www.maledatimes.com ይድረስ ለጋሽ ያሬድ ጥበቡ ( አብዮተኛ አንቱ አይባልም መሰል) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ይድረስ ለጋሽ ያሬድ ጥበቡ ( አብዮተኛ አንቱ አይባልም መሰል)

By   /   February 17, 2014  /   Comments Off on ይድረስ ለጋሽ ያሬድ ጥበቡ ( አብዮተኛ አንቱ አይባልም መሰል)

    Print       Email
0 0
Read Time:18 Minute, 40 Second

ጸሃፊ ሶሊያና

ያሬድ ጥበቡ

እንደምን ከርመሃል? ትላንትና እንደአጋጣሚ ሆኖ እንቁ መጽሄት ላይ የሰጠኅውን ቃለ መጠይቅ አነበብኩት፡፡ ከዚያ ደገምኩት፡፡ ከዚያ በሶሰተኛው ይህንን ደብዳቤ ልጽፍልህ ተነሳሁ፡፡ ይህንን የአብዮቱን 40 አመት የሚዲያ ጋጋታ አንገቴን ደፍቼ በዝምታ ላሳልፈው ፈልጌ ነበር፡፡ አንተ ተናገርክና አናገርከኝ፣ ተናግሮ አናጋሪ ሲመጣ እድሉን መጠቀም ነው ብየ ይህንን ጻፍኩልህ፡፡

እንደአጋጣሚ ስልህ መቼም መጽሄት እንኳን አንብባ እማታውቅ ሴት እንዴት አውቃኝ ለደብዳቤ ተነሳች ትል ይሆናል፡፡ ይኅውልህ እኛ ጋር ሚዲያ የሚባለውን ነገር ነፍስህ ይማር ብለን ከተሰናበትነው ቆይተናል፡፡ ብዙዎች ኑሮ ውድነቱ የተስፋ መቁረጡ ምክንያት አድርገው ሲያነሱት ሰምተህ ይሆናል፡ነገሩ ግን ከዚያ በላይ ነው፡። ተስፋ መቁረጥን ፌት ከሰጠኅው የምታነበው ደህና ሚዲያ ስታጣ ተስፋ ትቆርጣለህ፡፡ ይኅው ስንት ጊዜ ሆነኝ መሰለህ ከማገላበጥ ባለፈ በቁም ነገር የምቆጥረው ህትመት ከጠፋ፣ አልፎ አልፎ የአንተ አይነቱን ሰው ይዘው ሲወጡ ካልሆነ ከተጠፋፋን ቆይተናል፡፡ እሱ ብቻ አይምሰልህ ፣ ውይይት የሚባል ነገር ከአገሪትዋ ከጠፋ ከራርሞአል ፡፡ አገር ሙሉ ለመነጋገር መሞከር ሲያቅተው እኛ የመጀመሪያው ምሳሌ ሳንሆን አንቀርም ፡፡ በውይይት ላይ ተስፋ ከቆረጥኩ ቆየሁ፡፡ ቸልተኝነቱ ተስፋ ያስቆርጣል ፣ አንዳንዴ ሳስበው አንዲህ አይነት ምንም ጉዳይ ጉዳዩ የማይመስለው ህዝብ ሌላ አገርም አለ? እንዲህ አያገባኝም ላይ ደርሶ ጠንካራ ተሻካሚ እስኪሆን የት ነበርን ? ከአብዩቱ በፌት የነበሩትን ጊዜያት በደምብ ማወቅም የምፈልገው ለዚያ ነበር፡፡ ይሄ ህዝብ መቼም ይህንን ጭቆና እንቢ የሚል አይመስልም ብላችሁ ተስፋ ቆርጣችሁበት ነበር? ወይስ መሪ ብቻ ነው የሚፈልገው ብላችሁ ነው የተነሳችሁት? ተስፋ መቁረጥ በተስፋ መሞላት ለመተካትስ ስንተ ጊዜ ይፈጅበታል? ወይስ ይህ አዲሱ ህዝባዊ በሽታችን ነው? ተስፋ መቁረጥ በዚህ ብቻ አይደለም፣ ቢዘረዘር የማያልቅ ሆኖልሃል፡፡ በናንት ጊዜ መማር አንዴት ተስፋ እንደሆነ ታስታውሳለህ አይደል? አባቴ ሲነግረኝ መማር ነው ነጻ የሚያወጣው ይል ነበር፡፡አሁን ግን በትምህርቱም ተስፋ ከቆረጥን ከራረምን? ትምህርት ነጻ እንደማያወጣ ከተሰማን ማን ነጻ ሊያወጣን ነው? ብቻ ባጭሩ ተስፋ መቁረጥ ወደባህሪነት እያደገብን ሳይሆን አይቀርም የሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እገኛለሁ፡። ብቻ ይሄንን ደብዳቤ ስጽፍልህ ሃሳቤ የእኔን ተስፋ መቁረጥ ለማጋባት አልነበረም ፡፡ ይልቅስ ያልካቸው ሁለት ጉዳዪች ቀልቤን ወስደውብኝ እንጂ እውነቱን ለመናገር የአብዮቱን ውጤቶችና ኪሳራ ላይ የማልጋራቸው ሃሳቦች አንስተሃል፡። ግድ የለም የትውልድም የሚና ልዩነትም የስሜት ቅርበትም ተጨምሮበት ጥቂት ባንስማማ አይገርምም ፡። እኔ ማነኝና አንተ ነፍስህን ስለሰጠህላት አብዮት አፌን ሞልቼ እወቅሳለሁ፡። ለእኔ የአብዮቱ ትልቅ ኪሳራ መማሪያ ለመሆን እንኳን አለመብቃቱ ይመስለኛል፡፡ 40 ሙሉ ሳንማርበት ለመቅረታችን ደሞ አሁን ላለንበት ሁኔታ በላይ ምንም ማስረጃ የለም፡፡ አናንተ ያነገባችሁት የብሄር ጥያቄ ዛሬም ከ40 አመት በሁዋላ በቃላት እያታኮሰን ( መሳሪያ ቢሰጡን ከናንተ ባንብስ ነው?) እያየሁ ፣ ባለህበት እርገጥ የሆነ ታሪካችንን እያነብኩ አባቴ ያወራበትን አንተ የተዋጋህበትን ጉዳይ እኔም ከጓደኛየ ጋር ስኮራረፍበት መማር አለመቻላችንን ምነው እንደኪሳራ ሳታነሳው አለፍክ ? የእናንተ ትውልድ መፍታት ባለመቻሉ የተሻለች ኢትዮጲያን ባለማስረከቡ ልወቅሰው ባልነሳም ቢያንስ ቢያንስ አሁን የሄድንበትን 40 አመት ባለህበት እርገጥ እንደኪሳራ ብትጠቅሰው እወድ ነበር፡።

ይህንን ደብዳቤ ያጻፈኝ ዋናውን ንግግርህ ግን 

“አየህ ከብሄረሰቦቹ ድርጅቶች ካቋቋሙት ግለሰቦች ጋር በጦር ሜዳ እስከሞሻለቅ ድረስ ውጥረት ውስጥ ገብተን የነበረ ቢሆንም ያንን አልፈን ከአረጋዊ ፣ከስብሃት፣ከሌንጮ ከዲማ ጋር ቁጭ ብለን በማውራት በምንስማማባቸው መለስተኛ ፕሮግራሞች ተስማምተን በጋራ መስራት አንችል ነበር፡። ሆኖም የብሄረሰቦች ድርጅቶች ለህልውናቸው ማጠየቂያነት አፈታሪኮች የምር ተቀልብሰው መድረኩ ላይ ብቅ ያሉት ልጆቻቸው ግን አባቶቻቸውን ብሌን እየደነቆሉ ፌታቸው ላይ እየተፉ የሚገሰግሱ ሆነዋል፡። የኔ ትውልድ ኢትዮፒያውያን ከቀድሞዎቹ መሪዎች ጋር ተቀምጠን እንደምናወራው የእናንተ የወጣቶቹ ትውልድ ያንን ማድረግ የማትችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ይመስለኛል፡።” የሚለው ነው ፡።

በጣም ቢያሳዝነኝም ከዚህ ንግግር ጋር መቶ በመቶ ሳልስማማ አልቀረሁም፡። አሁንም ቢሆን በተወሰነ መልኩ ለዚህ መነጋገር የማይችል ትውልድ መፈጠር ሃላፌነቱን ለመውሰድ ፍቃደኝነት ማሳየት ያለባችሁ ይመስለኛል፡። የትውልዳችሁ አፈታሪክ ለምን ፌታቸው ላይ እየተፉ የሚሄዱ ልጆችን ፈጠረ ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ከልጆቹ እኩል አባቶቹን ቢቀየም እንዴት ተብሎ ማለት አይኖርባችሁም፡፡ ከላይ እነዳነሳሁት ከእናንተ የማይማር ትውልድ መፈጠሩ የአብዩቱ ኪሳራ ከመሆኑ ጋር ልትደምረውም ትችላለህ፡፡

አብዩቱ ሁልጊዜም በለቅሶ የሚነሳውም እንዲሁ አይደለም፡፡ እውነቱን እንናገር ከተባለም የመጀመሪያው የእንባ ዘለላ የሚመጣው ከእናንተው ከራሳችሁ ነው፡፡ ስለናንተ የተጻፈ መጽሃፍ ምረቃ ፣ እናንተን ለመዘከር የተቋቋመ ሙዝየም ጉብኝት፣ ስለእናነተ የሚያወራ ውይይት ስለእናንተ የተጻፈ ጽሁፍ መነሻውም መድረሻውም ለቅሶ ነው፡፡በድል ያልታጀበ መስዋእትነት መጨረሻው ለቅሶ ነውና አይግረምህ ለማለት ያህል ነው፡፡ እንኳን እናንተ እኛም ስናነበው እናለቅሳለን፡፡ የሚለቀስለት ትውልድ መሆን ምን ይመስላል? መቼም ለቅሶም ሳቅም ከሌለው ትውልድ ከመሆን ሳይሻል አይቀርም አይደል?
ከዚህ በፌት ስለእናንተ ስናወራ ለትምህርትነት እንጂ ለአርአያነት አትበቁም ብየ ነበር፡፡ አሁንም ሃሳቤን የቀየርኩ አይመስለኝም፡። ድሮ ድሮ ስለእናንተ ሳነብ በጀብደኝነታችሁ እቀና ነበር፣ ቀጥሎ መስዋእትነታችሁ ይስበኝ ነበር፣ በሁዋላ ትካዜ እንጂ ሌላ ትርፍ እያጣሁ ተቸገርኩ፡፡ አሁንም ከዚያ ስሜት እየወጣሁ አይመስለኝም፡፡ ከትውልዱ እንዴት እንደምንማር ግራ ገብቶን ደጋግመን ታሪኮቻችሁን የምንሰማ ሰዎች ቀላል አይደለንም፡፡ ብዙዎቻችንም በበቂ ሁኔታ ከእናንተ ሳንማር ስታለቅሱ እና ስትጣሉ እያየን ሌላ ትውልድ የመፍጠር ሃላፌነት ውስጥ እየገባን ነው፡፡ ይህ የአለመማማር አዙሪት ከ40 አመትም በላይ ሳያስከፍለን አልቀረም፡፡ መማር ሲያቅተን ከህዝቡ እንደአንዱ እየሆንን ቸልተኛነታችንን ወደማባበሉ እየተመለስን ነው፡፡ በትውልዳችሁ የመጨረሻ ዘመን ልታደርጉ የምትችሉት ትልቁ አስተዋእጾም ራሳችሁን ለመማሪያነት ሙሉ ለሙሉ ማቅረብ ይመስለኛል፡፡ እስቲ ሁሉንም እርግፍ አድርጋችሁ ትታችሁ የሆነች የመማማሪያ መድረክ ነገር አዘጋጁና ከስልጣን እና ተያያዥ ጉዳዩች የራቀ የቀሪ እድሜ ፕሮጀክት አድርጉት፡፡ ብዙ ወጣቶችን ከመክሸፍ ማዳኛ አንዱ መንገድ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ወደ ሁዋላ ለመሮጥ ለተዘጋጁ ለእንዴ አይነት ሰዎችም የተስፋ ምልክት ይሆናል፡፡

ትላንት ካነሳኀው ነገር አንዱ የማኅበረሰባዊ ችግራችን ነው፡። ከፓለቲካውን አሁን የሚበጠብጠው የግራ አስተሳሰብ ሳይሆን የቆየ የማህበረሰባዊ መግባባትና የመነጋገር ባህላችን ችግር መሆኑን አንስተሃል፡፡ እሱ ሁሉንም የሚያስማማ ሃሳብ ይመስለኛል፡፡ የእኔ ጥያቄ ያን ግዜም ይህ ማህበረሰባዊ ችግር እነደአንዱ አብዮታዊ ችግር አይታችሁት ነበር ወይስ ከእድሜ ጋር የመጣ ትምህርት ነው? እሱስ ቢሆን እንዴት ቢሆን ይስተካከላል? መቼም እንደመንግስት የሚቀይሩት ነገር አይደለም አይደል?

ጋሽ ያሬድ ከዚህ ሁሉ ወሬ ይልቅ ከአንተን ማንበቡ ደስ የሚለው ሰው ሰው የሚል የግል እይታ ስለምትጨምርበትም ነው ፡፡ ትዝ ይልህ ከሆነ ስለምርኮኛ አውራምባ ታይምስ ላይ ስትጽፍ ራስህን ውስጡ ከተህ ነበር፡፡ ያሬድን ፍለጋ ነበር ምርኮኛን ያነበብኩት፡፡ ትላንትና ስለጆሊ ባር ስታወራ ጆሊ ባር ታድሶ ታጥሮ የእኛ አይነቱ ሰው የማይገባበት ማታ ማታ ከፍተኛ ኑሮ ነዋሪዎች መኪና የሚደረደርበት ቦታ መቀየሩን እንዳልሰማህ ገባኝ፡፡ የአብዮቱ ክፋቱ አንተን ከታሪክህ አንተን ከትዝታህ ሩቅ አድርጎ ማስቀመጡ ለውጡን እያየህ ፈግግ/ ኮስተር እንድትል አለመፍቀዱ ነው፡፡ ጆሊ ባር ዛሬ ሰው በበሩ አያልፍም፡፡ አገራዊ ጉዳይ የሚያወሩ ጥቂት ወጣቶች በረንዳው ላይ ተሰብስበው ቡና አይጠጡም ምናልባት ምናልባት የአየር በአየር ንግዳቸውን አጧጡፈው ለዚያ ቤት መግባት ከቻለው ሊግ ሊቀላቀሉ ይጥሩ ይሆናል አንጂ

ጋሽ ያሬድ አንድ ቀን ከተሳካልን ጆሊ ባር ቢከብደን እንኳን ትሪያኖን በረንዳ ላይ ተቀምጠን የምጠይቅህ ጥያቄ ነበረኝ፡፡ ከእነዚያ አመታት የሚቆጭህ እንደዚያ ባላደርገው ኖሮ እንዲህ አይሆንም ነበር የምትለው ነገር የለም? ሳስበው ሳስበው ይህ ጥያቄ በታማኝነት ከተመለሰ ብዙ የሚያስተላልፈው ትምህርትና መልእክት ይኖረዋል፡፡ ለዛሬ ግን በቀይ ቀለም ያሳመርከው ጆሊ ባር ምን እንደሚመስል ፎቶውን አያይዥ ልኬልሃለሁ፡፡ ዘንድሮ እንደሆነ እጃችን ላይ ቀይ ቀለም ሳይሆን በየቦታው ፎቶ የሚያነሳ ካሜራ ነው ያለው 

አክባሪህ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on February 17, 2014
  • By:
  • Last Modified: February 17, 2014 @ 9:52 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar