www.maledatimes.com “የሚሊዮኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነት ዘመቻ” ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“የሚሊዮኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነት ዘመቻ” ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)

By   /   March 10, 2014  /   Comments Off on “የሚሊዮኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነት ዘመቻ” ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)

    Print       Email
0 0
Read Time:20 Minute, 26 Second

ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2006 (Monday, March 10, 2013)

ይኽን ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ዐርብ የካቲት 28 ቀን (March 7, 2014) አንድነቶች “የሚሊዮኖች ድምፅ
ለመሬት ባቤትነት” የሚል ህዝባዊ ንቅናቄ (ህዝባዊ ሰላማዊ ዘመቻ) በ14 ከተሞች {አዲስ አበባ፣ ደሴ፣ አዋሳ፣
አዳማ/ናዝሬት፣ መቀሌ፣ ደብረታቦር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ድሬ ደዋ፣ ጅንካ፣ ቁጫ፣ አሶሳ፣ ነቀምት፣ ለገጣፎ፣ እና
በተጓዳኝ ከተሞች ወልዲያ፣ ጋምቤላ፣ ም/አርማጨሆ(አብርሃ ጅራ)} እንደሚያደርጉ ማሳወቃቸው ነው።
መግለጫቸውን እንዳነበብኩ ዘመቻው ለታሪካችን፣ ለተያያዝነው የነፃነት ትግል እና አይናችን ለተከልነበት
የዴሞክራሲ ሽግግር የሚሰጣቸው ጠቀሚታዎች አሉን? የሚሉትን ጥያቄዎች አንስቼ ጥቂት ከራሴ ጋር ከተነጋገርኩ
በኋላ ለዘመቻው ድጋፌን በመስጠት እና አንድነቶችን በማበረታት ተሳትፎዬን እንድገልጽ ህሊናዬ የግድ አለኝ።
ስለዚህ የዚህ ጽሑፍ ግብ ዘመቻው የህውሃት/ኢህአዴግን የመሬት ባላቤትነት ፖሊሲ ለማሻሻል ብሎም ዛሬ
በኢትዮጵያ የምርጫ ፓርቲዎች የሚያካሂዱትን የነፃነት ትግል እና ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር
የምታደርገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ሊሰጥ የሚችለውን ጥቅም መመርመር ነው።

ታሪካችን እንደሚያመለክተው በዘውዳዊው ስርዓት የኢትዮጵያ መሬት ባላባቶች ነገስታቱ ነበሩ። የ1966 ዓ.ም.
ህዝባዊ አብዮት ጉልታዊውን ስርዓት ቢገረስስም የኢትዮጵያን ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት ማድረግ
ስላልቻለ ሽብርተኛው አምባገነን መንግስቱ ኃይለማሪያም (ደርግ) እራሱን አዲሱ የኢትዮጵያ መሬት ባላባት
(ባላባት) አድርጎ ሾመ። በ1983 ዓ.ም. ደግሞ ህውሃት/ኢህአዴግ በወታደራዊ ኃይል (ሌላ ሽብር) ደርግን አስወግዶ
የኢትዮጵያን የመንግስት ስልጣን እና የመሬት ባለቤትነት ጠቅልሎ በእጁ አስገባ።

የመሬት ባለቤትነት ለአምባገነኖች የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ነው። ሃቀኛው ባለቤት ህዝብ ነው። ይሁን እንጂ
አምባገነኖች በጉልበት የመሬት ባለቤት መሆናቸው የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትም ያደርጋቸዋል። ይህ
የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ከሌሎች የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ጋር ተዳምሮ የህዝባቸውን የፖለቲካ ጸባይ
ለመቆጣጠር (በፍራቻ መግዛት) ያስችላቸዋል። ህውሃት/ኢህአዴግ ደግሞ የመሬት ባለቤትነቱን የጎሳ ፖለቲካ
ስለቀባው ህዝብን ከፋፍሎ ለመግዛት የሚያስችል ተጨማሪ የፖለቲካ ኃይል (የፖለቲካ አቅም) መንጭቶለታል።

የህውሃት/ኢህአዴግ መንግስት መሬት ፖሊሲ በበርካታ ክልሎች መፈናቀል እና አለመረጋጋት ፈጥሯል። ለዚህ
ችግር ዋንኛ ምንጩ የህውሃት/ኢህአዴግ የጎሳ ፖለቲካ የተቀባው የመሬት ፖሊሲ ነው። ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ወደ
አገርህ ሂድ ተብሏል። ተፈናቃዩ ሃብቱን ንብረቱን ተዘርፏል። ይኽን ወንጀል የፈጸሙት የክልል ሹማምንት ዛሬም
ለፍርድ አልቀረቡም። ንብረታቸውን ተዘረፍው የተፈናቀሉ ዜጎችም እስከዛሬ ካሳ አልተከፈላቸውም። እስቲ ይሁን
ብለው በነበሩበት መኖር የቀጠሉት ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩት በስጋት ነው። በአገርህ በስጋት እንድትኖር
የሚያደርግህ የመሬት ፖሊሲ እንዲሻሻል ህዝቡ እንዲጠይቅ ለማድረግ ሰላማዊ ትግል ዘመቻ ካላደረግህ ለምን
ልትዘምት ነው? ስለዚህ የመሬት ፖሊሲ እንዲሻሻል ሰላማዊ ትግል ዘመቻ ማድረግ (መታገል) ለመብት መከበር
የሚደረግ ሰላማዊ ትግል እንጂ ህውሃት/ኢህአዴግ እንደሚለው “ህገ-መንግስት ለመጣስ” ወይንም “ልማትን
ለማሰናከል” የሚደረግ ሁከት አይደለም። ህውሃት/ኢህአዴግ ስለ “ህገ-መንግስት መጣስ” እና ስለ “ልማት
መሰናከል” የሚለፍፈው ህዝብን አሸማቆ በፍራቻ ለመግዛት ነው። እንደ እኔ ከሆነ ደግሞ ከባቡር ሃዲዱ
መዘርጋትም ሆነ ከስኳር ፋብሪካ መተከል በፊት ህዝብ በአገሩ በነፃነት ተንቀሳቅሶ በመረጠበት አካባቢ ኑሮውን
መስርቶ ካለስጋት የመኖር መብቱን የማክበር እና የማስከበር ግዴታ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የአለም
ህዝብም እምነት ነው። ዓለም አቀፋዊ ህግ ነው።

የህውሃት/ኢህአዴግ መንግስት መሬት ፖሊሲ በቡድን እና በግለሰብ መብቶች መካከል ሊኖር የሚገባውን ቅደም
ተከተል ፍትሃዊ በሆነ መንገድ አያስተናግድም። በምድረ ኢትዮጵያ ግለሰባዊ መብት ሳይከበር የቀድሞውም ሆኑ
የዛሬው ጠቅላይ ምንስቴር እየተካሄደ ነው የሚሉን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሙሉ በሙሉ ፌዝ ነው። የግለሰብ
መበት መከበር ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ቅድመ ሁኔታ ነው።

ህውሃት/ኢህአዴግ የገጠር መሬትን የፖለቲካ መጠቀሚያ በማድረግ የስልጣን ዘመኑን አራዝሟል። በየአምስት
አመት በሚደረገው አገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በገጠር የሚኖረውን አርሶ እና አርብቶ አደር የምርጫ ፖለቲካ
ጸባይ ሲቆጣጠርበት (በፍራቻ ተቃዋሚ እንዳይመርጥ ሲያደርግ) ቆይቷል። ህውሃት/ኢህአዴግን ያልመረጠ
ከመሬት ይፈናቀላል፣ የመሬት ማዳበሪያ አያገኝም፣ የተሰጠው መሬት ይቀነስበታል የሚሉትን እና ተመሳሳይ
ማስፈራሪያዎች ናቸው የፖለቲካ ጸባይ መቆጣጠሪያ ሽብርተኛ ፕሮፖጋንዳዎቹ። በምርጫ ዝግጅት ሰሞን እነዚህን የሽብር ፕሮፖጋንዳዎች በካድሬዎች አማካኝነት በማናፈስ የገጠሩ ኗሪ በፍራቻ ለነፃነቱ ሳይሆን ለህውሃት/ኢህአዴግ
ስልጣን ዘመን መራዘም እንዲመርጥ ሲያደርገው ቆይቷል። ስለዚህ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባቤትነት” ዘመቻ
የገጠሩን ዜጋ የራሱ ነፃ አውጭ እንዲሆን እና በምርጫ 2007 ከፍራቻ ነፃ ወጥቶ ለነፃነቴ ይበጁኛል ያላቸውን
ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲመርጥ ያበረታታዋል።

በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የከተማ መሬት ፖሊሲም እንደዚሁ የከተማ ኗሪውን የፖለቲካ ጸባይ ለመቆጣጠር
(ከተሜውን ፈሪ በማድረግ) የተቀየሰ አዲስ የህውሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ነው። እንግዲህ የከተማ
መሬት የመንግስት ከሆነ ህውሃት/ኢህአዴግን የሚቃወም የቤት ባለቤት መሬቱ የመንግስት ስለሆነ እቤትህን
አንስተህ የፈለክበት ሂድ ልትባል ትችላለህ። ይኼን ፖሊሲ ሳስታውስ ሁልጊዜ በአእምሮዬ የሚመጡ እና መልስ
ያላገኘሁላቸውን ጥያቄዎች ላንሳ፥ ሰው ሲሞትስ? እሬሳ ለመቅበር የሟች ቤተሰብ ከመንግስት በሊዝ (Lease)
መሬት ማግኘት አለበት ማለት ነው? ወይንስ እያንዳንዱ ዜጋ ቀደም ብሎ መቀበሪያውን በሊዝ (Lease) ተከራይቶ
ማስቀመጥ አለበት? ሊዙስ (Lease) ለስንት አመት ነው? “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባቤትነት” ዘመቻ ህዝቡ
እራሱን ከዚህ ሰብአዊ ክብር ነፋጊ የህውሃት/ኢህአዴግ አዲስ የፖለቲካ ኃይል ምንጭ በምርጫ 2007 ነፃ
እንዲያወጣ ያዘጋጀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተሰሩት ኮንዶሚኒየሞች የሚኖሩትን እና በመሰራት ላይ ባሉት ውስጥ ለመኖር ተመዝግበው
ተራቸውን የሚጠብቁትን ዜጎች ህውሃት/ኢህአዴግ አንድ ለአምስት የሚለውን መዋቅሩን ተጠቅሞ የዜጎችን
የምርጫ ፖለቲካ ጸባይ በቆጣጠር በምርጫ 2002 ህውሃት/ኢህአዴግን እንዲመርጡ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት
ማድረጉን እናስታውሳለን። ተቃዋሚን ከመረጥህ የተሰጠህን ቤት ትነጠቃለህ፣ ተራህን የምትጠብቅ ከሆነም ቤት
አይሰጥህም በሚሉ ሽብርተኛ ማስፈራሪያዎች በማሰራጨት ነበር የህውሃት/ኢህአዴግ ካድሬዎች የዜጎችን የፖለቲካ
ጸባይ ተቆጣጥረው ተቃዋሚዎችን እንዳይመርጡ ለማድረግ የሞከሩት። “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባቤትነት”
ዘመቻ ህዝብን ከዚህ አይነት የፖለቲካ ጸባይ ቁጥጥር ነፃ ለማውጣት ጠቃሚነቱ ግልጽ ነው።

በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ዜጋ (አርሶ አደሩን ጨምሮ) የመሬት ባለቤት የመሆን መብቱ በህግ ሲደነገግ ብቻ ነው
የመንግስት የመሬት ባላባትነት ገደብ ሊደረግለት የሚችለው። የግለሰቦች መብት ማክበር የመሬት ባለቤትነትን መብት
ያካትታል። በቋንቋ በተከፋፈለ ክልል ውስጥ የሚገኘው መሬት ብቸኛ ባለቤት የክልሉ መንግስት ብቻ ነው ከተባለ
በክልሉ የሚኖሩ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሂዱ ሊባሉ ይችላሉ ማለት ነው። ይኽ እርማት የሚያስፈልገው አደጋ ነው።

ሰላማዊ ትግል ዘመቻዎች ሚናቸው ህዝብን የራሱ ነፃ አውጪ ማድረግ ስለሆነ ይኼም ዘመቻ ለምርጫ 2007
የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ አድርጎ ይሄዳል የሚል እምነት አለኝ። “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባቤትነት”
የሚለውን ዘመቻ ከምር ቁምነገር የሚያስገኝ ዘመቻ ለማድረግ ከተፈለገ እያንዳንዱ ዘመቻ በደንብ ፕላን መደረግ
አለበት። ፕላን ሲሰላ ብዙ ነገሮች መስተዋል አለባቸው። ፕላን ማድረግ ማለት ከበርካታ ነገሮች በተጨማሪ
የኢትዮጵያ አየር ጸባይ ትንበያ የሚሰጠውን መረጃ በመጠቀም ዘመቻዎች ዝናብ በማይዘንብባቸው ቀናት እንዲሆኑ
ጥረት ማድረግን ሳይቀር ያካትታል። የእያንዳንዱ ዘመቻ ዜና ከፌስ ቡክ ባሻገር ሽፋን ማግኘት አለበት።
በኢትዮጵያ ሰራተኛው፣ ነጋዴው፣ ተማሪው፣ የቢሮክራሲ ሰራተኛው፣ ወ.ዘ.ተ. ዜናው በህትምት ወይንም በአየር
እንዲደርሰው ለማድረግ የተቻለው ጥረት ሁሉ መደረግ አለበት። እያንዳንዱ ዘመቻ የአገር ውስጥ እና የውጭ ነፃ
ፕሬስ እና ድረ-ገጾች፣ የኢቲቪ፣ የቪኦኤ፣ የጀርመን ሬዲዮ፣ የኢሳት ሽፋን እንዲያገኝ አስፈላጊው ጥረት በቅድሚያ
መደረግ አለበት። ዘመቻን ለመግለጽ ለህዝብ የሚቀርቡ ምስሎች፣ ዩ-ቲዩቦች ጥራት ሊኖራቸው ይገባል። በዘመቻ
ላይ ለግልጋሎት የሚውሉ የድምጽ ማጉያዎች ጥራት እንዲኖራቸው በቅድሚያ ጥረት መደረግ አለበት። ዘመቻውን
በፓልቶኮች ማሰራጨት ካስፈለገ የድምጽ እና የምስል ጥራት እንዲኖር በቅድሚያ ማስላት ያስፈልጋል። ይኼ ሁሉ
የፕላነሮች ስራ ነው።

በመጨረሻ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባቤትነት” ዘመቻ ህገ-መንግስቱ ውስጥ የተደነገጉትን የመቃወም መብቶች
በመጠቀም ዴሞክራሲ ግንባታን ለማገዝ የሚደረግ ሰላማዊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ነው። ይኼን ማድረግ ወደ
ዴሞክራሲ እና ስልጣኔ ለመሸጋገር የሚደረገውን ህጋዊ ጥረት የሚያግዝ እንጂ ህውሃት/ኢህአዴግ እንደሚለው
ህገ-መንግስት ለመናድ የሚደረግ ግርግር አይደለም። የህውሃት/ኢህአዴግ ፕሮፖጋንዳ ግብ ህዝብን አሸብሮ ፈርቶ
እንዲገዛ ማድረግ ነው። መብት ለማስከበር እና የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት መፍትሄው ደግሞ አለመፍራት
ነው። ስለዚህ በአገር ውስጥ እና ካገር ውጭ የሚኖሩ ዜጎች እና ባለሙያዎች “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት
ባቤትነት” በሚለው ታሪካዊ ዘመቻ በብዛት በመሳተፍ ማህተማቸውን ማስቀመጥ ያለባቸው ይመስለኛል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on March 10, 2014
  • By:
  • Last Modified: March 10, 2014 @ 10:21 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar