www.maledatimes.com ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ማንነት ‘አለ’ ‘የለም’ ተገቢ ክርክር ነውን? - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ማንነት ‘አለ’ ‘የለም’ ተገቢ ክርክር ነውን?

By   /   February 26, 2014  /   Comments Off on ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ማንነት ‘አለ’ ‘የለም’ ተገቢ ክርክር ነውን?

    Print       Email
0 0
Read Time:30 Minute, 37 Second

1. ሀገር ግንባታ(Nation Building)ና ኢትዮጵያ

‘የኢትዮጵያ ግንባታ እንደ ብዙ ሀገር ሁሉ በፈቃድ አልነበረም’ የሚለው ኢትዮጵያን እንደ ኢምፓየር የምንመለከት ከሆነ ትክክል ነው:: በጉልበት የተሰራች ኢምፓየር ነች::በሌላ አባባል ኢትዮጵያ የብዙ ትንንሽ አንዳንዴ ብሔሮች (ሀገረ-መንግስት) ወይም ነገስታተ-ምድር ስብስብ ነበረች:: እዚህ ላይ ብሔር (nation) የሚለውን ትርጉም እንዲይዝ ተደርጎ ይነበብልኝ:: በአማርኛ ለኢንግሊዘኛው Nation state አቻ ትርጉም እንዲሆን ሀገረ-መንግስት የሚለውን ይዘው ብቅ ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ናቸው:: ይህ ደግሞ ብሔር የሚለውን ስም ለመሸሽ የተጠቅሙበት ነው ብዬ ነው የምወሰደው::

አንዳንድ ሰው ብሔር በግዕዝ ሀገር የሚል ትርጉም ነው ያለው ብሎ ይቀበላል:: ግዕዝ ግን ዘብሔረ-ኢትዮጵያ ብሎ ሲጠቀም እምበዛም አይታይም:: ይልቁንም ዘብሔረ-አክሱም ዘብሔረ-ቡልጋ – ኤልያስ እምብሔረ-ህያዋን ይላል:: በዚህ መሰረት በ nation-state ስያሜ ውስጥ ‘ሀገር’ የሚለውን ትርጉም ብቻ ለ nation መስጠት ትክክል አይመስለኝም:: ‘ብሔር’ ኔሽንን በትክክል ባይገልጸውም ተቀራራቢው ነው ብዬ አምናለሁ:: ስለዚህ ከዚህ በታች ብሔር የሚለውን የምጠቀመው የአንድ ዘውግ ወይም á‹« ዘውግ የሚኖርበትን ግዛትና መዋቅር ጭምር ለመጠቆም ይሆናል::

ሀገረ-መንግስት ከምንለው ይልቅ ብሔረ-መንግስት ቢባል የተሻለ ነው:: ርዕሰ-ብሔር የሚለው ስያሜም የተዋጣ የሚሆነው ያኔ ይመስለኛል::በዚያ ላይ በትክክል ኔሽን ስቴት ለሚለው ትርጉም ይቀርባል::በተጨማሪ ኔሽን-ስቴት የፈረንሳይ አብዮት ውጤትና በኦርጂናል ትርጉሙ የአንድ ብሔር(ዘውግ) መንግስት ነበር::ኤድሞንድ ጄ. ኬለር ‘The Ethnogenesis of the Oromo Nation and its implications for politics in ethiopia’በሚለው ጥናታዊ ጽሁፉ እንደገለጠው ብሔረ-መንግስት ሲፈጠር የአንድ ዘውግ የሆነ አንድ ቋንቋ ታሪክ እና ባህል የሚጋራ መንግስት ተደርጎ ነው የተተለመው::ከፈረንሳይ አብዮት ወዲህ በተለይ በሃያኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ የአንድ ዓይነት ዘውግ ሀገራት ወይም ብሔረ-መንግስታት መሳጭነት እየከሰመ ሲሄድ በምትኩ ብዙኃን ብሔሮችን የሚያስተናግድና አንድ ሀገር-አቀፍ ማንነትን ባህልና ታሪክን በመጋራት ላይ የተመረኮዘ ስርዓት ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት ጀመረ::

2. ከኢምፓየር ወደ የብሔረ-ብዙኋን መንግስት

ብዙ ጥናቶች ኢትዮጵያን የሚመለከቱት ከኢምፓየር ወደ ብሔረ-ብዙኃን መንግስትነት የተቀየረች(የተሸጋገረች) አድርገው ነው:: የመሰረቷት ነገስታትም አንድ ሀገራዊ ማንነትን ለብዙኃን ብሔሮች በመሽጥ በኩል እንደተሳካላቸው ተደርገው ይታሰባሉ:: ይሁንና እኤአ ከ1974 የሰሎሞናዊው ሥርወ-መንግስት ነቀላ ወዲህ ይህ በሚገባ ያልተከወነ የቤት ስራ መሆኑን ማየት ተችሏል::

ፍራንክ ዴቭድ ማርኮ በ ‘Nation-Building Challenges in an African Empire: The Case of Ethiopia’ በሚለው ጥናቱ እንደገለጠው በኢትዮጵያ አብዛኞቹ የዓለም ኢምፓየሮች( ሩስያ ኦቶማን ቱርክና ኦስትሮ-ሀንጋሪ) ከሞቱባቸው የሃያኛው ክ/ዘመን በአንድ መቶ አመታት ዘግይቶ ነው የዘውግ ብሔርተኝነት ብቅ ያለው::ይህ ያለምክንያት አይደለም:: ትምህርት በቅድሚያ ስለራስ አካባቢና የማህበረሰብ አደረጃጀትን አበጥሮ የማወቅ ፍላጎትን(self consciousness)ያመጣል:: የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስነ ምህዳር ለበርካታ አመታት ብሔርተኝነት እንዲኖር (እንዲያብብ) አስፈላጊ ግብዓት የሆነው ከባቢና አካላቱ የሆኑ ሁለት ጠቃሚ ነገሮች አልነበሩትም::

አንደኛው ይህን (imagined national culture) የአገራዊ ባህልን ምስል ከመሃሉ ወደ ዳር ለማስተላለፍ የሚሆን ዋነኛው ቴክኒካዊ መሰረተ-ልማት ሲሆን ሌላኛው ክፍት አዕምሮ ያላቸው የተማሩ ሊቃውንት ያለመኖር ነው:: ሐይለስላሴ ይህን ለመገንባት በሚታገሉበት ወቅት አክራሪ ብሔርተኞችና ኮሚኒስት ቡድኖች በመብረቅ ፍጥነት ንጉሳዊውን አገዛዝ ገረሰሱት:: ስለዚህም ያልተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሀገር ግንባታ ፕሮዤ የደርግ የአፈሙዝ ጥበቃ ታክሎበት እስከ 1991 ቆየ::የጌንት ዩንቨርሲቲው ክርስቶፍ ቫን ደር ቤከን ኢትዮጵያ ከተማከለው ንጉሳዊ አገዛዝ ወደ ፌደራል ሪፐብሊክ በሚለው የአፍሪካ ፎከስ 2007 መጣጥፉም ሽግግሩን በሚመለከት በጥልቀት ጽፏል:: በተለይ አፍሪካ ውስጥ የብሔረ-መንግስት ምስረታው ስትራቴጂ አካል የሆነና ለሀገራዊው ማንነት በማድላት እና እንዲኖር የዘውግ ማህበረሰቦችን ማዳከም የሚል መሪ ሀሳብ ይተገበራል ይለናል::

3. ሌቭን እና ሌሎችም

ዶናልድ ሌቭን በኢትዮጵያ ታሪክና ማህበረሰብ ጉዳዮች ጥልቅ ጥናቶች በማድረግ የታወቀ አሜሪካዊ ፕሮፌሰር ነው:: ብዙ ስራዎቹ ለቀዳማዊ ኃይለስላሴ ባለው አድናቆትና ክብር ከመሸፈናቸው በቀር ‘ሀገራዊ’አጀንዳን አበረታች ነው:: እንደ ሌቭን በክብረ ነገስት ውስጥ ‘ብሔረ-‘ የሚለውን ስያሜ አራት አቻ ግን አሻሚ ትርጉሞች ሊኖሩት ይችላል ይለናል:: እነሱም መሬት(ሀገር) /land/ ህዝብ/people/ ዘውግ/nation/ና የፖለቲካ ማህበረሰብ/polity/:: በዚህ ላይ (ኢማጅንድ [አብሲንያዊ]ማህበረስብ)እና መሰረተ-ልማቱም በኢኦተ ቤተክርስቲያን ና በሊቃውንተ-ቤተክርስቲያን አማካይነት ተዘርግቶ ነበር ይለናል:: ችግሩ ኢትዮጵያ በተለይ ወደኋላ ከቀረችን አብሲንያ በእጅጉ ትሰፋለችም ውስብስብና የበርካታ ማህበረሰብ ጥርቅም ሀገርም ነች::

በእርግጥ ሌቭን ኢትዮጵያን አንድ ሀገር አንድ ህዝብና አንድ ሰንደቅ በሚለው መንገድ መውሰድ ይቃጣዋል:: የኢትዮጵያን ኔሽንነት አውሮፓውያን ይህን እይታ ከማምጣታቸው በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር ብሎ ይከራከራል:: ክብረ ነገስት የዚህ አይነተኛ ማሳያ ነው ይለናል:: ብሔር/ኔሽን/ የሚለው ጽንሰ ሀሳብ በጣም ዘመናዊ አስተሳሰብ መሆኑን ኤሊ ኬዱሪንና ክርያግ ካላሁንን ጠቅሶ በ 2003 ለ 15ኛው የኢትዮጵያ ጥናት Reconfiguring the Ethiopian Nation in a global era በሚል ርዕስ አቅርቧል::

በዚሁ ጥናት ውስጥ የተጠቀሰው ካዱሪ ናሽናሊዝምን እንደ አይዲዎሎጂ መለኪያ ነው የሚያየው እናም በዚህ አይዲዎሎጂያዊ ዶክትሪን መሰረት የሰው ልጅ በተፈጥሮው በብሔር የተከፋፈለ ነው ብሎ አያበቃም ነገር ግን ብሔሮች በታወቁ መገለጫዎች ይለያሉ እንደዚሁም በብሔር ላይ የተመሰረተ መንግስት ህጋዊ(legitmate)ነው ይለናል:: ይሁንና ሌቭን ብሔርን በካዱሪ አመለካከት አንጻር እንዴት እንደሚያየው (የአንድ ዘውግ ሃይማኖትና ባህል ግዛት ወይስ የድብልቅና ብዙኋን ህብረት )በግልጽ አስረግጦ ከማለፍ ይልቅ አምታቶት ያልፋል::

4. ምሁራዊው ጋዜጠኝነትና አይዲዎሎጂዊው ጋዜጠኝነት

እንደ ሌቭን ሁሉ ምሁራዊ የሚመስሉ ነገር ግን የአይዲዎሎጂ ትብታብ የሚያካፍሉ ምሁራንም ጋዜጠኞች አሉ:: በበኩሌ የምንፈልገውን አይዲዎሎጂያዊ አመለካከት ለመደገፍ ምሳሌዎችና ጽንሰ ሀሳቦችን ደርድሮ ለማሳመን መውተርተር ይቻላል ብቻ ሳይሆን መብትም ነው:: ነገር ግን ምሁራንና ወደዚህ የቀረቡ ተደርገው የሚሳሉ ጋዜጠኞች በዚህ መንገድ ለራስ ሀሳብና አመለካከት ሲያደሉ ማየት አይዋጥልኝም::

መስፍን ነጋሽ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በ 3.1, 3.2 እና 3.3 በሚባሉ ሶስት ክፍሎች ከፍሎ አቅርቦልናል:: ይሁንና በዚህ ደረጃ ለራሳቸው አይዲዎሎጂያዊ ሀሳብ ያደላሉ ብዬ ልጠቅሳቸው ከምፈልጋቸው ሰዎች መካከል ምናልባት የመጨረሻው መስፍን ነጋሽ ነው:: ይህ ነገር ወሰድ መልስ ስለማያደርገው ሳይሆን በአብዛኛው ከየትኛውም አይዲዎሎጂያዊ ክበብ ላለመካተት አስታራቂ ሚናን የሚጫወት ተደርጎ ስለሚሳል ወይም ስለሚሞክር ወይም እንዲያ እንዲታሰብ ስለሚጥር ይመስለኛል::

ባለፈው ጊዜ በየማነ ናግሽና በእርሱ መካከል በዶቼዎሌ ራዲዮ በተካሄደው ክርክር ውስጥ ‘ማን ነው አይዲዎሎጂ ያልታጠቀ ጋዜጠኛ?’ በሚለው ሀሳብ ላይ ከክርክሩ በፊትም በኋላም ሳስብበት ነበር::እንደኔ ‘ነጻ’ ጋዜጠኛ የሚባል በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ክበብ ውስጥ የለም የሚለው ሀሳብ ያስማማኛል::ምናልባት ጋዜጠኝነት አዲሱ ፒስአይአር (PSIR) ሆኖ እንደሆን አላውቅም:::: ሁሉም የየራሱ የአይዲዎሎጂ ጥግ አለው::ችግሩ አንድ ጋዜጠኛ ከዚህ ወይም ከዚያ ጥግ ስለሚመደብ አይደለም:: ይልቅ አንደኛውን ‘አይዲዎሎጂ የተጫነው’ ሌላውን ‘ነጻ’ የምናደርግበት መለኪያ ትክክል አይመስለኝም::

እዚህ ላይ አይዲዎሎጂ የሚለውን በሁለት መንገድ እንዲታይ እሻለሁ:: አንደኛው የአንድ ቡድንና አባላቱ መሰረታዊ እምነቶችና የእምነት ስርዓትን ይመለከታል የሚለው ነው::ሁለተኛው የተሳሳተ እምነት ወይም የሀሰት ንቃተ ህሊናን ይመለከታል:: ሁለተኛው በተለይ በማርክስ ጽሁፎች ውስጥ የሀሰት ንቃተ ህሊና አንድ ያለን ሁኔታ ለማስቀጠል የሚሻ ቡድን ይህን የሀሰት ንቃተ ህሊና ተጠቅሞ ያለውን ሁኔታ ህጋዊነት ለማላበስ ወይም እውነተኛው ማህበረሰባዊ ምጣኔ ሀብት በትክክል እንዳይታይ እንደ ጭንብል ለመደበቅ/ለማጭበርበር/ ይጠቀምበታል ይላል::

በዚህ መሰረት መስፍን ነጋሽ በጥንቃቄ የተጻፈ አይዲዎሎጂ ቀመስ የሆነ ጽሑፍ አቅርቦልናል ብዬ አምናለሁ:: ችግሩ አይዲዎሎጂ መለወሱ አይደለም:: ብዙዎች እንደ አስታራቂና ተራማጅ አድርገው ማሰባቸው ላይ ነው:: ተራማጅ አልለውም ምክንያቱም ለምሳሌ 3.1 ከሳይንስና ምክንያት ይልቅ ለሀይማኖት ይቀርባል:: ይህ ልክ ሰው ሁሉ የመንፈሳዊዋና የተመረጠችዋን ኢትዮጵያ ማህበረሰብን ምስል ከሚቀርጸው ክብረ ነገስት ጋር ይመሳሰላል::

ክብረ ነገስት የተመረጠ ህዝብነት በእስራኤል ስለከሽፈ ወደ ኢትዮጵያ ተላልፏል ብሎ ነው የሚሰብከው:: ቢያንስ አብዛኛው የክብረ ነገስት ክፍል ሲጻፍ የዛሬዋ ኢትዮጵያ አለመኖርዋ ግን ሀሳቡን ደካማ መከራከሪያ ያደርገዋል:: እንደዚሁም የተመረጠ ህዝብ ረሀብ የማይለቀው ችጋርና ድንቁርና የተጣባው መሆኑ ከበቂ በላይ ይህን አስተሳሰብ ውድቅ እንድናደርግ ይወተውተናል:: ይህ እንግዲህ መሰረታዊውን ‘መመረጥ’ የሚለውን አስተሳሰብ ጥያቄ ውስጥ ያለማስገባት ቸርነት ተጠናውቶን ጭምር ነው::

መስፍን በ3.1 እንደሚለው ” [ይህ] ኢትዮጵያዊ ማንነት ራሱን የሁሉም የአገራችን ብሔረሰቦች አካል አድርጎ ይመለከታል፤ ለአንዱ የተለየ ቅርበት አይሰማውም። እነዚህ ሰዎች ምክንያቱ ምንም ይሁን፣ ራሳቸውን የዚህ ወይም የዚያኛው አንድ ብሔረሰብ አባል አድርገው አይቆጥሩም። የዚህ ማንነት ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያዊ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ነገር እኩል ተጋሪ ባለቤት እንደሆነ ያምናል። ብሔረሰባዊ ማንነትን ያከብራል። ብሔረሰባዊ ማንነትን ተገዳዳሪው አድርጎ አይፈራውም። ይህ ማንነት ድንገት ከሰማይ ወርዶ የሁሉም አካል ነኝ የሚል፣ ባለቤት አልባ ማንነት አይደለም።” ይህን በእምነት ካልሆነ በቀር በተጨባጭ ምክንያት ማሳመን አይቻልም:: ከትምህርተ-ስላሴ አንድነትና ሶስትነት ምስጢር የሚበልጥ ዶግማ ነው::

በመስፍን ቸርነት 3.1 ጭምብል አጥልቀንለት እንጂ ልምዳችንም አመለካከቶቻችንን የሚያሳብቁት ስነቃሎቻችንም የሚሉት ቢኖር ይህን የመሰለ ኢትዮጵያዊነት ማንነት እኛ ሀገር አይደለም በምዕራባውያን ዘንድም ገና አልተፈጠረም:: ለምሳሌ በፍላንደርስ ሰሜኖቹና በፈረንሳዊያን ደቡቦች መካከል ያለው ፍትጊያ ቤልጅየማዊነት ገና ተሰርቶ ያለማለቁ ምልክት ነው:: ይህ በብሪታንያ በአራቱ አካሎቿ መካከል በተለይም በስኮትላንድ ጥያቄም ውስጥ ይንጸባረቃል:: ለምን ስኮትላንዶች ራሳቸውን በሁሉም የአገሪቱ አካሎች ጋር አብሮ ማየት ተሳናቸው?

ስለዚህ ይህ ከምድርም ከእውነትም የራቀ ማንነት ነው:: እንዲሁ ይሁን ብለን እንቀበልና ለ84ቱ ብሔሮች ወገንተኛ መሆን ወይም ራሳቸውን በዚያ ቦታ ማስቀመጥ ይቅርና በቅጡ የሚያውቁ ሰዎች ከዘጠና ሚሊዮን ህዝብ በጣት የሚቆጠሩ ነው የሚሆኑት:: እዚህ ላይ በዮርዳኖስ እንዳለው 3.1 ሲፋቅ 3.3 ይሆናል በሚለው እስማማለሁ:: በዚህ አገላለጽ 3.1 የተሳሳተ እምነት (ሚስጋይድድ ብሊፍ) ሲሆን 3.3ን ለማጽናት የሚንደረደር ጭምብል ነው ባይ ነኝ::

ከዚያ በተረፈ ማንነትን በተመለከተ የቀረቡ ሀሳቦችን እየፈታን ማየት ይኖርብናል:: ከዚህ በታች የአመክንዮ መፋለስ የማይበት ክፍልን አንድ ማሳያ አቀርባለሁ:: በመስፍን ጽሁፍ ውስጥ 1.1

1.1 ‘አንድ ማንነት በጉልህ የሚታየው ከሌላው ጋር ሲነጻጸር ነው::አንድ ሰው ማንነቱን የሚገልጽበት መንገድ እንደሁኔታው ይለያያል::’ በዚህ መሰረት ሀገራዊ ማንነት ከ ብሔረሰባዊ ማንነት በሚለው ንፅፅር ተገቢነት ላይ ጥያቄ አለኝ:: ምክንያቱም

ሀ)ይህ ንፅፅር ክርክሩ በኢትዮጵያውያን መካከል መሆኑን ሽምጦ ይክዳል::ይህም ማለት ኢትዮጵያዊ ማንነት አንዱ እንዳለው ሲቀበል የብሔር ማንነቴን ቅድሚያ እንዲሰጠው እፈልጋለሁ የሚለው በፍጥነት ኢትዮጵያዊ ማንነቱን እንዳወለቀ አድርጎ ይረዳል:: የ3.1 ማንነት በኢትዮጵያ ስም መቅረብ የለበትም:: የከተሜው ንዑስ ማንነት ነው:: ይህ ከተሜው በተለይም በቅንነት በልምድ ብዛት ወይም በትምህርት ከ3.3 ወደ 3.1 የተሽጋገረ አለ ብለን የተቀበልን እንደሆን ነው::

ለ) የብሔር ማንነትና ኢትዮጵያዊ ማንነት -ሁለቱ ለንፅፅር በአንድ አውድ የሚቀርቡ አይደሉም::ኢትዮጵያዊ ማንነትህን ከአፍሪካዊ ማንነትህ ወይም ከሰውነትህ ጋር አታነጻጽረውም::ኢትዮጵያዊ ነኝ ስትል ቢያንስ ከኢትዮጵያ ዜጎች የምትመደብ አፍሪካዊ መሆንህን እና ሰው መሆንህን መቀበል ይኖርበታል:: ኢትዮጵያዊ ማንነትህ ከናይጄሪያዊ ማንነቱ ከኬንያዊ ማንነቱ ወይም ከእንግሊዛዊ ማንነቱ ልታነጻጽር ትችላለህ:: ሀውሳነቱን ከናይጄሪያዊነቱ ወይም አማራነቱን ከኢትዮጵያዊነቱ አታነጻጽርም::የተለያየ መደብ ማንነቶች ናቸውና:: መዋቅራዊ ያደረግነው እንደሆን አንዱ ንዑስ አንዱ ከፍ ያለ ማንነቶች ይመስሉኛል::

ሐ)በዚያ ላይ በስብስብ ስሌት ሁሉም በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ያለ ብሔረሰባዊ ማንነት ኢትዮጵያዊ ለምንለው ማንነት አነሰም በዛም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አለው ብቻ ሳይሆን የማንነቱ አባልም ነው:: በሌላ አባባል 1) ብማ Є ኢማ ከሆነ:: 2)ብማ≠ኢማ እና ብማ ∩ ኢማ=ብማ ነው:: በመስፍን እይታ የሄድን እንደሆን ግን የብሔረሰብ ማንነትን ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር ስናነጻጸር ሁለቱ እኩል ግምቶች ያረጋቸዋል::ያ ደግሞ ትክክል አይመስለኝም:: ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች ሀገር ናት:: ከዚህ ውስጥ የሚመደብ አንድ ባህል ቋንቋና ሀይማኖት የዚህ ሞዚያክ አካል እንጂ ሁለንተናው አይደለም::

ከላይ እንደተባለው ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ተገንብታ ያላለቀች ሀገር ናት:: ኢትዮጵያዊ ማንነትም እንዲሁ ሁላችንም ልንደርስበት የሚገባንን ትልም ያሳየን ይሆናል እንጂ ያላለቀ ፕሮጀክት ነው:: አለቀ የምንለው እኔ የምቆረቆርላትን ኢትዮጵያ የኔን ያህል የሚቆረቆርላት ጋምቤላ ወይም ሱማሌ ወዘተ መፍጠር ሲቻል ነው::እኔን የሚነሽጠኝ ሀገራዊ ስሜት አፋርና ደቡብ ያለውን ህ/ሰብ አባል እኩል ሲነሽጠው ነው:: ከዚህ እጅግ በጣም እንርቃለን:: በኢትዮጵያ ስም ሊጠራ የሚችል ማንነት ገና መፍጠር ይጠበቅብናል:: አሁን እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ የምለው ጥቅሜን የምታስከብርልኝ ኢትዮጵያ ለሌሎችም ጥቅም እንደምትቆም እርግጠኛ ሲኮን ነው:: á‹« ካልሆነ ኢትዮጵያዊ ማንነት ያልነው ጠቦ የተሰፋ ‘አብሲኒያዊነት’ ሲከፋም አማራነት ወይም ትግራዋይነት ነው ማለት ነው:: ይህ ደግሞ ሌሎቹን የመስፍን በርካታ የመከራከርያ ነጥቦች በዚህ መንደርደሪያ ሀሳብ ላይ የተገነቡ ስለሆኑ ፉርሽ ያረጋቸዋል::

”ኢትዮጵያዊ ማንነት አለን” የሚሉት ኢትዮጵያዊ ማነነትም አለብን ከሆነ ትክክል ናቸው:: ችግሩ ኢትዮጵያዊ ማንነት መለኪያ ማለት እኛ ነን ሲሆን ነው:: የኢትዮጵያዊነት መለኪያዎች ነን ወደማለት የሚወስድም ነውና:: ቀስ በቀስም ግባት ነው እንጂ በራሱ ኢትዮጵያዊነትን ወክሎ የሚቆም አይደለም ብሏል መስፍን በኮመንቱ :: የኔ ጥያቄ ታዲያ ለምን ‘ኢትዮጵያዊ’ ማንነት ይባላል ነው? ምክንያቱም አስቀድሞ አሳሳች በመሆን በስሙ አዎንታዊና ቀና አመለካከት ለማግኘት ያለመ ይመስላል::

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on February 26, 2014
  • By:
  • Last Modified: February 26, 2014 @ 9:15 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar