www.maledatimes.com ምድሪቱን በምስጋና ጐርፍ ያጥለቀለቁት የዘማሪት ዘርፌ ዝማሬዎች - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ምድሪቱን በምስጋና ጐርፍ ያጥለቀለቁት የዘማሪት ዘርፌ ዝማሬዎች

By   /   December 15, 2013  /   Comments Off on ምድሪቱን በምስጋና ጐርፍ ያጥለቀለቁት የዘማሪት ዘርፌ ዝማሬዎች

    Print       Email
0 0
Read Time:39 Minute, 40 Second


በዲ/ን ሐብታሙ ዘዲማው ጊዮርጊስ

ያለም ቤዛ ኢየሱስ ነው

የፈወሰኝ ጌታ ነው

መዳን በሌላ የለም

እኔ አምናለሁ ዘላለም

በኦሪቱ ሥርዓት ፍጥረት ስላልዳነ

ለሚሻለው ኪዳን ኢየሱስ ዋስ ሆነ

ከባርነት ቀንበር ተቤዠኝ በደሙ

ያዳነኝ እርሱ ነው ይስማልኝ ዓለሙ

አንዴ ለዘላለም ደሙ ፈሶልኛል

አሁን ያለ ኀጢአት ወዴ ይታይልኛል

ነፍሴን እንዲያነጻ ታርዷል ፋሲካዬ

መርሕ ሆኖ ወደ ክብር አስገባኝ ቤዛዬ

የዘላለም ርስትን የተናዘዘልኝኝ

መቃብርን ቀብሮ በሰማይ ያለልኝ

ሞቶ በመስቀሉ ሰላም ያደረገው

እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው

እንድንበት ዘንድ ተሰጥቶናል ስሙ

አማራጭ የሌለው መዳኛ ነው ደሙ

ሞትን መሞት እንጂ መግደል የተቻለው

ከኢየሱስ በቀር ሌላ ጌታ ማነው?

የመቅደስ አዛዦች እጅ ቢጫንብኝ

ከክርስቶስ ፍቅር መቼም አይበልጥብኝ

በልቤ ያመንሁትን ልመስክረው በአፌ

አልችልም ዝምታ በሞቱ ተርፌ

ይህ ከሰሞኑ ከተለቀቀው የዘማሪት ዘርፌ ከበደ ድንቅ ዝማሬዎች አንዱ ነው፡፡ ዝማሬዎቹን በጥቂቱ ከመቃኘታችን በፊት ግን ወደኋላ መለስ ብለን የዝማሬያችንን መነሻ፣ ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶችና ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ እጅግ ባጭሩ ለመቃኘት እንሞክር፡፡

 

 

የቅዱስ ያሬድ ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያ ከያሬድ መነሣት ጀምሮ በዝማሬ የተባረከች አገር እንደሆነች ሁሉም የሚመሰክረው ሐቅ ነው፡፡ ለብዙ ምእት ዓመታት ቅዱሳት መጻሕፍትን መሰረት አድርገው በግእዝ በተደረሱ የያሬድ ዝማሬዎች የዘለቀው የዝማሬያችን ታሪክ ወደአማርኛ ዝማሬዎች ከተሸጋገረ እነሆ ሰባት ዐሥርት ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ በኢሳይያስ ዓለሜ ሐምሌ 16/1947 በዐማርኛ የታተመችውና መዝሙረ ጸሎት የተሰኘችው የመዝሙር መጽሐፍ ለአማርኛ ዝማሬዎች ፈር ቀዳጅ ናት፡፡ እስከዛሬም የዘለቁ “እንደ ቸርነትህ አቤቱ ማረኝ” ያሉ ዝማሬዎች የኢሳይያስ ዓለሜ ድርሰቶች ናቸው፡፡ ምን ያረጋል? ያን በመዝሙር 51 ላይ የተመሠረተ ድንቅ የንስሐ መዝሙር አንዳንድ ባሕታውያን ጰራቅሊጦስ የሚለውን ስም በተለያዩ የጻድቃንና የመላእክት ስሞች እየተኩ ድርሰቱን አበላሽተዉታል፡፡

“አሁን ትባርክ ዘንድ ማኅበራችን

ፈጥነህ ላክልነ ጰራቅሊጦስን”

በሚሉት ስንኞች አምሳል እንደ ዚቅ “… ፈጥነህ ላክልን ድንግል ማርያምን፣ ቅዱስ ሚካኤልን፣ ቅዱስ ገብርኤልን … በማለት ነው ያበላሹት፡፡ አሁን ጰራቅሊጦስ ከተባለው መንፈስ ቅዱስ በላይ ባራኪ ማን አለና ነው በእርሱ ላይ ሌሎችን መደረብ ያስፈለገው? በእውነቱ ይህ ትልቅ ክሕደትና አምልኮተ ባእድ ነው፡፡

 

ከኢሳይያስ ዓለሜ ለጥቆ በታላቁ ሊቅ በመሪጌታ ፀሐይ ብርሃኑ በአማርኛ የተደረሱትን የያዘውና “መዝሙረ ስብሐት” የተሰኘው ከኖታው ጋር ባስር ዓይነት ድምፅ የተዘጋጀ የመዝሙር መጽሐፍ ይገኛል፡፡ ይህም መጽሐፍ በጥር 3/1961 ዓ.ም. ነው የታተመው፡፡ ከእነዚህ ዝማሬዎች እስከዛሬ ድረስ የዘለቁ አሉ፡፡

“የአብርሃም አምላክ የይሥሐቅም ቤዛ

ወገኖቹን ሁሉ በራሱ ደም ገዛ”  የሚለው ይጠቀሳል፡፡

 

እነዚህ የዚያ ዘመን ወጣቶችና ጕልማሶች የዛሬ አባቶች የደረሷቸውን እነዚያን ዝማሬዎች ተከትሎ በርካታ ዝማሬዎች ሲፈስሱ ኖረዋል፡፡ በተለይም በሃይማኖተ አበውና በሌሎቹም በዚያ ዘመን በነበሩ የወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበሮች ውስጥ አጥንትን የሚያመለምልሙና በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረቱ ዝማሬዎች  ሲዘመሩ ኖረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ብቅ ያለውና የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ ጉዞ ወደኋላ ለመመለስ ሲታገል የኖረው ማኅበረ ቅዱሳን ከተፈጠረ ወዲህ ግን ዝማሬዎቻችን የኋሊት ተመልሰው “ማርያም ወረደች አሸዋ ላሸዋ” “ኧረ እንዴት ነሁ አቦዬ ኧረ እንዴት ነሁ ጻድቁ” አይነትና በባልቴቶች ተረት የተሞሉና መንፈሳዊ ጥማትን በማይቆርጡና አዚምና ድንዛዜን በምእመናን አእምሮ በሚረጩ እንጉርጉሮዎች ተተኩ፡፡ እነሃይማኖተ አበውና ሌሎችም መንፈሳውያን ማኅበራት እየተዳከሙ ማቅ መድረኩን መቆጣጠር ሲጀምር ግን የዝማሬው ጉዞ ተገትቶ በወንጌላውያኑ ወገን ግን ታላቅ የመዝሙር አብዮት ፈነዳ፡፡ ይህ በአንድ በኩል በኦርቶዶክሶች ዘንድ ዝማሬዎቻችን እየወረዱ ሲመጡ በተፈጠረ ክፍተት የተከሠተ አብዮት ነው ማለት ይቻላል፡፡ እነዚያ ዝማሬዎች ብዙ ኦርቶዶክሳውያንን መሳብና ከቤተክርስቲያን ማፍለስ ችለው ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የእነማቅና በእነርሱ መንገድ ለመዘመር የሞከሩ ዘማርያንና ዘማርያት እንጉርጉሮዎች እንኳን በሌላው ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ ኦርቶዶክሳውያንንም መያዝና ማቆየት አልቻሉም፡፡

 

በምርጫ 97 አካባቢ ዘማሪት ምርትነሽ  ይዛው ብቅ ያለችውና “ሰረገላዎችህ የእሳት ናቸው” የተሰኘው የዝማሬ አልበም ግን ለዓመታት ተዳፍነው ለቆዩት የአማርኛ ዝማሬዎች ትንሣኤን በመስጠት በአማርኛ መዝሙር ታሪክ ሌላ አብዮት አስነሣ፡፡ ዳግም የፈነዳውን ይህን የመዝሙር አብዮት ለመቀልበስ ማቅና መሰሎቹ መዝሙሩ ዘፈን ሆነ፣ ያሬዳዊ ዜማን አልጠበቀም፣ ከቤተክርስቲያን ሥርዓት ውጪ ነው ወዘተ. የሚሉ ጩኸቶችን ቢያሰሙም በየጋዜጣውና መጽሔቱ ላይ ቢለፍፉም ሰሚ አላገኙም፤ ምርትነሽ ካወጣችው ዝማሬ በግጥም ይዘትም በዜማ ጣዕምም የወረደ ሥራ ይዞ የመጣውን ዘማሪ ሁላ ሕዝቡ ባለመቀበልና ከገበያ ውጪ በማድረግ አይቀጡ ቅጣት እየቀጣ ከመድረክ እንዲገለል ሲያደርገው ማቅ በተደጋጋሚ የስም ማጥፋት ዘመቻ የከፈተባቸውን የዚህን ዘመን ዘማርያንንና ዘማርያትን ግን በልዩ አክብሮትና አድናቆት በመቀበል ዝማሬዎቻቸውን አድምጦላቸዋል፡፡ በየታክሲው፣ በየካፌውና በየሱቁ የሚደመጠው የእነርሱው ነው፡፡ ማውገዝና ስም ማጥፋት ያንን ሰው በከፍተኛ ሁኔታ ማስተዋወቅ መሆኑን ግን አውጋዦች እስካሁን አልተረዱትም፤ ለወደፊቱም አይረዱትም፡፡

 

ከሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በየክፍለ ሀገሩ በከፍተኛ ሁኔታ እየተደመጡ የሚገኙት የዘርፌ ዝማሬዎች በግጥማቸው ይዘትም ሆነ በዜማቸው ጥዑምነት ተወዳዳሪ አልተገኘላቸውም፡፡ የዘርፌ ዝማሬዎች ታላቅነት የሚመነጨው በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረቱ ከመሆናቸው ነው (ከአንዳንዶቹ ስንኞች አጠገብ የድርሰቱ ምንጭ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመጥቀስ ሞክረናልና ይመልከቱ)፡፡ በአብዛኛው የዘመረችው ቃሉን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ዘመን የማይሽረው፣ ወረት የማያውቀው፣ እርጅና የማያገኘው ሕያው ስለሆነ መቼም ቢሆን አይሰለችም፡፡ ስለዚህ በቃሉ ላይ የተመሠረቱ ዝማሬዎች ዘመን አይሽሬ ናቸው፡፡

 

ኧረ እንዳንተ ያለ ከወዴት አለ

የበደሌን ሸክም ያንከባለለ (ኢሳ. 53፡6)

ውዴ እንዳንተ ያለ ከወዴት አለ

ጻድቅ ጠፍቶ አንድ ስንኳ በሕጉ ፊት ሲመዘን (ሮሜ 3፡11)

አይደለም በደላችን ጽድቃችን መርገም ሲሆን (ኢሳ. 64፡6)

የእግዚአብሔር ልጅ ተገልጠህ የጠላት ምክሩ ፈርሷል (1ዮሐ. 3፡9)

ኢየሱስ ዕርቃን ሆነህ ትውልዱ ምሕረት ለብሷል

ባርያዋን እንድታነግሥ የባሪያን መልክ ይዘሃል (ፊል. 2፡7)

እንባዬን የዓይኔን ጅረት በደምህ ገድበሃል

የልቤ ልብ አንተ ነህ ነፍሷ እኮ ነህ የነፍሴ

መኖሬ ሕልም ነበር ባትሆነኝ እስትንፋሴ

ለጻድቅ ነፍሱን ‘ሚሰጥ በጭንቅ ይገኝ ይሆናል

ገና ደካማ ሳለሁ አንተ ግን ወደኸኛል(ሮሜ 5፡6-8)

በሞትህ እንደታረቅሁ በሕይወትህ እድናለሁ (ሮሜ 5፡9-10)

የዘላለም መሥዋዕቴ ዘላለም አምንሃለሁ

በኪዳን ነው ሕይወቴ በኪዳን ነው ኑሮዬ

ደምህ ነው ማዕተቤ ያጌጥሁበት ድሪዬ

ሞትህን በሚመስል ሞት ካንተ ጋር ብተባበር (ሮሜ 6፡5)

በትንሣኤህ ታድሼ ‘በራለሁ እንደ ንሥር

 

በሌላ በማንምና በምንም ሊከናወን ያልቻው መዳናችን በኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ሥራ መከናወኑን ቃሉን መሠረት በማድረግ የተሰናኘው ይህ የዝማሬ ግጥም ለነፍስ ትልቅ ዕረፍትን የሚያጎናጽፍ ነው፡፡ የስንኞቹ መልእክት ከዜማው ጣዕም ጋር ተዋሕዶ በዘርፌ ስርቅርቅ ድምፅ ሲንቆረቆር ለሚሰማ ሰው ከዚህ ዓለም ለይቶ በተመስጦ ቤዛችን ወደሚገኝባት ወደ ሰማያዊቱ መቅደስ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ ይህን ዝማሬ በተመስጦ እየሰማ ያዳነውን ጌታ ውለታ እያሰበ በፍቅሩ እሳት እየነደደ ጉንጮቹ በእንባ የማይርሱበት ማን አለ?

 

ሌላው የዘርፌ ዝማሬ ሁሉ የረሳውን መንፈስ ቅዱስን ያስታወሰና ለእርሱ ክብርን የሚያመጣው ዝማሬ ነው፡፡ ዓለማየሁ ሞገስ መንፈስ ቅዱስ በቤተክርስቲያናችን ምን ያህል የተረሳ መሆኑን ለማሳየት እንዲህ ብለው ነበር፡፡ “በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ መንፈስ ቅዱስ ችላ የተባለ ወይንም ያልታወቀ ከሦስቱ አካላት የለም፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ (በ1987 ዓ.ም. ነው መጽሐፉ የታተመው) በአዲስ አበባ 56 አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ስም የታነጸ ግን አንድም የለም፡፡ የሥላሴ 2 የእግዚአብሔር አብ 3፣ የመድኀኔዓለም 7፣ ይህም ከማርያም ስለተወለደ እንጂ ማን ዙሮ አይቶት አያ፣ በጠቅላላ በአስማተ ሠለስቱ ሥላሴ አሐዱ አምላክ 10 አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ የተቀረው ግን በማርያም፣ በመላእክት፣ በጻድቃን በሰማዕታት ስም ነው፡፡ ምስኪን የቤተክርስቲያን ጠባቂ መንፈስ ቅዱስ ግን አንድም እንኳ የለውም፡፡ ያመት እንጂ የወር በዓልም የለውም፡፡ ሰዎች ሲደነግጡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ሲሉ በቀር ስሙን ማን አንሥቶት አያ፣ ከእነዚሁም በጣም ካልደነገጡ በስመ አብ ብቻ ብለው ዝም የሚሉ አሉ” ብለው ነበር (ሁሉም ሁሉን ይወቅ ገጽ 140)፡፡

 

ዘርፌ በዝማሬዋ መንፈስ ቅዱስን አንሥታለች፡፡ ከሳሾች ስለማርያም አልተዘመረም፤ ስለቅዱሳን አልተዘመረም ወዘተ እንጂ ስለ መንፈስ ቅዱስ አልተዘመረም ሲሉ ሰምተን አናውቅም፡፡ ዘርፌ ግን በብዙ ስለተረሳው ስለመንፈስ ቅዱስ ስትዘምር መንፈስ ቅዱስን ለዝማሬ አነሣሿ፣ አጽናኟ፣ ልቧን አሳራፊ፣ መካሪዋ፣ እግዚአብሔርን አባ አባት ብላ እንድትጠራው የሚያደርጋት ኀይሏ ነው፡፡ ከዚያም በላይ ብዙ ነገሯ ነው!! ይህን አጽናኝ መንፈስ እንዲህ ስትል ነው የወደሰችው

መንፈስ ቅዱስ አገዘኝ

ዘምሪ ዘምሪ አለኝ

በእሳት ልሳን አጠበኝ (የሐዋ. 2፡3)

እንዳልፈራ አደረገኝ

ስውሩን የሚገልጸው ልቤን የሚያሳርፈው

አጽናኝና  መካሪ መሪዬ ነው መምህሬ

ሲናገረኝ እስማለሁ ሲያበረታኝ እጸናለሁ

አባ አባት ‘ሚያሰኝኝ እርሱ ነው ኀይል የኾነኝ (ሮሜ 8፥14-15)

 

ዘርፌ የቅድስት ማርያምን ታላቅነት የእግዚአብሔር ቃል በሚለው መሠረት አውስታ ዘምራለች፡፡

ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች

መንፈሴም በእርሱ ትደሰታለች

ብላ ዘመረች ድንግል ማርያም

መርጧታልና ለዘላለም

 

ያሬድም ይህንኑ በሉቃስ ወንጌል የተጻፈውን የማርያምን ጸሎት እንደ ወረደ ዜማ ሠርቶለት እንዲዘመር አድርጓል፡፡ “ተዓብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር ትቤ ማርያም ትቤ ማርያም እስመ ገብረ ሊተ ኀይለ ዐቢያተ ወቅዱስ ስሙ … ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች፤ ማርያም አለች፤ ማርያም አለች፤ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራን አድርጓልና ስሙም ቅዱስ ነው …” (ምዕራፍ ዘዘወትር ስብሐተ ነግህ)፡፡ ዘርፌም ያንን መንገድ መከተሏ የያሬድ እውነተኛ ልጅ የሚያሰኛት ነው፡፡ ማርያምን ጠቅሰን ልንዘምር በሚገባን ተገቢ መንገድ ዘምራለች፡፡ ማርያምን አለቅጥ ከፍ ከፍ አድርጋ ወደአምላክነት ደረጃ ከፍ ሳታደርግ መዘመሯ የሚያስመሰግናት ነው፡፡ ስለመላእክት ስለቅዱሳንን ጠቅሰን መዘመር ቢያስፈልግ በዚሁ መንገድ በተለይም በሦስተኛ መደብ “እርሷ እርሱ” እያለን ያለፈውን በመመስከር እንጂ በሁለተኛ መደብ “አንተ አንቺ” እያልንና ከእነርሱ ጋር እንደምንነጋር አድርገንና አምልኮ አከል ውዳሴና ልምና ለፍጡራን በማቅረብ መዘመር “ዘይቤ” ቢሆንም ከአምልኮት ጋር ሲገናኝ አምልኮተ ባዕድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ የመዝሙር ደራሲዎች ይህን ትክክለኛ መንገድ ተከተሉ፡፡

 

ሌላው ዝማሬ እንዲህ የሚለው ነው፤

ያለም ቤዛ ኢየሱስ ነው

የፈወሰኝ ጌታ ነው

መዳን በሌላ የለም (የሐዋ. 4፥12)

እኔ አምናለሁ ዘላለም

በኦሪቱ ሥርዓት ፍጥረት ስላልዳነ

ለሚሻለው ኪዳን ኢየሱስ ዋስ ሆነ (ዕብ. 7፡22)

ከባርነት ቀንበር ተቤዠኝ በደሙ

ያዳነኝ እርሱ ነው ይስማልኝ ዓለሙ

አንዴ ለዘላለም ደሙ ፈሶልኛል (ዕብ. 9፡28፤ 10፥10፡14)

አሁን ያለ ኀጢአት ወዴ ይታይልኛል (ዕብ. 9፥24፡28)

ነፍሴን እንዲያነጻ ታርዷል ፋሲካዬ (1ቆሮ. 5፡7)

መርሕ ሆኖ ወደ ክብር አስገባኝ ቤዛዬ (ዕብ. 2፡10)

የዘላለም ርስትን የተናዘዘልኝ

መቃብርን ቀብሮ በሰማይ ያለልኝ

ሞቶ በመስቀሉ ሰላም ያደረገው

እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው (ዕብ. 9፡15፤ 12፡24)

እንድንበት ዘንድ ተሰጥቶናል ስሙ (የሐዋ. 4፡12)

አማራጭ የሌለው መዳኛ ነው ደሙ

ሞትን መሞት እንጂ መግደል የተቻለው (2ጢሞ. 1፡11-12)

ከኢየሱስ በቀር ሌላ ጌታ ማነው? (1ቆሮ. 12፡3)

የመቅደስ አዛዦች እጅ ቢጫንብኝ

ከክርስቶስ ፍቅር መቼም አይበልጥብኝ

በልቤ ያመንሁትን ልመስክረው በአፌ

አልችልም ዝምታ በሞቱ ተርፌ

 

ዘርፌ በመንፈስ ቅዱስ የጀገነች ዘማሪት በመሆኗ “ኢየሱስ” ብሎ መዘመር እንደመናፍቅ በሚያስቆጥርበት ቤተክርስቲያን ውስጥ ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ በመሆን መዳን በሌላ የለም ብላ በመዘመሯ እውነተኛ ምስክር ሆናለች፡፡ እንዳለችው “የመቅደስ አዛዦች እጅ” ቢጫንባት ከክርስቶስ ፍቅር መቼም አይበልጥባትም፡፡ በልቧ ያመነችውን በአፏ ለመመስከር የደፈረችው በክርስቶስ ሞት የዳነች መሆኗን ስለተገነዘበችና ዝም ማለት ስለማትችል ነው፡፡ ጥንትም ሆነ ዛሬ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ስሙን ጠርተን አዳኝነቱን እንዳንመሰክር በልዩ ልዩ መንገድ ያስፈራሩናል፡፡ አንዳንዶቻችን ፈርተን ያመነውን ሳንመሰክር እንቀራለን፡፡ ሐዋርያት በዚህ ስም እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ ዝተን እናስፈራራቸው ብለው “በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው። እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው።” (የሐዋርያት ሥራ 4፥18-20)፡፡ የዘርፌም የዚህ ዝማሬ የመጨረሻ ስንኞች ይህን ታሪክ ያስታውሱናል፡፡ በእርግጥም በክርስቶስ ሞት መዳንሽን ከተረዳሽ ይህን እውነት አለመመስከር አትችይምና እኅታችን ሆይ እውነተኛ ምስክርነትሽን ግፊበት፡፡ ደግሞም በሌላው ዝማሬሽ፥

 

አንድ ጌታ ኢየሱስ አለኝ ክርስቶስ አለኝ (1ቆሮ. 8፡6)

ሰልፌን ሰልፉ ያደረገልኝ የሚዋጋልኝ

የማይፈታ ማተቤ ነው ደሙ

ከፍ ላ’ርገው ዐርማዬ ነው ስሙ

በማለት እንደገለጽሽው እርሱ ስላንቺ ይዋጋልና ጠንክሪ፡፡

 

ሌላው ዝማሬ ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስን ሊቀ ካህናትነት የሚመሰክረው ዝማሬ ነው፡፡ አዝማቹ እንዲህ የሚል ነው፡፡

ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ሊቀ ካህናት (ዕብ. 4፡14፤ 7፥26)

የአዲስ ኪዳን በግ ንጹሕ መሥዋዕት (ዮሐ. 1፡29)

መሥዋዕትም አቅራቢ ተቀባይም ሆነ

በደሙ ቤዛነት ፍጥረት ሁሉ ዳነ

 

ይህም ዝማሬ የክርስቶስን ሊቀ ካህናትነት መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ የተደረሰ በመሆኑ ዘመን አይሽሬ እውነት ነው፡፡ ሦስተኛው ስንኝ “መሥዋዕትም አቅራቢ ተቀባይም ሆነ” የሚለው “መሥዋዕት አቅራቢ ሊቀ ካህናት ሆነ” መባል ነበረበት የሚል እምነት አለን፡፡ እርግጥ “ለሊሁ ሠዋዒ ወለሊሁ ተሠዋዒ ወለሊሁ ተወካፌ መሥዋዕት ምስለ አብ ወመንፈስ ቅዱስ – እርሱ መሥዋዕት የሚያቀርብ ሊቀካህናት ነው፤ የሚሠዋ መሥዋዕትም ነው፡፡ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕቱን የሚቀበል ነው” የሚል ንባብ በአበው ሃይማኖት ውስጥ አለ፡፡ አበው ይህን ያሉበት ምክንያት ሥጋ የሆነው ቃል ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል መኾኑን ለማመልከት ነው፡፡ ይህ በራሱ ትክክል ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ የሠራውን የእርሱን ሥራ ለይቶ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ ሰው መሆን፣ መሥዋዕት መሆንና መሥዋዕት ማቅረብ በተለየ አካሉ ያከናወነው የእርሱ የብቻው የሊቀ ካህናትነቱ ግብር ነው፡፡ እርሱ መሥዋዕትና መሥዋዕቱን አቅራቢ ሊቀካህናት ነው፤ ያቀረበው ደግሞ ለእግዚአብሔር አብ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ያረጋግጥልናል፡፡ ለእግዚአብሔር አቀረበ ስለተባለ ክርስቶስ ዝቅ አይልም፤ ተቀባይም ሆነ ስለተባለ ደግሞ ከፍ አይልም፤ ከዚያ ይልቅ የእግዚአብሔር ሦስትነት በአንድነቱ ይጠቀለላል፡፡ ስለዚህ ይህ ወደሰባልዮስ ትምህርት ያዘነበለ አገላለጥ ነውና ሊታረም ይገባል እንላለን፡፡

 

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ።” (ኤፌ. 5፥2)

እንዲሁም “ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?” (ዕብ. 9፥14) ሐዋርያው ጳውሎስ በእነዚህ ክፍሎች ክርስቶስ ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው ለእግዚአብሔር ነው ይላል፡፡ እውነት ነው፡፡ አሊያ በምስጢረ ሥላሴ ላይ ተፋልሶ ይከተላል፡፡ አብና መንፈስ ቅዱስም እንደ ወልድ መሥዋዕት ሆነዋል፣ መሥዋዕት አቅርበዋል ልንል ነው፡፡ ስለዚህ የግጥሙ ደራሲ “መሥዋዕትም አቅራቢ ተቀባይም ሆነ” ከሚለው ይልቅ “መሥዋዕት አቅራቢ ሊቀ ካህናት ሆነ” ቢለው ኖሮ ምስጢሩ እንዴት ያረካ ነበር!! በተረፈ ግን ሌሎቹ ስንኞች ሁሉ ኃጢአት ላደከመው ሁሉ ዕረፍትን የሚሰጥ ታላቅ ዝማሬ ነው፡፡ ስለዚህ አዝማቹ በዚህ መንገድ ቢታረምስ

 

ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ሊቀ ካህናት

የአዲስ ኪዳን በግ ንጹሕ መሥዋዕት

መሥዋዕት አቅራቢ ሊቀካህናት ሆነ (ዕብ. 9፡11-12)

በደሙ ቤዛነት ፍጥረት ሁሉ ዳነ

የበግ የዋኖሱን – ብዙ ደም ቢያፈሱ (ዕብ. 10፡4)

የብሉይ ካህናት – ቢቆሙ በእርሱ ፊት

የሞት አገልግሎት – ሆኖባቸው ድግምት (2ቆሮ. 3፡7)

መሢሑን ናፈቁ – አዳኙን ዐወቁ

ክርክር የለኝም  – አላጕረመርምም

አመሰግናለሁ – በደሙ ድኛለሁ

እንደ መልከ ጼዴቅ – የነገሠው በጽድቅ

ታላቅ ናት ክህነቱ – ዘላለም መንግሥቱ (ዕብ. 5፡9-10፤ 6፥20)

መድኀኒት ተገልጧል – እኛም አይተነዋል

ሞታችን ተገድሏል – በጸጋው ድነናል

በይሥሐቅ ፈንታ – የተሠዋው ጌታ

እንደ በግ ታረደ – ሁሉንም ወደደ

ስንሠቃይ አይቶ – ክብሩን ሁሉ ትቶ

በሥቃይ ደቀቀ – ሊያነሣን ወደደ

ሲኦል ተብዝብዟል – ሥልጣኑ ተይዟል

ለተቤዠን ንጉሥ – ምስጋናችን ይድረስ

 

በዚህ የመዝሙር አልበም ውስጥ  የምናገኘው ሌላ ድንቅ ዝማሬ ይኸው፥

እኔስ ለአምላኬ እኔስ ለእግዚአብሔር

ምስጋና አለኝ ምስጋና አለኝ

ውለታው ስለበዛብኝ

አሳዳሪዬ መጋቢዬ የነፍሴን ጩኸት የምትሰማ

ከአንተ ጋር ስኖር በዘመኔ ክፉ ትዝታ የለኝ እኔ

ስለእርሱ የማወራው ብዙ ነገር አለኝ

ዘመንና ዕድሜ ጤና ከተሰጠኝ

ከግብጽ ያወጣኝ ከባርነት ባሕርን ከፍሎ በታምራት

መንገዴን መርቶ ያሳለፈኝ ከመስቀሉ ሥር ያሳረፈኝ

ስለእርሱ የማወራው ብዙ ነገር አለኝ

ዘመንና ዕድሜ ጤና ከተሰጠኝ

አለቅባቱ በላዬ ላይ ከፍ የሚያደርገኝ ወደሰማይ

ለታረደው በግ ምስክር ነኝ ቅኔ በገና ላስታጠቀኝ

ስለእርሱ የማወራው ብዙ ነገር አለኝ

ዘመንና ዕድሜ ጤና ከተሰጠኝ

እየባረክሁህ ልኑርልህ እየዘመርሁኝ ልሙትልህ

የማልጠቅመውን ከጠራኸኝ ላንተ ብቻ ነው የሠራኸኝ

ስለእርሱ የማወራው ብዙ ነገር አለኝ

ዘመንና እድሜ ጤና ከተሰጠኝ

 

 

በዚህ መዝሙር ውስጥ ጌታ ያደረገላትን ዋና ዋና ነገር ጠቃቅሳ አዳኟን ስትወድሰው ደጋግማ እንዳለችው በተለይም በመጨረሾቹ ስንኞች ውስጥ እየባረከችው ለመኖር እየዘመረችለት ለመሞት መወሰኗ ያለምክንያት አይደለም፡፡ የማትጠቅመውን እርሷን የጠራት ለእርሱ ብቻ እንድትኖር ለእርሱ ብቻ እንድትዘምር መሆኑን ስለተገነዘበች ነው፡፡ ስለእርሱ ብዙ እንድትዘምርና እንድታወራ ረጅም እድሜና ጤና ይስጣት እንላለን፡፡ ከዚህ የመዝሙር አልበም ጀርባ ያሉት ገጣሚዎችና ዜማ ደራሲዎቹም ሁሉ እጅግ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡  እግዚአብሔር የቃሉን ምስጢር ከዚህ በበለጠ ይግለጥላቸው፡፡ ነፍስን የሚያረካ ዜማም ይስጣቸው፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on December 15, 2013
  • By:
  • Last Modified: December 15, 2013 @ 3:39 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar