www.maledatimes.com ሐውልቱ ሥር ሆኜ እነዚያን ሰማዕታት ሳስብ! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ሐውልቱ ሥር ሆኜ እነዚያን ሰማዕታት ሳስብ!

By   /   February 17, 2014  /   Comments Off on ሐውልቱ ሥር ሆኜ እነዚያን ሰማዕታት ሳስብ!

    Print       Email
0 0
Read Time:15 Minute, 59 Second

ክፍል.1
በላይ ማናዬ

ስድስት ኪሎ አደባባይ የካቲት-12 ሰማዕታት ሐውልት ሥር ሆኜ ያን ዘመንና የወቅቱን አሰቃቂ ድርጊት ባሰብኩ ጊዜ ስቅጠት ተሰማኝ፡፡ የቆመው ሐውልት ማንን ለመዘከር እንደተጀነነ ባወኩ ጊዜ ደግሞ አንገቴን ቀና አድርጌ እኔም እንደ ሐውልቱ መጀነን ከጀለኝ፡፡ እናማ ሐውልቱ ሥር ሆኜ….ስሜቴ ዝብርቅርቅ ነው፤ ቋንቋዬ ብዙ ነው፤ መንፈሴ ጠንካራ ሐዘኔ መራራ ነው፤ ምናቤ የኋሊት ጎታች ምኞቴ ወደ ፊት ሸምጣጭ ነው፤ ሐውልቱ ለኔ የውስጠቱን ይገልጥልኛል፤ ታሪኩን ይነግረኛል….የተጋድሎ ታሪክ ይተርክልኛል፡፡

እንዲህ እያለ….
የካቲት 12 ከመባቱ በፊት የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ሌሎች መምጣት ያለባቸውና መገኘት የሚችሉ ሁሉ በዚህ በስድስት ኪሎ እንዲሰባሰቡ ጥሪ ቀረበ፡፡ እምቢልታ ተነፋ፤ ስማ በለው ተለፈፈ፤ ነጋሪት ተጎሰመ፤ ጥሩምባ ከወዲህም ከወዲያም አምባረቀ፡፡ ጥሪውን የሰማው ወገን ሁሉ በዕለቱ ለት ከተተ፡፡ የጥሪው መነሻ ፋሽስት ጣሊያን ሀገራችንን ከሞላ ጎደል ድል አድርጋ አዲስ አበባ ላይ ከከተመች ወዲህ መሪ ነኝ ባዩ ማርሻል ሮዶልፍ ግራዚያኒ «ሰርግና ምላሽ» የሚያደርግ መሆኑ ነበር፡፡ በዕለቱ የሮማ መንግስት ልዕልና እና የልጇ ልደት የሚዘከርበትም ጭምር ነበር፡፡

እናም ህዝብ አዳሜ ስድስት ኪሎን በዕለተ ሚካኤል አጥለቀለቀው፡፡ ህጻኑ፣ አዛውንቱ፣ ወጣቱ፣ ቆነጃጅቱ፣ ባንድ ቦታ ታደመ፡፡ ግራዚያኒ በጠባቂዎቹ ታጅቦ ግብር ለማብላት የንግስናው መንበር ላይ ተቀመጠ፤ ሰገነቱ ላይ ተንቆራጠጠ፡፡ ነጭና ሐበሻ ድምበር ለይቶም ቢሆን ተቀራርቦ የበረታው ቆሞ፣ የደከመው ተቀምጦ ሁኔታውን ያጤን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፈረሰኞችም አለፍ አለፍ ብለው ይታያሉ፤ ባንዳዎችም ሲያሸረግዱ የጉድ ነበር፡፡

ሰርግና ምላሹ ተጀምሮ ጥቂት ነገሮች በሰላም ከሄዱ በኋላ አካባቢው ተረበሸ፤ ከዚያ በሗላማ….
* * *
ሐውልቱ ሥር ሆኜ ታሪኩን አጣጣምኩት፤ ወደ ህይወት መለስኩት፤ ጊዜውን ጎትቼ አሁን ላይ አጫወትኩት፡፡ እናም እነዚያ ወጣቶች በሐገር ፍቅር ሲነዱ አየኋቸው፤ የወገን ጥቃት ሲያንገበግባቸው ተመለከትኩ፤ አውጥተው አውርደው መክረው ዘክረው ስለወሰኑት ውሳኔ አሰላሰልኩ፡፡ ውሳኔያቸውን የሚተገብሩበት ሰዓት ሲደርስ ተሰማኝ፤ ኢትዮጵያዊነት ወኔያቸው ወደ ፊት ሲገፋቸው፤ እምቢ ለሀገሬ ብለው ሲሸልሉ በውስጣቸው ሰመጥኩ፡፡
ባቀዱት መሰረት ወደ ተሰበሰበው ህዝብ ዘልቀው ገቡ፤ የያዙትን ነገር ደብቀው ወደ ግራዚያኒ እና ጠባቂዎቻቸው በቻሉት መጠን ተጠጉ፤ የወራሪዎች ትዕቢትና ንቀት ካሰቡት በላይ የሆነ መሰላቸው፡፡ የተሰበሰበው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያለበትን ስሜት አጤኑ፤ ከፋቸው! አዎ፣ ሀበሻ የበላይነት ተወስዶበታል፤ ችግረኛ ተምበርካኪ ሆኖ ታያቸው፡፡ በዱር በገደሉ ከወራሪው ጋር የሚፋለሙትን አርበኞችም አሰቧቸው፤ ልባቸው ደነደነ፡፡ በገጠር የሚፋለሙትን አርበኞች ማገዝ፣ መተባበር አለባቸው፡፡ ስለዚህም ያቀዱትን ሁሉ ዛሬ የካቲት 12 ቀን በግራዚያኒ ላይ መፈጸም አለባቸው፡፡

ሰዓቷ ደረሰች፤ የያዙትን የእጅ ቦምብ ፈቱት….ወደ ኢላማቸውም ሰነዘሩት! ግ…ር!….ሽብ..ር…..ሽብርብር! ምስቅልቅል! የድርጊቱ ፈጻሚዎች ወዲያውኑ አካባቢውን ከግርግሩ መሐል ገብተው በመሹለክለክ ተሰናበቱ፡፡ ግራዚያኒ በጥቃቱ ቆስሎ ተንገዳገደ፤ ጠባቂዎች ተረባበሹ፣ ቆሰሉ፣ ሞቱ…የአለቃቸው መጎዳትም ጎዳቸው፡፡
ግራዚያኒ ትዕዛዝ አስተላለፈ፤ «ይሄን ሐበሻ በሉት፤ እረዱት!!»
ወዲያው የፋሽስት ሰይፍ ተመዘዘ፡፡ የሚካኤል ሰይፍ ግን ተጠቂዎችን ለማዳን ሰገባውን ሾልኮ አልወጣም ነበር፤ የካቲት 12…ዕለተ ምካኤል በአዲስ አበባ መርገምት ወረደ፡፡ ውጥንቅጡ የወጣ ነገር….. የህጻናት ዋይታ…የእናት እሪታ…..የባንዳ ሽለላ…..የፋሽስት ጥይት ጨኸት….የአዛውንቶች እግዚኦ…..የእግሬ አውጭኝ ሩጫ…..የታጣቂ ጡጫ….የፈረሶች ርግጫ….የቀሳውስት ከንቱ ምልጃ…..የቆነጃጅት መቅበዝበዝ…..የጎልማሶችና ጎበዛዝት መደንዘዝ…ኦህ! ያማል!
የደም ጎርፍ….የተቀላ አንገት….የተቦደሰ ታፋ…..የተጎለጎለ አንጀት….የተቆረጠ እጅ…..የታረደ ጉሮሮ….የተገመሰ ጭንቅላት…..የተቆራረጠ ጣት…..የሚያቃስቱ ነፍሳት…..የተጋደመ ሬሳ….የተነባበረ የሰው ልጅ ክምር…..የአልሞት ባይ ተጋዳይ ትንቅንቅ…..የውስጥ አርበኞች ሽምቅ…..በደም ስካር….በግዳይ ሽለላ….ተጨማሪ ነፍሳትን ለመንጠቅ መታተር….ሐበሻን የመጨረስ ሩጫ…..እድሜ፣ ዖታ፣ እቴ…አባቴ ሳይሉ በያዙት መሳሪያ ማንከት….መሰየፍ….መቀልጠም….መረሸን…..አቤት ጭካኔ!! አቤት የግራዚያኒ ጭካኔ! አቤት አረመኔነት!

የሺዎች ጩኸት፣ የሺዎች ዋይታ፣ የሺዎች መሰዋት፣ የሺዎች እልቂት….መች በዚህ አበቃ፡፡ ግራዚያኒ ህክምናውን ተከታተለ፤ ሐበሻ ግን ጥራሞቱ እየተደመጠ፣ ማቃሰቱ እየታዬ፣ እስትንፋሱ እየተፈተሸ እንዲጨረስ ተደረገ፡፡ ግራዚያኒ እልቂቱን ባዬ ጊዜ ደስ አለው፤ እርካታ ሊያገኝ ግን አልቻለም፡፡ ስለዚህም ጭፍጨፋው ለሶስት ቀናት እንዲቀጥል አዘዘ፤ ገዳማት እንዲወድሙ መመሪያ ሰጠ፡፡
አዲስ አበባ በደም ጨቀየች፡፡ ስድስት ኪሎ በደም ጎርፍ ተጥለቀለቀች፡፡ ኢትዮጵያ ወገቧን በገመድ አስራ አዘነች፤ እምምም ብላ ወደ ፈጣሪ ተመለከተች፤ አንገቷን ከመድፋት ይልቅ ቀና ብላ ፈጣሪ ያለበትን ሰማየ ሰማያት አየች፡፡ ፋሽስትም አንገት ከመድፋት ይልቅ ቀና ማለትን የሐበሻ ይትብሓል ባዬ ጊዜ ፍርሃት ናጠው፤ የሀበሾች ንግርት ‘ስታጠቃኝ ጠንክሬ እዋጋሃለሁ’ የሚል ሆነበት፡፡ አርበኞችን ባሰበ ጊዜ የእንሺርት ውሃው ፈሰሰ፡፡

እነዚያን ጥቃት ፈጻሚ ወጣቶች ክፉኛ ኮነናቸው፤ የሮማን ሃያልነት መቀበል አንሻም ብለው «ኢትዮጵያ!!» ያሉትን ጀግኖች በአዕምሮው አመላልሶ አያቸው፡፡ የምር ቆራጦች ናቸው! የምር አርበኞች ናቸው! የምር ኢትዮጵያዊያን ናቸው! የምር አድዋ ላይ የግራዚያኒን አባቶች ያንበረከኩት ልጆች ናቸው!

ግራዚያኒ ስለነዚህ ወጣቶች በቀል በአዲስ አበባ ያደረገውን ተዘዋውሮ ተመለከተ፤ በእብሪት የተሞላው ልቡ ቅንጣት ታህል ሀዘን አልተሰማውም፤ እንዲያውም «በግዳዩ» ላይ በንቀት ምራቁን ጢቅ አደረገ፡፡ በሰማዕታት በድን ላይ በመኮፈስ ተራመደ፡፡

ግራዚያኒ የመግደል ሙከራ የተደረገበትን ስድስት ኪሎ ተመለከተ፡፡ የሬሳ መዓት አንዱ በአንዱ ላይ ተነባብሯል፤ እናት ልጇን እንደያዘች ባፍጢሟ ተደፍታለች፤ ጎልማሶች እጆቻቸውን ለጡጫ እንደጨበጡ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ተጋድመዋል፡፡ ግራዚያኒ እነዚህን መሰል ሬሳዎች ሲያይ እንደገና ደም ደም ይሸተዋል፡፡ ትንሽ አለፍ ሲል ደግሞ ሽለላ ላይ የነበሩ አዛውንቶች አፋቸውን ከፍተው ወድቀዋል፤ «አድዋ!!» ሲሉ እንደነበር እያሰበ በንዴት ይተክናል፡፡

ግራዚያኒ የባንዳ ሬሳ ሲመለከት ብቻ ሳቁ ይመጣበታል፤ እንዴት እርስ በእርሳቸው እንዳገዳደላቸው እያሰበ ይረካል፤ ባንዳዎች ሀገራቸውንና ወገናቸውን ከድተው ለሱ በማደራቸው ይንቃቸዋል፤ ፍርፋሪ ለመለቃቀም ሲሉ ከጎኑ ስለሆኑ ከሰውነት ተራ ያስወጣቸዋል፤ ጀግንነታቸው የፈሪ ጀግንነት እንደሆነ አድርጎ ያስባቸዋል፤ በህይወት ባሉ ባንዳዎች ዘንድም ትዝብት ያሳድርባቸዋል፡፡

á‹‹ አረመኔው ግራዚያኒ!…..ስንቱን ጦስ ይዘህ መጥተህ ነበር! በሶስት ቀናት ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ 30,000 ንጹሐን ተጨፈጨፉ፤ በታሪካዊው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ያሉ መነኮሳት ተረሸኑ፤ ቤተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ መኖሪያ ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ á‹‹ አረመኔው ግራዚያኒ!
* * *
ሐውልቱ ስር ሆኜ ያስታወስኩት ይህን ብቻ አልነበረም፤ ስለ የካቲት 12 ቀን፣ ስለነዚያ ወጣቶች እና ስለ ሌሎች የታሪኩ ተዋናዮችም ሳውጠነጥን ነበር፡፡ እነዚያ ወጣቶች ያልኩህ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስግዶምን ነው፡፡ በቀጣይ ስለነዚህ ወጣቶችና በዙሪያቸው ስለነበሩ የአርበኝነት ተጋድሎው አጋሮች እናወሳለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን የሐውልቱን ምስክርነት የሰማዕታቱን ሞገስ ስድስት ኪሎ ተገኝተህ ጎብኝ፡፡ እነዚያ ወጣቶች ጋር በቀጣይ እንገናኝ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on February 17, 2014
  • By:
  • Last Modified: February 17, 2014 @ 5:02 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar