www.maledatimes.com በስምምነት ላይ የተመሰረት ባህላዊ ውህደት Vs ህገ-መንግስታዊ ቀናዒነት - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በስምምነት ላይ የተመሰረት ባህላዊ ውህደት Vs ህገ-መንግስታዊ ቀናዒነት

By   /   April 6, 2014  /   Comments Off on በስምምነት ላይ የተመሰረት ባህላዊ ውህደት Vs ህገ-መንግስታዊ ቀናዒነት

    Print       Email
0 0
Read Time:56 Minute, 55 Second

         መግቢያ

በዚህ ጽሁፍ ሥር ለውይይት ይሆን ዘንድ የምናነሳው ኣሳብ   constitutional patriotism   ወይም ህገ መንግስታዊ ቀናዒነት ወይም ኣርበኝነት የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ ባለፈው በተከታታይ ካቀረብኳት የ  Conventional Cultural Unity  ወይም በስምምነት ላይ የተመሰረት ባህላዊ ውህደት ካልኩት ኣሳብ ጋር እንዴት እንደሚለያይና  በኢትዮጵያ ሁኔታ ከሁለቱ ኣሳቦች የትኛው ተገቢና ችግር ፈቺ ሊሆን እንደሚችል  ኣሳብ ለማፍራት ነው።

በቅድሚያ ኣንድን ፖለቲካዊ የሆነ ፍልስፍና ወይም ቲየሪ በኣንድ ሃገር ፖለቲካ ውስጥ መሰረታዊ የመጫወቻ ወለል ኣድርገን ከማንጠፋችን በፊት ቲየሪው ወይም ኣሳቡ በጣም መጠናትና ግልጽ መሆን ኣለበት። ግልጽነት ሳይኖረውና ሳንረዳው በስሜት ከተከተልነው ሁዋላ ላይ ጉምን እንደ መጨበጥ ይሆንና እናርፋለን። ለዚህ ምሳሌ ኣምጣ ብትሉኝ የኢትዮጵያን የኣሁን ዘመን ፖለቲካ መጥቀስ እችላለሁ። ባለፈው ኣርባና ኣምሳ ኣመት ገደማ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ነጻ እናወጣለን በሚል ብዙ መፈክር ተሰምቱዋል። መዝሙሮችም ተዘምረዋል ግጥሞችም ተገጥመዋል። ታዲያ ቆይቶ ኣጥብቆ ጠያቂ ትውልድ ሲመጣ ብሄር ብሄረሰብ ደግሞ ህዝቦች የሚባሉት የት የት ነው ያሉት? የሚል ጥያቄ ሲያመጣ ሞተንለታል ከሚሉት ሰዎች ደጅ መልሱ ጠፋ። እነዚህ የዋሆች የሞቱላቸው የፖለቲካው እግሮች (radicals) ባለም ላይ የሉም እስከ መባል ደርሶ እንዲሁ በዚህ ኣይነት ግልጽ ባልሆነ የፖለቲካ ኣስተሳሰብ ውስጥ ገብተዋል። ከዚያ ደግሞ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር ኣመጡና ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ማለት ምን ማለት ነው? እስቲ በይኑት(define ኣድርጉት) ቢባል የሚበይነው ጠፋ። ካድሬዎቹም መሪዎቹም ግልጽ ባልሆነ የፖለቲካ ርእዮት ውስጥ ይገኛሉ። እንዲህ ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮች የኣንድን ሃገር የፖለቲካ መሰረት ሲጥሉ ኣደጋው ሰፊ በመሆኑ መጀመሪያ ኣብጠርጥሮ ማወቅ ተገቢ ነው። ለዚህ ነው  የconstitutional patriotismን  ቲየሪ በሚገባ ማየት ኣለብን ያልኩት።  እንግዲህ ዝቅ ሲል  constitutional patriotismን   እና   Conventional Cultural Unityን   እያወዳደርን ኣይተን ከኢትዮጵያ ተፈጥሮና ተጨባጭ ችግሮች ኣንጻር የትኛው ተመራጭ ሊሆን እንደሚችል ለማየት እንሞክር። መልካም ንባብ።

 

 

 

1.  የconstitutional patriotism  ንድፈ ሃሳብ ታሪካዊ ኣመጣጥና የፍልስፍና መሰረቶቹ

ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በምስራቁ ክፍል ያለውን ግዛትዋን በቀድሞዋ ሶቪየት ዩኒየን በመነጠቋና ቀጥሎም ቀዝቃዛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በመጣው የዚህ ዓለም ኣተያይ ለጽንፍ ልዩነቶች ዳረጓት። ይህንኑ ቀዝቃዛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ ምእራቡ ክፍል የምእራቡን ዓለም ኣመለካከት ሲያስተናግድ ምስራቁ ክፍል ኣጥባቂ የኮሚኒስት ደጋፊ በመሆን በወቅቱ  ተፎካካሪ ለነበሩት ሶቪየት ዩኒየንና ምእራባውያን  ሁለቱ ጀርመኖች ለሁለቱ ጎራዎችደጋፊ በመሆናቸው ተለያይተው ለየብቻ ጎጆ ወጥተው መኖር ጀመሩ።

ሁለቱ ጀርመኖች ቋንቋቸው ኣንድ ይሁን እንጂ ይከተሉት የነበረው የዚህ ዓለም ኣተያይ ሁለት የተለያዩ ሰዎች እስኪያደርጋቸው ድረስ ልዩነታቸው ሰፋ። ምስራቁ ክፍል የኮሚኒዝምን የህይወት ፍሬዎች እያፈራ ቆየ። በኣንጻሩ ምእራቡ የካፒታሊስቱን ፍሬ እያፈራ ቆየ። ሁለቱ ወንድማማቾች ይከተሉት የነበረው የዚህ ዓለም የፖለቲካ ትምህርት በህይወታቸው የተለያየ ፍሬ እንዲያፈሩ ስላደረጋቸው የማንነት ልዩነቶችን ኣመጡ።

የማርቲን ሉተር ሃይማኖታዊ ሰው መነሻ የነበረችው ምስራቅ ጀርመን ሃይማኖትን ኣራክሳ የነበረ ሲሆን ሌላው ቀሮቶ ኣሁን ከተዋሃዱ በሁዋላ በ2012 OSW (Center for Eastern studies) ባደረገው ጥናት ካላት ህዝብ ከሃያ ስድስት በመቶ በታች የሚሆነው ህዝቡዋ ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄድባት ኣገር ሆና ስትገኝ በኣንጻሩ ምእራብ ጀርመናዊያን በግልባጩ ሰባ ሶስት በመቶ የሚሆነው ህዝቡዋ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል።ይህ የሚያሳየው በሃይማኖት ዝንባሌያቸው ምን ያህል ተራርቀው እንደነበር ነው። በኣጠቃላይ በዴሞክራሲ ኣረዳድ፣ በማሀራዊ ሃብት ክፍፍል፣ ወዘተ የተራራቀ መረዳትን ከመያዛቸው የተነሳ ያፈሩት ስብእና ነው የተለያየ ማንነትን ያመጣው።

እንግዲህ ሁዋላ ላይ በኣለም ላይ የኮሚኒዝም ስርዓት መንኮታኮት ሲጀምር ምስራቅ ጀርመንም በእጁዋ ያለውን የኮሚኒዝም ፍሬ ለማየት የጽሞና ጊዜ ኣገኘች። ለምስራቅ ጀርመን የለውጥ እንቅስቃሴ ያደረገው የውስጡ የህዝቡ በኮሚኒዝም ፍሬ ያለመርካት ዋናው ጉዳይ ሲሆን የሶቪየት ዩኒየኑ መሪ ሚካዔል ጎርቫቾቭ ሁዋላ ላይ ያመጡት የክፍትነት(openness) ኣሳብና ሶቪየትን እንደገና የማዋቀር ዓላማ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጦች እንደ ውጪያዊ ተጽእኖ የሚታይ ነው።

የምስራቅ ጀርመን ህዝብ በወቅቱ በነበረው ኣስተዳደር ኣዝኖ ውስጥ ውስጡን ለለውጥ ራሱን ማዘጋጀት ጀመረ። ሁዋላ ላይ በፕሮቴስታንቶች ቤተክርስቲያን ውስጥ ኣገራችን ውስጥ ምን እየሆነ ነው? የሚል ውይይት ከፍተው መወያየት ጀመሩ። የጽሞና ጊዜ ኣምጥተው ያለፉበትን የህይወት ልምድ መገምገም ጀመሩ። በርግጥ ባፈሩት ፍሬ ኣልተደሰቱም ነበርና በቤተክርስቲያን ውስጥ የጀመሩት ተቃውሞ እየሰፋ ሄዶ እልፎች ተቀላቀሉት። በየሳምንቱ ሰኞ ሰኞ ኣንድ ኣመት የዘለቀ ተቃውሞ ተሰማ። “እኛ ነን ህዝብ ማለት” (We are the people) እያሉ መዘመር ሲጀምሩ በጣም መሰረታዊ የዴሞክራሲ ወይም የህዝቦች ልእልና ጥያቄ ያነሱ መሆኑ ታወቀ። የኣንድ ፓርቲ የበላይነትን በመንቀፍ የህዝቦችን የበላይነት ጥያቄ ይዘው ታገሉ። ይህ የሚያሳየው ምስራቅ ጀርመናዊያን ዴሞክራሲን መጠማታቸውን ብቻ ሳይሆን የማንነት ለውጥ ለማምጣት መዘጋጀታቸውንም ነበር።

የለውጡ ግፊት እየበረታ መጣና 1990 የሁለቱ ጀርመኖች ውህደት ኣሳብ መጣ። የህዝቡ ንቅናቄ ያስደነገጣቸው የምስራቅ ጀርመን መሪዎች ማሻሻያ ለማድረግ ደፍ ደፍ ሲሉ ውህደቱ ቀደመና ያሻሻሉትን ህገ መንግስት ወዲያ ጥለው ሁለቱ ጀርመኖች ለውህደት በቁ። ሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች ያለያያቸውን የበርሊን ግንብ ኣፍርሰው ይገናኙ እንጂ ባለፈው ግማሽ ምእተ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ ያፈሩት የህይወት ፍሬ የተለያዩ ኣድርጉዋቸው እንደነበረ ይበልጥ ሳይገነዘቡ ኣልቀሩም። ለማናቸውም ውህደቱ ተሳካና የተባበረችውን ጀርመን ወጥ በሆነ የፖለቲካ ስርዓት ለመምራት ፖለቲከኞቹ ሲነሱ የብሄራዊ ማንነት ጥያቄ ተነሳ። ምንም እንኳን ኣንድ ቋንቋ ብንናገርም የተለያየን ሆነናልና ብሄራዊ ማንነታችን እንዴት ሊሆን ነው?ሁለቱም ጀርመኖች የባህላዊው ብሄራዊ ማንነት(Traditional national identity)  ኣልተመቻቸውምና እንዴት ነው ብሄራዊ ማንነታችንን የምንገንባው? የሚሉት ጥያቄዎች በወቅቱ ለነበሩ የጀርመን ፖለቲከኞች መከራከሪያና ዋና የመወያያ ጉዳይ ሆኖ ነበር። በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ሃበርማስ የተባለ ጀርመናዊ የሶሲዮሎጂ ፈላስፋ የህገ መንግስታዊ ቀናዒነትን ንድፈ ሃሳብ ይዞ ብቅ ያለው።

እንደ ሃበርማስ እነዚህ የተለያየ ማንነትን ያዳበሩ ህዝቦች ሊያገናኝ የሚችል፣ በቅድመ ማንነታቸው ወይም (traditional national identity ) ላይ ምቾት ያልተሰማቸው ህዝቦች ዘንድ ሌላ ድህረ ብሄራዊ ማንነት(post national identity) ሊመጣ የሚችለው ጀርመኖች ለህገ መንግስታቸው ቀናዒ ሲሆኑ ነው። ሑላችን ለህገ መንግስቱ ተገዢ ስንሆንና ለሊብራል ዴሞክራሲ ህገመንግስት እሴቶችና ኖርሞች ታማኝ ስንሆን የሰው መብት ስናከብር ስናስከብር በተቋማት ላይ መታመን ሲኖረን ያ የብሄራዊ ማንነታችን መገለጫ ይሆናል ማለት ነው የሚል ቁም ነገር ኣመጣ።። በመሆኑም  ህገ መንግስታዊ ቀናዒነት (constitutionl patriotism) የብሄራዊ ማንነታችንን ጥያቄ የሚፈታው ነው ብሎ ፖለቲከኞችን መጫን ጀመረ።

በወቅቱ የማንነት ጉዳይ ትልቅ ጥያቄ ሆኖባቸው ለነበሩት የጀርመን ፖለቲከኞችና በባህላዊው ማንነት ምቾት ያልተሰማቸው ጀርመኖች ኣዲስ ሊፈጥሩት ላሰቡት ማንነት ይህ የሃበርማስ ኣሳብ በርግጥም ልብ ኣሳራፊ ሆኖ በዚያን ጊዜ ተገኘ።

ለሁለቱ ጀርመኖች የመገናኛ መስመር ህገ መንግስቱ ሆኖ ሊብራል በሆነ ዴሞክራሲ ውስጥ ብሄራዊ ማንነታቸውን እንዲጥሉ ሃበርማስ መምከሩ በርግጥ ጥበብ የተሞላና ወቅታዊም ነበር ማለት ይቻላል።

ይህ የሃበርማስ ኣሳብ የጀርመንን ፖለቲከኞች ስሜት ያረጋ በመሆኑ እንደዚሁ የተለያየ ማንነትን ይዘው ብሄራዊ ማንነት ለመገንባት የተነሱ ኣገሮችም ለውስጥ ችግሮቻቸው መፍትሄ  ይሰጣል ብለው ሞክረውታል። ቦስኒያ ለዚህ ተጠቃሽ ናት::  ቦስኒያ ውስጥ በተለይ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ ይህ የሃበርማስ ኣሳብ በጣም የተቀነቀነ ነበር። የኣውሮፓ ህብረትም ይህንን የሃበርማስን ኣሳብ እንደተጠቀመበት ይታያል።

ሃበርማስ ለህገ መንግስቱ ቀናተኛነት ሲል ለፍትህ ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለሶሻል ዌልፌር መቆም እንደማለት ሲሆን እነዚህ ማንነቶች በርግጥ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ናቸው። ኣንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት የሃበርማስ ኣሳብ ኣንድን የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተነሳ ስለሆነ ኣገራዊ የሆነ ሰፋ ያለ ሶሊዳሪቲን ለማምጣት በጣም ይቀጥናል ይላሉ። በርግጥም ኣገር የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ፣ ፖለቲካዊ ይዘት ብቻ እንዳለው ኣድርጎ ማየቱና ብሄራዊ ማንነትን ከስቴት ጋር ብቻ ማጣበቁ ቀጣይነት ያለው ማህበረሰብ(sustainable community) ለመመስረት ኣይሳሳም ወይ የሚል ትችትም ሊቀርብበት ችሉዋል ። ያም ሆኖ ግን በወቅቱ የጀርመኖች ልዩነት ፖለቲካ የወለደው በመሆኑ የሃበርማስም ኣቀራረብ ፖለቲካዊ እንዲሆን ተጽእኖ ኣድርጎበት ነውና ኣሳቡ የሞራልና የሲቪሊቲ ጉዳዮችን ኣንስቶ የሚገጥሙትን የኮሙኒከሽን ችግሮች በትእግስት በማየት ተቻችሎ ለመኖር ጥሩ ምክር ነበር ማለት ይቻላል።

ከሁሉ በላይ ግን ሁለቱ ጀርመኖች ወደ ውህደት እየመጡ የነበሩት የማንነት መራራ  ጥያቄ ይዘው ኣልነበረም። ለሁለቱ ህዝቦች ውህደት ትልቅ ኣስተዋጾ ያደረገው የምስራቅ ጀርመን ህዝብ የማንነት ለውጥ ለማደርግ ፍላጎትና ጥማት በማሳየቱ ወይም እጅ በመስጠቱ ነው። ምእራብ ጀርመን ከነበራት ፖለቲካዊ ማንነት ንቅንቅ ሳትል ምስራቅ ናት ለውጥ እያመጣች ወደ ምእራቡ ኣሰተሳሰብ መቀላቀል ያማራት። በመሆኑም የሃበርማስ ኣሳብ የፖለቲከኞቹን ጥያቄ ወዲያ  ያርግብ እንጂ ውህደቱን ያሳለጠው ግን  ኣብዛኛው የምስራቁ ህዝብ የማንነት ለውጥ በማምጣቱ ነው።  ለዚህ ዋቢ የሚሆነን ጉዳይ ሁለቱ ሃገራት ወደ ውህደት ከመጡ በሁዋላ የጋራ ህገ መንግስት ሲያረቁ የምስራቁን ሀገ መንግስት ወዲያ ጥለው ከጥቂት ማሻሻያዎች ውጭ ምእራብ ጀርመን ትጠቀምበት የነበረውን ህገ መንግስት ነው እንዲቀጥል ያደረጉት። ይህ ማለት እነዚህ ህዝቦች ለመዋሃድ መሃከለኛ የሆነ የሁለቱን  ቅይጥ ሀገ መንግስት ኣላስፈለጋቸውም ነበር ማለት ነው።

ከፍ ሲል እንዳልኩት ምስራቅ ጀርመን የማንነት ለውጥ ለማድረግ በመወሰኑዋ ስትጠላው የነበረውን ያንኑ የምእራቡን ኣመለካከት እንደገና የህይወቱዋ መሪ ለማድረግ መወሰኑዋ ነው የውህደቱ መሰረት።። መሬት ላይ ያለው ሃቅ ይህ ከሆነ የሃበርማስ ሃሳብ በውስጠ ተዋዋቂ ምስራቅ ጀርመን የጀመረችውን ወደ ምእራቡ ኣስተሳሰብ የመዋሃድ (assimilation) እንቅስቃሴ ገፍታበት ሁለቱም ህዝቦች ቀድሞ ምእራብ ጀርመን እያሳደገችው የመጣችውን ፖለቲካዊ ማንነት የጋራ ድህረ ብሄራዊ ማንነት መገለጫ እንዲያደርጉት የሚገፋፋ ነው ማለት ይቻላል።

የሆነ ሆኖ ግን የሃበርማስ ኣሳብ ከፍ ሲል እንዳልኩት በፖለቲካው ለሂቅ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ከስሜት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ጉዳዮችን በማብረድ ለጀርመኖች ውህደት ትልቅ ኣፋጣኝ ሚና ተጫውቱዋል።

   2.   የሃበርማስ ኣሳብ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ማንነት ጥያቄ መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል ወይ?

መልካም። በመሰረቱ ሃበርማስ ያመጣው ይህ ኣሳብ በኣንዳንዶች ዘንድ ኣዲስ ተደርጎ ኣይወሰድም።ቀድሞውንም ቢሆን  ኣገሮች ህገ መንግስት ኣውጥተው ሲተዳደሩ እንደ ሃበርማስ  Constitutional patriootism  ብለው ኣይሰይሙት እንጂ ዞሮ ዞሮ በውስጠ ተዋዋቂ ያው ለህገ መንግስቱ ተገዢ በመሆን ህዝቦች በኣንድ የፖለቲካ ጥላ ስር ታምነው እንዲኖሩ ነው የሚፈልጉት። በመሆኑም ኣሳቡ በመጀመሪያ ደረጃ ኣዲስ ኣሳብ ሆኖም የቀረበ ኣይደለም። እንዴውም ሊብራል ዴሞክራሲ የሚባለው ኣመለካከት ይውጠዋል። ይህ ማለት የ Constitutional patriootism  ተግባራዊ ገጽታው ያው ዞሮ ዞሮ ሊብራል ዴሞክራሲ ነው የሚሆነውና ምንም ኣዲስ ነገር ኣልመጣም እየተባለ ይተቻል። ቲየርው ይዞ የመጣው ጉዳይ የሞራል፣ የምክር፣ ስሜትን የመቀስቀስ ኣይነት ነው። ሌላው የሃበርማስን ኣሳብ ስናይ በርግጥ ህገ መንግስታዊ ቀናዓኢነት የሚመጣው በህገ መንግስቱ ላይ በመታመን፣ ተቋማትን በማፍቀር ከሆነ ማፍቀርና መደገፍ ከሂደትነታቸው በላይ ውጤትነታቸው ነው ጎልት የሚታየው።  ዜጎች ለሀገ መንግስቱ ኣርበኞች እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ? ኣርበኛ ለመሆን ውጤት ሊጠብቁ ኣይችሉም ወይ? የፖለቲካ ተቋማቱን ፍሬ እያዩ ነው እያደር የሚያፈቅሩዋቸው።ሌላው ደግሞ የሃበርማስ ኣሳብ ጠበብ ያለ የፖለቲካ ማህበረሰብ በመፍጠር ብሄራዊ ማንነትን የመገንባት ኣሳብ የያዘ በመሆኑ ቁርጠኛ የፖለቲካ መሪዎች ከጠፉና ተቋማት መርከስ ከጀመሩ ዜጎች ኣርበኛ ስለማይሆኑ ኣገር ሊፈርስ፣ ብሄራዊ ማንነት ሊደመሰስ ነው ማለት ነው። በርግጥ የሃበርማስ ቲየሪ ቀጭን(thin) ቲየሪ ነው የሚሉትም ለዚህ ነው።

ወደ ዋናው ኣሳባችን ስንመጣ የሃበርማስን  ኣስተያየትወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የማንነት ጥያቄ መረዳት ያስፈልጋል። ጀርመኖች ያነሱት የማንነት ጥያቄ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ሲሆን የኢትዮጵያው ግን የተለየ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የማንነት ጉዳይ የመጣው የባህላዊ ቡድንን ማንነት ለብሶ የመጣ ሲሆን ቡድኖች በራሳቸው ኣባላት ራስን ማስተዳደር ይችላሉ የሚል ኣይነት ኣስተዳደርንና ኣስተዳደራዊ ችሎታን ከባህላዊ ማንነት ጋር ኣደባልቆ ብቅ ያለ የማንነት ጥያቄ ነው ያለው። ከዚህ የምንረዳው ሃቅ የኢትዮጵያ የማንነት ፖለቲካ ጥያቄዎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ኣደባልቆ የመጣ በመሆኑ ችግሩን ሊፈታ የሚችለው በሶሲዮ ፖለቲካል ቲየሪ ነው። ማንነቶችን ማደባለቅና ለብሄራዊ ማንነት የጠራ መልክ ማጣት የኢትዮጵያ ዋና ችግር ነው። እንዲህ ከሆነ ታዲያ የሃበርማስ ኣሳብ የሚጨነቀው ቨርቲካል ለሆነውና ፖለቲካዊ ለሆነው ማንነት ብቻ በመሆኑ የኢትዮጵያን ሶሺዮ ፖለቲካል ችግር ሊፈታው በጣም ይቀጥናል። ላሉብን ማህበራዊና ፖላቲካዊ ችግሮች የግድ የሶሺዮ ፖለቲክስ ንድፈ ሃሳብ ነው የሚያስፈልገንንና የሃበርማስ ኣሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው የማንነት ጥያቄ መፍትሄ ሊሰጥ ኣይችልም።

ካናዳን እንደምሳሌ ማንሳት እንችላለን። ካናዳን ብናይ የኮቤኮችን የቡድን ማንነት ጥያቄ የሃበርማስን ቲየሪ በመጠቀም በሊብራል ዴሞክራሲ ህገ መንግስት ሊፈታ ኣልቻለም ወይም ኮቤክ በዚህ ልባቸው ኣርፎ ኣልታየም። ከፍ ሲል እንዳልነው የኮቤኮች ጥያቄ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ጉዳዮችን ይዞ ስለመጣ ሃበርማስ እንደሚለው በሊብራል ህገ መንግስት የሚፈታ ኣልሆነም።

በሃገራችን ኢትዮጵያ በተለይ በ1960ዎቹ የተነሳው የቡድን ነጻነት ጉዳይ ሲነሳ ድንገት የተደባለቀው የቡድን ማንነትና የፖለቲካ ማንነት እንዲሁም መልኩ የደበዘዘው ብሄራዊ ማንነት ጠርቶ ሳይሄድ እስካሁን ቀርቱዋል። ከቀዝቃዛው ጦርነት በሁዋላ የጽንፈኝነት ፖለቲካ የከሰመ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን የራሱዋን ኣለም ሰርታ ኣሁንም በቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ ትገኛለች። እጅግ በሰፋና ጽንፈኛ በሆነ የፖለቲካ ኣስተሳሰብ ውስጥ ያለን በመሆኑ ዴሞክራሲ ሌላው ኣለም ላይ እያደገ ሲሄድ እኛ ጋር ቁልቁል ሲያድግ ይታያል።

የሃበርማስ ኣሳብ ኣንዱ ለኢትዮጵያ የማይሆንበት መንገድ ፖለቲካዊ ብቻ በመሆኑ ሲሆን ከሁሉ በላይ ኣንድ ቤት ሲሰራ ዋልታና ማገር ያስፈልጋል። ዋልታውንና ማገሩን እንደ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ልንመስለው እንችላለንና የጠነከረች መሰረት ያላትን ኢትዮጵያን ለመገንባት የሃበርማስ  ኣሳብ  ኣቅም ያጥረዋል። በመሆኑም እኛው ራሳችን ኣገር በቀል የሆነ ኣንድ ሶሺዮ ፖለቲካል ቲየሪ ልናመጣ ያስፈልገናል ከሚል ነው  የ CCU (Conventional cultural unity)   ኣሳብ የመጣው።

3.  CCU (Conventional cultural unity ) እንዴት ኢትዮጵያን መልሶ ለማዋቀር ሊረዳ ይችላል?

ኣሳቡ በዋናነት መሰረት ያደረገው የኢትዮጵያን ቡድኖች ቸርነት፣ ኣብሮ የመብላት፣ ኣብሮ የመኖር የማካፈል፣ ተፈጥሮ ነው። ከዚህ የተነሳ እነዚህ ቡድኖች ኣንድ ኣገር ሲመሰርቱ በቀጠነ ሁኔታ የፖለቲካ ማህበረሰብ ብቻ መሆን ሳይሆን የሚፈልጉት ለኣዲሱ ቤታቸው ነፍስ ሳይቀርላችው ያላቸውን ሁሉ ለኢትዮጵያዊነት የሚሰውበት ኣሳብ ነው። ባህል ስንል የምግብ ኣሰራር፣ ኣለባበስ፣ የበዓላት ኣከባበር ወዘተ ወግና ልማዶች ሲሆኑ እነዚህን ሁሉ ለማካፈልና ለኢትዮጵያዊነት ሰውቶ የጋራ ቤት ለመስራት ኢትዮጵያዊያን የቸርነት የጋራ ባህል ኣላቸውና ማህበራዊ ቲየሪው ይህንን ተፈጥሮ ያገናዘበ ነው።

በዚህ ኣገባብ ባህላዊ ውህደት ስንል ባህላዊ ቡድን የሚይዘውን ሁሉ ያቀፈ ነው። ይህ ማለት ቋቋ፣ ባህል፣ መልክዓምድር ወይም የተፈጥሮ ሃብትን ሁሉ የያዘ ነው። ቡድኖች ኢትዮጵያዊ መሆን (Being Ethiopian) ለምንለው ይህንን ሁሉ ሲሰው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በዜግነት መብታቸው እየተዘረዘረ በተግባር ይደርሳቸዋል ማለት ነው። ይህ ማህበራዊ ማንነት የፖለቲካ ማንነት ወለል ስለሚፈጥር በዚህ የጋራ ማንነት ስር የሚቆመውና በዚህ ጥላ ስር የሚጠለለው ፖለቲካ እንደ ማገር እየሆነ የጋራውን ቤት ይሰራል ማለት ነው።

ከዚህ በፊት እንዳልኩት ይህ ማለት ቡድኖች ባህላቸውን ያላቸውን ሁሉ ለኢትዮጵያዊነት ሰውት ማለት ከዚያ በሁዋላ ይጠፋሉ ማለት ኣይደለም። የቡድኖች ቋንቋና ባህል ጉዳይ ንብረትነቱ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ሆኖ ይሰዋ እንጂ በዚያ ቡድን ውስጥ እየገቡ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ያን ቋንቋና ባህል ወደላይ ጠብቀው እያሳደጉት ይኖራሉ። በጣም ተግባራዊ ምሳሌ ለማምጣት ኣንድ ኣባቱና እናቱ ኣማራ የሆኑ ሰው እሱ ኮንሶ ውስጥ ሄዶ ቋንቋውን ለምዶ ባህሉን ባህሉ ኣድርጎ ከኖረ ወይም ፈቃደኛ ከሆነ ኮንሶ ብሎ ራሱን ከባህል ኣንጻር የሚገልጽበት ኣውድ(context) ሲፈጠር በዚህ ራሱን ሊገልጽ ይችላል።  በዚህ ኣሳብ መሰረት ማንነት የሚቀየር የሚለወጥ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን በሰፊው የሃገራቸው ባህል ወስጥ የመሳተፍ የዚያን ቡድን ጥበብ የመደሰት መብት ኣላቸው። የቡድኖች ቤት ሁሉ ለኢትዮጵያዊያን ክፍት ይሆናል ማለት ነው። የተፈጥሮ ሃብትም ሆነ ሌሎች የቡድን ጥበቦች ሁሉ በእንደዚህ ኣይነት ማህበራዊ ስምምነት ስር መጀመሪያ ሊወድቅ ይገባዋል። ኢትዮጵያዊያንም ይህን ማህበራዊ የሆነ ኪዳን ከምንም በላይ ሊያስቀድሙ ይገባቸዋል። በዚህ ኣሳብ መሰረት የግዛትም ጉዳይ ኣንዱ ሲሆን ቡድኖች ኣገጣጥመው የሰሩዋትን የኢትዮጵያን ግዛት(territory) በሚመለከት ኣንዱ የቡድኖች መጣበቅ(attachment) መገለጫ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ግዛታቸው ከህልውናቸው ጋር በጥብቅ እንዲያያዝ ስለሚያደርግ ብሄራዊ ስሜትን ያጎለብታል።ከፍ ሲል እንዳልነው ይህ የቡድኖች ኪዳን ከሁሉ በላይ የሚውል ይሆንና ከዚያ ቀጥሎ በዚህ ማንነት ስር የሚገነባው የፖለቲካ ማንነት የራሱን ህገ መንግስት ኣውጥቶ በዚያ ይተዳደራል ኣገሪቱን ወደ በጎ ለውጦች ይመራል። የኢትዮጵያዊያን ብሄራዊ ማንነትም የነዚህ የሁለቱ ድምር ውጤት ይሆንና በማህበራዊም በፖለቲካዊም ጎኑ የተሙዋላ ብሄራዊ ማንነት እንገነባለን። የኢትዮጵያዊያን ብሄራዊ ማንነት በግዛት፣ በባህል ውህደት፣በዜግነት የሚገለጽ የዳበረ ማንነት እናፈራለን ማለት ነው። ወደዚህ ኪዳን ደፍረን መግባት፣ ሁሉንተናችንን በመተማመን ለኢትዮጵያዊነት መሰዋት ከቡድኖች ሁሉ የሚጠበቅ ጀብዱ ሲሆን ይህ ትውልድ ይህን ኣደረገ ማለት ኢትዮጵያ ኣሁን ተፈጠረች ተብሎ ሊወሰድ ግን ኣይችልም። ይህ ስራ ኢትዮጵያን መልሶ የማዋቀር ስራ እንጂ ኢትዮጵያ ለዘመናት የኖረች  ጥንታዊት ኣገራችን መሆኑዋ ኣያጠራጥርም።

4.ኪዳን ስንል ምን ማለታችን ነው? ምንን ምን ይይዛል?

በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ኪዳን የሚለው ጉዳይ ቡድኖች ለትውልድ የሚያስተላልፉት የስምምነት ሰነድ ነው። የተጻፈ ሰነድ ለትውልድ ማስተላልፍ መጀመሩ ለኢትዮጵያ የወደፊት ህይወት መልካም ነው። በመሆኑም ኪዳኑ የሚይዛቸው ጉዳዮች እጅግ የላቁ የቡድኖችን ስምምነት ሲሆን ይህ ስምምነት ዘመን የማይሽረው ይሆናል። የስምምነት ነጥቦቹን ቡድኖች በብሄራዊ እርቅ ሂደት ውስጥ ሲገቡ የሚያነሱዋቸው ሲሆን የማትከፋፈል ኢትዮጵያን ለትውድ ለማሳለፍ፣ የቡድኖች የባህል ውህድት ስምምነት፣ የህዝቦች የበላይነት ጉዳይ የኢትዮጵያን ፋውዴሽን ጉዳይና   ሌሎች እጅግ ከፍ ያሉ ኣሳቦች ሊሆኑ ይችላሉ።እንግዲህ ኢትዮጵያ በዚህ ኣሳብ መሰረት ሁለት ሰነድ የሚኖራት ሲሆን ኣንዱ ይህ ኪዳን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፍትህ ፣ እኩልነት፣  የመሳሰሉትን የሚያሳልጥ የእለት ተእለት ህይወቱዋን የምትመራበት ህገ መንግስት ይኖራታል።

CCU’s Structure

 

 

 

 

 

 

 

 

 

በዚህ ኣዲስ ኣወቃቀር መሰረት ሁለት ኣይነት ኣስተዳደር የሚኖራት ሲሆን ኣንደኛው ባህላዊ ኣስተዳደር ነው። ይህ ባህላዊ ኣስተዳደር የሚመሰረተው ከየቡድኑ ኣንድ ኣንድ ባህላዊ ተወካዮች ተመርጠው ይመጡና የኪዳኑን ኣርበኞች ቤት ይመሰርታሉ። እነዚህ ኣርበኞች እንደስምምነታቸው በየ ኣመቱ በእጣ እየመረጡ ንጉስ የሚሾሙ ሲሆን ይህ ንጉስ በዚያ በመጣበት ባህላዊ ቡድን ባህል መሰረት ይነግሳል። እንዲህ እያለ ሁሉም ቡድኖች በተራ እየነገሱ ይኖራሉ ማለት ነው። ይህ ኣካል ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ኣይገባም። ሃላፊነቱ የሽምግልና ስራዎችን መስራት፣ የተለያዩ የባህል ፌስቲቫሎችን ማዘጋጀትና መምራት፣ የኬር ቴከር ሃላፊነትን መውሰድና የፖለቲካ ችግር ሲፈጠር ኣገር ኣረጋግቶ መንግስትን መመስረት የመሳሰሉት ውሱን ስራዎችን የሚሰራ ነው። በባህላዊ ጉዳዮች ውስጥ ኣክቲቭ ሊሆን ይችላል።

ሌላው መዋቅር መንግስት ሲሆን በፓርላመንታሪም ይሁን ፕሬዚዳንታዊ ዘዴ የሚመሰረተው መንግስት ህግ ኣውጪው ኣስፈጻሚውና ተርጓሚው ነጻና እርስ በርስ ቼክ እና ባላንስ ያለበትን ስርዓት መስርቶ ይኖራል። ይህ የኢትዮጵያ ቅርጽ ሁለት መንኳን የሚያሳይ ሲሆን በኣንድ በኩል ማህበራዊውን ጉዳይ በሌላ በኩል ፖላቲካውን መልኳን ያሳያል። የነዚህ ድምር ውጤት በዜግነታችን የሚገለጸው ኢትዮጵያዊነት የወንዶችና የሴቶች ኢትዮጵያዊያን ብሄራዊ ማንነት መገለጫ ይሆናል ማለት ነው።

5. ያለፈ ትውስት (Past memories) በኣዲሱ ኪዳን እንዴት ይታያል?

ምእራብ ጀርመንና ምስራቅ ጀርመን ልዩነት ሲያምራቸው ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ጀምረው ነበር። ኣንዱ የጀርመኖችን ፖለቲካ ያራራቀውም ይሄው ነበር። በተለይ በናዚ ወቅት የተፈጸመውን የሆልኮስት ዘር ማጥፋት ወንጀል በተመለከተ ሁለቱ ጀርመኖች በተለያየ መረዳት መተርጎም ከመጀመራቸው ኣልፎ በርሊንና ቦን ሁለት ሙዚየሞች ቆመው የተለያየ ነገር ማስተማር ጀምረው ነበር። ያለፈውን ታሪክ ለማስታወስ የፈለጉበት ሞቲቭና ታሪኩን ወደ ትውልድ ለማሳለፍ የሞከሩበት ዘዴ ይለያይ ነበር።

ባለፈው ጊዜ ዶክተር መራራ ጉዲና ጥሩ ነገር ተናግረዋል። ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ኣናውለው ብለዋል። በርግጥ ጀርመን  ከታየው በላይ የኢትዮጵያን ኣጠቃላይ የታሪክ መሰረት የሚያምስ ሁኔታ ተፈጥሩዋል። ይህ የሆነው የማንነት ፖለቲካን ለማራገብ ታሪክ መሳሪያ ሆኖ በመቅረቡ ነው።

በርግጥ ኣንድ ሃገር ሲቆም ያለፈን ትውስታ ወዴትም ኣንጥለውም። ነገር ግን ትውስታችንን የምናይበትን መንገድ ማስተካከል ኣስፈላጊ ነው።

በ   CCU  ኣመለካከት በኢትዮጵያ ስቴት በመመስረቱ ሂደትና ከመሰረተች በሁዋላ የተፈጸሙ በጎም ሆኑ መጥፎ ታሪኮች ሁሉ የኢትዮጵያ ትውስታዎች (Past memories) ናቸው።  ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ትውስ የሚላት ታሪክ ነው። በጎ በጎውን መርጠን የመታሰቢያ ቀን ኣቁመን የጋራ ታሪካችን እያልን እየሞቅን መጥፎውን ነቅሰን ኣውጥተን ለኣንድ ቡድን ኣናላክክም። ሁሉም የኢትዮጵያ ታሪክ ነው። የሚያሳዝነው ያሳዝነናል፣ የሚያስደስተው ያስደስተናል።

ባለፉት ጊዚያት በግልም ይሁን ቡድንን እየለየ የተፈጸመ በደል ሁሉ የኢትዮጵያ ትውስታ(past memories) እንጂ ያ በደል የተፈጸመበት ቡደን  ቋንቋ ተናጋሪና ኣባል ብቻ ኣይደለም።

ሌላው ታሪክን በሚመለከት የዓለም ህዝብ ኢትዮጵያን እንዴት እነደሚያያትም መታወቅ ኣለበት። ከኣጠቃላዩ የዓለም ህዝብ ወደ 54.9 በመቶ የሚሆነው የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖተኛ ሲሆን ኢትዮጵያን የሚያያት በረጅም ጊዜ ታሪኳ ነው። ክርስቲያኑ በሃዋርያት ስራ ላይ የተገለጸውን ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ዋቢ በማድረግ ክርስትናን የተቀበለች ከዓለም ቀደምት ኣገር ናት ብሎ ያከብራታል። በብሉይም ስሙዋ የተጠቀሰ ተስፋ ያላት ኣገር ኣድርጎ ስለሚያምን ተስፋዋን ይጠብቃል።። ሙስሊሙ ህበረተሰብ ደግሞ ለመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች መጠጊያ ለመሆን የበቃች ኣገር ብለው ስለሚያምኑ እንደዚሁ በሙስሊሙ ህዝብም ዘንድ ታዋቂ ናት።። ይሄ ከፍተኛ ተጽእኖ ያለው ታሪክ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ህዝብ እንዲህ እንደሚያያት መገንዘብ ጠቃሚ ነው። ሌላው ያሉን ቁሳዊ ባህሎች እንደ ላሊበላ፣ ኣክሱም በደቡብና ኦሮሚያ የሚገኙ ሃውልቶች ሁሉ የኢትዮጵያን እድሜ ይናገራሉ። እነዚህ ታሪኮች ሁሉ የጥንታዊቱን ኢትዮጵያን ትውስታ እየሰጡን እንኖራለን።በኣጠቃላይ በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ያለፈውን ታሪክ እንደ ወል ታሪክ የሚያይ ይሆንና የሚከተሉትን ጉዳዮች በጥብቅ ይመረምራል።ይህም ታሪኩ ታሪክ ሆኖ መቅረት ብቻ ሳይሆን ኣሁን ድረስ ይጎተታል ወይ? በተለይ መጥፎ የምንለው ታሪክ ኣሁንም ካለ ይህን ታሪካዊ ዳራ ያልውን ችግር በሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ እና በብሄራዊ እርቅ ይፈታል ።

በኣጠቃላይ ያለፈውን ታሪክ የምናስታውሰው የወል ታሪክ ኣድርገን ሲሆን ይህንን የወል ታሪካችንን እንደ የወልነቱ ስናየው ትውስታችንን በጥሩ ሚዛን ላይ ያስቀምጠዋል።

ከዛሬ መቶ ኣመት በፊት የነበረውን ታሪካችንን ስንተነትን ኢትዮጵያን ለብቻዋ ንጥል ኣድርገን ሳይሆን ከኣለም የሰው ልጆች ታሪክ ጋር እያገናዘብን መፍረድ ኣለብን።ሌላው ኣሁን ያለንበት ከባቢስ ምን ይመስላል? በምን ኣይነት የፖለቲካና ማህበራዊ ከባቢውስጥ ሆነን ነው ታሪክን የምንተነትነው? ብለንም መጠየቅ ኣንዱ ለፍርድ በተሻለ የሞራል ደረጃ ላይ የሚያስቀምጠን ነው። ሌላው ማየት ያለብን የትውስታችን ፍላጎት ምንድነው? በታሪክ መረዳታችን ምን ልናደርግበት ነው? ብለን መጠየቅም መልካም ነው። በርግጥ ያለፉ ታሪኮችን ኣንስተን በቀልን ልናቅድ ነው? ወይስ የተሻለ ኣሰራር ለማምጣት መልካም እልህ ውስጥ ሊከተን ነው? ብለን መጠየቅ ኣለብን የሚል ምክር ይህ የባህላዊ ውህደት ኣስብ ኣዝሎኣል።

       ማጠቃለያ

ይህንን ወረቅት ስጽፍ ድፍረት ያበዛሁ እንደሆነ ገብቶኛል። ዋናው ጉዳይ መፍትሄ ስለናፈቀኝና በርግጥም የኢትዮጵያን ማህበራዊ ፖለቲካ ችግር ሊያቀል ይችላል ከሚል ነው። ኣንዳንዶቹ ያነሳሁዋቸው ነጥቦች ውሳኔ ሁሉ ይመስላሉ። ንጉስ ይኑር፣ በየኣመቱ ይሾም…. ስል ኣንባቢ የሚያስበውን እያሰብኩ ነው የጻፍኩት። ለማናቸውም ሁላችን እየተወያየን ከዚህ ብሄራዊ ማንነታችንን ካደበዘዘ ጨለምተኛ የፖለቲካ መዋቅር ፈጥነን መውጣት ኣለብን። በዚህ ጽሁፍ ላይ ኣስተያይት ካለ ጻፉልኝ። የህገ መንግስታዊ ኣርበኝነት ወይም ቀናዒነትና በስምምነት ላይ የተመሰረት ባህላዊ ውህደት ጽንሰ ሃሳብ ልዩነቶችን በሰንጠረዥ እንደሚከተለው ኣቅርቤ ጽሁፌን ላጠቃል። በዋናነት ግን ባለፈው እንደጻፍኳት ብጣቂ ኣርቲክል የቱንም ያህል መልካም ስርዓት ብናመጣ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ከሌለ ኣይጠቅመንምና ይህንን ጉዳይ ችላ እንዳንል ዛሬም ኣሳስባለሁ።

የሁለቱ ጽንሰ ሃሳቦች ልዩነቶች

  Constitutional patriotism Conventional Cultural Unity
1 ፓለቲካዊ ንድፈ ሃሳብ ነው የሶሲዮ ፖለቲካል ቲየሪ ነው
2 ቀጥታ ግንኙነትን (Vertical) ብቻ የሚያይ ነው ቀጥታና ተዋረዳዊ (Vertical & horizonatal) ግንኙነቶችን ይዳስሳል
3 ለህገ መንግስት ታማኝ በመሆን ፖለቲካዊ ብሄራዊ ማንነት ለመገንባት የቀረበ ነው

 

ባህላዊና ፖለቲካዊ ኣስተዳደሮችን በመዘርጋት ሁለንተናዊ የሆነ ብሄራዊ ማንነትን ለማዳበር የቀረበ ነው።
4 ዩኒቨርሳል የሆነ የሰባዊ መብትን መሰረት ያደረገ ነው ዩኒቨርሳል የሆነ የሰባዊ መብትን መሰረት ያደረገ ነው
5 ህገ መንግስት ከፍተኛው ሰነድ ነው

 

ሁለት ሰነዶች የሚኖሩ ሲሆን የኪዳኑ ሰነድና ህገ መንግስት ተብለው ቀርበዋል።

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ

ገለታው ዘለቀ geletawzeleke@gmail.com

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on April 6, 2014
  • By:
  • Last Modified: April 6, 2014 @ 10:00 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar