www.maledatimes.com ይድረስ ለነጥበበወርቅዬና መሰል የ“ጌታ ልጆች” ትንቢት ደረሰ – ከኢትዮጵያ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ይድረስ ለነጥበበ ወርቅዬና መሰል የ“ጌታ ልጆች” ትንቢት ደረሰ – ከኢትዮጵያ

By   /   December 30, 2013  /   Comments Off on ይድረስ ለነጥበበ ወርቅዬና መሰል የ“ጌታ ልጆች” ትንቢት ደረሰ – ከኢትዮጵያ

    Print       Email
0 0
Read Time:34 Minute, 40 Second

                    በአሁኑ ቅጽበት በኢቢኤስ ቴሌቪዥን አንድ ፕሮግራም እየተከታተልኩ ነው፡፡ ጥበበ ወርቅዬ የሚባለው አቀንቃኝ ማሊያ መለወጡንና የነበረበትን ሕይወት እየኮነነ፣ እየተራገመ፣ እያጣጣለና ሌሎች ጓደኞቹም የርሱን ፈለግ እንዲከተሉ እየጸለየ መሆኑን ከአንደበቱ ሰማሁ፡፡ ግሩም ነው፡፡ አዳሜ የልቧን ካደረሰች በኋላ የበፊት ሕይወቷን እየተጸየፈችና በዓለማዊነት እየፈረጀች “ወደተዘጋጀላት የዘላለም ሕይወት” ጎራ ትላለች – “እኛን ጭቃ ውስጥ ጥላ”፡፡ ይህ የጥበበ ወርቅዬ መንገድ አዲስ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም ብዙዎች ነጉደውበታል፡፡ መንገዳቸው አጽዳቂ መሆን አለመሆኑ እኔን አሁን አይመለከተኝም፡፡ መጽደቅ በሃይማኖት ሸሚዝ መለዋወጥ መሆን አለመሆኑን መግለጽም አይገባኝም፡፡ አነሳሴ ሌልኛ ነው፡፡ ሃይማኖት ለዋጮችም ሆኑ አስለዋጮች በጥንቃቄ እንዲሰሙኝ እሻለሁና ትንሽዬ ትኩረት ልለምን፡፡ መልካም የገና በዓል ግን፡፡ “እህሉ አንድ ዓይነት ሴቱ አሥራ ሁለት” የሚል ብሂል አሁን ለምን ትዝ እንዳለኝ እንጃ ብልጭ ብሎ ጠፋብኝ፡፡

በቅድሚያ አንዲት ምናልባትም ሁለት የትግርኛና የአማርኛ ሥነ ቃላዊ ትውፊቶችን ላስታውስ፡፡

ቀዳሚዋን የትግርኛዋን ላድርጋት፡፡ “ዝአክለን ጥህነን በዓል ማርያም ትብል” የምትለዋ ዛንታዊ አነጋገር ከትግርኛ ተረትና ምሳሌዎች ውስጥ በጣም ትመስጠኛለች፡፡ ወዳማርኛ ስትመለስ “የሚበቃትን ያህል ከፈጨች በኋላ ‹ውይ! ለካንስ ዛሬ ማርያም ናት› ትላለች” እንደማለት ነው፡፡ ሰዎች ስንባል አስመሳዮችና እስስቶች ነን፡፡ በጣም የምንገርም ፍጡራን ብንኖር ሰዎች ነን፡፡ በዚያ ላይ ማይምነት የሚባለው ቀንደኛ ጠላታችን ሲደመርብን የአስመሳይነታችንና የአጭበርባሪነታችን ደረጃ ወደር አይገኝለትም፡፡ ሁለተኛዋን ልጨምርና ወደቀሪ ትንተናዬ ልሂድ፡፡

አንድ ጀግና ጎልማሣ በበቅሎው ተሣፍሮ ረጂም ጫካ እያቋረጠ ነው፡፡ አንዱ ሥፍራ ላይ ሲደርስ እጁን ወደ ወገቡ ልኮ የሽጉጡን መኖር አለመኖር ሲያረጋግጥ ሽጉጡ የለችም፡፡ ያኔ በድንጋጤ ክው ይልና ለጭንቅ አማላጇ ለእመብርሃን እንዲህ ሲል ይሳላል፡- “ወላዲተ አምላክ፣ ያቺን ሽጉጤን ካስገኘሽልኝ አንድ ድፎ ዳቦና አንድ ጋን ጠላ በዕለተ ቀንሽ በተስኪያን አስገብቼ ለካህናት ግብር አበላለሁ” ይላል፡፡ ከዚያም በመጣበት መንገድ በዙሪያ ገባ ቅኝት ሽጉጡን እየፈለገ ወደኋላው ይመለሳል፡፡ ጥቂት ኪሎሜትሮችን እንደተጓዘ ማንም ሳይነካበት መንገዱ ላይ ወድቃ እያብለጨለጨች ያገኛታል፡፡ ዐይኑን አላመነም፡፡ እንደሕጻን በደስታ እየቦረቀ ከበቅሎው ወርዶ ብድግ ያደርጋትና “እመቤቴ ድንግል ማርያምዬ፤ አግኝቻታለሁና አትቸገሪ፤ ቅድም የነገርኩሽን ተይው” ብሏት ዕርፍ – ስለቱን ላለማስገባት፡፡ “ዱሮስ ያበሻ ነገር” ልል ነበር ፕሮፌሰር መስፍን የወሩን ኮታ ስድብና ዘለፋ ባለፈው ሰሞን ከበቂ በላይ ስላስታጠቁን ይቅርብኝ፤ ልተወው፡፡ የወደቀን የሚረባረብበት አያጣም፡፡ (እሳቸው ሰው ግን ምን ነካቸው? ዕውቀት ሲበዛ ያናፍል ይሆን? በአሉታዊ ነቀፌታዎች ያጥረገርጉን á‹«á‹™ እኮ! ደግነቱ ዳኛቸው ቢያድግልኝ የተባለ የሳይበርዎር የመስመር መኮንን በቀደምለት ተገቢ አምላሽ ሰጥቷቸዋል፡፡ ግን አንዘከርባቸው፤ ማርጀትም፣ ተስፋ መቁረጥም፣ የአሁኑ ኢትዮጵያዊነትም አንዴ ሣር አንዴ አፈር እያስደረጉ አቅልን ያስታሉና ብዙም አንፍረድባቸው፡፡ ይሄውና እኔስ ጨርቄን የመጣል ያህል በነጥበበ ነገር ተነክቼ የለም?)

አዎ፤ ጥበበ ወርቅዬ በዚያ የኢቢኤስ ቶክሾው ላይ ስመለከተው እውነቴን ነው እምላችሁ የሰው ልጅ ባጠቃላይ አስጠላኝ፡፡ ሰውን ምን ነካው?  ሃይማኖቱን በቀን አሥር ጊዜም ይለዋውጥ – የራሱ ጉዳይ ነው፡፡ የሚድንበትንና የሚጠፋበትን ሊያውቅ የሚችል ባለቤቱ በመሆኑ በተለይ ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነን ሰው በዚህ እመን ወይ በዚያ አትመን ብሎ መከራከር አይቻልም ብቻ ሳይሆን እንደዚያ ለማድረግ ማሰብ ራሱም ሞኝነት ነው፡፡ ግን ግን “እኔ የተቀበልኩትን አዲስ ሕይወት እናንተም ግቡና ቅመሱት፤ እኔ አዲስ ፍጡር ሆኛለሁ፤ እስካሁን የነበርኩበት ሕይወት የጨለማና የአጋንንት ነበር፡፡ እንደጠፋችሁ አትቅሩ …” ብሎ በአደባባይ ማወጅ የመጨረሻ ቂልነት ነው፡፡ ደግሞስ “ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ”  እንዲባል ማን ነው ማንን ሊኮንን የሚችል? የቀረበለትን ምግብ አስተካክሎ መጉረስ የማይችል ደንቆሮ ሁላ ሞቅ ባለውና የተጠጋው መንፈስ ምን ይሁን ምን ለይቶ ለማወቅ በማይቻለው ሁኔታ በስሜት ታውሮ እንደተልባ ቢንጣጣ እውነት ነው ሊባል ነውን? ምንድነው ይሄ እያስተዋልነው ያለነው የተዘበራረቀ ነገር ሁሉ? ወዴት እያመራን ነው?

ጥበበና መሰል አዲስ መንገደኞች ለውጣቸው የምር ከሆነ የልባቸው እስኪደርስና በሀብት እስኪደረጁ ምን አስጠበቃቸው? “ከመረቁ አውጡልን፤ ከሥጋው ጦመኞች ነን” ባዮቹ እነጥበበ ወርቅዬ ለውጣቸው እውነት ከሆነ በ‹ሰይጣን መንገድ ተጉዘው› ያከማቹትን ገንዘብና ጠቅላላ ሀብት ለምን ለሕዝብ ወይም ለድሃ አይመልሱም? ያኔ ነው እውነትም አዲስ ፍጡራን፣ አዲስ የኢየሱስ ልጆች እንደሆኑ የማምነው፡፡ አለበለዚያ እያንዳንዷ የልቧን ከሠራች በኋላ፣ በሀብትና ጥሪት ከደረጀች በኋላ፣ ሽንጣም አውቶሞቢል ከገዛችና በተንጣለለ ግቢ ቪላዋን ገጭ ካደረገች በኋላ ‹መንገዴን ለወጥኩ፤ ከአሁን በኋላ የማዝነው በሰይጣናዊ የዓለም መንገድ ለሚጓዙ ጓደኞቼ ነው› ቢሉ የሚታመኑ እንዳይመስላቸው – እንዲህ ማለት ራሱ ከጅልነት በበለጠ ወንጀልም ይመስለኛል፡፡ የመልካሙ እረኛ  አዲስ ተከታይ መሆንን ከመረጡ ክርስቶስ እንዳለው በኃጢኣት ያከማቹትን ሀብትና ንብረት መካድ አለባቸው – ወደመጣበት መመለስ፡፡ ያን የኃጢኣት ገንዘብ ወዲያ አሽቀንጥረው ጥለው በአዲስ መልክ “ሀ” ብለው አዲሱ መንፈስ በሚያዛቸው መሠረት ፍሬያማ ሥራ ሠርተው መክበር ወይም መክበርም ስለማይፈቀድና አግባብም ስላልሆነ ለመኖር ብቻ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ነው ሊያገኙ የሚገባቸው፡፡ በአሁኑ መንገድ ግን ሊያጭበረብሩ አይገባም፡፡ ማጭበርበር ትልቅ ኃጢኣት ነው፡፡ በ “ሰይጣን ገንዘብ” እየተምነሸነሹ የገንዘብና የዝና ምንጭን መናቅና ማንጓጠጥ ወይም በጠፍነት መፈረጅ ከዲያብሎስነት ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡

ከመጽሐፍ አንድ ነገር ልጥቀስ፡፡ አንድ ሰው ወደኢየሱስ ይቀርባል፡፡ “ጌታ ሆይ፤ መንግሥተ ሰማይን ለመውረስ ምን ላድርግ?” ብሎ ክርስቶስን ይጠይቀዋል፡፡ “ጓደኛህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ” ይለዋል፡፡ “እሱንማ ከልጅነቴ ጀምሮ የማደርገው ነው” ብሎ ይመልሳል፡፡ “እንዲያ ከሆነማ ደግ ነው፤ ስለዚህ አንተ ማድረግ ያለብህ ያለኽን ሀብትና ንብረት ለድሆች አከፋፍልና እኔን ተከተለኝ” ይለዋል፡፡ ያኔ ሰውዬው ለሀብቱ ሳሳና አመነታ፤ ሸሸም፡፡ በዚያን ጊዜ ነው ክርስቶስ አንዱን ግሩም አባባሉን “ሀብታም መንግሥተ ሰማይ ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል” ብሎ የተናገረው፡፡ እነጥበበም ማድረግ ያለባቸው በኋጢኣት ያከማቹትን ሀብት መንግሥት የለንም እንጂ ለመንግሥት ወይም በጎ አድራጎትም በቅጡ የለንም እንጂ ለበጎ አድራጎት አለዚያም ድሃው አለቅጥ በዛ እንጂ ለድሃ በመስጠት ባዶ እጃቸውን ነው አጨብጭበው ለጌታ ማደር ያለባቸው፡፡ በሁለት ቢላዎ መብላት ነውር ነው፡፡ የልብን ከሞሉ በኋላ በከበሩበት ሕዝብና የኪነ ጥበብ ታዳሚ ላይ እርጥብን ከደረቅ እያዛነቁ በአጓጉል ሰባኪነት ማሽቃነጥ አግባብ አይደለም፡፡ ቢያንስ ያስተዛዝባል፡፡ ከዚያም በላይ፡፡

ይህን የምለው አካሄዳቸው ስለሚያስጠላኝና ልክም ስላልሆነ ነው፡፡ በየሥርቻው ስለሚገኝ የሃይማኖት ህፀፅ መናገር ብፈልግ አይቸግረኝም – የሚነገር የብልግናና የጠያፍ ምግባር አብነት እስከጥግ ድረስ  ሞልቷል፡፡ እነማን ምን እንደሚያደርጉ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ሃይማኖትን እንደሸቀጥ በመቁጠር የገቢ ምንጭ የሚያደርጉ ጳጳሳትን፣ ፓስተሮችን፣ ኢማሞችን፣ ራባዮችንና ዳላይለማዎችን በነቂስ እየለዩ ገመናቸውን መዘክዘክ አይከብድም – በሌቦች ብዛት ዓለማችን ታምታ አታውቅም፤ ያጣነው እውነተኛ ሰው ነው፤ ያጣነው ከብልጭልጩ ዓለም በተቃራኒ የሚጓዝ ሃቀኛ መሲሕ ነው፡፡ ዓለማችንን እያጠፉ ያሉ እነሱ ማለትም አታላዮቹ የውሸት እረኞች መሆናቸውን አናውቅም አንልም፡፡ ግን ግን ዝም ማለታችን እስከዚህ ድረስ የልባቸው በሞላ ደናቁርት ሊያስንቀንና ሊያስወርፈን አይገባምና አንዳንዴ መናገር ልክንም ማሳየት ጥፋት አይደለም፡፡ እንደነሱ መሆን ቢያምረን ኖሮ ዓለም ያላት ሁሉ ነገር እኛም ዘንድ  በኖረ ነበር፡፡ ግን ሁሉም ከንቱና የከንቱ ከንቱ መሆኑን ከመገንዘብ አንጻር በሚሆነውና እየሆነ በምናየው ነገር እየተደነቅን በ “ቶባቶብቱልላህ” ቁዘማ አለን – የ‹ቂያማ ቀን›ን በጉጉት እየተጠባበቅን፡፡        ዘመኑን ታዲያን ልብ በሉ፤ በአስተውሎት አጢኑ፡፡ ሰይጣን እሳት ከሰማይ እስከማዝነብ የሚደርስ  ሥልጣን ተሰጥቶታል – ቀድሞ የተነገረውን ነው አሁን እዚህ ላይ እማስታውስ፡፡ የዘመናችን ሃይማኖት አቶ ብሩ ናቸው፡፡ አቶ ብሩ ወይም አቶ ገንዘቡ በሰዎች ውስጥ እየሰረጸ ሃይማኖትን ካለኮፒራይት እያባዙ መሸጥ ይቅርና ከዚህ የከፋ የዓለምን ዕልቂት እስከማስከተልም ይደርሳል፤ የጥበበ ወይም የሂሩት ወይም የሙሉቀን ወይም የተፈራና የሌሎች ወንድምና እህቶቻችን የመጨነቅ መንስኤና ውጤት ይገባናል – በዘመኑ መድረስም ልናላክክ እንችላለን፡፡ በአሁኑ ወቅት በኣራቱም አቅጣጫዎች ዓለማችንን ብናይ ዲያብሎስ የመጨረሻ የሚመስል ተልእኮውን በእንደራሴዎቹ አማካይነት የ‹ፀሐይ ግባት› ዘመቻውን በማፋጠን ላይ ይገኛል፡፡ ዛሬ ማታ አንድ ዓለም አቀፍ ቲቪ ሥር ቁጭ በሉና ከደቡብ ሱዳን እስከ አፍጋስታን፣ ከሶማሊያ እስከአላስካ በየቀኑ እየተከሰቱ ያሉ አጃኢብ የሚያሰኙ ወንጀሎችንና የጦርነት ዐውዶችን ልብ በሉ፤ በዛሬ ጊዜ የጽድቅ ሥራ እንጂ የሚያስወነጅል የኩነኔ ሥራ የተፈቀደ ያህል ከነውርነት ወጥቶ ይፋ ተለቋል፡፡ ለመሆኑ የሰላምና የልማት ዜና አልናፈቃችሁም?

የአስገድዶ መድፈር (ወንድንም ሴትንም ሕጻናትንም አእሩጋንንም ያጠቃልላል)፣  የግድያ ወንጀል፣ የዘር ማጥፋት፣ የርሀብና የጦርነት፣ የዘር መድሎ፣ የሙስናና ዘረፋ፣ የፍትህ መዛባትና የሰብኣዊ መብት ድፍጠጣ … አሳዛኝ ዜናዎች ከብርቅየነት አልፈው የዓለማችን የዕለት ከዕለት ነባራዊ ክስተት መሆናቸው ምንን ይጠቁማል? በዚህ ጊዜ ታዲያ የጥበበና መሰሎቹ በሃይማኖት ስም ማጭበርበር ምን ያስገርማል ብትል የራስህ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ግን ያልኩትንና የምለውን ብዬ ልጨርስ ነው፡፡

ሃይማኖት ለዋጮች ለውጡ፡፡ ስትለውጡ ግን በጥበብና በሥልት ይሁን፡፡ የበላችሁበትን ወጪት ደግሞ አትስበሩት፡፡ ትዝብት ውስጥ ድርግም ብላችሁ አትግቡ፡፡ ሁሉም እንደናንተው ደንቆሮ ከመሰላችሁ ልክ አይደላችሁም፡፡ የሚያውቅብን የለም ብላችሁ ከሆነም ስህተት ነው፡፡ ዝም እየተባላችሁ እንጂ ጓዳ ጎድጓዳችሁን እናውቃለን፡፡ “የዝምብን ልጃገረድ በሚያውቅ” ማኅበረሰብ ውስጥ መኖራችሁን ዘንግታችሁ እንደዚያ እሰው ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ እንዳለው ገልቱ ጅብ ለመሆን ካላማራችሁ በስተቀር “ሕይወቴ ከአሁን በኋላ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ መንፈስ ተሞልታለች፡፡ ጌታ እንደገና ፈጠረኝ …” እያላችሁ ራሳችሁን አሞኝታችሁ ሌላውን ልታሞኙ አትሞክሩም ነበር፤ ዘመናችን የመብልና መጠጥ እንዲሁም የአእምሮ ሰላም አሳጣን እንጂ የሃይማኖት ብፌ አላሳጣንምና በከንቱ አትጨነቁልን – ጭንቀታችሁን በከንቱ አታባክኑ፡፡ ጌታ የሚገኘው በሥራ፣ በፍቅርና በእምነት እንጂ በስብከት ብዛትና በጎራ መቀያየር አይደለም – አጭር ቃል፡፡

ሃይማኖት መለወጣችሁ የማታልፉት ጣጣ ከሆነባችሁ ደግሞ በኃጢኣት ያፈራችሁትን ገንዘብና ሀብት ንብረት ወደመጣበት የኃጢኣት ሥፍራ አንድም ሳታስቀሩ መልሱ፡፡ በዚህ ቀልድ የለም፡፡ ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን በአንድ ጊዜ ልትወዱ አትችሉም፤ አይገባምም፡፡ “በማን ላይ ቆመሽ ኢየሱስን ታሚያለሽ” እንዲሉ ነውና በምትንፈላሰሱበት መኪና ውስጥ የኔ አንዲት ብር አለችበት፤ በምቾት በምትኖሩበት ቤት ውስጥ የኔ አንዲት ብር አለችበት – ያቺ አንዲት ብሬ ደግሞ የኃጢኣት ፍሬ ስለሆነች ለአዲሱ ሕይወታችሁ አትመቻችሁም – ትቆረቁራችኋለችና እርሷን ሳትመልሱ ተለወጥን የማለታችሁ ዜና የሞራል ብቃት የማያላብሳችሁ ጉንጭ አልፋ ነው፡፡ ለአነጋገሩ ጠያፍነት ይቅርታና “‹ሽንት ቤት› ውስጥ ተቀምጦ ፈስ ገማኝ” ዓይነት መሆን ካላሰኛችሁ አንደበታችሁን ቆጠብ አድርጉና በቤተ አምልኮኣችሁ ብቻ የምትሉትን በሉ፡፡ “በሰው ሞራል አትረማመዱ”፡፡ በመሠረቱ በቦሌም ይሁን በባሌ የእናንተ መጽደቅ ያስደስተናል – ዋናው የሚፈለግ ነገር መጽደቃችሁ ነውና፡፡ የማያስደስተን ነገር በኛ መዋጮ ከከበራችሁ በኋላ እኛን እንደወንጀለኛና ኃጢኣተኛ፣ እናንተን ግን እንደነቢዩ ዳዊት ጻዲቅ እያደረጋችሁ መቁጠራችሁ ነው – ንስሃ የሚያሻው ታላቅ ስህተት፡፡ ስለዚህ አንዱን ተውልን፡፡ ገንዘባችንንም ጽድቁንም አትውሰዱብን፡፡ ሙያ በልብ ብላችሁ እዚያችው ቤተ አምልኮኣችሁ ውስጥ የሚመጡላችሁን ዜጎች ብቻ እንደፍጥርጥራችሁ አድርጓቸው፡፡ ይጽድቁባችሁ፤ ጽደቁባቸውም፡፡ “ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት” አሉ?

በአንድ ጊዜ ብዙ ዐወደ ግንባር መክፈት ደግ አይደለም እንጂ ከሃይማኖት አኳያ ብዙ መናገር በተቻለ ነበር፡፡ ግን ግን እንዲህ ሳልል ብቀር ሆድ ሆዴን ይበላኛልና እንዲህ ብዬ ልሰናበት፡፡

አዲስ አበባ ላይ በንግድ ስም ሕዝብን እየዘረፉና የደም ዕንባ እያስነቡ ከህግና ከኅሊና ዳኝነት ውጪ በሚሰበሰብ ገንዘብ ሐረር ወርደው ቁልቢን በገንዘብ ቢያሽሩ ፅድቅ አይገኝም፡፡ ሕዝብን በሥውር ቆንጨራ እያረዱ በሚገኝ ገንዘብ ቤተ ክርስቲያን ቢያንጹና ንዋየ ቅድሳትን ገዝተው ቢሰጡ ፈጣሪ ሞኝ አይደለምና የመንግሥተ ሰማይን ቁልፍ በቀላሉ እንደማይሰጥ ማወቅ ይገባል፡፡ የዱሮ የአውሮፓ  ካህናት በኢንደልጀንስ ካርድ ሕዝብን ያጭበረብሩ ነበር፡፡ አሁንም ብዙ የብዙ የክርስትና ሃይማኖት ዘርፍ ካህናትና የእምነቱ መሪዎች በሕዝብ እየተጫወቱ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ሰውን ማታለል ቀላል ነው – አንዴም፣ ሁለቴም፣ ሦስቴምና ከዚያም በላይ፡፡ የብርሃን አምላክ የሆነውን እግዚአብሔርን ማታለል ግን ፈጽሞውን አይቻልም፡፡ ይህንን እውነት ጊዜው ሲደርስ ብንነጋገርበት የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ለአሁኑ ግን የእግዜርን ለእግዜር፣ የቄሣርን ለቄሣር ብሎ መተው የተሻለ ነው፡፡ አናደበላልቅ፡፡ የልባችን ሲደርስ ደግሞ አንዱ አንዱን አይኮንን፡፡ በአንዱ ወጪ ሌላው “ለመጽደቅ” አይሞክር፡፡ ኤፌሶን ገላትያ እያልኩ ማምታታት አልፈልግም፡፡ ነገር ግን መዝፈን ከአሥራ አምስቱ መንግሥተ ሰማይን የሚያስከለክሉ ነገሮች ውስጥ አንዱ መሆኑን ለመረዳት በግድ በሙዚቃ ከብሮ መገኘትን እንደማይጠይቅ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ስንተዋወቅ አንተናነቅ፡፡ ይህን የምለው ማንንም የሃይማኖት ዘርፍ ለመደገፍ ወይም ለመቃወም አይደለም፤ ጣፋጭ ፍሬ ከዛፍ ላይ እንዳለ ያስታውቃልና በጎራዎችና በክፍልፋይ መጠሪያዎች ራሴንም ሆነ አስተሳሰቤን ልቀነብብ እንደማልፈልግ መግለጽ እወዳለሁ፡፡ መዳን የት እንዳለች ከመገመት ውጪ በትክክል የሚያውቅ ሰው ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ስለዚህም የሚከተለው ሃይማኖት ብቸኛ የመዳኛ መንገድ እንደሆነ የሚያምን ሰው ሲገጥመኝ አዝንለታለሁ፤ መልካም ነገርን በሚሠራ ግን እቀናለሁ፡፡ የየትኛውም እምነት ተከታይ ይሁን በፍቅር ስለፍቅር መልካም ነገርን የሚያደርግ ይህ ሰው ወደመዳን እንደቀረበ እገምታለሁ – ሰውነት ይቅደም፤ ከሁሉም በፊት በሰውነት ማመን ትልቁ ሃይማኖታችን ሊሆን በተገባው፡፡ ክፋትን ከሰውነት እውጥቶ መጣልና አንዳችም የዘርም ሆነ የቀለምና ሌላ ገደብ ያልተበጀለት ፍቅርን ለፍጡራን ሁሉ ማሳየት ትልቁ ሃይማኖት እንደሆነ ከግምት ባለፈ እረዳለሁ፡፡ ራስን በዶክትሪንና ዶግማ አጥር እያጠሩ አንዱን እንደውዳቂ ሌላውን እንደጸዳቂ ማድረግ ሰውኛ እንጂ አምላክኛ አይደለም፡፡ አንድ ፈጣሪ ፍጡራኑን በምንም መለኪያ አይለያይም – ነጣም ጠቆረ፣ ረዘመም አጠረ፣ ደኸዬም ከበረ፣ … ሁሉም ከርሱና ወደርሱ ነውና ለርሱ የኛ ተፈጥሯዊ መለያየት ጉዱዩም አይደለም ብዬ አምናሁ፡፡ እኛው በኛው በምንሠራቸው ሕጎችና ደንቦች የልዩነት አጥር አበጅተን በከንቱ እንቧቀሳለን እንጂ ፈጣሪ ለሁላችንም እኩል ነው፡፡ “እህሉ አንድ ዓይነት ሴቱ አሥራ ሁለት”፤ በድጋሚ አእምሮየ ውስጥ ብልጭ አለብኝ፡፡ አቶ ብሩን ግን እግዜር ይይለት! በሃይማኖት እንኳን በአሥር ሺዎች እኮ ነው የከፋፈለን – ለዚያውም አንዱም ላይረባ! የፈጣሪን ትዕዛዛት በትክክል የሚያከብር ቢያንስ አንድ የሃይማኖት ጎራ ቢኖረን ኖሮ የዓለማችን ችግር በግማሽ ሊቀንስ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ የስብከት ቃላትንና አለባበስን በማሳመር ወይም ታላላቅ ካቴድራሎችን በመገንባት ወይም ከአንዱ ዘርፍ ወደሌላው በመንከባለል ብቻ ቁሣዊም ይሁን መንፈሣዊ ችግር የማይወገድ በመሆኑ ግን እያየን የምንገኘውን የዓለም ቅርጽ እንድናይ ተገድደናል፡፡ ወዮ ለመጨረሻችን!!

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on December 30, 2013
  • By:
  • Last Modified: December 30, 2013 @ 9:53 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar