www.maledatimes.com ‹‹ማለፊያ መደሪያ አይሆንም…›› ግሩም ተ/ሀይማኖት - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

‹‹ማለፊያ መደሪያ አይሆንም…›› ግሩም ተ/ሀይማኖት

By   /   September 11, 2012  /   Comments Off on ‹‹ማለፊያ መደሪያ አይሆንም…›› ግሩም ተ/ሀይማኖት

    Print       Email
0 0
Read Time:19 Minute, 24 Second
      ዘንድሮ መታዘብ ከምንችለው በላይ የምንታዘበው ነገር ገጥሞናል፡፡ እንደ እባብ ቆዳቸውን ሸልቅቀው የሚቀይሩ፣ እንደ እስስት የሚለዋወጡ የቀበሮ ለምድ የለበሱ ባህታዊያንን መለየት ችለናል፡፡ ተቃዋሚ ነኝ ብሎ ሲያቅራራ የከረመ፣ ካለፈ ካገደመው ጋር ሰጋጁ ሁሉ በጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ለምዳቸው ተገፎ እርቃን ሆነው ታይተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹‹ቆጨኝ›› ብላ ያቀነቀነችውን ድምጻዊ የቆጫት ምኑ እንደሆነ ለማወቅ ፍንጭ አይተናል፡፡ በሀሳቧ ተጉዛ ቀበቶ ላይ ደርሳ ስለቀበቶ አውርታናለች፡፡ በየቦታው የታየው ጉድ ነው፡፡ እዚህ የመን እንኳን ተቃዋሚ ነን ብለው፣ ያለ እኛ ፖለቲካ አዋቂ ያሉበትን ቆርፋዳ ትንተና የሚግቱን፣ የስደተኛውን ኮሚቴ ካልመራን፣ ድምጽ የምንሆነው እኛ ነን የሚሉ ሁሉ እጅ ሲሰጡ አይተናል፡፡ ተቃዋሚ ነን ለእኛ ፓርቲ አባል ሁኑ ሲሉ የነበሩ ኤምባሲ ሄደው ሲያለቅሱ ካላለቀሳችሁ ብለው ሲጎተጉቱን አስተውለናል፡፡ ይህን ማድረግ መብታቸው ነው፡፡ ችግሩ አላማቸው የትኛው እንደሆነ ግራ ገብቷቸው ሰዉን ግራ ማጋባታቸው ነው፡፡  አፋኝ፣ ጨቋኝ ነው ባሉበት አንደበታቸው ያለ እሱ ለኢትዬጵያ…ሲሉ ‹‹እንክርዳድ እንክርድድ የተንከረደደ ስንዴ መስሎ ገብቶ ስንቱን አሳበደ…›› የሚለው የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን አስታወሱን፡፡
   በወቅቱ ጉዳይ ላይ አንድ ደቡብ አፍሪካ ካለ ጓደኛዬ ጋር ስናወራ ተቃዋሚ ነን ብለው ለተቃውሞም ለድጋፍም ስለሚያጨበጭቡ በማጨብጨብ አላማ ተጠማጆች አወጋኝ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ስላሉ አላማቸው ማጨብጨብ ስለሆነ ፖለቲከኞች ሲያወራኝ በሁሉም የደረሰ ነውና ብዬ አሰፈርኩት፡፡ እነሆ፡-
       ድሮ የሆነ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ‹‹ማለፊያ /መንገድ/ መኖሪያ አይደለም›› ይለኝ ነበር፡፡ እውነታው የተገለጸልኝ አሁን ነው፡፡ የሰሞኑ የሀገራችን ሁናታ ሲንቱን እንድታዘብ አደረገኝ መሰለህ፡፡ እዚህ ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ‹‹ኢሳት›› የገቢ ማሰባሰቢያ አዘጋጅቶ ነበር፡፡  ብዙዎች በቦታው በመገኘት ለኢትዮጵያ መልካም ዘመን እንዲመጣ መንግስትን በመቃወም ድምጽ አሰምተዋል፡፡ ብዙ ቅስቀሳዎች እና የኢሳትን አላማ የሚያስረዳ ትንታኔዎችን በአርቲስት ታማኝ በየነ ተደርጎ ነበር፡፡ በቦታው ባልገኝም ከብዙዎች የሰማሁት ቅስቀሳ፣ በቪዲዮ የተቀዳውን በሲዲ ሙሉ ፕሮግራም አይቼዋለሁ፡፡ በአዳራሹ የነበረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያኮራል፡፡ ይበል ያሰኛል፡፡ እዚህ ሀገር በመቆየትም ብዙዎቹን በአይን አውቃቸዋለሁ፡፡ አብዛኛዎቹም አልባሳቶቻቸው ሀገርን የሚያስታውሱ እና ወቅታዊውን መንግስት የሚቃወም በመርህ ቃል ደረጃ ‹‹በቃ!!..›› የሚል የተጻፈበት ቲ-ሸርት አድርገዋል፡፡ ሁሉም ነገር በመግባባትና በመተባበር ለኢትዮጵያ መፃዒ ነጻነትን ለማምጣት በገንዘብ፣ በእውቀት በሁሉ አስፈላጊ ነገሮች እንደሚረባረቡ ቃል ተገብቶ መንፈሱን እንደጠበቀ ዝግጅቱ ተጠናቀቀ፡፡
         አሁን ደግሞ ጆሀንስበርግ ያየሁት ነገር ባለፈው የኢሳት ገቢ ማሰቢያሰቢያ ፕሮግራም ላይ ከነበረው መንፈስ ጋር ተጋጭቶብኛል፡፡ በፍጹም መንፈስ የተቃረነ ሆነብኝ፡፡ እውነት ነው በሰው ልጅ ማንነት ውስጥ መፈለግ ደግሞም የፈለከውን የማድረግ ተፈጥሮዋዊ እውነት አለ፡፡ ህያው ቃሉ ‹‹..ሰው በልቡ እንዳሰበው እንደዛው ነው፡፡..›› እንደተባለው ማናችንም ከዚህ መሪ ቃል እውነት መዝለል አንችልም፡፡ ይሄ ሆኖ ሳለ በዛን እለት ያየሁዋቸው በጠ/ሚኒስትር መለስ ሞት ሀዘናቸውን ለመግለጽ በዋና ከተማዋ ፕሪቶሪያ በሚገኘው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ለመሄድ በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡  ማንኛውም ሰው እንደ ሰብዓዊ ፍጡር በሞት ሲለየን ሰው የሆነ ሁሉ ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ፣ ዜግነት ሳይጠይቅ ማዘኑ አይቀርም፡፡ በሰውኛ አይን ካየነው የሰው ሞት በራሱ ያሳዝናል፡፡ ምክንያቱም መልካም እና በጎ መስራት ሳያቅተን ክፋትን፣ በራስ ላይ ሊደረግብን የማንወደውን በሌሎች ላይ እያደረግን ሳናስበው እውነተኛውን የሞት ቲኬት በእጃችን ይዘን መዞራችንን አለማስተዋላችን ነው፡፡ እኔም በዛን ወቅት ያየሁት ነገር እጅግ አድርጎ አሳዘነኝ፡፡
     በአንድ ወቅት ጠ/ሚኒስትር መለስ ‹‹..አላማው ምንም ይሁን ምን አላማ ያለው ሰው አከብራለሁ..››ያሉትን አባባል ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ ታዲያ ዛሬ ጠ/ሚኒስትሩ ለአንዲት ሰከንድ ተመልሰው ማየት ቢችሉ ያሉት ነገር እንዴት እንደተጣረሰ አይተው ያዝናሉ፡፡ አላማ ያለው ሰው ቢፈልጉ አለመኖሩን ይረዳሉ፡፡  ሰዎቹ ግማሾቹ በኢሳት ገቢ ማሰባሰቢያ ላይ ‹‹በቃ!!..››  የሚለውን ቲ-ሸርት የለበሱ ሲሆኑ ግማሾቹ ደግሞ ገዢውን ፓርቲ ሲያንቋሽሹ የነበሩ ተቃዋሚ መሳይ የውስጥ አርበኛ አይነት መሆናቸውን ሲታዘቡ አላማ ያለው እንዳልተከተላቸው ያውቁ ነበር፡፡ አሽቃባጮቹ ግን ያኔ በለበሱት ‹‹በቃ!!..›› የሚለው ቲ-ሸርት ላይ ከፊቱ ‹‹አል››…..ከኋላው ‹‹ም›› የሚለውን ጨምረውበት ‹‹አልበቃም..›› ብለው አስርተው ቢለብሱት ያምርባቸው ነበር፡፡ ገና ነገም የሚመጣ ካለ ተቀብለው ይገለበጣሉ እና ለእንሱ ገና ነው አልበቃም፡፡ ሲገለባበጡ ይኖራሉ፡፡
      ያልገባኝ ነገር ያኔ በቃ!! የሚለውን ቲ-ሸርት የለበሱ እለት የጠ/ሚኒስትሩ ጀግንነት አልታያቸውም ይሆን? ወይስ በቃ ያሉት ጀግንነታቸውን ይሆን? ድጋፋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አላማቸው ግን ለራሳቸውም የገባቸው አይመስለኝም፡፡ ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት ከሄድን አላማቸው ለሌሎች ግራ ካጋባ አናከብራቸውም፡፡
    መናገር፣ መጻፍ፣ መቃወም፣ መደገፍ..ሁሉም አላማ አላቸው፡፡ አማራጭ የላቸውም፡፡ በአንድ ልብ ውስጥ ግን ሁለት የተለያዩ ሃሳቦችን መደገፍና መቃወምን ማስተናገድ ግራ ያጋባል፡፡ የሰው ልጅ አቋምም አይደለም፡፡ ቀድሞውኑ እንደዚህ አይነት መረዳት ጥያቄም ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ ሁሉ መጀመሪያውኑ ዝም ማለት ወደ አንድ ጎን ያራምዳል፡፡ ‹‹..ዝምታም እንደ አንድ ተቃውሞ ነው፡፡..›› ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ነበሩ፡፡ እራሳቸው የተናገሩትን አንዳንዴ  መጠቀሜ ሰዎቹ የያዙት ሀሳብ በአንድ ልብ ውስጥ ሁለት አይነት ሊያቀነቅኑ መሞከራቸው ከአባባሉ ጋር ምን ያክል የተጣረዘ እንደሆነ ለማሳየት ብዬ ነው፡፡ ከእነሱ ለእነሱ እንደማለት ነው፡፡ እኔማ ራሳቸውን ከራሳቸው ሰዎች አባባል  እየተነሱ ማየትም መታዘብም ጥሩ ነው ብዬ ነው፡፡ የትግራይ ተወላጅ መሆን፣ የህወሀት አባል መሆን….የመሪው ፓርቲ አባል መሆን ማለት ብቸኛው እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ማለት አይደለም፡፡ እነዚህን ሆኖ ለመገኘት ግን የግድ አላማ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ የምናያቸው ሰዎች ደግሞ አላማቸውን ያየነው ነው፡፡ አቋም ለመያዝ በነገሮች መውጣት መውረድ የማይናወጥ በሰዎች አንደበተ ርዕቱነት የማይሸራረፍ ቶሎ የማይቀልጥ አለት ልብ ያስፈልጋል፡፡
      እዚህ ደቡብ አፍሪካ እንዳየሁት በሶስት ወራት ድጋፍና ተቃውሞ ሲሰጡ አላማቸውን በማጣት እና በማግኘት ያልተፈተሹ ፖለቲከኛ መሳይ አስመሳዬች ኢትዮጵያችን እስከመቼ አዝላቸው እያበሰበሱዋት ይኖራሉ እላለሁ፡፡ ይህን ሳስብ እነዚህ ሰዎች ‹‹ማለፊያ መኖሪያ አይደለም..›› የሚለውን አባባል አልሰሙት ይሆን? ያሰኘኛል፡፡ ወይም ሲያምታቱ ተምታቶባቸው ማለፊያቸውን እና መኖሪያቸውን አለዩ ይሆናል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የራሳቸው የሰሩዋቸው በጎም መጥፎም ስራዎች አሉ፡፡ ታሪክ ያኖራቸዋል፣ ይፈርዳቸዋል፡፡ ለሁሉም ወቅት አለው፡፡ አሁን የተሰራውን የጨበራ ተስካርም ጊዜ ይፈታዋል፡፡ ይህን ለማለት ያስቻለኝ የታዘብኩትን ብዙዎች ይወቁት ብዬ ነው ያወራሁህ፡፡ ብዙ ሰው ሲሰማ ብዙ ሰው ይድናል የሚል መረዳት አለኝ፡፡ የዛሬ ኢትዬጵያችን ችግር የአላማ መምታታት ነው፡፡ ይሄ ክፉ ፈውስ የሚያስፈልገው በሽታ ነው፡፡ ሌላው እነዚህን ባለሁለት አላማዎች ያፈራች ሀራችን አየር መንገድ ባለፈው ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሰራውን ዜግነት የሚያጎድፍ ድርጊትም ወዳጄ ነግሮኝ ስለነበር ላውራችሁ፡፡
ኢትዮጵያችን የውጭዎች ወይስ የእኛ?   
     ጽሁፉን የላከልኝ ወዳጄ ‹‹ኢትዮጵያችን የጥቂቶች ወይስ የብዙዎች›› በሚል ርዕስ ነበር የላከልኝ፡፡ ሳየው ግን ከሀገሩ ዜጋ ይልቅ ለሌላ ክብር የሰጠ ጉዳይ ስለሆነብኝ ቀየርኩት፡፡
     ባለፈው ሳምንት በቀድሞው ጆሀንስበርግ ኢንተርናሽናል በአሁኑ ኦሊቨር ታምቦ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ እንደሚዘገይ ለመንገደኞች ይነገራል፡፡ ለወትሮው ከምሳ በኋላ 7፡00-8፡00(እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር) በረራውን የሚያደርገው የዛን እለት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ሊያዘገይ እንደሚችል ተነገራቸው፡፡ ችግሩ ግን አልታወቀም፡፡ አየር መንገዱ መንገደኞችን ስብስቦ ለእራት መመገቢያ በግሩፕ ከፍለው /መድበው/ ለየግሩፑ 250 የደቡብ አፍሪካ ገንዘብ መደቡ፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን ከአየር መንገዱ ደረጃ ጋር የሚቃረን እና አሳፋሪ ጭምር ነው፡፡  በኢንተርናሽና ደረጃ የምግብ ዋጋ 50 ዶላር በሆነበት ወቅት በግሩፕ ከአራት ሰው በላይ እየመደቡ ያደሉት ገንዘብ አሳፋሪ የሆነው ለኢትዮጵያዊያኖች ብቻ ነው፡፡ ለሌሎች የውጭ ዜጎች የተለየ ነበር፡፡ ይህ በመድሎ የታጠረ ዜግነትን ያወረደ አሳዛኝ ድርጊት ነበር፡፡ ብሎኛል፡፡ እዛው ሀገር ውስጥስ ኢትዮጵያችን ገንዘብ ያላቸው ሆና የሚታይ ጉዳይ አይደለ? ክብር ለዜጋ ቢሰጥማ ስንቱ ገንዘብ አዝሎ በመጣ የውጭ ዜጋ ኢንቨስተር ታፔላ ከእርሻ ቦታው እና መኖሪያው ባልተፈናቀለ፡፡ ለዜጋ ክብር ቢሰጥማ ለውጭ ባለሀብት እየተባለ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ቦታዎች ውዝግብ ባላስነሱ ነበር፡፡
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 11, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 11, 2012 @ 6:14 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar