆን ከብዙ
ለሥልጣን ከሚቋምጡት የተመለከትነው። እነ ሀሰን አሊ፤አባተ ኪሾ፤አብዱል መጅድ…ወዘተርፈ ይመለከቷል።
ለ/ ጤና በአማራ ክልል-የተወሰኑ ሆስፒታሎች የተሰሩ መሆኑን ጉግል በማድረግ ለማየት ሞክሬያለሁ፤የጤና ጣቢያዎች፤ የጤና ኬላዎችና ክሊኒኮችም አብበዋል
ይባላል ወደ ውስጥ ገብተን ስንመለከት ግን ሙያተኛና ሥራው ተገናኝተዋል ወይ?ሙያተኛው በቂ የሙያ ሥልጠና አግኝቶ ለሙያው ክብር ሰጥቶ የተሰማራ ነው
ወይ? እነዚህ ተንበሽብሸዋል የሚባሉት የጤና ተቋማት ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት የሚያደርስ በጀት ተመድቦላቸዋል ወይ? በቂ የሕክምና
መሣሪያዎችና መድኃኒቶች እነዚህ ተቋማት ካሉበት ይደርሳሉ ወይ? ለሕክምና የሚሄዱ ሕሙማን ተገቢው ሕክምና ይደረግላቸውል ወይ? የማይታሰብ ጉዳይ
ነው። ይህን አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉ ደህና ገንዘብ የዘረፉ ወይም የዘመኑ ባለሥልጣናት ብቻ ነው የሚታከሙት ወይም ከነርስ ወይም ከዶክተሮች ጋር
አብረው ግብር የበሉ መሆን ይኖርባቸዋል። እራሱ በካርድ የሚገባው ገቢ ላይ አነጣጥሮ የሚተኩስ ቢገኝ አቤት! ስንቱ ጉድ በወጣ ነበር። ለነገሩ እንኳን በአሁኑ
ሸውራራ ጊዜ ይቅርና በደህናው ጊዜም ይህ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ በአድሎ የተበከለ ነው የነበረው። በዚህ ምክንያት የአማራው ክልል ነዋሪ /አማራው/
ተገቢ አገልግሎት አያገኝም ።መድኃኒቱ እኮ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የአየር ባየር ነጋዴዎች እጅ ተደርጎ ነው። መቼም እውነቱን ሸምጥጠን እንክዳው ካልተባለ
ራሳቸው ባለሙያዎች ብዙ አስተማሪ ጉዳዮችን ሊያካፍሉን ይችላሉ። እያወራሁ ያለሁት ስለአማራው ክልል ስለሆነ ከሌላው ጋር አይዛመድም።
ሐ/ ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎቶች ውሃ ፤ መብራት ፤ ትርንስፖርት ፤ የስልክና የተለያዩ የሰርቪስ ጉዳይ ስንመለከት በአማራ ክልል በጣም አናሳ ነው። ይህ
በአጋጣሚ የሚደረግ አይደለም በንቃት ታስቦበት የሚፈፀም ሴራ ነው።ልማታዊ መንግሥት ተብየው የአማራውን ሕዝብ ከሚጎዳበት ብዙ መንገዶች አንዱን
ካርድ ልምዘዝና እንነጋገር። ክልሎች የራሳቸው የገቢ ምንጭ ያላቸው ሲሆን ከፌደራል መንግሥት በጀት ይመደብላቸዋል። ለሌሎች ክልሎች የተመደበው በጀት
ቶሎ እንዲደርሳቸው ሲደረግ ለአማራው ክልል የተመደበው በጀት የሚደርሰው ዘግይቶ ነው። በተጨማሪም የክልሉ ባለ ሥልጣናት ሕዝቡን የሚጠቅም እቅድ ከማውጣት ጋር በተያያዘ ችግር ያለባቸው ሲሆን በዓመቱ እንዲሰሩ የታቀዱ ፕሮጀክቶች ወይም የልማት እቅዶች ይጀመሩና በእንጉልቻ የሚጓዝ ሥራ ይጀመራል
እንደሚታወቀው ሰኔ ወር የበጀት መዝጊያ ነው። ለእነዚያ የልማት እቅዶች የተመደበው በጀት ሥራ ላይ ባለመዋሉ በየዓመቱ እየተንከባለለ ለፌደራሉ ተመላሽ
በመሆን የዘለቀ መሆኑ ይታወቃል። እንግዲህ አዳክሞ መግዛት ይሉታል ይህ ነው።
መ/ አማራው ጠብቆ ያቆያቸው ታሪካዊ ቅርሶች በተገቢው መንገድ አይጠበቁም። አማራው የራሱ የሆነ ልማድ ወግና ባህል ያለው እንደመሆኑ እነዚህን ቅርሶቹን
የሚያሳፍሩት አድርጎ እንዲመለከታቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ ስለሚደረግበትና አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር በመደረጉ እነዚያን ትውፊቶቹን እየተዋቸው እንዲመጣና
የህወሃትን ቅራቅንቦ ሳይወድ እንዲቀበል እየተደረገ ነው።ግልጽ ዘመቻም ተደርጎበታል። አንድ ምሳሌ ልጥቀስና ወደ ዐረብ አገር ወጣት ሴቶችንና ወንዶችን
የሚልከው ኩባንያ የህወሃት መሆኑን ከተስማማንበት ስማቸው ማን ተብሎ እንደሚጠራም ግልጽ ይሆንልናል። የተከበራችሁ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ! ክቡር አክሊሉ
ሀብተወልድን የማያውቅ ይኖራል ብየ አላስብም ለእድሜ ጠገቦቹ ማለቴ ነው ወጣቱንማ ከሳት ወደ ረመጥ የሆነ ሕይወት እንዲገፋ አድረገነው የለም እንዴ በምን
ሂሳብ አክሊሉን ሊያውቅ ይችላል? አክሊሉ ሪመምበርስ የሚለውን ፈልጋችሁ አግኙ ወይም የኤርትራ ጉዳይ የሚለውን የአምባስደር ዘውዴ ረታን መጽሐፍ
ስታነቡ ክቡር አክሊሉ ሀበተወልድ “አንቶኒዮ በሚል ፓስፖርት በመዘዋወር” ፋሽስት ኢጣሊያን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት ያደረጉትን ተጋድሎና ዲፕሎማሲያው
ሥራ ያሳያችኋል። ዛሬ ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትር( ፀሐፊ ክቡር አክሊሉ ሀብተወልድ) ወንበር ተቀምጠው ቀደም ሲል መለስ ዜናዊ አሁን ደግሞ ጉማሬ
የሚመስል ፊቱን ደቅኖ በመለስ የተተካው የህወሃት እስረኛ ጠ/ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የማያውቀውን ምሥጢር እንደሚያውቅ በመምሰል በዳር
ድንበራችንና በሰላማዊ መንገድ እየታገሉ ባሉ የተቃዋሚ ኃይላት ላይ የሚሰነዝረውን በክት የሆነ ንግግር ሰማ ሁሌ ያ! ደርግ በግፍ የገደለው የኢትዮጵያ ልጅ
አክሊሉ ሀብተወልድ እፊቴ ላይ ይደቀንብኛል። ክቡራን ወገኖቼ ዛሬ አማራውን አስመልክቶ የሰነዘርኳቸው ሀሳቦችን ስጠቅስ ሊሰማችሁ የሚችለውን አላጣውም
ነገር ግን ፍሬ ሀሳቡ አሁን ወይም ትናንት አማራው ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ነገ ወይም ዛሬ የእያንዳንዱን ነገድ ኢትዮጵያዊ ቤት እያንኳኳ ተራ በተራ እንደ ዓመት
በዓል በግና ዶሮ እየነጠለ ሊያጠፋን የተፈጠረ ህወሃት መሆኑን በመገንዘብ በጋራ ተደራጅተን ስንታገልና ስናስወግደው ብቻ እፎይ እንደምንል በትህትና
በመግለጽ ለዛሬ የተነሳሁበትን ነጥቤ እዚህ ላይ እደመድማለሁ።
እግዚአብሔር ከመጠላለፍ አንድነትን እንድንቀበል ይርዳን!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!
ሰላም ዴሞክርሲና ፍትሕ ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!
ቸር ይግጠመን።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on May 22, 2014
  • By:
  • Last Modified: May 22, 2014 @ 10:25 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar