www.maledatimes.com የየካቲት 12ቱ – ጥቋቁር ሰማዕታት! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የየካቲት 12ቱ – ጥቋቁር ሰማዕታት!

By   /   February 17, 2014  /   Comments Off on የየካቲት 12ቱ – ጥቋቁር ሰማዕታት!

    Print       Email
0 0
Read Time:35 Minute, 0 Second

(አናብስቱ በተኩላዎቹ ተሰለቀጡ-ወዮ! ወዮ! ወዮ!)

 
(በሰሎሞን ተሰማ ጂ.)
ከጥቁሩ ሰማይ ሥር፣ ባፍሪካ ትቢያ ላይ፤
በጥቁር ሕዝብ ርስት፣ ባፍሪካ ኮከብ-ጣይ፤
በጠራራው ቀትር፣ ባውላላ አደባባይ፤
የጥቁሮች ደም ፈሷል፣ ለቅኝ-ግዛት ሲሳይ፡፡
ለነጭ የዛር ግዳይ፣ ለዘር ምሱ አዋይ!
ፀሐይንም ጋርዷት፣ ጥቁር መጋረጃ፤
ምድርም ተጎናጽፋ፣ ጥቁር ከል-ስጋጃ፤
ጥቁሩ ዓለም ተግቷል፣ ያዘን-መከር ቀንጃ፡፡
(ግጥም፣ በሰ.ተ.ጂ)
የኢትዮጵያና የአፍሪካ አኅጉር መናገሻ ከተማ በሆነችው በአዲስ አበባ ውስጥ ካሉት ሃውልቶች መካከል፣ አምስቱ በኢትዮጵያና በኢጣሊያን መካከል በ1886ዓ.ም እና በ1928-1933ዓ.ም ለተደረጉት ጦርነቶች የድልና የግፍ መታሰቢያ የታነጹ ናቸው፡፡ አራዳ ጊዮርጊስ የሚገኘው “የአዱዋን ድል” የምንዘክርበትና አራት ኪሎ አደባባይ ላይ የቆመው “የሚያዝያ 27ን የነፃነትና የድል በዓል” ለመዘከር የቆሙ ሁለት ሃውልቶች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ለገሀር የሚገኘው “የይሁዳ አንበሳ” ሃውልት ደግሞ በፋሺስት ኢጣሊያን በ1928ዓ.ም ዘርፎ ተወስዶ የነበረና፣ በጥቅምት 23/1955ዓ.ም እንደገና ተመልሶ የቆመ ነው፡፡ አሁን በባቡር መስመር ግንባታ ሰበብ የተነሳውና በአምስት ኪሎ ብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ የቆመው የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልትም አራተኛው ማሳያ ነው፡፡ አምስተኛውና በቁመት ከሁሉም ጠሚበልጠው ደግሞ፣ በ1951ዓ.ም በዩጎዝሎቫያው ፕሬዝዳንት ማርሻል ዴኒስ ቲቶ ልዩ ድጋፍ እንደገና የቆመው የስድስት ኪሎው “የየካቲት 12ቱ ሰማዕታት” መታሰቢያ ሃውልት ነው፡፡ ሁለት የድል ማብሰሪያ ሃውልቶች፣ እና ሦስት የመከራና የእልቂት መዘከሪያ ሃውልቶች ቆመዋል፡፡ (በዛሬው መጣጥፋችንም ስለዚህ ስለአምስተኛው ሃውልትና ሊዘክራቸው ስለቆመው በመቶ ሺዎች ሲለሚቆጠሩት ሰማዕታት ይሆናል፤ መልካም ንባብ እንደሚሆንላችሁ እንመኛለን፡፡)
የካቲት 12 ቀን 1929á‹“.ም የዋለው በዕለተ ዓርብ ነበር፡፡ ሩዶልፎ ግራዚያኒ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ   ረፋድ 4፡00 ሰዓት ላይ፣(ከቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ መልስ) በገነተ-ልዑል ቤተ መንግሥት ፊት-ለፊት (የዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6ኪሎ ካምፓስ ፏፏቴው ጋር ነው፤) እንዲሰበሰቡ አዘዘ፡፡ ለነዲያንና ለችግረኞችም ለእያንዳንዳቸው ሁለት-ሁለት ሊሬ እንደሚሰጥ ጭምር አስለፈፈ፡፡ ነገር ግን፣ “ልክ በ4፡00 ሰዓት ይጀምራል” የተባለው ፕሮግራም  እስከ 4፡55 ድረስ ሳይጀመር ቀረ፡፡ ሰበቡም የግብፃዊው አቡን፣ (አቡነ ቄርሎስ፣) “ታምሜያለሁ!” ብሎ በመቅረቱ/በመዘግየቱ የተነሳ ነበር፡፡  እስኪመጣም ድረስ የዕለቱ መርሃ-ግበር ለአንድ ሰዓት ያህል  ዘገየ፡፡ ወታደሮች ተላኩና አበኑ ልክ 4፡55 ሲሆን ቤተ መንግሥት ደረሰ፡፡ ወንበር መጣለትና ከግራዚያኒ በስተቀኝ በኩል፣ ከከፍተኛዎቹ የፋሺስት ባለስልጣናትም ጎን ተቀመጠ፡፡ ከግራዚያኒም በስተግራ በኩል ጄኔራል ጋሪባልዲ፣ ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ (የአፄ ዮሐንስ የልጅ-ልጅ)፣ ራስ ኃይሉ(የጎጃሙ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት ልጅ) እና ከሌሎች ባንዶችም ጋር ተጎልቶ ነበር፡፡ ልክ 5፡00 ሲል ግራዚያኒ ሻኛው እንዳበጠ ኮርማ ቁና-ቁና እየተነፈሰ ኢትዮጵያውያንን ያበሻቅጥ ጀመር፡፡ “ይኼው አለሁ!… ሞቷል እያላችሁ የምታወሩትና የምታስወሩት ኹሉ ከንቱ ሟርት ነው፡፡” እያለ የኢትዮጵያን ሕዝብ በገዛ አገሩና በገዛ መሬቱ ላይ ያዋርደው ጀመር፡፡ (ግራዚያኒና ተባባሪዎቹ የነበሩበት ቦታ ወደ ራስ መኮንን አዳራሽ መግቢያ በር ላይ ያለው-የቤተ መንግሥቱ በረንዳ ላይ እንደነበር ልብ ይሏል፡፡)
ልክ 5፡15 ሰዓት ገደማ ሲሆን አብራሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም (የተባሉት ሁለት የኤርትራ ክፍለ-ሀገር ተወላጆች) ከበረንዳው በላይ ባለው ፎቅ ላይ/ግራዚያኒ ከቆመበት ሥፍራ ላይ ጥቁር ሸሚዝ (ፋሺስቶች ለባንዶች ያለብሱት የነበረውን ወታደራዊ/የአስካሪስ ልብስ) ለብሰው፣ኩታቸውን ተከናንበው ታዩ፡፡ ዓይኖቻቸው በንቃት ይንተገተጋሉ፡፡ ልክ 5፡30 ሲሆንም ለነዲያን ምጽዋት መሠጠት ተጀመረ፡፡ በሥፍራው ከሦስት ሺህ ሁለት መቶ (3,200) በላይ ነዲያን ተሰብስበው ነበር፡፡ እንዲሁም ግብር-ሊበሉ የመጡ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ግራዚያኒና ግብረ-አበሮቹ ከቆሙበት ስፍራ በአሥር ወይም አሥራ ሁለት ሜትር ርቀት ላይ ከበው ቆመዋል፡፡ ከሰዎቹም ፈንጠር ብለው ከዘጠና የማያንሱ መትረየሳቸውን የደገኑ ሶላቶዎችና አስካሪዎች በተጠንቀቅ ቆመዋል፡፡ ነዲያኑን ከበረንዳው አካባቢ ራቅ እንዲሉ ይገፏቸው ጀመር፡፡ ጫጫታና ውካታው ከፍ ብሎም ለአስር ደቂቃዎች ያህል ተሰማ፡፡
ነገር ግን፣ ኢያን ካምፔል (Ian Campbell; “The Plot to Kill Graziani”. ብሎ በ2003ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፉ ውስጥ እንደዘገበልን ከሆነ፣) በግምት ከ5፡40 እስከ 5፡45 ድረስ ባሉት አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ተከታትለው ቦንቦች እነአብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ካሉበት ደርብ ላይ ቁልቀል ተወረወሩ፡፡ የመጀመሪያው ቦንብ እንደተመረወረ፣ ብዙዎቹ ታዳሚዎች  ለስብሰባው ማድመቂያ መድፍ የተተኮሰ ነበር-የመሰላቸው፡፡ ሁለተኛው ሲወረወር ግን፣ አቡነ ቄርሎስና ግራዚያኒ መሬት ያዙ፡፡ በስተ-ግራ በኩልም ያሉት ሁለት ጥበቃዎች ወዲያውኑ ሞቱ፡፡ ሦስተኛውም ሲወረመር፣ ግራዚያኒ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሊገባ ፊቱን አዙሮ መሸምጠጥ ጀምሮ ነበር፡፡ ሆኖም፣ የሦስተኛው ቦንብ ፍንጣሪዎች አቆሠሉት፡፡ ዳኒሎ ብቢሪንዴሊ የተባው የካሜራ ባለሙያም እየደማና እያቃሰተ የነበረውን ግራዚያኒን ከወደቀበት አንስቶ፣ ከ5፡50 እስከ 6፡00 ባሉት አስር ደቂቃዎች ውስጥ ወደ መኪናው ከተተው፡፡ በፍጥነት ወደ “ኦስፒዳሌ ኢታሊያኖ” (“የጣሊያ ሆስፒታል” ለማለት ነው፤ የዛሬው “ራስ ደስታ ሆስፒታል” መሆኑን ልብ ይሏል፤) ወሰዱት፡፡
ከየካቲት 12 ቀን 1929á‹“.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓትም ጀምሮ እስከ የካቲት 14 ቀን 1929 á‹“.ም ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ድረስ ከሰላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በግፍ ተፈጁ፡፡ (የሚነገረው ቁጥር በአዲስ አበባ ብቻ የተፈፀመውን ግድያ የሚያሳይ ብቻ ነው፡፡ በደብረ ሊባኖስ ገድምና በዝቋላ አቦ የተረሸኑትም መነኮሳትና ምዕመናን እጅግ በርካታ ናቸው፡፡) በ1934á‹“.ም የመጀመሪያው የየካቲት 12ቱ ሰማዕታት መታሰቢያ በዓል በተከበረበት ዕለት የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ክስተቱን እንዲህ ሲል ነበር የዘገበው፤ “ያቺን ቀን እናስባት፤ አንርሳት፡፡ የኢትዮጵያ ሰማዕታት የክብር አክሊል የተቀበሉባትን፣ ደማቸው እንደጎርፍ በግፍ የፈሰሰባትን፣ ሥጋቸው እንደክትፎ የተከተፈባትን፣ አጥንታቸው እንደገል የተከሰከሰባትን፣ ዕለተ-ዓርብን፣ ያቺን ቀን አንርሳት!…መቼም የዕለተ-ዓርብ መከራና ሃዘን ማለቂያ የለውም! አስቀድሞ፣ ንጹሑ ክርስቶስስ በዕለተ-ዓርብ በ33á‹“.ም አልነበር የተሰቀለው!? የካቲት 12/1929á‹“.ም ደግሞ ሁለተኛው የንጹኃን ደም በከንቱ የፈሰሰበት ዕለት ኾነ፤” እያለ ይቀጥላል፡፡
የዚህም ጊዜ አርበኞቻችን ነቁ፤ ቆፍጠን ብለውም ታጠቁ! የደረሰው ግፍ፣ የተፈፀመው የግፍ-ግፍ አበረታቸው፡፡ የነጭ ፋሺስቶች ግፈኝነት እንደእግር እሳት መላ-አካላታቸውን አንገብግቦት ኖሮ፣ኢትዮጵያ እየበረታች ሄደች፡፡ ጥቁሮቹን አርበኞች፣ በከንቱ የተከነበለው “የጥቋቁሮቹ ሰማዕታት” ደም አጀግኗቸው ኖሮ፣ ከሸዋ እስከ ሽራሮ፣ ከኦሜድላ እስከ ቆራሄ፣ ከሞያሌ እስከ ዠማ፣ ከዱር-ቤቴ እስከ ሚሌ አንጠራወዛቸው፤ አንቀሳቀሳቸው፡፡ “የጥቋቁሮቹ ሰማዕታት” ደም እጅግ ንሮና ግሞ፣ የፋሺስትን ሃይል ይለበልበው ገባ፡፡ ራስ አበበ አረጋይ፣ ራስ መስፍን ስለሺና ወንድማቸው (ሌ/ጄኔራል) ደጃ/ች ይልማ ስለሺ፣ ደጃ/ች አባ ኮራን፣ ፊት/ሪ ገረሱ ዱኪ፣ ፊት/ሪ ገለታ ቆሪቾ፣ ፊት/ሪ በቀለ ወያ፣ ልጅ ጃጋማ ኬሎ፣ ደጃ/ች ፀሐይ እንቄ-ሥላሴ፣ ደጃ/ች ተሾመ እንቄ-ሥላሴ፣ ራስ ስዩም መንገሻና ባለቤታቸው፣ እና ሌሎችም ሆነው ከያሉበት የጣሊያንን ወራሪ ለመመከት ተንቀሳቀሱ፡፡ የሸዋው፣ የወሎው፣ የጎጃሙ፣ የጎንደሩ፣ የትግራዩ፣ የከፋው፣ የጋሞ-ጎፋው፣ የኢሉ-አባቦራው፣ የሲዳሞው፣ የአሩሲው፣ የሲዳሞው፣ የባሌውና የሐረርጌው ባንድነት ሆነው ከገጠር እስከ ከተማ ተንቀሳቀሱ፡፡ አንገዛም አሉ፡፡ የገጠሩና የከተማው ህዝብም ባንድነት ስለተረዳዳም፣ “አለሁ! አለሁ!” ይል የነበረው የፋሺስት ጦር እንደሌለ ሆነ፡፡ ኢምንት ሆነ፡፡ (ሕዝብ ሲተባበርና ሲረዳዳ፣ “አለሁ! አለሁ!” የሚሉ ግፈኞችና ጨቋኞች የሉም፡፡ መረዳዳቱና መተባበሩም በጦርነትና በጭንቅ ሰዓት ብቻም ሳይሆን፣ በአንፃራዊ ሰላምም ወቅት መደገም እንዳለበትም ለማስታወስ እንወዳለን፡፡)
ይህ በእንዲህ ሳለም፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት፣ በፋሺስት ኢጣሊያ ስላለቁት ወገኖቻችንና ስለደም ካሳቸው በተመለከተ ጥያቄ ማቅረብ የጀመረው ከ1936ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ ጥያቄውን የበለጠ ፖለቲካዊና ዓለማቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው አድርጎ፣ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ ወደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተቀየረበት የመጀመሪያው ዓመት ላይ፣ (በ1938ዓ.ም) የኢትዮጵያ መንግሥት ለመንግሥታቱ ማኅበር ሦስት ጥያቄዎችን አቅርቦ ነበር፡፡ “አንደኛ፣ ለኢጣሊያ ፋሺስታዊ መንግሥት ወረራ መነሻ የሆኑት ጥንታዊ ክፍለ-ሀገሮች ኤርትራና ሱማሊያ፣ ለኢትዮጵያ እንዲመለሱላት፤” የሚል ነበር፡፡ ሁለተኛ፣ “ለተቃጠሉት አብያተ-ክርስቲያናት፣ ለተበረበሩትና ለተዘረፉት ንዋየ-ቅዱሳት፣ ለተደመሰሰው የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብትና ንብረት፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በግፍ ለተሰውት ከ750ሺህ በላይ ንጹኃን ኢትዮጵያውያን ሕይወት፣ የኢጣሊያን መንግሥት ካሳ እንዲከፍል፤” የሚጠይቅ ነበር፡፡ ሦስተኛው ጥያቄ ደግሞ፣ “በኢትዮጵያ ለተፈጸሙት ወንጀሎች ኹሉ ዓብይ አርእስት ሆኖ የሚገመተው በግራዚያኒ መሪነት የተፈፀመው የየካቲት 12/1929ኙ ዓ.ም ዕልቂት፣ ከማናቸውም የፋሺስት የግፍ ሥራዎች ኹሉ ከፍተኝነትና ኢ-ሰብዓዊነት ስላለውም፣ ጭፍጨፋው እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡት የጦር አዛዦችና ግብረ-አበሮቻቸው በሙሉ፣ ፍርዳቸውን ግፉን በሰሩበት ቦታ እንዲቀበሉና ግፉ ስለተፈፀመባቸውም ወገኖቻችን የደም ካሳ እንዲከፈል፤” የሚጠይቅ ነበር፡፡ በኹሉም/በሦስቱም ጥያቄዎች ውስጥ ገኖ የሚታየው ጥያቄ፣ “የጥቁሮቹ ሰማዕታት” ጩኸት ነው፡፡
ሆኖም ግን፣ በሚያዝያ 19/1940ዓ.ም ኢትዮጵያ (ያን ጊዜ፣ በምክትል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በነበሩት-ክቡር አቶ አክሊሉ ሀብተ-ወልድ አማካይነት) ያቀረበችው አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡ ይህንም ውሳኔ እንደኔዘርላንድና ኢራን የመሳሰሉት አገሮች በፓርላማዎቻቸው አቅርበው አጸድቀውታልም፡፡ ነገር ግን፣ የኢጣሊያና የሮማንያ መንግሥታት ባቀረቡት ይግባኝ መሠረት፣ (ለመንግሥታቱ ዋና ፀሐፊ ባስገቡት ማመልከቻ መሠረት፣) ጉዳዩ እንደገና እንዲመረምር ተደረገ፡፡ ከዚያንም ጊዜ ጀምሮ፣ እስካለንበት ዘመን ድረስ እንደተዳፈነ ነው፡፡ ይባስም ብሎ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ “ጭፍጨፋው እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡት የጦር አዛዦችና ግብረ-አበሮቻቸው በሞላ የጦር ወንጀሉን በፈጸመበት ቦታ/ሀገር ፍርዳቸውን መቀበል ይገባቸዋል፤” ብሎ ያመለከተውን እግዚኦታ ከቁብም ሳይቆጥሩ፣ ለዚያ የተኩላ ልጅ (የሚላኑ መስፍን) ብለው ሃውልት አቆሙለት፡፡ ይህ አባዜ፣ የነጩ ዓለም ለጥቁሮች ያለውን ከፍተኛ ንቀትና መዘባበት የሚያሳብቅ ነው፡፡ መረሳት የሌለበት ግዙፍ እውነት ከፊታችን ተገትሯል፡፡ እርሱም የያንኪዎቹና የያፌታውያኑ ናላ፣ ለእኛ ለካማውያን ወንድሞቹ ያለውን አሉታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህንን ሃሳብ በተከታዮቹ አንቀፆች አማካይነት ላብራራው እወዳለኹ፡፡
ነጮቹ ያፌታውያን፣ የቀይ ሕንዶቹን ከምድረ-ገጽ ጠራርገው ሲያጠፏቸው ለታሪክና ለህሊና ለመታሰቢያ የሚሆን ሃውልት አላቆሙላቸውም፡፡ ያንን ዘረኛና ኢ-ሰብአዊ ግፍ የፈፀሙትም አረማዊዎች አልተጠየቁም፡፡ ነጮቹ ያፌታውያን፣ ባህር አቋርጠው ሄደው አውስትራሊያ ያሉትን የአቦርጂኒያ ጥቁሮች ሲደመሷቸውም ተመሳሳይ መታሰቢያ አላቆሙላቸውም፡፡ ለመቶ ዓመታት ያህል የአውሮፓ የባህር ላይ ወንበዴዎች (Pirates) እጅግ ቆፍጣናዎቹንና ጡንቸኛዎቹን ወጣቶች እየፈነገሉ ለሸንኮራ አገዳ ቆረጣና ለእረኝነት ሲወስዷቸው የጮኸ የለም፡፡ ያንን ግፍና ኢ-ሰብዓዊ በደልም የሚዘክር በቂ ስነ-ጽሑፍና ኪነጥበባዊ ሥራ አልተሰራላቸውም፡፡ (ታላቁ ዚቀኛ ሼክስፒር እንኳን (The Tempest) በተባለው ተውኔቱ አማካይነት በአፍሪካውያኑ ላይ የተደረገውን የባሪያ ፍንገላ ልዩ እውቅና ሰጥቶታል፡፡) ከኩሽ ቤት/ከሊቢያና ከሞሮኮ የሄዱት ኩርዶች፣ ቫስኮችና ጂብሲዎችም በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ አገር-አልባ ሆነው፣ ከሰብዓዊ ፍጡር በታች ተደርገው ሲኖሩ ማንም ከመጤፍ አልቆጠራቸውም፡፡ ማንም ታሪካዊ መሬታቸውንና ግዛታቸውን አልመለሰላቸውም፡፡ ደቡብ አፍሪካ-ሱዎቶ ላይ በጠራራ ፀሐይ የተጨፈጨፉትን ጥቁር አፍሪካውያን የሚዘክር አንድም እንኳን ፊልም አልተሰራላቸውም፡፡ ሃውልትም አልቆመላቸውም፡፡ ነገር ግን፣ በ1983ዓ.ም በጥቁር ወንድማማቾች መካከል የተደረገውን የሩዋንዳና የቡሩንዲውን (የሁቱና ቱትሲ) ሰብዓዊ ዕልቂት፣ አንዴ “የዘር ማጥፋት! Genocide” ሌላም ጊዜ የዘር ማጥራት! Ethnic Cleansing” ወዘተርፈ የሚል ቅጽል ስም እየሰጡ፣ በሆሊውድና በሌሎችም ተቋሞቻቸው አማካይነት ይሸቅሉበታል፡፡ መጽሐፍ ጽፈውም ይቸበችቡታል፡፡ ሩዋንዳውን የቡሩንዲውን፣ የአንጎላውን፣ የዛየር ኮንጎውን፣ የላይቤሪያውን፣ የሱማሌያውን፣ የሱዳኑንና የዚምባቡዌውን ችግር ከመጠን በላይ እያጋነኑ በማቅረብ ለካም ቤት ያላቸውን ንቀትና ፌዝ ይግቱናል፡፡
ነገር ግን፣ የቦሲኒያውና የሄርዞ-ጎቪኒያው ጉዳይ ሲመጣ ሌላ ሽፋን ይሰጡታል፡፡ የሃይማኖት መለያየት የፈጠረው ጣጣ እንደሆነ ሊሰብኩን ይጣጣራሉ፡፡ አለያም ደግሞ የርዕዮተ-ዓለም ግጭቶች ጣጣ ውጤት እንደተፈጠረ አድርገው ሊያሳምኑን ይፍጨረጨራሉ፡፡ ይህ ዘረኛና ከያፌታዊ ትምክህት የመነጨው አስተሳሰብ ነው፤ በተለያየ ዘመን በከንቱ የተሰውትን ጥቋቁር ሰማዕታት ደመ-ከልብ ያደረጋቸው፡፡ በየትም ቦታ ጥቁሮች ለያፌታውያንና ለአንዳንድ ቡርዣ ሴማውያን አሽከርና አገልጋይ ሆነው የምጽዓት ጊዜ እንዲደርስ ይፈለጋል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችልበት መጠነኛ እድልም አለው፡፡ የካም ቤት ተከፋፍሎና ተበታትኖ ነው ያለው፡፡ ታላቁ ንጉሠ ነገሥታችን አፄ ኃይለ ሥላሴና እነአቶ ከተማ ይፍሩ የተለሙትን አፍሪካንና መላውን የጥቁር ህዝብ አስተባብረን እንዲረዳዳ ማድረግ ካልቻልን ያፌታውያኑ እንደልባቸው ይፈነጩብናል፡፡ አንዳንድ ሴማዊ ቡርዣዎችም፣ እንደባሪያ ፈንጋይ እየሆኑ፣ ሴቶቻችንን ለጭን-ገረድነት፣ ወንዶቻችንንም ለዘበኝነት ይዳርጓቸዋል፡፡ (እንዳጋጣሚ ሆኖ፣ በአሜሪካንም-ይህ ወር የጥቁሮች ወር ነው፡፡ በአፍሪካ ደግሞ ትልቁ የጥቁር ህዝብ ድል የተበሰረበት የአዱዋም ድል የሚከበረው በዚሁ ወር ነው፡፡ በተጨማሪም ትልቁ የጥቁር ሕዝቦች ኢ-ሰብዓዊ ጭፍጨፋም የተካሄደበት ወር ነው፡፡ በመሆኑም፣ በመላው ዓለም ያሉትን ጥቁሮች፣ በከንቱ ስለቀሩት “ጥቋቁር ሰማዕታት” ጋራ ልንጮኽላቸው ይገባናል፡፡)
ማጠቃለያ፤
በሀገራችን የኖረ አባባል አለ፤ እንዲህ የሚል ነው፣ “በእጅ ያለ ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል፤ ወይም እኩል ነው፤” ይባላል፡፡ የባርነትን ዋጋ ባንቀምሰው ኖሮ፣ የነፃነትን ዋጋና ጣዕምም አናውቀውም ነበር፡፡ በነፃነት ደጃፍ መኖርን የለመደ ሰው፣ ከባርነት ይልቅ ሞትን ይመርጣል፡፡ ለኢትዮጵያውያንንና ለመላው የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች የባርነትን ብርቱ ስቃይ ከሚያሳዩት ቀኖችም አንዱ “የየካቲት 12ቱ የጥቋቁር ሰማዕታት”በዓል ነው፡፡ ከሰባ ስምንት ዓመታት በፊት በጥቁር አፍሪካውያን ላይ የተፈጸመው ግፍ ያዩት ሰዎች እጅግ ነው የሚያንገፈግፋቸው፡፡ የብሔራዊ ነፃነታችን ምልክት የሆነው ሰንደቅ ዓላማችን በኢትዮጵያና በአፍሪካ አኅጉር መናገሻ ከተማ በማይውለበለብብት በዚያ የባርነት ወቅት፣ በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ እንኳን ከሰላሳ ሺህ በላይ ዜጎች አልቀዋል፡፡ ሰንደቅ ዓላማችን በግፍ ወርዶ የፋሺስት ባንዲራ ከተካው አስር ወር እንኳን ሳይሞላው፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ኃዘን ሰፍኖ ነበር፡፡ ህዝቡ አቀርቅሮ መሄድ ጀምሯል፡፡ ኩራት የለም! እራትም አልነበረም፡፡ አለኝታ የለም፤ ገበያና አደባባይም ወጥቶ በሰላም ለመመለስ ዋስትና አልነበረም፡፡
የጥቁር ህዝብ የድል-ብስራት ማወጃ የሆነችው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በባርነት ሥር ሆነው እጅግ ተሳቀዋል፡፡ በባርነት ስር ያለ ህዝብ ማናቸውም ነገር ሊደርስበት ይችላል፡፡ ቢታሰር፣ ቢረገጥ፣ በሰደብ፣ ቢደበደብም ሆነ ቢገደል ለምን ብሎ መጠየቅ አይችልም፡፡ ምክንያቱም፣ በባርነት ቀንበር ሥር ያለ ህዝብ ማናቸውም መዓት ይደርስበታላ! በባርነት ሥር ያለ ህልውና በእርግጥ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በነፃነት መኖር ሕይወታችን ነው፡፡ ኑሯችን ነው፡፡ በነፃነት መሥራት፣ በነፃነት ማሰብ፣ በነፃነት መማርና በነፃነት መብትን የማስከበር ልዩ ትዕምርት አለን፡፡ ልዩ ባሕልም አለን፡፡ እነዚህ ከሌሉ ሕይወታችን የለችም፡፡ “ያለነፃነት የምንኖር ከሆንን፣ እንደሮቦት የምንንቀሳቀስ ሕቁራን (Inferior) ፍጡሮች ነን፤” ማለት ነው፡፡ ከዚህ ሕቁርነት ሰውሮን፣ የጥቁሮቹን ሰማዕታት ደም ሕያው ለማድረግ ያብቃን!….       
( በአዲስጉዳይ መጽሔት፣ በቅጽ 8 ቁጥር 203፣ ቅዳሜ የካቲት 8፣ 2006 ዓ.ም ዕትም ላይ የወጣ ነው፡፡  http://semnaworeq.blogspot.com   Email: solomontessemag@gmail.com
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on February 17, 2014
  • By:
  • Last Modified: February 17, 2014 @ 2:33 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar