www.maledatimes.com መለስ “የሠላም አባት” ተቀበሩ ግርማ ደገፋ ገዳ І girmariver@gmail.com І - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

መለስ “የሠላም አባት” ተቀበሩ ግርማ ደገፋ ገዳ І girmariver@gmail.com І

By   /   September 2, 2012  /   2 Comments

    Print       Email
0 0
Read Time:20 Minute, 37 Second

 

Meles Zenawi burial

የፖለቲካና የዜጋ ወገብ ሰባሪ ቃላትን ሲያንቦለቡሉ የነበሩትን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርን፤ “የሰላም አባት” “በአንድና አንድ ሰላም የሚያምኑ” “በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ ውዝግቦችን ለመፍታት የሞከሩ” “ቄጤማ ጎዝጓዥ” “ዘንባባብ ዘንጣፊ” እየተባለ፣ ማርና ወተት ብቻ ሲያርከፈክፉ እንደከረሙ እየተደረገ ከእንባ ጋር ሲሟሟቅ ሰነበተና ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙት አካል ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ መቃብር ገባ። በሥልጣን ዘመናቸው በግፍ ለተገደሉ ንጹሃን ዜጎች አንድም ቀን በይፋ ሳያዝኑ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩትና ለተቀበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ይቅርታ ሳይጠይቁ ማለፋቸውን በማሰብ ሳይሆን፣ ግማሽ አካሉ አፈር በለበሰው ኢሕአዴግ ትእዛዝ ምክንያት የቤተሰባቸውን ሀዘን የሚጋራ በርክቶ እንደነበር ተስተውሏል።  ከኢሕአዴግ መሥራቾች ውስጥ፣ ቱባ ቱባና ትራፊ ባለሥልጣናት ከየተደበቁበት ጎሬያቸው እየወጡ “ባለራእዩ” እያሉ የሥልጣን ሽሚያ በሚያስመስል ሁኔታ በእልህና በሲቃ ሀዘናቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። ‘ከኢሕአዴግ ውስጥ የሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር አንድ ጭንቅላት የሚተካ አንድ ጭንቅላት ስለሌለ ሰባት ጭንቅላት ያስፈልጋል’ ብለው ሰባት ሰዎች ባዋጡት ጭንቅላት ሀገር ከዳር እስከ ዳር ወደ ለቅሶ ቤት ተለውጦ ከርሞ ነበር። በሳቸው የ21 ዓመት የሥልጣን ዘመን፣ ለተገደሉ ኢትዮጵያውያን ማንም ኃላፊነት ሲወስድ አልተሰማም። ፍርድ ቤት የቆመ ማንም ገዳይ የለም። ወላጆች ለተገደሉ ልጆቻቸው እውነተኛ ዳኝነት አላገኙም። ካሳ’ማ የማይታሰብ ነው። እንኳን ፍትህና ካሳ ጉዳያቸውን ወደ ፍትህ ለመውሰድ ነጻነትና መብት አልነበራቸውም። ዛሬም የላቸውም። የተለወጠ ምንም ነገር እንደሌለም በሰባት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተነግሯል። የሳቸው አመራር፣ ለ21 ዓመት በዜጎች ላይ የሚቀልድ ሥርዓት ተክሎ፣ በመጨረሻም “የሰላም አባት” እየተዘመረላቸው ሙት አካላቸው መቃብር ገብቷል።

ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የቤተክርስትያን ወይም የመስኪድ መሪ አልነበሩም። ከትግራይ አዲስ አበባ ለመምጣት የፈጀባቸውን 17 ጎምዛዛ ዓመት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቁራን ሲሰብኩበት አይደለም የጨረሱት። “የዚህን ዓለም ሕይወት እርሱት! የወዲያኛውን ለመጨበት ተግታችሁ ጸልዩ” እያሉ እንዳልመጡ ማንም ያውቃል። ታንክ የታጠቀ የፖለቲካና የነጻነት ግንባር እየመሩ ነበር አዲስ አበባ የደረሱት። እያስገደሉ፣ እያስቆረጡ፣ እያሳሰሩ፣ እያሳፈሱ፣ ዙ−23 የሰው ግንባር ላይ እያስለቀቁ፣ አንገት በቢኤም ሮኬት እያሳጨዱ፣ ደረት በመድፍ እያስገመሱ፣ መትረትየሶች እያስመረቁ፣ በቦምብ እያስደፈቁ፤ ያንን የግድያ ዝናቸውን በከበሮና ክራር አሳጅበው በሕዝባዊ ወይኔ ሓርነት ትግራይ ራዲዮ “500 ገደልን፣ 1000 አቆሰልን” እያስነገሩ ነው ከመዲናዋ የደረሱት። በሳቸው የነጻነትና የግንባር መሪነት ዘመን የተገደሉት በሙሉ ኢትዮጵያውያን እንጂ የሌላ ሀገር ዜጎች አልነበሩም። “ጠላት!” እየተባሉ የላውንቸር መጫወቻ፣ “ደርግ!” እየተባሉ የቦምብ መተረቻ የነበሩት ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ቀርቶ ሮቦት የነበሩ ይመስል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን “የሰላም አባት” እያሉ ከሰላም አባትነት ተግባር ጋር ማላተም ምን አመጣው? እሳቸው በሕይወት በነበሩበት ወቅት ተሳስተው እንኳ “የሰላም አባት ነኝ” ብለው አያውቁም። “ደርግን አነካከትነው!” የመሳሰሉ አባባሎችን በየዓመቱና በየምክንያቱ መደጋገማቸው እሙን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ፣ ዓይን ውስጥ ሊገባ የሚችል የልማት ሥራ አሰርተው የማያውቁ፣ ወጣቶችን ፈንጂ ውስጥ ገፍትረው በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩትን የፈንጂ ራት ያስደረጉ፣ እስር ቤቶችን በፖለቲካ እስረኞች ያጨናነቁና የሥልጣን ጊዜያቸውን ሁሉ ዙፋናቸውን በመከላከል ብቻ ቆርጥመው የጨረሱ ናቸው። ከ1997 ዓ.ም በኋላም ሕዝብ እየተንጫጫ፣ ለሕዝብ ምሬትና አቤቱታ ምንም ግድ ሳይሰጣቸው የሀገሪቱን ምእራባዊ ዳርቻዎች “ድርሻችሁ ነው” እያሉ ለሱዳን የሰጡ፣ አንድ ሄክታር በአንድ ዶላር ለውጭ ዜጋ ሲቸበችቡ የከረሙ ናቸው። የከተማውን ነዋሪ፣ “ጣራና ግድግዳው የናንተ ነው፤ ቤቱ ያረፈበት መሬት የኢሕአዴግ ነው” በማለት የሕዝቡን መሬት የመቀማት ሂደት ለማጧጧፍ የሚረዳ አዋጅ ያጸደቁና እሱን ለማስፈጸም ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩ ናቸው።

“እህህህህ…. እህ…..እህ…..እሳቸው እኮ!…..የሰላም አባት፣ የአፍሪካ ቁጥር አንድ አደራዳሪ፣ የልማትና የግድብ ባለራእይ፣ ተራራ ለመናድ፣ ጉብታውን  ድርምስምሱን ለማውጣት፣ ሜዳውን በእህል አዝመራ ለማጨናነቅ ሌት ተቀን የለፉ…..” እየተባለ ነበር የተለቀሰው። ቤተመንግሥታቸውን በሕይወት ዘመናቸው ምን እንደሚመስል ለማሳየት ፍላጎት ያልነበራቸው፣ በታንክና ብዙ ዙር ባለው አጃቢና እንደካቴና ተያይዘው በታጠሩ የመትረየሶች ጋጋታ ሲጠበቁ የነበሩ ሰው፣ ባልታሰበና ባልታወቀ ሁኔታ በአጭሩ ሲቀጩ፤ ቤተመንግሥታቸውም ዜጎች ያለፍተሻ ግን በትእዛዝ እምባቸውን የሚያርከፈክፉበት ትልቅ ድንኳን ሆኖ ነበር። የሰላም አባት ግን አይደሉም።  ማንም እንዳይደርስባቸው ራሳቸውን ከታንክና መትረየሶች ባሻገር በየጊዜው በሚወጡ አዋጆችና መመሪያዎች ሲከላከሉ የነበሩ ሰው፤ በመጨረሻ ሠዓት፣ አጃቢ፣ ታንክና አዋጆች ሊገቱት በማይችለው ሞት እንደ ማንኛውም ሰው ተነጥቀው መቃብር ገብተዋል። ይሁንና የሰላም አባት ተብለው የሚጠሩ አይደሉም። ይህንን ለተገነዘበ አንድ የፖለቲካዊ ግንባር ወይም ኢሕአዴጋዊ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መሆን የሚያስፈልገው፣ ሥልጣን ያሳበደው ፖለቲከኛ ሳይሆን ቅን መሆን ብቻ ነው። ቅን መሆንን በትእቢት ለውጦ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባልዋሉበት የሰላም ጎራ “የሰላም አባት” እያሉ የሚቀጥለው ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ቴሌቪዥን ላይ በእንባ እየተጫወቱ መፎካከር፤ ከሟች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኋላ አይሰራም። እንደዚያ ዓይነቱ ሥርዓት ተሸራርፎ ለመቀበር ቀኑን የሚጠብቅ በመሆኑ፣ á‹« የመጨረሻ ቀን ከመምጣቱ በፊት ቴሌቪዥን ላይ ‘ማን የበለጠ አለቀሰ?’ ውድድር ከማድረግ ይልቅ፣ በግፍ ያሰሯቸውን ዜጎች ‘እንቁጣጣሽ፣ መስቀል’ እያሉ ምክንያት ሳያበዙ በጅምላ ቢለቋቸው የተሻለ ይሆናል።

ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ሰዎችን በጅምላና በነጠላ አፈርድሜ ማስበላታቸው ሳያንስ፣ በሚሰጡት ምክንያቶች ሳቢያ የተጎጂዎች ቤቴሰቦች አንጀትን ማሳረር፣ ከዚያም አልፎ ማሾፍ፣ መቀለድና መዛት ከሞት አላስጣላቸውም። የታጠቁም ይሁኑ ያልታጠቁ፣ በትጥቅ ትግል ወይም በሰላማዊ እምቢተኝነት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥልጣን ጎትቶ ለመወርወር ጫካም የገቡ ይሁን ከተማ ውስጥ የመሸጉ ድርጅቶች፣ ዋና ዓላማቸው የነበረው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ድርጅታቸውን ከሥልጣን በማንሳት በምትኩ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ፕሮግራም ማስፈን ነበር። ዛሬ ኢሕአዴግ ባይሄድም ወይም ኢሕአዴግ ራሱን ለማሻሻል ቃል ባይገባም፣ አንድ ነገር መቶ በመቶ እርግጥ ሆኗል−ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላይመለሱ አሸልበው ከመቃብር ወርደዋል። ከሳቸው ጋር ተያይዞ የነበረው ልዩ ልዩ ሰንሰለት ተበጣጥሷል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸው የ40 ዓመት እንቅስቃሴ አንድ ቦታ ላይ እጅ ሰጥቶ፣ ሂደቱ በህትመትና በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች አማካይነት ታሪክ መሆን ጀምሯል። ማሰር፣ ማሳሰር፣ መሳደብና መዛት አይችሉም። ጂ8 ወይም ጂ20 ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ወይም አፍሪካን ሳይሆን ኔፓድን ወክለው መገኘት አይችሉም። የኢሕአዴግ ዓመታዊ ስብሰባ፣ የሕወሓት ዓመታዊ ጉባዔ፣ ግምገማ ሂስና ግለሂስ፣ የፓርላማ አንድ ቁጥር፣ ሚኒስትሮችን ለሥልጣን ማጨት፣ የቁጩ መርማሪ ኮምሽን ማቅረብ፣ የቦናፓርቲዝም ወረቀት መበተን አይችሉም። ከንግሥት ኤልሳቤት ጋር ለመጨባበጥ ተራ ደርሷቸው በኪንግሃም ቤተመንግሥት ሲገቡ፣ በደጋፊዎቻቸው “አንበሳው” ተብለው ነበር። ዛሬ ሞቶና ወደ መቃብር የወረደ አንበሳ እንጂ በሕይወት ያለ አንበሳ ሊሆኑላቸው አይችሉም። የሰላም አባትም አልነበሩም።

እንግዲህ የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል። ከመቃብራቸው ይዘውት የሄዱት ምንም ነገር የለም። ሥልጣናቸው አዲስ አበባ ላይ፣ ገንዘባቸው ከባንክ፣ ልብሳቸው ከቁም ሳጥናቸው ቀርቷል። ሚስትና ልጆቻቸው ከአሁን በኋላ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤተሰብ አባል በመሆናቸው፣ ቤተመንግሥቱን ለቀው የት እንደሚሄዱ አይታወቅም። ብዙ ሚኒስትሮች በተለያዩ ምክንያቶች ከመንግሥት ኃላፊነታቸው ሲገለሉ፣ የመንግሥትን ቤት ተገደው እንዲለቁ እንደሚደረገው ሁሉ ለነሱም ሶስት መስመር ደብዳቤ ይደርሳቸው ይሆናል። “ወይዘሮ አዜብ መስፍን የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ” ተብሎ ቀልድ እስካልተጀመረ ድረስ እቃቸውን ሰብስበው ወዴት እንደሚሄዱ ሕዝብ ያያል።

ከቀብሩ ማግሥት ጀምሮ፣ በሰባቱ ጭንቅላቶች ወይም በሰባቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ መሰረቱ የሚጣል የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ተራ በተራ ይፋ ይሆናል። ሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር የሚያስታውሱ ትላልቅ ሀውልቶችን በየከተማው እንዲታነጹ ማድረግ ዋነኛው ነው። ድልድዮች፣ ወንዞች፣ ተራራዎች፣ ግድቦች፥ ትምህርት ቤቶች፣ ወታደራዊ ክፍሎች፣ አደባባዮች፣ መንገዶች፣ አውሮፕላን ማረፊያዎችና ሆስፒታሎች በሙሉ በሳቸው ስም ይሰየማሉ። የደጋፊዎች ግንባር፣ አንገት፣ ጀርባና ደረት ላይ የሚለጣጠፉ ነገሮች እንደ አሸን ይፈላሉ። የፈረደባቸው የመንግሥት ሰራተኞችም የወር ደሞዛቸውን ለአንዲት ጥቡቆ ይለቃሉ። ኢሕአዴግ እስካለ ድረስ፣ ፓርላማውም ሆነ ኢሕአዴጋዊ ጉባዔዎች ሲከፈቱ “እስቲ ባለራእዩን ለአንድ ደቂቃ እናስበው” የማይጀመርበት ምክንያት አይኖርም። ግን በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የሰላም አባት ሊሆኑ አይችሉም፤ የስድብና የ“እኔ ብቻ” አባትነትን ግን የሚቀማቸው አይኖርም። በዚያ እየታወሱ የቀረውን መቃብራዊ ሕይወታቸውን ይቀጥላሉ። ከመቃብራቸውም ሆነው “እሳቸውን የሚተካ የለም” የተባለለትን ኢሕአዴግን ያስተዳድራሉ።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 2, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 2, 2012 @ 6:44 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar