www.maledatimes.com “የመሬት ባላባቱ” ሚኒስትር!! ምስጢሩን ያጋለጠው መሃንዲስ የት ደረሰ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“የመሬት ባላባቱ” ሚኒስትር!! ምስጢሩን ያጋለጠው መሃንዲስ የት ደረሰ

By   /   September 20, 2012  /   Comments Off on “የመሬት ባላባቱ” ሚኒስትር!! ምስጢሩን ያጋለጠው መሃንዲስ የት ደረሰ

    Print       Email
0 0
Read Time:19 Minute, 28 Second

 

aby tsehaye the first dad of corruption

አቶ አባይ ጸሀዬ በዘመዶቻቸው ስም በርካታ መሬቶች መውስዳቸው፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ባስቀመጡት ሃላፊ አማካይነት በመሬት ንግድ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘታቸው፣ ህጋዊ ሰነድና ካርታ ያለው ቁልፍ ቦታ ከባለቤቱ ተነጥቆ ለእርሳቸው ዘመድ መሰጠቱ ሲረጋገጥ ምርመራው እንዲቆም መታዘዙ ታወቀ። በየክልሉ ተመሳሳይ ንቅዘት አለ።

በህዝብና በቦሌ ክፍለ ከተማ ሰራተኞች፣ እንዲሁም ለአብነት የተጠቀሱት ንብረታቸው የተወሰደባቸው ሴት ወ/ሮ ጉዳያቸውን የትኛውም ቦታ ሲወስዱ መጀመሪያ ቀጠሮ እንደሚሰጣቸው፣ በቀጠሮዋቸው ቀን ሲሄዱ ምን ምላሽ እንደማያገኙ ጠቅሰው  ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት የተጀመረው የምርመራ ስራ ይህንን ይመስላል።

ቀደም ሲል ተጠሪነቱ ለአቶ መለስ የነበረው የፌደራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና  ኮሚሽን መርማሪዎች አቶ አባይ ጸሃዬን “የመሬት ከበርቴው” የሚል ስም ሰጥተዋቸዋል። ስያሜውም የተሰጣቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ሲነግዱ ስለነበር ነው።

የኮሚሽኑ የጎልጉል ምንጭ እንዳመለከቱት አቶ አባይ ጸሀዬ መሬት ሲነግዱ እንደ ነበር የታወቀው በክፍለ ከተማው በተካሄደ ምርመራ ነው። በክፍለ ከተማው በጠራራ ጸሃይ የግለሰቦችን መሬት ሳይቀር እየቸበቸበ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ በደረሰው ተደጋጋሚ ጥቆማ መሰረት የሚመለከተው መምሪያ መነሻ ጥናት ያዘጋጅና ምርመራው እንዲጀምር ይታዘዛል።

በዚሁ መሰረት የኮሚሽኑ መርማሪዎች ስራቸውን ይጀምራሉ። የኮሚሽኑ ባለሙያዎች  ምርመራ እንደጀመሩ መሬት በህገወጥ መንገድ ሲቸበቸብ እንደነበር ይረዱና ከመሬት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ያሽጋሉ። የመሬት ልኬትም ሆነ ከመሬት ጋር የተያያዘ ስራ እንዳይሰራ ያግዳሉ። በተጨማሪም መሬት እየለኩ ሲሰጡ የነበሩ መሃንዲሶች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጎ ምርመራው በጥብቅ እንዲካሄድ ይደረጋል።

ክፍለ ከተማው ክልሉን ወደ ገጠር ቀበሌዎች እያሰፋ መሬት ይከልላል። መሬታቸው የተወሰደባቸው ደካማዎችን ቦሌ ክፍለ ከተማ ካሳ ለመውሰድ ሲንከራተቱ ማየት የተለመደ ነው። አራት ዓመት፣ አምስት ዓመት ከዚያም በላይ ካሳ ሳያገኙ የሚመላለሱ ደካሞች አሁን ድረስ አሉ። ባለንብረት ለንብረቱ ካሳ የሚከፍለው አጥቶ ይንከራተታል፤ መሬት የመንግስት እንደሆነ ያወጀው መንግስት በከፍተኛ ባለስልጣኖቹ አማካይነት መሬት አየር በአየር ይቸበችባል። ይህ የአሰራሩ ግድፈት ሲሆን ለአብነት የተጠቆመው ጉዳይ አስከፊነትና የወንጀሉ ርህራሄ አልባነት እዚህ ላይ ጎልቶ ይታያል።

አሳዛኝ የተባለው የምርመራ ውጤት ታሪክ የሚጀምርው እዚህ ላይ ነው። መሃንዲሶች በሙሉ ታስረው ተመረመሩ። ምርመራው በሙሉ ወደ አንድ ሰው ቢያመላክትም ያንን ሰው ደፍሮ የሚናገር ጠፋ። ይህን ጊዜ “ለምን” የሚል ጥያቄ ተነሳ። የመሬት አስተዳደር ሃላፊውና የክፍለከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ ጉዳዩ የማይመለከታቸው ተደርጎ መወሰዱ፤  መሬት በህገወጥ ስለመቸብቸቡ በቂ መረጃና ማስረጃ በቀረበበት ሁኔታ፣ መሬታቸውን በግፍ ተነጥቀው ለሌላ ሰው የተሰጠባቸው እንዳሉ ተረጋግጦ ሳለ ካርታ ላይ የሚፈርሙትና ለመሃንዲሶች ትዕዛዝ የሚያስተላልፉት የመሬት አስተዳደር እንዲታሰሩና እንዲመረመሩ አለመደረጉ በጓሮ ኮሚሽኑ የሚታማበት ጉዳይ ሆነ። “ጥርስ የሌለው አንበሳና የመለስ አሽከር” የሚለው የኮሚሽኑ ስም በስፋት ተነሳ!!

“ለፀረሙስና ኮሚሽን ሌላ ጸረ ሙስና ኮሚሽን” በሚል የክፍለ ከተማው ሰራተኛ የሆኑ ደብዳቤ በመጻፍ ወቀሳ ሰንዝረው ምርመራው በወጉ እንዲከናወን ጥቆማና አስተያየታቸውን ላኩ። አንዳንድ ስማቸውንና ማንነታቸውን የደበቁ ሰዎች ጉዳዩን ለግል ሚዲያና ለመንግስት መገናኛዎች እንደሚያቀብሉ ዛቱ። ማንም ምን ቢል የሚሰማም የሚደነግጥም ጠፋ።

ምርመራ ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ለአብነት የተቀመጠው ዛሬ ህንጻ በብድር ተገነብቶበት ከፍተኛ ኪራይ የሚሰበሰብበት ከመገናኛ ወደ ገርጂ በሚወስደው አዲሱ ጎዳና ዳር ላይ ያለ አንድ ቦታ ጉዳይ ሲጎተት ሚስጥሩን ገለጠው። የመረጃው ምንጭ እንዳስረዱት ምርመራውን የያዘው ባልደረባቸው እንደነገራቸው ምስጢሩ ሲገለጽ ማመን አቅቶት ነበር።

ለክፍለከተማው የመሬት አስተዳደር ሃላፊ ቅርብ ተጠሪ የሆነው መሃንዲስ ምርመራ ሲካሄድበት “እንግዲያውስ እውነቱ ይህ ነው” በማለት አብራራ። በግፍ የተወሰደው ከላይ የተገለጸው ቦታ የተሰጠው ለአቶ አባይ ጸሃዬ ዘመድ መሆኑን ይፋ አደረገ። መሬቱ የቀድሞው ባለቤቶች ለመሆኑ የሚገልጽ በቂ ማስረጃ እንዳለው ቢታወቅም አለቃው አዲስ የባለቤትነት ማስረጃ ቀደም ሲል እንደነበር ተደርጎ እንዲያዘጋጅ ባዘዘው መሰረት የሰው ንብረት አሳልፎ መስጠቱን አስታወቀ። ይህን ጊዜ ምርመራው ባስቸኳይ ወደ ሌላ መርማሪ እንዲዛወር ተደረገ።

የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደር ሃላፊ አቶ መሠረት የአቶ አባይ ጸሃዬ የቅርብ የስጋ ዘመድ ሲሆኑ፣ በእርሳቸው ትዕዛዝና አጽዳቂነት በክፍለ ከተማው በርካታ ቁልፍ ቦታዎች ለዘመድ አዝማድ በሽርክና፣ ለባለ ገንዘብ በሽያጭ እንዲዘዋወሩ መደረጉ በምርመራ እንደታወቀ አስቸኳይ መመሪያ ተላለፈ።

መመሪያው እስረኛው መሃንዲስ ባስቸኳይ እንዲለቀቅ፣ ምርመራውም እንዲቋረጥ የሚል ነበር። ከፍተኛ የሙስና ወንጀልና የስነምግበር ጉድለት መከሰቱን፣ በግፍ ንብረታቸውን ተቀምተው ባዶ እጃቸውን የቀሩ እንዳሉና፣ በማስፋፊያ ስም ቁልፍ ቦታዎች ከህግ ውጪ መተላለፋቸውን ይፋ ለማድረግ ሰፊ ጊዜ ወስዶ የተሰራው ስራ ሙሉ በሙሉ ይፋ ሳይሆን ተዳፈነ። የተልከሰከሰ የስራ ሪፖርት እንዲቀርብ ተደርጎ ፋይሉ ተዘጋ። ከእስር የተፈታው መሃንዲስም ደብዛ ጠፋ። የአገር ደህንነት ከበርካታ ተመሳሳይ ወንጀሎች ጋር ጉዳዩን እንደያዘው የጎልጉል ዘጋቢ አረጋግጧል።

የድርጊቱ ዋና ተዋናይ የአቶ አባይ ዘመድ እንኳንስ ሊታሰሩ በእድገት የከንቲባ ኩማ ደመቅሳ አማካሪ ሆነው አዲስ አበባ አስተዳደር ተመደቡ። ዋና ስራ አሰፈጻሚው የፌደራል ስራና ከተማ ልማት ሚኒስትር ውስጥ ከፍተኛ ሹመት ተሰጣቸው። በአሁኑ ወቅት የከንቲባው አማካሪ የሆኑት የአባይ ጸሃዬ ዘመድ መሬትን አስመልክተው ኪራይ ሰብሳቢነት ስለመስፋፋቱ ክፍለ ከተሞችን ሰብስበው ይሰብካሉ። ስለ ሙስና አደገኛነት በየመድረኩ እንዲያስተምሩ ተደረገ። ድርጊቱ በርካቶችን አስቆጣ። በርካታ የወቀሳ ደብዳቤ ለኮሚሽኑ ጎረፈለት። በአካል ቀርበው ምስክርነት የሰጡና ኮሚሽኑ ሊመሰርት አቅዶት ለነበረው ክስ ምስክር ለመሆን የተስማሙ ደነገጡ።

ጉዳዩ እንዲዳፈን ስለተደረገበት ምክንያት ሲያስረዱ “በየትኛውም ደረጃ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ በደህንነት ውስጥ ያሉ ባለስልጣናትና መካከለኛ ደረጃ ሃላፊዎች በግልጽ ሙስና ውስጥ መዘፈቃቸው በመረጃ ቢቀርብም ኮሚሽኑ እርምጃ የማይወስደው ሙስና አንዱ የስርዓቱ እድሜ ማራዘሚያ መንገድ በመሆኑ ነው” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

“ኢህአዴግን እያገለገሉ ያሉ ባለስልጣኖች ህወሃትን በሚገባ መከራከር የማይችሉትና በታዛዥነት እያጎበደዱ ለመኖር የሚገደዱት የገቡበትን የሙስና ማጥ ስለሚያውቁት ከተቃወምን እንታሰራለን” በሚል ፍርሃቻ መሆኑን የኮሚሽኑ ባልደረባ ለጎልጉል የአዲስ አበባ ምንጭ ተናግረዋል። ባለሙያው አያይዘውም “በአገሪቱ የተንሰራፋው ሙስና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፤ ከላይ እስከታች ተበለሻሽቷል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

“ባለሥልጣናትን በሙስና ማበስበስ” የስርዓቱ ዋንኛ የማኮሰሻና የማዋረጃ ስልት እንደሆነ የተለያዩ ማስረጃዎችን በማጣቀስ “አቶ መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ” በሚል ርዕስ ባቀረብነው ቃለ ምልልስ ማስነበባችን ይታወሳል። ኢህአዴግ ለትምህርት ውጪ አገር የላከቸውና ስማቸውን ለጊዜው መግለጽ ያልፈለጉት ተናጋሪ “ስርዓቱ በስብሷል” ባይ ናቸው።

“ባለኝ መረጃ መሰረት የኔ ስጋት እነዚህ ያለቀረጥ የሚነግዱ፣ ገንዘብ የሚያቀባብሉ፣ የገንዘብ ዝውውር ላይ የተሰማሩ፣ ድርጅት ያላቸው፣ በቅጽበት ተመንጥቀው ባለሚሊዮኖች የሆኑ፣ የባንክ ብቸኛ ተጠቃሚዎች፣ ሸቃጮችና አወራራጆች ከትንሽ እስከ ትልቅ ስራውን የሚሰሩት ከባለስልጣናት ጋር ነው። ከመከላከያ አመራሮች ጋር ነው። ከደህንነትና ከዋናው የስልጣን እርከን ጋር በመመሳጠርም ነው” በማለት ቃለ ምልልስ አድራጊው በውል የሚያውቁትን ተናግረዋል። አያይዘውም “ስርዓት ሲበሰብስ ልዩ ምልክቱ ትናንሽ መንግስታት ማቆጥቆጣቸው ነው። በኢህአዴግ መበስበስ አቶ መለስን ጨምሮ በርካቶች ይስማማሉ። ኢህአዴግ መዓዛውን አልቀየረም የሚሉት በአገሪቱ ድፍን ቆዳ ላይ የራሳቸውን መንግስት የተከሉ ተጠቃሚዎች ብቻ ናቸው። እነሱ ክሬሙን እየላሱ ስለሆነ የመበስበስ አደጋ አይታያቸውም። ስለመበስበስ ለማሰብም ጊዜ የላቸውም። የበሰበሰው ነገር ሲናድ የሚበላው ግን አስቀድሞ እነሱን ነው። ምክንያቱም አቶ መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ በጣም ትልቅ ነው” በማለት ፍርሃቻቸውን ይገልጻሉ።

የፌዴራል መንግስት የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና በገለልተኛ ወገን አስጠንቶ ያገኘውና ይፋ የተደረገው ውጤት አስደንጋጭ መሆኑ ይታወሳል። በዚሁ ጥናት መሰረት ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቶች፣ አጠቃላይ የፍትህ ተቋማትና ራሱ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ቀዳሚ ሙስና የተንሰራፋባቸው ተቋማት መሆናቸውን ማረጋገጡ፣ ተቋማቱም በጥናቱ ቅር መሰኘታቸውን በመግለጻቸው በዝርዝር ይቀርባል የተባለው ጥናት እስካሁን ይፋ ሊሆን አለመቻሉም ታውቋል፡፡

የፊታችን አርብ ቃለ መሃላ የሚፈጽሙት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ እንደ አቶ መለስ የጸረ ሙስና ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለእርቸው ስለሆነ አዲስ በሚያቋቁሙት ካቢኔ ውስጥ መካተት የሌለባቸውን የነቀዙ ባለስልጣናት ለመለየት ፋይላቸውን ከኮሚሽኑ መውሰድ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 20, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 21, 2012 @ 7:48 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With: ,

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar