www.maledatimes.com የየካቲት ፲፪ ሠማዕታትን ስናስብ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የየካቲት ፲፪ ሠማዕታትን ስናስብ

By   /   February 19, 2014  /   Comments Off on የየካቲት ፲፪ ሠማዕታትን ስናስብ

    Print       Email
0 0
Read Time:9 Minute, 42 Second

MWAO_V2No11_ረቡዕ የካቲት ፲፪ ቀን ፪ሺህ፮ ዓም_(Wed 19 Feb 2014)_የየካቲት ፲፪ ሠማዕታትን ስናስብ (3)

የየካቲት ፲፪ ሠማዕታትን ስናስብ
የካቲት ፲፪ ቀን ፋሽስት ኢጣሊያ ጦር በአዲስ አበባ እና በሌሎችም ዋና ዋና የኢትዮጵያ ከተሞች በ፲ሺህዎች የሚቆጠሩ
ኢትዮጵያውያንን በአሠቃቂ ሁኔታ የጨፈጨፈበትን ድርጊት የምናስታውስበት ዕለት ነው። ልክ የዛሬ ፸፯ (ሰባ ሰባት) ዓመት፣ በዕለተ-
አርብ በአዲስ አበባ ከተማ የገነተ-ልዑል ቤተመንግሥት ቅፅር ግቢ (የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኑቨርሲቲ ዋናው ግቢ)፣ በኢጣሊያን
ፋሽስቶች የጦር መሪ ጄኔራል ሮዶልፎ ግራዚያኒ ትዕዛዝ፣ በሦሥት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ፴ሺህ የማያንሱ ንፁሃን ኢትዮጵያውያን
የተጨፈጨፉበት ድርጊት የተጀመረበት ነበር። ዘወትር ስለጭፍጨፋው አጀማመር ሠበብ ተብሎ የሚቀርበው ኤርትራውያኑ አብርሃ
ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒ በአደባባይ ቆሞ ኢትዮጵያውያንን ሲዘልፍ እና ሲያጣጥል ተበሣጭተው ቦንብ በመወርወራቸው
እንደሆነ ተደርጎ ይቀርባል። የሁለቱ ኤርትራውያን ድርጊት ለጭፍጨፋው ተጨማሪ አቀጣጣይ ነዳጅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣
ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያውያንን በጅምላ ለመጨፍጨፍ አኅጉር ተሻግሮ፣ ባሕር አቋርጦ የመጣ ጨካኝ ጠላት መሆኑ ሊዘነጋ
አይገባም። እንዲያውም በአዲስ አበባ ከተማ እና በአካባቢው ብቻ ሣይሆን በደብረሊባኖስ እና በዝቋላ ገዳማት፣ በፍቼ፣ በደብረብርሃን፣
በደብረማርቆስ እና በሌሎችም የኢትዮጵያ ከተሞች፣ በተለይ የተማሩት እና በአርበኝነት ትግል ይሣተፋሉ ተብለው የሚጠረጠሩ
ኢትዮጵያውያን ሁሉ እየተለቀሙ የተፈጁት በግራዚያኒ ላይ በቦንብ የግድያ ሙከራ ከመደረጉ በፊት ነበር። ስለዚህ የየካቲት ፲፱፻፳፱
ዓ.ም. ጭፍጨፋ ሆን ተብሎና ታቅዶ በፋሽስት ጣሊያኖች ታቅዶ የተከናወነ የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን መካድ አይቻልም።
ኢትዮጵያ ከ፩ ሚሊዮን የማያንሱ ዜጎቿን ገብራ፣ ከ፭ ዓመታት የአርበኝነት ትግል በኋላ ጀግኖች አርበኞቿ በ፲፱፻፴፫ ዓ.ም.
የፋሽስት ኢጣሊያንን ድል በማድረግ ነፃነቷን አቀዳጇት። የድሉ መገኘት ለኢትዮጵያውያን አርበኞች ውለታ ተከፋይ ባያደርጋቸውም፣
ለሠማዕታቱ መታሠቢያ የሚሆኑ ሐውልቶችን ግን ለማስገንባት ምክንያት ሆኗል። በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ፦
 በየካቲት ፲፱፻፴፬ ዓ.ም. በዩጎዝላቪያ መንግሥት ድጋፍ የየካቲት ፲፪ የሠማዕታት መታሠቢያ ሐውልት ቆመ፤
 በ፲፱፻፴፮ ዓ.ም. የሚያዝያ ፳፯ የድል ሐውልት በአራት ኪሎ አደባባይ ቆመ፤
 በሐምሌ ፲፮ ቀን ፲፱፻፴፰ ዓ.ም. ለሠማዕቱ ለአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ቆመላቸው፤
 በታኅሣሥ ፲፪ ቀን ፲፱፻፶ ዓ.ም. የማይጨው (ሜክሲኮ) አደባባይ በይፋ ተመረቀ፤
ከእነዚህ በተጨማሪም በመላ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ከተሞች ለአርበኞች መታሠቢያ የሚሆኑ ሐውልቶች እና አደባባዮች ተገንብተው
ነበር። ዛሬስ ምን እየተደረገ ነው?
ባለፉት ፳፫ የትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ዓመታት የኢትዮጵያ አርበኞችን የዘመናት ተጋድሎ በቃላት ከማንኳሰስ አልፈው፣ በጠራራ
ፀሐይ ያለምንም ሃግ ባይ ለመታሠቢያነት የቆሙትን ሐውልቶች እና የተገነቡትን አደባባዮች በማፈራረስ ላይ ይገኛሉ። በዚህ የወያኔዎች
እኩይ ተግባር የመጀመሪያ ሠለባ የሆነው በጅጅጋ ከተማ ለታላቁ የቆራሄ-ወልወል አርበኛ ለደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሠማዕት
መታሠቢያ የቆመው ሐውልት ሲፈርስ ነው። ወያኔዎች በዚህ ሣይገቱ በኢትዮጵያ ግዛት በሁሉም ሥፍራዎች ለኢትዮጵያ አርበኞች
መታሠቢያ የቆሙ ሐውልቶችን እና አደባባዮችን ማፈራረሱን በመቀጠል ባለፈውም ዓመት የሠማዕቱን የአቡነ ጴጥሮስን ሐውልት
አረሱ። ዘንድሮም የሜክሲኮ አደባባይን አፍርሰዋል። የሚቀጥሉት የወያኔ ሠለባ ከሚሆኑት መካከል፦ የየካቲት ፲፪ የሠማዕታት
መታሠቢያ እና የሚያዝያ ፳፯ የድል ሐውልቶች እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐውልት የመፍረስ
ወር-ተራቸውን እየጠበቁ መሆናቸውን መጠራጠር አያሻም።
ይህ ሁሉ ሲፈፀም የዘመኑ ኢትዮጵያውያን ቢበዛ ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ እርባና ያለው ተቃውሞ እንኳን አላደረግንም።
ሆኖም በዚህ አሣፋሪ ድርጊት ይህ ትውልድ ከታሪክ ተጠያቂነት አያመልጥም። ስለዚህ ተገቢው ዕርምጃ አባቶቻችን እና እናቶቻችን
የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ያስከበሩልንን ነፃነት፣ እኛ በንዝህላልነት በከንቱ የጣልነው ስለሆነ፣ ከያዘን የቁም ሠመመን ተላቅቀን፣
በጋራ ለብሔራዊ ክብራችን መቆም ብቻ ነው። ይህንን በማድረግ የየካቲት ፲፪ ሠማዕታትን መስዋዕትነት በከንቱ እንዳይቀር መታደግ
እንችላለን።

ለጀግኖች አርበኞቻችን መስዋዕትነት ክብር እንስጥ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on February 19, 2014
  • By:
  • Last Modified: February 19, 2014 @ 10:28 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar