www.maledatimes.com ኢህአዴግን የምደግፍበት አንድ ነገር አገኘሁ- መሬት አይሸጥም አይለወጥም! – ፋሲል የኔዓለም (ጋዜጠኛ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ኢህአዴግን የምደግፍበት አንድ ነገር አገኘሁ- መሬት አይሸጥም አይለወጥም! – ፋሲል የኔዓለም (ጋዜጠኛ)

By   /   March 28, 2014  /   Comments Off on ኢህአዴግን የምደግፍበት አንድ ነገር አገኘሁ- መሬት አይሸጥም አይለወጥም! – ፋሲል የኔዓለም (ጋዜጠኛ)

    Print       Email
0 0
Read Time:15 Minute, 53 Second

ለመጀመሪያ ጊዜ ኢህአደግን የምደግፍበት ነገር አግኝቻለሁ። ኢህአዴግ በመቃብሬ ላይ ካልሆነ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ይላል። ትክክለኛና ብራቮ የሚያስብል አቋም ነው።

መሬት የሃብት ሁሉ ምንጭ ነው፤ መሬት ያለው “ምንም” ነገር ባይኖረው ሃብታም ነው። ከጊዜ በሁዋላ እንኳንስ የእርሻና የቤት መስሪያ ቦታ ማግኘት ቀርቶ ለመቀበሪያ የሚሆን ቦታ ማግኘትም ጭንቅ ይሆናል – የሰው ልጅ እንደ አሜባ በፍጥነት ይራባል፣ መሬት ደግሞ በዛው ልክ እየጠበበች ትሄዳለች። እናም ይህን ብርቀየ ሃብት በስርዓት መንከባከብ ግድ ይላል። 

መሬት በግለሰቦች እጅ መሆኑ ምርትን ለማሳደግ ይጠቅማል የሚለው መከራከሪያ አሳማኝ ነው ። ኢህአዴግ ገበሬውንና የከተማውን ሰው እንደፈለገ የሚቆጣጠረው መሬት የመንግስት ስለሆነ ነው የሚለው መከራከሪያም እንዲሁ አሳማኝ ነው። ለመሬቱ ሲል ፈቅዶ የኢህአዴግ ባሪያ ለመሆን የመረጠ ብዙ ወገን አለ፤ መሬትን ነጻ ማድረግ ኢህአዴግ ከዘረጋው የባርነት ቀንበር ነጻ ለመውጣት አንድ እርምጃ ነው ተብሎም ሊታሰብ ይችላል። እርግጠኛ ባልሆንም እያመነታሁ እቀበለዋለሁ። ። በአጭሩ መሬት ወደ ግለሰቦች መዞሩን በመርህ ደረጃ እደግፋለሁ። ነገር ግን ዘረኝነትና ሙሰኝነት ባህሪው በሆነው መንግስት ስር ሆነን፣ መሬት ወደ ግል ይዙር ቢባል ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ይመስለኛል ፣ ከኢህዴግ ባርነት ነጻ እንወጣለን ስንል የዘመናት ባርነትን እንዳንከናነብ እሰጋለሁ ። ኢህአዴግ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መሬትን ወደ ግል የማዞር ብቃት የለውም። ይህን ደግሞ በ1980ዎቹ፣ በአማራ ክልል የመሬት ክፍፍል በተደረገበት ወቅት አይተነዋል። ሰዎች በፖለቲካ አቋማቸው ብቻ መሬት እንዳያገኙ መደረጉን በጊዜው ይወጡ የነበሩትን ዘገባዎች አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል።
አዲስ ስርአት እስኪመጣ መሬት ወደ ግል ባይዞር በብዙ መልኩ ተመራጭ ነው።

ባለፉት 23 ዓመታት ዋና ዋና የሚባሉ የከተማ መሬቶችን የህወሃት ሹሞችና ተላላኪዎቻቸው ተቆጣጥረዋቸዋል። ከከተሞች አልፎ በገጠር ለም የሚባሉትን የእርሻ መሬቶችንም እየተቆጣጠሩዋቸው ነው። ጋምቤላ፣ ኦሮምያ፣ ቤንሻንጉል፣ አፋር እንዲሁም ሰሜን አማራ ብትሄዱ ሰፋፊ መሬቶች በዘመኑ ሰዎች የተያዙ ናቸው። በአዲስ አበባ በአንድ ወቅት በተደረገ ጥናት አብዛኞቹ የከተማዋ ቁልፍ መሬቶች በህወሃትና ተላላኪዎቻቸው የተያዙ መሆኑ ተረጋግጧል ። መሬትን እየተሽቀዳደሙ የመያዙ እሩጫም በቀላሉ የሚቆም አይመስልም፣ አይቆምም። በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ( ኢህአዴግ በህይወት ከኖረ) እስካሁን ያልተያዙት ሰፋፊ የእርሻና የከተማ ቦታዎች በጥቂት የዘመኑ ባለሃብቶች ቁጥጥር ስር እንደሚውሉ ለመተንበይ ሼህ ጅብሪል ወይም የፍጥሞውን ዮሃንስ መሆንን አይጠይቅም። ምክንያቱም ግልጽ ነውና ። መሬት የሃብት ምንጭ ነው፤ ሃብት ያለው ጉልበት አለው፤ ጉልበት ያለው ስልጣን አለው፤ ስልጣን ያለው ሁሉም አለው ።

አሁን ባለው መንግስት መሬት ወደ ግል ይዞታ ይዙር ማለት ላለፉት 22 ዓመታት ሰፋፊ መሬቶችን ዘርፈው የያዙ የዘመኑ ባለሃብቶች የግል መሬት እንዲኖራቸው መፍቀድ ማለት ነው። የሚመጣው መንግስት የእነዚህን ባለሃብቶች መሬት ቀምቶ ለማከፋፈል ቢሞክር ከአለማቀፍ ድርጅቶች ሳይቀር ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥመዋል። በደርግ ዘመን የግል ባለሀብቶች ንብረት ወደ መንግስት በዞረበት ወቅት ከምእራባዊያን አገራት ትልቅ ተቃውሞ መነሳቱን አንዘነጋም። አሁን ባለው የአለም ስርአት የግል ባለሀብቶችን መንካት ማለት ከምእራባዊያንና ከገንዘብ ተቋሞቻቸው ጋር መላተም ማለት ነው። ይሄ መንግስት እስከሚለወጥ መሬት በመንግስት እጅ ከቆየ፣ መጪው መንግስት የእነዚህን ሰዎች መሬት ቀምቶ ለማከፋፈል ቢሞክር ከየትኛውም ወገን ተቃውሞ አይደርስበትም፣ ምክንያቱም መሬት የመንግስት ነውና። ” አስፈላጊው ካሳ ተሰጥቷቸው መሬታቸው ቢቀማ ተቃውሞ አይኖርም ” ቢባል እንኳ፣ በህገወጥ መንገድ ለያዙት መሬት ካሳ መክፈል የሞራልና የፍትሃዊነት ጥያቄ ያስነሳል። አዲሱ መንግስት የኢትዮጵያን የመሬት ስሪት በደንብ አጥንቶና ሁኔታዎችን ሁሉ አመቻችቶ መሬት ወደ ግል ቢያዞር ያን ጊዜ ቁጥር አንድ ደጋፊ እሆናለሁ። ዝምባብዌ ነጻ ከመውጣቱ በፊት መሬት የመንግስት ቢሆን ኖሮ፣ ነጻ በወጣ ማግስት መሬት ከግለሰቦች እየቀማ ያከፋፈለው የዝምባቡዌ መንግስት አሁን የገጠመውን ተቃውሞ ያክል አይገጥመውም ነበር፤ ደቡብ አፍሪካም ነጻ ሲወጣ መሬት የመንግስት ቢሆን ኖሮ፣ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ለብዙ ጥቁሮች መሬት እንደፈለገ ለማከፋፈል አይቸግረውም ነበር። በኢህአዴግ ዘመን መሬት ቢከፋፈል የዝምባብዌና የደቡብ አፍሪካ እጣ ይገጥመናል። መሬቱ ሁሉ በጥቂት የዘመኑ ሰዎች እጅ ይገባና እነሱ ” ነጮች” እኛ “ጥቁሮች” እንሆናለን። መጪው መንግስት መሬትን በፍትሃዊነት ማከፋፈል ይችል ዘንድ መሬት በመንግስት እጅ ሆኖ መቆየት አለበት። ኢህአዴግ መውደቁን ካወቀ፣ መሬትን ወደ ግል አዙሮ ለመጪው መንግስት ችግር አውርሶት ያልፍ ይሆን እያልኩ እሰጋለሁ።

በኢህአዴግ ዘመን መሬትን ወደ ግል እንዲዞር መፍቀድ ማለት እነዚህ ጥቂት የዘመኑ ሰዎች አሁን ከያዙትም በላይ ሰፋፊ መሬቶችን በፍጥነት እንዲያግበሰብሱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ማለት ነው። ዘመነኞቹ “መሬት ወደ ግል ሊዞር ነው” የሚለውን ሲሰሙ፣ በውጭ ባንኮች የከዘኑትን ገንዘብ እያወጡ መሬት በፍጥነት ለመግዛት ይጣደፋሉ። ስርአቱም የተወሰኑ ሰዎች ሰፋፊ መሬቶችን እንዲይዙ ሁኔታውን ያመቻችላቸዋል። ያልተያዙ መሬቶችን ለመግዛት ገንዘብ ቢያጥራቸው እንኳን የባንክ ብድር ይመቻችላቸዋል። የመንግስት ድርጅቶች ወደ ግል ሲዞሩ ያየነው ህገወጥ አሰራር በመሬት ሽያጭ ላይ እንደማይደገም ምንም ማረጋገጫ የለም ። የሻኪሶ ወርቅ ማእድን በስንት ነው የተሸጠው? በርካታ የመንግስት የንግድ ድርጅቶች እንዴት ነው ወደ ግለሰቦች የዞሩት? የተሸጡበት ገንዘብ መጠን ለህዝብ ተነግሮ ያውቃል? ገንዘቡስ መንግስት ካዝና መግባቱ ይታወቃል?
ቅንጅት አዲስ አበባን ሲያሸንፍ፣ የስርአቱ ልጆች ሰፋፊ መሬቶችን መቀራመት ጀመሩ፣ ኢህአዴግም ሆን ብሎ ሁኔታዎችን አመቻቸላቸው። ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስር ያለች ትመስል ነበር። ቅንጅት ቢጨንቀው ” የመሬት ዝርፊያው በአስቸኳይ እንዲቆም” የሚጠይቅ መግለጫ አወጣ። የሚሰማ ግን አልነበረም። አላሙዲ ሳይቀር ጊዮርጊስ መሃል አደባባይ ላይ ለአመታት አጥሮ ያስቀመጠውን ቦታ እንዳልቀማ ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ አረሰው። ከዚያ ወዲህ ድፍን አስር አመት ምንም ስራ አልሰራበትም። ቅንጅት አዲስ አበባን እንደማይረከብ ሲያውቅ፣ ኢህአዴግ በመናኛ ገንዘብ ያዘረፈውን መሬት መልሶ ለመሰብሰብ ተሳነው። መሬት ወደ ግል ሊዞር ነው ቢባል ተመሳሳይ ነገር እንደሚፈጠር አልጠራጠርም።

በዚህ በዘርና በጥቅም በተማከለ ስርዓት ውስጥ ሆኖ መሬት ወደ ግል ይዙር ብሎ መጠየቅ በራስ ላይ እባብ እንደመጠምጠም ይቆጠራል ። ስለመሬት መሸጥና መለወጥ ለማውራት ኢህአደግ መቃብር እስኪገባ ድረስ መጠበቅ ግድ ይለናል። መታገል ያልብንም ኢህአዴግን ወደ መቃብር ለመሸኘት ነው። በእርሱ መቃብር ላይ አዲስ ስርአት ስንፈጥር ፣ ያን ጊዜ፣ ሁሉንም በማያስደስት ፣ ሁሉንም በማያስከፋ መልኩ መሬት ማከፋፈል ይቻላል።
ኢህአዴግ እስኪወድቅ መሬት በመንግስት እጅ መሆኑን በጽኑ እደግፋለሁ!

( ማሳሰቢያ ይሄ የግል አቋሜ ነው። አንድነት ፓርቲ በቅርቡ
ካስተዋወቀው የሚሊዮኖች ድምጽ ጋር በፍጹም አይያያዝም። ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ Wealth Over Work- በሚል ርዕስ ፓውል ክሩግማን The New York Times ላይ የጻፈው ጽሁፍ ነው። በዚህ ዙሪያ ሰፊ ክርክር እንደሚኖር እጠብቃለሁ)

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on March 28, 2014
  • By:
  • Last Modified: March 28, 2014 @ 8:36 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar