www.maledatimes.com በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርት (አንድነት) በሰላማዊ ትግልና ባህሪያቱ ክፍል አራት በአቶ ግርማ ሞገስ በስካይፕ የሚሰጠው ስልጠና ተጠናቋል። ዝርዝሩ ዝቅ ብሎ ቀርቧል። - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርት (አንድነት) በሰላማዊ ትግልና ባህሪያቱ ክፍል አራት በአቶ ግርማ ሞገስ በስካይፕ የሚሰጠው ስልጠና ተጠናቋል። ዝርዝሩ ዝቅ ብሎ ቀርቧል።

By   /   December 15, 2013  /   Comments Off on በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርት (አንድነት) በሰላማዊ ትግልና ባህሪያቱ ክፍል አራት በአቶ ግርማ ሞገስ በስካይፕ የሚሰጠው ስልጠና ተጠናቋል። ዝርዝሩ ዝቅ ብሎ ቀርቧል።

    Print       Email
0 0
Read Time:80 Minute, 34 Second

ሰላማዊ ትግል እና ባህሪያቱ

ስልጠና ክፍል አራት፥ ሰላማዊ ትግል፣ ምርጫ እና መፈንቅለ-መንግስት
ቅዳሜ ታህሳስ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. [December 14, 2013]
የስልጠና ክፍል አራት ግብ የሚከተሉትን ማጥናት ነው፥ (1ኛ) ስለ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምንነት እና ሰላማዊ
የፖለቲካ ትግል ለውጥ የሚያመጣባቸው 3 መንገዶች፣ (2ኛ) በዴሞክራሲ አገሮች የሚደረጉ ምርጫዎች ግባቸው
እና ፎርሙላቸው ምን እንደሆነ፣ (3ኛ) አምባገነን መንግስቶች የሚያደርጉዋቸው ምርጫዎች ግባቸው እና
ፎርሙላቸው ምን እንደሆነ፣ (4ኛ) አምባገነን መንግስቶች በሚጠራቸው ምርጫዎች ተቃዋሚ የምርጫ ፓርቲዎች
ምን ማድረግ እንዳለባቸው እና በመጨረሻ (5ኛ) በህዝብ የተመረጠን መንግስት ከስልጣን ለማውረድ የሚፈጸምን
መፈንቅለ-መንግስት እንዴት በሰላማዊ ትግል መከላከል እና ማስወገድ እንደሚቻል ማጥናት።

(1ኛ) ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለውጥ የሚያመጣባቸው 3 መንገዶች፣

አምባገነኖች ስልጣን ላይ ለመቆየት ህጋዊነት፣ የህዝብ ድጋፍ እና ትብብር፣ የአገር ተፈጥሮ እና የኢኮኖሚ ሃብት
ባለቤትነት የተባሉትን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች መቆጣጠር አለባቸው። የፖለቲካ ኃይል ምንጮች የሚኖሩት
ሰማይ ውስጥ ወይንም አምባገነኖች ደም ውስጥ ሳይሆን ባለቤታቸው ከሆነው ህዝብ ጋር እንደሆነ በስልጣና ክፍል
ሶስት አጥንተናል። እርግጥ አምባገነኖች በእነዚህ የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ላይ ያላቸውን ቁጥጥር የሚያገኙት
ህዝብ ፈቅዶላቸው ወይንም ፈርቶዋቸው ወይንም የተወሰነው ህዝብ ፈቅዶላቸው የቀረው ህዝብ ደግሞ ፈርቷቸው
ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይኽ የእነዚህ የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ባለቤት እራሱ ህዝብ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ለዚህም ነው የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ማለትም የመንግስት ስልጣን ምንጭ ወይንም ባለቤት ህዝብ ነው
የሚባለው። ህዝብ የፖለቲካ ነፃነቱን የሚነጠቀውም ይኽን የፖለቲካ (የመንግስት) ስልጣን ባለቤትነቱን በኃይል
በአምባገነኖች ሲነጠቅ ነው። ነፃ ሆኖ የተወለደ የሰው ዘር ለምን ነፃነቱን ለጥቂት አምባገነን ገዢዎች አስረክቦ
ካለነፃነት መገዛትን ይቀበላል? የሚለውን ጥንታዊ የፖለቲካ ፈላስፎች እና ተመራማሪዎች ጥያቄ አንስተን በክፍል
ሶስት ማጥናታችን ይታወሳል።

ሰላማዊ ትግል ህዝብ እራሱን በራሱ ከአምባገነኖች ነፃ የሚያወጣበት የትግል ዘዴ ነው። ህዝብ የነፃነት ሰላማዊ
ትግሉን የሚያራምደው እራሱ በራሱ ሊፈጽማቸው በሚችላቸው (1) ተቃውሞ እና ማግባባት፣ (2) ትብብር
መንፈግ እና (3) ጣልቃ መግባት በተባሉት በሶስት አብይ ክፍሎች ውስጥ በሚካተቱ ቁጥራቸው 200 ግድም
በሚደርሱ የሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች ነው። ለዚህም ነው ሰላማዊ ትግል ህዝብን የራሱ ነፃ አውጭ
ያደርገዋል የሚባለው።

የስልጣን ምንጭ ባለቤት እራሱ ህዝብ እንደሆነ ከፍ ብለን አስተውለናል። ስለዚህ የስልጣን ምንጭ ባለቤት እራሱ
ህዝብ በመሆኑ በቀላሉ ለገዢዎቹ የለገሰውን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች (ስልጣን) በሰላማዊ ትግል በመንፈግ
እራሱን ነፃ ያወጣል እንጂ እርስ በርስ የሚያገዳድሉትን ጠብ-ምንጃ፣ ቦንብ፣ ታንክ፣ መድፍ እና የመሳሰሉትን የርስ
በርስ ጦርነት ማራመጃ መሳሪያዎች አይጠቀመም። የሰላም ትግል ማራመጃ መሳሪያዎችን በስልጠና ክፍል ሶስት
አጥንተናል። ስለዚህ ከ200 ውስጥ ትቂቱን ሰላማዊ ትግል ማራማጀ መሳሪያዎች በመጠቀም ብቻ ህዝብ
በፈቃደኛነት ወይንም በፍራቻ ለአምባገነኖች የለገሰውን ህጋዊነት፣ ድጋፍ እና ትብብር፣ የአገር ተፈጥሮ እና
ኢኮኖሚ ሃብት የመሳሰሉትን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች በመንፈግ በራሱ ቁጥጥር ስር ሊያደርጋቸው ይችላል።
የፖለቲካ ኃይል ምንጮችን በመቆጣጠር የመንግስትን ኃይል መቆጣጠር ይችላል። ከሞቆጣጠር አልፎ ሙሉ
የተደራጀ ህዝባዊ እምቢተኛነት በመፈጸም ህዝብ የአምባገነን መንግስትን የፖለቲካ ኃይል (አቅም) ከምንጩ
ማድረቅ እንደሚችል ግልጽ ነው።

ማንኛውም አምባገነን መንግስት የአገር ሃብት እና የኢኮኖሚ ባለቤትነት የመሳሰሉት የፖለቲካ ኃይል ምንጮች
ከደረቁበት ደግፈውት የቆሙ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች ማለትም ሲቪል ሰርቫንት (ቢሮክራሲው)፣
ፖሊስ፣ የጦር ኃይል፣ የሚዲያ ሰራተኞች፣ ካድሪዎች፣ ወ.ዘ.ተ. ለሚለግሱት ድጋፍ እንደቀድሞው ክፍያ ማድረግ (ድሞዝ መክፈል) ይሳነዋል። የከፈለ ያዛል የሚለው አባባል በፖለቲካም ይሰራል። ስለዚህ ደሞዝ መክፈል
ለማይችል መንግስት የሚታዘዝ አይኖርም። ይኽን ለማድረግ ደግሞ ህዝብ ቦንብ እና ታንክ መጠቀም ቀርቶ ክፉ
ቃል መጠቀም እንኳን እንደማያስፈልገው ግልጽ ነው።

የሰላማዊ ትግላችን ግብ ጉለበተኛውን አምባገነን ደሞዝ ከፋይ በሰላማዊ ትግል ማስወገድ እና ሃቀኛውን የአገር
ሃብት እና ኢኮኖሚ ባለቤት (ሃቀኛ ደሞዝ ከፋይ)ማድረግ ነው። ሃቀኛውን የፌዴራል እና የክልሎች ፖለቲካ ኃይል
ምንጮች ባለቤት የፌዴራል መንግስት እና የክልል መንግስቶች ስልጣን ባለቤት ለማድረግ ነው። በኢትዮጵያ 9
ያህል የክልል መንግስቶች ያሉ ይመስለኛል። የሆነው ሆኖ ሰላማዊ ትግል ለውጥ እንዴት እንደሚያመጣ ማለትም
ሰላማዊ ትግል ለውጥ የሚያመጣባቸውን መንገዶች (Ways/Mechanics) ማጥናት ያስፈልጋል።

ሰላማዊ ትግል ለውጥ የሚያመጣው በሶስት መንገዶች ነው። አንደኛው መንገድ የሰውን እምነት፣ አስተሳሰብ፣
ዝንባሌ፣ ፖሊሲ፣ በሰላማዊ መንገድ በመቀየር/መለወጥ (Peaceful conversion) ነው። ይኽ ለውጥ ማምጫ
መንገድ በአብዛኛው ተቃውሞ እና ማግባባት በተባለው የሰላም ትግል ማራመጃ አብይ ክፍል ውስጥ የተዘረዘሩትን
የሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች ይጠቀማል። ይኽ ለውጥ ማምጫ መንገድ በተለያዩ ምክንያቶች ቀደም
ብለው የመንግስት ደጋፊ የሆኑ እና በምርጫም ድምጻቸውን ይለግሱት የነበሩ ሰዎችን፣ ባለስልጣኖችን፣ የመንግስት
ሰራተኞችን (ቢሮክራሲው፣ ፖሊስ እና የቀረው መለዮ ለባሽ)፣ የኢንዱስትሪ ሰራተኛውን፣ ተማሪውን፣ ምሁሩ፣
ነጋዴው እና ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል አስተሳሰብ በመለወጥ ሰላማዊ ትግሉን እንዲቀላቀሉ ያደርጋል።
በውጤቱም የሰላማዊ ትግሉን አቅም ይገነባል ይኽ መንገድ። የሰላማዊ ትግል አቅም መገንባት ደግሞ የመንግስትን
የፖለቲካ ኃይል (አቅም) ለመቆጣጠር፣ በምርጫ ለማሸነፍም፣ ከምርጫ በኋላ ድምጽ ቢሰረቅ የህዝብ ድምጽ
ለማስከበር አስፈላጊነቱ ግልጽ ነው። ይኼን ለውጥ ማምጫ መንገድ የአሜሪካው ማርቲን ሉተር ኪንግ በአሜሪካ
እኩልነት ለማምጣት ተጠቅሞበታል። ጋንዲ በህንድ ሰላማዊ ትግሉን ለመገንባት ተጠቅሞበታል። የምስራቅ
አውሮፓ አገሮች እና ብራዚልን የመሳሰሉ የላቲን አሜሪካ አገሮችም የሰላማዊ ትግላቸውን አቅም ለመገንባት
ተጠቅመውበታል።
ሁለተኛው ለውጥ ማምጫ መንገድ መቻቻል (accommodation) የተባለው ነው። በየአራት እና አምስት አመቶች
የሚካሄድ ምርጫ በዚህ በሁለተኛው የሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጫ መንገድ ውስጥ ይካተታል። ምርጫ
በኢትዮጵያም ህገ መንግስት ተካቷል። አምባገነኖች የሚጠሩት ምርጫ ግን ዴሞክራሲ አገሮች ከሚያካሂዱት
ምርጫ ይለያል። አምባገነኖች ምርጫን የሚፈልጉት ህጋዊነትን ለማግኘት ብቻ ነው። ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ
መካከል እና በምርጫ ሰሞን የመጀመሪያውን ለውጥ ማምጫ መንገድ በመጠቀም ያላቸውን የህዝብ ድጋፍ ማሳደግ
አለባቸው። የህዝብ ድጋፍ መጠን የፖለቲካ ኃይልን (አቅምን) መጠን ይወስናል። በሰላማዊ ትግል ደግሞ ድል
አድራጊነትን የሚወስነው የህዝብ ድጋፍ ቁጥር እና ዝግጅት ናቸው።
ሶስተኛው ለውጥ ማምጫ መንገድ ደግሞ አንደኛውን፣ ሁለተኛውን እና ሶስተኛውን አብይ የሰላም ትግል
መሳሪያዎች እንደ አስፈላጊነታቸው እና ጠቃሚነታቸው አቀናብሮ በመጠቀም በአምባገነን መንግስት ላይ ሰላማዊ
ቅጣት ይፈጽማል። ይኽ መንገድ የአምባገነን መንግስት የፖለቲካ ኃይል ምንጮቹ ደርቀው የድጋፍ ምሶሶዎቹ
በራሳቸው መቆም ተስኗቸው እንዲደረመሱ እና የተሸከሙት መንግስት ወድቆ እንዲፈረካከስ ያደርጋል። ሶስቱም
ለውጥ ማምጫ መንገዶች ተጋጋዦች ናቸው። ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት።
ምሳሌ 1፥ ከ1997 ቀደም ብሎ ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ በሰርቢያ በተደረገው ሰላማዊ ትግል ተቃዋሚ
የምርጫ ፓርቲዎች ከአንደኛው ለውጥ ማምጫ መንገድ እስከ ሶስተኛው ለውጥ ማምጫ መንገድ ተጠቅመዋል።
በዚህን ጊዜ በሰርቢያ ሁለት ነፃ ያልነበሩ ምርጫዎች ተካሂደዋል። የመጀመሪያው ምርጫ እንደ ኢትዮጵያ ሳይሆን
እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1997 በስልጣን ላይ የነበረው የሞልሶቪች መንግስት የጠራው ምርጫ ሲሆን በዚያ
ምርጫ ተቃዋሚዎች ብዙም ህብረት አልነበራቸው አልፎም በገጠር ያገኙትን ድምጽ የአምባገነኑ ሞሊሶቪች
መንግስት ነጠቃቸው። በተወሰኑ ከተሞች ያገኙዋቸውን ድሎች መስረቅ ስላቃታው አሸናፊነታቸውን ተቀበለ።
ለአጭር ጊዜ ድምጽ በመሰረቁ መጣራት አለበት እና ፓርላማ አንገባም የሚሉ ጫጫታዎች ካሰሙ በኋላ ሰላማዊ
ትግል አቅማቸውን ሳይስመቱ እና ከምርጫው ያገኙትን ፖለቲካዊ እና ድርጅታዊ ድል ሳያባክኑ ታቃዋሚዎች
ፓርላማ ገቡ። የሆነው ሆኖ ከ1997 ዓ.ም. ቀደም ብለው ጀምረው ተቃዋሚዎች የመጀመሪያውን ለውጥ ማምጫ
መንገድ በመጠቀም የሞልሶቪችን መንግስት አጋልጠዋል። የህዝብ ድጋፍ መሰረታቸውን አሳድገዋል።
የመራጫቸውን ህዝብ ቁጥር አሳድገዋል። ፓርላማ ከገቡም በኋላ በ2000 ዓ.ም. የሚደረገው ምርጫ እስኪደርስ
ድረስ ባለው ረጅም ጊዜ 16 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመለስተኛ ፕሮግራም ለመስማማት እና ህብረት ለመፍጠርም
ችለዋል። ይኽን ረጅም ጊዜ በመጠቀም ተቃዋሚዎች በከተማም ሆነ በአብዛኛው ገጠር ድምጽ እንዳይሰረቅ
ለማድረግ የሚያስችል ቀጣይነት ያለው ሰላማዊ ትግል ማድረግ የሚያስችል ዝግጅት አድርገዋል። ከዝግጅቶቹ
ውስጥ ጥቂቶቹ ህዝብ በብዛት ወጥቶ እንዲመርጥ እና ድምጹን ከስርቆት እንዲጠብቅ ማሰልጠን፣ በሰላማዊ ትግል ድስፕሊን የታነጹ በየምርጫ ጣቢያው የሚሰማሩ የምርጫ ታዛቢዎች ማሰልጠን እና ተፎካካሪ እጩዎች
ማዘጋጀት፣ በተጠራ ጊዜ ለጥሪው ቀጣይነት ያለው ተገቢ ምላሽ መስጠት የሚችል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላት
ያሉት የሰላም ትግል ሰራዊት መገንባት እና የመሳሰሉት ነበሩ። ምርጫውን ተከትሎ የአምባገነኑን መንግስት ፍጡር
የሆነው ምርጫ ቦርድ ፈጣሪውን አምባገነን መንግስት የምርጫው አሸናፊ አድርጎ ሲያውጅ የ16 ተቃዋሚ
ፓርቲዎች ህብረት ህዝብ ድምጹን እንዲያስከብር ሶስተኛውን የሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጫ መንገድ ማለትም
ስኬታማ የህዝብ እምቢተኛነት ሰላማዊ ትግል ጠራ። ተቃዋሚው ቀደም ብሎ የተለያዩ ሁኔታዎችን (Scenarios)
ከግንዛቤ አስገብቶ በእያንዳንዱ ሁኔታ (Scenario) ላይ “ይህ ቢሆንስ? ባይሆንስ? (What if)” የሚሉ ሰፊ ጥናቶች
አድርጎ ስለነበር ለአምባገነኑ ሞሊሶቪች መንግስት የሚያመቹ ቀዳዳዎችን በሙሉ ለመድፈን የሚያስችሉ ዝግጅቶች
አድርጎ ስለነበር ካለአንዳች መደናገር ህዝባዊ እምቢተኛነትን ጠርቶ መራ። አምባገነኑ ሞሊሶቪች በፖለቲካ ኃይል
ምንጮች ላይ የነበረውን ቁጥጥር እንዲለቅ ተገደደ። ለሚያገለግሉት የመንግስት ሰራተኞች (መለዮ ለባሹን
ጨምሮ) ደሞዝ መክፈል ተሳነው። መለዮ ለባሹ ከዳው። የሞሊሶቪች አምባገነን መንግስት በሰላም የመንግስት
ስልጣን ከማስረከብ የተሻለ አማራጭ እንደሌለው በአይኑ እንዲያ ተደረገ በተቀናበረ ህዝባዊ እምቢተኛነት። በዚህ
አይነት ነበር የ16ቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሰርቢያን ህዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ የመንግስት ስልጣን ባለቤት
ማድረግ የቻለው።
ስለዚህ በ2000 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ የሰርቢያ ተቃዋሚ ምርጫ ፓርቲዎች በህብረት ለሁለተኛ ጊዜ የሰላማዊ
ትግል ለውጥ ማምጫን መንገድ በመጠቀም በምርጫ 1997 ያገኙትን ፖለቲካዊ እና ድርጅታዊ ድል ወደ ከፍተኛ
ደረጃ ማለትም ህዝባቸውን የመንግስት ስልጣን ባለቤት መሆን ከቻለበት ደረጃ አድርሰውታል። ከዚያ ቀደም
ብለው በተስማሙበት ውል መሰረት ሶስት ወይንም አራት አመቶች 16ቱ ፓርቲዎች በህብረት ህዝባቸውን
ካስተዳደሩ በኋላ በሰርቢያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃ ምርጫ ተደረገ። አብላጫ የህዝብ ድምጽ ያገኘው ፓርቲ
የመንግስት ስልጣን ገዢ ፓርቲ ሆነ። የቀሩት ፓርቲዎች ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኑ። በዚህ አይነት የዴሞክራሲ ስርዓት
ግንባታ በሰርቢያ ጉዞውን ቀጠለ።
ምሳሌ 2፥ የግብጽ ወጣቶች የፈጸሙትን እንመልከት። የመጀመሪያውን እና ሶስተኛውን የለውጣ ማምጫ መንገዶች
ተጠቅመው አምባገነኑን የሙባረክ መንግስት ከስልጣን አወረዱ። ከዚያ ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር የሰላማዊ
ትግል ሁለተኛውን ለውጥ ማምጫ መንገድ ተጠቀሙ። ሁለተኛውን የለውጥ ማምጫ መንገድ ሲጠቀሙ ግን ሶስት
ዴሞክራቶች ለፕሬዘዳንትነት ስለተፎካከሩ የዴሞክራሲ ኃይሎች ለዴሞክራሲ ሽግግር የሰጡትን 25 በመቶ ድምጽ
ለሶስት ተካፈሉት። ስለዚኽ እያንዳንዱ ዴሞክራት እጩ ያገኘው ድምጽ የሙዝሊም ብራዘርሁዱ ብቸኛ
ፕረዜዳንታዊ እጩ ሞርሲ ለብቻው ካገኘው 12 ከመቶ ድምጽ ያነሰ ሆነ። ስለዚህ የሙዝሊም ብራዘርሁድ እጩ
አሸነፎ የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ሆነ። ይሁን እንጂ ሞሪስ በስልጣን ላይ ሳለ ይበልጥ አምባገነን እየሆነ በመሄዱ የግብጽ
ወጣቶች ለሁለተኛ ጊዜ አንደኛውን እና ሶስተኛውን የሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጫ መንገዶች ተጠቅመው
ስልጣን እንዲለቅ እንዳደረጉት እናስታውሳለን። ሶስቱ ዴሞክራት ፕረዘዳንታዊ እጩዎች የግል ፓርቲያቸውን ግለኛ
ፍላጎት ወደጎን አድርገው ህዝባቸውን ወደ ዴሞክራሲ ማሸጋገርን አስቀድመው በምርጫው አንዳቸው ብቻ
ከሞርሲ ጋር መፎካከር ነበረባቸው። ታላላቅ ሰዎች የሚወስዱትን ያን አይነት ምርጫ የግብጽ ዴሞክራት እጩዎች
ማድረግ ስለተሳናቸው ይኸው ዛሬ ግብጽ ወደ ዴሞክራሲ የሚያደርሰውን ረጅሙን መንገድ ይዛለች።
(2ኛ) እንደ አሜሪካ እና እንግሊዝ አይነቶቹ ዴሞክራሲ አገሮች የሚደረጉዋቸው ምርጫዎች ግባቸው እና
ፎርሙላቸው ምንድን ነው?
የዴሞክራሲ አገሮች ምርጫ ግብ፥ ህዝቡ ለሚቀጥሉት አራት ወይንም አምስት አመቶች አስተዳደሪዎቹን በነፃ
እንዲመርጥ ማድረግ ነው። በእነዚህ አገሮች ህዝቡ አስተዳዳሪዎቹን የሚመርጥበት መንገድ ነው ምርጫ። በእነዚህ
አገሮች ምርጫ ህዝቡ አስተዳዳሪዎቹን የሚቀጥርበት እና ከስራ የሚያሰናብትበት መንገድ ነው ማለት ይቻላል።

የዴሞክራሲ አገሮች ምርጫ ፎርሙላ (ተቋሞች እና የምርጫ ደንቦች)፥ በእነዚህ አገሮች መንግስት እና ፓርቲ
የተለያዩ በመሆናቸው በቅድመ-ምርጫ፣ በምርጫ እለት እና የምርጫ ውጤት ይፋ ተደርጎ ተቀባይነት እስኪያገኝ
ድረስ ባሉት ቀናት (1) በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል መቻቻል እንጂ የገዢ እና የተገዢ ፓርቲዎች ግንኙነት
አይኖርም፣ (2) የቀድሞ ገዢ ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት የምረጡኝ ዘመቻ የመንግስት ንብረት
(ገንዘብ፣መኪናዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ወ.ዘ.ተ.) አይጠቀሙም፣ (3) ምርጫው ነፃ ነው፣ (4) የምርጫ ቦርድ
እና የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኞች ናቸው፣ (5) ተፎካካሪ ፓርቲዎች የየራሳቸውን የድምጽ አሰጣጥ እና ድምጽ
ቆጠራ ታዛቢዎች አሰልጥነው በየምርጫ ጣቢያው ወይንም በሚጠራጠሩባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ
ማስቀመጥ ይችላሉ፣ (6) ህግ-ተርጓሚው የመንግስት ዘርፍ (ዳኝነት) ከፖለቲካ ገለልተኛ ነው። እንደ ፈንሳይ
ባሉት አገሮች ደግሞ ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ስራው ህገ-መንግስት መተርጎም እና ማስከበር ብቻ የሆኑ ገለልተኛ ፍርድ
ቤቶች አሉ።
በእነዚህ አገሮች የምርጫ መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ ተቋሞች፣ የህዝቡ የረጅም ጊዜ የምርጫ ባህል እና ልማድ
ለረጅም ጊዜ በስራ ላይ መዋላቸው ተደማምረው ድምጽ መስረቅን ከባድ ያደርገዋል።

(3ኛ) አምባገነን መንግስቶች የሚያደርጉዋቸው ምርጫዎች ግባቸው እና ፎርሙላቸው፣
የአምባገነን መንግስቶች ምርጫ ግብ፥ የሶቪየት ህብረትን መውደቅ ተከትሎ ካፒታሊዝም በአለም አቀፍ ደረጃ የበላይነትን ካገኘበት ጊዜ ወዲህ ጀምሮ በስልጣን
ላይ የሚገኙ አምባገነኖች በየአራት ወይንም አምስት አመቶች ምርጫ መጥራት ጀምረዋል። ምርጫ የሚያደርጉት
በምዕራቡ አለም ዘንድ ህጋዊነት ለማግኘት ብቻ ነው። ህጋዊነትን የሚፈልጉበት ምክንያት ደግሞ ህዝባቸውን
አክብረው ሳይሆን ዛሬ ካፕታሊዝም በአለም አቀፍ መድረክ የበላይነትን ስለያዘ የምዕራብ አገሮችን እውቅና
ለማግኘት እና ተከትሎም ድጋፍ እና እርዳታ ለማግኘት ነው።

ህጋዊነትን በነፃ ምርጫ ማግኘት ፍጹም ግባቸው አይደለም። ነፃ ፉክክር ማድረግ የአምባገነኖች ባህል አይደለም።
ስልጣን ከወጡበት ጊዜ አንስቶ በአምባገነንነታቸው የምንከሳቸው አምባገነኖች በምርጫ ሰሞን ዴሞክራቶች
አይሆኑም። ስለዚህ በምርጫ ሰሞን ተቃዋሚዎች ምርጫው ነፃ ይሆናል ብለው መጠበቅ የለባቸውም።

ስለዚህ ተቃዋሚ የምርጫ ፓርቲዎች ምርጫው ነፃ ስላልሆነ አንሳተፍም ቢሉ አምባገነኖች ደስታውን
አይችሉትም። የምርጫ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት አምባገነኖች ሆን ብለው ተቃዋሚዎች ገና በማለዳ ተስፋ
ቆርጠው ከምርጫው እራሳቸውን እንዲያገሉ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ዘመቻዎች ሊያደርጉ እንደሚችሉ ቀደም ብለን
መገምት እና መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። ተቃዋሚዎች ከምርጫው ቢወጡም ህዝብ በምርጫ እስከተሳተፈ ድረስ
አምባገነኖች በከፍተኛ ጥማት የሚሹትን ህጋዊነት ያገኛሉ። ምዕራቡ የጥቅም ሸሪካቸው ከሆነ ደግሞ ህጋዊነቱን
ለማግኘት አፍታም አይፈጅባቸውም።

አምባገነኖች ህጋዊነትን ለማግኘት የሚጠቀሙበት የምርጫ ፎርሙላ፥
ፎርሙላቸው ግልጽ ነው። ከተቻለ በምርጫ ማሸነፍ ካልተቻለ ደግሞ ምርጫ መስረቅ ነው ፎርሙላቸው። ስለዚህ
አምባገነኖች ወደ ምርጫ ሲመጡ ሁለት ፕላኖች (ፕላን ሀ እና ፕላን ለ) ይኖሩዋቸዋል። የፕላን ሀ ግብ በምርጫ
ከልብ ተፎካክሮ ለማሸነፍ ፍላጎት ያላቸው ለመምሰል የሚያሳዩት ድራማ ነው። በምርጫ 97 አምባገነነኑ መለስ
ዜናዊ “እንከን የለሽ ምርጫ” ብሎ እንደሰየመው ድራማ ማለት ነው። የፕላን ለ ግብ ደግሞ ድምጽ መስረቅ ነው።
የፕላን ሀ እና የፕላን ለ ግባቸው አምባገነኖችን በስልጣን ላይ ማቆየት ነው።

ስለዚህ አምባገነኖች ደፍረው ምርጫ የሚያደርጉት የሚከተሉትን ፎርሙላዎች በመጠቀም ስልጣን ከእጃችን
አይወጣም ብለው ስለሚገምቱ ነው፥

(1) ህዝቡ ስለሚደግፈን በነፃ ምርጫ እናሸንፋለን ብለው ሳይሆን መራጩን በማስፈራራት የምርጫውን ውጤት
ለመስረቅ የሚያስችል እውቀት፣ ብልሃት፣ ዘዴ፣ አቅም አለን ከሚል እምነት በመነሳት፣

(2) የመንግስት መዋቅሩም፣ የመንግስት ሃብትም፣ አስመራጭ ቦርዱም፣ ምርጫ አስፈጻሚዎችም፣ ሚዲያውም፣
የዳኝነት ዘርፉም፣ እምባ ጠባቂውም፣ ሚዲያውም፣ ካድሬውም፣ ፖሊሱም፣ ደህንነቱም ሁሉም በጃችን በደጃችን
ስለሆነ ምርጫውን ለመስረቅ ምንም የሚያግደን ነገር የለም የሚል እምነት በመያዝ፣

(3) ኃይላችንን ተጠቅመን ህዝብ እናደናግራለን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሆነ ባልሆነው እየከሰስን እናስፈራራለን፣
እንከፋፍላቸዋለን፣ እርስ በርስ እናጋጫቸዋለን፣ ምርጫው ነፃ አይደለም ብለው ተቃዋሚዎች እራሳቸውን
ከምርጫው እንዲያገሉ በማድረግ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያቀርቡዋቸውን እጩዎች እናዋክባለን፣ እጩዎችን
አስፈራርተን አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሄዱ እና በምርጫ ቀን እንዳይገኙ እናደርጋለን፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች
ታዛቢዎች ውስጥ ህሊና ደካሞቹን በጥቅም እንደልላለን፣ ፈሪዎቹን አስፈራርተን ወደ ተመደቡበት ምርጫ ጣቢያ
እንዳይመጡ እናደርጋለን፣ ደፋሮቹን እናስፈራራለን ብለው ስለሚያምኑ፣

(4) እጩዎችም ሆኑ የምርጫ ታዛቢዎች በሚያደርጉት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ስህተት በመስራት ቀዳዳ ከከፈቱልን
ደግሞ ምርጫው እስኪያልፍ ድረስ ክስ መስርተን ጉዳያቸው እስኪጣራ ድረስ በሚል እናስራቸዋለን ብለው
ስለሚወስኑ፣
(5) ድምጽ መስርቅን በሚመለከት ደግሞ አብዛኛው ጣቢያዎች ያለታዛቢ እንዲካሀዱ በማድረግ፣ ከፍተኛ ቁጥር
ያላቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች አስቀድመው የገዢው ፓርቲ ምልክት ተደርጎባቸው በየምርጫ ጣቢያው
እንዲሰማሩ በማድረግ፣ ኮሮጆዎች ከድምጽ መስጫ ጊዜ በፊት በሞምላት፣ ድምጽ ተሰጥቶ ካበቃ በኋላ ኮሮጆዎች
በመዝረፍ፣ ኮሮጆዎች በመጓጓዝ ላይ ሳሉ በመንገድ ላይ ትክክለኛ የህዝብ ድምጽ የሆነውን ዘርግፎ ማቃጠል እና
በምትኩ የኢህአዴግ ምልክት በያዘ ድምጽ በመተካት እና በመሳሰሉት መንገዶች ይፈጸማሉ።

ስለዚህ ለጥቀን በአምባገነ አገሮች የሚታገሉ ዲሞክራሲያዊ ተቃዋሚ የምርጫ ፓርቲዎች ግባቸው እና
ፎርሙላቸው ምን መሆን አለበት ብለን እንጠይቃለን።

(4ኛ) በኢትዮጵያ የሚታገሉ የምርጫ ፓርቲዎች ግባቸው እና ፎርሙላቸው ምን መሆን አለበት?
ግባቸው፥ ነፃ መውጣት ነው። ነፃ መውጣት በፌዴራል፣ በክልሎች እና በቀበሌዎች ደረጃ። በእነዚህ ሶስት ስልጣን
እርከኖች የኢትዮጵያን ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት ማድረግ ነው ግባቸው። የትጥቅ ትግል መሰረቶች
ከመንግስት እና ከህዝብ የራቁ የገጠር ክፍሎች ሲሆኑ የሰላማዊ ትግል መሰረቶች ደግሞ ከተሞች መሆናቸውን
በስልጠና ክፍል ሁለት አጥንተናል። የፌዴራል፣ 9 የክልል እና በኢትዮጵያ የሚገኙ የቀበሌ እና የወረዳ ምክር
ቤቶች በሙሉ የሚገኙት ህዝብ በሚኖርባቸው ከተሞች ስለሆነ መሰረቱን በከተሞች ያደረገው ሰላማዊ ትግል
እነዚህን ምክር ቤቶች ነፃ ማውጣት ግቦቹ መሆን አለበት። እርግጥ ይኽ ሁሉ ግብ በአንድ ምርጫ ተፈጻሚ
ማድረግ እንደማይቻል ግልጽ ነው።። ስለዚህ የኢትዮጵያ ምርጫ ፓርቲዎች ግባቸው አምባገነኖች በሚጠሩዋቸው
ነፃ ያልሆኑ ምርጫዎች ተሳትፈው፥
(1) ከተቻለ በአንድ ጊዜ የሁሉም ምክር ቤቶች አሸናፊ በመሆን ህዝባቸውን ነፃ ማውጣት እና የመንግስት
ስልጣን ባለቤት ማድረግ
(2) በአንድ ጊዜ የሁሉም ምክር ቤቶች አሸናፊ መሆን የማይቻል ከሆነ ደግሞ ለፌዴራል እና ለክልሎች ምክር
ቤት መቀመጫዎች በሚደረጉ ምርጫዎች እየተሳተፉ በድርጅት እና በፖለቲካ ተጠናክረው በመውጣት
ለሚቀጥለው ምርጫ ጥሩ ቁመት መያዝ።

በምርጫ 2007 በፌዴራሉ እና በክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ለመሳተፍ የምር ዝግጅት ከወዲሁ መጀመር ያለበት
ይመስለኛል። የተወሰኑ ቀላል ኢላማ ናቸው የሚባሉ የክልል ምክር ቤቶች ካሉም ጥናት ማድረግ እና መዘጋጀት
የሚጠቅም ይመስለኛል።

እርግጥ በ2005 ዓ.ም. ማለቂያ ግድም በተካሄደው የቀበሌ እና የወረዳ ምርጫ ኢዴፓ በአንድ የምርጫ ወረዳ
(ጨርቆስ መሰለኝ) ካደረገው ተሳትፎ በስተቀር ተቃዋሚው ምርጫው ነፃ አይደለም በማለት ባለመሳተፉ (ህዝቡ
ግን በመሳተፉ) እነዚህን ምክር ቤቶች በሙሉ ለሚቀጥሉት አምስት አመቶች ለህውሃት/ኢህአዴግ ለቀውለታል።
ተቃዋሚው አኩርፎ ከምርጫው እራሱን እንዲያገል በማድረግ ህውሃት/ኢህአዴግ ካለምንም ድካም በደስታ
በእነዚህ ምክር ቤቶች ላይ የሚፈልገውን ህጋዊነት ለሚቀጥሉት አምስት አመቶች አግኝቷል። እርግጥ ሟቹ
አምባገነን መለስ የቀበሌ እና የወረዳ ምርጫ እጩዎችን ቁጥር እጅግ በማብዛት ለተቃዋሚው እጩዎች ለማቅረብ
አዳጋች አድርጎባቸውል። ቢሆንም ግን የማሸነፍ እድላቸው መቶ ከመቶ በሆኑ በተመረጡ ከተሞች ወይንም
ወረዳዎች ተቃዋሚው በምርጫው ተሳትፎ ቢሆን ጥሩ ነበር። ለምን አንድ ወንበር አትሆንም? ትጠቅማለች።
አለዚያማ ምኑን የምርጫ ፓርቲ ተሆነ?

ስለዚህ በአሁነ ሰዓት ፌዴራል፣ 9 ክልሎች፣ የወረዳ እና የቀበሌ ምክር ቤቶች በአምባገነኑ ህውሃት/ኢህአዴግ
ቁጥጥር ስር በመሆናቸው በተለይ በ2007 በሚደረገው ምርጫ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የምርጫ ፓርቲዎች ሙሉ
በሙሉ ነፃ ባልሆነ ምርጫ ተወዳድረው ለማሸነፍ መዘጋጀት እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ተቃዋሚ ፓርቲዎች
ነፃነትን የሚሹትን ያህል በስልጣን ላይ ያለው ህውሃት/ኢህአዴግ ደግሞ በስልጣን የሚያቆየውን ህጋዊነት ማግኘት
ይፈልጋል። ሁለት እጅግ ተቃራኒ እና የማይታረቁ ግቦች። ስለዚህ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የምርጫ ፓርቲዎች
ግባቸውን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችላቸው የምርጫ ፎርሙላቸው ምንድን ነው ብለን እንድንጠይቅ
እንገደዳለን።

የኢትዮጵያ የምርጫ ፓርቲዎች ነፃ ለምወጣት የሚያስፈልጋቸው የምርጫ ፎርሙላ፥ ነፃ ለመውጣት የኢትዮጵያ
ምርጫ ፓርቲዎች በትንሹ የሚከተሉትን ማድረግ አለባቸው።
(1) በምርጫዎች መካከል ባለው ሰፊ ጊዜ ተቃዋሚዎች የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችሉ የተለያዩ
የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መብቶችን መከበር መነሻቸው ያደረጉ ዘመቻዎች ማኪያሄድ (2) በምርጫዎች መካከል ባለው ሰፊ ጊዜ ተቃዋሚዎች በስልጣን ላይ ያለው አምባገነን መንግስት ምርጫ
የሚያኪያሂደው ህጋዊነት ለማግኘት ብቻ እንደሆነ ቀደም ብሎ በመገንዘብ ያንን የሚመኘውን ህጋዊነት
ለማግኘት የሚጠቀምበትን የምርጫ ፎርሙላውን ዝርዝር እርምጃዎች በጥልቀት ማጥናት እና
መከላከያዎች በማዘጋጀት ቀዳዳዎችን በሙሉ በመድፈን የአምባገነኖችን ፎርሙላ ፋይዳ ቢስ ማድረግ፣
(3) በምርጫዎች መካከል ባለው ሰፊ ጊዜ ተቃዋሚዎች በሶስቱ አብይ የሰላም ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች
ውስጥ በኢትዮጵያ ለፈጸሙ የሚችሉትን መርጦ በማውጣት ከሶስቱ የሰላም ትግል ለውጥ ማምጫ
መንገዶች ጋር አቀናብሮ ለመጠቀም የሚያስችል የእውቀት፣ የሰው፣ የድርጅት፣ የገንዘብ፣ የሚዲያ (ቀደም
ባለው ጊዜ ቢያንስ በሳምንት አንዴ በምርጫ እና በድህረ ምርጫ ሰሞን ደግሞ ሁለት ጊዜ ለንባብ
የሚቀርብ ጥራት ያለው ጋዜጣ የማተም) አቅም መገንባት
(4) በምርጫዎች መካከል ባለው ሰፊ ጊዜ ተቃዋሚዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠር በሰላማዊ ትግል እና
በምርጫ ፖለቲካ የሰለጠኑ የሰላም ትግል እና የምርጫ ሰራዊት፣ የሰላም ትግል ፕላነሮች፣ የምርጫ
እጩዎች እና የምርጫ ታዛቢዎች ማሰልጠን አለባቸው። በምርጫ 97 እንደሆነው መቀመጫውን ባህር
ዳር ባደረገው ምክር ቤት እንዲያገለግሉት ህዝብ መርጦ የላካቸው የተወሰኑ የክልል ምክር ቤት የምርጫ
97ን ቀውስ ተከትሎ እዚህ ግባ የማይሉት ምክንያቶች እየፈጠሩ የህዝብ አደራ ክደው አውሮፓ የገቡት
አይነት ግለሰቦች ለእጩነት መቅረብ የለባቸውም።
(5) ቁጥራቸው እጅግ ከፍተኛ የሆነ የውጭ አገር ታዛቢዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እና በየሆቴላቸው
ከመቀመጥ ፈንታ ሁሉም በየምርጫ ጣቢያ እየተዘዋወሩ የተላኩበትን ኃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ፣
(6) ኢሰመጉ እንደተለመደው (ከተቻለም ከተለመደው በላይ) የምርጫ ታዛቢዎች እና የሰብአዊ መብት
ዘጋቢዎች በመላ አገሪቱ ማሰማራት
(7) በምርጫ እለት በየጣቢያው በከፍተኛ ድምጽ ለማሸነፍ መዘጋጀት። በምርጫ 97 ተቃዋሚው በአዲስ
አበባ እንዳሸነፈው። በከፍተኛ ድምጽ የተገኘን ድል ማጭበርበር ያዳግታል። በከፍተኛ ድምጽ የተገኘ ድል
ቢሰረቅም ድምጽ ለማስከበር አደባባይ የሚወጣው ህዝብ ቁጥሩ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት
የለብንም፡፡ ስለዚህ በየምርጫ ጣቢያው በ80 በመቶ እና በ90 በመቶ ማሸነፍ።
(8) የተቃዋሚው ካምፕ (በተለይ አንድነት-መድረክ፣ ትብብር ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ፣ ኢዴፓ እና
ሰማያዊ) ግራ እና ቀኝ እጆች የሚሰሩት ስራ የሚዳመር እንጂ የሚጣፋ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ
አለባቸው። በግብጽ ሞርሲን ለስልጣን ያበቃው የዴሞክራት እጩዎች ስህተት በምርጫ 2007
እንዳይፈጸም መደረገ አለበት።

ስለዚህ የሰላማዊ ትግል እና የምርጫ ፕላነሮች ከመርጫ ቀደም ብሎ ባለው ጊዜ፣ በመርጫ ሰሞን፣ በምርጫ ቀን
እና ከምርጫ ቀን ቀጥሎ ባሉት ቀናት እና ሳምንቶች በገዢው ፓርቲ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በሶስተኛ ፓርቲ
(ምዕራቡ፣ የውጭ ፖለቲካ ወይንም ጦርነት) እና በመሳሰሉ ምክንያቶች የተነሳ ሊፈጠሩ የሚችሉትን የተለያዩ
ዝርዝር ሁኔታዎች (Scenarios) ቀደም ብለው በመገመት ለእያንዳንዱ ሁኔታ (Scenario) . . . ቢሆንስ?
ባይሆንስ? (What If . . . ) የሚል ትንታኔ በማድረግ ውድቀት ሊያመጡባቸው የሚችሉትን ቀዳዳዎችን በሙሉ
መድፈን የሚያስችሉ ፕላኖች (አኪያሄዶች) መቀየስ አለባቸው። ምርጫ 97ን ከውድቀት ካደረሱት ምክንያቶች
ውስጥ አንዱ ይኽን አይነት መሰረታዊ የሰላማዊ ትግል ሀሁ ዝግጅት ፍጹም ባለማድረጉ ነበር።

የዝግጅት አድማስ ሰፊ ነው። የሰላማዊ ትግል እና የምርጫ ፕላነሮች ዝግጅት (1) እጅግ አስከፊ ካልሆኑ ሁኔታዎች
(Scenarios) ጠርዝ አንስቶ እስከ (2) እጅግ አስከፊ የሆኑ ሁኔታዎች (Scenarios) ጠርዝ ድረስ መሸፈን አለበት።
በሁለቱ ጠርዞች መካከል ባለው ክፍት ቦታ ሊመደቡ የሚችሉ ሁኔታዎች (Scenarios) ይኖራሉ። ለምሳሌ ያህል
የሚከተሉት (1) እጅግ አስከፊ ካልሆኑ ሁኔታዎች (Scenarios) ጠርዝ ሊካተቱ ይችላሉ፥ ምርጫው ነፃ አይሆንም፣
በርጫው መራጭ ማዋከብ ይኖራል፣ የታቃዋሚ ፓርቲዎችን ታዛቢዎች ማስፈራራት፣ ማሰር እና ከየጣቢያው
ማበረር ይፈጸማል፣ በዝናብ ብዛት የተነሳ መራጩ ህዝብ በብዛት ወጥቶ መምረጥ ቢሳነውስ፣ በአንዳንድ ጣቢያዎች
ድምጽ ተሰርቋል ግን የተሰረቀውን ድምጽ መጠን በእርግጠኝነት ማረጋገጥ አዳጋች ቢሆንስ እና የመሳሰሉ
ሁኔታዎች። የሚከተሉት ሁኔታዎች ደግሞ (2) እጅግ አስከፊ ሁኔታዎች (Scenarios) ጠርዝ ሊካተቱ ይችላሉ፥ ነፃ
ባልሆነ ምርጫ ተሳትፈን አሸንፈን ስልጣን በጠበንጃ የጨበጠው ህውሃት/ኢህአዴግ ግን ሽንፈትን ባይቀበልስ?
እርግጥ ገዢው ፓርቲ መሸነፉን በእርግጣኛነት አውቀን ነገር ግን መሸነፍን ሳይሆን የህብረት መንግስት የሚለውን
አማራጭ የሚቀበል ቢሆንስ? ሽንፈቱን እንዲቀበል የሚያደርግ ሰላማዊ ትግል ጥሪ ሲደረግ የተቃዋሚው ህብረት
ቢናጋስ? ሽንፈትን እንዲቀበል የምንጠራው ትብብር የመንፈግ ህዝባዊ እምቢተኛነት የማይሳካ ቢመስለንስ? ገዢው
ቡድን በርግጎ አጥፍቼ አጠፋለሁ የሚል አቋም ቢይዝስ? በድህረ ምርጫ ገዢው ቡድን ሽንፈቱን እንዲቀበል
በምንጯጯኽበት ወቅት ወይንም ዘግየት ብሎ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር በማድረግ ላይ ሳለን መፈንቅለ-መንግስት
ቢከሰትስ? የሚሉት ሁኔታዎች (Scenarios) በሙሉ ከምርጫው ቀደም ብለው ተነስተው ሊጠኑ እና በአገር እና በምርጫው ላይ ወድቀት የሚያስከትሉ ቀዳዳዎችን በሙሉ መደፈን የሚያስችሉ ዝግጅቶች መደረግ አለባቸው።
እንደመስቀል ወፍ በምርጫ ሰሞን ብቻ ብቅ በማለት ግርግር መፍጠር ለአገራችን ጎጂ ነው። የትጥቅ ትግል
ግርግርም አገራችንን ወደ ስልጣኔ እና ዘመናዊነት አይወስዳትም።

ስለዚህ በአምባገነ መንግስቶች በሚገዙ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የምርጫ ፓርቲዎች ግብ ነፃነት እነደሆነ እና
የገዢው አምባገነን መንግስት ምርጫ ግብ የምዕራቡን አለም ህጋዊነት ማገኘት መሆኑን ቀደም ብለው በመገንዘብ
በምርጫዎች መካከል ባለው ሰፊ ጊዜ መዘጋጀት እንዳለባቸው ግልጽ ነው። በተለይ ዛሬ ምዕራቡ ብቻውን አለምን
በተቆጣጠረበት ዘመን ዲፕሎማሲያዊ እውቅናም ሆነ የገንዘብ እርዳታ ለማግኘት ለአምባገነኖች በምርጫ ህጋዊነት
ማግኘት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። እንዲሁም ሌላው እኩል መዘንጋት የሌለብን ጉዳይ ምዕራቡ
ሸሪኮቹ ከሆኑት እና ካልሆኑት አምባገነኖች የሚጠይቀው ህጋዊነት ደረጃ የተለያየ መሆኑን ነው። ለምሳሌ የፖለቲካ
ጠላታቸው ከሆነው የዙምባቡዌው አምባገነን ሙጋቤ የሚጠይቁት ህጋዊነት ደረጃ ከፍ እንደሚል እና ከወዳጃቸው
ህውሃት/ኢህአዴግ የሚጠይቁት ህጋዊነት ዝቅ ሊል እንደሚችል ከወዲሁ በመገመት አጭበርባሪውን
ህውሃት/ኢህአዴግ የማጋላጥ ስራ ተጠናክሮ መካሄድ አለበት። ተጨማሪ መዘንጋት የሌለብን ጉዳይ ደግሞ
ኢትዮጵያን የትኛውም ፓርቲ ቢገዛት ምዕራቡ ደንታ እንደሌለው እና የምዕራቡ ቋሚ ጓደኛው ጥቅሙ ብቻ
እንደሆነም ነው። ህውሃት/ኢህአዴግን ዘለዓለማዊ ጓደኛው አድርጎ አያምንም ምዕራቡ ማለቴ ነው። ተቃዋሚው
በርትቶ አማራጭ ኃይል ሆኖ ከወጣ ምዕራቡ ተለማምጦ ከተቃዋሚው ይጠጋል ።

ለጥቀን የምንመረምረው በድህረ-ምርጫም ሆነ በማንኛውም ጊዜ የሚነሳ መፈንቅለ-መንግስት እንዴት በሰላማዊ
ትግል ሊወገድ እንደሚችል ነው።

(5ኛ) ሰላማዊ ትግል መፈንቅለ መንግስትን እንዴት ሊገታ እና ሊያስወግድ ይችላል?
ምርጫን ተከትሎ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሽግግር ለመቀልበስ መፈንቅለ-መንግስት ሊከሰት ይችላል። ይኽ
ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል የሰላም ትግል ፕላነሮች ቀደም ብለው ሊገምቱ እና ህዝባዊ እምቢተኛነት ፕላን
ሊቀይሱ ይገባል። መፈንቅለ-መንግስትን ለመግታት እና ገና ከጅማሬው እንዲሞት ለማድረግ መድሃኒቱ የፖለቲካ
ኃይል ምንጮች ባለቤት እንዳይሆን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትብብር መንፈግ ነው። ስለዚህ
ሶስተኛውን የሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጫ መንገድ በመጠቀም መፈንቅለ መንግስትን ማስወገድ ይቻላል።
ሶስተኛው ለውጥ ማምጫ መንገድ ትብብር የመንፈግ አገር-አቀፍ ህዝባዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ
እምቢተኛነት ነው። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1920 ዓ.ም. በጀርመኒ የተፈጸመ አጭር ታሪክ እንመልከት።

በጀርመን ህዝብ የተመረጠው ፕሬዘዳንት ፍሬድሪክ ኢበርት የሚመራው መንግስት ሲሆን መፈንቅለ-መንግስቱ
ደግሞ በዶክተር ካፕ መሪነት የተነሳው ህገ ወጥ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ነበር። የመፈንቅለ-መንግስቱ ግብ
በህዝብ ድምጽ የተመረጠውን ወጣት መንግስት መገልበጥ እና የቀድሞውን አምባገነናዊ ስርዓት መመለስ ነበር።

ይኽ አጭር ታሪክ የመፈንቅለ-መንግስቱን አነሳስ፣ የአዲሱ-ዴሞክራሲያዊ የህዝብ መንግስት ህዝቡ ድምጹን
እንዲያስከብር የጠራውን ህዝባዊ እምቢተኛነት ሰላማዊ ትግል ጥሪ፣ በተለያዩ ከተሞች የተፈጸሙትን ህዝባዊ-
እምቢተኛነት ሰላማዊ ትግሎች፣ መፈንቅለ-መንግስቱን የመረው ቡድን ግቡን ተፈጻሚ ለማድረግ የሞከራቸው
የተለያዩ ሙከራዎች፣ የህገ-ወጡ ቡድን አወዳደቅ እና ህዝቡ ድምጹን በማስከበር የመረጠውን መንግስት
በስልጣን ላይ እንዲቆይ ያደረገበትን ድል-አድራጊ ትግል ይተርካል።
መጋቢት 2 ቀን 1920 ዓ.ም. በመፈንቅለ መንግስቱ መሪ በዶክተር ካፕ የተሾሞው ጀነራል ሉትዊዝ ለህጋዊው
መንግስት ፕሬዘዳንት ኢበርት ስልጣን በፈቃዱ እንዲለቅ የጊዜ ገደብ ትዕዛዝ ሰጠው። የኢበርት መንግስት ስልጣን
ከህዝብ እንደተሰጠው በመግለጽ የወታደራዊውን ቡድን የጊዜ ገደብ ውድቅ አደረገ። ከህገ ወጡ ወታደራዊ ቡድን
ለሚመጡ ማስፈራራት፣ ዛቻ እና ሌሎች ጥያቄዎች ትብብር ነፈገ ህጋዊው ፕሬዘዳንት። እንዲያውም የመረጠው
የጀርመን ህዝብ ለወታደራዊው ቡድን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ትብብር እንዳይለግሰው አጠቃላይ
የስራ ማቆም አድማ ጥሪ እንደሚያደርግ ለጀኔራል ሉትዊዝ ማስጠንቀቂያ ሰጠው። የመፈንቅለ መንግስቱ ቡድን
መሪ በበኩሉ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ውድቅ አደረገ።
መጋቢት 4 ቀን የዶክተር ካፕ ታዛዥ ብርጌድ ጦር ከባልቲክ ወደ በርሊን ዘመተ። በመንገዳቸው የገጠሙዋቸው
የፖሊስ መኮንኖች እና የመንግስት ሰራዊት ባልደረቦች መፈንቅለ መንግስት ለመፈጸም በሚጓዙት ወታደሮች ላይ
አንድም ጥይት አልተኮሱም። ይኽ መፈንቅለ መንግስት ከጀመረው ቡድን ጋር የመወገን ምልክት ነበር። ስለዚህ
የኢበርት መንግስት መቀመጫውን ከበርሊን ከተማ ድሬስደን ወደ ተባለ ሌላ የጀርመን ከተማ ለወጠ። ቅዳሜ መጋቢት 5 ቀን በርሊንን የያዘው ወታደራዊ ቡድን አዲስ መንግስት አወጀ። ይኹን እንጂ ህጋዊው
የኢልበርት መንግስት ለክፍለ አገር መንግስቶች የካፕን ወታደራዊ መንግስት እንዳይተባበሩ እና ግንኙነታቸው
ከህጋዊው መንግስት ጋር ብቻ እንዲሆን መመሪያ ሰጥቶ ነበር።
እሁድ ከሰዓትት በኋላ መጋቢት 5 ቀን የመፈንቅለ መንግስቱ ታዝዥ ወታደሮች ሁለት የመንግስት ጋዜጣ ቢሮዎችን
ያዙ። የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ህትምት እና ስርጭት ስራ ሊጀምሩ። ይሁን እንጂ በበርሊን ውስጥ የሚገኙ የህትምት
ድርጅቶች በሙሉ የስራ ማቆም አድማ መጀመራቸውን አስወቁ። ወታደራዊው አዲስ መንግስት ጋዜጦች ማተም
እና ማሰራጨት ተሳነው። ህዝብ ቀድሞ ህዝባዊ እምቢተኛነት መጀመሩን የሚያሳይ ምልክት ነው።
በዚሁ መጋቢት 5 ቀን ምሽት የኢበርት መንግስት ካቢኔ እና በስልጣን ላይ የነበረው ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ
ለመፈንቅለ መንግስቱ አጠቃላይ ትብብር እንዲነፈግ ለጀርመን ህዝብ ጥሪ አደረጉ። በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገሪቱን
ኢኮኖሚ ሽባ ሊያደርግ የሚችል የስራ ማቆም አድማ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጠለ። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ
በበርሊን የሚገኙ ሰራተኞችም አጠቃላይ የስራ ማቆም ጥሪውን ተቀላቀሉ። የኮምኒስት ፓርቲው መጀመሪያ
መወላውለው ቢያሳይም ህዝባዊ እምቢተኛነት ሰላማዊ ትግል ጥሪ የሁሉንም ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሃይማኖቶች
ድጋፍ አግኝቷል። የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሲቪል ሰራተኞች (ሲቪል ሰርቫንቶች) ማለትም የተለያዩ ምኒስትር
መስሪያ ቤቶች፣ የባንክ እና የገንዘብ ድርጅቶች ሳይቀሩ ለወታደራዊው መንግስት ትብብር ነፈጉ። የፖለቲካ ድጋፍ
ምሶሶዎች አልተባበርቱም ማለት ነው። በበርሊን መፈንቅለ መንግስቱን የሚተባበር አንድም እጅ በመጥፋቱ የካፕ
ወታደራዊ መንግስት የገንዘብ እጥረት ደረሰበት። የፖለቲካ ኃይል ምንጮችን መቆጣጠር ተሳነው ማለት ነው። ዋና
ከተማ የነበረችው በርሊን የፍልሚያ ማዕከል ሆነች። ስለዚህ በወታደራዊው ቡድን ላይ የተጠራው ትብብር
የመንፈግ ሰላማዊ ትግል በበርሊን እጅግ የተጠናከረ ነበር።
መጋቢት 7 ቀን የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ለኢበርት መንግስት የስልጣን መጋራት ጥሪ አደረገ። ያቀረበው
ምክንያት እርስ በርስ በመዋጋት አገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ከምናስገባት የመንግስት ስልጣን እንጋራ የሚል
ነበር። ሆነም አልሆነ የወታደራዊው ቡድን ጥሪ ቢያንስ በአፍ ደረጃ ማፈግፈግ እንደጀመረ የሚያሳይ ምልክት
ነው። በፕሬዘዳንት ኢበርት የሚመራው መንግስት የስልጣን መጋራት ጥሪውን ውድቅ አደረገ።
በካፕ የሚመራው ወታደራዊ መንግስት፥ (1) ከህዝቡ የገዥነት መብት እና ክብርን ባለማግኘቱ፣ (2) ህዝቡ ስራ
በማቆም የአገር ሃብት ባለቤትነትን ስለነፈገው፣ (3) የቢሮክራሲውን እሽታ ባለማግኘቱ የአገሪቱን የፖለቲካ ኃይል
ምንጮች ትብብር ማግኘት እንደማችል ግልጽ ነበር። እነዚህን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች በህዝብ የተመረጠው
የኢበርት መንግስት (ማለትም ህዝቡ) ስለተቆጣጠራቸው እና ወታደራዊው መንግስት ለተባበሩት ወታደሮች
እንኳን የሚከፍለው ደሞዝ ሊኖረው እንደማይችል ወለል ብሎ ሲታየው ነበር የጥምር መንግስት የመመስረት
ጥያቄን ያቀረበው። ደሞዝ የማይከፍል ማዘዝ አይችልም የሚለው አባባል በፖለቲካም እንደሚሰራ እናውቃለን።
ስለዚህ ነበር ህጋዊው መንግስት የተደረገለትን የስልጣን መጋራት ጥሪ ወዲያው ውድቅ ያደረገው።
በዚህን ጊዜ በመወላወል ላይ የነበሩት ደጋፊዎቹ ወታደራዊውን ቡድን መክዳት ጀመሩ። በዚህ የተነሳ ቀደም ሲል
የተወሰኑ የጀርመን ወታደር ኮማንደሮች ለህጋዊው መንግስት ያሳዩትን ገለልተኛነት እያስወገዱ ምክንያት እየፈለጉ
ታማኝነታቸውን መግለጽ ጀመሩ። “የወታደራዊው አምባገነን መንግስት መውደቅ” የሚሉ ጽሑፎች በበርሊን
ሰማይ ከሚበሩ አውሮፕላኖች ይዘንቡ ጀመር። የካፕ ወታደራዊው መንግስት የበርሊንን ህዝብ አግባብቶ፣
ተለማምጦ፣ አጨብርብሮ፣ አስፈራርቶ፣ አዋክቦ እና ገድሎም ትብብሩን ለማግኘት ያልፈነቀለው ድንጋይ
አልነበረም። ግን አልተሳካለትም።
በመጨረሻ መጋቢት 9 ቀን የበርሊን የጸጥታ ፖሊስ ካፕ ከስልጣን እንዲወርድ ጠየቀ። ከዚያ ካፕ ጀኔራል
ሉትዊዝን ዋና አዛዥ አድርጎ ስልጣን መልቀቁን አሳውቆ ወደ ስዊድን በረረ (ተሰደደ)። የመፈንቅለ መንግስቱ
አቀናባሪ እና ተባባሪዎች ስለፈሩ በምሽት የሲቪል ልብስ እየለበሱ ከበርሊን አመለጡ።
መጋቢት 10 ቀን የባሊትክ ብርጌድ በርሊንን ለቆ እንዲወጣ በፕረዜዳንት ኢበርት የሚመራው መንግስት ትዕዛዝ
ሰጠው። የብርጌዱ ወታደሮች በመውጣት ላይ ሳሉ በመንገዳቸው ላይ በሚያላግጥባቸው እና በሚያንጓጥጣቸው
የበርሊን ከተማ ጥቂት ሲቪሎች ላይ ይቅርታ የማይደረግለት ግድያ ፈጸሙ። መፈንቅለ መንግስቱ ከሸፈ። በህዝብ
ድምጽ የተመረጠው መንግስት በመረጠው ህዝብ ትብብር ከውድቀት ተረፈ። የህዝብን ትብብር ያላገኘ ቡድን የመንግስት ስልጣን ላይ ሊቆይ አይችልም የሚለውን ሃቅ ትክክለኛነት ለማስረዳት
ከዚህ የቀለለ ታሪካዊ ማስረጃ ማግኘት አይቻልም!

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on December 15, 2013
  • By:
  • Last Modified: December 15, 2013 @ 3:41 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar