www.maledatimes.com ምንሊክን በጎሪጥ (ከባዩ በየነ- ቶሮንቶ ካናዳ-March 2, 2014) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ምንሊክን በጎሪጥ (ከባዩ በየነ- ቶሮንቶ ካናዳ-March 2, 2014)

By   /   March 5, 2014  /   Comments Off on ምንሊክን በጎሪጥ (ከባዩ በየነ- ቶሮንቶ ካናዳ-March 2, 2014)

    Print       Email
0 0
Read Time:27 Minute, 14 Second

1

መኮንን ረጋሳ star bucks የሚሉት ቡና መጠጫ ፀጥ ባለ ክፍል reserve ባስደረገው ጠረጴዛ ላይ ትንሿን ኮምፒዩተር
አስቀምጦ ከወንበሩ ላይ አረፍ አለ። ኢትዮጵያን እንደቡና ሊያሸታት ሲፈልግ ከአበሻ ሬስቶራንት ቀጥሎ የሚያዘወትረው
star bucksን ሰለሆነ አስተናጋጆቹ ያውቁታል።
መኮንን ረጋሳ በናቱ ትግሬ ነው። እናቱ ግን የሃማሴንም የጎንደሬም ደም እንዳላቸው ያወሩ ነበር። አባቱ ረጋሳ ደሞ ያው
ረጋሳ ናቸው፤ የለም የለም እሳቸውም ቢሆኑ ‘የሶዶ ጉራጌነቴ ያመዝናል’ እያሉ ዘራቸውን ሲያስቆጥሩት ነበር። እንግዲህ ይህን
ሁሉ የተደበላለቀ እሱነቱን ይዞ ነው ስለ አድዋ በዓል ትንሽ ነገር ሊከትብ አስቦ የተቀመጠው። የአድዋን ውሎ በዓይነ-
ህሊናው እየቃኘ ሳለ የሃሳብ ጎርፍ ጠለፈው። በሃሳብ መጠለፍ – የሥደተኛ አበሻ ግብር፣ ዕዳ፡
ቀዳማዊ ሃይለሥላሴ ‘ተማር’ ብለው ፈረንጅ አገር ሲልኩት ምኞቱ አገሩን የሚያስነክሳትን የድህነት እሾህ መንግሎ መጣል
ነበር።፡ተዛ ወዲህ አገሩን ያየው አንዴ ብቻ ነው – ለዛውም በግርግር ውስጥ። ተሥፋ ቆርጦ ተመለሰ። በገባበት የፖለቲካ
ትርምስምስ አገሩን ማየት አይችልም። እናቱን ፣ አባቱን አልቀበረም፤ ጓደኞቹ፣ ዘመዶቹ ሁሉ ባብዛኛው አልቀዋል።
በጉርምስናው ዘመን ከፍቅረኛው ጋር ከንፈር የተሳሳመባት የወይራ ዛፍ ወይ ደርቃለች ወይም ደሞ በከርሰ-መቃብሯ ላይ
እንደ ጥይት ባንዴ የተተኮሰ የዘመኑ ሃብታም ብዙም ህይወት የማይታይበት አሥር ፎቅ አቁሞበት ይሆናል። መገመት ብቻ
ነው የሚችለው ። እንዲያው በደፈናው ሁሉም ነገር ትዝታ ብቻ ነው …..
መኮንን የሃሳብ ጎርፍ ሳይሆን የሃሳብ ጎርፎች አዋከቡት። ሁሉም ሃሳቦች አጋፋሪ ያላቸው ይመስላል፤ ‘በዚህ ና!’ ፣ ‘የለም
በዚህ ይሻልሃል’ እያሉ የተጠቀለለ የሃሳብ ክምራቸውን በየፈርጁ እንደስጋጃ ምንጣፍ እየተለተሉ ይጋብዙታል። ተሁሉም
የጎላው የሃሳብ ፈርጅ እንደ አርሲ የገብስ ማሳ ፊቱ ተዘረጋ። ‘አርሲ!’ – ‘አሃ!’ አለ። አርሲ የሚለው ቃል የሰሞኑን ዕብደት
አስታወሰው፤ወደ አድዋ፣ ወደ ሚኒሊክም መለሰው። እናም እሱን መረጠው። አጋፋሪው እንዳደገደገ ሲጠባበቀው ስላየ
‘እጅህ ከምን?’ አለው። አጋፋሪውም የሰሞኑን ምዋዕለ-ዜና አምበለበለለት – እንዲህ እያለ….
“አቀንቃኙ ‘ጥቁር ሰው ብሎ አቀነቀነ፤ ምንሊክን ዘከረ፤ ከጎኑ ተሰልፈው የአድዋን ድል ያስጨበጡንን የኦሮሞ ጀግኖች ሆን
ተብሎ በተቋጠረ ሥንኝ በሥም እየጠራ አወደሰ። ያለነሱ የወዝ፣ የደም እና የህይወት ግብር ‘ እኔን አልሆንም ነበር እኔ’ እያለ
አማራጭ የነበረውን ውርደትና ሞት እንዴት እንዳመለጥን አስታወሰን። ምክንያቱ ግልፅ ነበር፤ በምንሊክና በኦሮሞ ህዝብ
መካከል በውሸትም፣ በግነትም ሆነ በእውነት ላይ ተመርኩዞ ዘላለማዊ ባላንጣነትን ለመፍጠር፣ ትውልድን ለመመረዝና
አገርን ለመበተን የሚደረገውን አሰልቺ ዲስኩር ‘ይቅርብን፣ አይበጀንም’ ለማለት ይመስላል። ገሚሱ ያገሬ ሰው ተደሰተ ኮራ፤
ገሚሱ በተለይም ዘመንተኛው ጠባብ፣ ሊቅ ነኝ ባዩ አጉተመተመ…..
“በምንሊክ ህልፈተ-ህይወት መቶኛ አመት መቃረቢያ ግለቱ አየለ – አዲስ ጣሪያ ነካ – ፈረንጆቹ ‘a new high’ እንደሚሉት
ዓይነት። ሥድቡ አዲስ ዝቅጠት ወረደ -ፈርንጆቹ a new low እንደሚሉት።የምንሊክን ጀግንነት እና ላገር የዋለውን ውለታ
ሊዘክሩ ቁጭ ብድግ የሚሉት ‘ጀግና፣ ደግ፣ ጥበበኛ!’ ሲሉ ሌሎቹ ደሞ ‘ራሱ ድል ከመታው ፋሺስት ጣልያን ያልተሻለ
ጨካኝ፣ ግፈኛ፣ በአርሲ ጡት ያስቆረጠ!’ እያሉ ሬዲዮኑን፣ ቴሌቪዥኑን ኢንተርኔቱን አጣበቡት። የምንሊክ መሰደብ
እንዳርጩሜ የቆጠቆጣቸው የአፀፋ ምት በሚመስል መነሰሳት በሰላ ብዕራቸው ‘ ጡትና ብልት መቁረጥማ የአማራ ባህል
አይደለም፣ የምንሊክም ስብዕና አይደለም፤ ይልቁንም የዚህ ዘር ባህል ነው’ እያሉ እራሳቸው የሚጠሉትን ጥቅል ውንጀላ
ባንድ ዘር ላይ አሳረፉ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ግጭቱ ያስደሰታቸው ዳር ቆመው ይሥቃሉ….ወንድሜ! ብታይ የሰሞኑ ውሎ ልብ
ይሰብራል…አቅል ያሳጣል…” አለው።
መኮንን በሌላ የራሱ ሃሳብ ጭልጥ አለ፦
‘የፈረደበት የኦሮሞ ህዝብ – ጫፍና ጫፍ ቆመው የሚጓተቱ ጠባብ ልሂቃን በታኝ የሆነ ድራማቸውን የሚተነውኑበት ስቴጅ
ነው፤ ካንድ ጫፍ “እንዳንበጣ ከሰማይ የዘነብክ፣ ከኬንያ ወይም ከኡጋንዳ ፈልሰህ ኢትዮጵያን የወረርክ፣ በጭካኔ
እየጨፈጨፍክ ተስፋፍተህ የሰው መሬት ይዘህ ሳለ ባንተው ብሶ ‘ልሂድ፣ ልገንጠል’’ ትላለህ” ይሉታል። በወዙ የህዝቡን
ሆድ እንዳልሞላ፣ በደም ባጥንቱ ኢትዮጵያን እንዳልጠበቀ፣ ታሪኳን እንዳልሰራ፣ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያን ሆና በኖረችበት
ዘመን ሁሉ እንዳልነበረ ባዕድ ያደርጉታል፤ ለማጅ ኮሜዲያንስ አፋቸውን ያሟሹበታል! 2

በሌላ ጫፍ ደግሞ የራሱ ተወላጅ የሆኑ የዘመናችን ጉዶች “ኢትዮጵያዊ አይደለህም፣ አገርህም ‘ኦሮሚያ’ የምትባል የቃል
ኪዳን አገር -the promise land- ናት፤ኢትዮጵያ በሚሏት ኢምፓየር -በበጎዋም በክፉዋም እጅህ የለበትም፣ ሃውልቱም፣
ታሪኩም፣ ቋንቋውም ያንተ አይደለም” ይሉታል። ‘ለመሆኑ የአማርኛን ፊደል ለአማራ ማን ሰጠው?’ ብሎ የሚጠይቅ የኦሮሞ
ጀግና ጠፍቶ በሥነ-ቋንቋ ጠቢብነት በተሽሞነሞነ ጥላቻ ብቻ የራሱን ሥልጣኔ ጠልቶ በላቲን ፊደል እንዲጠለል አደረጉት፤
ኢትዮጵዮጵያ የራስዋ ፊደል ያላት ብቸኛ አፍሪካዊት አገር ነች ሲባል የኦሮሞ ህዝብ በላቲን ጥላ ስር ተጠልሎ እንዴት የዚህ
ቱሩፋት ባለቤት ሊሆን ይችላል? ያማርኛ ፊደል ለኦሮምኛ ቃላት አጠራር ያስቸግራል ቢሉ እንኳ እነዚህ ሊቆች ለምንድነው
የራሳችንን ፊደል አቃንተው ወይም አጉብጠው ለኦሮምኛ እንዲስማማ ለማድረግ የቋንቋ ጠቢብነታቸውን ያላሳዩን?
“ኢትዮጵያ ያንተም ነች፣ አክሱምም፣ አድዋም፣ ማይጨውም፣ ጉራኤም፣ ፊደሉም፣ በጎውም ክፉውም ሁሉ ያንተም ነው!”
የሚለው የኦሮሞ ጀግና ጠፍቶ…
‘በሽታችን ጠንቶብናል፣ ታሪካችን የታሪክን ዕድፍ እየጠጡ እራስ ማዞር ስለሆነ አገርና ነፃነት የሰጡንን አባቶች ‘ፋሽስቶች’
እያልን የምንጠራ ለከት ያጣን ዘመንተኞች ሆነናል….

መኮንን ምንሊክን አሰበው…እንደሰው…እንደኔ…እንዳንተ… እንዳንቺ…
አባቱን በህፃንነቱ ያጣ፣ አባቱ ያሠረለትን የውርሥ ክታብ እንኳ ምን እንደሆን ተመራምሮ ለማወቅ ያልሞከረ፤ ይልቁንም
በቃልኪዳኑ ጠብቆ ያቆየ፤ በየዋህነት አንገቱን ለቴዎድሮስ መስዋዕት አቅርቦ ክታቡን ያስረከበ፤ ከወላጅ ትንፋሽ ርቆ ለሱ
አዲስ በሆነ ዓለም ከ 9 ዓመት በላይ የታገተ፣ እስቲመለስባት ድረስ በሸዋ ናፍቆት የነደደደ፤ በመልኩ እና በእናቱ የዘር
ማንነት እስተዛሬ ድረስ በሃሜት ጦር የሚ’ወጋ፣ በትውልድ፣ በጋብቻ፣ በወዳጅነት ከኦሮሞ ድርና ማግ ሰብዕናው
የተፈተለች፤ ድፍረትና ዘዴ ያለው፣ እንደሰውም የሚፈራ, የሚያፈገፍግ፣ ሚስቱን የሚሰማ፣ ባገሩ ጠኔ ሲገባ ዶማ ይዞ
እየቆፈረ ‘በከብት ብቻ አይደለም የሚታረስ’፣ ብሎ ያስተማረ፣ ባሪያ አትፈንግሉ፣ ጥበበኛን አትስደቡ ብሎ ያስተማረ፣
የማረካቸውን ጠላቶች ቁስላቸውን እያጠበ በጋቢው ያደረቀ፣ የወጉትን ጣልያኖች የጭነት ከብት ሰጥቶ ‘ሂዱ’ ያለ፣ ‘ያባቶቼን
አገር መልሼ እንዳቋቁም እርዱኝ’ እያለ ፈረንጆችን ደጅ የጠና፣ ገብረህ ከኖርክ የራሰህን ሰው እሾምልሃለሁ እምቢ ካልከኝ
እቀጣሃለሁ’ እያለ በዘዴም በጉልበትም አገር ያቆመ፣ የታሪክ ምሁራን ‘የ 20ኛውን ምዕተዓመት የአፍሪካ ነፃነት ምዕራፍን
የከፈተ ድል ነው ብለው የፃፉለትን አድዋ የሰጠንን መሪ ዘረኛ እና ፋሽስት ብለው ሰደቡት…
‘ ምንድነው ችግራችን? ፍቅር ማጣት? ጂጂ ትዝ አለችው – “እኔን የራበኝ ፍቅር ነው!”:: ፍቅርማ ለቻለበት በጎ ነው:: ግን እኮ
ፍቅር እንደጉም ነው – ወይም ሰማይ ነው…ሰማይ ደግሞ ሰማይ ነው…. አብሮ ለመኖርና ለማደግ የግድ ‘አፍቅረኝ’ አይደለም
የምልህ; ‘ባንቀልባ አዝለኸኝ ዙር’ አይደለም የምልህ…ታሪካችንን የኛ ነው እንበል፣ ሁላችንም ሃላፊነትና ባለቤትነት
እንውሰድ፣ አንጓተት…አየህ እኔና አንተ ስንጓተት ቤታችን ትፈርሳለች፤ ቤታችን ሰትፈርስ ደሞ እንታረዛለን፤ እንጠለልበት
ጣሪያ እናጣለን…ችግር ቸነፈር ዕጣችን ይሆናል…እግራችን ይራመድ…አዎ እዛው ጂጂ ዘፈን ውስጥ ‘እግር ተራመድ…ምን
ያኳትንሃል ቆንጥር ለቆንጥር….’ የሚል ቋጠሮ አለ አይደለም እንዴ? 21ኛው ክ/ዘመን ላይ ቂጥ ብሎ 19ኛውን ክ/ዘመን
በጎሪጥ እያዩ ህፀፅ ማደን ህፀፅ መብላት ህፀፅ መተንፈስ ቢበቃ ምን አለ…..
አሃ! እንዲያውም ስለዚህ ነው መፃፍ ያለብኝ…ጨዋታ ብጤ…ምንሊክን ከተኛበት አስነሳውና መድረኩ ላይ 19ኛው ክ/ዘመን
ተብሎ በተሰየመ ዓለም በግራ በኩል አስቀምጠዋለሁ፤ እኔ ደሞ 21ኛው ክ/ዘመን በሚባለው ዓለም ጥግ እቆምና iPhone
በጆሮዬ እንደወተፍኩ እሞግተዋለሁ፦
መኮንን:- ምንሊክ ክስ ቀርቦብሃል፣ ተከላከል!
1ኛ) ሥልጣን የያዝከው ሳትመረጥ፣ መድበለ-ፓርቲ ሥርዓት ሳይኖር፣ ገለልተኛ ፍ/ቤትና የምርጫ ቦርድ በሌለበት
ነው…ባጠቃላይ ዲሞክራሲያዊ አልነበረም
ምንሊክ፡ ምን አልከኝ? ዲ…ሞ…
መኮንን:- ሄሎ! ዲሞክራሲ …አንድ ሰው አንድ ድምጽ ….secret ballot! 3

ምንሊክ፡ ምንድነው እሱ?
መኮንን:- መልስ ሥጥ እንጂ!
ምንሊክ፡ እሱን የሚያብረቀርቅ ነገር ጆሮህ ወትፈህ አልሰማኸኝም እንጂ ‘ምንድነው የምትለው?’ ብዬህ ነበር
መኮንን:-Never mind…
2ኛ) ያኔ አገር አቆማለሁ እያልክ ስትዞር እምቢ ያሉህን ክፉኛ ትቀጣ ነበር ይባላል፤ እንዲያውም አሮሞን
ትጠላለህ፤ ጡት ሁሉ አስቆረጠሃል ይሉሃል
ምንሊክ፡ በሥም-አብ ፣ ወወልድ ፣ ወመንፈስ ቅዱስ
መኮንን:- መልስ የለህማ!
ምንሊክ፡ ያምላኬን ሥም ጠርቼ ተማማተብ በላይ ምን መልስ አለ?
መኮንን:- ቢሆንም አንዳንዱ የተሰራው ነገር ከ ጄኔቫ ኮንቬንሽን ጋር አይሄድም!
ምንሊክ፡ ምን አልከኝ?
መኮንን:- ኔቨር ማይንድ!
3ኛ) በአድዋ ጦርነት በርግጥ ድል አድርጋችኋል…ቢሆንም ካስራ ስንት ሺህ ሰው በላይ አልቋል…በነፍስ ወከፍ
መሣሪያ ዘምቶ ያን ሁሉ ሰው ከማስጨረስ አንድ ሁለት ተዋጊ ጀቶች ልኮ ጣልያንን ማርበድበድ ይቻል ነበር
ምንሊክ፡ እሱ ደሞ ምንድነው?
መኮንን:-አይ! እሱን እንኳ ተወው – it would not be fair on you…አሁን ትዝ ሲለኝ ለካስ በአድዋ ጊዜ አውሮፕላን ገና
አልተፈለሰፈም …በፈርንጆች 1902 አካባቢ ነው የተፈለሰፈው…በቃ ተወው…ግን ቢሆንም ታንኮች ምናምን፤ ቢ. አር.
ምናምን መጠቀም ይቻል ነበር…..
4ኛ) እና መጨረሻ፡ ለኢትዮጵያ መሠልጠን ብዙ ለፍተሃል እያሉ ይክቡሃል…ለምሣሌ ሥልክ፣ ፖስታ፣ ተሌግራፍ፣
ባቡር ምናምን….ግን ኢንተርኔት፣ ሞባይል፣ ኢሜል ምናምን አላስገባህም …እንዲያውም ብዙ ሰዎች ለምን
ሞባይልና ኢንተርኔት እንዳይስፋፋ እንደምትከለክል ይገርማቸዋል!
ምንሊክ፡ ምን አልከኝ?
መኮንን: -You know…wireless, computer, Bill Gate…hello!!!!!!

ምንሊክ፡ ከመቀመጫው ይነሳል…” በል ተወው ልጄ… ከቀልብህ ያለህ አትመስለኝም….ለማንኛውም ስለጠየከኝ ጉዳይ ሁሉ
ጣይቱ ታውቅ እንደሆን እጠይቃታለሁ…ወትሮም ቢሆን እንዲህ እንዲህ ያለውን አፍ የምታውቅ እሷ ናት…ልባም ናት
እሱዋ…እኔማ…እኔማ ምን ልብ አለኝ “ ብሎ አንገቱን እንደደፋ በትካዜ ከመኮንን ዓይን ራቀ።
መኮንን: -Menilik! Come on now! … don’t be sad! This is just a play….(ወደ ህዝቡ እያየ)… He
really took it personally, didn’t he? ok bye Menelik… Facebook ላይ like አረግሃለሁ ok?
መኮንን በምናቡ ያሰበው ፣ ነገር ግን ያልፃፈው ድራማ በዚህ ሁኔታ ሲፈፀም ምንሊክ አሳዘነው። እናም እንዴት ልካሰው
ሲል እራሱን ጠየቀ። 4

አዎን! ድርሰት፣ ድራማ፣ ተዋናይ፣ መድረክ፣ መጋረጃ፣ ምናምን ከሚሉት ሽሽት ወጥቼ እኔ እንደ ሰው እንደ ኢትዮጵያዊ
ጀግኖቻችን ለዋሉልን ውለታ መወድስ፤ ምንሊክ ለተሰደበው ሥድብ መልስ እንዲሆን የቶሮንቶ ህዝብ የአድዋን በዓል
ሊያከብር እንደታደመ ከፊቱ ቆሜ አመሰግነዋለሁ…አዎ…አመሰግነዋለሁ -በክራር በታጀበ ድምፀት እንዲህ እያልኩ
አመሰግነዋለሁ፦ (በሃሳቡ ክራሩን ያነሳል…ያነበንባል)
 “አሜሪካኖች አውሮፓን በተለይም እንግሊዞችን በነገር ጦር ሲወጓቸው፣ በውለታ ሸክም
ሊያጎብጧቸው ሲፈልጉ፡ “እኛ ባንደርሰላችሁ ኖሮ ይሄኔ ጀርመንኛ ነበር የምታወሩት” ይሏቸዋል።
የ 2ኛው ዓለም ጦርነትን ለምታቅውቁ አባባሉ እውነትነትም ውሸትም ግነትም አለው…
 “ቢሆንም በቋንቋ ከተገለፀው ሽሙጥ ጀርባ ያለው ቁምነገር ሃይለኛ ነው….
 “ቋንቋንማ ገዝተው ይማሩታል፣ ፈልገው ያውቁታል፤ እሱ አይደለም መልዕክቱ…
 “መልዕክቱ፣ ‘እኛ ባንደርስላችሁ ኖሮ የራሳችሁን ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነት ሳይሆን የሌሎችን
ቋንቋ ፣ ባህል፣ ታሪክ በግድ የምትማሩና ብውርደት የምትኖሩ ፣ ባሮች ትሆኑ ነበር ‘ ነው።

 “እናም፣ ምንሊክ፣ ጣይቱ፣ አሉላ፣ መኮንን፣ ገበየሁ፣ መንገሻ፣ ወሌ፣ ሚካኤል፣ ተክለ-ሃይማኖት፣
ባልቻ፣ ሃብተ-ጎርጊስ፣ ጎበና፣
 “የፊተኞቹም ቴድሮስ፣ ዩሃንስ….
 “የኋለኞቹም፣ አብዲሳ፣ እምሩ፣ በላይ፣ ጃጋማ፣ ዘርዓይ፣……
 “እንዲሁም- መኳንንት ወይም መሣፍንት ስላልነበራችሁ ሥማችሁ ያልታወቀ ያገሬ አማሮች፣
ኦሮሞዎች፣ ትግሬዎች፣ ጉራጌዎች፣ ሱማሌዎች…..
 “-ታሪካችሁ እየተድበሰበሰ ጀግንነታችሁ ያልተፃፈላችሁ ነገር ግን የአድዋንም የማይጨውንም
ሸክም በጀርባችሁ የተሸከማችሁ ሴቶች ጀግኖቻችን….
“አማርኛን ፣ ኦሮምኛን እንጂ! ትግርኛን ፣ አገውኛን እንጂ! አፋርኛን ፣ ሶማልኛን እንጂ!….
ጣልያንኛን፣ ቱርክኛን፣ ወይም አረብኛን ተገደን ከመናገር ስላዳናችሁን፤
“ይህችን በጎረቤቱ፣ በቤተዘመዱ፤ በዕድሩ፣ በሰንበቴው፤ በክርስትናው በእሥልምናው፤ በጥምቀቱ፣
በኢሬቻው፣ በሠርጉ በለቅሶው፣ በድህነታችን በምንቀልደው ቀልድ- እየተገለጠች፣ እየተከሰተች፣ ገሃድ
እየሆነች፣ ማንነታችንን የምታሳየንን መሥታወት ኢትዮጵያን ስለጠበቃችሁልን….
“ይህችን ሲኖሩባትም ሲርቋትም የምትናፍቅ እናት ዓለም ኢትዮጵያን ሰለሰጣችሁን፣ስላቆያችሁልን….
ከልብ እናመሰግናለን!!! አዎን እናመሰግናለን!!!! እናመሰግናለን!!!! ”

አለቀ
bayu777@yahoo.com

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on March 5, 2014
  • By:
  • Last Modified: March 5, 2014 @ 9:46 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar