(Sebhat Amare- Norway)
የሂዩማን ራይትስ ዎች የዓለም አቀፍ ዘገባ ስለ ኢትዮጵያ፤ በኢትዮጵያ የፖሊስ ሃይል፤ በጦር አባላትና በሌሎችም ተመሳሳይ አባላት፤ በደህንነት አባላት በቅጣት መልክ በተቃዋሚ ደጋፊዎችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ላይ የሚፈጸመው ስቃይና የእስረኞች የአያያዝ ሁኔታ አሳሳቢነትና መከራ የከፋ ከመሆኑም ባሻገር በሚስጣራዊ ማጎሪያዎች፤ በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ በእስር የሚገኙት ንጹሃን ዜጎች ሁኔታ አሳሳቢነቱ በየጊዜው እየከፋ የሚሄድ መሆኑን በተደጋጋሚ በግልጽ አስቀምጧል፡፡በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች መለቀቅ አለባቸው፡፡ ሁኔታቸው በአሜሪካን መንግሥት ሰበአዊ መብት ሪፖርት፤ በተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዘገባ ውስጥ በገሃድ ተቀምጠው በተደጋጋሚ ታይተዋል፡፡ የአሜሪካን ስቴት ዲፓርትመነት የሰብአዊ መብት ሪፖርት ባሰፈረው እውነታ መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት ወህኒ ቤቶች ያለውን ሕገ ወጥ ግድያ፤ ስቃይ፤ ድብደባ፤ የታሳሪዎችን አለአግባብ መሰቃየት፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በፖሊስ የሚደርስባቸውን ወከባና ግፍ የተሞላው አበሳ፤ በልዩ የፖሊስ ሃይልና ሚሊሺያዎች የሚሰነዘረውን ሕገ ወጥ ድርጊት፤ በወህኒ ቤቶቹ ያለውን ዝቅተኛና መኖር የማያስችል ሁኔታ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎችና መልካም አሳቢዎች አለአግባብ በዘፈቀደ መያዝ፤ ያለፍርድ ለረጂም ጊዜ በወህኒ ቤት መሰቃየት እና ሌሎችም በዝርዝር ተዘግቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የጸረ ቶርቸር(የስቃይ አያያዝ) ኮሚቴ (ኖቬምበር 2010) ዘገባው በፖሊስ አባላት በወህኒ ቤት ሃላፊዎች፤ በደህንነት አባላት፤ እንዲሁም በወታደራዊው ክፍል አባላት የሚደርሰውን ግፍና መከራ፤ በፖለቲካ ተቃዋሚ አባላትና ደጋፊዎች፤ በተማሪዎች ላይ፤ ሽብርተኞች ተብለው በሚፈረጁ ላይ፤ የተቃዋሚ ሃይላት ደጋፊዎች ወይንም ተጠርጣሪ ደጋፊዎች የተባሉትን ሁሉ በተለያዩ ቦታ በማጎር የሚደርስባቸውን ስቃይ በአግባቡ በመዘገብ ይፋ አድርጓል፡፡ ማጎሪያዎቹ ከታወቁት ማጎሪያዎች በተጨማሪ፤ ፖሊስ ጣቢያዎች፤ ወታደራዊ ካምፖችና ይፋ ያለሆኑ ቦታዎች ጭምር ዜጎች በግፍ እየታፈኑ እንደሚሰቃዩ ሪፖርቱ ጨምሮ ይፋ አውጥቷል፡፡በኢትዮጵያ ምን ያህል እስረኞች እንዳሉ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሁኔታውን እንዲያዩም ሆነ ታሳሪዎችን እንዲያነጋግሩ አይፈቀድላቸውም፡፡ የተለያዩ አካላት ግምታዊ ቁጥር ሲያስቀምጡ፤ ከብዙ መቶዎች እስከ አሰርት ሺዎች እንደሚደርሱ ይገምታሉ፡፡ በቅርቡ የወጣው የጄኖሳይድ ዎች ሪፖርት የፖለቲካ እስረኞችን ብዛት በመቶ ሺህ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ በየቀኑ የፖለቲካ ሰዎች፤ ያለውን መንግስት የሚተቹ፤ ተቃዋሚ ሃይላት፤ ለእስር በመዳረግ ላይ ናቸው፡፡ ባለፉት ዓመታት በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ የተነሳ ቁጥራቸው የበዛ አባላት ለእስር ተዳርገዋል፡፡ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲ ተቃዋሚ አባላት አባሎቻቸው ለእስር እንደተዳረጉ አስታውቀዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ጦማሪዎች፤ ጋዜጠኞች፤ የተቃዋሚ ፓርቲ ደሃፊዎችና አመራሮች፤ ቆራጥና አልበገር ባዩን የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሩን አንዱ ዓለም አራጌን፤ ዓለም አቀፋዊ ክብርና ሞገስ የተሰጣቸውን እስክንድር ነጋንና ርዕዮት ዓለሙን፤ ኤዲትር ውብሸት ታየን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች የረጅም ዓመታት እስር አለአግባብ ተፈርዶባቸዋል፡፡
የመልካም አስተዳርና የዴሞክራሲ ግንባታን ቀፍድዶ የያዘው ጸረ ሽብርተኝነት ተብሎ የተቀመጠውንም አዋጅ ቁ›. 652/2009 በሚገባ መስተካከል ይገባዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይሄ ሕግ የፖለቲካ ተቃዋሚ አባላትንና ደጋፊዎችን፤ አመራሮችን፤ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ለማገትና ወደ ወህኒ ለመጣል በመሳርያነት ያገለገለ ነው፡፡ ሕጉ በሁሉም ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ተወግዟል፡፡የሁማን ራትስ ዎች ሕጉን ”ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማፈን፤ በነጻ የመንግስትን ፖሊሲ የሚተቹትን የሰብአዊ መበት ተሟጋቾችን ለማስደንገጫና ለማሰርያ መጠቀሚያ ነው” በማለት አጣጥሎታል፡፡ ”የጸረሽብርተኛነት ሕግ የተባለው ሕግ ሳይሆን መንግስት የሚፈራቸውንና ለስልጣኔ አደገኞች ናቸው፤ ይቀናቀኑኛል ብሎ የሚያስባቸውን ንጹሃን ዜጎች ዝም ለማሰኛ የተቀረጸ የገዢው መንግስት የብረት መሳርያ ነው” ይለዋል፡፡ ”ማንኛውንም ያለውን መንግስት ሂደትና ተግባር በገንቢ ጎኑም ሆነ መታረም በሚገባው አለያም ስህተቱን በማንሳት የሚተቸውን በሙሉ ሽብርተኛ በማለት እየኮነነ ለእስር የሚያበቃ ነው” ይለዋል፡፡
ይህ ‘ህግ’ እንደሚለው:-
.-ማንኛውንም አይነት ጽሁፍ መንግስትን የሚቃወም ከሆነና ተቃዋሚን የሚያበረታታ ከሆነ ለእስር ያስዳርጋል ፡፡
.-ማንኛውም ግለሰብ በሽብርተኝነት ከተጠረጠረ ሰው ጋር የዋለ ወይም ያነጋገረ አለያም የሱን ሃሳብ የደገፈ እራሱም እንደሽብርተኛ ይፈረጃል ፡፡
.-ማንኛውም ሰው በተጠረጠረ ሰው ላይ አዎንታዊ አስተያየቱን ቢያሰፍር አለያም ሕጉ አላግባብ ነው የተተረጎመው በሚል አስተያየቱን ቢሰጥ እሱም ሽብርተኛ ነው ፡፡
.-ማንኛውም ቤተሰብ ጎረቤት ሽብርተኛ ብሎ የጠረጠረውን ወዲያውኑ ለፖሊስ ሳያሳውቅ ቢቀር በ10 ዓመታት እስር ይቀጣል ፡፡
.-ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ከሽብርተኛነት ተጠርጣሪ ጋር ሆነው ከተገኙ ለሽብርተኝነት እንዳሴሩ ተቆጥረው በሽብርተኝነት ይፈረጃሉ ይላል ሕጉ፡፡
በዚህ ጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ መሰረት አንድ ፖሊስ ማንንም የጠረጠረውን ዜጋ ያላንዳች ማስረጃና ያላንዳች የፍርድ ቤትም የመያዣ ትዕዛዝ በዘፈቀደ ጠርጥሬዋለሁ፤ መስሎኛል፤ አይነ ውሃው አላማረኝም በሚሉ ነጥቦች ሳቢያ በቁጥጥር ስር ሊያውለውና ለበርካታ ቀናት፤ ሳምንታት ወይንም ወራት በእስር ሊያቆየው ሕጉ ይደነግግለታል፡፡ በዚህም መሰረት አንድ ፖሊስ የጠረጠረውን ሰው ንብረት፤ ቤቱን፤ የስልክ ጥሪዎቹን፤ የሞባይል ግንኙነቶቹን፤ ሬዲዮ፤ ፖስታ፤ እና መሳይ ግንኙነቶችን የመጥለፍና የመቅዳት እንዲሁም ቤቱንም በድብቅ የመበርበር መብት በሕጉ ተደንገጎለታል፡፡ ፖሊስ ማንኛቸውንም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ባለስልጣን፤ ባንክን እና የግል ድርጅቶችን፤ ወይም ግለሰብን፤ ዶኩሜንቶችን እንዲያስረክብ፤ ምስክርነት እንዲሰጥ ያስገድደዋል፡፡ አንድ የሽብር ተጠርጣሪ ያለፍርድ በወህኒ ቤት ለአራት ወራት ሊማቅቅ ደንቡ ያዛል፡፡ ማንኛቸውም በመንግስት አቃቤ ሕግ የቀረበ ማስረጃ ሁሉ፤ ‘የማይታበል ሃቅ’ ተብሎ ተቀባይነት ያገኛል፡፡ እንዲሁም ከተጠርጣሪው ላይ በማሰቃየትና በግርፊያ በድበደባ የተገኘ የ’እምነት’ ቃል ተጠርጣሪውን በማሰቃየት የተገኘም የግፍ ወለድ ማስረጃም ቢሆን ተቀባይነት ያገኛል ይላል ሕጉ፡፡
ይህ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ በግል አመለካከቴ ዴሞክራሲያዊ የሲቪል ማሕበረሰብን መኖርም ጭምር የሚጻረር መሆኑን ነው፡፡
.-አለመስማማትም ሽብርተኝነት ነው፡፡
.-ማሰብም ሽብርተኝነት ነው፡፡
.-ባለው አገዛዝ ላይ ስህተቱን መናገርም ሽብርተኝነት ነው፡፡
.-የራስ ሕሊና ባለቤት መሆንም ሽብርተኝነት ነው፡፡
.-ሰላማዊ ተቃውሞም ሽብርተኝነት ነው፡፡
.-እራስን አለመሸጥና በአቋም መጽናትም ሽብርተኝነት ነው፡፡
.-ለሰብአዊ መብትና ለዴሞክራሲ ጥብቅና መቆምም ሽብርተኝነት ነው፡፡
.-ለሕግ የበላይነት መቆምም ሽብርተኝነት ነው፡፡
.-በሃገር ላይ ለሚሰነዘር ሽብርተኝነትም በሰላማዊ መንገድ መቃወምም ሽብርተኝነት ነው፡፡
.-ማንም ቢሆን ስለሽብርተኝነት በቂ ግንዛቤ ሊኖረው ተገቢ ነው፡፡
ኔልሰን ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ በነበረው አፓርታይድ አገዛዝ ለ27 ዓመታት ሽብርተኛ ተብለው ነው ወደ ወህኒ የተጣሉት፡፡ ከእስር ሲለቁቅም ”ትላንት ሽብርተኛ ተብዬ ነበር፤ ከእስር ስለቀቅ ግን ሁሉም ወገኖቼ አሳሪዎቼም ጭምር አቅፈውኝ ነበር፡፡ ደጋግሜ እናገር እንደነበረው ለነጻነታቸው የሚታገሉ ሁሉ በሃገራቸው መሪዎች ሽብርተኞች ይባላሉ፡፡”
ስለሆነም ይህ የ’ጸረሽብርተኛ ሕግ’ የሚባለው ‘ሕግ’ ለወገን፤ ለአገር እንዲሁም ለእኩልነትና ለሰብዓዊ መብት ታጋዮች ማሰናከያ ሰይጣናዊ ሰነድ ነውና መወገድ አለበት፡፡
አሁን እጅ ለእጅ ተጨባብጠን፤እርስ በርሳችን ተቃቅፈን፤ሁለንተናችንን ለአዲሲቱ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ፤ የሕግ የበላይነት የተከበረባት ኢትዮጵያ፤ሰብአዊ መብት የተጠበቀባትና ዴሞክራቲክ ስነስራት የተከበሩባት ኢትዮጵያን ለመገንባት መዋል ይገባናል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ በመክፈት ጥላቻንና ቂም በቀልን ወደ ኋላ በመተው የምንቀጥልበት ወቅት ነገ ሳይሆን ዛሬ መሆን ያለበት፡፡ እራሳችንን ካለፈው የመከራ ሸክምና ካሰረን የሰንሰለት ቋጠሮ አላቀን ለዘመናት ሲያመን የነበረውን ቁስል በማከምና በማዳን ከእንግዲህ ፈጽሞ ያለፈውን በማመንዠክ የምንም ሁኔታ እስረኞች ላለመሆን ለመጪው ንጹህ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ልናረጋግጥለት የሚገባን ዛሬ ነው፡፡
Average Rating