www.maledatimes.com ስለ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ፖለቲካዊ ሰብዕናና ከሚኒልክ በዘር መዛመዳቸው (አንድነት ይልማ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ስለ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ፖለቲካዊ ሰብዕናና ከሚኒልክ በዘር መዛመዳቸው (አንድነት ይልማ)

By   /   September 1, 2012  /   Comments Off on ስለ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ፖለቲካዊ ሰብዕናና ከሚኒልክ በዘር መዛመዳቸው (አንድነት ይልማ)

    Print       Email
0 0
Read Time:21 Minute, 1 Second

ethio media
ሰለአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፤ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር(?) ሰብእና ብዙ የሚታወቅ ባለመሆኑና፤ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ግን በቅርብ ርቀት የሚያውቃቸው ሰው በመሆናቸው ይህችን አጭር ፅሁፍ ለመፃፍ አነሳሳኝ። አቶ መለስ ዜናዊ ካወረሱን ቅርሶች አንዱ “የዘሬን ያንዘርዝረኝ” ነውና፤ የአቶ ሀይለማርያምን ሰብእና ስዳስስ ከዘር ብጀምር አይፈረድብኝም። ሀይለማርያም ደሳለኝ እንደ ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ በእናታቸው ብቻ ሳይሆን፤ ሙሉ በሙሉ (በእናትም በአባትም) በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙት 48 ብሄረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው የወላይታ ተወላጅና ንፁህ ወላይታ ናቸው። የወላይታ ብሄረሰበ ህዝብ ብዛት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋና፤ ከኢትዮጵያ ህዝብም 3% ያህል የሚሆን ነው። ሀይለማርያም ደሳለኝ በእምነታቸው ፕሮቴስታንት (ፔንቴኮስታል ክርስቲያን) ሲሆኑ፤ በመንፈሳዊ ህይወታቸውም የሚፀልዩና መፅሀፍ ቅዱስ የሚያነቡ ትጉህ ሰው እንደሆኑ ብዙ ሰዎች ይመሰክሩላቸዋል።
ከእምነታቸውና ከሞራላቸውም ሊሆን ይችላል እንደ በርካታ የህወሀት-ኢህአዴግ ባለስልጣናት በሙስና (corruption) ውስጥ አልተዘፈቁም። አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ለህወሃት- ኢህአዲግ
የድል አጥቢያ አርበኛ ሰው ናቸው። “የድል አጥቢያ አርበኛ” ትርጉም እንደ ህወሀት ለ17 አመታት በበረሃ ታግሎ ያልመጣና፤ ነገርግን ከግንቦት 20 ቀን 1983 ድል በሁዋላ ኢህአዴግን በአባልነትና በደጋፊነት ለተቀላቀለ ሰው ሁሉ የሚሰጠው ስም ነው።
ሀይለማርያም ደሳለኝ እድሜው በአርባዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኝ፤ በትምህርት ዝግጅቱም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንጀሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪና፤ እንዲሁም ከአውሮፓም ሁለተኛ ዲግሪውን በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ያጠናቀቀ ሰው ነው። የሙያ ልምዱም በኮሌጅ መምህነት፤ በኮሌጅ ዲንነት (ሃላፊነት)፤ በደቡብ ክልል መንግስት አስተዳዳሪነት ወይም ፕሬዜዳንትነት፤ በጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ በሚንስትር ማእረግ አማካሪነት እና በቅርቡም የውጭ ጉዳይ ሚንስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ዋነኞቹ ናቸው።ግላዊ ሰብዕናውን በተመለከተ፤ ሀይለማርያም ቅንነትና ትህትና የሚታይበት፤ ሰውን ሁሉ የሚያከብር፤ የማይመፃደቅ ተግባቢ ምሁር ፤በራሱ የሚተማመን፤ ስብሰባ ሲመራም ሆነ ሀገር ሲያስተዳድር የማያስፈራራና የማይደነፋ፤ ተቃራኒ ሀሳብ የሚቀበልና ባግባቡ ምላሽ የሚሰጥ፤ በአግብኦ (አሽሙር) ወይም በማሽሟጠጥ የማይመልስ፤ የበታችነት ወይም የበላይነት ስሜት የማይሰማው፤ ፈገግታ የማይለየውና ለማነጋገርም የማይከብድ ሰው መሆኑን እኔ በሚገባ አወቃለሁ፤ እመሰክራለሁም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአቶ ሀይማርያም ትልቁ ሰብእና፤ የኢህአዲግ ባለስልጣን ይቅርና፤ ጠቅላይ ሚንስትር ቢሆንም ባይሆንም፤ ራሱን ችሎ፤ በሰላምና በነፃነት ለመኖር እንደሚችል አስቀድሞ የተረዳ ሰው በመሆኑ፤ አምባገነን ልሁን ቢል እንኳን ለመሆን የማይችል ሰው ይመስለኛል። በነዚህና በሌሎችም ዋና ዋና ባህርያትና እንዲሁም አቶ መለስ ዜናዊ ኦሮሞዎችንና ምናልባትም አማራዎችን ለጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣን መተካካት (በህወሀት-ኢህአዴግ ቋንቋ) ባለማመናቸው ምክንያት አቶ ሀይለማርያምን ወደ ቤተመንግስታቸው በማቅረብ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው እንዲለማመዱና እንዲተኩዋቸውም ያስጠጉዋቸው ይመስለኛል። በእኔ ግንዛቤ፤ የአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ትልቁ ድክመት ሊሆን የሚችለው፤ ሀይለማርያም አፍተልታይ ፖለቲከኛ ያለመሆናቸው ጉዳይ ዋናው ይመስለኛል። ለምሳሌ፤ ታላላቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ለመወሰን አቅም የማጣት ሳይሆን የመፍራት፤ የተሸረበ ፖለቲካዊ ነገርን ለመለየት መቸገር፤ የህወሐት አድራጊና ፈጣሪ ሰዎችን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቋቋም አለመቻል፤ ሰዎችን ለማግባባት ሲሉ ውሳኔ ላይ የመዘግየት ችግር ወዘተ ሊኖር ይችላል የሚል ግምት አለኝ። እንደዚሁም ደግሞ እንደ ህወሀት- ኢህአዴግ ባህርይ ከሆነም፤ ሀይለማርያም ነገር አዋቂና ሰንጣቂ፤ እጅ-ጠምዛዥና አስጠምዛዥ፤ በስውርም የፈለጉትን ነገር የሚያስደርጉ፤ ደግሞም ተጠራጣሪም ሰው ባለመሆናቸው፤ ከህወሀት-ኢህአዴግ ቀንጨራ ፖለቲከኞች፤ አድርባዮችና፤ በሙስና
የተዘፈቁ መሰሪዎች ጋር ባንድነት ሊሰሩ እንዴት እንደሚችሉ ሳስብ ግርታ ይፈጥርብኛል። በአጠቃላይ አቶ ሀይለማርያም ከመሪነት ይልቅ ወደ አሰተዳዳሪነት የማድላት ተፈጥሮ ስላላቸው፤ የዘር ፖለቲካን እየሸረቡ፤ እሁድን ሰኞን ነው፤ ድንጋዩን ዳቦ ነው፤ ጭለማውን ብርሀን ነው፤ በማለት በአፈ ጮሌነትና በማስመሰል ለመኖር የሚችሉ ሰው ፈፅሞ አይመስሉኝም። ባጠቃላይ አነጋገር፤ ሀይለማርያም
በጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ላይ ራሳቸውን ሆነው ካልሰሩ በስተቀር፤ ህወሐት-ኢህአዴግ ለሃይለማርያም፤ ወይም ደግሞ ሀይለማርያም ለህወሀት-ኢህአዴግ ትክክለኛው ምርጫ ባለመሆናቸው የሚኳኳኑ አይመስለኝም።
የዘር የፖለቲካ ስልጣንን ባለቤትነትን በተመለከተም፤ ዘርን በጣም አንዘርዝረን ካየነው ደግሞ የአፄ ሚኒልክና የአቶ ሀይለማርያም ዘር ከወላይታ መሆን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን ከአማራና ከትግሬ በመቀጠልና ሀገራችንን በመምራት ወላይታዎች ሶስተኛዎቹ መሆናቸው ነው። ምንም እንኳን አቶ ሀይለማርያም ሚኒልክ ቤተመንግስት በመግባት በእናታቸው ወላይታ ከሆኑት ከአፄ
ሚኒልክ ቀጥሎ የወላይታ ተወላጅ ቢሆኑም፤ ስልጣኑን ባጋጣሚና በችሮታ እንጂ፤ በምርጫ ወይም በትግል ሜዳ ያገኙት በአለመሆኑ፤ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ2 በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስልጣን ባለቤትና ባላንጣ ከሆነው ከህወሀት የፖለቲካ አጥር ክልል ውጪ መጫወት እንዳይችሉ ሆነው የተቀመጡ ለመሆናቸው በቅርብ የምናየው ክስተት ይሆናል። ፖለቲካዊ ስልጣኑ በእውነት ለአቶ ሀይለማርያም ያልተሰጣቸው ከሆነም ዲሞክራሲ፤ የህግ የበላይነት፤ መልካም አስተዳደርና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚጠቅም አኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት የማይችሉ ሰው ስለሚሆኑ በስልጣን ላይ የሚቆዩ አይመስለኝም። ነገር ግን ኢህአዴግ ሆነው በስልጣን ለመቆየት ከፈልጉ የአቶ መለስ ዜናዊን ሰብዕናን የግድ መላበስ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ውጭ በእውነተኛ ስልጣን በትክክል ከሰሩ ግን እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ሊታደግ በጊዜው ያስቀመጣቸው የመጀመሪያው ፋና ወጊ፤ መሰረት ጣይ፤ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ጀማሪ ሆነው ብቅ የሚሉ አገልጋይ መሪ ሆነው ይወጡ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። በጎውን መመኘት መልካም ነው።
ዳግማዊ አፄ ሚኒልክም እንደ አቶ ሀይለማርያም ወላይታ ወደ መሆናቸው ጉዳይ ስንመጣ፤ ንጉሰ ነገስት ሚኒልክ በእናታቸው ወላይታ እንደሆኑ እጅግ አብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሚያውቁት ታሪክ ስላልመሰኝ፤ ትኩረትም እንድታገኝ፤ ይህችን መጣጥፍ የዳግማዊ አፄ ሚኒልክና የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የዘር ግንድ አንድ ነው ብዬ ሰየምኳት። የሚኒልክ እናት ታሪክ እጅግ ባጭሩ የሚከተለው ነው። የአፄ ምኒልክ አያት ንጉስ ሳሕለ ስላሴ በዘርዋ ወላይታ የሆነች ብልህ ልጃገረድ የቤት ሰራተኛ ነበረቻቸው።
መልካም የሚመስላቸውን ታሪክ ብቻ በመምረጥ፤ ደግሞም የነገስታትንና የጦርነት ታሪክን ብቻ የሚተርኩልን ተወቃሽ የታሪክ ፀሀፊዎቻችን፤ የህዝቦችን ታሪክ እየደበቁና፤ እየዘዘሉ እንደሚፅፉልን ሁሉ፤ የሚኒልክ እናት የሆነችውን የዚህችን ጎበዝና አርቆ አሳቢ ወጣት የቤት ሰራተኛ ታላቅ ታሪክ ሳይፅፉ አልፈውታል። የተወሰኑ ገዢ መደቦች የበላይነት ታሪክ ብቻ የሚንፀባረቅበት ጊዜ በመሆኑ
ሊሆን ይችላል ምክንያታቸው። ነገር ግን እውነት እውነት ናትና ልትደበቅ ባለመቻልዋ፤ በአፈ-ታሪክና በተለያዩ ታሪካዊ ፅሁፎች ላይ ስለሚሰፍር ታሪክ ተደብቆ ሊቀር አይችልም። ወደፊትም ያልተፃፈው እውነተኛው የህዝቦች ታሪክ ሲፃፍ እንዲህ አይነት ታሪክ የሚዘለል አይመስለኝም። የህዝቦችን እውነተኛ ታሪክ ከመፃፍ የበለጠ ለሀገር አንድነትና ለህዝቦች መስተጋብር መገለጫ የሚጠቅም
የለምና። በርግጥ ድሮም ቢሆን፤ በተለይ በሀገራችን መሪዎች ህይወት ዙሪያ የተደበቀውን ታሪካዊ ምስጢር፤ አገሬው፤ ገበሬው በስፋት የሚያውቀውና በአፈ ታሪክነት ሲቀባበለው እየቆየ እዚህ ከደረሱት ታሪኮች አንዱ ይኸው የሚኒልክ እናት ሙሉ በሙሉ ወላይታ የመሆንዋ ታሪክ አንዱ ነው።
አስተዋይና ደፋር የሆነችው ይህች የወላይታ ልጃገረድ፤ የዳግማዊ አፄ ሚኒልክ እናት፤ የሰራችው ታሪክ እርስዋም እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን፤ የዘር ፖለቲካ መቀየጥን ጠቀሜታውን ሳታውቅ ያመጣችው ታላቅ ተፅዕኖ ጥቅሙ የጎላ ነው። ይኸውም ይህች ወንድ የማታውቅ ወጣት ልጃገረድ፤ ለንጉሱ ባለሟል ከብልቴ ፀሀይ ሲወጣ በህልሜ አየሁ በማለት በመናገርዋ የተነሳ፤ የንጉሱ ባለሟልም ይህ ጉዳይ አስገርሞት፤ ለንጉሱም ተናግሮ ኖሮ፤ ንጉሱም ብልህ ሰው ነበሩና፤ በጊዜው ትንቢት አስመርምረው ወይም ወደፊት ሊሆን የሚችለውን ነገር በመገመት፤ ከወንድ ልጆቻቸው አንደኛውን (ከእርሳቸው በሁዋላ ንጉስ የሆነውን) ሀይለ መለኮትን በማስጠራት፤ እዚህች ልጃገረድ የቤት ሰራተኛቸው ላይ እንዲደርስባት (እንዲገናኛት) አስደርገው ሀይለኛውና፤ አሰተዋዩ ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ ሊወለድ ችሏል። ከብዙ የህይወት ከፍታና ዝቅታም በሁዋላ፤ ጊዜውን ጠብቆ ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ ተብሎ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት በመሆን፤ ለኢትዮጵያ የስልጣኔን በር በመክፈት፤ አንድነትዋን በማስጠበቅና የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን በአድዋ ድል በመንሳት፤ ብቸኛው ጥቁር የአፍሪካና የኢትዮጵያ የኩራት ልጅ ሊሆን ችሏል። ታላቁ የኢትዮጵያ መሪ ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ በአባቱ አማራ ቢሆንም በእናቱ ንፁህ ወላይታ መሆኑ፤ ዛሬ ሀይለማርያም ደሳለኝ ከወላይታ ብሄር የመጣ የኢትዮጵያ መሪ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው የተፈበረከ የጫወታ ታሪክ ያለመሆኑን ታሪክ ብንመርምር እንደርስበታለን እላለሁ። በዚህ አጋጣሚም የሌሎች መሪዎቻችን የቀዳማዊ ሀይለስላሴ፤ የኮረኔል መንግሰቱ ሀይለማርያምና የአቶ መለስ ዜናዊ እውነተኛው ሰብእናና የዘር ግንድ ታሪክ ቢፃፍ ታሪካችን መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ለእውነተኛው የህዝቦች አንድነት እና መስተጋብር መገለጫነት በአያሌው ይጠቅማልና ታሪክ ፀሀፊዎች ችላ አትበሉ እላለሁ። በመጨረሻም አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ስልጣኑ ከዘለቀላቸው በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው
የፕሮቴስታንት ክርስቲያን መሪ መሆናቸው ነው።
ቸር እንሰንብት
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com
August 30, 2012

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 1, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 1, 2012 @ 6:05 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar