www.maledatimes.com ደስታና ቀቢጸ ተስፋ! በእውቀቱ ሥዩም - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ደስታና ቀቢጸ ተስፋ! በእውቀቱ ሥዩም

By   /   December 5, 2013  /   Comments Off on ደስታና ቀቢጸ ተስፋ! በእውቀቱ ሥዩም

    Print       Email
0 0
Read Time:21 Minute, 24 Second

ውሃ ልማት በተባለው የኛ ሠፈር ውስጥ፣ ሁለት ዝነኛ ተማሪ-ቤቶች ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያው እንደ ቅርስ የሚቆጠረው አንጋፋው ‹‹ብርሃንህ ዛሬ
››ትምርት ቤት ሲሆን፣ ሁለተኛው የሀዲስ አለማየሁ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምርትቤት ነው፡፡ በሁለቱ ትምርት-ቤቶች መካከል በግምት ሦስት
መቶ ሜትር ርዝመት ያለው የእግር መንገድ ተዘርግቷል፡፡ ከእግር መንገዱ ግራና ቀኝ፣ መጻህፍት ቤቶች፣ ወይም ጽሕፈት መሣሪያ ሱቆች አይታዩም፡፡
አካባቢውን የወረሩት መሥረሪያ ቤቶች (ፔንሲዮኖች) ብቻ ናቸው፡፡ ከቦዘኔ ቀኖች ባንዱ ሥራየ ብየ ግራ ቀኙን ማስተዋል ጀመርሁ፡፡ አቮካዶ
ፔንሲዮን-ዜድ ቢ ፔንሲዮን-ደስታ ፔንሲዮን-ጌት ፔንሲዮን-ሐይሌ-ፔንሲዮን-ኒውዴይ ማሳጅ-አህመድና ወዳጆ ጫት ቤት-መሲ ራያ ባር-ኦርዮን
ፔንሲዮን-ክላሲካል ፔንሲዮን በግራ በቀኜ ተሰልፈዋል፡፡

የፔንሲዮኖች ሠልፍ በሚጠናቀቅበት ቦታ ላይ ‹‹ሴማህ የማህጸን ክሊኒክ›› ካልጋ ላይ ጦርነት የተጎዱ ቁስለኞችን ተቀብሎ ለማስተናገድ፣
ስትራቴጂካዊ ቦታ መርጦ ጉብ ብሏል፡፡ ባጠቃላይ እዚህ አካባቢ የሙዝ ልጣጭ ያዳለጠው ሰው የሚወድቀው አልጋ ላይ ነው፡፡

ይህ የኛ ሠፈር መልክ ከሞላ ጎደል የዛሬይቱ ኢትዮጵያ መልክ ነው፡፡ ያጋነንኩ ከመሰላችሁ፣ ሠፈራችሁን ግራና ቀኝ ተመልከቱ፡፡ በመቋቋም ላይ
የሚገኙት የንግድ ቤቶች፣ ከመብል ቤት፣ ከመጠጥ ቤት፣ ከልብስ ቤት፣ ከምኝታ ቤት ከጭፈራ ቤት አያልፉም፡፡ ባሁኑ ጊዜ፣ አንገቴን ወለም አለኝ
ስትል፣ ሙታንታህ ሥር ገብተው የሚያሹህ ማሳጅ ቤቶች፣ በሽተኛ የጫነ አምቡላንስ በር ላይ አቁሞ የሚቅም ሾፌር ሳይቀር፣ የሚያስተናግዱ ጫት
ቤቶች፣ ድፍን መንደር እንደ ጋን ገልብጠው በጭስ የሚያጥኑ ሺሻ ቤቶች ተበራክተዋል፡፡

በግሌ፣ እንደ ከበደ ሚካኤል ‹‹ደስታ ጭቅቅት ነው ነፍስን ያሳድፋል›› የምል መናኝ አይደለሁም፡፡ ምድራዊ ተድላ ባለበት ቦታ ሁሉ ታጥቄ
ብሠማራ አልጠላም፡፡ የሚከተለውን የምጽፈው መደሰቻ ቤቶችን መፍላት ለማውገዝ አይደለም፡፡ ዓላማየ፣ አዲሱን የተድላ ዝንባሌ ከየት
እንደመነጨ ያቅሜን ያክል ለማሳየት ነው፡፡

‹‹የመሥረሪያ ቤቶች፣ የጫት ቤቶች፣ የመጠጥ ቤቶች ወዘተ፣..በየቦታው መፍላት የሚያመለክተው ደስታ መግዛት የሚችሉ ሰዎች መበራከታቸውን
ነው፡፡ ይህም የዜጎችን የገቢ መጠን ማደግ ያሳያል፡፡ በተዘዋዋሪም የአገሪቱን እድገት ያመለክታል፡፡ ታድያ ምናባህ ቆርጦህ ታማርራለህ?›› የሚለኝ
አይጠፋም፡፡ እኔን የሚያሳስበኝ፣ ያእምሮ ተቋማት ከተድላ ቤቶች ጎን ለጎን ማደግ አለመቻላቸው ነው፡፡ የመዲናይቱ መመኪያዎች የነበሩት የቡክ
ወርልድ መጻፍት ሱቆች በፍጥነት መዘጋታቸው፤ በባንኮችና በአበባ ሱቆች መተካታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ አራት ኪሎ የሚገኘው፤
አንጋፋው‹‹ የኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅት›› ሳይቀር ዓይናችን እያየ ወደ ካፍቴርያ ተቀይሯል፡፡ የምርምር ማዕከሎች፣ ቤተ መዘክሮች፣ ማተሚያ
ቤቶች በግንባታ መስመር ላይ አይታዩም፡፡ ከፈጠራ፣ ከምርምር፣ እንቆቅልሾችን በመፍታት የሚገኝ ደስታ ደብዛው የለም፡፡ ያለው ሥጋዊ ደስታ ብቻ
ነው፡፡

ከጥቂት ጊዜያት አስቀድሞ፣ ከመንፈቀ ሌሊት በፊት መንገድ ዳር የምትቆም ሴት፣ ታክሲ ጠባቂ የቤት እመቤት ስትሆን፣ ከመንፈቀ ሌሊት በኋላ
መንገድ ዳር በከፊል ተራቁታ የምትቆም ሴት ደግሞ ደንበኛ የምትጠባበቅ ሴተኛ-አዳሪ ናት ብየ አስብ ነበር፡፡ አሁን ሴተኛ- አዳሪዎች ከምሽቱ ሁለት
ሰዓት ጀምረው ሲቆሙ አያለሁ፡፡ አሁን ያለው ማህበራዊ ሞገድ ብርቱ ከመሆኑ የተነሣ፣ የቤት እመቤቶችን ጊዜና የሴተኛ አዳሪዎችን ጊዜ የሚለየውን
ድንበር አፍርሶታል፡፡ የወሲብ ገበያ፣ በጠፍ ጨረቃ፣ በሽሽግ የሚካሄድ መሆኑ ቀርቷል፡፡

አዲሱ ለውጥ በግበረገብ ስብከት የሚቀለበስ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የዜጎች ጠባይ ከአገዛዝ ሥርአት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነውና፡፡

የፖለቲካ ጭቆና በበረታበት አገር ውስጥ ወሲባዊ ልቅነት የመጨረሻው የነጻነት አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አመንዝራነት፣ ዜጎች፣ ሌላው ቢቀር፣
ብልታቸው በመንግሥት ቁጥጥር ስር አለመሆኑን የሚያሳዩበት መንገድ ነው፡፡

አባቶቻችን ከእኛ የተሻለ የደስታ ምንጮች ነበሯቸው፡፡ ቢያንስ ከጀብዱ የሚገኝ ደስታ ነበራቸው፡፡ አንድ ሰው ከጦርነት የሚገኝ ግዳይ ባይቀናው
እንኳ፣ ቆላ ወርዶ፣ የፈረደባትን ቀጭኔ ገድሎ በመመለስ ቤቱ ውስጥ ከበሮ ማስደለቅ ይችል ነበር፡፡ ‹‹ደስታ ማለት፣ ኃይለኛ የመሆን ስሜት ነው››
የሚለው የኒቸ ሐሳብ፣ በጊዜ የተፈተነ ሐቅ መሆኑን አንርሣ፡፡

ከዓለም ተነጥላ በብህትውና በምትኖር አገር ውስጥ መኖር በራሱ የሚያጎናጽፈው ያላዋቂነት ደስታ ነበር፡፡ ቀደምቶቻችን ራሳቸውን ከሌሎች አገሮች
ብልጽግና ጋር አነጻጽረው እርር ድብን የሚሉበት አጋጣሚ ብዙ አልነበረም፡፡ ስለራሳቸው፣ ስለአካባቢያቸው የነበራቸው እምነት በእርካታ የተሞላ
ነበር፡፡ እዚህ ላይ ጸሐፌ ትአዛዝ ገብረሥላሴ ስለ አዲስአበባ ምሥረታ የጻፉትን ማንሣት አለብኝ፡፡ እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹ወይዘሮ ጣይቱ፣ …ከዝያች ከፍል ውሀው አጠገብ ከተሠራችው ቤት ወርደው ተቀመጡ፡፡ ከተማ መሥራትም ተጀመረ፡፡ መኩዋንንቱም ቦታ
ቦታውን እየተመራ ቤቱን ይሠራ ጀመር …አገሩም እጅግ ያማረ ሆነ፡፡ ሠራዊቱም ወደደው፡፡ ወይዘሮ ጣይቱም ይህንን ከተማ ስሙን አዲስ አበባ በሉ
ብለው አዘዙ፡፡››

አዲስ አበባ የተቆረቆረች ሰሞን የነበራትን መልክ በፎቶ የተመለከተ የዛሬ ዘበን ሰው ‹‹አገሩም እጅግ ያማረ ሆነ›› የሚለው የጸሐፌ ትእዛዙ አስተያየት
ሰማይ የሚያክል ቀልድ ይሆንበታል፡፡ ከተማይቱ ባብዛኛው የደሳሳ ጎጀዎች ጥርቅም ነበረች፡፡ ደግነቱ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ የከተማይቱን ትልልቅ የወፍ
ጎጆዎች ከፓሪስና ከለንደን ማለፍያ ሕንጻዎች ጋር አወዳድረው የሚሸማቀቁበት እድል አልነበረም፡፡ የከተማይቱ እጅግ የተጋነነ ስያሜ ይህን ያሳያል፡፡
እቴጌ፣ ከተማይቱን አደይ አበባ፣ ጽጌረዳ አበባ፣ የሱፍ አበባ ብለው መጥራት ይችሉ ነበር፡፡ ግን በጊዜው የነበረው የአበባ ዝርያ ሁላ ‹‹እጅግ ያማረ
ሆነ›› የተባለውን የከተማይቱን ውበት ለመግለጽ በቂ ሆኖ ስላላገኙት ‹‹አዲስ አበባ ›› ለማለት ተገደዱ፡፡ አለማወዳደር ደጉ!!

እኛ እኒህ የደስታ ምንጮች ደርቀውብናል፡፡ ሌላው ቢቀር ባለሐመሩን ባለጸጋና ባለዊልቸሩን ለማኝ እኩል የሚያስፈነድቁት የግርኳስና የሩጫ ድሎች
እየመነመነኑብን በመሄድ ላይ ናቸው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ፣ ያገራችንን ስቃይ ከሌሎች አገሮች ሲሳይ ጋር የምናወዳድርበት መስኮት በየቦታው
ይጠብቀናል፡፡

ባንድ ምሽት ኤድናሞል በተባለው ስመጥር የቦሌ ሕንጻ ሥር አልፋለሁ፡፡ አንድ ትንሽ ለማኝ ልጅ ካፍያ እየመታው አዳፋ ነጠላውን ተከናንቦ
ኩርትም ብሎ ተቀምጦ ቀና ብሎ ህንጻው ላይ ያለውን ባለግዙፍ ስክሪን ቲቪ ይመለከታል፡፡ ከቲቪው የሚፈልቅ ሰማያዊ ብርሀን በመከረኛ ፊቱ ላይ
አርፎ አቫታርን አስመስሎታል፡፡ አልፌው ስሄድ በስክሪኑ ውስጥ የሚያየውን ለመገመት አልተቸገርሁም፡፡ ተዋናይት ሙሉ ዓለም ታደሰ፣ ምቾት
ያሳበጣቸውን ብላቴኖች ‹‹ሶያ›› ስትመግብ ያያል፡፡ አስረስ በቀለ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ፓስታ ሲበላ ያያል፡፡ የጠገቡ ፈረንጆች ሲዘሉ ያያል፡፡
መከረኛ ሕይወቱን ስክሪኑ ውስጥ ከሚያየው በድሎት የተሞላ ዓለም ጋር ሲያወዳድረው ምንድነው የሚሰማው? በዲጂታል ሚድያ በተጥለቀለቀ
ዘመን ውስጥ፣ የብዙ ኢትዮጵያውያን እድል ከዚህ ልጅ እድል የተለየ አይደለም፡፡

ከድል የሚመነጭ ደስታ ካጣን፣ በማወዳደር ምክንያት ማግኘት የሚገባንን ደስታና ርካታ ካጣን የመጨረሻው አማራጭ ምንድነው? በጦርሜዳ፣
ወይም ባደን ያጣነውን ጀብዱ ባንዲት ድሀ ሴት ላይ ጉልበታችንን በመፈተን ልናካክሰው እንሞክራለን፡፡ በምርቃና፣ በስካር እና በቀለጠ አሸሸገዳሜ
ውስጥ ገብተን አስፈሪውን ኑሮአችንን ለማምለጥ እንሞክራለን፡፡

ቅጥ ያጣ የደስታ ፍላጎት ከቀቢጸ ተስፋም ይመነጫል፡፡ ቱሲዲድየስ የተባለ የጥንት ግሪክ ጸሐፊ ባንድ ወቅት አቴንስን አጥቅቷት ስለነበረው ወረርሽኝ
ይጽፋል፡፡ ጸሐፊው፤ ዜጎች በበሽታው እንደ ‹‹ዝንብ›› ተራ ሞት እየሞቱ ማለቃቸውን ከዘገበ በኋላ የሚከተለውን ይጨምራል፡፡

‹‹ወረርሽኙ ድንገት ባቴናውያን ላይ የልቅነት ጸባይ አሰፈነ፡፡ ባለጸጎች ድንገት ሲሞቱ ድሆች የሙት ባለጸጎችን ንብረት ወረሱ፡፡ ይህንን የተመለከቱ
ሰዎች ጥንት በጓዳቸው ውስጥ ሸሽገውት ያኖሩትን አመላቸውን ወደ አደባባይ አወጡት፡፡ ገንዘባቸውን በፍጥነት እየመዘዙ፣ ደስታ ሊሸምቱበት
ተጣደፉ፡፡ ገንዘብና ሕይወት እኩል አላፊ ጠፊ መሆናቸውን አይተዋልና፡፡ በጊዜው ሕግ የማክበር ፍላጎት የነበረው አንድም ሰው አልነበረም፡፡
በሕይወት ተርፌ ለፍርድ እቀርባለሁ ብሎ የሚያስብ ሰው አልነበረም፡፡ በጊዜው፣ ዋጋ ያለው ነገር ጊዜያዊ ፌሽታ ብቻ ነበር፡፡ ፈሪሐ- እግዚአብሔርም
ሆነ ሰው ሰራሽ ሕግ ፋይዳ አልነበራቸውም፡፡ ..ሁሉም ሰው፣ የሞት ፍርድ የተፈረደበት ሰው አድርጎ ራሱን ይቆጥር ስለነበር የስቅላቱ ጊዜ ከመድረሱ
በፊት የተገኘችውን ደስታ ለማጣጣም ተሸቀዳደመ፡፡››

በኔ ዘመንና በጥንት አቴናውያን የቸነፈር ዘመን መካከል መሠረታዊ መመሳሰል አለ፡፡ በሁለቱም ዘመኖች ውስጥ ስለነገ ተስፋ ማድረግ የለም፡፡ ለፍቺ
የሠራሁት ቤቴን ባቡር ይሁን ሰርጓጅ መርከብ በውል ያልታወቀ ነገር ጥሶት የሚያልፍ ከሆነ ቤት ለመሥራት እንዴት ላቅድ እችላለሁ? ሰባት መቶ
ሺህ ብር የገዛሁትን ቤቴን በክረምት አፍርሶ ፣ ደርዘን ጃንጥላ የማይገዛ ፍራንክ ሸጎጥ አድርጎ የሚያባርረኝ ባለስልጣን ባለበት አገር ውስጥ ጎጆ ለምን
እቀልሳለሁ? ጌቶች ለችግር ቀኔ ያጠራቀምኩትን ብር በችግር ቀናቸው የሚወርሱብኝ ከሆነ የባንክ ደብተር የማወጣው ለምንድን ነው? ልጄ
በሕይወት እያለሁ እጓለ ማውታ ሊሆን እንደሚችል እያወቅሁ ‹‹የዛሬ አመት የማሙሽ ልደት፡›› እያልሁ የማዘፍንበት ምክንያት ለምንድን ነው?፣
‹‹ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር›› ከሚለው መፈክር በስተቀር ኢትዮጵያን ለዘላለም የሚያኖራት መሠረት መፍረሱን እያወቅሁ ለሚቀጥለው ዓመት
እንዴት ላቅድ እችላለሁ? ተው ባክህ!! እኔም እንደ ጥንት አቴናውያን የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ሰው እኖራለሁ፡፡ የመስቀያው ገመድ አንገቴ
ውስጥ እስኪገባ ድረስ የጥንቱን የባላገር ግጥም በቃሌ እወጣለሁ፡፡

‹‹የራበህም ብላ፣ የጠማህም ጠጣ

ከዚህ የተሻለ ፣ ምንም ቀን አይመጣ

ላገኝ ነው በማለት፣ ሞትሁኝ በሰቀቀን
ሄዶ ሄዶ አለቀ፣ የምጠብቀው ቀን››

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on December 5, 2013
  • By:
  • Last Modified: December 5, 2013 @ 10:48 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar