www.maledatimes.com ድምፅ አልባው አብዮት በኢትዮጵያ ራሚደስ 7/01/2005 - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ድምፅ አልባው አብዮት በኢትዮጵያ ራሚደስ 7/01/2005

By   /   September 20, 2012  /   Comments Off on ድምፅ አልባው አብዮት በኢትዮጵያ ራሚደስ 7/01/2005

    Print       Email
0 0
Read Time:28 Minute, 36 Second


ላለፉት ሁለት አስርት አመታት በህዝቡ ጫንቃ ላይ ተጭኖ የኖረውና በብልጣብልጡ መሪ መለስ ዜናዊ በተቀየሰው መስመር መሰረት ለመጪው አራትና አምስት አስርት ዓመታትም ይቀጥላል ተብሎ ሲፎክርበት የነበረው የትግሬ አፓርታይድ አገዛዝ ባልታሰበና ባልተጠበቀ መልኩ ፍሬን መያዙ ብቻም ሳይሆን ሿፈሪዎቹ ከመሪ ጨበጣው ገለል መደረጋቸው እውነትም ሀገሪቷ የድምፅ አልባ አብዮት እያስተናገደች መሆኗን የሚያሳይ ተጨባጭ ምልከታ ሳይሆን አልቀረም፡፡ ይህ አይታሰቤና ድንገቴ ክስተት ተጠራጣሪዎቹ እንደሚገምቱት አስቀድሞ በሚስጥር የተቀነባበረ (አንዳንዶች የጠቅላይ ሚኒስተሩ ምክንያተ- ቅስፈት የማይታዩ እጆች አሉበት ብለው እንደሚጠረጥሩት) አልያም እንደብዙዎቹ እምነት ‹‹የእግዚአብሔር ስራ›› ተብሎ ለጊዜው ሊታለፍ ቢቻልም ቅሉ ይህ አብዮት ተጀመረ እንጂ ተጠናቀቀ ብሎ የየዋህ ከበሮ ድለቃ ውስጥ እንደማያስገባ ማወቅ ከምንም በላይ አስፈላጊ ይመስላል፡፡ እስከ መጪው ሀገራዊ ምርጫ የሚያደርሱን ቀጣዮቹ ሶስት አመታት የድምፅ አልባው አብዮት ዘላቂነት አልያም አብዮቱ ድምፅ አውጥቶ የሚጮህበት ጊዜ መሆኑን መገመቱ አይከፈልም፡፡
የትግሬ አፓርታይድ አገዛዝን ሲዘውሩት የነበሩት ፅንፈኛ የህ.ው.ሃ.ት ሰዎች በትረ- ሙሴውን አምነውበት፣ አቅደውትና ፈቅደው አልያም ለዴሞክራሲ መርሆች ተገዢ ሆነው በህዝብ ሳይሆን በዛው በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ የም/ቤት አባላት ድምፅ ለተሰጣቸው ሰዎች ያስተላለፉት መሆኑን ብናምን ኖሮ እውነትም ድቅድቅ ጨለማ የዋጠው የሀገራችን የዴሞክራሲ ጎዳና ጫፍ ላይ ብርሃን እየታየ ነውና በተደሰትን ነበር፡፡ ዳሩ ግን እውነታው ከዚህ ፍፁም የራቀ ይመስላል፡፡ ይህ ድምዳምያችን የአቶ ኃይለማርያም አባት አቶ ደሳለኝ የትግሬ ዝርያ አለባቸው እየተባለ የሚናፈሰውን ወሬ ከቁብ ሳንቆጥር መሆኑ ነው፡፡ ነገሩ እንደ ‹‹ነጋሲ ግደይ›› አይነት ሸሙጥ ይሆናልና አቶ ኃይለማርያም የአያታቸውን ስም ነግረው ቢገላግሉን መልካም ነበር፡፡ ወደ ቁምነገሩ እንመለስና ከህልፈተ- ህይወቱ በኋላ ‹‹ድንቅ ስትራቴጂስት›› እየተባለ የሚቆለጳጰሰው መለስ ዜናዊ ላለፉት ሀያ አመታት የተጓዘበት መንገድ እራሱ በቀየሰው ‹‹የትግሬ የበላይነትን ማስጠበቂያ›› መሆኑ ቀርቶ የስትራቴጂው ውጤት በተቃራኒው ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ማድላቱ ታይቷል፡፡
የአፄ ዮሐንስን ‹‹ስህተት›› ላለመድገም ‹‹ስጋ ብፅዓት›› እያለ ይምልና ይገዘት የነበረው ሰው የህ.ው.ሃ.ትን የበላይነት ማስቀጠያ አማራጮችን ሁሉ ደምስሶ በብቸኝነት በራሱ ተክለ ሰውነት ልክ በዙሪያው እንዲጠመጠሙ የፈቀደላቸው ሰዎች በስተቀር ጎምቱ፣ ጎምቱ የህ.ው.ሃ.ት አመራሮች አልፎ ተርፎም ግልገል የብ.አ.ዴ.ን፣ የኦ.ሆ.ዴ.ድና የደ.ኢ.ህ.ዴ.ን ተከታዮችን ብቻ ከጎኑ በማሰለፍ በሙሉ አይን (የተፈጥሮ አይነ- ሸውራራነታቸውን ማለቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ) ቀና ብለው ሊያዩት የማይደፍሩትን ኃይለማርያም ደሳለኝን ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስተር በማድረግ፣ የመከላለያና የደህንነት ተዋረዶችን በመንደር ልጆች ጠርንፎ በመያዝ በዴሞክራሲ አቀንቃኞች ዘንድ በማያሰማ መልኩ ከመጋረጃው በስተጀርባ ሊተገብረው አቅዶ የነበረውን የስትራቴጂ ንድፍ ተግባራዊ ሳያደርግ በሜዳ ተበትኖ ቀረ፡፡ ለዚህም ይመስላል አንጋፋው የህ.ው.ሃ.ት ሰው ስብሀት ነጋ ‹‹መለስ እራሱን ብቻ ሳይሆን ህ.ው.ሃ.ትንም ጭምር ገድሎ ነው የሞተው›› ማለታቸው፡፡
በመሆኑም አክራሪ ብሔርተኛ የህ.ው.ሃ.ት ሰዎች በአንድ ሰው ትከሻ ላይ ተማምነው የጫኑት ጭነት በድንገትና ሳያስቡት መራገፎ አይቀሬ ሆነ፡፡ በነሱ አባባል የአፄ ዮሐንስ ‹‹ስህተት››ን ያለመድገም ፉከራ ፎረሸ ማለት ነው፡፡ ምናልባትም የኃያላኖቹ በተለይም የአሜሪካ ተፅዕኖ ይህንን መራራ ፍሬ ለጊዜውም ቢሆን ለመዋጥ ሳያስገድዳቸው የቀረ አይመስልም፡፡ ይህ ማለት ግን አሁንም ተመልሷል መሪውን የመጨበጥና ያንን እኩያ አላማ ለመተግበር የሚያስችላቸው አቅም አሟጠዋል ማለት እንዳልሆነ እሙን ነው፡፡
ፅንፈኛ የህ.ው.ሃ.ት ሰዎች በትረ- ሙሴውን ዳግም ለማስመለስ የማይፈነቅሉት ድንጋይና የማይምሱት ጉድጓድ እንደማይኖር ማመኑ ከወዲሁ ለሁሉም የሚበጅ ይመስላል፡፡ የም/ጠቅላይ ሚኒስትሩን የተተኪነት ስልጣን በፓርላማ የማፅደቅ ስነ ስርዓትን ማስተላለፍ፣በህ.ው.ሃ.ትና በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ዝግ ስብሰባዎች የነበሩትን የተካረሩ እሰጣ- ገባዎች እንዲሁም በቅርቡ በእሽቅድምድም የተከናወኑ የጄነራሎች ሹመት (ከሰላሳ ሰባቱ ሀያ ስድስቱ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ያጤኗል) ለታዘበ ህ.ው.ሃ.ቶች እስከ መጨረሻው ሰዓት መፍጨርጨራቸውን ያመለክታል፡፡ ይህንንም ሙከራ በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ ለመተግበር እንደሚሞክሩ መገመቱ ብልህነት ይሆናል፡፡ ድምፅ አልባውን አብዮት የማስቀልበስና በትረ- ስልጣኑን ደግሞ የመጨበጥ አልያም አብዮቱ ልጆቿን እየበላች እሪ ብላ የምትጮህበት ደማቅ ቀያይ መስመሮች ከወዲሁ ሊፈተሹና ግንዛቤ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡
የመጀመሪያው መንገድ ላለፉት ሀያ አንድ አመታት በመላ ሀገሪቷ በሚገኙ ተቋማት ውስጥ በተዘረጋው የህ.ው.ሃ.ት መረብ በመታገዝ በአዲሱ አመራር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደር ይሆናል፡፡ ከጦሩና ደህንነቱ ማዋቅሮች በተጨማሪ እስከ ወረዳ/ ቀበሌ በሚገኙት መንግስት ተቋማትና የግሉ ዘርፎች ተሰግስገውና ቁልፍ የአመራር ቦታዎችን ተቆናጠው የሚገኙ የህ.ው.ሃ.ት አባላትን በተደራጀ መልኩ ማንቀሳቀስ ከተቻለ የነኃይለማርያም ካቢኔ በርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ የማሽከርከሩ አቅም ብቻም ሳይሆን በቀጣዩ ጥቂት አመታት ውስጥ በድምፅ አልባው አብዮት በድንገቴ የተነጠቁት የፖለቲካ አመራር መዘውር መልሰው ሊጨብጡ አለመቻላቸውን በድፍረት መናገር ሊያዳግት ይችላል፡፡ እርግጥ ነው ይህ መስመር ‹‹ምጡቅ ስትራቴጂስቱ›› በህይወት ኖሮ ቢሆን ምነኛ በቀለላቸው ነበር፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ግን በተለያዩ ‹‹የባለስልጣን›› በሽታዎች ተደሽቀው የምናያቸው የትጥቅ ትግሉ አንጋፋ የህ.ው.ሃ.ት ሰዎችም ሆኑ በትግል ውስጥ እምብዛም ያልተሳተፉት ‹‹ወጣት ተተኪ ትውልዶች›› በረከት
ስምኦን የሚመራውን የብ.አ.ዴ.ን፣ የኦ.ህ.ዴ.ድ፣ የደ.ኢ.ህ.ዴ.ንና አፍቃሪ ኤርትራ የሆኑ የህ.ው.ሃ.ት አባላት ጥምረት በቀላሉ ሊያስገብሩት እንደማይችሉ ባያጠራጥርም ቅሉ ይህ
መስመር አይሞከሬ እንዳልሆነ መገመቱ አይከፋም፡፡ ሁለተኛው ቀይ መስመር ደግሞ ምናልባት የመጀመሪያው ሙከራ ካልተሳካ አልያም ከመጀመሪያው አካሄድ ጋር በማጣመር ህ.ው.ሃ.ቶች ሊያስኬዱት እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ይህም መንገድ አሁንም ላለፉት ሀያ አንድ አመታት የተሰራውን ሰራ መሰረት በማድረግ እንደ ወገብ ቅማል በሀገሪቷ ወሳኝ ተቋማቶች ውስጥ ተለጥፈው የሚገኙት የህ.ው.ሃ.ት አገልጋዮች ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን የማጓተት አካሄድ ጀምሮ ህዝቡን በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ብሎም በፀጥታ ጉዳዮች እንዲያማርርና ለዚህ ሁሉ ውድቀት
የፈረደበት የሀይለማርያምና ካቢኔው ‹‹የአቅም ማነስ›› ፕሮፖጋንዳ በማስጮህ ህዝቡን ‹‹መለስ ማረን›› እስከማሰኘት ሊያስኬዱ ይችሉ ይሆናል፡፡ ሌላው ቀርቶ አቶ መለስ የአረብ አብዮትን
መዛመት ማስቀየሻ የተጠቀሙበት የአባይ ግድብን ጨምሮ ለፖለቲካ ፍጆታነት ያልዘለሉትን ትላልቅ የባቡር መስመር ዝርጋታዎች፣ ራላቸው ለአቶ መለስ ዳገት የሆኑባቸውን የሱኳር
ፋብሪካዎችን ጨምሮ የተለያዪ ኢንዱስትሪዎች ግንባታ ‹‹አለማሳካት›› የአዲሱ አመራር ‹‹የአቅም እጦት›› ማመላከቻ አድርገው እንደሚጠቀሙባቸው አያጠራጥርም፡፡ ይህ አካሄድ የድምፅ አልባውን አብዮት ከመቀልበሱም በላይ ላለፉት ሀያ አንድ አመታት ፊታቸው የተለመዱ የህ.ው.ሃ.ት ሰዎችን ‹‹መተካካቱን›› ወደጎን ትቶ ወደ በትረ-ሹመቱ ሊመልሳቸው ያስችል ያሆናል፡፡ ጉዳዩ ሀገርንና ህዝብን የማዳን ነውና ልምድ ያላቸው ይመለሱ ይሆናል አካሄዱ፡፡ አልፎ ተርፎም የበረከት ሚዲያን በቀላሉ መቆጣጠር ቢያዳግታቸውም እንን በተገኘው አጋጣሚ ሰርስረው በመግባት አቶ ኃይለማርያምን ሀሌሉያ እያሉ ጌታን ሲያመሰግኑ፣ አቶ ደመቀም ቢሆኑ በወሎ ከራማ ለአላህ ዱአ ሲያደርጉ በቴሌቪዥን መስኰት አስጮልቀው ቢያሳዮን በህዝቡ መካከል መጠራጠርንና መከፋፈልን በመጫር አዲሱ አመራር በድንገቴ ያገኙትን የህዝብ ይሁንታ የመከፋፈልና የማቀጨጭ ሙከራ ከማድረግ እንደማይቆጠቡ መገመቱ አይከፋም፡፡
ህ.ው.ሃ.ቶች በርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያው የኃይለማሪያምን አመራር ሊሾፍሩት ካልቻሉ ወይም ህዝቡ በአዲሱ አመራር እንዲማረር፣ እንዲጠራጠርና አመኔታ እንዲነፍገው አልያም አሁን በጀመሩት ‹‹የብሔር ተዋፅኦን ያማከለ የመተካከት ሂደት›› ክርክር ገፍተው ለውጤት ካልደረሱ ሶስተኛውን አማራጭ መስመር ሊይዙ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህም መስመር መለስ ዜናዊ ብቻም ሳይሆን ትግል ጓዶቻቸው የነበሩት የሻዕቢያና የወያኔ ሰዎች እየተጠቀሙበት እዚህ ደረጃ ያደረሳቸው በቂ ተሞክሮና ልምድ ያካበቱበት የመጠፋፋት መስመር ነው፡፡ ከየትኛውም ተቋማት በበለጠ ትኩረት የተሰጠው ደህንነት መ/ቤትን በመጠቀም እምቢኝ አሻፈረኝ ብለው የትግሬ አፓርታይድ አገዛዝን ለማደናቀፍና ህ.ው.ሃ.ቶች የፖለቲካ መዘውሩን ዳግም ለመጨበጥ የሚያደርጉትን መፍጨርጨር ሊገታ ወይም ሊያሰናክል የሚሞክርን ግለሰብም ሆነ ቡድን በተለመዱት የሀገር ክህደት፣ ሙስናና በተለያዩ ክሶች በማዋከብ እንዲሁም ቀድሞ ደህንነቱ ለክፉ ቀን በሰበሰባቸው የባለስልጣናት የግልም ሆነ
የቤተሰብ ሚስጥሮች በማሸማቀቅና በማስበርገግ ከአመራር አስፈንጥረው የማስወጣ አካሄድ ሊጠቀሙ ይችሉ ይሆናል፡፡ ከስልጣ ግፍተራውና ከቃሊቲው ሽኝት በዘለለ መልኩም ቁንጮ በረከትን ጨምሮ የሃይለማርያን ስብስቦች በአደጋም ሆነ የመለስን ሞት ባፋጠነው ‹‹ኢንፌክሽን›› ተጣድፈው አለመሞታቸው አልያም እንደ አ.ህ.ዴ.ዱ አለማየሁ አቶምሳ ከአልጋ አለመቆራኘታቸው ማን ያውቃል፡፡ ይህ ሁሉ ቀያይ መሰመሮች ወደታሰበው መንገድ ካላደረሱ ጦሩ ሌላ ደርግ አቋቁሞ (አሜሪካ ዴሞክራሲሽን ይዘሽ በለማሊሞ አቋራጪ) አለማለታቸውስ ምን ዋስትና ይኖረናል፡፡ ይህንንስ የጨለማ ዘመን አታምጣው ብሎ መለመኑ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ወትሮስ ቢሆን ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር አይደል የምትዘረጋው፡፡
ተመስገን ነው ህ.ው.ሃ.ቶች አንገቷን እንጂ እጆቿን ገና አልቆረጡባትምና፡፡ የሆነው ሆኖ ቀጣዮቹን አመታት ለሀገሪቷና ለህዝቧ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ ጫና የሚፈጥርባቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ገምቶ መንቀሳቀሱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ድምፅ አልባው አብዮት ተጀመረ እንጂ አልተቋጨም የተባለውም ለዚሁ ነው፡፡ ምንም እንኳን የህዝቡ ተለዋዋጭ ባህሪ በፖለቲካና ማህበራዊ ጥናት አጥኚዎች ጥልቅ ሙሁራዊ ዳሰሳ ማካሄድ ማስፈለጉ የግድ እያለ መምጣቱ ባይካድም አሁን የተከሰተው አልታሰቤ ለውጥ በበጎ አጋጣሚነቱ ለመጠቀም ህዝቡ ቁርጠኝነት መላበስና አንዳንድ ጋሬጣዎች በቀላሉ ጠልፈው እንዳይጥሉት መጠንቀቁ አይከፋም፡፡
አዲሱ አመራርም ሳይፈራና ሳይርበተበት የጓዶቹን ምክርና እገዛ ከኋላው በማስተካከል (አቶ ኃይለማርያም ደንግጠው ከፊትም በመሆን ቢሉም ቅሉ) እንደ ቀድሞ መሪ ከህዝብ ተራርቀው ሳይሆን በመቀራረብ መስራቱ በማይጨበጠው ‹‹አባይን የደፈረ›› ጀግንነት ሳይሆን በሀገር ማዳንና ታሪክን በመቀየር ጀግንነቱን አስመዝግቦ ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ባልተቻኮለና ባልተጓተተ ውሳኔዎች የሀገሪቷን ወሳኝ ተቋማት ቅርፅና ይዘት መከለሱ ከምንም በላይ ግድ የሚል ቀዳሚ እርምጃ እንደሆነ መቼስ አቶ በረከት አያጡትምና አካሄዱን ለአቶ ኃይለማርያም ሹክ ማለታቸው እንደማይቀር እውን ነው፡፡
ከፊታችን ባሉት በጣም ጥቂት አመታት ውስጥ አዳዲሶቹ አመራሮች የራሳቸው አቅምና ድፍረት በማጎልበተ፣ የውጭ ግንኙነታቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ አቶ በረከት የተመኙላቸውን ከቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በኋላ የስልጣን ወንበሩን ይዞ የመቆየት እሳቤ ለማደናቀፍ የሚፍጨረጨረው ኃይል ሳይቀድማቸው ‹‹ለቁርስ ማድረሱ›› የግድ የሚል ይመስላል፡፡ አቶ ኃይለማርያም በአጋጣሚ ያገኙትን የህዝብ ይሁንታ ምክንያታዊና ዘላቂ ይሆን ዘንድ የማንም መሳሪያ ሳይሆኑ በቆራጥነት የተገኘውን እድል መጠቀም የሚችሉበት ወሳኝና ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ መሆናቸውን በአፅንኦት ሊገነዘቡት ይገባል፡፡
አቶ ኃይለማርያም የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት እቅድ ሊነድፉ እንደሚገባቸው ሁሉ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችም በተለይም በውጭ አለም የሚገኙት ለአዲሱ አመራር እድል እንዲሰጡ የግድ የሚል ሁኔታ ውስጥ ያለን ይመስላል፡፡ አዲሱ አመራር ትላልቅ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ አሁኑኑ ይደራደር ብሎ ጠርዝ ላይ ቆሞ መገፋፋቱ ብልህነት እንዳልሆነ ሁሉ ለወደፊቱ በአንኳር ሀገራዊ ጉዳዪች ላይ ለመነጋገር መስማማቱና በየማጎሪያው ተወርውረው የሚገኙ የህሊና እስረኞችን የመፍታት ጅማሮ ለነገ የማይባል የህዝብ ወገንተኝነትን አመላካች ነው፡፡ ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት ከመሬት ላይ ተፈጥፍጠው የነበሩትን ሀገራዊ እሴቶቻችንን ዳግም የማነሳሳት ታሪካዊ ሀላፊነትን በቁርጠኝነት መወጣትን አሁንም ህዝቡ ከአዲሱ አመራር የሚጠብቀው እርምጃ መሆኑን ተገንዝቦ መንቀሳቀስ ግድ ይላል፡፡
በተዛማጅ ህ.ው.ሃ.ቶችም ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ሀገር እንደሌላቸው አስረግጠው አምነው፣ የፖለቲካ ቁማራቸውን አቁመው፣ የእስከዛሬውን ይባርክ ብለው ከእንግዲህ በፍትሃዊ መንገድ ከሌላው ወገናቸው ጋር በእኩልነት ለመኖር ይወስኑ ዘንድ ተስፋዬ ገ/አብ እንዳለው ሁሌ ‹‹ያለፍላጎቱና ያለግብሩ ፖለቲካ ውስጥ እየነከርን መከራውን የምናሳየው›› እግዚአብሔር ልቦና ይሰጥልን ዘንድ እንፀልይ ይሆን? ምን ይደረግ ‹‹የቸገረው ….. ›› አይደል ተረቱ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 20, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 21, 2012 @ 7:52 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar