www.maledatimes.com ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ! መጠላለፍ ወደየትኛው ገደል እየመራን ነው? by መስፍን ወልደ-ማርያም - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ! መጠላለፍ ወደየትኛው ገደል እየመራን ነው? by መስፍን ወልደ-ማርያም

By   /   April 2, 2014  /   Comments Off on ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ! መጠላለፍ ወደየትኛው ገደል እየመራን ነው? by መስፍን ወልደ-ማርያም

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 51 Second

መስፍን ወልደ ማርያም
መጋቢት 2008

የአዲስ አበባን መኪናዎች በተለይም በጫት የሚሽከረከሩት ታክሲዎችን በማንኛውም መስቀልኛ መንገድ ላይ ለአምስት ደቂቃ ቆሞ የተመለከተ ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው ‹እኔ ካላለፍሁ ማንም አያልፍም!› በሚል መመሪያ መኪናዎቹ ተቆላልፈው እንዲቆሙ ማድረግ ነው፤ እንደሚመስለኝ የአባቶቻችንን ዕዳ እየከፈልን ነው፤ ዱሮ በደጉ ዘመን ሁለት ኢትዮጵያውያን መስቀልኛ መንገድ ላይ ሲገናኙ አንተ-እለፍ አንተ-እለፍ እየተባባሉ የሰማዕታቱንና የቅዱሳኑን ስም እየጠሩ ይገባበዙ ነበር! ይህ ባህል በጠንካራ የሥልጣኔ ላጲስ ተደምስሶ ጠፍቶ በምትኩ እኔ ካላለፍሁ ማንም አያልፍም መንገዱን ሁሉ መቆላለፍ አዲስ የመጠላለፍ ባህል እየተተከለ ነው፤ የመጠላለፍ ባህል የሚታየው በባቡር መንገዶች ላይ ብቻ አይደለም፤ በብዙ ነገር መጠላለፍ ባህል እየሆነ ነው! የዚህ ዝንባሌ መጨረሻው አሸናፊ የሌለበት ሙሉ ጥፋት ነው።
በመንገዶች ላይ ጥቂት በጫት የሚነዱ መኪናዎች በመቶ የሚቆጠሩ መኪናዎች እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ይችላሉ፤ ሲያደርጉም በየቀኑ እየታየ ነው፤ በማኅበረሰባዊና በፖሊቲካ ግንኙነትም አንድ ሰው የሚዘራው መርዝ የጊዜው ሁኔታ በሚፈቅድለት ፍጥነት የማኅበረሰቡን አባላት ያዳርሳል፤ እንቆቅልሹ እንደሚለው ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ! ማለት መርዝ፣ እሳት፣ ተላላፊ በሽታ በሕዝቡ ላይ ማሰራጨት ከአምስትና ከአሥር ዓመታት በኋላ ውጤቱ ምን እንደሚሆን መገመት አያቅትም።
ድብብቆሽ አይጠቅምም፤ሁለት ነገሮችን በግልጽ ማውጣት አለብን፤አንደኛ በአሜሪካና በአውሮፓ መሽጎ ፍርሃቱንና ሽቁጥቁጥነቱን ለመሸሸግ መርዙን በኢትዮጵያውያን ላይ የሚረጨው ለምንድን ነው? አገዛዙ ይህንን የሚያደርግበት ምክንያት ግልጽ ነው፤ ከፋፍሎ የመግዛት ዘዴ ነው፤ ከአገዛዙ ጋር በሚደረግ ትግል ከታች ሆነው ከሥልጣን ውጭ የሆኑ ዜጎች በሥልጣን ላይ ከተቀመጡት ጋር እየተቆራቆዙና እየተጋጩ ናቸው፤ ይህንን እኔ የላይና-የታች ግጭት (vertical conflict) የምለው ነው፤ ከወያኔ/ኢሕአዴግ ጋር የሚደረገው ትግል ይህ ነው፤ ይህንን ለማክሸፍ ወያኔ/ኢሕአዴግ ትግሉን ከላይና-ታች አውጥቶ ወደጎን-ለጎን ግጭት (horizontal conflict) ሊለውጠው ይፈልጋል፤ ከወያኔ/ኢሕአዴግም ውጭ በጎሠኛነትና በሃይማኖት አክራሪነት የደነዘዙ ሰዎችም ትግሉን ጎን-ለጎን ሊያደርጉት እየሞከሩ ናቸው።
የፖሊቲካ ትግልን የሚመሩ ሰዎች በጎሠኛነትና በሃይማኖት አክራሪነት ስሜት እየተሳቡ ትግሉን የላይና-የታችነቱን ጠብቀው በተደራቢነት የጎን-ለጎን ትግሉን ይጨምሩበታል፤ ይህ ሲሆን ሀሳብ፣ ጉልበትና ሀብት ይከፋፈላል፤ ይበታተናል፤ ወደዓላማ ለመድረስም ያስቸግራል፤ ወያኔ ወደመጨረሻው ላይ ኢሕአዴግ ብሎ የሰየመውን ቀፎ አስቲፈጥር ድረስ በስሙ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያነሣ ነገር አልነበረውም፤ ወያኔን ለድል ያበቃው የማታለያ ስሙ እንደሆነ በበኩሌ አልጠራጠርም፤ ከሃያ ሁለት ዓመታት የጎሣ ሥርዓት በኋላ ኢትዮጵያ ቆስላለች እንጂ አልሞተችም፤ የአሐዝ ማስረጃ ለማቅረብ ባልችልም በብዙ ጎሣዎች መሀከል ጋብቻ እንደዱሮው እየቀጠለ ነው፤ ይህንን የቆየ የዝምድና ሰንሰለት ለመበጠስ የሚጥሩም አሉ።
ኒው ዮርክ ተቀምጦ ትኩስ ውሻ (ሆት ዶግ!) እየበላ ለእስላም ኦሮሞዎች የመገዳደያ መመሪያ የሚሰጥ ሰው የመንፈስ ጤንነቱን እጠራጠራለሁ፤ ይህንን የኒው ዮርክ ቀረርቶ ተከትሎ ሌላ የመጠላለፍ አዋጅ ሰማን፤ ቴዎድሮስ ካሣሁን ለአጼ ምኒልክ ስለዘፈነ ከበዴሌ ቢራ ፋብሪካ ጋር ለማስታወቂያ የገባው ውል ሥራ ላይ ከዋለ የበዴሌን ቢራ አንጠጣም ተባለና ማስታወቂያው ተሰረዘ ይመስለኛል፤ ማን እንዳሸነፈ ወደፊት ጊዜ ይነግረናል፤ አሁን ደግሞ ሌላ ማዘዣ ሰማሁ፤ ‹‹የስ›› በሚለው ውሀ ጠርሙስ ላይ እንስራ የተሸከመችው ኮረዳ መስቀል አድርጋ ነበር፤ ልጅቱ ከነመስቀልዋ የምትታይበትን ውሀ እስላሞች አንገዛም ስላሉ ነጋዴዎቹ መስቀሉን አወለቁባት! ይህንን ማዘዣ ላወጣው አክራሪ እስላም ወረባቦ ቅዳሜ ገበያ ሄዶ እንዲጎበኝ አሳስበዋለሁ፤ ዛሬ ተለውጦ እንደሆነ አላውቅም እንጂ እኔ ብዙ ጊዜ ተመላልሼ እንዳየሁት የወረባቦ ኮረዶች ሁሉ ትልልቅ መስቀል በአንገታቸው ላይ ይታይ ነበር፤ መስቀል የእምነት መግለጫ ይሆናል፤ አያጠራጥርም፤ ግን መስቀል ጌጥም ይሆናል! መስቀል የናዚ ምልክትም ሆኖ ነበር! ለማናቸውም የዚህ ዓይነቱን መጠላለፊያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገምዱ ሰዎች ዓላማቸው ማንንም ለመጥቀም ሳይሆን ፍቅርንና ሰላምን ለማደፍረስ ነው፤ የኢየሱስ ክርስቶስ መሠረታዊ ትምህርት ክፉን በክፉ አትመልሱ ነውና ለተበጠሰው መስቀል አጸፋውን ለመመለስ ማሰብ አይገባም።
ከኒው ዮርክ የተሰማው ቀረርቶም ሆነ የመስቀል ማስወለቁ ጉዳይ የተከሰተበትን ጊዜ ልብ ልንለው ይገባል፤ እስላሞች ስለነጻነት የሚያደርጉት ንቅናቄ በጣም እየጋለ በመሄድ ላይ እያለ ክርስቲያኖችም የዜግነት ግዳጃቸው አድርገውት ድጋፋቸውን በሚሰጡበት ጊዜ ነበር፤ ይህ መሆኑ ጥርጣሬን ይጋብዛል፤ የገጠመውን የእስላሞችና የክርስቲያኖች ሰልፍ በማደፍረስ ወይም በመክፈል የሚጠቀም ማን ነው? የሚጎዳውስ ማን ነው? ሁሉም የትግል አጋፋሪዎች ለዚህ ጉዳይ የሚያስፈልገውን ክብደት ቢሰጡት ትግሉ በጎን-ለጎን እንዳይሄድና እንዳይዳከም ይረዳል፤ ከዚያም በላይ አክራሪነት የሚባለውና የሚያስከትለውም ሽብርተኛነት የሚመጣው እንዲህ እያለ ነው፤ እግዚአብሔር ከዚያ ያውጣን!

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on April 2, 2014
  • By:
  • Last Modified: April 2, 2014 @ 9:23 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar