www.maledatimes.com 20 ዓመት ሙሉ ውህደትና ጥምረት ያልሰመረለት የተቃዋሚ ጎራ (ኤልሳቤጥ እቁባይ እና አለማየሁ አንበሴ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

20 ዓመት ሙሉ ውህደትና ጥምረት ያልሰመረለት የተቃዋሚ ጎራ (ኤልሳቤጥ እቁባይ እና አለማየሁ አንበሴ)

By   /   March 22, 2014  /   Comments Off on 20 ዓመት ሙሉ ውህደትና ጥምረት ያልሰመረለት የተቃዋሚ ጎራ (ኤልሳቤጥ እቁባይ እና አለማየሁ አንበሴ)

    Print       Email
0 0
Read Time:34 Minute, 49 Second

20 ዓመት ሙሉ ውህደትና ጥምረት ያልሰመረለት የተቃዋሚ ጎራየሐሙሱ የመኢአድና አንድነት ውህደት ሳይጀመረ ፈረሰ
ምርጫን ብቻ ግብ ያደረጉ ጥምረቶች ዋጋ አይኖራቸውም
የፓርቲዎች ውህደት ባይሳካም የተገኘው ልምድ ቀላል አይደለም
ለተቃዋሚዎች አለመጠናከር ኢህአዴግ ተጠያቂ ነው
“በሀገራችን የፓርቲ ፖለቲካ ብዙ ዘመን አስቆጥሯል ማለት
ባይቻልም በአሁኑ ጊዜ ፓርቲዎች ማደግ ሲገባቸው እየቀጨጩ ነው፣ በሜዳው ላይ መኖር የማይገባቸው ፓርቲዎችም አሉ፡፡ ፕሮግራማቸው አንድ ሆኖ እንኳ ተከፍለው መንቀሳቀሳቸው ትክክለኛ አካሄድ ካለመሆኑ በተጨማሪ ለገዥው ፓርቲም የስልጣን እድሜን እየሰጠ ነው ያሉት ከዚህ ቀደም በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራረርነት ቆይተው አሁን ላይ ከፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸው ያገለሉት ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም ናቸው፡፡

አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) እና የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ውህደት ይፈፅማሉ ተብሎ ሲጠበቅ መኢአድ ለአንድነት በፃፈው ደብዳቤ፣ ውህደቱ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን አስታውቋል፡፡ በመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኃሪ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፣ የፕሮግራምና የደንብ ጉዳይ፣ የስያሜ፣ የኃላፊነት፣ አንድነት ከመድረክ ጋር ስላለው ግንኙነት እንዲሁም የንብረት ጉዳዮችን በተመለከተ ተጨማሪ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል፡፡
ረቡዕ እለት ደብዳቤው እንደደረሳቸው የገለፁት የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ ስዩም መንገሻ፤ እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም የሁለቱም ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በመኢአድ ፅ/ቤት ተገናኝተው ባካሄዱት የጋራ ውይይት ላይ ድርድሩ ማለቁን በማመልከት፣ ውህደቱ ከመጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም እንዳያልፍ አሳስበው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
“አባላቱ በጥቃቅን ምክንያት ውህደቱን እንዳታሰናክሉ የሚል ማሳሰቢያ ሠጥተውን ነበር” ያሉት አቶ ስዩም፤በዚህ መሰረት አንድነት አስፈላጊ ዝግጅቶችን አጠናቆና  የሆቴል አዳራሽ ተከራይቶ ካጠናቀቀ በኋላ ደብዳቤው እንደደረሰው ተናግረዋል፡፡ “አሁን ኳሱ በመኢአድ እጅ ነው ያለው” ያሉት አቶ ስዩም፤ በአንድነት በኩል እንደ ምክንያት የተጠቀሱት ጉዳዮች በድርድሩ እልባት አግኝተዋል የሚል እምነት አለ ብለዋል፡፡
የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኃሪ በበኩላቸው፤ ሰሞኑን በወጣ አንድ ጋዜጣ ላይ በአንድነት በኩል “ከመድረክ ጋር እንቀጥላለን” የሚል መግለጫ በመሰጠቱ ውህደቱን ልናዘገየው ተገድደናል ብለዋል።    “ድርድሩ ቆሟል ማለት አይደለም፤ይቀጥላል ነገር ግን መኢአድ በደብዳቤው የጠየቃቸው ካልተሟሉ ውህደቱ ላይፈፀም ይችላል” ብለዋል-ፕሬዚዳንቱ፡፡
ውህደት፣ቅንጅት፣ጥምረት…
ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ከተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የመላ አማራ ህዝብ ድርጅት (መአኅድ) ሲሆን ነሐሴ 5 ቀን 1994 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ ወደ አገር አቀፍ ፓርቲነት በመለወጥ መኢአድ በሚል ስያሜ እንደሚንቀሳቀስ ይፋ አደረገ፡፡ ይሄኔ በአባላቱ መካከል ክፍፍል ተፈጠረ፡፡ መኢአድ ሆኖ ከተዋቀረ በኋላ በልዩነት ከፓርቲው የወጡ ሰዎችም ኢዴአፓን አቋቋሙ፡፡  ኢዴአፓ፤ከኢዲዩ፣ ከኢዳግ እና ከመድህን ጋር ውህደት ፈፅሟል፡፡ መስከረም 20 ቀን 1997 ዓ.ም ኢዴአፓ (ከመኢአድ የወጣ) እና መድህን መዋሀዳቸውንና  በግንቦት ወር የሚከናወነው ምርጫ፤ ነፃና ሚዛናዊ እንዲሆን  በመንግስት በኩል መሟላት ያለባቸው ጥያቄዎች ቢኖሩም በምርጫው እንደሚሳተፉ ገለፁ፡፡
ውህደታቸውን ተከትሎም ዶክተር አድማሱ ገበየሁ ፕሬዚደንት፣ ዶክተር ኃይሉ አርአያና ዶክተር ጎሹ ወልዴ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም አቶ ልደቱ አያሌው ዋና ፀሀፊ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ በዛው ሰሞን ኢዴአፓ፣መድህንና መኢአድ ለመዋሃድ ያደረጉት ሙከራ ጫፍ ላይ ከደረሰ በኋላ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ጥቅምት 1997 ዓ.ም ኢዴአፓ መድህን፣ መኢአድ ኢድሊ እና ቀስተ ደመና ቅንጅትን መስርተው ኢህአዴግን በግንቦቱ ምርጫ በብርቱ ለመፎካከር መዘጋጀታቸውን አስታወቁ፡፡ ህዳር 9 ቀን 1997 ዓ.ም አራቱ ፓርቲዎች በምርጫው ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ በሚል ስያሜ ለመወዳደር መወሰናቸውን በፊርማቸው አረጋገጡ፡፡ በምርጫው ቢሸነፉ እንኳን ተዋህደው አንድ ፓርቲ የመሆን የረጅም ጊዜ እቅድ እንዳላቸውም አስታወቁ፡፡ ቅንጅቱ አልፎ አልፎ ከሚሰሙ ልዩነቶች ውጪ ብዙዎችን ከጎኑ በማሰለፍ እና  ደጋፊዎችን በማሰባሰብ፣ ኢህአዴግን የሚገዳደር ጠንካራ ፓርቲ ሆነ፡፡ ምርጫው ግንቦት ተካሂዶ ሰኔ ላይ የልዩነት ወሬዎች በስፋት መውጣት ጀመሩ፡፡ በዚያው ወር መኢአድ በውስጣዊ ችግር መተብተቡ የተነገረ ሲሆን ድርጅቱን ከመፍረስ ለመታደግ ኮሚቴ አቋቁሞ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ የቅንጅቱ ክፍፍል እየተብላላ ቆይቶ ጥቅምት ላይ ከኢዴአፓ መድህን አቶ ልደቱ አያሌውንና አቶ ሙሼ ሰሙን አገደ፡፡
የቅንጅት አመራሮች ከታሰሩ በኋላ የተወሰኑ  ፓርላማውን የተቀላቀሉ የቅንጅቱ ተመራጮች  ኢዴፓ፣ የፓርላማ ቡድን፣ መኢአድ  እና ቅንጅት በሚል ተከፋፍለው መቀመጫቸውን ያዙ፡፡ ምርጫ 2002 ዓ.ም ሲቃረብም ምርጫን ዓላማ ያደረጉ የትብብር ስምምነቶች፣ ግንባር እና መድረክ መፍጠር እንዲሁም መቀናጀት ይፋ ተደረጉ፡፡ ህዳር 25 ቀን 2002 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት በግንባር ደረጃ ተቀናጅተው እንደሚንቀሳቀሱ ገለፁ፡፡ የካቲት 21 ቀን 2002 ዓ.ም በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ አምስት የኦሮሞ ድርጅቶች- የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ አንድነት ነፃነት ግንባር፣ የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ፣ የኦሮሚያ ነፃነት ብሄራዊ ፓርቲ እና የመላው ኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ለቀጣዩ ምርጫ በቅንጅት ለመንቀሳቀስ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ፡፡
አንድነት ከተቋቋመ በኋላም በታህሳስ 2001 ዓ.ም “መርህ ይከበር” የሚል መሪ ቃል ያነገቡ ወገኖች ከፓርቲው ወጥተው ሰማያዊ ፓርቲን አቋቋሙ፡፡ በሰኔ 2000 ዓ.ም መድረክን ለማቋቋም መምከር ተጀመረ፡፡ የካቲት 2001 ዓ.ም ደግሞ የስድስት ፓርቲዎች ጥምረት ተመሰረተ፡፡ መስከረም 24 ቀን 2003 ወደ ግንባር ተሸጋገረ፡፡ በያዝነው ዓመት አንድነት ከመድረክ የታገደ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ  ከመኢአድ ጋር ውህደት ለመፈፀም በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
“ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ፓርቲዎች የተጓዙበት መንገድ ሲገመገም፣ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ተጨባጭ ውጤት አላመጣም፡፡ ንቅናቄያቸውም በየጊዜው እየቀጨጨ የሚሄድ ሲሆን  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ አብሮ ለመስራት ያላቸው ተነሣሽነትና ፍላጐት የተዳከመ ብሎም ተስፋ የሚያስቆርጥ ደረጃ ላይ የደረሰ ነው” ይላሉ – የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኃሪ፡፡
ባለፉት 23 አመታት በሀገሪቱ ያሉ ዋና ዋና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲቀናጁ፣ ሲጣመሩ፣ ሲዋሃዱ  ሲፈርሱ ነው የኖሩት፡፡ አቶ አበባው እንደሚሉት፤ለዚህ ምክንያቱ ከሃገራዊነት ስሜት ይልቅ የግለሰቦች ስሜትና ፍላጐት አይሎ መውጣቱ ነው፡፡ “የተሞከሩት ቅንጅቶች እና ጥምረቶች በሙሉ ሴራ ያልተለያቸው፤ የግለሰቦችን ፍላጐት ብቻ ጠብቀው የተፈጠሩ በመሆኑ በትንሽ ተንኮል ይፈርሳሉ፡፡ ዛሬ  ይህ ተንኮል ይበልጥ መልኩን ቀይሮ ተባብሮ ለመስራት ሳይሆን አንዱ ሌላውን ፓርቲ ለመውረስ ነው የሚጥረው” ብለዋል – አቶ አበባው። በ1997 á‹“.ም በተደረገው ምርጫ ከፍተኛ የፖለቲካ መነቃቃት የፈጠረው ቅንጅት፤ የፈረሰበት ምክንያትም በዚህ መሰሉ ሴራ ነው ይላሉ – ቅንጅቱ ፓርቲዎች ሠምና ወርቅ ሣይሆን ውሃና ዘይት ሆነው የተቀናጁበት መሆኑን በመጠቆም፡፡
በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት መኢአድ የስበት ማዕከል ሆኖ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ አበባው፤ፓርቲው ከሌሎች ጋር ለመጣመርና ለመዋሃድ ያደረጋቸው ሙከራዎች ያልሰመሩት ፓርቲዎች ወደ መኢአድ ሲመጡ በቅንነት ሳይሆን ህልውናውን በሚፈታተን መልኩ ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ሠላማዊ ትግሉ በእነዚህ ምክንያቶች ውጤት አልባ ሆኖ ቆይቷል የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለውጤት አልባነቱ ኢህአዴግም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ ይወቅሣሉ፡፡ “የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆነ ገበሬ፣ መሬት እና የግብርና ግብአቶች እንዳያገኝ፣ የመንግስት ሠራተኛ ከሆነ ከስራው እንዲፈናቀል፣ እርዳታ ፈላጊ እርዳታ እንዳያገኝ እየተደረገ፣ ሰዎች በነፃነት መብታቸውን እንዳያስከብሩና በፈለጉት የፖለቲካ ፓርቲ ጥላ ስር እንዳይሰባሰቡ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና ፈጥሯል” ሲሉ ይኮንናሉ፡፡ ኢህአዴግ  ባለፉት 23 አመታት በትጋት ተቃዋሚዎችን ለማቀጨጭና ከተቻለውም ለማጥፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሲሠራ፤ ህብረቶችንና ቅንጅቶችን በሴራ ሲያፈርስ ነው የኖረው ሲሉም አምርረው ይወቅሳሉ፡፡
“ለዲሞክራሲ ምቹ የሆንን ሰዎች አይደለንም” የሚሉት አቶ አበባው፤ ከጥቂት አመታት በፊት በጦርነት ሲታመሱ የነበሩ እንደ ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን የመሳሰሉ ሃገሮች እንኳ ከኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ ዲሞክራሲን እየተገበሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ ተቃዋሚ ሆኖ ለዲሞክራሲ የሚደረግ ትግል ውስጥ ውጤት ለማምጣት ብዙ ሂደቶችን ማለፍ እንደሚጠበቅ ገልፀው፤ በዚህ ረገድ የሚፈለገውን ያህል ተስፋ የሚሠጥ ባይሆንም ህዝቡን በማነቃቃት ረገድ ተቃዋሚዎች የነበራቸው ሚና የሚዘነጋ አለመሆኑን አቶ አበባው አመልክተዋል፡፡
ቀደም ሲል የመኢአድ አባል በመሆን በፓርቲው ውስጥ ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ በተፈጠሩ አለመግባባቶች አዲስ ፓርቲ ወደማቋቋም ከተሸጋገሩት አቶ ልደቱ አያሌውና ሌሎች ግለሰቦች ጋር በመሆን የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን (ኢዴፓ) የመሠረቱት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ ባለፉት 23 አመታት በመቀናጀት፣ ግንባርና ጥምረት በመፍጠር ረገድ ውጤት ያመጣና አላማውን ያሳካ ፓርቲ አላየሁም ሲሉ የአቶ አበባውን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ በትንሹ ሊጠቀስ የሚችለው 1997 ላይ የተፈጠረው ቅንጅት ብቻ ነው የሚሉት አቶ ሙሼ፤ እሱም ቢሆን ጠንካራ ስላልነበረ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ መሆን እንዳልቻለ ይገልፃሉ፡፡ በዋናነትም የፓርቲዎች ጋብቻ ውጤታማ የማይሆነው ጥምረታቸው ከፕሮግራም፣ ከአላማ እና ከግብ አንድነት በሚመነጭ ሳይሆን ኢህአዴግን ተሰባስቦ ለማሸነፍ ካለ ፍላጐት ወቅታዊ ጉዳይን ብቻ መነሻ አድርጐ የሚፈጠር በመሆኑ ነው የሚሉት አቶ ሙሼ፤ ምርጫ ሲደርስ ብቻ ፓርቲዎች ለመቀናጀትና ለመጣመር መሯሯጣቸውም ይህን ያመለከታል፣ ምርጫን ብቻ ግብ ያደረጉ ጥምረቶች  ደግሞ ከምርጫው በኋላ ዋጋ አይኖራቸውም ብለዋል፡፡
“የውህደት ጥምረት እና ቅንጅት ምስረታ ውጥኖች ከሚከሽፉባቸው ምክንያቶች መካከልም ፓርቲዎች አንድነቱን ከመፈለግ ባሻገር ማን አመራር ይሁን በሚለውና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በቂ የስነ ልቦና ዝግጅት አለማድረጋቸው እና አርቆ አለማሰባቸው ዋናው ነው” ይላሉ አቶ ሙሼ፡፡
ፓርቲያቸው ኢዴፓ ከተመሰረተ ጀምሮ ከሶስት ፓርቲዎች ጋር ስኬታማ ውህደት መፍጠሩን አቶ ሙሼ ይጠቅሳሉ፡፡ ከኢዳግ፣ ኢዲዩ እና ከመድህን ጋር ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ውጤታማ ውህደት መፈጠሩን ያስታወሱት አቶ ሙሼ፤ ከመኢአድ ጋርም በ1996 መጨረሻ አካባቢ ለመዋኃድ የተደረገው የድርድር ሂደት 90 በመቶ ከደረሰ በኋላ መክሸፉን ከፓርቲያቸው ያልተሳኩ ተሞክሮዎች አንዱ ነበር ይላሉ፡፡ በወቅቱ መኢአድ እና ኢዴፓ በበርካታ ጉዳዮች ላይ የተስማሙ ቢሆንም በስራ አስፈፃሚ ውስጥ ትልቁ ድርሻ የማን ነው? የሚለውን መሰረታዊ ጉዳይ ጨምሮ ምን አይነት የመንግስት አወቃቀር ሊኖር ይገባል፣በመሬትና በቋንቋ ጉዳይ ላይ እንዲሁም በፓርቲው ስያሜ ልዩነት ተፈጥሮ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ መኢአድ በወቅቱ የመንግስት ስርአቱ ፕሬዚዳንታዊ ይሁን ሲል ኢዴፓ የለም ፓርላሜንታዊ ይሁን በማለቱ የተፈጠሩ የፕሮግራም ልዩነቶችን መነሻ አድርጎ እስከ መዘላለፍና መወነጃጀል የደረሱ አለመግባባቶች መፈጠራቸውንም አቶ ሙሼ ያስታውሳሉ፡፡ ፓርቲያቸው ከቅንጅት ጋር የፈጠረው ጥምረትም በአላማ እና በአካሄድ ልዩነት መክሸፉን አመልክተው፣ ፓርቲው ካደረጋቸው ውጤታማ ውህደቶች መካከልም ከኢዲዩ ጋር የነበረውን ይጠቅሳሉ። በአንዳንድ ግለሰቦች ምክንያት እክል አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም  መፍትሄ አግኝቶ አብሮ መጓዝ እንደተቻለ ያስታውሳሉ፡፡
የእስከ ዛሬው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉዞ ጠቅለል ብሎ ሲገመገም፣ ህዝብን ተስፋ ያስቆረጠ ነበር ያሉት አቶ ሙሼ፤ ከዚህ በኋላም ቢሆን አንድ ላይ ለመስራት ከፍላጎት ባሻገር የስነልቦና ዝግጅት ሳይደረግ የሚፈጠሩ ውህደቶች እና ጥምረቶች ከሚፈለገው ውጤት ላይ መድረስ አይችሉም ይላሉ፡፡ “የተጠናቀረ ፓርቲ መፍጠር ቀላል አይደለም” የሚሉት አቶ ሙሼ፤ 23 ዓመት ኢህአዴግን የሚገዳደር ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር የሚያስችል በቂ ጊዜ ነበር ለማለት አያስደፍርም ብለዋል፡፡ “ማህበረሰቡ ምርጫ ያስፈልጋል ብሎ እንዲያስብ፣ ገዥው ፓርቲ ልጓም አልባ እንዳይሆን በማድረግ በኩል ተቃዋሚዎች የማይናቅ ድርሻ ነበራቸው” ይላሉ አቶ ሙሼ፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በሃገሪቱ ለተስተዋለው ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ በስልጣን ላይ ካለው ኢህአዴግ በበለጠ ተቃዋሚዎች ተጠያቂዎች ናቸው የሚሉት ደግሞ የአንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ናቸው፡፡ ህብረት፣ ቅንጅት፣ አማራጭ ኃይሎች፣ መድረክ እየተባለ እስከዛሬ ቢዘለቅም ያስገኘው ውጤት ሲገመገም በዜሮ የሚጣፋ ነው የሚሉት ሊቀመንበሩ፤የፓርቲ አመራሮች ከአመት አመት ከስህተታችን ሳንማር የኢትዮጵያን ህዝብ በድለነዋል፤ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጉጉቱንም አጨልመንበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለኢህአዴግ ጠንካራ መሆን የተቃዋሚዎች ድክመት አስተዋፅኦ ማበርከቱን በአፅንኦት የሚገልፁት ኢ/ሩ፤ ውጤት አልባው ሂደት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቁ አሳዛኝ ታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“በሀገራችን የፓርቲ ፖለቲካ ብዙ ዘመን አስቆጥሯል ማለት ባይቻልም በአሁኑ ጊዜ ፓርቲዎች ማደግ ሲገባቸው እየቀጨጩ ነው፣ በሜዳው ላይ መኖር የማይገባቸው ፓርቲዎችም አሉ፡፡ ፕሮግራማቸው አንድ ሆኖ እንኳ ተከፍለው መንቀሳቀሳቸው ትክክለኛ አካሄድ ካለመሆኑ በተጨማሪ ለገዥው ፓርቲም የስልጣን እድሜን እየሰጠ ነው ያሉት ከዚህ ቀደም በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራረርነት ቆይተው አሁን ላይ ከፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸው ያገለሉት ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም ናቸው፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪው ከሆነ የፓርቲዎች ስኬትና ውድቀት የሚያጋጥም ከመሆኑም በላይ በሀገራችን ጠንካራና አስተማማኝ ተቀናቃኝ ፓርቲ ለመፍጠር ጊዜው አልረፈደም፡፡ ከዚህ በፊት የተደረጉ የጥምረት፣ ህብረት፣ ቅንጅት— ሙከራዎች ፍፃሜ አልሠምር ካለባቸው ምክንያቶች አንዱ የፓርቲ ስልጣን ጥመኝት ነው ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤“ጥመኝነቱ ምናልባትም ብሔራዊ ፀባያችን ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል፡፡ እንደተቀሩት አስተያየት ሠጪዎችም ባለፉት 23 አመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላለመጠናከራቸው ኢህአዴግን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ጠንካራ ከነበረው ቅንጅት መፍረስ ጀምሮ አሁን ድረስ የሚደረጉ ተመሳሳይ ሙከራዎች ስኬት አልባ ለመሆናቸውም የገዥው ፓርቲ ረጅም እጅ አለበት ሲሉ ዶ/ር ያዕቆብ ይወቅሳሉ የፓርቲ አመራሮችን በቅንጅት ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ለእስራት መዳረጉን በዋቢነት በመጥቀስ፡፡
ከኦነግ ታጋይነት እስከ ኢህአዴግ ከዚያም የአገሪቱ ፕሬዚዳንትነት በመጨረሻም የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፤የፓርቲዎቹ የውህደት እና ጥምረት ስኬታማ ባይሆኑም የተገኘው ልምድ የማይናቅ ነው ይላሉ፡፡ ለፓርቲዎች ጥምረት ውጤት አልባነት ዶ/ር ነጋሶ በምክንያትነት ከጠቀሷቸው መካከል በፓርቲዎች መካከል የሚፈጠሩ አላስፈላጊ ፉክክሮች፣ የስልጣን ጥመኝነት፣ የአላማ እና የአደረጃጀት ግልጽ አለመሆን፣ ህዝቡ ከዳር ሆኖ ከመተቸት ባለፈ በየአደረጃጀቱ ገብቶ ተጽዕኖ ለመፍጠር አለመቻሉ እንዲሁም በፓርቲዎች ላይ ተጽእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ህዝባዊ አደረጃጀቶች አለመኖራቸው ይገኙበታል፡፡
የእስከዛሬ የፓርቲዎች የቅንጅት፣ ጥምረት እና ውህደት ውጤት አልባ ናቸው የሚለውን ሃሳብ የሚጋሩት ዶ/ር ነጋሶ፤በግንባር ደረጃ ከተሄደ ግን እስከ ዛሬ ሁለት የግንባር አደረጃጀቶች መኖራቸውን ያስቀምጣሉ። አንደኛው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ሲሆን ሌላኛው “መድረክ” ነው፡፡ የመድረክን ውጤታማነት በተመለከተ በሂደት የምናየው ይሆናል ብለዋል ፤ዶ/ር ነጋሶ፡፡
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳንና የቀድሞውን የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ስየ አብርሀን  በማካተት የቅንጅት አመራሮች ከእስር ከተፈቱ በኋላ የተወሰኑት አመራሮች አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ የሚል ፓርቲ አቋቋሙ። ምርጫ 2002 መቃረቡን ተከትሎ አንድነት ፣ ኦፌዴን ፣ ኦብኮ፣ አረና ተሰባስበው መድረክን አቋቋሙ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on March 22, 2014
  • By:
  • Last Modified: March 22, 2014 @ 9:27 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar