www.maledatimes.com ብር እና ክብር !(ቴዲ አትላንታ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ብር እና ክብር !(ቴዲ አትላንታ)

By   /   February 17, 2014  /   Comments Off on ብር እና ክብር !(ቴዲ አትላንታ)

    Print       Email
0 0
Read Time:12 Minute, 12 Second

ድህነት መጥፎ ነው፣ ያዋርዳል። ክብር ያሳጣል። አፋሽ አጎንባሽ ያደርጋል፣ ደጅ ያስጠናል። ማንነትን ያስክዳል። በአንጻሩም ጥጋብ ከቁመት በላይ ያሳስባል፣ ሌላውን ዝቅ አድርጎ ማየትን ያላብሳል። ሰው ያስንቃል፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ ያስብላል፣ ሁሉን የበታች ማየትን ያመጣል። ራስን ሰማይ ሌላውን መሬት፣ ራስን ጥንቸል ሌላውን ኤሊ .. ራስን ዝሆን ሌላውን አይጥ የሚያደርግ ስሜትን ይፈጥራል።

በአንጻሩ ቢጠግቡም ሰው የማይንቁና የማያዋርዱ አሉ፣ ባንጻሩ ቢደኸዩም ክብራቸውን አሳልፈው የማይሰጡ አሉ። ከነ ክብሬ ልሙት እንጂ ራሴን ለገንዘብና ለዳቦ ብዬ አላዋርድም የሚሉ ብዙ አሉ። ከዓመታት በፊት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ይመሩት የነበረው ኢሰመጉ ከስዊትዘርላንድ መንግስት ለመጽሃፍ ማሳተሚያ በሚል 10ሺ ዶላር ተቀብሎ ወይም ተሰጥቶት ነበር። መጽሃፉ ከታተመ በኋላ ግን የስዊዝ ኤምባሲ አምባሳደር፣ መጽሃፉን ቀድሜ ሳላየው [ እንደሳቸው አባባል .. የምትጽፉትን ነገር ቀድማችሁ ሳታሳዩኝ፣ የምፈልገውን አስቀርቼ የማልፈልገውን ሳልደልዝ፣ ይህን ቀይሩ ያን ቀይሩ ብዬ ሳላዛችሁ፣ ከኔ የመጨረሻው ፈቃድ ሳታገኙ እንዴት አተማችሁት?] ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ አሉ።

ስለ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉዳይ ለሚጻፍ መጽሃፍ የስዊትዘርላንድ አምባሳደር ያን ሁሉ ያሉት በሳቸው የ10ሺ ዶላር ርዳታ በመታተሙ ነበር። ርግጥ ነው ያን ጊዜ 10ሺ ዶላር በጣም ብዙ ነው። በጊዜው ርዳታውን በመስጠታቸውም ይመሰገናሉ። ግን ርዳታቸውን የዲታ እና የመናጢ ነገር አስመሰሉት። በብራቸው ተመክተው እኔ ሳልፈርምበት የናንተ መጽሃፍ ለምን ወጣ አሉ። ያን የማለት ድፍረት ያገኙት በገንዘባቸው ምክንያት ነበር።

በሳቸው ይህን ማለት ደግም ለጊዜው ኢሰመጉ ውርደት ተሰማው፣ እንደሌላው ቢሆን፣ “ልክ ነዎት ጋሼ አምባሳደር ይቅርታ ፣ ሌላ ጊዜ አይለምደንም” ሊባል ይችል ነበር። ፕሮፌሰር መስፍንም ሆኑ ኢሰመጉ ግን እንደዚያ አላደርገም። ይልቁኑ ባጭር ቃል “ልክ እንደ ግል አሽከርዎ ሊያዙን የሞከሩት ፣ በሰጡን ገንዘብ ምክንያት በመሆኑ፣ ምንም እንኳን ገንዘብዎን ለማተማያ ቤት የከፈልነው ቢሆንም፣ ከየትም ብለን (ፕሮፌሰሩ መኪናዬን ሸጬም ቢሆን ብለዋል) እንመልሳለን፣ ከዚያ በኋላ ግን በኛ ላይ ያሳዩትን የአዛዥነት መንፈስ እንዲያቆሙ በአክብሮት እንጠይቃለን” አላቸው።

እዚህ ላይ ድህነት ክብርን አላስነካም ማለት ነው። ክብርና ማንነት ከገንዘብ በላይ መሆኑ ታየ ማለት ነው። ይህ ነገር ትዝ ያለኝ፣ በዚህ ሰሞን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለዩጋንዳው መሪ ላኩት የተባለው መልክትና ማስጠንቀቂያ ነው። ኦባማ በላኩት መልክት “ኡጋንዳ በአስቸኳይ በግብረሰዶማውያን ላይ የጣለችውን ቅጣት ካላነሳች ዋ!! የምንሰጥዎትን ገንዘብ ነው የምናቆመው! .. መብታቸው ነውና ግብረሰዶም ተግባር ላይ የተገኙትን በፍጹም እንዳይነኳቸው!” ነበር ያሉት። ለዚያውም የኡጋንዳ ፓርላማ ያሳለፈው ውሳኔ ላይ ፕሬዚዳንቱ ፊርማቸውን እንዳይሰቀምጡ እኮ ነው ማስፈራሪያው።

ለፕሬዚዳንት ኦባማ ያለን ክብርና አድናቆት እንዳለ ሆኖ፣ ከአክብሮት ጋር እኛም አቅም ቢኖረንና እኛ ብንሆን ሃብታሞቹ፣ መልሰን እንዲህ እንላቸው ነበር “ፕሬዚዳንት ኦባማ ፣ የወንድ ለወንድ፣ የሴት ለሴት ጋብቻን እፈቅዳለሁ እያሉ የሰው ዘር እንዲጠፋ የሚያደግ ነገር ማበረታታትዎን እንዲያቆሙ እንጠይቃለን አለበለዚያ .. ! ….. ፕሬዚዳንት ኦባማ .. በአገርዎ ያለውንና ገንዘብ ተከፍሎበት በአደባባይ ሰዎች ወሲብ ሲፈጽሙ የሚታይበትን ርካሽ ቦታ እንዲዘጉ እንጠይቃለን… ! .. በአገርዎ እንደ ማሪዋና ያለ አደንዛዥ ዕጽ በግልጽ በየቦታው እንዲሸጥ መፈቀዱን እንዲያስቀሩ እንሳስባለን .. “ … ልንል እንችል ነበር። [አንልም እንጂ- ምክንያቱም በራሳቸው አገር መብታቸው ነውና]

ግን አንድ ነገር አለ። ፕሬዚዳንት ኦባማ ይህን ያሉት ገንዘብ ስላላቸው ብቻ ነው፣ ገንዘብ ስላላቸው አፍሪካ ውስጥ የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉ ይመስላቸዋል። በዓመት የሆነ ያህል ዶላር ስለሰጡ፣ አገራት ለሳቸው ብለው ባህላቸውን፣ ሃይማኖታቸውን፣ ወጋቸውን፣ እሴታቸውን እንዲተዉ፣ ሳይፈልጉ በግድ እንደሳቸው እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። አንድ አገር ከራሱ ባህልና ዕምነት፣ ወግና ሥርዓት ጋር በተገናኘ የራሱን ህግ ያወጣል። በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራት በሙሉ ተስማምተውበት የፈረሙት ህግ ካለ ማክበር አለበት – ለምሳሌ እንደ አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ያለ። ነገር ግን ወንድና ወንድ ካላጋባችሁ ብሎ ማስፈራራት ከጥጋብ የመነጨ፣ ደሃን ከመናቅ የመነጨ ካልሆነ ሌላም ምንም ሊሆን አይችልም።

አገሮቻችን ምንም ደሃ ቢሆኑ፣ ዛሬ ለዩጋንዳ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ለሁላችንም አገር እንደተሰጠ ቢቆጠር ደስ ይለኛል። ራስን እየገደሉ የሚመጣ ርዳታ ቢቀርስ? ቢያንስ በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ ህብረት ማሳየት ይኖርብናል። አሜሪካ ለራሷ ሲሆን “ሴተኛ አዳሪነትን” ትከለክላለች፣ ለመሆኑ “መብታቸው ነው በራሳቸው ገላ ምን አገባሽ?” ብትባል እሺ ትላለች? አትልም። በአሜሪካ ህግ ሌላው አገር እንደማያገባው ሁሉ አሜሪካ በሌላው አገር ህግ ለምን ጥልቅ እንደምትል ግልጽ አይደለም። ይህ እኮ የተባበሩት መንግስታት አውቆ ያጸደቀው፣ አገራት ሁሉ ተስማምተው የፈረሙበት አይደለም። ይህ አሁን የመጣ፣ የግለሰቦች ፍላጎትና ጫጫታ ነው። አቅም ቢኖርማ ነገሩ ተገልብጦ “እንዴት አንቺ ተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ፈቀድሽ?” ተብላ መጠየቅ የነበረባት ራሷ አሜሪካ ነበረች። መጥፎ አድራጊው ጥሩ አድራጊውን “ተው” የሚልበት ዘመን ላይ መድረሳችን አስገራሚ ነው።

አሁንም ድርጊቱን ፈጻሚዎች ይፈለጡ ፣ ይቆረጡ፣ የሚል ዕምነት የለኝም። ዋናው ነጥቤ በአንድ አገር ህግ ላይ ሃብታም ደሃውን በገንዘቡ ተመክቶ እጁን ለመጠምዝዝ ሲሞክር ማየት እንዴት የዓለምን ፍርደ ገምድልነት እንደሚያሳይ ለማሳየት ነው። አፍሪካውያን መሪዎች “ገንዘባችሁን እንኩ፣ ክብራችንን መልሱ” የሚሉ ፕሮፌሰር መስፍኖች ቢሆኑ ደስ ይለኛል። ነገሩ ግን ቀላል አይደለም፣ ጽናት ይስጣቸው ከማለት ሌላ ምን ይባላል?

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on February 17, 2014
  • By:
  • Last Modified: February 17, 2014 @ 4:51 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar