www.maledatimes.com ‪‎አውቀን_እንታረም‬ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

‪‎አውቀን_እንታረም‬

By   /   April 4, 2014  /   Comments Off on ‪‎አውቀን_እንታረም‬

    Print       Email
0 0
Read Time:16 Minute, 19 Second

“ትንቢት ከነገር ይቀድማል” ይላሉ፡- አበው፡፡ እውነት ነው፡፡ አባባሉ እውነትነት ያለው መሆኑ በተለያየ ዘመን፣ ሁኔታ እና አጋጣሚ ታይቷልና፡፡

አንደንድ ሰዎች በዘመናቸው ከደረሱበትና ከደረሰባቸው ሁኔታ በመነሳት በግል ሕይወታቸው፣ በማህበረሰባቸው፣ ብሎም በሀገራቸው …ወዘተ ላይ ሊመጣ ይችላል የሚሉትን መልካምም ሆነ ክፉ ነገር አስቀድመው “ይተነብያሉ”፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች በነገሮች ላይ ካለቸው ዕይታ ተነስተው በቃልም ሆነ በፅሁፍ ሥጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ያሰጋቸው ነገር እንዳይከሰት በቃልም ሆነ በፅሁፍ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት የትንቢት ተናጋሪነት ችሮታ ኖሮአቸው ወይም ትንቢት ተናጋሪ ሆነው አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በቃልም የተናገሩት ሆነ በፅሁፍ ያስተላለፉት መልዕክት የኋላ ኋላ በራሳቸውም የግል ህይወት ጭምር ይከሰትና እውነትነቱ ይገለጣል፡፡ የተናገሩት ነገር በህይወት እያሉም ሆነ ከሞቱ በኋላ ዕውነትነቱ ሊገለጥ ይችል ይሆናል፡- እንዲያ ሲሆን ይመስለኛል “ለካ ትንቢት ነበር የተናገሩት” የሚባለው፤ ነውም፡፡

ይህንን ሁሉ የዘበዘብኩት አንዲት “ኮስማና የዱሮ” መፅሐፍ ውስጥ ያገኘሁትን መራር ቁምነገር ላካፍላችሁ ፈልጌ ነው፡፡ መፅሐፏ ከአንድ እጅ መዳፍ ትንሽ በለጥ የምትል ናት፡፡ በ59 ገፅ ብቻ ቅልብጭ ብላ የተሸከፈች ናት፡፡ በ1955 ዓ.ም ነው ለሕትመት የበቃችው፡፡ “አውቀን እንታረም” ትሰኛለች፡፡ ደራሲው በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በከፍተኛ የመንግስት ሥልጣን ላይ ያገለገሉት ጄኔራል አበበ ናቸው፡፡

አንዳንድ የታሪክ ምሁራን የጄኔራል አቢይ አበበ “አውቀን እንታረም የአጼ ኃይለስላሴ ስርዓት እንዲታረም የጠቆመ፣ የማይታረም ከሆነ የመጨረሻ ውድቀቱ የማያምርና አሰቃቂ እንደሚሆን አስቀድማ ያመላከተ” መፅሐፍ ነው ሲሉ ይመሰክሩለታል፡፡ በሌላ ወጊ በአጼው ታሪክ ውስጥ ፋና ወጊ ለውጥ እንዲመጣ የወተወተ መልዕክት ነበር ማለት ነው፡- ጄ/ል አቢይ አበበ “አውቀን እንታረም” በተሰኘችው “ኮስማና” መፅሐፋቸው ያስተላለፉት፡፡ ነገር ግን ጄ/ል አቢይ አበበ የሚሰማቸው አልተገኘም፡፡ “የፈሩት ይደርሳል….” እንዲሉ ሆነ፡፡

ጄ/ል አቢይ አበበ፣ በዚያ ዘመን “አውቀን እንታረም” በተሰኘው መፅሐፋቸው በ59 ገፆች ያስተላለፉት መልዕክት እጅግ ትሁት፣ ቀናነት እና ብርቱ ሀገራዊ ፍቅር የታጨቀበት ነው፡፡ ሀገራዊ ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ የአስተዳደር ዘይቤ፣ ኢኮኖሚ፣ ወታደራዊ አቅም ግንባታ … ወዘተ ያላነሱት ጉዳይ የለም፡፡

ይህ መፅሐፋቸው ደራሲው “ፈላስፋ”ም ናቸው የሚያሰኝ ነው፡፡ ፍልስፍናቸው ስለ ሰው፣ ሰውነት የሚያጠይቅ ነው፡፡ ፍልስፍናቸው ከራሳቸው ጋር በሚያደርጉት ሙግት የተሰናሰነ ነው፡፡ ለዚህ ፅሁፍ ማጣቀሻ አድርጌ የማደርገው ደራሲው (ጄ/ል አቢይ አበበ) ለመልዕክታቸው መንደርደሪያ ይሁናቸው ዘንድ “መነሻ” በሚል ንዑስ ርዕስ የሰጡትንና ከገፅ 2 – 10 ካሰፈሩት ሐተታ ጥቂቱን ነው፡፡ እነሆ፡-

“….. ከብዙ ጊዜያት ጀምሮ ሰውንም ታዝቤአለሁ፡፡ አጥርቼም ተመልክቼም ተመራምሬአለሁ፡፡ ወደየትም እንደሚያመራ የትእንደሚደርስም ተመልክቼአለሁ፡፡ የየራሱን ጉዞና ማረፊያ ሰው ሁሉ ያውቀዋል፡፡ ግን አጥርቶ አይረዳውምና ሰዉ መሆኑን አክብሮ ለጊዜው ይኖራል፡፡

“ሰው ሆኖ መፈጠር ሰውነትን ለማክበርና ምድርን ለመሙላት ብቻ ሳይሆን ትዕዛዛተን ለማከበርና ህግጋትን ለመፈፀም፣ እንደዚሁም እውነትንና ትክክለኛ መንገድን ተከትሎ ከልብ ለመፈቃቀርም በሆነ ነበር፡፡ (ገፅ 2)

ጄ/ሉ ይህቺ ዓለም መራር እና ጣፋጭ መሆኗን በሚከተለው መልኩ በምሳሌ ያትታሉ፡-

“ትናትና ደስ ብሎህ ነበር፤ ሃሳብህም ፍላጎትህም ምኞትህም ሆኖልሃል፡፡ ከብዙ ዘመድ ወዳጆችህ ጋር ተገናኝተህ፣ ስለደስታህም ስለሆነልህም ነገር በመፍለቅለቅ ውለህ አምሽተሀል፡፡ ፍንጠዛህም ከልክ አልፎ የምትጨብጠውን አሳጥቶህ የበለጠ ከምታፈቅረው ወይም ከማንም አብልጠህ ከምትወደው ገንዘብህ ላይ ቆንጥረህ ለደስታህ መታሰቢያ ሰውተህ፣ ምግብና መጠጥ አዘጋጅተህ ጓደኞችህን ስታማታ ውለሀል፡፡ ምክንያቱ ምን ይሆን? ንግድህ ሆኖልህ ብዙ ገንዘብ አግኝተሃል፤ ሥልጣን ላይ ወጥተሀል፤ ልጅህን ድረሃል፤ ወይም ሚስት አግብተሃል ልጅ ወልደሀል እንበል፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ የምትጎነጨው ከአንደኛው ወገን ያለውን ጣፋጭ ነው፡፡

“ዛሬ ደግሞ እንደትናንትናው አይደለህም፤ ሃዘን ተከናንበህ ትታያለህ፤ ራስህንም ታማርራለህ፤ ሰዉነትህን ንቀህ ያቀበጠብጠሃል፤ የምትናገረውንም አታውቅም፤ ጭንቅላትህንም በሁለት እጆችህ ጨብጠህ አቀርቅረሃል፡፡ የትናንትናው ቡረቃህ ትዝም አይልህ፡፡ በእንባም ተጨማልቀሀል፡፡ ለገላጋይም አልመች ብለህ የመጨነቅህ ብዛት ያስጓራሀል፡፡ ምን ሆነህ ይሆን? ከስልጣን ወርደሀል፤ ሀብትህ ተበዝብዟል፤ ዘመድህንም ተረድተሃል፤ አለበለዚያም ሌላው የአንተ ቢጤ ሰው እንደያውቅብህ የማትፈልገው ነገር ደርሶብሃል ልበል፡፡ አሁን ደግሞ ተገድደህ የምትጎነጨው ከሌላኛው ወገን በብዛት ከሚፈልቀው የምሬት ጣዕም ነው፡፡ (ገፅ 4- 5)

ጄ/ል አቢይ አበበ በመፅሐፋቸው መንደርደሪያ የሕይወትን (የዓለምን) ምሬት እና ጥፍጥና እንዲህና እንደያ እየተነተኑ ስለ ሃገር እና ስለ ትውልድ ያቀነቅናሉ፡፡ የዚህ ፅሁፍም ዋነኛ አስኳል ይህ ነው፡፡ ከላይ “ትንቢት” በሚል ቃል የገለፅኩትን ጉዳይ ይዟልና፡፡ እነሆ፡-

“የተለመደውን ሐተታ በመያዝ ድካማችን ለሀገራችንና ለመጪው ትውልድ ነው የሚል ሞልቶ ይሆናል፡፡ ይህንን መናገር የሚገባው በአንድ ትውልድ ዘመን አብሮት ላለው ጓደኛው የሚያስብ አዕምሮ ያለው ሰው መሆን አለበት፡፡ እንግዲያውስ እንደሚታየው ከሆነ ድካማችን ለየግ ልፍላጎታችን ሆኖ፣ የድካማችንም ፍሬ በልቶ መሞት ብቻ ነው፡፡

“ሞታተንም ቅጣታችን ነው፡፡ እሰከዚያው ድረስ ግን ግንብ በሌለው ዘበኛ በማይጠብቀው ክፍት ወህኒ ቤት ውስጥ ሆነን እንደልባችን እየተቀናጣን፣ ለምኞታችን እየተገዛን ምንም የሚደርስብን አይመስለንም፡፡ ጊዜው በደረሰ ጊዜ ግን አየተነው የማናውቀው የብረት አጥር በዙሪያችን እንደነበረ ይከሰትልናል፡፡ ትልቁም የብረት በር እፊታችን ተደቅኖ ይታያል፡፡ ያን ጊዜ መንጥቆ የሚያስወጣንም ዘበኛ ይገለጣል፡፡ በአጠገባችንም ይንጎራደዳል፡፡ እንደከብት ስንታገድ የኖርንባት እኛ ለማዳዎቹ አውሬዎች የሰባንባት መሬት ተራዋን ልትበላንና ሰብታም ሌላውን ለመመገብ አፏን ከፍታ ትቀበለናለች፤ ከዚህም የሚያድነን የለም፡፡ ተመልሰን ልንመጣም አንችልምና የእኛ ተራ በዚሁ ይወሰናል፡፡” (ገፅ 7)

ጄ/ል አቢይ አበበ የመፅሐፋቸውን መግቢያ ሃተታ ስንጠቀልለው “ጥቂትም ቢሆን ደግ ነገር እንስራ፤ አውቀን እንታረም” ብለው ነው የሚደመድሙት፡፡

ይህ መፅሐፋቸው ለአጼ ኃይለሥላሴ የማንቂያ ደውል ነበር፡፡ ሆኖም ደወሉን አልሰሙትም፡፡ ሊሰሙትም አልፈቀዱም፡፡ በመጨረሻ ጄ/ል አቢይ አበበ “የተነበዩት” ጊዜ ደረሰ፡፡ ያ ጊዜ 1966 ዓም ነበር፡፡

በታሪክ ውስጥ 60ዎቹ ሚኒስትሮች ተበለው የሚታወቁት የአጼው ሹመኞች ወደእስርቤት ተወሰዱ፡፡ ከዚያም በጅምላ ተረሸኑ፡፡ ከእነዚህ ከተረሸኑት 60 ሚኒስትሮች ውስጥ አንዱ አስቀድመው “አውቀን እንታረም” ሲሉ የተናገሩት ጄ/ል አቢይ አበበም ናቸው፡፡

‪#‎ጊዜው_በደረሰ_ጊዜ_ግን_አይተነው_የማናውቀው_የብረት_አጥር_በዙሪያችን_እንደነበረ_ይከሰትልናል‬፡፡ ትልቁም የብረት በር እፊታችን ተደቅኖ ይታያል፡፡ ያን ጊዜ መንጥቆ የሚያስወጣንም ዘበኛ ይገለጣል፡፡ በአጠገባችንም ይንጎራደዳል፡፡ እንደከብት ስንታገድ የኖርንባት እኛ ለማዳዎቹ አውሬዎች የሰባንባት መሬት ተራዋን ልትበላንና ሰብታም ሌላውን ለመመገብ አፏን ከፍታ ትቀበለናለች፤‪#‎ከዚህም_የሚያድነን_የለም_ተመልሰን_ልንመጣም_አንችልምና_የእኛ_ተራ_በዚሁ_‬ ይወሰናል፡፡”

ትንቢት ከነገር ይቀድማል ማለት ይኼ አይደል!?

እነሆ ታሪክ ይህንን ይነግረናል፡፡ እንደኔ እንደኔ “አውቀን እንታረም” ያለፈ ታሪክ የሚባል ብቻ አይደለም፡- የአሁንም እንጂ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on April 4, 2014
  • By:
  • Last Modified: April 4, 2014 @ 11:14 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar