ከአንበሳው ይብራ
“የማይጮሁት በአሉ ግርማን የበሉት ጅቦች”በሚል ርእስ አበራ ለማ ለጻፈው ፅሁፍ አንድ ማተቤ መለሰ የሚባሉ ሰው ከኖርዌይ የላኩት ምላሽ ፅሁፍ የሚያሳዝን ሆኖ አግኝቸዋለሁ ። አንደኛ አሳባቸው እርስ-በርሱ የተምታታ ፤ አንዴ ስለ አበራ ለማ በኖርዌይ ኑሮው የተገለለ ለመሆኑ ፤ ወይም ደግሞ ስለአበራ ለማ አዲስ አበባ መመላለስ ፤ ስለጅቦች ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስለጎጃሞች ፤ ስለአማርኛ ቅኔ አዋቂነት ፤ ስለህዝብ መዋረድ እና ስለመሳሰሉት አትተዋል ወንድሜ አቶ ማተቤ ። ካተቷቸው ነገሮች ሁሉ አሳፋሪውን ልንገርዎት ። አበራ ለማ “ጅቦች” ሲል የጻፈውን ቃል የተጠቀመበት ፤ እርስዎ እንዳሰቡት ጎጃሜ ወንድምዎትን ሙሉጌታ ሉሌንና እርስዎ እንዳሉት የጎጃምን ህዝብ ለማዋረድ ሳይሆን ራሱ ሙሉጌታ ሉሌ “ ጅብ ቲበላህ በልተኽው ተቀደስ” በሚል ርዕስ የጻፈውንና በኢንተርኔት የበተነውን ፅሁፍ ለመግለፅ የተጠቀመበት ነው ። ይህ የሚያሳየው ደግሞ በቁመናቸው ለታላቅነታቸው የተከራከሩላቸው የሙሉጌታ ሉሌን ፅሁፍ አቶ ማተቤ እንዳላነበቡ ነው ።
ሌላው አሳፋሪው አባባልዎ አማርኛ ሁለተኛ ቋንቋው የሆነው አበራ ለማ አማርኛን ለባለቅኔዎቹ ለናንተ በቅኔ ሊነግረን አይችልም ያሉት ነው ። አበራ ለማ እኮ በፅሁፉ ላይ ቅኔ አልተናገረም ። ግልፅ የሆነ ፅሁፍ ነው ያቀረበው ። አማርኛ ቋንቋ አንደኛውም ሆነ ሁለተኛ ቋንቋው ለሆነ ሰው ያልተወሳሰበ ፤ ሃሳቡ ሳይዛነፍ ኮለል ብሎ በጥራት አንዱ ከሌላው ተያይዞ የቀረበ ፅሁፍ ነው ያስነበበን ። አብባልዎ ግን ውስጡ የታመመ ነው ። እርስዎ ባልተፃፈ ነገር ላይ ተነስተው ፤ ራስዎ በፈጠሩት ጥርጣሬ ላይ ተመርኩዘው የቋንቋ ባለቤትነት መብት ለራስዎ ያጎናፅፋሉ ።( እኔ የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነኝ ፤) አማርኛ ሁለተኛ ቋንቋህ ነው ያሉት የአበራ ለማን ፅሁፍ ፣ እንደ አማርኛ ስነ-ፅሁፍ ፤ ምነው እኔም አማርኛ ቋንቋ ሁለተኛ ቋንቋየ ሆኖ እንደሱ በተዋጣልኝ የሚያሰኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ። በባዶ ሜዳ በትምክህት የተወጠረ ገለባ አስተሳሰብ አገራችንን ምን ላይ እንዳደረሳት ማስተዋል ይገባል ፤ አሳፋሪ ነው ያልኩትም ለዚህ ነው ።
ወደአገር ቢት ደርሶ መመለስም ወንጀል አይደለም ። ወደ አገር ቤት ሄዶ የመጣ ሁሉ ወያኔ ቢሮ እየገባ መመሪያ እየተሰጠው የሚመጣ ነው የምንል ከሆነ ፤ ባልተጨበጠ ነገር ላይ የቀረበ ባዶ ክስ ነው ። በዚሁ ክሳቸው ላይ ፤ የበአሉ ግርማን አፅም መታከክ ፤ “ከወያኔ ጋር ያለ የጥቅም ግንኙነት መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መስታወት ነው” ብለዋል ለመሆኑ ምን ማለት ነው ይህ አባባል ? ስለ በአሉ ግርማ መጻፍ ከወያኔ ጋር መስራት ነው ማለት ነው ? ወይስ የግል ጥላቻ የፈጠረው ጥላሸት የመቀባት አባዜ ነው ።
ባጠቃላይ ስለአቶ ማተቤ መለሰ ፅሁፍ የገባኝን ከራሳቸው አብባል ልጥቀስና ልዝጋው ። “አበራ ለማ በአስነዋሪ ምግባሩ በሚኖርበት ሃገር ተገልሎ ነው ያለው” ፤ ብለውናል ።
አበራ ለማ ተገልሎ የሚኖረው ብልግናን ፤ ተራ ምቀኝነትን ፤ አሉባልታን ፤ ባዶ ትምክህትን ፤ ጎጠኝነትን ፤ ጥላሸት መቀባባትን ፤ ስም ማጥፋትን ብሎም ነውርን ተጠይፎ ከሆነ ትክክል ነው ። ብልህና የራሱን የውስጥ መንፈስ ከዚህ ሁሉ ጉድፍ የተከላከለና ሰላሙን የጠበቀ ሰው ነው እላለሁ ። ከሰው ተገልሎ ስለመኖሩ ግን እጠራጠራለሁ ።
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ስለራሳችን ትልቅ ግምት እንሰጥና ማንነታችንን ማየት ይሳነናል ። አቶ ማተቤ ሃሳቤን በግልፅ በማስቀመጤ እንደማይቀየሙኝ ተስፋ በማደረግ ይህን ሃሳብ የምሰነዝረው ከራስዎ ፅሁፍ በመነሳት ነው ። እርስዎን ከመሰሉ ሰዎች መራቅ ከሰው መገለል እንዳልሆነና ሊገነዘቡት ይገባል ። አበቃ ።
ሌላዋ በአበራ ለማ ላይ ትችት ያቀረቡ ፀሃፊ አዜብ ጌታቸው የተባሉ ወይዘሮ ወይም ወይዘሪት ናቸው ። የረጅም ጊዜ የፅሁፍ ችሎታ ያላቸው ሰው እንደሆኑ አፃፃፋቸውና ብእራቸው ይመሰክራል ። ገና ከጅምራቸው ስለ አንዳርጋቸው ፅጌ በ99% ያሟሙቁና ፣ ይህ ሁሉ ሰው ዛሬ ስለአንዳርጋቸው ብቻ እየተናገረ ባለበት ወቅት ስለበአሉ ግርማ ማንሳት ተገቢ አልነበረም ሊሉን ይከጅላሉ ። አደራዋትን አዜብ ሆይ ስለአንዳርጋቸው በይደር ያቆዩትን ፅሁፍ ጨርሰው ያስነብቡን ፤ ታዲያ በአዜብ ስም መሆን ይገባዋል ። በሌላ በአርአያ ፤ በገብረመድህን ወይም በፀጋዬ መሆን የለበትም በአዜብ ብቻ ። ቃል ገብተውልናላ ! (በነገራችን ላይ እኔም የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እንደብዙው ኢትዮጵያዊ ወገን በአንዳርጋቸው ፅጌ ላይ የደረሰው ሁኔታ ልቤን ቅጥል እንዳደረገው ልገልፅልዎ እፈልጋለሁ።)
ወደተነሳንበት ወደ በአሉ ግርማ ጉዳይ እንመለስ ። ወረድ ይሉና አዜብ እንደገና ከዚህ እንደሚከተለው አስፍረዋል ፤ እጠቅሳለሁ “በአሉ ግርማን መዘከርህ ጥሩ ሆኖ ፤ ግን 30ኛ አመቱ ገና 8 ወራት እንደቀሩት እየታወቀ ዛሬ ለምን ዝክሩን ማውጣት አስፈለገ?” ይላሉ ። እኔ እንደገባኝ የእርስዎ አባባል ፅሁፎች ሁሉ ታሪካዊ ክስተቶች የተፈፀሙበትን ቀን ብቻ እየተጠበቀ መፃፍ ይኖርበታል ማለት ነው ? የሰው ልጅ የማሰብና የመፃፍ ነፃነትስ ! ፅሁፉንስ በፈለገበት ጊዜ የማውጣት መብትስ ! በርስዎ በአዜብ ቀመር መሄድ አለበት ? ለምሳሌ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የጀመሩት “የመብታችን ይከበር ትግል የአወሊያ ትምህርት ቤት የተዘጋበትን ቀን ብቻ እያስታወስን መፃፍ አለብን ማለት ይሆን ?
በዚህ ላይ ይህን ፅሁፍ 7አመት አቶ አበራ ለማ እጁ ላይ እንዳቆየው ተናግረዋል አዜብ ። ይቅርታ ይደረግልኝ አዜብ ብቻ እያልኩ በመፃፌ ፤ ወይዘሮ ይሁኑ ወይዘሪት ባለማወቄ ነው ። ለእርስዎ አቶ አበራ ነግሮዎት ነው ? ወይስ አቶ አበራን ይከታተሉት ነበር በወዳጆቹ በኩል ። የሚከታተሉት ከሆነና እንቅስቃሴውን ሁሉ መቆጣጠር ከፈለጉስ ለምን ? አዜብ ሆይ ! የአበራ ለማን መውጫና መግቢያ ይከታተሉ እንደነበር ደሞ የራስዎ ጽሁፍ ያጋልጣል ። ብርሃኑ ነጋ አባት ቤት “ፔን ኢትዮጵያን” አቋቁመሃል ። ተለጣፊም ነው ለማለትም ዳርዳር ብለዋል ። መቸም ሃሜትና ጥርጣሬ ለሚወደው አብዛኛው ሰው በር ገርበብ ገርበብ አድርገው ትተዋል ፣ መንጠቆው ከያዘ ።
በተጨማሪ በአበራ ለማ ላይ አዜብ የወነጨፉት ቀስት ዲያስፖራ ሆይ አበራ ለማ ሰድቦሃልና ይህን ሊንክ አዳምጥና ጥላው አይነት ነው ።
በዚህ ላይ ገነት አንበሴ አየለ ያቀረበችው ኮለኔል መንግስቱ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ በሜጋ አሳታሚ ድርጅት ስለታተመ ተወላግዶ ቀርቧልና ዋጋ የለውም አይነት ድምፀትም ተሰምቷል ከፅሁፍዎ ። ሜጋም አሳተመው ፤ ገነት አየለም አወላገደችው ፤ ዲያስፖራው አበራ ለማን ጠላው ፤ ወይ የብርሃኑ አባት ቤት ፔን ኢትዮጵያ ተቋቋመ የሚለው ጂኒ ጃንካ ሁሉ አበራ ለማ በማስረጃ ካቀረበው የበአሉ አሟሟት ጉዳይ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ። ጽለዚህ ስለበአሉ ግርማ አሟሟት የምታውቁትን ንገሩን ነው አቢዩ የአበራ ለማ ጥያቄ ! በነገራችን ላይ ገነት አየለ አንበሴ አወላገደችው ከተባለው የተሻለና የተቃና ማስረጃ እስከአሁን አለመቅረቡ ደሞ የሚገርም ነው ።
በዚህ ላይ አበራ ለማ አቶ አስፋው ዳምጤንም ጠይቀዋል የኩራዝ አሳታሚ ድርጅትን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩትን ።
የገነት አየለ አንበሴን መጽሃፍ ጠቅሰው መረጃቸውን አቅርበዋል ።
ኮለኔል መንግስቱም እንደዋሹ ጠቅሰው ጽፈዋል ፡ የሚያውቁትንም እንዲናገሩ ጠይቀዋል ።
*ሻምበል ፍቅረ-ስላሴንም በኛና አብዮቱ መጽሃፋቸው ላይ የሚያውቁትን ባለመግለጻቸው ወቅሰዋል።
ጋዜጠኛ ንጉሴ ተፈራም ስለ በአሉ ግርማ በሸገር ራዲዮ የተናገረው ሁሉ ተጠቅሷል ።
አቶ ሙሉጌታ ሉሌስ ቢጠየቁ ምን ችግር አለበት ፡ የሚያውቅቁት ነገር አለና ይንገሩን ነው የተባለው ፡፡ ውይስ አቶ ሙሉጌታ የሹም ዶሮ ናቸውና እሽሽ አትበሏቸው ነው ።
የሚገርመው እኮ ሙሉጌታ ሉሌ አንድም ፅሁፉ ላይ ኮለኔል መንግስቱ አስጠርተውኝ ከሳቸው ጋር ምሳ አልበላሁም ስለ በአሉ ግርማም አልተነጋገርኩም ብለው መልስ ሰጥተው አያውቁም ።
አዜብ ሆይ ! እርስዎን የመሳሰሉ የሙሉጌታ ሉሌ ወገኖች ባደረጋችሁት ውትወታ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ በቅርቡ ብቅ ማለታቸውን እኔም ብሆን አደንቃለሁ፤ ረበሽበሽ ያሏት ነገር ከልቤ ብታስቀኝም ።በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ልናገር ፤ በኢሳት ራዲዮ “የሰራዊቱ ድምፅ” በሚባለው በቅርቡ የተጀመረ ፕሮግራም ላይ ሙሉጌታ ሉሌ የቦርድ አባል ሆው ተሰይመዋል ፤ የራዲዮው ፕሮግራም በራሱ ግልፅ አይደለም ፤ የቀድሞው ሰራዊት ድምጽ ነው ወይስ የግንቦት 7 ሰራዊት ድምፅ ? የቀድሞ ሰራዊቱ ማህበር አመራሮች የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ይገልጻሉ ፤ ሙሉጌታ ሉሌ ደግሞ የሰራዊቱ አባል አይደሉም በእናንተ በወገኖቻቸው ተጨማሪ ውትወታ ይሆን እንዴ የሰራዊቱ ድምፅ የቦርድ አባል የሆኑት? በብእራቸው ብቻ ረበሽበሽ ያለው ወያኔ ደግሞ ከጦሩ ጋር ሲመጡበት እንዴት እንድሚብረከረክ እገምታለሁ በሃሳቤ ።
ሌላው ሙሉጌታ ሉሌ ዛሬ የኢሳት የፖለቲካ ተንታይ በመሆን ደመወዝ እየተከፈላቸው ከኤርትራ ጋር መስራት አማራጭ የሌለው መንገድ ነው እያሉ የፖለቲካ ትንተና እያደረጉልን ነው ። እንደእምነት ወስደውት ከሆነ አከብራለሁ ። ግን አይደለም ብየ እገምታለሁ ። ለዚህም እንደማስረጃ አድርጌ ለማቅረብ የምፈልገው ፤ አንድ ጋዜጠኛ በዋሽንግተን ዲሲ በሚተላለፍ አንድ ራዲዮ ላይ ፤ በሰጠው ቃለ ምልልስ ወቅት የታዘበውን በግልጽ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር ። (ጋዜጠኛው ከጦርነቱ በኋላ ወደአስመራ በመሄድ የመጀመሪያው ነበር ። ለነገሩ እስካሁንም ቢሆን ከሱ ሌላ ወደዚያ የሄደ ሙያዊ ጋዜጠኛ የለም ። ለምን እዚያ ሄዶ ያየውን ሁሉ እንደማይፅፍ ግን እስካሁን ግልፅ አይደለም ።) ይህ ጋዜጠኛ ከሙሉጌታ ሉሌ ጋር ዋሽንግተን ዲሲ አንድ ፓርኪንግ ካምፓኒ ውስጥ አብሮ ሰርቷል ። ጋዜጠኛው አስመራ ደርሶ ሲመለስ ስለ ኤርትራ ጉዞው ሙሉጌታ ሉሌን አነጋግሮቸው ነበር ። ሙሉጌታ ሉሌም በኤርትራ በኩል ምንም ነገር መስራት አይቻልምና ብትተወት ይሻላችኋል ፣ ብለውት እንደነበርና ዛሬ የኢሳት ደመወዝተኛ ሲሆኑ ደግሞ በኤርትራ በኩል የሚደረገው ትግል አማራጭ የሌለው ነው ሲሉ በመስማቱ ተለዋዋጭነታቸው አስገርሞት ሲናገር በቃለ-መጠይቁ ላይ ሰምቸዋለሁ ።
አዜብ ሆይ! አንድ ጥያቄ አቶ ሙሉጌታ ሉሌን ይጠይቁልን ። ይኽውም እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ የምንኖር ሰዎች የምናውቀው ነገር ስላለ ነው ። አቶ ሙሉጌታ ሉሌ እኮ ላለፉት አስር አመታት በላይ የጴንጤ ሃይማኖት ተከታይ ሆነው ስለነበር ነው ፅሁፍ አቁመው የነበረው ።ሃይማኖቱን ትተውት ወጥተው ነው እንደገና ወደ ፅሁፍ የገቡት ወይስ አሁንም እዚያው ናቸው? የእምነት ነፃነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ ለማወቅ ያህል ነው ። Public figure ናቸውና ስለሳቸው የማወቅ መብት አለን ።
አዜብ ሆይ! ሌላው ያስደነቀኝን ጉዳይ ልንገርዎት ። ኢትዮ ሜዲያ የአበራ ለማን ፅሁፍ በማውጣቱ የፃፏት ሃረግ እንደሚከተለው ይነበባል ።
“………………… ኢትዮ-ሚዲያም በአንድ ወቅት የማስታወቂያ ሚኒስተር ባልደረባ ስለነበር በአቶ አበራ ጽሁፍ ውስጥ የራሱ ፍላጎት በመንጸባረቁ ሊሆን እንደሚችል ገምተው ፤ እንደኔ እምነት ግን ኢትዮ-ሚዲያ ከራሱ ግለሰባዊ ፍላጎት በበለጠ ለሞያው ክብር የሚሰጥ ሰው ይመስለኛልና አውቆ ወይም ሆን ብሎ ሙያውን ያቀለለውን አበራ ለማን ለማሞካሸት ይነሳል ብዬ አልገምትም።” ብለዋል ።
ከንቱ ውዳሴና ማስፈራሪያ ቢጤ ቅላፄም አላት የላይኛዋ አባብል ። መጨረሻ ላይ ያስቀመጧት ሃረግ ግን በእጅጉ ተስማምታኛለች ።
“ውድ ወገኖቼ ዛሬ አብሮ መብላትና መጠጣትን ምክንያት አድርገው በሚንጸባረቁ የይሉኝታ ስሜት የምንሸበብበት፤ አይተን እንዳላየን የምናልፍበት፤ አውቀን እንዳላወቅን የምንሆንበት ግዜ ላይ አለመሆናችንን ልንረዳ ይገባል።………………” እኔም እስማማለሁ።
በዚሁ ላብቃ !
Average Rating