www.maledatimes.com የእሳት ፖለቲካ በኢትዮጵያ (Fire Politics in Ethiopia) ይሄይስ አእምሮ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የእሳት ፖለቲካ በኢትዮጵያ (Fire Politics in Ethiopia) ይሄይስ አእምሮ

By   /   March 25, 2014  /   Comments Off on የእሳት ፖለቲካ በኢትዮጵያ (Fire Politics in Ethiopia) ይሄይስ አእምሮ

    Print       Email
0 0
Read Time:32 Minute, 17 Second

                    በሃይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች ዙሪያ ሰሞኑን አንዲት መጣጥፍ ጽፌ ለድረ ገፆች ልኬ ነበር፡፡ ለኅሊናቸው ተገዢ የሆኑ አወጡት – አስነበቡን፤ እግዚአብሔር ይስጣቸው፡፡ ለባህልና ለይሉኝታ ያደሩት እንዲሁም እነሱ በሚፈልጉት ሙዚቃ ብቻ ታንጎና ማሪንጌ መደነስ የሚፈልጉት ወደቅርጫታቸው ከተቱት – ይክተቱት፡፡ ሁሉም የመሰለውን የማድረግ መብት አለውና ያነበበም ያስነበበም፣ ያፈነም ያሳፈነም የኅሊናው ዳኝነት ይፍረደው ከማለት ውጪ በዚህ በውዥንብር ዘመን መወቃቀሱም ሆነ መካሰሱ ፋይዳ የለውም፡፡ ግን ግን የእውነት አምላክ ለሁላችንም እውነተኛውን የልቦናና የኅሊና ሚዛን እንዲሰጠን እጸልያለሁ፡፡ ሁለትና ሁለት ሲደመር አራት ብቻ የሚሆንበት ሃቀኛ ዘመን እንዲመጣልንም እንዲሁ፡፡ በተረፈ የልጆቼ ልጆች “Mother stomach is ranger.” ሲሉ እሰማለሁና በዚያ “ሜጀር” የተቃኘ የቅሬታ ዘፈኔን ጋብዣቸው በገዢዎቻችን አነጋገር ንቅድሚት እላለሁ፤ ሕይወት እንዲህ ናትና፡፡

አንድ የብዕር ወዳጄ ያቺን መጣጥፍ ካነበበ በኋላ በነካ እጄ በዚህች ወያኔያዊ የእሳት ፖለቲካ ላይ ጥቂት ነገር እንድል አሳሰበኝ፡፡ ርዕሲቱንም የሰጠኝ እርሱ ራሱ ነው – Please take the credit dear Mr. Thingummy, wherever you may be.

ሀገራችን ተመልካች ያጣ የሕዝብ ብዛት ብቻ ሣይሆን ጭንቅት የሚያዞሩ እጅግ በርካታ ችግሮች የሚርመሰመሱባት በመሆኗ አንባቢን ላለማስቸገር ወይም ብዙ አንባቢ የለም በሚል ተስፋ መቁረጥ ወይም “አድማጭና የእርምት እርምጃ ወሳጅ ኃላፊነት የሚሰማው ጤናማ ወገን በሌለበት የኳስ አበደች ሀገራዊ ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ ተነቦስ ምን ፋይዳ ሊያመጣ?” ከሚል ብሶት የተነሣ ሆን ብለን እየተውነው እንጂ መጻፍ የምንፈልግ ዜጎች የምንጽፈበት ጉዳይ በሽበሽ ነው፤ በበኩሌ አድማጭ ቢኖር ሃያ አራት ሰዓት ብጽፍ የማይደክመኝና የሚያጽፍ ጉዳይም ሞልቶ የተረፈ መሆኑን የምገልጸው የሚያፍኑኝን ድረ ገፆች ደስ አይበላቸው በሚል የመከፋት ስሜት ሳይሆን ተናግረን አድማጭ ባለመኖሩ ሳቢያ በእጅጉ የምቆረቆር መሆኔን በሚጠቁም የቁጭት ስሜት ነው፡፡ የወያኔው የዘረኝነት አባዜ ካስከተለብን ተነግሮ የማያልቅ ሰቆቃና የግፍ አስተዳደር ጀምሮ እነሚሚ ስብሃቱን የመሳሰሉ የሥርዓቱ ዘውጋዊ አባላትና እበላ ባይ ሆዳም ደጋፊዎቻቸው ባቋቋሟቸው የሠራተኛ አስቀጣሪ ድርጅቶች አማካይነት የሚካሄደውን ዘመናዊ ባርነት ብንመለከት ጉዳችን በጽሑፍም ሆነ በቃል ተዘርዝሮ የማያልቅ አስገራሚ ፍጡራን ሆነናል – እኛ “ኢትዮጵያውያን”፡፡ ቴዲ አፍሮ “እዚህ ጋ’ም እሳት፣ እዚያ ጋ’ም እሳት፣ እሳት፣ እሳት፣እሳት…” ሲል እንዳቀነቀነው ሀገራችን ወያኔያዊ እቶን ላይ ተጥዳ በየአቅጣጫው እንደባቄላ አሹቅ እየተንገረገበች ናት፡፡ ፖለቲካው እሳት፣ ሃይማኖቱ እሳት፣ ፌዴራሉ እሳት፣ ፖሊሱ እሳት፣ ቀኑና ሣምንቱ እሳት፣ ወሩና ዓመቱ እሳት፣ ኑሮው እሳት፣ ባለሥልጣናቱ እሳት፣ ነጋዴው እሳት፣ ዳኛው እሳት፣ በሽታው እሳት፣ ርሀቡ እሳት፣…፡፡ ሁሉም በእሳት አለንጋ ይጋረፋል፤ ይጠብሳል፤ ይሸነቁጣል፤ የት እንድረስ? የትስ እንግባ? ከነዚህ ከሲዖል ካመለጡ ሽፍቶች የሚታደገን ማን ነው? አምላከ ኢትዮጵያ ወዴት አለ? ኤሎሄ! ኤሎሄ! ኤሎሁም!  በዚህ መከራችን ላይ ነው እንግዲህ ወያኔ በሐረርም በአዲስ አበባም እንደዚያች ተዘውትራ እንደሚነገርላትና “እዚህ አካባቢ እሳት ይነሳል ብያለሁ” ብላ ባስጠነቀቀች ማግስት ራሷ እንደምትለኩሰው የደሴዋ ዕብድ ሴት በሹምባሾቹ አማካይነት በሚፈልጋቸው ቦታዎች ላይ እሳት እየለኮሰ፣ እንዳይጠፋም ከልካይ ዘብ እያቆመ በሀገር ሀብትና በሕዝብ ዕንባ እየተዝናና የሚገኘው፡፡ ለማንኛውም አስታዋሼን ላመስግንና በጠቆመኝ ሃሳብ ዙሪያ እንዳመጣብኝ ትንሽ ልብከንከን፡፡  እውነትን ላለማየት ዐይነ ኅሊናቸው የታወረ፣  እውነትን ላለመስማት ዕዝነ ልቦናቸው የተደፈነ፣ አእምሯቸው በፀረ-ለውጥ ቫይረስ ለፈውስ ባስቸገረ ሁኔታ  “corrupted” ለሆነ የ“ሚዲያ ሰዎች”ም የቮልቴርን አባባል ባስታውሳቸው ቅር አይለኝም – ቮልቴር እንዲህ አለ አሉ፡- “በምትናገረው ሁሉ ባልስማማም መናገር የምትፈልገውን ጉዳይ በነፃነት መናገር እንድትችል ግን ሕይወቴንም ቢሆን እገብርልሃለሁ!” አይ ኢትዮጵያ! በሁሉም ድሃ፡፡ ግን ተስፋ አለኝ – ትልቅ ተስፋ፡- ወደፊት አንድ ቀን ይህ ሁሉ ድንቁርናችንና ከንቱ ትምክህታችን እንደጤዛ ሲረግፍልን ሰው እንደምንሆን፡፡

በዓለማችን የፖለቲካ ዓይነቶች ብዙ መሆናቸው ከናንተ የተሠወረ አይደለም፡፡ የድንበር ፖለቲካ፣ የውኃ ፖለቲካ፣ የዘር ፖለቲካ፣ የዘውግ ፖለቲካ፣ የውጭ ብድርና ዕርዳታ ፖለቲካ፣ የሀገር ውስጥ የድርቅ ጊዜና የርሀብ ወቅት ዕርዳታ ፖለቲካ፣ የሃይማኖት ፖለቲካ፣ … ዝርዝሩ ብዙና ኪስን ሳይሆን አንጎልን የሚቀድ ነው፡፡ ወያኔ በኢትዮጵያ ላይ ያልሞከረው የፖለቲካ ዓይነት ደግሞ የለም፡፡ እርግጥ ነው ወያኔ ብቻውን አይደለም፡፡ ይህ ቀረሽ የማይባል ሁለንተናዊ ድጋፍ ለወያኔዎች በገፍ እየሰጡ በ17 ዓመታት ውስጥ የሰው ኃይሉን ከሰባት ሰውነት ወደሚሊዮንነት በማሳደግ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋማቸውን በተግባር የገለጡት የውጭ ጠላቶቻችንም በዚህ ኢትዮጵያን ወደፖለቲካዊ ቤተ ሙከራነት የመለወጡ ሂደት ውስጥ ያሳዩት ጉልህ ተሳትፎም ለአፍታ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከዓለም ሕዝቦች መካከል እኛ ኢትዮጵያውያን ላይ ያልተፈተሸ ፖለቲካዊ መርዝ የለም፡፡ ባጭሩ የወያኔ ብቻ ሣይሆን የፈረንጆቹም guinea pig ሆነን የቀረን ብቸኛ መዘባበቻ ዜጎች ብንኖር እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ እርግጥ ነው እነኢራቅንና አፍጋኒስታንን ብንረሳ አግባብ አይደለም – እኛን እየገረፈን ያለው የኃያላኑ የእሳት ወላፈን እነሱንም እየጠበሰ ነውና፡፡ “አልማሊኪ ቡሽ፣ ካርዛይ ቡሽና መለስ ቡሽ እያሉ ሃቀኛ ሰላም አይኖርም፡፡”

ወያኔ ተግባር ላይ ካዋላቸው ሕዝብን የማሰቃያና ሀገርን የማውደሚያ መንገዶች አንደኛው እሳት ነው፡፡ እንዲህ የምላችሁ ወዳጄ አሁን ስላስታወሰኝ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከጥንትም በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ ለነገሩ ጨካኝና አምባገነን መንግሥታት ለዓላማቸው ስኬት የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ ደርግም በተወሰነ ደረጃ ይህን የእሳት ፖለቲካ ይጠቀምበት እንደነበር በጊዜው ሰምቻለሁ፡፡ ሞኙ ደርግ እሳትን ይጠቀምበት የነበረው ኮንትሮባንድን ከመቆጣጠር አንጻርና በጣም በጥንቃቄ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ አሁን ድረስ ያስታውሳሉ፡፡ የወያኔ ግን የተለዬ ነው፡፡

በመሠረቱ ወያኔ ምን እንደሆነ መናገር የዐዋጁን በጆሮ ነው፡፡ ይሁንና ወያኔዎች በተጣባቸው የትውልድ መርገምት ምክንያትም ይሁን በሌላ ከሆዳቸውና ያሻቸውን እንዲሠሩ ከሚጠቅማቸው የጨበጡት ሥልጣን በስተቀር የኢትዮጵያዊነት ስሜት በጭራሽ የሌላቸው፣ እንዲያውም ከያዙት ጥቅምና ሥልጣን ያስወግደናል ብለው የሚፈሩት በቀን ሰመመንና በሌት ቅዠት የሚያባትታቸው የኢትዮጵያዊነት ስሜት በመሆኑ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚልን ዜጋ ሁሉ በየሄደበት እያሳደዱና እየገደሉ በደም ባሕር እየዋኙ የሚኖሩ፣ ጥላቸውንም የማያምኑ የከተማ ወሮበሎች መሆናቸውን እዚህም ላይ በድጋሚ ማስታወሱ በአሰልችነት ሊያስወቅስ አይገባም፡፡ እናም አስታውሱ – ወያኔ የዜጎችን የላብ ውጤት የሆነ ሀብትና ንብረታቸውን ማቃጠል ብቻም ሣይሆን ሕዝብን በሠልፍ ኮልኩሎ እንደሂትለር የኦሽትዊዝ ቻምበር የማይፈልጋቸውን በጋዝ እየለበለበ ቢፈጃቸው የሰይጣናዊ ተፈጥሮው የሞራል ምሰሶ ክፋትና ጥፋት ነውና ደስታን የሚያስገኝለት እንጂ ሰብኣዊነት የሚሰማው ሩህሩህ ፍጡር አይደለም፡፡ ሰብኣዊነትና ወያኔ ዐይንና ናጫ ናቸው፡፡

ወያኔዎች እንደገቡ ሰሞን የምንሰማቸው ብዙ የእሳት አደጋዎች ነበሩ፡፡ እነዚያ እሳቶች እንደሰሞነኞቹ የሕዝብን አንጡራ ሀብትና ገንዘብ ለማቃጠል የታለሙ ሣይሆኑ ጫካና ደን የማያውቁት መደዴዎቹ ወያኔዎች ደቡብ ኢትዮጵያንም እንደሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለማራቆት የታቀዱ ደኖችን የማቃጠል ወያኔያዊ የክተት ዘመቻዎች ነበሩ፡፡ በርካታ የደቡብና የኦሮሞ ብሔር መኖሪያ አካባቢዎች በነዚያ ወያኔ በቀሰቀሳቸው የሰደድ እሳቶች ተቃጥለዋል – አንጀታቸው ለተፈጥሮም የሚጨክን አረመኔዎች ናቸው፡፡ በምክንያትነት ሲቀርብ የነበረው ግን የኦነግን ሸማቂዎች ከምንጫቸው ለማድረቅና መደበቂያ ቦታ ለማሳጣት የሚል ነበር፡፡ ትግራይ ውስጥ ወያኔን ሊደብቅ የሚችል ዋሻ ካልሆነ በስተቀር ደንና ጫካ እንዳልነበረ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ጫካ ቢኖር ኖሮ ወያኔን ለማጥፋት በሚል ሰበብ የደርግ መንግሥት ነዳጅ በቦቴ መኪናዎች ጫካ ውስጥ እየደፋ በአብሪ ጥይትም በአሻጋሪ እየለኮሰ ሀገር ለማቃጠል የሚያበቃው የሞራል ድቀት ውስጥ እንዳልነበረ ያንጀቴን እመሰክራለሁ – ሰው ካልሞተ ሚስትም ካልተፈታች ወይ ካልሞተች አይመሰገኑም ወንድማለም፡፡ ደርግ ዜጎችንና ሀገርን በእሳት አይቀጣም፤ ደርግ ኢትዮጵያዊ ጨካኝ እንጂ እንደወያኔ ወፍዘራሽ የባንዳ ውላጅ አልነበረም፡፡ እሳት ባለጌ ነው፡፡ እሳት እጅግ መጥፎ ነው፡፡ ምሕረትን አያውቅም፡፡ እንኳንስ ዜጋህን ጠላትህንም ቢሆን በአግባቡ ውጋው እንጂ፣ በአግባቡ ቅጣው እንጂ ኢ-ሰብኣዊ በሆነ ሁኔታ በእሳት አትገርፈውም፡፡ እነሂትለርና ሙሶሊኒ እንኳንስ ዜጎቻቸውን ጠላቶቻቸውንም ቢሆን በሰደድ እሳት አልቀጡም፤ በእሳት መቅጣት የጀግና ሙያ ሳይሆን የፈሪ ዱላ ነው፡፡ ወያኔ ግን ከየትኛው የጀሃነብ ሰማይ እንደወረደብን አይታወቅም ይሄውና ጫካና ደንን ከማቃጠል አልፎ የምሥኪን ዜጎችን ቤትና ንብረት እንዳሻው በሚያዛቸው ኅሊናቢስ ጀሌዎቹ እያቃጠለ ይገኛል፡፡ ወያኔ እኮ በእሳትም ብቻ ሳይሆን እንደተራ ተንኮለኛ ዜጋ ምግብንና መጠጥን በመመረዝና የታወቀ ጠንቋይ ቤት ድረስም በመሄድ የሚጠላቸውን የሚያስወግድ ጉደኛ ፍጡር ነው፡፡ ኪሮስ አለማየሁ እንዴት ሞተ? አለማየሁ አቶምሳስ? በውነት ቆሻሾች ናቸው፡፡ ምን አድርገን ይሆን ፈጣሪ እነዚህ ለቅጣት የሰጠን ግን? እስኪ ወደዬኅሊና ጓዳችን እንግባና ራሳችንን በቅጡ እንመርምር፡፡

በዚያን ሰሞን ሐረር ውስጥ የተቃጠለው መንደር የዚሁ የወያኔን ዜጎችን በእሳት የመቅጣት የእሳት ፖለቲካ ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያን ገንዘብ ለራሱ ፖለቲካ በመጠቀም ዜጎችን በአነስተኛና ቀጫጭን የሚባል አዲስ ፈሊጥ እያደራጀ አንዱን ርሃብተኛ ሌላውን ጥጋበኛ እያደረገ እናያለን፡፡ በጥቃቅን የማይደራጅን በጠላትነት በመፈረጅ በገቡበት እየገባ ያሳድዳቸዋል፡፡ ከወያኔ የተለዬ ነጋዴ ኑሮውና ግብሩ እሳት ሆነው እንዲያቃጥሉትና ከሀገር እንዲጠፋ ወይም በርሀብ አለንጋ ተገርፎ እንዲሞት ሲደረግ ወያኔን የተጠጋ ሆድ አደር ግን እምብርቱ እስኪገለበጥ እየበላና እየጠጣ ተንደላቅቆ ይኖራል፡፡ እንዲህ እንዲኖርም በመዥገሮች የተወረረችው እናት ሀገር በወያኔዎቹ አማካይነት ለአንዱ የእንጀራ እናት ለሌላው ደግሞ የእውነት እናት ሆና ለሆዳም ጥገኞቹ ሁሉንም ነገር እያመቻቸችላቸው ትገኛለች፡፡ ለምሳሌ በወያኔ ማኅበር ያልተደራጀ ዜጋ ሁለት በሁለት ለሆነች የንግድ ቤት ከገቢው ጋር ፈጽሞ የማይመጣጠን እጅግ ከፍተኛ ኪራይና ግብር እንዲከፍል ሲገደድ (ሂድ አትበለው እንዲሄድ ግን አድርገው በሚሉት ፈሊጣቸው) ለሆዳሞቹ ግን ካስፈለገ ካለኪራይና ካለአንዳች ግብር በሕዝብ ገንዘብ እንደፈለጉ ይሆናሉ፡፡ ባንኮች ሳይቀሩ ለነሱ የግል ጥገቶች ናቸው፡፡ የሀገር ስሜት ዛሬ ያልጠፋ ታዲያ መቼ ይጥፋ?

ይህ መሰሉና ሌላው ግፍ ሁሉ አልበቃ ብሎ ነው እንግዲህ የእሳቱ ፖለቲካ በሀገር ደረጃ እየተፋፋመ የሚገኘው፡፡ እንደሰማነው በሐረር ከአንዴም ሁለት ጊዜ ቃጠሎ ተነስቶ በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ብርና ሀብትና ንብረት ወድሟል፡፡ ይህ የሆነው በወያኔው ፈቃድና ይሁንታ መሆኑን የምንረዳበት መንገድ ደግሞ እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ሲደረግ አስቀድሞ የተዘጋጀው የወያኔ ጦር እሳቱን ከብቦ አላሰቀርብም ማለቱና የእሳት አደጋ ሠራተኞችም እሳቱ የሚፈለገውን ጥፋት ካገባደደ በኋላ ሥራቸውን እንዲሠሩ መፈቀዱ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ግፍ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚደረግ አይመስለኝም፤ እንዲያውም አይደረግም፡፡ ምክንያቱም የሀገር ዜግነቱን የካደና ሀገር እየቸረቸረ የሚሸጥ የሀገር መሪ ከኢትዮጵያ ውጪ በየትም ሥፍራ ይኖራል ብዬ አላምንምና፡፡

የሐረሩ እሳት መንስኤው ወያኔ ሆኖ ዓላማው ደግሞ ቦታውን ለወያኔያዊ ባለሀብቶች ለመስጠትና በእግረ መንገድም ተቀናቃኝ ኢ-ወያኔያዊ ባለሀብቶችን ለማክሰም ነው – ይህን እውነት ለማወቅ ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም፡፡ በጣም ግልጽ ነው፡፡ መንታ ዓላማ  ያነገበ ቃጠሎ ነበር ማለት ነው፡፡ አንደኛውና ዋነኛው በሥርዓቱ የማይፈለጉ ዜጎችን ማደኽት – ሁለተኛው በነሱ ቦታ ደግሞ ለሥርዓቱ ዕድሜ ቀን ከሌት ተንበርክከው ሰይጣንን የሚለምኑ ፍቁራን አባላትንና ደጋፊዎችን ማቋቋም፤ በቃ፡፡ በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ መሬት፣ በኢትዮጵያውያን ሀብትና ንብረት ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ የመንግሥትን ሞሰብ ገልባጮችና ደጋፊዎቻቸው ይገባበዙበታል፤ ይጠቃቀሙበታል፡፡ እንግዴ ልጅ ሀገር ሻጭ ማዕዱን ሲጫወትበት ልጅ ከበይ ተመልካችነትም ወርዶ የሥቃይ ሰለባ ሆኗል፡፡ እየተራቡ በሀገር መኖርም ክልክል ሆኖ ለሞትና ለስደት መዳረግ ዕጣችን እንዲሆን ተፈርዶብናል፡፡ ይህን ቅሚያና ዘረፋ፣ ይህን የግፎች ሁሉ የበላይ የሆነ ግፍ በእሳት አማካይነት እውን ለማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያን መለዮ ለባሽ ይጠቀማሉ -በዓይነቱ ልዩ የሆነ የታሪክ ምፀት ማለት ይህ ነው፡፡ á‹‹ እኔን! ይህች ቀን ልታልፍ እምቢልታው ሲነፋ እነዚህ ጉግማንጉጎች ምን ይውጣቸው ይሆን?

አዲስ አበባም ውስጥ በትንሹ ሁለት ያህል ቃጠሎዎች በነዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ተከስተዋል፡፡ አንደኛው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲሆን ሌላኛው በአንድ ግለሰብ ቤት የደረሰና የሦስት ሰዎችን ሕይወት የጠየቀ ቃጠሎ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡ ነፍሳቸውን ይማር፡፡ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤቱ ግን ያጠያይቃል፡፡ እርግጥ ነው – ቃጠሎው ተፈጥሯዊ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደማንኛውም አደጋ ሆን ተብሎ ሳይሆን ድንገት ሊነሳ የመቻሉ ዕድል እንዳለ ሆኖ ከወያኔ ባሕርይ ተነስተን ስንገምት መነሾው ፖለቲካዊ አንድምታም ሊኖረው እንደሚችል ብንጠረጥር “ጠርጣሪዎች(skeptics)” ተብለን ልንታማ አይገባም፡፡ እንዲያውም ስንትና ስንት ጥበቃ የሚደረግለት ትልቅ ድርጅት በቀላሉ ለእሳት ይዳረጋል ብሎ ከማሰብ አለማሰብ ይሻላል ብለን ብንከራከር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ከድንገቴ አደጋነት ይልቅ የወያኔው ተንኮል እንደሚኖርበት መገመት አይከብድም፡፡ ወያኔ ለምን ብርሃንና ሰላምን ያቃጥላል? ምን ያገኛል? ከመገመት ባለፈ እውነተኛውን ነገር ማወቅ ሊከብድ ይችላል፤ መገመት ደግሞ ለማንም የማይከለከል የሁሉም መብት ነው፡፡

ከሁሉም በፊት ግን አንድ አጠቃላይ እውነት መኖሩን እንመን፡፡ ያም እውነት ወያኔ ቢቻል ቢቻል ኢትዮጵያ እንዳለች ብትቃጠል ወይም እንጦርጦስ ብትወርድ ደስ ይለዋል እንጂ የማይከፋ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስሟ ሲነሳ የሚዘገንናቸውና ጠበል በመጠመቅ ያለ ሰው ላይ እንደተከሰተ ሰይጣን የሚያንዘረዝራቸው እነበረከትንና ሣሞራን የመሳሰሉ መፃጉዕ ዜጎች የሚገኙበት መንግሥታዊ መዋቅር የኢትዮጵያ ታሪክ የሚዘከርበትና አእምሯዊ ቅርስ የሚቀመጥበት ማዕከል ቢቃጠል አይደሰትም ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ በዕንቆቅልሽ ሀገር ውስጥ ልንጠብቅ የማይገባንን ነገር ብንጠብቅ ብልህነት እንጂ ትዝብት ውስጥ ሊያስገባን የሚችል ሞኝነት አይደለም፡፡

በመሆኑም ወያኔ ይህን የእሳት ፖለቲካውን በመጠቀም ዜጎችን ራቁታቸውን ማስቀረቱንና ወደበረንዳ ሕይወት መለወጡን እንዲያቆም፣ የዘመናት ቅርሳችንን እያቃጠለ ታሪክ አልባ ሆነን እንድንቀር ማድረጉን እንዲገታና እስከተቻለ ደግሞ ነፃነታችንን እውን ለማድረግ የምንችልበትን የጋራ ሥልት መቀየስ እንድንችል የጋራ ጥረት እንድናደርግ ጥሪየን አቀርባለሁ፡፡ ሰላም፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on March 25, 2014
  • By:
  • Last Modified: March 25, 2014 @ 3:30 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar