www.maledatimes.com “የኤደን ክፍል” (በዙፋን ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“የኤደን ክፍል” (በዙፋን )

By   /   March 9, 2014  /   Comments Off on “የኤደን ክፍል” (በዙፋን )

    Print       Email
0 0
Read Time:22 Minute, 53 Second

ኔትዎርኩ አያወላዳም ::ኢንተርኔት ካፌ መጠቀም እንዳልብኝ አስቤ ስገባ ውርውር የሚለው ብዛቱ ደስ አይልም::ከፍቼ የማነበውን በድንገት ከች ብሎ የሚመለከት ባለኢንተርኔት ካፌ ቤት(ተቀጣሪም) ገጥሞኛል::የኔ ቢጤ እንግዳ ሲሆን ደግሞ ቁጥጥሩ ይጠብቃል::ከሪያድ ተመልሳ ወደ ሀገር ገብታ ኢንተርኔት ካፌ ከከፈተች ልጅ ተዋውቄ ትንሽ ዘና እያደረገችኝ ነው::ኤደን ትባላለች::
ሳኡዲያን በጣም ትወዳለች::ምንም ያህል ስለ ሳኡዲያ ብታወራ አይሰለቻትም::ጓደኛዋ እንደነበርኩ ለሰዎች አስተዋውቃለች::እኔም ይሁንልሽ ብያታለሁ::
ኤደን ሪያድ አብረዋት ከነበሩ ጓደኞቿ የቂማ ፕሮግራም ለዛሬ (ሀሙስ)እንዳላት ነግራኝ ስለነበር በሰአቱ ከካፌዋ ተገኘሁ::ከጀርባ ከተያያዘው ካለው አንድ ክፍል ገባሁ::ሳኡዲ አረቢያ ካሉ ያማሩ ቤቶች የሚለየው የአየር ማቀዝቀዣ ያለመኖሩ ብቻ ነበር::
ጓደኞቿ በየተራ የተለያዩ ለቂማ ወይም ለሆድ የሚሆኑ ቁሶች ይዘው መጡ::አዲስ በመሆኔ ህግ ለመተላለፌ ይቅርታ ጠይቄ ቦርሳዬን ከፈትኩ::
ኤደንና አራቱም ሴቶች ስጋቸው ብቻ እንጂ ሁለመናቸው ሳኡዲያ ነበር::አይግረማችሁና አማርኛ የሚጠቀሙት በስሱ ነው::አፍ መፍቻ ቋንቋቸው አረብኛ ነው የሚመስለው!ሺሻው፣ከሰሉ፣ሙዚቃው ክፍሉን ድብልቅልቅ አድርጎት ላየ የጠንቋይ ግርድ ይመስላል::ያለእድሜያቸው በትዝታ ከሚኖሩ እነዚህ አምስት ሴቶች መሀል መገኘቴ ምቾት አልሰጠኝም::ከዛሬና ነገ ይልቅ ትናንትናን መዘከር ይወዳሉ::ከሚያደርጉት ውስጥ የምፈቅደው ወይም የማልጠላው የለኝም::ሪያድ እያሉ ስለሰሯቸው ወንጀሎች እንደጀብድ እያውካኩ ያወራሉ::እኔም እያማጥኩ የገረጣ ፈገግታዬን አሳያለሁ::
ኤደን ትናንት ስለጓደኞቿ ከነገረችኝ አንድ የሳበኝ ታሪክ ስለነበረ ነው ዛሬ ከነሱ የተወዘትኩት::ባለ ታሪኳ “ሳምራዊት” ብትባልም ትክክለኛ ስሟ እንዳልሆነ አውቄላታለሁ::
“ሳምራ አሁን ምን እየሰራሽ ነው?”አልኳት
“እንደመጣሁ ጸጉር ቤት ከፍቼ ነበር ::ከሰርኩና ዘጋሁ::ከመዝጋቴ በፊት በደንበኝነት ያወቅኳት ሰው አንድ ታዋቂ የውበት ሳሎን በጥሩ ደመወዝ ሰራተኛ መቅጠር እንደሚፈልግ ነግራኝ ከሀላፊዋ አገኛኘችኝ::አሜሪካ የምትኖር ሰው የከፈተችው ይሄ ቤት የውበት ሳሎን ይባል እንጂ ከዚያ የራቀ ስራ ይሰራበታል::የሰውነት መታሻ፣የሌዘር(የውስጥ ገላ ጸጉር ማንሳት ያካትታል) አገልግሎት ይሰጥበታል::
ጥሩ ደመወዝ ይከፍላሉ::ትኩረቴ ያ ስለሆነ ተስማምቶኛል::ከጸጉር ስራ ይልቅ መታሻ(ሳውና) የበለጠ ክፍያ አለው::መጀመርያ ይከብዱኝ የነበሩ ስራዎች አሁን ተላምጃቸዋለሁ::በተለይ ወንዶችን ራቁታቸውን ማሸት፥በጣም ጥሩ ለሚከፍሉ ደምበኞች ቤታቸው ሄዶ የማሸት ወይም መታሸት አገልግሎት ለሚፈልጉ”ክትክት ብላ ሳቀችና ሲጋራዋን በረጅሙ ማገች፥ቡልቅ ስታደርገው በሚወጣው የጭስ ህብረ ስእል ቅዝዝ አለች::
“በተለይ ስራ የጀመርኩ ሰሞን ቁርጥማት አለብኝ ብለው የወሰዱኝ ሽማግሌ ሌሊቱን ከጓደኛቸው ሲያሰቃዩኝ ነበር ያደሩት”
“እንዴት?”
“ዙፍ አልተረዳሽኝም መሰለኝ፥ስራው ሁለገብ ነው::ወንድ ወይም ሴት ደምበኛ በመታሸት ስም ሴቶች ወይም ወንዶች ጋ ይገባና ሸርሙጦ አለያ ሸርሙጣ ትወጣለች::ቁርጥማት ተሰምቷት ለመታሸት የመጣች የቤት እመቤት ጎበዝ ማሳጀር አለ ብለው ወንድ እንድትመርጥ ያደርጓታል::ባልጠበቀችው ሁኔታ ሁሉን ትደረግና የቤቱ ዘለአለማዊ ደምበኛ ሁና ትቀራለች::”
ግራ መጋባቴ ተረዳችልኝ
በሀኪም ትእዛዝ ለመታሸት መጥተው ቤቱን ከተላመዱ በኋላ እየከፈሉ ዝሙት የሚሰራባቸው የመንግስት ሰራተኞች እና የቤት እመቤቶች ወይም ልጃገረዶች ብዙ ናቸው::ከሁሉ የሚደብረው ወንዶቹ ከወንዶቹ የሚያደርጉት ነው::”ብላ ፊቷን አጨፈገገችው::
“እኛ ሴቶቹ ጋ የሚመጡ ሌዝቢያኖችም አሉ::ግን ፊት ያያሉ::እኔ ስለማይጥሙኝ አንዲት አይጥ አለች ለሷ አስተላልፋቸዋለሁ::”
“ሳምራ ይሄ ሁሉ ሲሆን የመንግስት ቁጥጥር የለም?”ስላት
“ኧረ ባክሽ ቅዳሜና እሁድ የመንግስት ባለስልጣናት ነው ቤቱን የሚያጣብቡት::”ብላ ትከሻዋን ሰበቀች::
እድሜና ኔትወርክ ካገኘን እንቀጥላለን::
ይህን ጽሁፍ በሌሎች ገጾች ሊንክ ብታደርጉ አትኮነኑም::እኛ ዘንድ ከጸሀዩ በቀር ሁሉም ብሎክ ነው!እሱንም ቢችሉ ብሎክ ያደርጉብን ነበር!ጓደኞቿን መስላ ለመኖር በምታደርገው ራሷን አጥታለች::ውበቷን ያጠራው ልጅነቷ እይታ ይጫናል::የአነጋገር ዘዬዋ የተወለደችበትን ክልል ያሳብቃል::ዜድ እያሉ ነው የሚጠሯት::ዚነት መሆኗን ብዙም ደስ ሳይላት ነው የተረጎመችልኝ::
ከተሜ መምሰል ትፈልጋለች::ምናልባትም “አራዳ” ለመሆን ወሳኙ የሚስጥር ቁልፍ አድርጋ ወስዳው ይመስለኛል::እነኤደን በድርጊቷ ሁሉ ሙድ ይዘው ይስቁባታል::እኔ እሳቀቅላታለሁ::እሷ ደግሞ ሁሉን ቸል ብላ የመሰላትን ትናገራለች:: ኤደን “አራድነትና ወራድነት አልለየችም::” ብላ ሹክ ብላኛለች ተገርሜ ስመለከታት::
ዚነት ከመቶ ስድሳ ሺ በላይ ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገር ሲመለስ አዲስ አበባ ብትመጣም እስካሁን ቤተሰቦቿ ሳኡዲ እንዳለች ነው የሚያውቁት::በእጇ ላይ የነበረው ገንዘብ እስኪያበቃ አሜሪካ ጊቢ አካባቢ አልቤርጎ ተከራይታ ወደሌላ አረብ ሀገር ለመውጣት በደላላ ስትሞካክር ገንዘቧን ወስደውባት ባዶ አስቀሯት::በዚህ የጭንቅ ወቅቷ ሪያድ በአይን ከምታውቃት ሶስና ተገናኘች:: ወደፈለገችው ሀገር እንደምትሸኛት አግባብታ ወደ ቤቷ ይዛት ሄደች::
ዚነት ሶስናን እጅግ ታመሰግናታለች::ሶስናም ተመጻዳቂ ነገር ስለሆነች አሮጊቷ እናቷ ለዚነት በዋለችው ውለታ እንደሚጸልዩላት በድፍረት ነግራኛለች::
የኤደን ክፍል ከህብረ ቀለም አምፖሎች የተናበረ ጭስ አፍኖታል::
ዚነት በሶስና አማካይነት ወንዶች ተዋውቃለች::ከማናቸውም ፍቅር እንዳይዛት ተመክራለች::አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ ቅዳሜና እሁድ ወደሆነበት ከተማ ወጣ ይሉና ከሌሎች ወንዶች ይዝናናሉ::ሶስና ከሌሎች እየተጨዋወተች ልቧ እኔና ዚነት ጋ መሆኑ አውቄላታለሁ::ነጻነቷን ሁሉ ገፋታለች::የመናገር፣የመልበስ፣የመምረጥ መብቷን ተረክባታለች::ምስኪኗ ዚነት የሶስና እቃ ናት ማለት አምላክ ፊት የሚያስወቅስ ሀሜት አይደለም::የሶስና እጆች ዚነት ገላ ላይ ሲያርፉ የሚዳስሱት አካል ለመመልከት ለኔ ቢጤዋ ድፍረት ይነሳል:: ጨዋነት የማይፈቅደው ያስተማረቻት ክፉ ነገር እንዳለ ያስታውቅባታል::ዚነት በቀላሉ የምትታለል፥ጥሬ ልብ ያላት፥በራስ መተማመኗን እንደባርኔጣ ያወለቀች፥ብርጉግ፥ነጻነቷን የሸጠች ፍጡር!
“ዜ ሌላው ቢቀር ለቤተሰቦችሽ እዚህ መሆንሽን ለምን አታሳውቂም?”ከማለቴ
“ምን ያደርጉላታል ቤተሰቦቿ?እስካሁንስ ሳይሰሙ ቀርተው ነው?የኛ ሰው ገንዘብ እንጂ መቸ ልጁን ይፈልጋል?”ብላ ሶስና አምቧረቀች::ዚነት አንገቷን ሰብራ ተከዘች::በጫት ከተወጠረው ጉንጯ የደም ስሯ በስሱ ይታያል::አንድ ማለት የምትፈልገው፥ከውስጧ የሚሄድ ሀሳብ መኖሩን አይነ ውሀዋ አዋጅ ይላል::ከሶስና ጋር ያቆራኛቸው መተዛዘን ብቻ አይመስልም::ሶስና በሰብአዊነት እየረዳቻት ለመሆኑ ሰጋሁ::በልጅነቷ፣በውበቷ እየተጠቀመችባት መሰለኝ:: “ምን ልረዳት እችላለሁ?”ብዬ ራሴን ጠየቅኩት::
“ዜድ የየት ሀገር ሰው ነሽ?”
“ዜድ ተነሽና ይሄን ሲዲ ቀይሪው!”ሶስና ከቦክስ በተስተካከለ ግልምጫ አጎነችኝ::በቃ መልእክቱ በወጉ ደርሶኛል::ሶስና ነገረስራዬ አልተመቻትም::ይህችን ልጅ ለመርዳት ለማልችለው ከአሳዳሪዋ ሶስና ባልቀያየም መረጥኩ::ቢያንስ እነዚህ አምስት ሴቶች ለዛሬ በሰላም አብሬያቸው ማሳለፌ አንድ መጽሀፍ ከማንበብ ያልተናነስ እውቀት እንደምሸምትበት አውቄያለሁ::
አዝማሪውን የማይለዩት የአረቢኛ ሙዚቃ ከፍተው ለመደነስ ተነሱ::ልቤ ዚነትን መሰል ስንት ሺዎች በሶስና አይነቱ መደፍ ወድቆ የስሜት መጫወቻ እንደሆኑ እየመዘነ ነበር::
ዚነት ነገን እንዳታስብ፣የዛሬ ኑሮዋን እንዳትኖር በሀሳብ ግርዶሽ የታጠረባት፥በጭካኔ ሸለቆ የምትዋትት የዋህ ፍጡር ናት!ዛሬ ባላት ውበት የሚስብ እሷነቷ አንዳች ቀሳፊ በሽታ እንዳይጭንባት ተመኘሁላት::ባያምርባትም ሰውን ለመምሰል ብላ በአረቢኛው ሙዚቃ የምትውረገረገው ዚነት የእሳት እራት መሰለችኝ!
ምንም ልረዳት እንደማልችል ትዝ ሲለኝ ባለቤቱን የረሳሁለት “ማሰብም ይደክማል” የሚለው የፌስ ቡክ ግጥም አስታወስኩ::
ካልሰለቻችሁ “የኤደን ክፍል” ሌላም ታሪክ አለው!
የግብጹ ሆስኒ ሙባረክ በስልጣን ዘመኑ የኑሮ ውድነት በማባባስ ህዝቡ ስለኑሮው ብቻ በመጨናነቅ በመሯሯጥ ፖለቲካውን እንዲረሳለት ይሰራ ነበር::ዛሬ ሀገርህ ኢትዮጵያ ኮፒውን ነው የምታነበው::
ስምንት ሰአት የሚሰራ ባተሌ ከአራት ሰአት በላይ በትራንስፖርት እንዲንከራተት መተው፥የቴሌፎን እና ኤንተርኔት አገልግሎት ለመቆጣጠር ኔትወርክ ማገድ…..ባካችሁን ቅኝ ይሁን ግራ የምንገዛው አልገባ ብሎኛል!!ለማንኛውም እናንተዬ በአይኔ እየዞራችሁ በኔትዎርክ ማእቀብ ልደርስባችሁ ያለመቻሌን እወቁልኝ::ሶስት በሶስት የሚሆነው ኤደን ክፍል እንመለስ
ከወደአፌ የገባው ፔፕሲ አልኮል እስኪመስለኝ ብው ብያለሁ::እነሱ በቃሙት እኔም መረቀንኩ::ሁለት ለሁለት በያዝነው ጨዋታ ከአምሳለ አፍ ገጠምን::የአሰበ ተፈሪ ልጅ ናት::ተግባረ እድ የሙያ ትምህርት ቤት ሁለት አመት ሞክራ በችግር አቋርጣ ወደ ሪያድ እንደሄደች ነው የነገረችኝ::ቀለም ቀመስ መሆኗን የማያስዋሽ ነገሮች አሏት::
“ሰርቼም ተሰርቼም ነበር የቤተሰብ ህይወት ለመቀየር የደከምኩት::ድህነትን ዘርሬ ለማለፍ ገንዘብ ማግኘት የምችልበት ሁሉን ነገር ሞክሬያለሁ::ከግርድና እስከ…” በምሬት ከእጇ ያለውን የጫት ቀንበጥ ወረወረችው::”…ኑሮ ተስተካክሏል ብዬ ስመጣ ያገኘሁት ያልጠበቅኩትን ሆነ፥ሰውነቴን ሸጬ የሰበሰብኩትን አብከነክነው ጠበቁኝ::በወንድሜ ስም የገዛሁት ሚኒባስ፥ የለም!ባንክ በስሜ እንዲያስቀምጡልኝ እልከው የነበረ ገንዘብ የለም!ከጆሮና አንገቴ ለቅሜ የላኩትን ጌጥ ሊጠብቁልኝ አልቻሉም::ወላጅ እናቴን ልጣላ ወይስ ማንን?ከሳኡዲ ውጡ ተብለን ስመጣ እመቤት ሆኜ እንደምኖር ያሰብኩት ሰው ቤተሰቦቼ ሴተኛ አዳሪ አደረጉኝ!…”
አምሳለ ታሳዝናለች::ከልቧ ነው የተማረረችው::
“…ታውቂያለሽ ቤተሰብ በሌለው ሰው እንደምቀና?እነሱን ሰው ለማድረግ ብዬ እንጂ አንዱን ቁሌታም አረብ አግብቼ ተከብሬ እኖር ነበር:፡ኧረ ያባከኑብኝ ብር ሀገሬ ውስጥም እንደጩሎ የማዘው ባል እገዛበት ነበር::ወንድሞቼ ገንዘቡን ተጠቅመው ራሳቸውን ቀይረውበት ቢሆን እጽናና ነበር::ማናችንም ሳንጠቀም ተጣልተን እና ፊታቸውን ላለማየት ተቆራርጫቸው መለያየቴ ነው የሚነደኝ::..”ሲጋራዋን ለኮሰች::
አምሳለ ወዲህና ወዲያ እያለች ነው የምትኖረው::በየጎዳና ከሚያነሳት ማደሯ በተጨማሪ በደምበኞቿ ባለታክሲዎች እየተረዳች ውንብድናም እንደምትደፍር አልደበቀችኝም::
ኤደንን ‘እግዚያብሄር በክፉ ቀን የሰጠኝ እህቴ’ ትላታለች::ሁሉም ነገር ሲበለሻሽ ወደ ኤደን እየመጣች ታሳልፋለች:፡ገንዘቧንም በአደራ ትጠብቅላታለች::ከቤተሰቦቿ ልታስታርቃት እንደምትሞክርም ነግራኛለች::
“…ቤተሰቦችሽን የምትረጂ ከሆንሽ፥የዛሬ የነሱን ችግር ብቻ ሳይሆን የነገ የራስሽን መውደቂያ አትርሺ::ነገ ሸክም ልትሆኚባቸው ዛሬ የማይዘልቅ ጥጋብ ብታላምጃቸው ሁላችሁንም ይጎዳል!!…”ጠንካራ መልእክቷን እንደምስማማበት ራሴን ነቅንቄ አረጋገጥኩላት::
የአምሳለን እንባ የሚያነቡ ብዙ አስር ሺዎች እንዳሉ አምናለሁ::በተለይ በአረቡ አለም የሚኖረው ሰዋችን ነገን መዝኖ የማሰብ ብቃቱ መፈተሽ ይፈልጋል::

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on March 9, 2014
  • By:
  • Last Modified: March 9, 2014 @ 4:28 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar