www.maledatimes.com የፌስቡክ ተቃርኖዎች (ጽዮን ግርማ ከአዲስ አበባ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የፌስቡክ ተቃርኖዎች (ጽዮን ግርማ ከአዲስ አበባ)

By   /   December 16, 2013  /   Comments Off on የፌስቡክ ተቃርኖዎች (ጽዮን ግርማ ከአዲስ አበባ)

    Print       Email
0 0
Read Time:29 Minute, 59 Second

tsiongir@gmail.com

በዓለም ዙሪያ አንድ ቢልዮን ያህል ተጠቃሚዎችን አፍርቷል፡፡ በተጠቃሚዎቹ ብዛት ከማኅበራዊ ድር ዐምባዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል፡፡ በቢልዮን ከሚቆጠሩት የፌስቡክ ተስተናጋጆች መካከል ከግማሽ ሚልዮን በላይ (867,000) የሚኾኑት ከኢትዮጵያ የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ይህ አኀዝ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ ብዛት 0.99 በመቶውን ብቻ እንደሚይዝ በየጊዜው መጠናዊ መረጃ የሚሰጠው የሶሻል ቤከርስ (Social Bakers) ድረ ገጽ ያስረዳል፡፡ በዚህ አኀዝ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ሲጨመር የተገልጋዩን ቁጥር ወደ 1.2 ሚሊዮን ከፍ እንደሚያደርጉት ይገመታል፡፡

ፌስቡክ በተጠቃሚዎች ብዛት ከማኅበራዊ ድረ ገፆች ቀዳሚውን ስፍራ ቢይዝም የተጠቃሚዎቹ ማንነትና የአጠቃቀም አያዎቹ (ተቃርኖዎቹ) በብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡ ማንነታቸውን ደብቀው ራሳቸውን በተለያየ ማንነት ከሚያስተዋውቁ ስመ ብዙዎች – ፌስቡክን የፎቶ አልበም እስከሚያስመስሉቱ፤ በለዘብታ ተዋስኦ ከተመሰጡት – የተዋስኦውን ስክነት (ፍሰት) እስከሚያውኩቱ፤ ሳይተቹ ሳይፈርዱ ‹‹ላይክ›› ከሚያደርጉ አመስጋኞች ወተቱን አጥቁረው ማሩን አምርረው እስከሚያነውሩቱ፤ ሃይማኖትን ከሚሰብኩ አማኞች – እምነትንና ምእመናንን እስከሚያንጓጥጡ እንዳሻዎች፣ ከቄሳራዊ ካድሬዎች እስከ ተቃዋሚ ዲስኩረኞች፣ አዘቦታቸውን ከሚዘግቡ ስንክሳረኞች በተቆጠሩ ፊደላት እስከሚያወያዩ ተንታኞች…. የሚያሰባስብ ነው፡፡

የፌስቡክ ስመ ብዙዎች
ዲጂታል ሚዲያው እንደ ፌስቡክ ያሉ ማኅበራዊ ድረ ገፆችን ለአገልግሎት ማብቃት ሲጀምር የመጻፍና የመናገር ነጻነት መብት በታፈነባቸው አገሮች ኒው ሚዲያ በመባል ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ እንደ ዐይነተኛ ሚዲያ ኾኖ፣ ዐይነተኛ ሚዲያን መስሎ (main stream) የነገሮች ሁሉ መቀስቀሻ፣ መደራጃ፣ መተዋወቂያ ኾኗል፡፡ ይህን መድረክ እንደ ዐይነተኛ ሚዲያ ከሚገለገሉበት ተጠቃሚዎች ውስጥ አዲስ መረጃዎችን የሚያቀርቡ፣ ሐሳባቸውን በለዘብታ ተዋስኦ የሚያንሸራሽሩ፤ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቋም በሚያንጸባርቋቸው አስተያየቶች የሚገልጹና ርቱዕ ሐሳቦችን በማመንጨት የሚያወያዩ፣ የሚያነቃቁ፣ የሚከራከሩና የሚዋቀሱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በአንጻሩ የሐሳብ ድርና ማግ በሚሸመንባቸው ገጾች እውነተኛ ማንነታቸውን ሰውረው የአደባባይ ተዋስኦ እንዳይዳብር በሽጉጥ ሐሳቦች የሚያነቅፉ፣ ሚዛን የሚያሳጡና የሚሸራደዱ፤ የተነሣውን ሐሳብ የሚያዳምኑና መድረኩን ተቀባይነት ለማሳጣትና ለማስነቀፍ የሚታትሩ አሳቾችና ስመ – ብዙዎች በርካታ ናቸው፡፡

ትምህርትን በኢንተርኔት ስለ ማቅረብ (e – learning) አስመልክቶ በውጭ አገር ጥናት ያደረገው የጋዜጠኝነት መምህሩ እንዳልካቸው ኀይለ ሚካኤል÷ ‹‹ሰዎች ማንነታቸውን በተለያየ ምክንያት በመደበቅ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ሊጽፉ ይችላሉ፤›› ይላል፡፡ መምህሩ ምክንያቶቹን ሲያብራራ÷ ከባህል ያፈነገጡ ድርጊቶችን በማስተላለፍ ሊጠቀሙበት ሲፈልጉ የሚደርስባቸውን ማኅበራዊ መገለል ለመሸሽ፣ በሚያንጸባርቁት ፖሊቲካዊና ሃይማኖታዊ አቋም እንዲሁም የሰብአዊ መብቶችን ጥሰት በመቃወም በሚሰጡት አስተያየት ከመንግሥት ሊደርስባቸው የሚችለውን ተጽዕኖ በመፍራት፤ ለስድብ፣ ለአሉባልታ፣ ስም ለማጥፋት፣ ለማታለል፣ ለብቀላ….. መጠቀሚያ ማድረግ ሲፈልጉ ማንነታቸውን ሊደብቁ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡
ዜጐች በመንግሥት ላይ የሚሰጡትን ትችትና ትክክለኛ አስተያየት ኾነ ብለው በረብ የለሽ ትችቶች የሚያንኳስሱ ‹‹ተከፋይ ጸሐፊዎች›› መኖራቸውን የሚጠረጥረው እንዳልካቸው÷ በዋናነት የተነሣና በሂደት ሊዳብር የሚችል ጥልቅ ሐሳብ ወደ ጎን ተብሎ በማይረባው ጉዳይ ላይ ለመነታረክ አጀንዳ የሚያስቱና መንገድ የሚመሩ ‹‹ስመ ብዙዎች››ን ማንነታቸውን ከሚደብቁት ውስጥ ይመድባቸዋል፡፡

‹‹ማንነትን ሰውሮ መጻፍ ድብቅነትን ያበረታታል፡፡ ድብቅነት ደግሞ የተጠቀሱትን ችግሮች ያመጣል፡፡ ከመንግሥት ሊደርስባቸው የሚችለውን ጫና በመገመት ከአቅም በላይ በኾነ ምክንያት ራሳቸውን ከሚደብቁት በቀር እኔ በግሌ ድብቅነትን አላበረታታም፤›› የሚለው እንዳልካቸው÷ የትውልዱ ዐይነተኛ ሚዲያ ኾኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው ማኅበራዊ ድረ ገጽ የተሻለ መድረክ ኾኖ እንዲቀጥል የዲጂታል ሚዲያ ዕውቀት ከፍ ማለት እንዳለበት ይጠቁማል፡፡

በመቐሌ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና በሳውዝ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ጥናቱን በመከታተል ላይ የሚገኘው ኣብርሃ ደስታ÷ በፌስቡክ ህ.ወ.ሓ.ት/ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግን የተመለከቱ የውስጥ መረጃዎችንና ተጓዳኝ ሐሳቦችን በነጻነት በመግለጽ ይታወቃል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ ከህ.ወ.ሓ.ት ድርጅታዊ ጉባኤ ጋራ በተያያዘ አመራሩና ክልሉ በአጠቃላይ ስለሚገኝበት ኹኔታ ውስጥ ዐወቅ መረጃዎችን በፌስቡክ ገጹ ያሰፍራል፡፡

ኣብርሃ በሚጽፋቸው ጽሑፎች ላይ ለሚሰጡት አስተያየቶች በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ በትጋት መልስ ይሰጣል፡፡ ምላሾቹን የሚያስረዳበት ቃላትና ሐሳብ ጨዋነት የጐደላቸውና ያፈነገጡ እንዳይኾኑ ይጥራል፤ ስድብ አዘል አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ሐሳብን በሐሳብ መሞገት እንጂ የሰውን ሐሳብ በስድብ ማራከስ ተገቢ አለመኾኑን በመግለጽ ይመክራል፤ ውይይቱና ክርክሩ ተገቢውን መሥመር ተከትሎ እንዲሄድ ሳይታክት ይጥራል፡፡ እነዚህ ጥረቶቹ ግን ኣብርሃን ከመተቸት አልታደገውም፡፡ ጸሐፊው ስለ ገዢው ፓርቲ በተለይም ስለ ህ.ወ.ሓ.ት ‹‹ድክመት እና ስሕተት›› እንዲሁም ከመብት ጋራ ስለተያያዙ ጉዳዮች ትችት ባቀረበ ቁጥር ከሚሰጡት አስተያየቶች መካከል ስድብ፣ ማንቋሸሽና ማስፈራራት የማይቀሩ ናቸው፡፡

‹‹በእኔ ገጽ ውስጥ ገብተው የሚሳደቡና አጀንዳ ለማስቀየር የሚሞክሩ ተጠቃሚዎች ከ50 አይበልጡም፡፡ እነርሱም ኾን ብለው የተዘጋጁ ጥቂቶች ሊኾኑ ይችላሉ፤›› የሚለው ኣብርሃ÷ ስድቡንና ዘለፋውን ተቋቁሞ ሐሳብን የማንሸራሸር ባህል ማዳበር እንደሚገባ ይመክራል፡፡ ሊተቹ የሚገባቸው ጉዳዮች በሙሉ በተገኘው መድረክ ፊት ለፊት ወጥተው ለክርክር መቅረብ እንዳለባቸው ያምናል፡፡ በድብቅ ማንነት ገጽ የሚከፍቱ ሰዎች ኾን ብለው ሐሳብን በማስቀየስ መድረኩን ለማስፈረጅ እንደሚሠሩ የሚጠረጥረው ኣብርሃ÷ ‹‹ይህን መቆጣጠር የሚችሉት ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው ናቸው፤›› በማለት፡፡

ባለፉት ሳምንታት ውስጥ በተወሰኑ ቡድኖች በተከፈተበት ዘመቻ ‹‹ኣብርሃ ደስታ›› በሚል ስም ገጽ ከፍቶ የሚጠቀመው በሌላ ሰው ስምና ፎቶ በመኾኑ እንዲታገድ የሚጠይቅ ማመልከቻ ‹‹ኣብርሃ ደስታ እኔ ነኝ›› ያለ ሌላ ግለሰብ ለድረ ገጹ አስተዳዳሪዎች አቤቱታ በማቅረቡ ገጹ ተዘግቶ ነበር፡፡
ቆይቶ ግን የገጹ አስተዳዳሪዎች ኣብርሃ ትክክለኛ የገጹ ባለቤት ስለመኾኑ ማንነቱን የሚያረጋግጡ ሕጋዊ ሰነዶች እንዲልክ ጠየቁት፡፡ የተጠየቀውን አሟልቶ በማቅረቡ ከ25 ሰዓታት በኋላ የፌስቡክ ቲም ማናጀር ገጹ በይፋ መከፈቱን ከሚገልፅ ደብዳቤ ጋር አብስሮታል፡፡

የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም ባለሞያው በፈቃዱ ኀይሉ በድብቅ ማንነታቸውም እየተጠቀሙ በጨዋ ቋንቋ ሐሳባቸውን የሚገልጹና ጠንካራ መከራከሪያዎችን የሚያቀርቡ ተጠቃሚዎች የመኖራቸውን ያህል÷ ዋናውን ሐሳብ ትተው መታለፍ የሚችሉ ጥቃቅን ስሕተቶችን እየመዘዙ አጀንዳ የሚያስቱ መኖራቸውን መታዘቡን ይናገራል፡፡ የማንነታቸው መደበቅ በሚሰጣቸውን ገደብ አልባ ነጻነት ተጠቅመው መድረኩ በጥላቻ፣ በጥርጣሬና በፍራቻ እንዲታይ ለማድረግ የሚሞክሩ መኖራቸውንም ይጠቁማል፡፡

ከዚህ ሐሳብ በመነጨ ኾን ብሎ የተከታተላቸው በድብቅ ማንነት የተከፈቱ አምስት የተለያዩ የፌስቡክ ገጽ ባለቤቶች፤ ጠንከር ያሉ ሐሳቦችን ተመርኩዘው በሚቀርቡ የትንታኔ ገጾችና መንግሥትን የሚተቹ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጹሑፎች በሚቀርብበት ገጽ ላይ በተለያየ ሰዓት እየገቡ የውይይቱን መንፈስ ለማስቀየር፣ ጸሐፊውን ወደፈለጉበት ቅርጫት በመወርወር ለማስፈረጅ ሲሞክሩ አስተውያለኹ የሚለው ፈቃዱ÷ ‹‹እኔ በየትኛውም መልኩ አስተያየት በሚሰጥ ሰው ላይ ገደብ አላደርግም፤ ገጼ ለሁሉም ሰው ክፍት ነው፡፡ የማበረታታው ግን ሰዎች ሐሳብን በስድብ ሳይኾን በሐሳብ የመምታት ልምድ ማዳበርን ነው፤›› ይላል፡፡

ማኅበራዊ ድረ ገጹ ከበርካታ ችግሮቹ ጋራም ቢኾን ለማኅበረሰቡ ዐይነተኛ ሐሳብን በነጻነት የማንሸራሸሪያ መድረክ መኾኑን ሦስቱም አስተያየት ሰጪዎች ያምናሉ፡፡
ፌስቡክ በተጠቃሚዎች የማንነትና የአጠቃቀም ተቃርኖዎች የታጨቀ ነው፡፡ ፌስቡክን ዋነኛ መድረክ በማድረግ ለማካሄድ የሚሞከረው የአደባባይ ተዋስኦ እንዳይኮሰምን መድረኩን እንደ ዐይነተኛ ሚዲያ አዘውትረው የሚጠቀሙበት ተሳታፊዎች በየጊዜው የዲጂታል ሚዲያ ዕውቀታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ባለሞያዎች ይመክራሉ፡፡

አርቲስቶች እና የማያውቁት የፌስቡክ ገጾቻቸው
የፌስቡክና ትዊተር ገጾች ለአርቲስቶችና ታዋቂ ሰዎች ዐይነተኛ የመገናኛ መድረኮቻቸው ናቸው፡፡ ድርስ ሥራዎችና የመድረክ ዝግጅቶች ሲኖሯቸው ያስተዋውቁባቸዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የመልካም ምኞት መግለጫዎቻቸውን ያስተላለፉበታል፡፡ በጉዳዮች ላይ ሐሳብ ሲኖራቸው አስተያየታቸውን ያሰፍሩበታል፡፡

ማኅበራዊ ድረ ገጽን በዚህ መንገድ የሚጠቀሙበት ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ጥቂት ናቸው፡፡ በምትኩ ያለአርቲስቶቹ ዕውቅናና ፈቃድ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ስማቸውንና ምስል ገጻቸውን እየተጠቀሙ የሚያንቀሳቅሷቸው የፌስቡክ ገጽ ባለቤቶች ቁጥር ከፍ ያለውን ቁጥር ይይዛል፡፡

አርቲስት መሠረት መብራቴ በስሟ የተከፈተው የፌስቡክ ገጽ በመበራከቱ መጀመሪያ እጠቀምበታለኹ በሚል የጀመረችውን ገጽ ትታ መውጣቷን ትናገራለች፡፡ ‹‹ፌስቡክን በአግባቡ መገልገል ብንችል ለመረጃ ማስተላለፊያ መሣሪያ እንጠቀምበት ነበር፤ ነገር ግን እኔ የማላዝባቸው ገጾች ባሉበት ሜዳ ውስጥ ገብቶ መጠቀም የባሰ ሰዉን ማምታታት ይኾንብኛል ብዬ መጠቀም አቁሜያለኹ፤›› ትላለች አርቲስት መሠረት፡፡ ገጾቹን ለማሳገድ እንደሚቻል ከመስማት ባለፈ በተግባር ያደረገችው ምንም ሙከራ የለም፡፡
አርቲስት ዕፀ ሕይወት አበበ÷ በፌስ ቡክ አማካይነት የግል ፎቶዎቿ ተብትነው እንደቀሩ መጥፎ አጋጣሚዋን በመጥቀስ ትናገራለች፡፡ ለእርግዝናዋ ወራት ማስታወሻ ይኾናት ዘንድ ከባለቤቷ ጋራና ለብቻዋ የተነሣቻቸውን በርካታ ፎቶዎች የያዘው ስልኳ በግሏ ትጠቀምበት ከነበረው የፌስቡክ አድራሻዋ ጭምር ተሰርቆ ስለነበር ስልኩን ያገኙ ሰዎች ፎቶዎቹን በራሷ ገጽ ላይ ይለጥፉታል፡፡ ይህን ጉዳይ እንዳወቀች ፎቶዎቹን በመሰረዝና ፓስወርዶቹን በመቀየር ለመጠቀም ብትሞክርም ግለሰቦቹ ከተለያዩ ቦታዎች ያሰባሰቧቸውን ሌሎች ፎቶዎች በግሏ ከተነሣችው ፎቶ ጋራ በመጨመር አዲስ ገጽ ከፍተው ጨዋነት በጎደለው ቋንቋ እርሷን መስለው ይጻጻፋሉ፡፡

በዕፀ ሕይወት ስም የተከፈቱት ገጾች ከ60 በመቶ በላይ በአጸያፊ ስድቦች የታጨቁ ናቸው፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ፎቶዎቹን ከመተቸትና ለትችታቸው በሚሰጠው ምላሽ እየተበሳጩ ሌላ ስድብ ከመጨመር ባለፈ የባለቤቱን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚጠይቁ አስተያየቶች እንኳ አይነበቡም፡፡ አርቲስቷ ገጾቹን ለማዘጋት ብዙ ደክማለች፤ ነገር ግን በስሟ የተከፈቱት ገጾች በርካታ ከመኾናቸው የተነሣ የተወሰኑትን ብታዘጋም ቁጥራቸውን ከመቀነስ ውጭ ሁሉንም ለማሳገድ አልቻለችም፡፡ አሁንም በስሟ የተከፈቱ በርካታ ገጾች መኖራቸውንና አንዳቸውም የእርሷ አለመኾናቸውን ትናገራለች፡፡

በአርቲስት ኩኩ ሰብስቤ፣ ሙሉ ዓለም ታደሰ፣ ማኅደር አሰፋ፣ ፍቅር አዲስ ነቅዐ ጥበብና በሌሎችም በርካታ አርቲስቶች ስምና ምስል የተከፈቱ ነገር ግን እነርሱ የማይጠቀሙባቸው ብዙም ጠቀሜታ የሌላቸው ገጾች በሌሎች ሰው አማካይነት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በቅርቡ ሦስተኛ ዓመቱን የሚያከብረው ‹‹የዳንኤል እይታዎች›› ጦማሪ የበርካታ መጻሕፍት አዘጋጅ ነው፡፡ በስሙና በፎቶው ተከፍተው የነበሩ ሦስት ገጾችን ማዘጋቱን ቢገልጽም በእርሱ ስም የተከፈቱ አራት የተለያዩ ገጾች አሁንም ይገኛሉ፡፡ አድራጎቱን በብርቱ የተቃወመው ዲያቆን ዳንኤል÷ ‹‹እንደ ጋዜጣና መጽሔት ያሉ ሐሳብን የመግለጫ መንገዶችን ለማግኘት ብዙ ሂደቶችን ማለፍና ከባድ መሥዋዕትነት መክፈልን ይጠይቃል፡፡ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ግን በግለሰብ ይኹን በቡድን ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ይሰጣሉ፤ ነገር ግን በሌሎች ስምና ምስል ያለፈቃድ ገጽ እየከፈቱ ተገቢ ያልኾኑ ተግባራትን ማከናወን ነጻነቱን ማራከስና አርቲስቶችም ኾኑ ሌሎች በዚህ ነጻነት ተጠቅመው የሚፈልጉትን ሐሳብ እንዳያስተላልፉ የሚያደርጉ፣ ዕድሉንም የሚያጠቡ ናቸው፡፡›› ይላል፡፡

ማንነቱን በማያውቀው ሰው በስሙና በፎቶው የፌስቡክ ገጽ ተከፍቶ እንደነበር የሚናገረው ገጣሚው በዕውቀቱ ሥዩም÷ ሰዎች በእርሱ ስም ተጠቅመው የፌስቡክ ገጽ መክፈታቸውን ሲያውቅ ‹‹ከስሙ የሚገኘውን ጥቅም ለመካፈል›› ፌስቡክን መቀላቀሉን ይገልጻል፡፡ ‹‹መጀመሪያ ላይ እኔ የፌስቡክ ተጠቃሚ አልነበርኹም፤ በኋላ ላይ ግን ሰዎች ሲያገኙኝ ጽፈንልኸ መልስ አልሰጠኸንም፤ እንዴት እንዲህ ብለህ ትለጥፋለኽ፤ ባለፈው ጊዜ ኦንላይን አግኝቼህ ሰላም ስልኸ ዘጋኸኝ የሚሉ ተደጋጋሚ ወቀሳዎች ሲቀርቡብኝ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኹ፤›› ይላል ገጣሚ በዕውቀቱ፡፡

ለንደን ላይ ተካሂዶ በነበረው ኦሎምፒክ ዋዜማ የግጥም ትሩፋታቸውን እንዲያቀርቡ ከተጋበዙት አንዱ በነበረው በበዕውቀቱ ስም የፌስቡክ ገጹን ከፍቶ የሚጠቀመው ሰው በዕውቀቱ ለንደን ከገባ ከቀናት በኋላ ‹‹ወደ ለንደን እየሄድኩ ነው›› የሚል መልእክት ለጥፎ የመልካም መንገድ ምኞቶች ተዥጎድጉደውለት ያዩ ወዳጆቹ ሹክ አሉት፡፡ በዕውቀቱ ከአንድ ወዳጁ ጋራ ተመካክሮ ከእርሱ ዕውቅና ውጪ የተከፈተውን የፌስቡክ ገጽ ለአስተዳዳሪዎች በማመልከት ማዘጋቱን ይገልጻል፡፡ አሁን በስሙ ያለው ገጽ ራሱ የሚጠቀምበት ብቻ መኾኑንም ይናገራል፡፡

‹‹ከግለሰቡ ዕውቅና ውጭ በስሙ በሚከፈቱ ገጾች የሚተላለፉ መልእክቶች ባለቤቱን የሚወክሉ ስለማይኾኑ ሰውየው የሚጠነቀቅለትን ሰብእና ያበላሻሉ፤›› የሚለው በዕውቀቱ እንዲህ ያለ ተግባር የሚፈጽሙ ሰዎች ማኅበራዊ ድረ ገጹ የተቋቋመበትን ዓላማ ካለማወቅ መኾኑን ይናገራል፡፡ ‹‹ፌስቡክን ወዳጅነትንና በጎ ነገርን ለማጠናከርያነት መጠቀም ሲገባን በሰው ስምና ምስል ተጠቅሞ ሌላ ገጽ በመክፈት ሌሎች ሰዎችን ማሳሳትና በማይታወቅ ስም ገጽ ከፍቶ ተገቢና ጨዋነት የጎደለው መልእክት ማስተላለፍ ቴክኖሎጂውን ካለማወቅ የመነጨ ነው፤›› ይላል በዕውቀቱ፡፡

‹‹በፌስቡክ ላይ የሚስተዋሉት ተቃርኖዎች የአደባባይ ውይይትና የክርክር ባህላችንን ድክመት የሚያሳይ ነው፤›› የሚለው ገጣሚው በዕውቀቱ ሥዩም፣ ‹‹ቴክኖሎጂውን ለመጥፎ ነገሮች ከመጠቀም ይልቅ ከእርሱ የሚገኙ በጎ ነገሮችን በመምረጥ ማኅበራዊ ድረ ገጽን በአግባቡ መገልገል ጥቅም የሚያስገኝ ነገር ነው፤›› ይላል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on December 16, 2013
  • By:
  • Last Modified: December 16, 2013 @ 6:59 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar