www.maledatimes.com ኢትዮጵያ ከ ሱዳን – ታሪክ እና የእግርኳስ ተቀናቃኝነት ሲዳሰስ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ኢትዮጵያ ከ ሱዳን – ታሪክ እና የእግርኳስ ተቀናቃኝነት ሲዳሰስ

By   /   September 14, 2012  /   Comments Off on ኢትዮጵያ ከ ሱዳን – ታሪክ እና የእግርኳስ ተቀናቃኝነት ሲዳሰስ

    Print       Email
0 0
Read Time:18 Minute, 29 Second
source http://www.total433.com the web site founder and writer
 

በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚጫወቱት የኢትዮጵያ እና የሱዳን ብሄራዊ ቡድኖች

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የቀሩት ከሱዳን ጋር የሚያደርጋቸው ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ብቻ ናቸው። ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ካርቱም ላይ የመልሱን ደግሞ አዲስ አበባ ላይ የሚያደርጉ ሲሆን በተለይ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እ.አ.አ ከ1982 ዓ.ም በኋላ ወደአፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ የሚያስችለው አጋጣሚ በመሆኑ ጨዋታው ወሳኝ ነው። በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚሰለጥነው ቡድን ከሜዳው ውጪ በቅርቡ ባደረጋቸው የአለም እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች አስደናቂ ብቃቱን ያሳየ በመሆኑ ምን አልባት በካርቱሙ ጨዋታ የተሻለ ውጤት ይዞ ወደአዲስ አበባ ለመመለስ እንደሚችል የሚጠቁሙ ግምቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሰጡ ነው።

ለመሆኑ ሁለቱ የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽንን ከግብጽ ጋር በመሆን የመሰረቱት ሱዳን እና ኢትዮጵያ በእግርኳሱ ምን ያህል ጊዜ ተገናኝተዋል? ያስመዘገቧቸው ውጤቶችስ? በዚህ ጽሁፍ የሁለቱን ሀገሮች በእግርኳሱ የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ መነሻ በማድረግ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

የኢትዮጵያና ሱዳን እግርኳስ ብሄራዊ ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪካቸው የተገናኙት እ.እ.አ ህዳር 16 ቀን 1956 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ሲሆን በጊዜው በአሸናፊነት ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ነበር። ጨዋታውን ኢትዮጵያ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።

በግንቦት ወር 1959 ዓ.ም በተካሄደው የሁለተኛው አፍሪካ ዋንጫ ሁለቱ ሀገሮች ለሁለተኛ ጊዜ በታሪካቸው የተገናኙበት ውድድር ነበር። በካይሮው አል-አህሊ ስታዲዬም 40 ሺህ ተመልካች ተገኝቶ በተከታተለው በዚህ ጨዋታ የሱዳን ብሄራዊ ቡድን የኢትዮጵያ አቻውን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸነፈ።

ከዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ሰባት ወራት ቆይታ በኋላ እ.አ.አ በ1959 ዓ.ም ካርቱም ላይ በአል-መሪክ ስታዲዬም በተካሄደው የኦሎምፒክ እግርኳስ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ሱዳን ኢትዮጵያን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ስታሸንፍ፣ ከአንድ ወራት ቆይታ በኋላ አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የመልስ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ሳይሸናነፉ 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።

ከዚህ በኋላ የሁለቱ ሀገሮች ብሄራዊ እግርኳስ ቡድኖች እንደገና ለመገናኘት ስድስት አመታት ያህል ወስዶባቸዋል። እ.አ.አ በ1965 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ባደረጉት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ባለሜዳው የሱዳን ብሄራዊ ቡድን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በሚያዚያ ወር አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የማጣሪያው መልስ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፎ እዳውን መልሷል።

እ.አ.አ በጥር ወር መጀመሪያ 1966 ዓ.ም ሁለቱ ቡድኖች አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያዩ፣ ከአንድ አመት ቆይታ በኋላ ካርቱም ላይ ባደረጉት ሌላ የወዳጅነት ጨዋታ 1 ለ 1 ተለያይተዋል።

በታሪክ መዝገብ ላይ ከሰፈሩት የሁለቱ ሀገሮች ብሄራዊ ቡድኖች ጨዋታዎች መካከል በአንድ ጨዋታ በርካታ ጎሎች የተመዘገቡበት እ.አ.አ የካቲት 26 ቀን 1967 ዓ.ም ካርቱም ላይ በአል-መሪክ ስታዲዬም በተደረገ የወዳጅነት ጨዋታ ሱዳን ኢትዮጵያን 5 ለ 3 በሆነ ውጤት ያሸነፈችበት ነው።

በጥር ወር 1969 ዓ.ም ሁለቱ ሀገሮች አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት ሌላ የወዳጅነት ጨዋታ እንግዳው የሱዳን ብሄራዊ ቡድን ባለሜዳው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ሲረታ፣ እ.አ.አ ግንቦት አራት ቀን 1969 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ሳይሸናነፉ 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። ከአንድ ሳምንት ቆይታ በኋላ ካርቱም ላይ በተካሄደው የአለም ዋንጫ ማጣሪያው የመልስ ጨዋታ የሱዳን ብሄራዊ ቡድን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

እ.አ.አ በ1970 ዓ.ም በሱዳን አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ውስጥ አብረው የተደለደሉት የኢትዮጵያ እና የሱዳን ብሄራዊ ቡድኖች ባደረጉት ጨዋታ ሱዳን ጋጋሪን፣ ሀሳቡ ኤል-ሻጋር እና ጃክሳ ከመረብ ባሳረፏቸው ጎሎች ኢትዮጵያን 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች። ከሁለት አመት ቆይታ በኋላ በ1972 ዓ.ም በተካሄደው የኦሎምፒክ እግርኳስ ማጣሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያዩ፣ በመልሱ ጨዋታ ካርቱም ላይ ሱዳን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።

እ.አ.አ በጥር ወር መጀመሪያ 1973 ዓ.ም ካርቱም ላይ በተካሄደ የወዳጅነት ጨዋታ ሱዳን ኢትዮጵያን 1 ለ 0 ከረታች በኋላ ሁለቱ ቡድኖች እንደገና የተገናኙት ከስምንት አመታት ቆይታ በኋላ በ1981 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ባደረጓቸው ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ነበር። በመጀመሪያው ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ሲለያዩ፣ በሁለተኛው ኢትዮጵያ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።

እ.አ.አ በ1983 ዓ.ም በኬኒያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገሮች የእግርኳስ ሻምፒዮና በምድብ አንድ የተደለደሉት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ባደረጉት ጨዋታ የሱዳን ብሄራዊ ቡድን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የበላይነቱን አሳይቷል።

እ.አ.አ ግንቦት 24 ቀን 1992 ዓ.ም ሁለቱ ቡድኖች አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ፍጹም የበላይነትን በማሳየት ሱዳንን 5 ለ 1 በሆነ ውጤት ከረታ በኋላ በዛው አመት ነሀሴ ወር ላይ ሁለቱ ቡድኖች ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አዲስ አበባ ላይ አድርገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሱዳን አቻውን 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

እ.አ.አ ግንቦት 26 ቀን 1993 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ሁለቱ ቡድኖች ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ከተለያዩ ከሁለት ወራት ቆይታ በኋላ ካርቱም ላይ ባደረጉት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ የሱዳን ብሄራዊ ቡድን የኢትዮጵያ አቻውን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የተገናኙት በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ1996 ዓ.ም በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ እ.አ.አ በጥር እና ሀምሌ ወሮች 1995 ዓ.ም በምድብ አራት ውስጥ ተደልድለው ባደረጓቸው ሁለት የደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ነበር። ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ሱዳንን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ስትረታ፣ በመልሱ ጨዋታ ካርቱም ላይ ሱዳን ኢትዮጵያን 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።

እ.አ.አ በ1999 ዓ.ም በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገሮች የእግርኳስ ሻምፒዮና በምድብ ሶስት ውስጥ የተደለደሉት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያለግብ በአቻ ውጤት ሲለያዩ፣ በመጋቢት ወር 2000 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ኢትዮጵያ ሱዳንን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች። ከሁለት አመታት ቆይታ በኋላ ካርቱም ላይ ሁለቱ ቡድኖች ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ሱዳን ኢትዮጵያን 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ስትረታ፣ እ.አ.አ በ2005 ዓ.ም በህዳር ወር የካርቱሙ አል-መሪክ ስታዲዬም  ላይ ኢትዮጵያ ሱዳንን 5 ለ 1 በሆነ ውጤት የረታችበት ጨዋታ በአስደናቂ ውጤትነቱ ሲታወስ የሚውል ነው። ከሜዳው ውጪ የተጫወተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ይሄን የመሰለ አስደናቂ ውጤት ማግኘቱ በጊዜው ብዙዎችን አስገርሟል።

ይሄንኑ አስደናቂ ብቃት በመቀጠል በ2005 ዓ.ም በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግርኳስ ሻምፒዮና በምድብ ሁለት የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሱዳን አቻውን በአማሆሮ ስታዲዬም ገጥሞ በሰብስቤ ሸገሬ ሁለት ጎሎች እና በአንተነህ አላምረው አንድ ጎል 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እ.አ.አ በ2005 ዓ.ም የተካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገሮች ሻምፒዮና የዋንጫ ባለቤት መሆኑ ይታወሳል።

ሱዳን እና ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ የተገናኙት እ.አ.አ በ2007 ዓ.ም በታንዛኒያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገሮች ሻምፒዮና ሲሆን፣ በምድብ ሶስት የተደለደሉት ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን ያለግብ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። የሱዳን ብሄራዊ ቡድን የዚሁ ሻምፒዮና ዋንጫ ባለቤት በመሆን አጠናቋል።

እ.አ.አ 2011 ዓ.ም በታንዛኒያ አስተናጋጅነት የተካሄደው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገሮች የእግርኳስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያና ሱዳን በቅርቡ ከሚካሄዱት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዊች በፊት እርስ-በርስ ያደረጉት የመጨረሻ ጨዋታ ነበር። በምድብ ሶስት ውስጥ የተደለደሉት የሁለቱ ሀገሮች ብሄራዊ ቡድኖች ህዳር 28 ቀን ባደረጉት ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ለመሆኑ በሁለቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ማን አሸንፎ በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ይሳተፋል? አብረን የምናየው ይሆናል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 14, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 14, 2012 @ 5:44 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar