www.maledatimes.com በህይወት የምትገኙ ባለዕዳ ናችሁ፡፡ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በህይወት የምትገኙ ባለዕዳ ናችሁ፡፡

By   /   June 7, 2014  /   Comments Off on በህይወት የምትገኙ ባለዕዳ ናችሁ፡፡

    Print       Email
0 0
Read Time:20 Minute, 48 Second

ይድረስ ለጋሽ እያሱ አለማየሁ

ከአዲስ አበባ

ከለማ መርሻ

lemmamersha@gmail.com

ሰሞኑን ማርታ ተስፋዬ የምትባል የፌስ ቡክ ጓደኛዬ “እያሱ አለማየሁን እከሳለሁ” በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ በፌስ ቡክ ገፆ ላይ ማስነበቧን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች ሲስተናገዱ ሰንበተዋል፡፡ መልእክቱ አንተንና አንተን የመሰሉ የእዛን ዘመን ትውልድ ያውቃሉ የተባሉ የታሪክ ተጋሪዎችን ይመለከታል የሚል ይዘት ስለነበረው “ኢሕአፓና ታሪኩ” ስትል የፃፍከውን ምላሽ አነበብኩ፡፡ እርሷም በምላሽህ መደሰቷን በፌስ ቡክ ገፃ ላይ መልሳ ፅፋ ተመለከትኩ፡፡ ይሁን ጥያቄዎቿን ብጋራም ደስታዋን መጋራት ሳልችል ቀረው፡፡ ምክንያቴም እንደሚከተለው ነው፡፡

እርግጥ ነው በእኔና በአንተ እድሜ፣ አውቀትና አስተሳሰብ መካከል በጣም የተራራቁ ልዩነቶች እንዳሉ ስለማውቅ ነው ጋሽ እያሱ ብዬ መጀመሬ፡፡ ከዛም አልፎ አንተንና የአንተን ሰዎች ለተሻለች ኢትዮጵያ ያደረጋችሁትን መራራ ትግል በተወሰነም ደረጃ ቢሆን  በማንበቡና በመስማት የማደንቃችሁ፣ በተወሰነም ደረጃ ባለኝ እውቀትና አቅም የምወቅሳችሁ ናችሁ፡፡

የኢሕአፓ ታሪክ የአንድ ቡድን፣ ግለሰብ ሀ ወይም ለ፣ የአንጃና የክሊክ፣  ሳይሆን በርካታ ወጣቶች ነፃነታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ጊዜቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ብሎም በስቃይ የታጀበ ህይወታቸውን የሰውበት ድርጅት መሆኑ ሁሉንም የሚያስማማ ስለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ እስካሁንም ድረስ የእዚችን ሀገር ህዝብና አመራር አስተሳሰብና እድገት የለወጠ ትውልድ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በተለይም ደግሞ ድርጅቱ ይከተለው በነበረው ስትራቴጂ ምክንያት ታሪኩ በትክክል በገለልተኛ ወገን ሳይዘገብ በመቆየቱ ለተለያዩ የታሪክ ውዥንብሮች፣ አለመግባባቶችና ግርታዎች መፈጠር አይነተኛ ምክንያት ሆነው ይታያሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ነፃነታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ጊዜቸውን፣ ገንዘባቸውን ብሎም በስቃይ የታጀበ ህይወታቸውን የሰውበት ድርጅት ከመሆን ዘሎ  የአጥፊና አልሚ፣ የአንጃና የክሊክ፣ የኮናኝና ተኮናኝ ድርጅት ሆኖ በዚህኛው በተለይም በእኔ ትውልድ ውስጥ ድርጅቱ ያለው ምስል የፀለምተኝነት፣ የደም፤ የመጠፋፋት፣ የአውዳሚነትና እኔ ብቻ ልደመጥ አመለካከት ያለው የሚል ምስል ተቀፅላዎች ተቀርፆበት ይገኛል፡፡

ለዚህም ይመስለኛል አንድ እንደወቅቱ የድርጅት መሪነትህ፣ እንደቀድሞ የታሪክ ተጋሪነትህ የፌስ ቡክ ወዳጄ “እያሱ አለማየሁን እከሳለሁ” ስትል በህይወትም  በአካል ሆነ በመንፈስ ለትግሉ የከፈሉ ታጋዮች ስም ሃላፊነት እናዳለባችሁ ለማስገንዘብ አቤት ያለችው፡፡ ሌሎቹ እርሷ ያነሳቻቸው ሃሳቦችን ሙሉ ለሙሉ ባልስማማባቸውም ለዚህ ለእኛ ትውልድ የእናንተ ትውልድ በተለይም ደግሞ እንደ ድርጅት ታሪኩን ከትቦ ፅፎ ማስተላላፍ ይጠበቅበት ነበር የሚለውን ሃሳቧን ሙሉ ለሙሉ እጋራለው፡፡

ይሁን እንጂ የኢሕአፓ ታሪክ በሚል ርእስ ለዚህች ልጅና ለመሰሎቿ የሰጠኸው ምላሽ በተለይም ደግሞ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ያነሳሃቸው ነጥቦች ዙሪያ ጥቂት ነገሮችን ማለት እንደሚገባኝ ስለወሰንኩ የሚከተለውን ለማለት ወደድኩ፡፡ (በነገራችን ላይ ላንተ ካለን ክብርና ስም አንፃር የፅሁፍህን ወጥነትና ፍሰት በፍፁም ለመቀበል ከብዶኝ እንደነበር ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ አርግጥ ያ የተባ ብዕር የነበረው እያሱ አለማየሁ ነው ሳልል አለቀረውም፡፡)

  1. የፅሁፍ መጀመሪያ ታሪክ ሲባል ምንድነው የሚለው የሚለውን ጥያቄህን በማስቀደም ብትጀምርም ሳታብራራው ወያኔዎች የሚለው ወቀሳና ዘለፋፈ ውስጥ ትገባለህ፡፡  ታሪክ ለሚለው ስያሜ የሰጠህው  ማብራሪያ ግልፅ አይደለም፡፡ በመሆኑም አንተ አንሰተህ የዘለልከው ይህ የታሪክ ትርጓሜ ቀጥሎ ለማነሳቸው ነጥቦች እንደመንደርደሪ ስለሚገለግሉን ጥቂት መዝገበ ቃላዊ ትርጓሜ ለማስፈር እሞክራለው፡፡  በቅርቡ በባህሩ ዘርጋው ግዛው የታተመው ዘርጋው ከፍተኛ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ታሪክ የሚለውን ሲተረጉመው ”በጊዜ ቅደም ተከተል ተዘርዝሮ በሰዎችና በተፈጥሮ አካባቢ መካከል የነበሩ መስተጋብሮች ውጤት የሆ ድርጊት ሁኔታዎች በቦታና በጊዜ ሸንሽኖ በተጨባጭ መረጃ በማጥናትና በማገናዘብ የሰዎችን ያሉ ተግባራት የሚያብራራ የእውቀት ዘርፍ“ ብሎ ሲተረጉመውም ታሪክ ፀሐፊ “የሀገርን፣ የህዝብን፣ የመንግስትን፣ የመሪዎችን ክንዋኔ እያጠና እየመረመረ ሳያዛንፍ መዝግቦ አጠቃላይ ገፅታውን የሚያሳይ ባለሙያ” ሲል ይተነትነዋል፡፡
  2. ታሪክ በተለያዩ  ሰዎች፣ አመለካከትና የአፃፃፍ ስልቶች ሊፃፉ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የፖለቲካ ትግል ውስጥም ሆነ በሌሎች ታሪክ አፃፃፍ ውስጥ የምናገኛቸው አውነታዎች ናቸው፡፡  ልጅቷም ሆነች እኔ ጥያቄያችን አንተ እንደምትለው “ወያኔ ስለፃፈው የተሳሳተ፣ የተበረዘ እንዲሁም ተጣረሰ” ታሪክ አይደለም፡፡ የወያኔ ታሪክ ምን አልባትም ከኢሕአፓ የታሪክ ክፍል ውስጥ አንዱ ሊሆን ይችል ይሆናል እንጂ ከኢሕአፓ ከመሰለ ትልቅ ድርጅት ውስጥ የሚሰራው፣ የሚዶልተውና የሚሰነቅረው ምንም ነገር የለም፡፡ ምን አልባትም ይህ አይነት አመለካከት ያመጣብህ አሁን ያለውንና ያለህበትን ነባራዊ ሁኔታ እየተመለከትክ ሳይሆን አይቀርም ብዬ እገምታለው፡፡ ይሁን እንጂ የኢሕአፓ ታሪክ ወያኔ ላይ ብቻ የተንጠላጠለ ነው ብሎ ማመን በራሱ ታሪክን ማዛባት መስሎ ይሰማኛል፡፡
  3. አንድ መፅሐፍ ከተፃፈ መድረሻው የት ነው ሲባል አንባቢን ጋር መሆኑ አይካድም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ፀሐፊዎች ላጠፉት ጊዜ፣ ገንዘብና እውቀት በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ (የተሸጠውም መፅሐፍ ብዙን ጊዜ ይህንንም አይመልስም፡፡) ገንዘብ ቢያገኙ የቱ ጋር ተገቢነቱ እንደሚያጣ ለእኔ ግልፅ አይደለም፡፡ አዚህ ጋር ሁለት ነገሮችን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡  አንተን ራስህን ብትጠይቅህ ኢሕአፓን የመሰለ የመቶ ሺህ ወጣቶች ታሪክ ደም፣ እስትንፋስ፣ ትግል፣ ስቃይ የያዘ ታሪክ  ስንት መፅሐፍ ተፃፈ ብትባል ከአስርና ከአስራ አምስት በላይ መፅሐፍ መቁጠርህን እጠራጠራለሁ፡፡ ሁለተኛው ከዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ይህንን ታሪክ ምን ያህሉ አንብቦታል የሚለው ጥያቄ ሌላኛው ምላሽ የሚሻው ጉዳይ ይመስለኛል፡፡( ብዙዎቹ መፅሐፍት ግፋ ቢል ከአምስት ሺህ ኮፒ በላይ አይሸጡም በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ከተባለ ታውር ኢን ዘ ስካይ አስር ሺህ ኮፒና ፣የአሲባ ፍቅር 20 ሺህ ኮፒ፣ ምርኮኛ 40 ሺህ ኮፒ ይመስሉኛል፡፡) በነገራችን ላይ እናንተም ቢሆን የምትፅፉት ታሪክ በነፃ እንደማታሰራጩት ግልፅ ይመስለኛል፡፡ በጎ አድራጎት ድርጅት አልያም ስፖንሰር ካላገናችሁ በስተቀር፡፡ ስለዚህ ኢሕአፓ መፅሐፍት ንግድ ደርቷል መሰለኝ የሚለው አባባል ፍፁም የተሳሳተና የተዛባ አመለካከት ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ፀሐፍት ሲሉ እንደምንሰማውም የመፃፋቸው አላማ አንድም እናንተ በመሳሰሉ የትግሉ መሪዎች ሊደረግ የሚገባውን ታሪክን መፃፍና ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፉ ስራ ባለመፈፀሙ ታሪክ ለመከተብ በሌላ መልኩ  ካለባቸው የጓዶቻቸው ህይወት ባለህዳነት በትንሹም ቢሆን እፎይ ለማለት መሆኑን ነው፡፡
  4. ሌላኛው ጉዳይ ታሪክ አፃፃፍ ተበላሸ የሚለው አስተሳሰብህ ነው፡፡  ታሪክ ተበላሸ ብለህ ካመንክ ሃላፊነቱ የአንተና የጓዶችህ ጭምር ነው፡፡ ልክ ነው ያሉትማ ፅፈው እያስነበቡን ነው፡፡ አንተና አንተ መሰሎች ግን እስካሁን ባለው ሁኔታ ፀሐፊዎቹ ላይ በአብዛኛው አንዳንዴም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ አሉታዊ ዘመቻ ከማስተላለፍ የዘለለ  አንዳችም የተሻገረ ነገር ስታደርጉ አልተመለከትንም፡፡ ለዚህም ምስክሩ ጊዜና ተግባር ነው፡፡ አብዛኛው በአንተ እድሜ የሚገኙ ሰዎች ምንም ነገር ሳይሉ ወዲያናው አለም በመሄድ ላይ መገኘታቸው ግልፅ ነው፡፡ በዚህ አስተሳሰበህ ሌላው ወደ አህምህሮዬ የመጣው  የዲሞክራሲና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በተመለከተ ያለህ መርዕ ጥያቄ ውስጥ እንዳለ ነው፡፡
  5. ሌላኛው በጣም የሚገርመኝ ነገር የኢሕአፓ ታሪክ ላይ ፀሀፊ እንዲሆን የምትፈልገው “በትግሉ የተሳታፉ አባላት በተለይም አሁንም ስለድርጅቱ ቀና የሆነ አመለካከተ ያላቸው ናቸው፡፡” ስትል መስፈርትህን ታስቀምጣለህ፡፡ ድርጅቱ መልካም  ስምና ዝና ብቻ ቢኖረው ኖሮ እዚህ ደረጃ ላይ ይደርስ ነበር ብለህ ታምን ይሆን? አይመስኝም ምክንያቱም ድርጅቱ እንደ ተቋም መልካምና ጥሩ ጎን እንደነበሩት ሁሉ ሊስተካክላቸው የሚገባ ብርቱ መሪ የሚፈልጉ አንገብጋቢ ጉዳዮች እንደነበሩት የአደባባይ ሚስጥር ነበረና መስፈርቶችህ ሚዛናዊነት የሚጎለው አመለካከት ነው፡፡ ይህም ወገንተኝነት የታሪክ ድርሳን አፃፃፍ ደጋፊ መሆንህን ታሳየናለህ፡፡ በመሆኑም አንተም በወያኔ ቅጥረኞች የሚፃፉ ታሪኮች የሚለውን የድርጅት ስም ከመቀየር ውጪ ትርጉም የሌለው ታሪክ ማስተላለፍ ምርጫ ያላደረግህ ትመስላለህ፡፡  በሌላ በኩል ፅሁፍህ ላይ ከላይ ጀምሮ አንተም ከወገንተኝነት ላይ አለመዝለለህና እናንተም አካባቢ ቢሆን የሚፃፈው ታሪክ ትክክለኛ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆኑን ከላይ ያነሳሃቸውን ሁሉ የሚያፈርስ ሀሳብ በመደምደሚያህ ላይ “የኢሕአፓ ታሪክ እኔ ብቻ ልፅፍ አልችልም፡፡ ይልቁንስ ሁሉም በማን ያወራ የነበረ የየበኩሉን ቢፅፍ የተሟላ ታሪክ ሊፃፍ ይችላል፡፡”  ትልና ከላይ የወገርካቸውን ፀሃፊዎች ልክ መሆናቻውን አረጋግጠህ ያንተ ሃሳብ ልክ አለመሆኑንኑ በራስ ፅሁፍ ትነግረናለህ፡፡

ጋሽ እያሱ ኢሕአፓ ህይወታቸውን የከፈሉ ወጣቶች፣ አካላቸው፣ ስሜታቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ማንነታቸውን ብሎም ገበሬውን የገበሩለት እናም ዛሬም በህይወት የሚገኙ ታላቆቻችን ታሪክ ብዙ አልተባለም ከታሪኩ ባህርም በጭለፋ የተዘገነ መስሎ አይሰማኝም፡፡ ለዚህኛው አሁን በህይወት የምትገኙ ባለዕዳ ናችሁ፡፡ የትውልዳችሁ እዳ፡፡ የሞቱ ጓዶቻችሁ እዳ፡፡ እኔ እንደሁም ለአንተና ለተቋማችሁ በዚህ ዘመን የምመክራቸሁ ታሪካችሁ በበለጠ እንዲፃፍ የሞራል፣ የማሳተም ቢቻል የገንዘብ  ድጋፍ በማድረግ ታሪካችሁ ትውልድ ተሸጋሪ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡

ያለበለዚህ ለኢትዮጵያ ህዝቦችና አንድነት ያደረጋችሁት ትግል የትም ዘለል ሳይል ለዚኛውም ትውልድ በበጎም ሆነ በመጥፎ መማሪያነት ሳገለግል ከሁለተኛው የታሪኩ ባለቤት ካልሆነው አካል የመስማት አማራጭ ብቻ ይኖረናል፡፡ በመሆኑም በእኔ ትውልድ ውስጥ ላላችሁን ስም በሞት ለተነጠቁት ጓዶቻችሁና በህይወት ኖረው በቁጭትና በመንገብገብ ለሚያሳልፉ ግን እንደእናንተ አቅም ለሌላቸው የትውልድ ተጋሪዎቻችሁ ስትሉ ታሪካችሁን ፃፉ፡፡

 

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on June 7, 2014
  • By:
  • Last Modified: June 7, 2014 @ 12:15 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar