www.maledatimes.com “ሕወሓት ከመለስ ሞት በኋላ እየተዳከመ ያለ ድርጅት ነው፤ ኢህአዴግ ለዘለዓለም መግዛት አለብኝ የሚል ድርጅት ነው” ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“ሕወሓት ከመለስ ሞት በኋላ እየተዳከመ ያለ ድርጅት ነው፤ ኢህአዴግ ለዘለዓለም መግዛት አለብኝ የሚል ድርጅት ነው” ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ

By   /   December 16, 2013  /   Comments Off on “ሕወሓት ከመለስ ሞት በኋላ እየተዳከመ ያለ ድርጅት ነው፤ ኢህአዴግ ለዘለዓለም መግዛት አለብኝ የሚል ድርጅት ነው” ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ

    Print       Email
0 0
Read Time:33 Minute, 9 Second

ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ ከህወሓት ጋር 17 ዓመታት በትግል ያሣለፉ እና ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዷ ነበሩ፡፡ በ1993 ዓ.ም ከፓርቲው ከተሰናበቱ አባላት አንደ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የ“አረና” ፓርቲ አባል የሆኑት ወ/ሮ አረጋሽ በአጠቃላይ ጉዳዮች ዙሪያ ከ“ሎሚ” አዘጋጅ ቶማስ አያሌው ጋር ያደረጉት ቆይታ የመጀመሪያ ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ሎሚ፡- የኢህአዴግ ጭቆናና፣ አፈና፣ የተንሰራፈው በመላው ሀገሪቱ ነው የሚል አቋም ካላችሁ፣ ብሔር ተኮር ፓርቲ የመሰረታችሁበት ምክንያት ምንድነው;
አረጋሽ፡- ፓርቲ የሚመሰረተው በአካባቢ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት አድርጐ ነው፡፡ ተጨባጭ ሁኔታ ስል የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሰብዓዊ መብት፣ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመጥቀስ ፈልጌ ነው፡፡ ማንኛውም ድርጅት በዚህ መልኩ ነው የሚመሰረተው፡፡ አረናም በዚሁ መሠረት የተመሠረተ ፓርቲ ነው፡፡

ከሕወሐት ክፍፍል በኋላ አረና ሲደራጅ፣ ለአገራችን የታገልንለት ዓላማ ሙሉ በሙሉ ስላልተሣካ፣ ያልተሣካው እንዲስተካከል አለያም የተሻለ ለማድረግ የራሣችንን ጫና ማሣደር አለብን ብለን ነው አቋም የያዝነው፡፡ ስንደራጅ ሀገራዊ ፓርቲ የመመስረት ዓላማም ፍላጐትም ነበረን፡፡ ነገር ግን በነበርንበት ሁኔታ አገራዊ ድርጅት መመስረት ቀላል አልነበረም፡፡ ጠንካራ ርዕዮተ ዓለም፣ በጣም ወሣኝ አባላት ያሉት አገራዊ ድርጅት መመስረት አሁንም ቢሆን አስቸጋሪ ነው፡፡ ሀገራዊ ድርጅት የመመስረት ፍላጐት ቢኖረንም የነበርንበት ተጨባጭ ሁኔታ አልፈቀደልንም፡፡ በተግባር ስንመለከተው የብሔረሰቦች መብት ሙሉ ለሙሉ ባይከበሩም፣ ሀገራዊ ፓርቲ ለመመስረት ሁኔታዎች እስኪፈቅዱልን ድረስ ብለን አረናን መሰረትን፡፡
ይህን ካደረግን በኋላ አረናን ይዘን ቁጭ አላልንም፡፡ ሀገራዊ ፓርቲ ካልተመሠረተ የትግራይም ይሁን የሌላው ብሔር ብሔረሰቦች ችግር ይፈታል ብለን አናምንም፡፡ ሀገራዊ ፓርቲ የሚመሠረትበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን ብለን ከሌሎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ህጋዊ እውቅና ካላቸውና በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ ፓርቲዎች ጋር በአጭር ጊዜ ውይይት ጀመርን፡፡ መድረክ በሚባለው ድርጅትም የገባነው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
ሎሚ፡- ከክፍፍሉ በኋላ ተዘጋጅቶ የነበረው “ሕዝባዊ” የተባለ ጋዜጣ በምርጫ 97 በጋዜጣው ርዕሰ አንቀፅ ከገዢው ፓርቲ ይልቅ ቅንጅት ላይ ጠንካራ ትችት ታቀርቡ ነበር ይባላል፤ እንዲያ ተደርጎ ከሆነ ትኩረታችሁን ወደ ተቃዋሚ ፓርቲ ያነጣጠራችሁበት ምክንያቱ ምንነበር;
አረጋሽ፡- ከኢህአዴግ ይልቅ ወደ ቅንጅት ያተኮረ ነበር የሚለው አስተያየት ለኔ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ጋዜጣውን በትክክል አንብቦ ተረድቶ የተሰጠ አስተያየት አይመስለኝም፡፡ ያኔ ኢህአዴግን ነበር የምንታገለው፡፡ ከዴሞክራሲ አንፃር፣ ከህግ ልዕልና አንፃር፣ ከመናገርና መደራጀት አንፃር፣ ከፕሬስ ነፃነት አንፃር… እነዚህን እና ሌሎች ተጨባጭ ሁኔታዎችን መነሻ እያደረግን በጋዜጣችን ጠንከር ጠንከር ያሉ አስተያየቶችን እንሰጥ ነበር፡፡ የ97 እንቅስቃሴ ሲመጣም ኢህአዴግ “ዴሞክራሲያዊ፣ ግልፅ እና ነፃ ምርጫ ይመጣል” ብሎ ከጀመረ በኋላ ኃይሉ ሲዛባበት፣ ስልጣኑ እየተንገዳገደ መሆኑን ሲረዳ ቀድሞ የገባውን ቃል ማጠፍ ጀመረ፡፡ እንዲያውም የመሸነፍ አዝማሚያ ሲያይ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በቴሌቪዥን በመቅረብ “ኢህአዴግ አሸንፏል” ነበር ያለው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ፀረ-ዴሞክራሲ የሆኑ አዋጆችን አውጇል፡፡
ከዚህ በመነሣት ተገቢ አለመሆኑን በሚመለከት በርካታ ነገሮች ፅፈናል፡፡ “ይሄ የዴሞክራሲውን አካሄድ ማጥበብ እንደሆነ፣ ገና ቆጠራው ሣይጠናቀቅ እኛ አሸንፈናል ብሎ መናገር ኢ-ዴሞክራሲያዊ እና አምባገነናዊነት እንደሆነ፣ ተቃዋሚዎቹም ቢሆኑ በህጉና በአግባቡ መያዝ እንዳለባቸው፣ የሕዝብ ድምፅ በአግባቡ ሊቆጠርና ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባው፣ መሸነፉን አምኖ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መቀበል እንዳለበት በሚመለከት ደጋግመን ፅፈናል፡፡ ከዚህ አንፃር ካየነው ቅንጅትን የሚያጠቃ አቋም ነበራችሁ የሚለው አስተያየት አሳማኝ አይደለም፡፡ ቅንጅት ላይ ጫና ወይም ትኩረት ማድረግ ሳይሆን፣ ቅንጅቶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የጠቆምንበት ሁኔታ ነበር፡፡
ሎሚ፡- ፓርቲያችሁ አረና በ2006 ዓ.ም. ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው;
አረጋሽ፡- አረና ጳጉሜ ውስጥ ሦስተኛ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ አንዳንድ ሕገ ደንቦቹን አስተካክሏል፤ የሚሻሻሉ ነገሮችን አሻሽሏል፡፡ አዳዲስ አመራሮችን መርጧል፤ ለምሣሌ የቀድሞው የፓርቲው ሊቀ-መንበር በአዲስ እንዲተኩ አድርገናል፡፡ ወጣቶችን ወደ አመራር አምጥተናል፡፡ ለውጥና የማሸጋሸግ ስራ ተሰርቷል፡፡ ወጣቱ ወደ ፖለቲካው መድረክ ቢመጣ የትግል ሂደቱን እየተላመደና እየተማረበት ይሔዳል በሚል ነው፡፡ እኛ የወደፊት መሪዎች አይደለንም፤ የወደፊት መሪዎቹ ወጣቶቹ ናቸው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ የዕቅድ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡ በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገራዊ ፓርቲ እንዲፈጠር የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል እያደረግንም ነው፡፡ በእውነቱ ይህ በእኛ ፍላጐት ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ የሌሎቹም ፍላጐት ያስፈልጋል፡፡
እንዲሁም ሀገሪቱ የወጣት ምሁራን የተሻለ አመራር እንድታገኝ የማድረግ ኃላፊነት አለብን የሚሉ ግለሰቦችን የማሰባሰብ አቅም ያስፈልጋል፡፡ እኛ ይህ ሁኔታ እንዲፈጠርና እንዲመቻች ካሉት ፓርቲዎች ጋር በፕሮግራሞቻችን ተስማምተን ሀገራዊ ፓርቲ እንዲመሠረት እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ንዑስ ኮሚቴ ከኛም ከሌሎችም ድርጅቶች ተውጣጥቶ እየተንቀሣቀሰ ነው፡፡ የአረና ጉባኤ አንደኛው ማጠንጠኛም ይሔ ነው፡፡ ሌላው የጉባኤው አጀንዳ ፓርቲው በተጠናከረ መልኩ ከሕዝቡ ጋር መገናኘት፣ እስከ ገጠር የዘለቀ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለብን የሚያሳስብ ነው፡፡ ይሁንና እነዚህን ነገሮች እንዳናደርግ የሚያግዱን ችግሮች አሉ፡፡ አንዱ የገንዘብ አቅም ነው፡፡ ህዝቡ ከስጋትና ከፍራቻ አልወጣም፡፡ ቢሆንም ባለን አቅምና ችሎታ በትናንሽ ከተማዎች ስብሰባ በማድረግ እንቅስቃሴያችንን ጀምረናል፡፡ እንዲሁም ከመድረክ ጋር በመሆን በናዝሬት፣ ሀዋሳ፣ መቀሌ ከተማዎች ሕዝባዊ ስብሰባ ለመጥራት በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡
ሎሚ- ፓርቲያችሁ ባደረገው ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ “ውህድ ፓርቲ” እንደሚያስፈልግ ደጋግሞ ገልጿል፡፡ ወደዚህ አቋም የመጣችሁበትን አቋም ቢያብራሩልን;
አረጋሽ፡- ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ሀገራዊ ድርጅት ቁልፍ ሚና አለው፡፡ በተበታተነ መንገድ በክልሎች ብቻ ተደራጅቶ ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ያሉት ችግሮች ሀገራዊ መፍትሔ ካልተቀመጠላቸው በስተቀር በክልል ደረጃ ብቻ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የምንፈልገውን ለውጥ አናመጣም፡፡ ጠንካራ አመራር ያስፈልጋል፡፡ ሀገር የሚቀይር ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ሀገር እንዲቀየር ከተፈለገ ሀገራዊ ፓርቲ መኖር አለበት፡፡ ይሕም ማለት ውህደት መፍጠር ማለቴ ነው፡፡ ውህደት ሲኖር ነው በሀገርም ሆነ በክልል ደረጃ ያለውን ችግር አብሮ መፍታት የሚቻለው፡፡ በግንባር ደረጃ ብቻ አብሮ መታገል መንግስትን ላይፈትነው ይችላል፡፡ ተገቢውን ጫና አሳድሮ መንግስት ነፃና ግልፅ የሆነ ምርጫ እንዲያደርግ ሊያስገድደው አይችልም፡፡ ስለዚህ ሀገራዊ ፓርቲ ተፈጥሮ፣ ሀገራዊ አመራር ካልተመሠረተ ለየብቻ በሚደረግ ትግል የሚመጣ ለውጥ የትም አያደርስም በሚል ነው ለውህደት የተነሳነው፡፡
ሎሚ፡- የህወሓት መመስረቻና መቀመጫ በሆነው ትግራይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ ወጣቶች በማህበራዊ ድረ ገፆችና በሌሎች ሚዲያዎችም በገዢው ፓርቲ ላይ ተቃውሟቸውን እየገለፁ ነው፡፡ ይሔ ምንን ተከትሎ የመጣ ይመስልዎታል;… በአንፃሩ የሴቶች እንቅስቃሴ የማይንፀባረቀውስ ለምንድን ነው;
አረጋሽ፡- የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እየሄደ ነው፡፡ መሠረታዊ መነሻውም ትግራይ ውስጥ ያለው ኢ-ፍትሃዊ ስርዓት አካሄድ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ያ ሁኔታ በወጣቱ ላይ ተንፀባርቋል፡፡ ሕዝቡ ደጋግሞ የታገለ ሕዝብ ነው፡፡ ብዙ መስዋዕትነት የከፈለ ሕዝብ ነው፡፡ መስዋዕትነት የከፈለው ደግሞ የዲሞክራሲ፣ የኑሮ፣ የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲመጣ ነው፡፡ ሕዝቡ ከዚህ በኋላ የምንበደልበት ስርዓት አይኖርም ብሎ ነው ሦስትና አራት ልጆቹን ከአንድ ቤት ልኮ ያታገለው፡፡ ያንን እምነት ይዞ የታገለ ሕዝብ፣ መልሶ ለዚህ ዓላማ ነው የታገልኩት የሚለው ድርጅት (ህወሓት) ሲጨቁነው ምሬት ሊሰማው የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡
አስተዳደሩ ሕዝቡን ከሌሎች ክልሎች በበለጠ ተቆጣጥሮና ወጥሮ ይዞታል፡፡ በትግራይ ውስጥ ሁሉንም ሕዝብ በወጣት፣ በሴቶች፣ በተለያዩ ማህበሮች አደራጅቶ ከህወሓት ትዕዛዝ ውጭ እንዳይመራ እየተደረገ ነው፡፡ የወገንተኝነት፣ የዝምድና ሥራ፣ የሙስናም ጉዳይ አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ችግሬ እየተሰማ አይደለም የሚል ስሜትም አለ፡፡ ይህንን መሠል እሮሮዎች እየወጡ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የተማረው ክፍል በተወሰነ መልኩም ቢሆን የነፃነት ስሜት ስላለው ያንን ማስተጋባት ጀምሯል፡፡ ተቃውሞው ከዚህ የመነጨ ይመስለኛል፡፡ ሌላኛው የሕወሓት ሥጋት ተጨማሪ ኃይል እየፈጠረ ያለው የአረና እንቅስቃሴ ነው፡፡ የአረና እንቅስቃሴ ወጣቶችን እያደራጀ ነው፤ ወጣቶችን ወደ አመራርነት እያመጣ ነው፡፡ ዓላማውን እየገለፁ ነው፤ ትግራይ ውስጥ ያለውን ችግር አብሮ እየተወያየበትና እየመከረበት ነው፡፡ ይሔ ደግሞ የበለጠ እንዲነቃቃ አድርጐታል፡፡ በተለይ እኛ የቀድሞ የህወሓት አባላት ለሕዝብ ችግር መታገል አለብን ብለን መንቀሳቀሳችን ትልቅ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር፣ የሕዝቡ ምሬት፣ የእኛ እንቅስቃሴ ተዳምሮ ወጣቱን እንዲነሳሳ እያደረገው ነው፡፡
የሴቶች ተሳትፎን በሚመለከት… አረና ከተመሰረተ ገና አምስት ዓመቱ ነው፡፡ እንቅስቃሴያችን ደግሞ ውሱን ነበር፡፡ ሴቶችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ በማህበር ተደራጅተዋል፤ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ሳይቀር በሊግ (በአንድ ለአምስት) ተጠርንፈዋል፡፡ ይሕም ሆኖ የአረና አባላት የሆኑ ሴቶች አሉ፡፡ በአመራር ደረጃም የተወሰኑ አሉ፡፡ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴያችን እየጠነከረ ሲሄድ ሴቶቹ የመምጣታቸው ነገር ይጨምራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢህአዴግ ዋነኛ ኃይሎቹ ሴቶች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በልማት፣ በማህበር አደራጅቶ እንዲንቀሣቀሱ ያደረገው ሴቶችን ነው፡፡ ይህም ጥቅም ፈጥሮለታል፡፡ እኛ ይህን አዝማሚያ መስበር አለብን፡፡ ግን በሂደት ለውጦች ተፈጥረው የሴቶች እንቅስቃሴም እየጐላ መምጣቱ አይቀርም፡፡
ሎሚ፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች እንቅስቃሴ በማይታይበት ሁኔታ እንደ ብርቱካን ሚደቅሳና፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ያሉ ሴቶች እስከ መታሰር የሚከፍሉትን መስዕዋትነት እንዴት ይመለከቱታል;
አረጋሽ፡- የእነሱ ወደ እስር ቤት መሄድ በተናጠል የሚታይ ነገር አይደለም፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ስልጣኑን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መልቀቅ የማይፈልግ ድርጅት ስለሆነ፣ ለይስሙላ ዴሞክራሲ አለ፣ ነጻ ምርጫ እናደርጋለን እያለ በሚዲያ ቢያስተጋባም በተግባር ግን ዜሮ ነው፡፡ በሕዝብ ድምፅ ተሸንፎ ሥልጣኑን ለማስረከብ የተዘጋጀ ድርጅት አይደለም፡፡ ከስልጣን የመውረድ ስጋትና ፍራቻ ስላለው፣ ዴሞክራቲክ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን አይፈልግም፡፡ ኃይል ያለው ሀሳብን፣ ኃይል ያለው ፅሁፍን ይፈራል፡፡
የሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው ድርጅቶች… እንዲጠናከሩ፣ እንዲያብቡ ወደ መድረክ እንዲመጡ አይፈልግም፡፡ ብዙኃኑን ሕዝብ ያንቀሳቅሳሉ ያላቸውን ሰዎች በአጭር ጊዜም ይሁን በረጅም ጊዜ ለይቶ ያዳክማቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሀሣባቸው ወይም የሚያነሱት ጥያቄ የራሣቸው “የግል” አይደለም ብሎ ስለሚያስብና ሕዝብ ጋ ከደረሰ ችግር ይፈጥራል ብሎ ስለሚሰጋ በአጭሩ የመቅጨት ስራ ይሰራል፡፡
የብርቱካንም ይሁን የርዕዮት እንዲሁም የሌሎች የፖለቲካ ታሳሪዎች ሁኔታ ከኢህአዴግ ስጋት የመነጨ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ሀሣብ እንዲስተጋባና እንዲሰማ አይፈልግም፡፡ አዲስ ሀሣብ ሕዝቡ ጋር ደርሶ ኃይል እንዲፈጥር አይፈልግም፡፡ በሽብር እና በሌሎች ምክንያቶች በማሳበብ ሊወጡበት የማይችሉበት ቦታ ውስጥ ያስገባቸዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ከማሰር ጐን ለጐን የማሳቀቅና ከመንገዳቸው የማስወጣት ሥራዎችም ይሰራል፡፡ በአጠቃላይ በብዙ መንገድ ይኮረኩማል፡፡ ኢህአዴግ ነፃና ግልፅ የሆነ ምርጫ አካሂዶ ሲሸነፍ ሊወርድ፣ ካልተሸነፈ ሊቆይ የተዘጋጀ ፓርቲ አይደለም፡፡ ለዘላለም እኔ ነኝ መግዛት ያለብኝ ብሎ የሚያምን ድርጅት ነው፡፡ ይሔንን አስተሳሰቡን የሚፃረረውን ድርጅትም ይሁን ግለሰብ ማጥፋት የለመደ ፓርቲ ስለሆነ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ከዚህ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
ሎሚ፡- ህወሓት “የአዲስ አበባ እና የመቀሌ” በሚል ቡድን ለሁለት መከፈሉ ይነገራል፤ የኢህአዴግ “አስኳል” ነው የሚባለው ህወሓት ውስጥ መከፋፈል መከሰቱ የሚፈጥረው አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ውጤት ይኖራል;
አረጋሽ፡- በህወሓት ውስጥ ክፍፍል አለ፤ ለሁለት ተከፍሏል የሚባለውን ነገር ላውቀው አልቻልኩም፡፡ ክፍፍል አለ ብዬ ለመውሰድ ትክክለኛ መረጃ የለኝም፡፡ “ተከፋፍለዋል” የሚል እምነት የለኝም፤ አንድ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንኳን ተከፋፍለው አንድ ሆነውም ለመዝለቅ የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ናቸው የሚለው ጥያቄ ቢነሣ ነው የሚሻለው፡፡
በአጠቃላይ ሕወሓት ከመለስ ሞት በኋላ እየተዳከመ ያለ ድርጅት ነው፡፡ ሁልጊዜም ደጋግመው “የጠ/ሚ መለስን ራዕይ እናስተገብራለን” ነው የሚሉት፡፡ ራዕይ ለተወሰነ ጊዜ ትቶላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ሁኔታዎች ግን በየጊዜው ነው የሚቀያየሩት፡፡ ከሁኔታውና ከጊዜው ጋር የሚሄድ “ራዕይ” ካልያዙ የያዙት እምነት የሚገድላቸው ይመስለኛል፡፡ አዳዲስ ሀሣቦችን፣ አዳዲስ አቅጣጫዎችን ከነባራዊው ሁኔታ ጋር እያስተሳሰሩ መሔድ ካልቻሉ ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ሕዝብ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች ግምት ውስጥ የሚያስገባ ራዕይ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሕዝቡ ተበደልን ሲል፣ ዴሞክራሲ የለም ሲል የህግ ልዕልና የለም ሲል፣ ፍትህ የለም ሲል፣ ጉቦና ወገንተኝነት እየተስፋፋ ነው ሲል፣ መፍትሄ አምጡልን ሲል፣ “ሀገሪቱ በእድገት ላይ ነች፤ አንዳንድ ችግሮች ብቻ ነው፤ እነሱንም በሂደት እንፈታቸዋለን” የሚል ምላሽ እየሰጡ መዝለቅ አይችሉም፡፡ ተከፋፍለዋል የሚለው ግን እኔ የተከፋፈሉበትን ሁኔታ ስላላየሁ ስለሱ አስተያየት ለመስጠት ይከብደኛል፡፡
ሎሚ፡- የትግራይ ሕዝብና የህወሓት ግንኙነትስ ምን ይመስላል;
አረጋሽ፡- ህወሓት ከትግራይ ሕዝብ ጋር የተሳሰረ ታሪክ አለው፡፡ 17 ዓመት ሙሉ ሕዝቡ ታግሏል፡፡ አመራሩ ተለወጠ እንጂ አሁንም ሕዝቡ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ነው፡፡ ያንን ሁሉ ትግል ያደረገው ደግሞ ደህና ስርዓት ይመጣል ብሎ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብሮ በመኖር ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርአት ይመጣል ብሎ ነው መስዕዋትነት የከፈለው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ደግሞ ህወሓት ይሔንን እንዳይቀጥል እያጠፋ፣ ኢ-ዴሞክራሲያዊ፣ ኢ-ፍትሃዊ እየሆነ፣ አፋኝ እየሆነ ነው ያለው፡፡ ከዚህ አንፃር የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ላይ እየተማረረ ነው፡፡ መፍትሄ ስጡን እያለ ነው፡፡ ስብሰባ በተደረገ ቁጥር ችግሩን በስፋት ይገልፃል፡፡ እንዲሰሙትም እየጠየቀ ነው፡፡ ይሁንና ተደጋግሞ ጥያቄ ቢያቀርብም መፍትሄ ግን አላገኘም፡፡ በዚህ ምክንያት ቅሬታ እየተፈጠረ ነው፡፡ ጠንካራ የሆነ ድርጅት ከተፈጠረ የትግራይ ሕዝብ አብሮ ከመታገል ወደኋላ አይልም፡፡ አሁን ግን የእኛ አቅም ነው የሚወስነው፡፡ ሀገራዊ በምንለውና ይፈጠራል በምንለው ፓርቲ ዙሪያ የሚወሰን ነው፡፡ ለትግልም ሆነ ለመብቱ በሰላማዊ መንገድ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመታገል የትግራይ ሕዝብ ዝግጁ ነው፡፡ እኛ ጋ ድረሱ፤ ከተማ ብቻ ቁጭ አትበሉ እያለ ነው፡፡ አንድ ጊዜ አለን ትላላችሁ፤ ሌላ ጊዜ ትጠፋላችሁ የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ እየተነሳ ነው፡፡ የህወሓትና የትግራይ ሕዝብ ሁኔታም እየሻከረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ለውጥ ፈላጊ ነው፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on December 16, 2013
  • By:
  • Last Modified: December 16, 2013 @ 11:02 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar