www.maledatimes.com በመዲናዋ ምስጢራዊ የወሲብ ገበያ ደርቷል - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Addis Admas  >  Current Article

በመዲናዋ ምስጢራዊ የወሲብ ገበያ ደርቷል

By   /   December 7, 2013  /   Comments Off on በመዲናዋ ምስጢራዊ የወሲብ ገበያ ደርቷል

    Print       Email
0 0
Read Time:23 Minute, 18 Second

AddisAdmass
የትላልቅ ድርጅቶች ፀሃፊዎች፣ ሞዴሎችና ተዋናዮች አሉበት
ድንግልናን በ10ሺ ብር የሚያሻሽጡ ደላሎች ሞልተዋል
የከተማዋ ቱባ ባለሃብቶች “የአገልግሎቱ” ተጠቃሚዎች ናቸው

ሲኤምሲ ሣሚት ማዞሪያ አካባቢ ካሉት ዘመናዊ ቪላ ቤቶች በአንደኛው 12ሺ ብር ወርሃዊ ኪራይ እየከፈለች ትኖራለች፡፡ የምታሽከረክረው ኤክስኪዩቲቭ ቶዮታ፣ በየዕለቱ የምትቀያይራቸው እጅግ ውድ ዋጋ ያላቸው አልባሳቶቿና በየመዝናኛ ሥፍራው የምትመዘው ረብጣ ብር የተንደላቀቀ ኑሮ እንደምትመራ ይመሰክራሉ፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናትና መዲናችን አለማቀፋዊ ስብሰባዎችን በምናስተናግድበት ጊዜያት እሷን ፈልጐ ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡
ቦሌ ፍሬንድሽፕ ሕንፃ ላይ በከፈተችው ቡቲክ የምታገኘው ገቢ ይሄን ያህል ሊያዝናናት እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ገቢ ወጪዋን አጥብቃ የማትቆጣጠርበትን ይህንኑ ቡቲኳን ታናሽ እህቷ ትውልበታለች፡፡ እሷም አልፎ አልፎ “ሥራ” በማይኖራት ጊዜ ብቅ እያለች ትጐበኘዋለች፡፡ ታናሽ እህቷ ቤተሰቡን ሁሉ ቀጥ አድርጋ የምታስተዳድረው እህቷ፤ ስለምትሰራው ምስጢራዊ ሥራ አንዳችም የምታውቀው ነገር ያለ አይመስልም፡፡ እሷ የምታውቀው ከተለያዩ የውጪ አገር ሰዎች ጋር የአየር ባየር ንግድ እንደምታጧጡፍና በየጊዜው ወደተለያዩ አገራት ለሥራ ጉዳይ እንደምትመላለስ ብቻ ነው። ሥራዋ የግል ሚስጢሯ ብቻ ሆኖ እንዲኖር የምትፈልገው ህሊና (ስሟ ለዚህ ጽሑፍ የተቀየረ) ይህንን የእህቷን እምነት አጥብቃ ትፈልገዋለች። በተለያዩ የመዝናኛ ሥፍራዎች ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ደንበኞቿ ጋር እየከረመች በመጣች ቁጥር ለእህቷ የተለያዩ ቸኮሌቶችና ስጦታዎችን እየያዘችላት መምጣቷ የእህቷን እምነት አጠናክሮላታል፡፡
እሷ “ቢዝነስ” ብላ የገባችበት ህይወት ገቢ፣ እህቷ ቀኑን ሙሉ ተገትራ ከምትውልበት ቡቲክ ገቢ ጋር ሊወዳደር እንደማይችል ስለሚገባት “ሥራውን” አጥብቃ መያዙን ትፈልገዋለች፡፡ የንግድ ፍቃድ እድሣት፣ ቫት ምዝገባ፣ ሪሲት ማሽን፣ ቀረጥና ታክስ የሚሉ ዝባዝንኬዎች የሌሉበት፣ “ራስን እያስደሰቱ ሌሎችን በማዝናናት” በቀን የሚገኝ ረብጣ ብር ከቡቲኳ ወርሃዊ ገቢ በእጅጉ ይልቃል። ተፈጥሮ ያደላትን ውበትና ማራኪ ቁመናዋን ለገበያ እያቀረቡ በተሻለ ገንዘብ ለመሸጥና ጠቀም ያለ የኮሚሽን ገንዘብ ለመቀበል አሰፍስፈው የሚጠባበቁ ደላላ ደንበኞች አሏት፡፡ ለዚህ ተግባር ብቻ የምትጠቀምበት የሞባይል ስልኳ ሲጮህ “ሥራ” እንደተገኘ እርግጠኛ ትሆናለች። ቅያሬ ልብሶችን የምትይዘበትና ሁሌም ለጉዞ ዝግጁ የምታደርገውን ቦርሣዋን አንጠልጥላ ውልቅ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ወደ ሥራ የምትንቀሳቀሰው በደላሎቹ መኪና ነው። ደላላው እሷን ካለችበት ወስዶ ወደምትፈለግበት፣ ሥራዋን ስትጨርስ ደግሞ ወደነበረችበት የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ የኮሚሽን ክፍያው እነዚህን አገልግሎቶች ያካተተ ነው፡፡ ህሊና ይህንን ህይወት ላለፉት አራት አመታት ኖራበታለች። ከዚህ ህይወት ስለመውጣትና ቢዝነሱን ስለመተው ለአፍታም አስባ አታውቅም፡፡
ባላት ትርፍ ሰዓት ሁሉ ራሷን እጅግ አድርጋ መጠበቅ፣ ጂም መሥራት፣ ሳውና፣ ስቲምና ማሣጅ በየጊዜው መግባት ታዘወትራለች፡፡ ውበቷንና ጥሩ ቁመናዋን ጠብቃ ለማቆየት ማድረግ የሚገባትን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አትልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለዚህ ሁሉ አዱኛ ያበቃት እሱ በመሆኑ የሚፈልገውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበት ታምናለች፡፡ ይህ የህሊና ህይወት የብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴቶች ህይወት እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ በመዲናችን አዲስ አበባ እየተጧጧፈ የመጣውን ምስጢራዊ የወሲብ ገበያ የተቀላቀሉ የከተማችን ወጣት ሴቶች የትላልቅ ድርጅቶች ኤክስኪዩቲቭ ፀሐፊዎች፣ የሽያጭ ሰራተኞች፣ ሞዴሎች፣ የፊልም ተዋናዮች፣ የዩኒቨርስቲዎችና የኮሌጅ ተማሪዎችና ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያላጠናቀቁ የሀብታም ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህን ወጣት ሴቶች ለወሲብ ሽያጭ “ሥራ” የሚያመቻቹና የማገናኘት ተግባሩን በቅልጥፍና የሚወጡ ፈረንጆች “ፒምፕ” የሚሏቸው አይነት ደላሎች በከተማችን እየተበራከቱ ነው፡፡ ደላሎቹ ራሳቸው በኔትዎርክ የተሣሰሩ፣ የራሳቸውን መኪና ይዘው የሚንቀሳቀሱ፣ በከተማው ውስጥ አሉ የተባሉ ሆቴል ቤቶችን፣ እንግዳ ማረፊያዎችን፣ መቃሚያ ቤቶችንና የመዝናኛ ሥፍራዎችን በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉ ናቸው፡፡

ደላሎቹ ወደ እነዚህ ሥፍራ የሚመጡ አዳዲስ እንግዶችንና ነባር ደንበኞቻቸውን ለማጥመድና እንደ እንግዳው ፍላጐት የሚጠይቀውን ለማቅረብ ሁሌም ዝግጁ ናቸው፡፡ በአንዳንድ የከተማችን ሆቴሎችና እንግዳ ማረፊያዎች ውስጥ የሚሰሩ እንግዳ ተቀባዮች፣ (receptionists) አስተናጋጆችና የትላልቅ ቪላ አከራዮች የኔትዎርኩ አባላት ናቸው፡፡ አዲስ እንግዳ የመምጣቱ ዜና እነዚህ ደላሎች ጆሮ ለመድረስ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ይበቃሉ፡፡ ከዛም ደላሎቹ ሥራቸውን ይጀምራሉ። በእንግዳው መውጫና መግቢያ ላይ መረቡ ይዘረጋል። አብዛኛውን ጊዜ የደላሎቹ መረብ አሣውን ሣያጠምድ አይመለስም። ከልጃገረድ እስከ ቤት ልጅ፣ ከቤት ልጅ እስከ የቡና ቤት ሴት ድረስ እንግዳው የጠየቀው ይቀርብለታል። በዚሁ የሴት ድለላ ተግባር ላይ የተሰማሩ ደላላዎች እንደነገሩኝ፤ በአሁኑ ወቅት በከተማችን ለገበያ የሚቀርቡ ልጃገረድ ሴቶች እየተበራከቱ ነው። ሴቶቹ በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከ14-17 ዓመት የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ናቸው፡፡ አልፎ አልፎም ከክፍለ ሃገር የሚመጡ ታዳጊ ልጆች የዚህ ድርጊት ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ወደ አረብ አገራት ለመሄድ ከተለያዩ የአገራችን ክልሎች ይመጡ የነበሩት ታዳጊ ሴቶችም የእነዚህ ደላሎች ወጥመድ ውስጥ የሚገቡበት አጋጣሚ እንዳለ ይታወቃል፡፡
ልጃገረዶቹ ድንግልናቸውን በሽርፍራፊ ገንዘብ በደላላ ሸጠው ወዳሰቡበት ባህር ማዶ ይሻገራሉ፡፡ ይህ ወደ አረብ አገር ባቀኑ በርካታ ሴት እህቶቻችን ላይ ሲፈፀም የኖረ ሃቅ እንደሆነ ደላሎቹ ያለሀፍረት ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተረፈ በተለያዩ ማባባያዎችና ጉትጐታዎች ከቤታቸው የሚወጡ ከየትምህርት ቤቱ የሚወሰዱ ታዳጊ ሴቶች፤ ድንግልናቸውን ከእነሱ በእድሜ እጅግ ለሚበልጣቸው (አንዳንዴም ለወጣት ሀብታም ነጋዴዎች) በ10ሺዎች በሚቆጠር ብር ይሸጣሉ፡፡ ይህ ተግባር በስፋት የሚከናወንባቸው ሆቴሎችና እንግዳ ማረፊያዎች በተለይም ከአዲስ አበባ ወጣ ባሉ ከተሞች (ዱከም፣ ደብረዘይት፣ ሞጆና ናዝሬት… በብዛት ይጠቀሳሉ) በስፋት ይገኛሉ፡፡ በዚህ “የልጃገረዶች የድንግልና ግብይት” ውስጥ በብዛት ተሣታፊ የሚሆኑት የከተማችን ቱጃር ነጋዴዎችና አልፎ አልፎ ዲያስፖራዎች ናቸው፡፡
ቀይ፣ ጠይም፣ ጠቆር ያለች፣ ረዥም፣ ቀጭን፣ ቁመናዋ ያማረ… እንደ እንግዳው ስሜትና ምርጫ ተፈላጊዋን በደቂቃዎች ውስጥ መኝታ ቤት ድረስ ማምጣት ለደላሎቹ አዳጋች ሥራ አይደለም። ከውጭ አገራት ከሚመጡና ይህንን አይነት አገልግሎት በስፋት ከሚጠይቁ የውጪ ዜጐች መካከል አብዛኛዎቹ አረቦች እንደሆኑ በስራው ላይ የተሰማሩ ደላሎች ይናገራሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሱዳኖችም በብዛት እንደሚመጡ እነዚሁ ደላሎች ገልፀውልኛል። ለረዥም አመታት ውጪ ኖረው ወደ አገራቸው የተመለሱ ዳያስፖራዎች፣ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዲፕሎማቶችና በተለያዩ ስብሰባዎችና ሥራ ሰበብ አሊያም ለጉብኝት የኢትዮጵያን ምድር የሚረግጡ የውጪ ዜጐች ሁሉ የዚህ “አገልግሎት” ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ከተማችን የምታስተናግደው አለማቀፋዊ ስብሰባ በሚኖርበት ወቅት የደላሎቹ ወይም የግብይቱ ኔትወርክ ይጨናነቃል፡፡ የአብዛኛዎቹ “አገልግሎት” ፈላጊዎች ጥያቄም “ቆንጆ የቤት ልጅ እፈልጋለሁ” የሚል ነው፡፡ ጥያቄያቸውን በአግባቡ መመለስ የቻለ ዳጐስ ካለ ክፍያ በተጨማሪ ወፈር ያለ ጉርሻ ማግኘቱም እርግጥ ነው፡፡ “አንዳንድ ጊዜ “የቤት ልጆች” ከገበያ የሚጠፉበት ወቅት አለ። እንዳልኩሽ ስብሰባዎች በሚኖርበት ወቅት ገበያው ስለሚሟሟቅ የቤት ልጆች በጊዜ ያልቃሉ፡፡ ስለዚህ ያለን አማራጭ ብዙም ያልተጐሳቆሉ ሴተኛ አዳሪዎችን እየፈለግን በቤት ልጅ ታርጋ ለገበያ ማቅረብ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ ይባነንበታል፡፡ ሰዎቹ የቤት ልጅና ሴተኛ አዳሪን የሚለዩበት የራሳቸው መንገድ አላቸው ብሎኛል ከገበያው ደላሎች አንዱ፡፡”
በከተማችን የተለያዩ ሥፍራዎች ቦሌ፣ ወሎ ሰፈር፣ ሳር ቤት፣ ሳሚት፣ መስቀል ፍላወርና መገናኛ አካባቢዎች የሚገኙ ቪላ ቤቶች ከነሙሉ የቤት ዕቃዎቻቸው ለቀናት፣ ለሳምንታትና ለወራት ከውጪ የሚመጡ እንግዶችን ይቀበላሉ፡፡ የእነዚህ ቤቶች የጥበቃ ሠራተኞች ከደላሎቹ ጋር በኔትዎርክ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ለሴቶቹ የሚከፈለው ዋጋ እንደ እንግዳው አይነትና እንደ ሴቷ የማስተናገድ ብቃት እንደሚለያይ ደላላው ይናገራል፡፡ ሴቷ እንግዳው በፈለገው መንገድና ሁኔታ ልታስተናግደው (ያፈነገጠ የወሲብ ጥያቄን ያካትታል) ፈቃደኛ ከሆነች ክፍያዋ ከፍ ይላል፡፡ በአብዛኛው ግን ለውጪ አገር ዜጐች የሚቀርቡ ሴቶች ለአንድ ምሽት ከ300-400 ዶላር ክፍያን ይጠይቃሉ፡፡ የቆይታ ጊዜያቸው የሚራዘምና እነሱም የሚመቻቹ ከሆነ ግን ክፍያው እንደየሁኔታው ሊለዋወጥ ይችላል። ለሁለትና ለሶስት ቀናት በነበራቸው ቆይታ እጅግ ተደስተው ከዋናው ክፍያ ጋር ተጨማሪ ቲፕ (በገንዘብም በአይነትም) ለምሳሌ ላፕቶፕ፣ ካሜራ፣ አይፎንና መሰል ውድ ዋጋ ያላቸውን ንብረቶች በስጦታ ሰጥተዋቸው የሚሄዱም አሉ። ከዚህ ባስ ሲልም ወደ አገራቸው እስከ መውሰድ የሚደርሱም ይኖራሉ፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ትላልቅ የመቃሚያ ቤቶችን እንደ እጁ መዳፍ አብጠርጥሮ እንደሚያውቃቸው የሚናገረውና በዚሁ ሴቶችን በመደለል “ቢዝነስ” ላይ የተሰማራው ሌላው የላዳ ታክሲ ሾፌሩ ታዲዮስ፤ በአሁኑ ወቅት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የምትገኝን “የቤት ልጅ” አንጠልጥሎ ለወሲብ ገበያ ማቅረብ ለእሱ እጅግ ቀላል ሥራ እንደሆነ ይናገራል፡፡

“ሴቶቹ የብር ፍቅር ሊገላቸው ነው ዝም ብለሽ እኮ አንዳንድ ትላልቅ የቁንጅና ሣሎኖች፣ ካፌዎችና መዝናኛ ሥፍራዎች ብትሄጂ ሆን ብለው ለጠለፋ የሚወጡ የቤት ልጆችን ማግኘት ትችያለሽ፡፡ በየመቃሚያ ቤቱ ለዚሁ ተግባር የሚዞሩ ሴቶች ነፍ ናቸው፡፡ እኛ ደግሞ ፈላጊና ተፈላጊን ማገናኘት ነው ሥራችን። እነሱ ሲመቻቹ እኛም ይመቸናል” ይላል ታዲዮስ። በከተማዋ ካሉ ትላልቅ ሆቴሎች በአንዱ በእንግዳ ተቀባይነት የሚሰራው ፍፁም (ስሙ የተየቀረ) በሆቴሉ ውስጥ ከሚያርፉ እንግዶች አብዛኛዎቹ የተለያዩ አገር ዜጐች እንደሆኑ በመጠቆም፤ በሥራው ወቅት የሚያጋጥመውና እጅግ ያስመረረው ጉዳይ ግን የእነዚህን እንግዶች “ሴት አስምጣልን” ጥያቄ መመለስ እንደሆነ ይናገራል። የእንግዶቹን ጥያቄ መመለስ ካቃተው እንግዶቹ በአግባቡ እንዳልተስተናገዱ ለሆቴሎቹ ኃላፊዎች ከመናገር ወደ ኋላ እንደማይሉም ይገልፃል፡፡ ይህ እንዳይሆንም በእነ ታዲዮስ ኔትወርክ መታቀፍ ግድ ሆኖበታል፡፡ እንግዶቹ በዚህ ዓይነት መንገድ በከተማችን በሚጧጧፈው ምስጢራዊ የወሲብ ገበያ ውስጥ ተዋናይ ሆነው ቆይተው ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ወቅት ከአበሻ ውብ ቆነጃጅት ጋር የፈፀሙትን የወሲብ ገድል እንደ ፌስ ቡክ፣ ትዊተር ባሉ የማህበረሰብ ድረገፆች ላይ በማስፈር ለዓለም ያስኮመኩማሉ፡፡ ጐበዝ! ወዴት እየተጓዝን ይሆን? ምስጢሩም ቢገለጥ ዝምታውም ቢበቃ አይሻልም ትላላችሁ፡፡ ምንም ቢሆን መወያየቱ አይከፋም እላለሁ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

Ethiopia’s Media Under Siege Amid Escalating Conflict in Amhara

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar