www.maledatimes.com «ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን» ምንድን ነው? - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

«ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን» ምንድን ነው?

By   /   December 5, 2013  /   Comments Off on «ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን» ምንድን ነው?

    Print       Email
0 0
Read Time:39 Minute, 43 Second

«በሰላም ተሳስራችሁ ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን ለመጠበቅ ትጉ። በተጠራችሁ ጊዜ ለአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ
ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ። እንዲሁም አንድ ጌታ አንድ እምነት እና አንድ ጥምቀት አለ። ደግሞም
ከሁሉ በላይ የሆነ በሁሉም የሚሠራ፤ በሁሉም የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።» ኤፌ4፤3-7
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በዘመናችን የደረሰባት የመለያየት እና የመከፋፈል ዘመን፤ አንዱ ሌላውን
ለማጥቃት ቀን ቆርጦ፣ቦታ መርጦ፣ ዘገር ነቅንቆ፣ ጦር ሰብቆ፣ ዝናር ታጥቆ፤ነፍጥ ቀስሮ ወረድ እንውረድ ተባብሎ
በጦር መሳሪያ መዋጋት እና በሀገር፣ በሰው ኃይል፣ በማህበራዊ ግኑኝነትና ማህበራዊ ኑሮ፣በኢኮኖሚ ጥፋት ሀገሪቱን
ከአንድነት ወደ መበታተን፣ ከማዕከላዊ የንጉሳዊ አስተዳደር የክፍፍሎሽ ሰለባ በማደረግ እድገትዋን እና ሥልጣኔዋን
አንቆ ይዞ ለሰባ ስምንት ዓመታት ሲያንገላታት የቆየውን የዘመነ መሳፍንት ታሪካዊ የጥፋት ክስተት ወይም አገዛዝ ጋር
የሚዛመድ ነው።
ቤተ ክርስቲያን የሀገራችን ኢትዩጵያን አብላጫ ቁጥር ያለውን ሕዝብ በሃይማኖት የምትመራ በመሆንዋ ሕዝቡን
በቀላሉ ለመቆጣጠር ወይም ከአንድነት አስወጥቶ ከፋፍሎ ለማስተዳደር ያመች ዘንድ በተለይም ከዘውዳዊ ሥርዎ
በመንግሥት ለውጥ በኃላ እራሳቸውን መንግሥት ያደረጉት ያለፉት አርባ ዓመታት የኢትዮጵያ መንግስታት፤ መንግሥት
ሆነው ከዙፋናቸው በወጡ ማግስት ሕገወጥ ጥቃታቸውን እና ጣልቃ ገብነታቸውን የሚፈጽሙት በኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነው።
ቀደም ብሎም ቢሆን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገሥት መፈንቅለ ዘውዳዊ መንግስት አደርጎ እራሱን ጊዚያዊ
ወታደራዊ አስተዳደር መንግስት ብሎ የጠራው ደርግ፤ ንጉሰ ነገሥቱን በግፍ ከገደለ በኃላ ፊቱን ወደ ቤተ ክርስቲያኗ
በማዞር ውስጥ ውስጡን እጅግ ተናጋሪ ደፋር የሆኑትን እነ ባህታዊ ቀለመወርቅ ካሣሁን እና ሌሎችንም ካህናት
መልምሎ በለውጡ ማዕበል በማጥመቅ በቤተ ክርስቲያን ጉልላትን ዘመቻ ጀመረ፤ አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳትም
የፓትርያርክነት ስልጣን ፈላጊ በመሆን በደፈጣ የለውጥ አራማጆችን ደጋፊ በመሆን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ
ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በደርግ በግፍ ነዲገደሉ አስተዋጽዖ አድርገዋል።
በድጋሜ ከደርግ መንግሥት ላይ ከኤርትራው የገንጣይ ፓርቲ ጋር በመተጋገዘና በመረዳዳት ለአስራ ሰባት ዓመታት
የትጥቅ ትግል ያደርገው የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር (ሕወሀት) በግንቦታ 20 ቀ 1983ዓ.ም ደርግን ተክቶ አዲስ
መንግሥት ሆኖ ሥልጣኑን በተቆጣጠረበት ማግስት በኢትዮጵያ አርቶኦክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያደረገው
ጣልቃገብነት በዋናነት የሚጠቀስ ቢሆንም፤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ በአራት ኪሎ እና በአካባቢው
የሚገኙ መሀል ሰፋሪዎች ጥቂት አደባርት ካህናት ጣልቃ ገብነቱን በማጠናክር ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ችግሩን
ማባባሳቸው የሚዘነጋ አይደለም።ከዚያም በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን በልዩ ልዩ ምክንያት ግራ በማጋባታ እና
በማዋከብ ከመንበራቸው ወርደው በግዞት እንዲቀመጡ አስገዳጂ ትዕዛዝ ደረሰባቸው፤ ከዚያም ቀጥሎ የሚጠብቃቸው
የብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ እጣ ፋንታ መሆኑን ተረድተው የሚወዷትን ሀገራቸውን ጥለው ለስደት
ሕይወት ተዳረጉ።
ታሪኩን ለማሳጠር መንግሥት በተለወጠ ቁጥር በቤተ ክርስትያኗ ላይ የሚታየው ጣልቃ ገብነት ተደጋግሞ የታየ ሲሆን
በዚህ ሃይማኖታዊ ጣልቃ ገብነት ምክንያት በቤተ ክርስቲአቲያን የአንደነት አስተዳደር ያስከተለው ችግር እጂግ
በጣም መጠነ ሰፊ ነው።ከዚህም አንጻር «ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ አይመረጥም» ከሚለው
ሃይማኖታዊ ሕግጋት እና ትችት አልፎም ቤተ መግሥቱና ቤተ ክህነቱ በአንድ ክፍለ ሀገር በተለይም በአንድ የአድዋ
ተወላጆች ቁጥጥር ሥር በመዋሉ መንግሥትን ይበልጥ በጠባብ ጎሰኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዳደር እጂግ በጣም
ክፍተኛ በሆነ ደረጃ እያስተቸው መጣ። የቤተ ክርስቲያኗም አስተዳደር ከመንፈሳዊነት ይልቅ ሥጋዊነትና የጎሳ ልዩነት
ጎልቶ የሚታይበት ነው! የሚለው ሐሜታና ትችት የአደባባይ ምስጢር ሆነ። ይህ በዚህ ላይ እንዳለ አሁን በዋናነት
የሚታየው የቤተ ክርስትያን መከፋፈል ጎልቶ ወጣ፤ ይኸውም፦
1ኛ. በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳሎስ/አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ አዲስ
አበባ፤ ኢትዮጵያ፤
2ኛ. በብጽዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ኒውዬርክ፤ አሜሪካ 3ኛ. «ገለልተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን» በማለት እራሳቸውን የሰየሙ አዲስ ባለታሪኮች
በአሜሪካ ና በአውሮፓ የሚገኙ ናቸው።
በዚህ የመከፋፈል ዘመን ከሰባት ሚሊዮን በላይ የቤተ ክርስትያኗ ተክታዮች የጠፉ ስለመሆናቸው አንዳንድ በጉዳዩ ላይ
ሰፊ ጥናት ያደረጉ አባቶች ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው። ይህን ያክል ቁጥር ያለው የቤተ ክርስቲኒቱ አንጡራ ሀብቶች
ሲጠፉ ተጠያቂው ማን ነው? የሚለውን ምላሽ በኃላፊነት መልስ የሰጠ የቤተ ክርስትያኗ አካል ባይኖርም፤ በዚህ ጽሑፍ
አቅራቢ እምነት ለአንድ መንጋ አንድ እረኛ አለመኖሩ፤ ለአንዲት አማናዊት ቤተ ክርስቲያን አንድ ቅዱስ ሲኖዶስ
አለምኖሩ፣የሃይማኖቱ ባለአደራዎች ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች የተፈጠረውን መክፋፈል ለመመለስ በቂ ጥረት
አለማድረጋቸውና ከዚያም አልፎ አዲሱ የመለያየት አርበኛ «የገለልተኛው»ክፍል የውጭውን የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር
ደጀን አድርጎ በግለሰባዊ የጥቅም ተገዥነት የቤተ ክርስትያኗን የመከራ ዘመን እንዲራዘም አቀንቃኝ እና አራጋቢ ሆኖ
በመገኘቱ ጭምር ነው።
በተለይ አሜሪካን ሀገር በኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ስም ለገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን መፈልፈል የተመቻቸች ሰገነት
ሁናለች። ዛሬ በአሜሪካን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሚለው ስያሜ እየተዘነጋ፤ ከሀገር ውስጥ ነው ወይስ ከወጭው ሲኖዶስ፤
ከገለልተኛ የሸዋ ፤ የጎንደር፤ የጎጃ፤ የወሎ፤ የጉራጌ፣ የኦሮሞ… ቤተ ክርስቲያን በሚል ቤተ ክርስቲያንን የመከፋፈል
የዘመነ መሳፍንት አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን አንድነት ላይ ያነጣጠረ የጥፋት «ገለልተኛ» ዘመን እያንሰራራ መጥቷል።
ይህ አስከፊ ተግባር እና መድኅኒት የጠፋለት የጥፋት በሽታ ከአሜሪካም አልፎ ወደ አውርፓ ዘለቆ በመግባት በርዕሰ
አድባራት ሎንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን «ሲኖዶስን እንቀብላለን ፓትርያርኩን
አንቀበልም» በሚለው ሰንካላ ምክንያት በር ከፋችነት የንብረት አስተዳደር በምዕምናን ብቻ በሌላ መልኩ የመንፈሳዊ
አገልግሎት አስተዳደር በካህናት ብቻ ፤ የሰብካ ጉባዔ አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ እና ሥራ አስፈጻሚ ያለሆነ ተብሎ
በአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስትያን የመክፋፈል ጥያቄ አስነስቶ ቤተ ክርስቲያንን ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ኩባንያ
በማስመዝገብ፣ በመጭረሻም ሕንጻውን በግል ባለቤትነት ይገባኛል ጥያቄ የተነሳ የተፈጠረው አስቀያሚ ውዝግብ ቤተ
ክርስቲያንን አስገደዶ እስከማዘጋት እና ምዕመናኑን በመከፋፈል ያደረሰው አደጋ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
«ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልቦና በአንድ ሐሳብ የተባበራችሁ እንድትሆኑ
እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኃለሁ።» 1ኛ ቆሮንቶስ 1፤10
ከላይ በተራ ቁጥር 1ኛ እና 2ኛ የተጠቀሱት ቤተ ክርስቲያን እና በተክታዩ ምዕመናን የተፈጠረው መከፋፈል እጅግ
የሚያሳዘን ሲሆን፤ ቅዱስ ሲኖዶሳቱ በአጠራሩ ሕጋዊ ቢሆንም ባይሆንም እራሱን የቻለ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው
የየራሳቸው ምክንያት ያላቸው እንደመሆኑ መጠን፤ ግራቀኙ ችግራቸውን በማወቅ በመረዳት ለእርቅ የመደራደርና
የመቀራረብ ሙከራ በማድረግ ላይ ቆይተዋል። የዚህን ዝርዝር ሐተታ በሌላ ጊዜ የምንመለስበት ሲሆን ለዛሬው
በተነሳሁበት «ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን» ምንድን ነው? በሚለው ብቻ በማተኮሩ መልካም ነው ።
«ገለልተኛ» የሚለው የአማርኛ ቃል በእንግዚዘኛው «Independent» የሚለውን ተመጣጣኝ (አቻ) ቃል ያገኛል።
ትርጉሙም ከሌላ ውጫዊ ኃይል ተጽኖ ነጻ መሆን፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሙሉ ለሞሉም በማንም በምንም
አለመታዘዝ እና አለመመራት፤ በሌሎች ላይ ጥገኛ እና ግኑኝነት ወይም ውህደት እና አንድነት አለመፍጠር፤ እራስን ችሎ
በነጻነት መንቀሳቀስ የሚሉትን ትርጉሞች ይይዛል።
ከዚህም አንጻር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ገኖ ከነበረ የምራብ ሀግሮች (የኮሎኒአይዜሽን) የእጂ አዙር ቅኝ አገዛዝ «ገለልተኛ»
«Independent» ነጻ የሆነች አንድ ሀገር ናት ሲባል፤ የተለያዩ ብሔሮች ቋንቋወች ባህሎች ሳይነጣጠሉ ሳይለያዩ
በአንድነት ተቻችለው እና ግንባር ፈጥረው በወቅቱ የነብረውን የምራብ ሀገሮች የኢኮኖሚ፣ የቋንቋ፣ የአስተዳደር፣
የባህል፣የፓለቲካ እና የተገዥነት(ባርነትን)፣ማንነትን አሳልፎ መስጠት .. ከመሳሰሉት ተጽኖዎች ገለልተኛ (ነጻ) መሆንኗን
በራስ መመራትን ብቃትን እና ተከላካይነትን ያመለክታል። ይህም ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ለዘመናት እንደምናውቀውና
እንደተማርነው Indepandant Nation ክቀኝተገዥነት ገለልተኛ ወይም ነጻ መሆን የሚለውን የእንግሊዘኛ አቻ ቃል
የሚይዝ መሆኑን ያስረዳናል ማለት ነው።
በመሆኑም «ገለልተኛ» የሚለውን ቃል ለመጠቀም ፓለቲካዊ ይዘት እና ሌሎችም በገሀዱ ዓለም በሥጋዊ ፍላጎት እና
ተምኔት ዕራይና ተልዕኮ ለሚከናወኑ አንድነት እና ውህደት የሌላቸው ግለሰባዊ እና ቡደናዊ ድርጂቶች መሥሪያቤቶች እንዲሁም የሳይንሳዊ ጠባይ ያላቸው ነገሮች እና የመሳሰሉት ሰዋዊ የምርምር ግኝቶች መገለጫ መሆኑን ይበልጥ
ያስተምረናል እንጅ በክርስቲያናዊ ሕይወት እና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ገብቶ የሚሰራ ቃል አይሆንም።
ይሁን እንጂ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት በክርስቲናዊ ሃይማኖታዊ ትውፊት እና ቤተ ክርስቲያናዊ አወቃቀር ቀኖና እና
ስያሜ አንጻር «ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን» የሚለው መጠሪያነት ግለሰባዊ ጠቀሜታ እና ፍላጎትን የማስከበር ዓላማ
ያለው በሌላ በኩል ደግሞ ተዋህዶና እንድነት ፈጥሮ ከመኖር ይልቅ የመለያየት፣ የመበታተን የመከፋፈልና ብሎም
የነበረን ማንነትን (መጠሪያን) የማጣት እና ከአንድነት ጉባኤ የመለየት የመጥፋት አመሠራረት ነው። «ሐዋርያት
በሰሯት በአንዲት ቅደስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን» ከሚለው ሁሉም ካናትና እና ምዕመና በሁሉም አብያተ
ከርስቲያናት በየቀኑ ከሚጸለየው የአንደነት የሃይማኖት ጽሎት እና የሊቃውንት ሃይማኖታዊ ድንጋጌ የመወጣት ነው።
ለቤተ ክርስትያናችን አንድነት የእምነታችን ሥራዓት፣ቀኖና እና ሕግጋት፣ ትውፊትና አፈጻጸም፣ አስተዳደርና የስተዳደር
መዋቅር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግኑኝነት ጥገኝነት፣ መሠረትነት፣
ተጠቃሽነት አስረጂነት የሌለው ሃይማኖታዊ ክዋኔ ሁሉ ተቀባይነት የለውም። በቤተ ክርስትያን ውስጥ የሚገኙት
አገልጋዮች እና ተገልጋዮች በአንድነት ክርስቲያኖች፣ የሚደርጉት አገልግሎቶች መንፈሳዊ እና መገልገያዎች ሁሉ ንዋየ
ቅሳት ተብለው የሚጠሩት በዚሁ ምክንያት ነው። ስለሆነም እነዚህ ቃላት ተደጋጋፊ ወይም ጥርስና ከንፈር ሆነው አንድ
ሆነው የሚኖሩ እንጂ ምክንያት እየፈጠሩ አንዱ ከአንዱ የማይነካካ «ገለልተኛ» ተብሎ የሚጠራ አይደለም ።
መጽሐፍ ቅዱስ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነሱም የብሉ ኪዳን መጽሐፍ ነቢያት በዘመን፣ በጊዜ፣ በቦታ፣
በቀን በሳዓታት፣ አመላክተው ወደፊት የሚፈጸመውን የተናገሩትን የትንቢትና የሕግ መጻሕፍትን የሚያጠቃልል ሲሆን
ሁልተኛው የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ክፍል ፈጣሪ በተነገረለት ትንቢት፣ በተቆጠረለት ዘመን፣ በታወጀለት ቦታ በኃይለ
መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከተወለደበት ከቤተልሔም፣ በተሰደደበት ግብጽ፣ ተዘዋውሮ
ባስተማረባት በከንአን/ኢስራኤል፣ በጸለየበት ገዳመ ቆረንቶስ፣ ከተሰቀለበት ቀራንዮ፣ ከተቀበረበት ጎልጎታ በአምላክነቱ
ሞትን ድል አድርጎ እስከተናሳበት ድረስ ያሰተማረውን፣ ያደረገውን ገቢረ ታምራት፣የሙታን ማስነሳት እና ለእኛ
የሰጠውን ተስፋ መንግስተ ሰማያት የሚያስተምረውን ነው። የሁለቱ ክፍል ጥምረት፣ አስረጂነት፣ ገላጭነትና
ተወራራሽነት፣ ተግባቢነትና ተደጋጋፊነት በአንድነት መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ ይጠራል።በመሆኑም በውስጡ ባሉት
የመጽሐፍት አንድነት መካከል «ገለልተኛ» የሚለው ስያሜ፤ አወቃቀርና አመሠራረት ቦታ የለውም።
በመጽሐፍ ቅዱስ የአንድነት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት መጽሐፍት ነጻ፣ ግኑኝነት የሌለው፣ እራሱን የቻለ፣ ለየብቻው
የሆነ፣ የተከፋፈለ፣ የተለየ ግንዛቤ የሚሰጥ «ገለልተኛ» መጽሐፍ የለም፤ ይልቁንም አንዱ በአንዱ ላይ ጥገኝነት
አንድነት፣ ተግባቢነትና አንድ አይነት መልዕክት የሚያስተላልፍ አንድ ቅዱስ መጽሐፍ ተብሎ የሚጠራ ዘመን
የማይሽረው፣ ጥቅም የማይለያየው፣ ተነጣጥሎና ተለያይቶ የማይታይ ሁሉም በአንድነት ሕያው የአንድ የአምላክ ቃል
ብለን የምንቀበለው እና የምናምነው ነው። ስለሆነም «ገለልተኛ» ብለን የምንሰይመው አንድም ነገር የለም ሊኖርም
አይችልም።
«ይህንንም ያደረገው የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ ምእመናን ለክርስቲያናዊ አገለግሎት
ለማዘጋጀት ነው። እንዲሁም በእምነት የእግዚአብሔርን ልጅ በማወቅ ወድሚገኘው አንድነት ደርሰን ክርስቶስ
ፍጹምና ሙሉ እንደሆነው እኛም ሙሉ ሰው እንድንሆን ነው።» ኤፌ 4፤12-13 እንግዲህ ከላይ በዝርዘር
እንደተመለከትናው ከወንጌልና ከሀገራችን ታሪክ ጋር እንዳገንዘብነው በማስረጃ ይዘን እንደተከታተልነው «ገለልተኛ ቤተ
ክርስትያን» የሚለው አስተሳሰብ ግለሰባዊ ጥቅም፣ ፍላጎትና እና ግብዝነት የተፈጠረ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀባይነት
የሌለው ተግባር መሆኑን እንረዳለን።
«ገለልተኛ ቤተ ክርስትያን» የሚለው ከኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ አንዲት ቤተ ክርስቲያን የወጣ፣ የብልጣብልጦች የንግድ
መርከብ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የአኩራፊዎች ወይም እንቢተኞች በራሳቸው ፈቃድ የመሠረቱት መደበቂያ ዋሻ መሆኑ
በሁሉም ዘንድ ይታወቃል። ይሁን እንጂ «ወልድ ሲነካ አብ ይነካል» በማለት ወንጌል የጠገቡ ምስጢር የመረምሩ
አባቶቻችን እንደሚተርቱት ሁሉ ቤተ ክርስቲያኗን በሚበታትን ደካማ «የገለልተኝነት» ግለሰባዊ የመክፋፈል አስተሳሰብ
ብዙዎቹ ታታላቅ የሚባሉ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያንዋ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ አባቶች ጭምር የዚህ አሳፋሪ እና የአንድነት
አደራ ጠባቂነት ጉድለት ተግባር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተባባሪ እና ተሳታፊ ሆነው ቆይተዋል ፤ ለሃይማኖቱ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ አንዳንድ ማህበራትም እንደዚህ ያለውን ሕገወጥ «የገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን» የሚለውን የአንድነት
አፍራሽ ተውሳክ ለማጋለጥ አልደፈሩም።
ይህ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚታየው «የገለልተኝነት» ጥቃት አዲስ የሚመሠረቱትን አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይሆን
ከላይ እንደተ ገለጸው ወደ አውሮፓም ዘለቆ በመግባት በተለይም የዛሬ አርባ ዓመት በቅድስ ሲኖዶስ ውሳኔ እና በብጹ
ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የተመሠረተችውን መንፈሳዊ መዋቅሩን ጠብቃ
ስትመራና ስትገለግል የቆየችውን የርዕሰ አደባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድሥት ማርያም ነባር ቤተ ክርስቲያንን
የተደራጁ ግለሰቦች የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የግል ባለቤት ለመሆን በገለልተኝነት ለማደራጀት ባስነሱት ከፍተኛ አመጽ
ምክንያት መንፈሳዊ አገለግሎቱ በኃይል ተቋርጦ ምዕመናን ተከፋፍለው ከአንድ ዓመት በላይ የቆየ ውዘግብ ፈጥሮ
በመጨረሻ በዚሁ ምክንያት እጅግ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ መንፈሳዊ አገልግሎቱ በግፍ ተቋርጦ ቤተ ክርስትያኑ
ከተዘጋ ስምንት ወራት ተቆጠሩ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሲመሠረተው ቢያንስ ክአራት መቶ ያላነሱ ምዕመናን
የሚገለገሉበት ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግላቸው ካህን እንደሚያስፈልጋቸው እና ለመንፈሳዊ አገልግሎቱ የሚሆነውን
መባውን፣ ማስቀደሻውን እና ማወደሻውን ሁሉ እንደሚችሉ ተፈራርመው ሲያቀርቡና አስፈላጊነቱ በቅዱስ ሲኖዶስ
ሲታመንበት ይመሠረታል። ነገር ግን «ገለልተኛ ቤተክርስትያን» የሚለው ይህን መመዘኛ ሳያሟላ በአስተዳደር በደል
ደረሰብኝ ብለው ያኮረፉ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በግል ጥቅመኝነት ግለስባዊ ፍላጎት ያላቸው ካህናትና መነኮሳት ወዳጂነት
ካላቸው ጳጳሳት በግል ጽላት እያስባረኩ እንደ ሱቅ በደረቴ በተመቻቸው አጋጣሚ «ገለልተኛ» አድርገው ይሰይሙታል።
መነገጃ ታርጋው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሚል ነው። እውነታው ግን የወቅቱን ግርግር
ተጠግቶ በግለሰቦች ፈቃድ ብቻ የተመሠረተ ከአንድነት ጉባዔ የተለየ አስመሳይ «ገለልተኝነት» ነው። ምክንያቱም
ግለሶቹ ያለፈቀዱለት ሊቀ ጳጳስ ገብቶ ያማይባርክበት፣ ግለሰቦቹ ያልፈቀዱለት ካህን የማያገለግልበት፣ ምዕመናን ቢሆን
እንደ መጻተኛ ለጎሪጥ የሚታዩበት የሚገላመጡበት እና «መጤዎች» ተብለው የሚሰደቡበት የተበሻቀጠ ግንዛቤ
የጎደለው ስሪት ነው። በመሆኑም አሁን በሎንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ችግር የዚህ
በሽታ አዛማቾች ወይም ተላላኪወች «ገለልተኛ» እና የቤተ ክርስቲያንን ሕንጻ በግለሰብ ለመያዝ የሚደረግ እጅግ
በሚቀፍ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አስተዳደር መዋቅር ላይ የተደረገ በመለያየት የተሞላው የጥቅም ያደነዘዘው
አሳዛኝ ዘመቻ ነው።
«ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን» ማለት በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠውን የአባቶች መለያየት ክፍተት እንዲቀጥል የተሳሳተ
መገድ የሚጠርግ ነው። ቤተ ክርስቲያን ሁሉም የክርስትያኖች ማምለኪያ፣ የመንፈስ ቅዱስ ሀብት መሆንዋ ቀርቶ ጊዜ
የፈቀደላቸው፣ኃይለ የተሰማቸው፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው የተመኩ ግለሰቦች በቡድን ተደራጅተው በቤተ
ክርስትያኗ ውስጥ ግንዛቤ የጎደላቸው ግብረ በላተኞችን እና ገንዘብ አምላኪ መሰል ካህናትን በማስተባበር፤ ከቤተ
ክርስቲያን አንድነት የወጣ፣በጠባብ ጎሰኝነትን መሠረት ያደረገ፣ በግለሰቦች የግል ባለቤትነት የተያዘ፣ አስታራቂም
ታራቂም ያልሆነ፣ የቤተ ክርስቲያን ማዕከላዊ መንፈሳዊ መዋቅር የተለየው፣ ተቆጣጣሪና የበላይ ጠባቂ የማይታወቅበት፣
መለያየትና መበታተን የሚጠናከርበት ከሀገራችን ኢትዩጵያ እና ከኢትዩጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን
የአንድነት ታሪክ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ጸረ አንድነት አስተሳሰብ እኩይ ተግባር ነው።
ስለዚህ ሁሉም ኢትዩጵያዊ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተክታዩች ሁላችን «እርስ በርስሷ
የተለያየች መንግሥት አትጸናም» ብሎ መጽሐፍ እንደሚያስተምረን እምነትን በፍቅር በሰላም ለማከናወን የሀገር
አንድነትን ለማስጠበቅ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ለውጥ ለማምጣት የሚቻለው የእምነትና የታሪክ በለአደራ
የሆነችውን ቅደስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በሐዋርያት ትዕዛዝ መሠረት በአንድነት ስንጠብቅ
እምነታችን የጸና መሆኑን አወቀን «ገለልተኛ» በማለት እየተቋቋሙ የቤተ ክርስቲያንን የመከራ ጊዜ የሚያረዘሙ ትርጉም
የጠፋለትን የጸረ አንድነት ግለሰባዊ የጥቅመኞች ጎዞ እንዲገታ ማድረግ የአዲሱ ትውልድ ታሪካዊ ግዴታ ነው።
እንዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችን በአንድነት ይጠብቅልን!
መ/ጥ መንገሻ መልኬ
ኅዳር 2006 ዓመተ ምረት ዘመነ ማርቆስ ወንጌላዊ፤

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on December 5, 2013
  • By:
  • Last Modified: December 5, 2013 @ 9:36 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar