www.maledatimes.com የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ‹‹ኮማንድ ፖስት›› የተባለ አዲስ አደረጃጀት ሊያስተዋውቅ ነው - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ‹‹ኮማንድ ፖስት›› የተባለ አዲስ አደረጃጀት ሊያስተዋውቅ ነው

By   /   December 24, 2013  /   Comments Off on የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ‹‹ኮማንድ ፖስት›› የተባለ አዲስ አደረጃጀት ሊያስተዋውቅ ነው

    Print       Email
0 0
Read Time:13 Minute, 28 Second

በ

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ በከተማው ውስጥ በሚገኙ አንደኛና  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማር ማስተማሩን ሒደት በጥራት ለማከናወን ይረዳል በማለት ‹‹ኮማንድ ፖስት›› የተሰኘና ሌሎች ተጨማሪ አደረጃጀቶች ሊያስተዋውቅ ነው፡፡

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በዳግማዊ ምንሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በከተማው ከሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለተጠሩ ርዕሳነ መምህራን፣

ሱፐርቫይዘሮችና ከሁሉም ክፍላት ከተሞችና ወረዳ ጽሕፈት ቤቶች ለተወከሉ ኃላፊዎች በአዲሶቹ አደረጃጀቶች ዙሪያ ግንዛቤ የሰጠ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎቹ መካከል በተለይ ርዕሳነ መምህራን ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

የትምህርት ቢሮ ኃላፊው አቶ ዲላሞ አቶሬ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት ትዕዛዝ መሠረት ወደ ታች ትምህርት ቤቶች ዘልቆ ሲሠራበት የቆየው ተጓዳኝ በኋላም ‹‹ግንባር ቀደም›› በመባል ሲተገበር የነበረው አደረጃጀት የታሰበውን ያህል ውጤት ባለማምጣቱ፣ አዲስ አደረጃጀት ማስፈለጉን ለተሳታፊዎች መግለጻቸውን ሪፖርተር የስብሰባው ተሳታፊ ከነበሩ ርዕሳነ መምህራን ለመረዳት ችሏል፡፡

በቅርቡ ወደ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ይወርዳል ከተባለው የኮማንድ ፖስት አደረጃጀት በተጨማሪ፣ ‹‹ትራንስፎርሜሽን ፎረም›› እና ‹‹የልማት ቡድን›› የሚሰኙ አደረጃጀቶችም ይተዋወቃሉ መባሉን  ምንጮች ገልጸዋል፡፡

‹‹ኮማንድ ፖስት›› አደረጃጀት ዋና ተግባሩ ትምህርት ቤቶችን ከሕዝባዊና  ከመንግሥት ክንፎች ጋር ማስተባበር እንደሆነ አቶ ዲላሞ መናገራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የ‹‹ትራንስፎርሜሸን ፎረም›› እና ‹‹የልማት ቡድን›› የተባሉት አደረጃጀቶችም በየትምህርት ቤቱ በሚገኙ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ተግባራዊ የሚደረጉ ሲሆን፣ ‹‹አንድ ለአምስት›› በሚል ስያሜ የተጀመረውን አደረጃጀት ለማጠናከርና ለማስቀጠል ጠቃሚ መሆኑንም እየተነገረ ነው፡፡

ስለአዲሶቹ አደረጃጀት በተለይም ስለ ‹‹ኮማንድ ፖስት›› ከርዕሰ መምህራኑ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ የሰጡት አቶ ዲላሞ፣ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በ‹‹ግንባር ቀደም›› አደረጃጀት በኋላም በ‹‹ተጓዳኝ›› አማካይነት የተከናወነው ሥራ የታሰበውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉ ግልጽ ነው ብለዋል፡፡ ይኼንን በማስቀረት አሁን ‹‹ኮማንድ ፖስት››ን ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማርን ሒደት ለማገዝና የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ‹‹ተጓዳኝ›› የሚባለውን አደረጃጀት ማምጣቱን መንግሥት በተደጋጋሚ ቢገልጽም፣ አንዳንድ መምህራን ግን መንግሥት መምህራኑን ‹‹ለመጠርነፍ›› ሲል ያመጣቸውና ‹‹ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን አላስፈላጊ መሣሪያ›› ነው ሲሉ ይተቻሉ፡፡

ርዕሰ መምህራን ለትምህርት ቢሮ ኃላፊው፣ ‹‹አደረጃጀት በዛ፣ እኛም ለማስፈጸም እየተቸገርን ነው፤›› በማለት ገልጸውላቸዋል፡፡ ያለፈውን ልምዳቸውን በማስታወስ በተለያዩ ጊዜያት የመጡት አደረጃጀቶች ምንም አለመፈየዳቸውን ማስረዳታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ዲላሞ የተነሳውን ጥያቄ ከሰሙ በኋላ የግድ የማሳመን ሥራ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ መምህራኑን አሳስበዋል፡፡

‹‹ምሁራን ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን ለመቀበል ጥያቄ ማንሳታቸውና ምሁራዊ ጥያቄ ማቅረባቸው የማይቀር ምሁራዊ ባህሪ ነው፡፡ በምንም መንገድ ማሳመን የእናንተ የርዕሰ መምህራን ሥራ ስለሆነ የግድ ጥረት ማድረግ አለባችሁ፤›› ማለታቸውን ሪፖርተር ያናገራቸው አንድ የትምህርት ባለሙያ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም አንድ ሪፖርተር ያናገራቸው መምህር ስለአደረጃጀት መብዛት ተጠይቀው ሲገልጹ፣ ‹‹አደረጃጀት በማለት መንግሥት በየትምህርት ቤቶቻችን የሚያመጣብን አሠራሮች ብዙ ጊዜ መምህራን ከማባሳጨት አልፎ የትምህርት ጥራትን የባሰ እየገደለ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ለምሳሌ በ2000 ዓ.ም. አካባቢ ‹‹ግንባር ቀደም›› በሚባል ስያሜ ከድርጅት አባላት የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እነሱ በትምህርት ጥራትና በማስተማር አፈጻጸም የተሻሉ እንደሆኑ በመውሰድ ሌሎች ነባር መመህራን ችሎታ እንደሌላቸው  ለመቁጠር ሲሞከር ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የድርጅት አባል ያልሆነ መምህርን የማስተማር ሞራል ሲጎዳ በመቆየቱ በትምህርት ጥራት ላይ ትልቅ ችግር ፈጥሯል፤›› ካሉ በኋላ፣ ይኼን ለማሻሻል ብለው ስሙን በመቀየር ‹‹ተጓዳኝ›› በማለት ሌላ ቡድን ቢፈጠርም፣ ‹‹ምንም ዓይነት ጥቅም ሊያመጣ አልቻለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መምህራኑ የ‹‹አንድ ለአምስት›› አደረጃጀትን ከማስፈጽም ባሻገር አንድ ርዕሰ መምህር ዘጠኝ ዓመታዊ ዕቅዶችን ስለሚያወጣ  በማመር ማስተማሩና በመምህራን ላይ ጫና ያመጣል በማለት ይተቻሉ፡፡ አንድ ርዕሰ መምህር ዋናውን የትምህርት አገልግሎቱን ከመምራት በላይ ሪፖርት በመጻፍና ዕቅድ በማውጣት ጊዜውን ያሳልፋል ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች መንግሥት ‹‹አንድ ለአምስት›› በሚባለው አደረጃጀት ኅብረተሰቡን በተለይም ሲቪል ሰርቫንቱን ቀፍድዶ በመያዝ ለዲሞክራሲ ዕድገት የሚያደርገውን ትግል ለማክሸፍ እየተጠቀሙበት  ነው በማለት ይከሳሉ፡፡ በቅርቡ የመድረክ የወቅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር መራራ ጉዲና በዚህ ጉዳይ ላይ ወቀሳ መሰንዘራቸው ይታወሳል፡፡

መንግሥስት የ‹‹አንድ ለአምስት›› አደረጃጀት በስፋት በሁሉም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በስፋት እየገፋበት መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለጸ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይኼንን አደረጃጀት አጠናክሮ እንደያዘው መረዳት ተችሏል፡፡ በተለይ ለምክር ቤቱ ከሥራ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ሪፖርቶች በሚቀርቡበት ወቅት በምክር ቤቱ አባላት በሚነሱ ጥያቄዎችም ሆነ በሚሰጡት አስተያየቶች ‹‹አንድ ለአምስት›› አደረጃጀት ቀዳሚ ሥፍራ ከሚሰጣቸው አበይት ጉዳዮች መካከል መሆኑ በተደጋጋሚ እየተስተዋለ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በርከት ያሉ የአሠራርና የማሻሻያ አደረጃጀቶችን ሲያስተዋውቅ ቆይቷል፡፡  ከእነዚህም መካከል «ተሃድሶ፣ ሪፎርሜሽን፣ መሠረታዊ የሥራ ሒደት (BPR)፤ የልማት ሠራዊት፣ ውጤት ተኮር፣ ተማሪን ያማከለ የማስተማር ሒደት፣ የትምህርት ጥራት ፓኬጅ» የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on December 24, 2013
  • By:
  • Last Modified: December 24, 2013 @ 2:56 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar