www.maledatimes.com የጎሣ ግጭቶችና የአለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ሚና - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የጎሣ ግጭቶችና የአለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ሚና

By   /   March 19, 2014  /   Comments Off on የጎሣ ግጭቶችና የአለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ሚና

    Print       Email
0 0
Read Time:25 Minute, 26 Second


(ክፍል ሁለት)

ከያሬድ ኃይለማርያም

ብራስልስ፣ ቤልጂየም

መጋቢት 11 ቀን 2006

የተባበሩት መንግሥታት በ1948 ዓ.ም. ባወጣው የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ መግለጫ አንቀጽ 2 ላይ እያንዳንዱ ሰው በዘር፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አስተያየት፣ በኅብረተሰብ ምንጭ፣ በሃብት፣ በትውልድ፣ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ምንም ዓይንነት ልዩነት ሳይደረግበት በመግለጫው ላይ በተጠቀሱት መብቶችና ነፃነቶች በእኩል የመጠቀም መብት እንዳለው የደነግጋል። ይህንን ድንጋጌም መነሻ በማድረግ ዘረኝነትንና ሌሎች ከሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች ጋር የሚቃረኑ የአድልዎ ተግባራትን ለማስቀረት በሚል በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ስምምነቶችና መግለዋዎች በተባበሩት መንግስታት አባል አገራት ጸድቀው ወጥተዋል።

ከእነዚህም መካከል በተባበሩት መንግስታት ጸድቆ የወጣውና ከጃንዋሪ 04 ቀን 1969 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው “ማንኛውንም ዓይነት የዘር አድልዎ ለማስወገድ የተደረገ ዓለም አቀፍ ስምምነት” በሚል የሚታወቀው ሰንድ በመግቢያው ላይ ስምምነቱ ያስፈለፈበትን አላማ ይገልጻል። ይኽውም፤ በዘር ልዩነት ላይ የተመሠረተ የበላይነት ፍልስፍና ሳይንሳዊ እውነትነት የሌለው፣ ከሥነ ምግባር አንጻር የሚወገዝ፣ ከማኅበራዊ ኑሮ አንፃር ፍትሕ የጎደለውና ትክክል ያልሆነና አደገኛ አስተሳሰብ መሆኑን፤ እንዲሁም በንድፈ ሃሳብ ደረጃም ሆን በተግባር የትም ቦታ ለአድሏዊ የዘር ልዩነት መኖር በቂ ምክንያት የሌለ መሆኑን ይገልጻል። አክሎም፤ በሰው ልጆች መካከል በዘራቸው፣ በቀለማቸው፣ ወይም በጎሣቸው ምክንያት የሚደረግ መድሎ በሕዝቦች መካከል ወዳጅነት የተሞላበትን ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር እንቅፋት የሚሆን የሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት፣ በአንድ መንግሥት ሥር አብረው በመልካም ሁኔታ ተስማምተው የሚኖሩትንም ሰዎች ሕይወት የሚያናውጥ መሆኑን ይገልጻል።

በአለም ታሪክ ጎልተው የሚጠቀሱት የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጥራት ወንጀሎች አብዛኛዎቹ መንሰዔዎቻቸው የጎሣ እና ዘርን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች ናቸው። በ1915 አንድ ሚሊዮን አርመናዊያን በቱርኮች የጭካኔ እርምጃ ያለቁበትን ክስተት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የፖሊሽ ጁ ዎች በሂትለር የተጨፈጨፉበትን፣ 2 ሚሊዮን ካምቦዳዊያን ኮሚኒስት በነበረውና Khmer Rouge ተብሎ በሚጠራው የአማፂ ቡድን የተገደሉበትን፣ በመቶ ሺህ የሚጠጉ የኢራቅ ኩርዶች ከ1987-1988 ዓ.ም. በቀድሞው መሪ ሳዳም ሁሴን የተጨፈጨፉበትን፣ ከ8 መቶ ሺ በላይ የሰው ህይወት የጥፋበት የ1994ቱ የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide) እና ከ1992 እስከ 1995 ባለው ጊዜ ውስጥ በዩጎዝላቪያ ሰርቦች በሰነዘሩት ጥቃት ከ2 መቶ ሺ በላይ ቦስኒዎች ያላቁበትን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ልንመለከት እንችላለን። እነዚህ እና ሌሎች ያልጠቀስኳቸውን ነገር ግን በሰው ዘር ላይ ቀላል የማይባል እልቂቶችን ያስከተሉ ክስተቶችን ብንመረምር የአለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ባህሪ፣ ለጎሣ ግጭቶች የተሰጠውን የትኩረት መጠን፣ የአለም አቀፉን ፖለቲካ አቅጣጫና ባህሪይ፤ እንዲሁም በእንዲህ ያሉ ግጭቶች ዙሪያ አውንታዊ እና አሉታዊ ገጽታውን ለመረዳት ያስችሉናል።

በእዚህ ዘርፍ ዙሪያ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ያካሄዱት እና ከላይ በተጠቀሱት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ላይም ጥልቅ ምርምር በማድረግ “A Problem from Hell” America and the Age of Genocide የሚል መጽሐፍ ያሳታሙት፤ በ Harvard’s John F. Kennedy School of Government የሰብአዊ መብቶችና የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መምህርት የነበሩትና (እንዲህ ያለ መጽሐፍ ከጻፉ በኋላ ምን ነክቷቸው እንደሆነ ግራ ቢገባኝም) በቅርቡ በኦባማ አስተዳደር በተባበሩት መንግስታት የዩናይትድ ስቴተ አምባሳደር ተደርገው የተሾሙት Prof. Samantha Power ከእነዚህ እልቂቶች ጀርባ ያለውን የአለም አቀፉን፤ በተለይም የአሜሪካን መንግስትን አወንታዊ ሚና በርካታ መረጃዎችን በማጣቀስ አስቀምጠዋል። 602 ገጾች ባለው በዚህ መጽሐፋቸው ውስጥ ፕሮፌሰሯ ከእያንዳንዱ እልቂት ጀርባ ድርጊቱ ሆን ተብሎ እንዲፈጸም ሁኔታዎችን በማመቻቸት ወይም ሆን ብሎ በመፍቀድ፣ ወይም ድርጊቱ ሊፈጸም እንደሚችል እና የበርካቶችን ህይወት ሊቀጥፍ እንደሚችል አስቀድሞ እየታወቀ ችላ በማለት እና በአንዳንድ ሁኔታዎችም እልቂቱን ለሚፈጽሙት አካላት የፋይናንስና ሌሎች የቁስ ድጋፎችን በማድረግ የአለም አቀፍ ማኅበረሰቡ፤ በተለይም አገራቸው አሜሪካ የተጫወተችውን ሚና አጉልተው አስቀምጠዋል።

ከላይ በዘረዘርኳቸው እና የአለምን ሕዝብ እጅግ ባሳዘኑትና ባስደነበሩት የጭካኔ እርምጃዎች ዙሪያ ፕ/ር ሳማንታ ፓወር በመጽሐፋቸው ውስጥ በሰፊው የሰጡትን ማብራሪያ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ለማግኘት ለምትፈልጉ አንባቢያን እየተውኩ በአፍሪካ ውስጥ ከተከሰተው የሩዋንዳው እልቂት ጋር በተያያዘ ያቀረቡትን ትንታኔ ብቻ ባጭሩ ልጥቀስ። የሩዋንዳውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የመረጥኩት አፍሪካ ውስጥ የተከሰተ እልቂት ስለሆነና ከሁኔታው ለኢትዮጵያም ትምህርት ሊሆን የሚችል ነገር ይኖረዋል ከሚል ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በዚህ እልቂት ዙሪያ የተባበሩት መንግስታት እና ከኃያላኖቹ አገሮች መካከል የአሜሪካን መንግስት አቋምና ባህሪም በቅጡ እንድንረዳ ያስችለናል በሚል ነው።

የ1994 ዓ.ም.ቱ የሩዋንዳው እልቂት ከመከሰቱ ሦስት ወራት በፊት በአገሪቱ ውስጥ ያለው በሁቱ እና በቱትሲ ጎሣዎች መካከል የተከሰተ የጎሣ ቅራኔ ወደ ተባባሰ ደረጃ ላይ መድረሱን የተረዱት በሩዋንዳ የተባበሩት መንግስታተ የሰላም አስከባሪ ኃይል መሪ የሆኑት ካናዳዊው ሜጀር ጀነራል ሮሜዎ ዳላይሬ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ለመንግስታቱ ድርጅት ሰጥተው ነበር። በማስጠንቀቂያቸውም ላይ ሊደርስ የሚችለውን የቀረበ የእልቂት አደጋ በመጠቆም ሁኔታውን ከወዲሁ ለመቆጣጠር እንዲቻል የሰላም አስከባሪው ኃይል የሁቱ ታጣቂ ሚሊሻዎችን ትጥቅ እንዲያስፈታ እና በቱትሲዎች ላይ የተነጣጠረውን የጭፍጨፋ እቅድ እንዲያከሽፍ መመሪያ እንዲሰጠውና ተጨማሪም የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲመደብለት የሚጠይቅ ነበር። ይሁንና የሆነው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነበር። ከተባበሩት መንግስታት የተገኘው ምላሽ ግን የጀነራሉን ጥያቄ ወደጎን በመተው ተጨማሪ ኃይል ከመላክ ይቅር  እዲያውም በጀነራሉ ስር ከነበረው የሩዋንዳ ሰላም አስከባሪ ውስጥ አብዛኛው አገሪቱን ለቆ እንዲወጣ የሚያዝ ነበር። እንዲሁም እልቂቱን በማስተባበር ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የነበረውን የሩዋንዳ ሬዲዮ ጣቢያ አሜሪያ ያላትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ስርጭቱን እንድታግድ ለቀረበውም ማሳሰቢያ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። በዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ የ 8 መቶ ሺ ሰው ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ሊያልፍ ችሏል።

የሩዋንዳውን እልቂት በተመለከተ የአሜሪካ መንግስት የነበረውን አቋም እና የተወሰዱትን እርምጃዎች በተመለከተ ፕ/ር ሳማንታ ፓወር በመጽሐፋቸው ገጽ 338 ላይ ያስቀመጡትን ማብራሪያ እንዳለ ለአንባቢያን ለማስቀመጥ እወዳለሁ። ይህውም፦

… The commission’s March 1993 report found that more than 10, 000 Tutsi had been detained and 2,000 murdered since the RPF’s 1990 invasion. Government-supported killers had carried out at least three major massacres of Tutsi. Extremist, racist rhetoric and militias were proliferating. The international commission and a UN rapporteru who soon followed warned explicitly of a possible genocide.

Low-ranking U.S. intelligence analysts were keenly aware of Rwanda’s history and the possiblilty that atrocity would occur. A January 1993 CIA report warened of the likelihood of large –scale ethnic violence. A December 1993 CIA study found that some 4 million tons of small arms had been transferred from Poland to Rwanda, via Belgium, an extraordinary quantity for a government allegedly committed to a peace process. And in January 1994 a U.S. government intelligence analyst predicated that if conflict restarted in Rwanda, “the worst case scenario would involve one-half million people dying”. … When Woods of the Defense Department’s African affairs bureau suggested that the Pentagon add Rwanda-Burundi to its list of potential trouble spots, his bosses told him, in his words, “Look, if something happens in Rwanda-Burrundi, we don’t care. Take it off the list. US national interest is not involved and we can’t put all these silly humanitarian issues on lists. … Just make it go away.”

ከላይ በተጠቀሰው ጽሑፍ ውስጥ በግልጽ እንደሚታየው የአለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሩዋንዳው እልቂት ከመፈጸሙ በፊት እና እየተፈጸመ በነበረበተም ወቅት (100 ቀናት የፈጀ እልቂት ስለነበር) ድርጊቱ እንዳይከሰት ወይም ለማስቆምም ሆነ አደጋውን ለመቀነስ የሚችልበት አስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንደ ነበር ነው። ይሁንና ይህን ማድረግ ስላልተፈለገ ምንም አይነት እርምጃ ሳይወሰድ ድርጊቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከዳር ቆሞ መመልከትን መርጧል። እንደውም እልቂቱ በዚህ መልኩ እንዲጠናቀቅ ቀድሞውንም የታሰብ እስኪመስል ድረስ የተባበሩት መንግስታት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያውን ወደጎ መተው እና አደጋ መኖሩ እየታወቀ በተቃራኒው ያለውንም ኃይል ከስፍራው ላይ ማውጣቱ፣ ፖላንድ ላይ የተመረተውን 4 ሚሊዮን ቶን የሚመዝን የተለያዩ የእጅ መሣሪያዎች (ቢላ፣ ገጀራ እና መጥረቢያዎች) ለእርስ በእርስ ግጭቱ እንደሚውል እየታወቀ ወደ ሩዋንዳ እንዲገባ መደረጉ፣ የሩዋንዳን ሕዝብ በዘር በመከፋፈል እርስ በርሱ በጠላትነት እንዲቧደን ቁልፉን ሚና የተጫወተችው ቤልጂየም የቀበረቸው የዘር ፈንጂ የሚፈነዳበት ጊዜው መቃረቡን ስታውቅ በሩዋንዳ የነበረውን የራሷን ሰላም አስከባሪ ኃይል አስቀድማ እንዲወጣ ከማድረጓም ባሻገር በፖላንድ የተመረተውን 4 ሚሊዮን የጦር መሣሪያ ተቀብላ ወገናቸውን ለመጨረስ ለተሰናዱት ሁቱዎች እንዲደርስ ማድረጓ፣ እንዲሁም ይህን ሁኔታ እያወቀ የአሜሪካ መንግስት የወሰደውን ኃላፊነት የጎደለው እና የምንቸገረኝ እርምጃ ስንመለከት እንዲህ አይነቶቹ እልቂቶች ምንም እንኳን አገራዊ ይዘት ቢኖራቸውም እና በጎሣዎች መካከል የሚፈጠሩ ቢሆኑም ሁኔታዎቹ እንዲባባሱም ሆነ ወደ ከፋ እልቂት እንዲያመሩ የሚደረገው ርብርቦሽ ግን አለም አቀፋዊ ይዘት ያለው መሆኑን በበቂ ሁኔታ ያሳያል።   

ይህ ሁሉ ሕዝብ በተቀነባበር ሁኔታ በሩዋንዳ ብቻ አይደለም በሌሎቹም የዘር ማጥፋት ወንጅል በተፈጸመባቸ አገሮች ሁሉ እንዲያልቅ ከተደረገ በኋላ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለፍትሕ እና ለሰብአዊ መብቶች መከበር ዘብ የቆመ ለመምሰል የሚያደርገው ሽር ጉድ ከልብ መሆኑን እንድንጠራጠር ያደርጋል። እነዚህ እልቂቶች ከተፈጸሙ በኋላ በአለም አቀፍ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አለም አቀፍ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል፣ በርካታ መጽሐፎችና የጥናት ሥራዎች ተከናውነዋል። ለዚህም በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ ፈሷል። ዛሬም ብዙዎች እነኝህን የሕዝብ እልቂቶች እያነሱ እና እየጣሉ ገቢ ማግኛና መተዳደሪያ አደርገውታል። አለም ካለፉት እልቂቶች አሁንም ያልተማረ መሆኑን ግን በየእለቱ በምንሰማቸው ዜናዎች ላይ እንደምናየው በመካከለኛው ምስራቅ የተለያዩ አገሮች በተለይም በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅና በሶሪያ፤ እንዲሁም በአፍሪካ ውስጥ በላይቤሪያ፣ በሱማሊያ፣ በማሊ፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ በሁለቱም ሱዳኖች፣ በሌሎች በርካታ አገሮች ወንድማማቾችና እህትማማቾች በዘር ጥላቻ እርስ በርስ ሲጨራረሱ እየታዘብን ነው። በዛሬዎቹም እልቂቶች የአለም አቀፉ ማኅበረሰብ በከፋ ሁኔታ ማድረግ የሚገባውን ባለማድረግ እና ማድረግ የማይገባውን በማድረግ አሉታዊ አስተዋጾውን እያበረከተ ነው። ለዚህም ለሁለት የተከፈለችው ሱዳን፣ የተበታተነችው ሱማሊያ፣ የተንኮታኮተችው ኢራቅ፣ ሥርአት አልበኝነት የነገሰባትን ሊቢያና በጦርነት እየታመሰች ያለችውን ሶሪያን ጨምሮ ሌሎች አገሮች የሚገኙበትን ሁኔታ ማየት ይቻላል።

እነዚህ አገሮች ዛሬ ለሚገኙበት ሁኔታ በውስጣቸው ካለው የመልካም አስተዳደር፣ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መጥፋት እና የሰብአዊ መብቶች መጓደል ባሻገር አይን ያወጣው የምዕራቡ አለም ቅጥ ያጣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥቅም ፍለጋ እንደ ዋና ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል። አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞችም ይህን ሁኔታ የዳግም ቅኝ ግዛት ፓሊሲ ውጤት እንደሆነ ይገልጻሉ። እነኚህ የቅርብ ጊዜ ክስተቶች እንደሚያሳዩን ከሆነ ለአንድ ኃያል አገር የነዳጅ ዘይትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ጂ-ኦ ፖለቲካዊ ጥቅሞች ሲባል አንድ ሌላ ድሃ ሃገር ከነ ሕዝቡ ሊወድም፣ ሊጠፋና እና ሊፈረካክስ እንደሚችል ነው። እጅግ የሚያስፈራው ደግሞ ከእንደነዚህ ኃይሎች የሚያስጥልና መከታ ሊሆን የሚችል ወይም ከተበደሉም በኋላ ፍትህ የሚገኝበት እና ኃያሎቹ አጥፊዎች የሚጠየቁበት አለም አቀፍና ገለልተኛ የሆነ የፍትህ መድረክ መታጣቱ ነው።

እጅግ ሰፊ እና ውስብስብ የሆነውን የአለም አቀፍ ፖለቲካ ባህሪይን ከጎሣ ግጭት ጋር በማያያዝ በትንሹም ቢሆን ከሩዋንዳው እልቂት በመነሳት ለማሳየት የፈለኩት አንድ አገር ወደ እንደዚህ አይነቱ የእልቂት ደረጃ አያምራ እንጂ መንገዱን ከተያያዘው በኋላ ግን ቀጣዩ ጉዞ ጭልጥ ያለ ድጥና ቁልቁለት መሆኑን ዛሬ በጎሣ ፖለቲካና በጎሣ ግጭት ላይ በሚቧልቱ የኢትዮጵያን ፖለቲከኞች ለማሳሰብ ነው።

በቸር እንሰንብት!

http://humanrightsinethiopia.wordpress.com/

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on March 19, 2014
  • By:
  • Last Modified: March 19, 2014 @ 9:21 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar