www.maledatimes.com የሰአሊው ጥበብ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የሰአሊው ጥበብ

By   /   December 16, 2013  /   Comments Off on የሰአሊው ጥበብ

    Print       Email
0 0
Read Time:7 Minute, 36 Second
አቤት!! ጊዜው እንዴት ይነጉዳል?

10 ዓመት!!

ድፍን 10 ዓመት ሆነ፡- ከተያየን፡፡

ይገርማል!!
ከ10 አመት በፊት ነበር እንደዘበት ጓደኝነታችን የተጀመረው፡፡ በሥራ አጋጣሚ ነው ለትውውቅ የበቃነው፡፡ እሱ የሥዕል ኢግዚቢሽን አዘጋጅቶ ነበር፡- በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ አዳራሽ፡፡

ያኔ በረቂቅ የሥዕል ስራዎቹ የተነሳ እንደዘበት የጀመርነው ውይይት ነው ወደጥብቅ ግንኙነት የተቀየረው፡፡ እርግጥ ነው ከዚያ በፊትም ትውውቅ ነበረን፡፡ በሰዓሊነት ሙያው ቦሌ ማተሚያ ድርጅት ዲዛይን ክፍል ውስጥ ሲሰራ ትውውቅ ነበረን፡፡ ይሁን እንጂ ትውውቃችን ጥልቀት አልነበረውም፡፡ በአሊያንስ የስዕል ኢግዚቢሽኑን ለጥበብ አፍቃሪዎች አቅርቦ ያሳየ ቀን ግን የበለጠ ተዋወቅን፡፡

ምን መተዋወቅ ብቻ ወደጥልቅ ጓደኝነት ተሸጋገርን፡፡ በሳምንት፤ አሊያም በ15 ቀን አንድ ቀን ውሎዬ በእሱ የግል ሥዕል ስቱዲዮ ውስጥ ሆነ፡፡ ሥለ ሥዕል፤ በአጠቃላይ ስለኪነጥበብ እናወራለን፡፡ እንወያያለን፡፡ እንከራከራለን፡፡ አንዳንዴ ውይይታችን እና ክርክራችን የፀብ እስኪመስል ድረስ የስዕል ስቱዲዮው “ቀውጢ” ይሆናል፡፡ ያኔ የስዕል ጥበብ አስተምህሮቶችን እንዳውቅ ብዙ ነገሮችን ነግሮኛል፡፡ ስለ ሥዕል ጥበብ የተሻለ እውቀት እንዲኖረኝ ረድቶኛል፡፡

ስዕሎቹ ይመስጡኝ ነበር፡፡ የራሱ የአሳሳል ዘይቤ ነበረው፡፡ ሥዕሎቹ ውስጥ የፈረስ ምስል ዓይነተኛ ቦታ ነበረው፡፡ሥዕሎቹ ውስጥ ያየሁት ፈረስ ሸራ ላይ ሳይሆን በሕይወት የሚንቀሳቀስ ያህል ያስደንቅ ነበር፡፡ ሥዕሎቹ ውስጥ የፈረሱ ባቶች ሲያረገርጉ፤ እያንዳንዱ የፈረሱ ጡንቻ ሲያለድል ይታያል፡፡ ያስደንቃል፡፡

እነሆ ይህን የቅርብ ጓደኛዬን ካየሁት 10 ዓመት ሞላኝ፡፡ እርግጥ ነው ፒያሣ ሲኒማ አምፔር አጠገብ የሚገኘው ራዜል ካፌ ቡና ለመጠጣት ጎራ ስል በተለየ መልኩ አስታውሰዋለሁ፡፡ በካፌው አንደኛው ጥግ በረዥሙ የተሰተረው የፈረስ ምስል እሱን ያስታውሰኛል፡፡ ደግሞም ይህ ምስል የእሱ ሥራ ነው፡፡ ከራዜል ካፌ ቆንጆ ቆንጆ አስተናጆች በላይ ዓይኔን የሚስበው፣ ሕሊናዬን የሚገዛው የእሱ ስዕል ነው፡፡

በዚህ መልኩ ባስታውስም፤ እሱን ካየሁት 10 ዓመት ሞላኝ፡፡ ዛሬ ግን አገኘሁት፡፡ እዚሁ ፌስቡክ ሰሌዳ ላይ፡፡ ምስሉን ሳየው ደነገጥኩ፡፡ የፌስ ቡክ ጓደኛዬ መሆኑን በእርግጠኝነት አላውቅም ነበር፡፡

እናም ከፎቶው ሥር “ሥዕሎችህን ማየት ናፍቆኛል” ብዬ ፃፍኩ፡፡

እዚያው ሰሌዳ ላይ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጠኝ፡- “ February 2, 2014 sheveport exhibition ታየኛለህ፡፡”

ሳቅኩ፡፡ ከልብ ሣቅኩ፡፡ “እኔና ዋሊያ ከሃገርውጪ እንደማንገኝ አላወቀም” ብዬ ሳቅሁ፡፡

ለማንኛውም ይህ ድንቅ ሰዓሊ፤ ለካስ አሁንም ጓደኛዬ ነው አልኩ፡፡ በውስጥ መስመርም አወራሁት፡፡ ከሰዓሊነት ሥራው ራሱን ያገለለ መስሎኝ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም በሥዕል ጥበብ ባህር ውስጥ ነው፡- ባሕር ማዶ ሃገረ አሜሪካ፡፡

እሁንም እየተጠበበ ነው፤ አሁንም በቀለማት ህብር ሕይወትን እየኳለ ነው፡፡ እንደውም በቅርቡ የሥዕል ሥራውን ለኢግዚቢሽን ያቀርባል፡፡ ሠዓሊ ተስፋዬ ንጉሴ፡፡

ሠዓሊ ተስፋዬ ንጉሴ ለየት ያለ የሥዕል ዘይቤ የሚከተል ድንቅ ጥበበኛ ነው፡፡ ይህንን እኔ ብቻ ሳልሆን በሙያው ውስጥ ያሉ አጋሮቹ በሙሉ ይመሰክሩለታል፡፡ ምርጥ ሰዓሊ ነው፡፡ ወደፊት የሃገራችንን ስም ሊያስጠሩ ከሚችሉ ተስፋ ከሚጣልባቸው ወጣት ሰዓሊያን መሃል አንዱ ነው፡፡ አሁንም በሃገረ-አሜሪካ የጥበብ ስራውን እነሆኝ ማለቱን ቀጥሏል፡፡ በዚያ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን የተስፋዬ የጥበብ ሥራ ተመልከቱት፡፡ ትደነቃላችሁ፡፡ ትኮራላችሁ፡፡ እኔ ያልኩትን ሁሉ ደግማችሁ እንደምትመሰክሩ አልጠራጠርም፡፡

እዩት!!! ይህንን ጥበበኛ እዩት!!! ሠዓሊ ተስፋዬ ንጉሴን በሥራዎቹ ውስጥ እዩት!!!
ድንቅ ሰዓሊ ነው!!! —

PhotoPhoto
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on December 16, 2013
  • By:
  • Last Modified: December 16, 2013 @ 7:21 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar