www.maledatimes.com የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒሊክ ትውልድ! ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2006 á‹“.ም. (Thursday, April 3, 2014) ————- ግርማ ሞገስ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒሊክ ትውልድ! ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2006 á‹“.ም. (Thursday, April 3, 2014) ————- ግርማ ሞገስ

By   /   April 3, 2014  /   Comments Off on የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒሊክ ትውልድ! ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2006 á‹“.ም. (Thursday, April 3, 2014) ————- ግርማ ሞገስ

    Print       Email
0 0
Read Time:29 Minute, 50 Second

የዚህ ጽሑፍ ግብ በመንግስት ስልጣን ሽሚያ የተነሳ በአንድ ወገን በዮሐንስ እና በአሉላ ትውልድ በሌላ ወገን
በምኒልክ እና በጎበና ትውልድ መካከል የነበረውን የፖለቲካ ባላንጣነት፣ ለስልጣን ሲሉ የተደራረጉትን እና
የፈጸሙትን ስህተት መተረክ አይደለም። በመካከላቸው የነበረው ጸብ ዙፋኑ ለእኔ ይገባ ነበር የሚል ጸብ ነበር፡፡
የስልጣን ጸብ ነበር። በእርስ በርስ ጦርነት የሚፈጸመው ስርዓት አልባው የመንግስት ሽግግር ባህላችን የፈጠረው
ጸብ ነበር። ይህ የቀድሞ አባቶቻችን የፖለቲካ ባህል ችግር ዛሬም አብሮን አለ። ያን ችግር ለማስወገድ ሰላማዊ
ትግል ጀምረናል። የኢትዮጵያን ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት ለማድረግ ጉዞ ላይ ነን። ወደ ዴሞክራሲ
ለመሸጋጋር በቁርጠኛነት ተነስተናል።

የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒልክ ትውልድን የፖለቲካ አሰራር ስንመረምር እና ስንመዝን በ19ኛው ክፍለ
ዘመን በነበራቸው እውቀት እና የፖለቲካ ባህል ደረጃ መሆን አለበት። ዴሞክራሲያዊ መሆን ነበረባቸው ማለት
አንችልም። እኛ ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ብዙ እውቀት አግኝተንም ገና ዴሞክራሲ አልሆንም። በየደረ ገጹ እና
በኢቲቪ እንደታየው እኛ ዛሬ የሰው ልጅ ከነህይወቱ ጉድጓድ ውስጥ እንጥል የለም እንዴ? እኛ ያልደረስንበትን
ስልጣኔ እነሱ ለምን አልደረሰቡትም ብሎ መውቀስ ትክክል አይደለም። እንዲያውም እነሱ ፈሪሃ እግዚአብሐር
ነበራቸው። የአልቤኒያው ደብተራ መለስ ዜናዊ እና ተከታዮች ግን ፈሪሐ እግዚአብሔር የላቸውም።

የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒልክ ትውልድን በ21ኛው ክፍል ዘመን ባገኘነው እውቀት እና ባህል ደረጃ
እንስፈራቸው ካልን አንድም ብስለት የለንም አሊያም የጥላቻ እና የክፍፍል ፖለቲካ ሆን ብለን መርጨት ላይ ነን።
በጎ ስራ ሰርቶ የህዝብ ድጋፍ ማግኘት እና የስልጣን እድሜ ማራዘም ይቻላል። ያን ማድረግ ሲሳንህ ግን ሌላውን
እንዲጠላ በማድረግ መወደድን አገኛለሁ ብለህ የምታስብ ከሆነ ተሳስተሃል። በዚህ አይነት የስልጣን እድሜ
ለማራዘም እችላለሁ ብለህ ከሆነ ቆም ብለህ አስብ! ህዝብን አንዴ እና ሁለቴ ማታለል ትችል ይሆናል። ሁሌ
ማታለል ግን አትችልም።

ስለዚህ የዚህ ጽሑፍ ግብ ዙፋን ለእኔ ይገባል ከሚል ይነሳ የነበረውን የፖለቲካ ባላንጣነታቸውን መተንተን
ሳይሆን የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒልክ ትውልድ እንደ ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ እና ለቀጣይ ትውልድ
ሰርቶ እና አውርሶ የሄደውን መመርመር ነው። የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒልክ ትውልድ የሚጠበቅበትን
ሰርቶ ሄዷል ወይ? ሊመሰገን እና ሊወደስ ይገባል ወይ? ልናከብረው ይገባል ወይ? በአልቤኒያው ደብተራ መለስ
ዜናዊ እና ተከታዮቹ ሊወቀስ ይገባል ወይ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ መስጠት ነው። ለእነዚህ ጥያቄዎች በቀላሉ
መልስ መስጠት እንድንችል የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒልክ ትውልድ የመጣበትን ዘመን በአጭሩ
በመጎብኘት እንጀምራለን። ለረጅም ዘመን የአባይ ወንዝ ባለቤትነት ምኞት የነበራት ግብጽ ኢትዮጵያን በወታደራዊ ኃይል ከሱዳን ቀላቅላ
በመግዛት የጣና ሐይቅና የአባይ ወንዝ ሸለቆ ባለቤት ለመሆን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 1875 (እ.ኢ.አ. 1863)
ዓ.ም. ግድም (1) በሰሜን ከመረብ ወዲያ ያለውን ደጋማውን ግዛት ተሻግራ እስከ አድዋ፣ (2) በምዕራብ ከቋራ
አልፋ ቤጌምድርን፣ (3) ከቶጆራ ጅቡቲ ተነስታ አውሳንና ሸዋን እንዲሁም (4) ከዜይላ ተነስታ ሐረርጌን
ለመውረር ጎንበስ ቀና ማለት ላይ በነበረችበት ሰዓት ነበር የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒልክ ትውልድ
የፖለቲካ ኃይል ከምድር የተነሳው።
የቴዎድሮስ ትውልድ የቅኝ አገዛዝ ዋዜማ ትውልድ ነው። አሰብን በመግዛት ረገድ ሁነኛ ሚና የተጫወተው
ጣሊያናዊ በቴድሮስ ዘመን በሚስዮናዊነት በሰሜን ኢትዮጵያ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሰው ነው። በቅኝ አገዛዝ ዋዜማ
የአውሮፓ ኃያላን መንግስታት በአፍሪካ ውስጥ ባሰራጩዋቸው በዘመናዊ ትምህርት (ፖለቲካ፣ ስለላ፣
ኢኮኖሚክስ፣ ህክምና፣ የመንገድ ስራ፣ የህንጻ እና ድልድይ ስራ፣ የአናጺነት ሙያ ወ.ዘ.ተ.) የሰለጠኑ
ሚስዮናውያን፣ ተመራማሪዎችና ቆንሲሎቻቸው አማካኝነት አፍሪካን መውጫዋን፣ መግቢያዋን፣ የተፈጥሮ
ሃብቷን፣ የህዝቧን በስልጣኔ ወደ ኋላ መቅረት፣ የዘርና የፖለቲካ ክፍፍሏ ሳይቀር በዝርዝር እየተጠና በሪፖርት እና
በመጽሐፍ መልክ ይላክላቸው ነበር። እነዚህ ሪፖርቶች እና መጽሐፍቶች በውጭ ጉዳይ ምኒስትር ቢሮዎች
በተቀመጡ እውቅ የፖለቲካ አቀንቃኞች ከልብ እየተጠኑ ለአዲስ መልዕክተኞች ስልጠና ይሰጥ ነበር። በሌላ በኩል
ደግሞ በስብሰባም፣ በመልዕክትም፣ በቃልም፣ በፅህፈትም አፍሪካን እንዴት እርስ በርስ ሳይጋጩ በሰላም
መከፋፈል እንደሚችሉ አሳብ ለአሳብ ሲለዋወጡ ነበር። በዚህ አይነት አውሮፓውያን እርስ በርስ ሳይጣሉና
ሳይዋጉ አፍሪካን የሚይዙበትን፣ ንግዳቸው የሚስፋፋበትን፣ በቀይ ባህር የመርከቦቻቸው ዝውውር በሰላም
የሚከናወንበትን ስምምነት ሊዋዋሉ ዝግጅት ላይ ሳሉ ነበር የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒልክ ትውልድ
በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ብቅ ያለው።
በቀይ ባህር የመርከቦቻቸውን ዝውውር ለማሳካት አውሮፓውያን በቀይ ባህር ዳርቻ ባሉ አገሮች ባህር በሮች
እግራቸውን ማስገባት ጀመሩ። በዚህ ረገድ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 1885 ዓ.ም. ግብጾች ሐረርጌን ሲለቁ ቀደም
ብለው ይዘውት የነበረውን የዜይላ እና የበርበራ (ሰሜን ሶማሊያ) ባህር በሮች እንግሊዝ ያዘች። እንግሊዝ ሐረርም
ዲፕሎማቶች ትልክ ነበር። ተመራማሪዎች በሚል ሽፋን ፈረንሳይ እና ጣሊያንም ሰላዮቻቸውን ወደ ሐረር ይልኩ
ነበር። በመጨረሻ ግብጽ፣ ሱዳን እና ኬኒያም የእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ሆኑ። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1862
ግድም ፈረንሳይ ከኦቦክ ባላባቶች የኦቦክን የመርከብ ማቆሚያ ከገዛች በኋላ በወታደራዊ ኃይል ወደ ቶጆራና ጅቡቲ
ገባች። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1882 ዓ.ም. ጣሊያን እግሩን በአሰብ አስገብቶ የቅኝ ገዢ ባንዲራውን
ማውለብለብ ከጀመረ ወዲህ ወደ ውስጥ እስከ ሸዋ ድረስ ዘልቆ ልዑካን በመላክ በቀን ስለንግድና ፍቅር እያወራ
በለሊት ከአሰብ ወደ ምጽዋ መንፏቀቅ ጀምሮ ነበር። ከዚያ ጣሊያን በወታደራዊ ኃይል እግሩን ምጽዋ አስገባ።
በመቅድሾም ተተከለ። ኢትዮጵያ በዚህ አይነት በቅኝ ገዢዎች በተከበበችበት ወቅት ነበር የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና
እና የምኒልክ ትውልድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ህይወት የገባው።
ስለዚህ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 1884 (እ.ኢ.አ 1877) ዓ.ም. የአውሮፓ ኃያላን አገሮች በጀርመን (በርሊን)
ተገናኝተው አፍሪካን በሰላም እንደ ቅርጫ ለመቀራመት በአሳብ ደረጃ የነበራቸውን ስምምነት በፊርማቸው ሲያጸድቁ የአሉላ እና የዮሐንስ ትውልድ በሰሜን ኢትዮጵያ የጎበና እና የምንሊክ ትውልድ በደቡብ እና በምስራቅ
ኢትዮጵያ አገር የመጠበቅ እና የመገንባት ዘመቻዎች በማድረግ ላይ ነበር። ለጥቀን ለናሙና ያህል በአጭር በአጭሩ
የአሉላ እና የዮሐንስ ትውልድ በሰሜን ኢትዮጵያ የጎበና እና የምኒልክ ትውልድ በደቡብ እና በምስራቅ ኢትዮጵያ
የፈጸሙትን እንጎብኝ።
በሰሜን ኢትዮጵያ የአሉላ እና የዮሐንስ ትውልድ በ1875/6 በጉንደት እና በጉራ የግብጽን ወረራ አከሸፈ። ምጽዋን
ለማስመለስ እንዲሁም ከሰላን የኢትዮጵያ ለማድረግ እንግሊዝን ብዙ ታግሏል። እንግሊዝ በፈጸመችው ተደጋጋሚ
ክህደት ሳይሳካ ቀረ። በዶጋሊ ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር መታ። በዚህን ጊዜ እነ አሉላ ደማቸውን እየጠረጉ ነበር
ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የተዋጉት። ዮሐንስ ወደ ሰሐጢ ለመዝመት ዝግጅት ላይ ሳሉ ነበር መኳንቶቻቸውን
ሰብስበው ለኢትዮጵያ መሞት እንደሚፈልጉ የገለጹት። ዮሐንስ ወዲህ ወዲያ አያውቁም። የሚያደርጉትን የሚነገሩ
ሰው ነበሩ። የደርቡሾች በጎንደር እና በጎጃም ህዝብ ላይ የፈጸሙትን ለመበቀል ዘምተው ደማቸውን አፈሰሱ።
እንደፈለጉት ለኢትዮጵያ ሞቱ ድንበር ጥበቃ ላይ ሳሉ። አሉላ በአድዋ ዘምተዋል። በደቡብ እና በምስራቅ
ኢትዮጵያ ደግሞ የጎበና እና የምኒልክ ትውልድ ባደረገው የመስፋፋት እና የያውን ግዛት የመጠበቅ ዘመቻዎች
በሱዳን፣ በኬኒያ እና በበርበራ በተተከለው እንግሊዝ፣ በጅቡቲ በተተከለው ፈረንሳይ፣ በአሰብ እና በመቅድሾ
እግሩን ባስገባው ጣሊያን የዛሬው ምስራቃዊ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራባዊ የኢትዮጵያ ግዛት እንዳይዝ
አድርገዋል። ዮሐንስ እንደሞቱ ደርቡሽ ከሱዳን እየተነሳ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የጥቃት ዘመቻዎች ጀምሮ
ነበር። ጎበና ለአንዴም ለሁሌም አቆመው። የአድዋም ድል ቢሆን እንደ ዶጋሊ ድል አገርን ከቅኝ ገዢ የመጠበቅ
ድል ነበር። እስቲ ስለሐረጌ ጨመር አድርገን እንመልከት።
ግብጾች ከሐረርጌ እንደወጡ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ሐረርጌ ላይ አይናቸው አረፈ። ሁለቱ የረጅም ጊዜ የጥቅም
ባላንጣዎች ስለነበሩ ብዙ ጊዜ ተዋግተዋል። በዚህን ጊዜ ግን ሁለታችንም ሐረርጌን አንይዝም የሚል ውል
በመፈራረም ውጊያን አስወገዱ። ይሁን እንጂ ኢንግሊዝ ሐረርጌን ከዜይላ ቀላቅሎ የመግዛት ስውር ምኞት
ነበራት። ፈረንሳይም ከእንግሊዝ ጋር የተፈራረመችውን ውል ክዳ ሐረርጌን ከቶጆራንና ጅቡቲ ለመቀላቀል
የምትችልበትን አመቺ ጊዜ እየጠበቀች ነበር። ጣሊያንም በበኩሏ እንግሊዝ እና ፈረንሳይን ሸውዳ ሐረርጌን ከአሰብ
ለመቀላቀል ትልቅ ምኞት ነበራት። ስለዚህ ሁሉም በየበኩላቸው አድብተው በአገር ጂኦግራፊ ምርምር ሽፋን
ሰዎቻቸውን ወደ ሐረርጌ እየላኩ መንገዱን፣ ወንዛ ወንዙን፣ መውጫ መግቢያውን፣ ተራራውን ሲያስመረምሩ
ነበር። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1886 ዓ.ም. ግድም ጣሊያናዊ አገር መርማሪዎች (ወይንም አንድ መርማሪ)
በሐረር ሲዘዋወሩ ሐርቲ የተባለ ቦታ ሲደርሱ የሐርረ አሚር አብዱላሂ ሰዎች ገደሉዋቸው። ጣሊያን “የዜጋዬን
መገደል መበቀል ህጋዊ መብቴ ነው አለች።” ሐረርጌን ለመያዝ በቂ ሽፋን አገኘች። ጣሊያን በወታደራዊ ወረራ
ሐረርጌን ለመያዝ ፕላንና ጊዜ በማማረጥ ላይ ባለችበት ጊዜ ነበር የጎበናና እና የምኒልክ ትውልድ ሐረርጌን
ከኢትዮጵያ የቀላቀለው። ምኒልክ ሲዘምት ጎበና በሸዋ ሆኖ አገር ያስተዳድራል። ጎበና ሲዘምት ምኒልክም በሸዋ
ሆኖ አገር ያስተዳድራል። በዚህን ጊዜ ምኒሊክ ወደ ሐረርጌ ዘመተ። ጣይቱ የዛሬዋን አዲስ አበባ ከተማ
የቆረቆረችው ምኒልክ ከሐረርጌ ሳይመለስ ነበር። ስለዚህ እንደ ኢጣሊያ ምኞት ቢሆን ኖሮ ምናልባት ዛሬ ሐረርጌ ከአሰብና ከምፅዋ ጋር ተቀላቅላ በኤርትራ ግዛት
ወስጥ ልትሆን ትችል ነበር። እንዲሁም እንግሊዝ እንደ አሰበችው ቀንቷት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሐረርጌ ከዜይላ ጋር
ተቀላቅላ የሰሜን ሶማሊያ አካል ትሆን ነበር። አሊያም የጅቡቲ አካል ትሆን ነበር ፈረንሳይ ያሰበቸው ቢሳካላት
ኖሮ። ሐረርጌ በምኒልክ መያዙን እንግሊዞችንም፣ ፈረንሳዮችንም፣ ጣሊያኖችም በጣም ቆጭቷቸዋል።
ኢትዮጵያን ከቅኝ ገዥዎች በመጠበቅ እና ለቀጣይ ትውልድ በማስረከብ ረገድ የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና
የምኒሊክ ስራዎች ተጋጋዦች ነበሩ። ግብጽ በጉንደት እና በጉራ መሸነፏ ያደረሰባት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ድቀት
ሐረርን ማስተዳደር እንዳትችል አደረጋት። የዶጋሊ ድል የአድዋ ቅድመ-ድል ነበር። ይህ ትውልድ በአላማ አንድ
ነበር። አገር ጠብቆ አውርሶ ሄዷል።

ስለዚህ በየዘመኑ የመጡት የቀድሞ አባቶቻችን በዘመናቸው የሚያውቁትን አሰራር ተጠቅመው አገር ገንብተው እና
ጠብቀው በማውረሳቸው ሊመሰገኑ እንጂ ሊኮነኑ አይገባም። ከስህተታቸው መማር በሚል ሽፋን የአልቤኒያው
ደብተራ መለስ ዜናዊ እና ተከታዮቹ ከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ መቆም አለበት። ከስህተት መማር ማለት ቀደም ብለው
የተፈጸሙ ስህተቶች እንዳይደገሙ ህዝብን ማስተማር ማለት እንጂ ህዝብ መካከል ጥላቻ መትከል ማለት
አይደለም። የቀድሞ አባቶቻችንን ስህተቶች ብቻ እያባዙ እና እያሳበጡ (እየፈጠሩም) አገር አውርሰውን የሄዱትን
ዛሬ በህይወት የሌሉ የቀድሞ አባቶች በቋሚነት መክሰስ ስህተት ነው። በህይወት ቢኖሩ ኖሮ የሚቀርቡባቸውን
ክሶች መከላከል ይችሉ ነበር። በዚህ አይነት ዛሬን እና ነገን የትናንት እስረኛ ማድረግም ከጥቅሙ ጉዳቱ
ይበልጣል። ያን የሚያደርጉ ሰዎች አንድም ስለ አለም ህዝብ እና ህብረተሰብ እድገት ታሪክ እውቀት የላቸውም
አሊያም ሆን ብለው ከፋፍሎ የመግዛት ፖለቲካ በማራመድ የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ጥረት ማድረግ ላይ
ናቸው። ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ከፋፍሎ መግዛት ፖሊሲያቸው ነው። ለጥቀን የአልቤኒያው ደብተራ መለስ ዜናዊ
እና ተከታዮቹ የመጡበትን ዘመን፣ የፈጸሙትን እና ለቀጣይ ትውልድ ያወረሱትን በአጭር በአጭሩ በመመልከት
አጭር ንፅፅር እናድርግ፥
(1) የመጡበት ዘመን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር ባለበት ዘመን ሲሆን ያደረጉት ግን ለስልጣናቸው
እድሜ ማራዘሚያ ሲሉ ኢትዮጵያን ቅኝ ገዥ በማድረግ አገር ማፍረስ እና ኢትዮጵያን ባህር በር አልባ
ማድረግ። የሱዳን፣ የጅቡቲ እና የሌሎች ጎረቤት አገሮች ወደቦች ጥገኛ (ፖለቲካዊ፣ ንግድ፣ ወታደራዊ፣
ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት) ማድረግ። የሚከፈለውን ክፍያ ሳናነሳ። የምዕራቡን የኢትዮጵያ ለም መሬት
ለደርቡሾች (ለሱዳን) መስጠት ነው። የዮሐንስ ደም የፈሰሰበት መሬት ሳይቀር ለደርቡሽ መስጠት።
ለመጪው ትውልድ የሚያወርሱትም ይህንን ነው። አሳፋሪ ውርስ ነው።
(2) የመጡበት ዘመን ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ መሸጋገር በምትሻበት ጊዜ ነው። ያደረጉት ግን የከፋፍለህ
ግዛ ፖለቲካ ማሰራጨት። ታሪክን መነሻው ያደረገ ከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ። የቀድሞ አባቶችን ስራ
መሰረት ያደረገ ከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ። ጎሳን መስፈንጠሪያው ያደረገ ከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ። ዛሬም
ዴሞክራሲ የለም። ለመጪው ትውልድ የሚያወርሱትም ይህንን ነው። አሳፋሪ ውርስ።
(3) የመጡበት ዘመን ቀድም ብለው በታሪካችን የነበሩ ሚዛናዊ ያልነበሩ ግንኙነቶች በአግባብ እየተጠኑ
ህዝብን ባሳተፈ መልኩ መፍትሄ መስጠት በሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። ያደረጉት ግን ሚዛናዊ ያልነበሩ ግንኙነቶችን እያነሱ ለራሳቸው ስልጣን ላይ መቆየት በሚጠቅም መንገድ ማወሳሰብ ነው። ለቀጣይ
ትውልድ የሚያወርሱትም ይህንኑ ነው።

ስለዚህ የአልቤኒያው ደብተራ መለስ ዜናዊ እና ተከታዮቹ ከአሉላ፣ ከዮሐንስ፣ ከጎበና እና ከምኒሊክ ትውልድ ጋር
ፍጹም ሊነጻጸሩ አይችሉም። ቢነጻጸሩም የአልቤኒያው ደብተራ መለስ ዜናዊ እና ተከታዮቹ በታሪካችን እጅግ
ዝቅተኞች ቦታ ይይዛሉ። የአሉላ፣ የዮሐንስ፣ የጎበና እና የምኒሊክ ትውልድ ያን የቅኝ አገዛዝ ዘመን በመሃይም
አዕምሮዋቸው ሁለት እና ሶስት የኮሌጅ ድግሪ የያዙ ቅኝ ገዢዎችን ተቋቁሞ ከሞላ ጎደል አገር ጠብቆ ለቀጣይ
ትውልድ በማውረሱ ዛሬ በቅኝ ገዢዎች ያልተገዛች አገር አለን። ስለዚህ እንደእኔ ከሆነ ትውልዱን የሚወክል አራቱ
ሰዎች በተርታ ያሉበት ሐውልት መትከል አለብን። ባለውለታዎች መሆናችንን የሚገልጽ ሐውልት።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on April 3, 2014
  • By:
  • Last Modified: April 3, 2014 @ 2:15 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar