www.maledatimes.com የአሳታሚው ማስታወሻ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአሳታሚው ማስታወሻ

By   /   December 22, 2013  /   Comments Off on የአሳታሚው ማስታወሻ

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 39 Second

የኢትዮጵያን አብዮት በሁለተኛነት የመሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረሥላሴ  ወግደረስ በዚህ መጽሐፋቸው የአብዮቱን ሂደት እንደቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ሁሉ የራሳቸውን ዕይታ ያካፍሉናል። ‘እኛና አብዮቱ’ ብለው እንደ ደርግ አባልነታቸው በጋራ ያመኑበትን፣ የተማከሩትን፣ የወሰኑትን፣ የሰሩትን፣ የገጠማቸውንና
በቅርብ በዓይን ምስክርነት ያዩትን ተንትነው ያስነብቡናል።
የቅርቡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የዛሬ ዓመት ገደማ ድንገት ሕይወታቸው ማለፉን ስሰማ ካዘኑ ሰዎች አንዱ ነበርኩ። በሥልጣን ዘመናቸው የሠሯቸውን ሥራዎችና የወሰዷቸውን እርምጃዎች ከሚቃወሙና ውሳኔዎቻቸው ለወደፊት ሊያስከትል የሚችለውን አንድምታ ከሚፈሩ አንዱ ነበርኩና ይህ የማላውቀው ስሜት ከየት እንደመጣ
ራሴን ፈተሽኩ። ያዘንኩት አሁን አብሯቸው ለተቀበረውና ውስጣቸው ለቀረው መረጃ ታሪካችን ነበር። እናም ምነው ሥልጣን ቀድመው በለቀቁ፣ ኖረው አስተውለውም በጻፉ፤ የጻፉትንም ባነበብኩ፣ የእርሳቸውንም ዕይታ በቅጡ በተረዳሁ ኖሮ አልኩ።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ለአስራ አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን አብዮት የመሩ፣ ወደ መጨረሻው ከሥልጣን በጡረታ ስም የተሰናበቱ፣ ደርግን በጣለው መንግሥትም ለዓመታት የታሰሩ፣ በወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት የተመላለሱ፣ የሞትም ፍርድ የተበየነባቸውና በኋላም ሕገ-መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት የቀድሞው
ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የሞቱን ፍርድ ወደ ዕድሜ ልክ ስላዘዋወሩላቸው ከሃያ ዓመት እሥራት በኋላ ከእሥር ቤት የወጡ ግለሰብ ናቸው።
በሃያ ዓመታት የእስር ቤት ኑሯቸው ያሰላሰሉትን፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ያብላሉትን፣ በብጥስጣሽ ወረቀቶች የጣጣፉትንና ዛሬ ደግሞ ከእስር ቤት ወጥተው በመጽሐፍ መልክ ጽፈው ያዘጋጁትን እነሆ እናቀርባለን።
በዚህ መጽሐፍ ‘እኛ’ ከሚሏቸው የሥራና የእስር ቤት አጋሮቻቸውን የወል ተግባር ከአርባ ዓመት በኋላ ትናንት እንደሆነ ሁሉ በግልጽ ሲያካፍሉን፡ የተጓደለውን ታሪካችንን በአንጻሩ ያሟላልናል ብዬ ከማመንም ባሻገር እንደዚህ በየታሪክ አጋጣሚው የፖለቲካ አመራር ላይ ከተሳተፉ ግለሰቦች የምናነብበው ታሪክ ዕይታችንንና ግንዛቤያችንን በማስፋት
የታሪካችን ባለቤት ያደርገናልና መልካም ሥራ ነው። በርቱ ተበራቱም ያሰኛል።
ለሃገርና በሃገር ስም በፖለቲካ ድርጅትም ሆነ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ሆነው የሰሩ፣ የታገሉ፣ ያታገሉ፣ የተገለሉ፣ የመሩና የተመሩ ወይም የተማረሩ ግለሰቦች ትናንት ሥልጣን ላይ ለነበሩም ዛሬ ላሉም ሁሉ ‘እናንተስ?’ የሚያስብል ነውና ይኼን ያነበበ ያስተውል፤ የሰማም ያዳምጥ፤ ሥራውንም ይጀምር እንላለን።
የተማረ፣ ያወቀና ያደገ ትውልድና ዜጋ ምልክቱ የተጻፈን ማንበቡ፣ ያነበበውን ማብላላቱና ካነበበው ውስጥ ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየቱ ሲሆን፤ እራሱም አስተውሎና አገናዝቦ መጻፉ ደግሞ መማሩን ብቻ ሳይሆን መመራመሩንና ማወቁን የሚያሳይ ታላቅ ተግባር ነው። ለዚህም ደግሞ ግላዊ ነጻነት ያስፈልገዋልና ጫንቃው ላይ ያሉትን ግላዊና
ታሪካዊ ቀንበሮች የሰበረ ነጻ ሰው መሆን ይጠበቅበታል።
ትምህርትና ዕውቀት አስተዋይነትንና ጥልቀትን ከራስ በላይ ለትውልድ አሳቢነትን የሚያመለክት ታላቅ ኃላፊነት ነው። ለዚህም እንደ ትናንቱ ‘የተማረ ይግደለን’ ሳይሆን፤ የተማረ ያስተምረን፣ ያስተዳድረን ብሎም ይምራን በምንልበት ዘመን ከምናነብበው ውስጥ ያልተስማማንበትን በጨዋነት የመቃወም፣ የፈቀድነውን እንደ ስሜታችን የመደገፍና ተሳሳተ
የምንለውን ለእርማት መጠቆም ግላዊ መብታችን ነው።
ነገር ግን በተቃውሞ ስምና ‘ከኔ በላይ ላሳር’ በሚል ግላዊነት የጽሑፍ፣ የሕትመትና የንባብን ስርጭት ማደናቀፍ ሕገወጥ ከመሆኑም በላይ የሚያሳየው የተግባሩን ፈጻሚ፣ አባሪና ተባባሪዎች አዋቂነት፣ ቀናነትና አስተዋይነት ሳይሆን አጥፊነታቸውን ነውና ከዚህ እኩይ ተግባር እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፤ እንለምናለንም።
ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት መጻሕፍትን በጥራት ለአንባብያን ለማቅረብ የሚያከናውነውን ሥራ በትጋት በመቀጠል ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ በኢትዮጵያ ታሪክና ጥናት ላይ ያተኮሩ አስር መጻሕፍትን አዘጋጅተን በማሳተም ለንባብ አብቅተናል። ለእነዚህም መጻሕፍት ዝግጅት፣ ቅንብርና ስርጭት የየበኩላቸውን ላደረጉና ለሚያደርጉ ተሳታፊ
ባልደረቦቻችን እንዲሁም እንደ እርስዎም ላሉ አንባብያን ሁሉ የከበረ ሰላምታችንና ልባዊ ምስጋናችን ይድረስዎ።
ለዚህ መጽሐፍ መሳካት ተባባሪና ተሳታፊ ለሆኑ ባልደረቦቻችን አቶ አዲስ አዱኛ፣ አቶ ተሾመ ተስፋዬ እና አቶ ክፍሌ ሙላትን ከልብ እናመሰግናለን።
በዚህ አጋጣሚ በተለያዩ የኢትዮጵያ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት ያሳተምናቸውን መጻሕፍት ድረ ገጻችን [www.tsehaipublishers.com]
ላይ በመሄድ እንድትጎበኙ፣ ብሎም ገዝታችሁ፣ አልያም ከቤተ መጻሕፍት ተውሳችሁ እንድታነብቡ እናበረታታለን።
ለሀገራችን ኢትዮጵያ መልካም ምኞታችን ብቻ ሳይሆን፣ ባለን ሞያ ሁሉ ተግባራዊ ጥረታችንም ይሁን። ባለንበት እንበርታ! መልካም ንባብ።
ጤና ይስጥልን!
ኤልያስ ወንድሙ
አሳታሚና አርታኢ
ታኅሣሥ 2006 ዓ.ም tsehay publisher9781599070780-Perfect.indd

፰

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on December 22, 2013
  • By:
  • Last Modified: December 22, 2013 @ 10:01 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar