www.maledatimes.com በአሉ ግርማና አስፋው ዳምጤ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በአሉ ግርማና አስፋው ዳምጤ

By   /   September 8, 2014  /   Comments Off on በአሉ ግርማና አስፋው ዳምጤ

    Print       Email
0 0
Read Time:9 Minute, 12 Second

anbesawyibra@gmail.com ባለፉት ወራት የአገር ቤቶቹንም ሆነ ውጪ ያሉትን የሚዲያ አውታሮች በተለያየ መልክ ያነጋገረው የበአሉ ግርማ አሟሟት ላለፉት 30 አመታት ሲያነታርክ ቆይቶአል ። እስከደርግ መጨረሻ ድረስ በድብቅ ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ በግልፅ አነታርኳል ። ይህም የሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው ። አንደኛው ምክንያት በአሉ ግርማ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ስነ-ፅሁፍ አቻ የማይገኝለት ደራሲ በመሆኑና በብዙ አንባቢዎቹ ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው መሆኑ ሲሆን ፣ ሁለተኛው ደግሞ ፍትህንና እውነትን ፈላጊ ተስፋ የማይቆርጥ ቤተሰብ ስላለው ነው ። በተለይ ደግሞ ባለቤቱ ወ/ሮ አልማዝ አበራ ። ለፍትህ እታገላለሁ የሚል ወገን ሁሉ ለበአሉ ግርማ ቤተሰብ ፍትህ ማግኘት የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ ። ይህን ያልኩበት ምክንያት በውጪም ሆነ በአገርቤት “በቃ በአሉ ግርማን ደርግ ገድሎታል ሁላችንም የምናውቀው ነውና እንተወው ፦ የሚሉ ወገኖች ስላሉ ፤ በተለይ የእያንዳንዱ ግለሰብ የግል ነጻነት ተከብሮ በሚኖርበት አውሮጳና አሜሪካ እየተኖረ ይህን የመሰለ ድፍን ያለ ድምዳሜ ላይ መድረስ በስደት ከየምንኖርበት አገር የፍትህ ስርአት የተማርነው እንደሌለና ሆዳችንን ከመሙላት በቀር ምንም ትርፍ እንዳላመጣን ማሳያ ይሆናልና ነው ። ይህን ካልኩ በኋላ ለዛሬ አብይ ነው ብዬ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልምጣ ። አቶ አስፋው ዳምጤ “በበአሉ ግርማ ጉዳይ ላይ ከህሊና እዳ ነፃ ነኝ” በሚል ርዕስ ስለ በአሉ ግርማ መሰወር ጉዳይ የሰጡትን ቃለ- መጠይቅ ፍቱን ከምትባል መፅሄት ላይ ተወስዶ በአንድ ዌብ ሳይት ላይ ተለጥፎ አግኝቼ አነበብኩትና ከቃለ መጠይቁ የተረዳሁትን ለአንባቢ ለማሳወቅ ፈልጌ ነው ። አቶ አስፋው ፤ በመጀመሪያ በራስዎ ስም መልስ ለመስጠት በመሞከርዎ ላድንቅዎ እፈልጋለሁ ።የሰጡት መልስ አሳማኝም ይሁን አይሁን ዋናው ለቀረበብዎት ጥያቄ በቃለ-መጠይቅ መልክ መልስ ለመስጠት ሞክረዋል ። ያስመሰግንዎታል ።

ከቃለ መጠይቅ ይልቅ በራስዎ ፅሁፍ የነበረውን ሁኔታ ቢገልፁልን ኖሮ ደግሞ ተመራጭ ይሆን ነበር ። አዲስ አበባ ተወልደው ስላደጉም ይሆናል በወዳጅ በዘመድ አፅፈው በጎን ለማለፍ አለመፈለግዎ ፤ ትልቅ ነገር ነው ።(በጋዜጠኛው አቀራረብ ላይ ጥያቄ ቢኖረኝም)። ያነጋገርዎ ጋዜጠኛ እንደነገረን የመጀመሪያ ዲግሪዎን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛውን ደግሞ ከካምብሪጅ አግኝተዋል ። ከዚያም ለረጂም ዘመናት በገንዘብ ሚኒስቴር ሰርተዋል ። ከዚህ በመነሳት ትምህርትዎ የጋዜጠኝነት ወይም የስነ-ፅሁፍ እንዳልሆነና economics ሊሆን እንደሚችል ጠርጥሬአለሁ ። ተሳስቼ እንደሆን ለመታረም ዝግጁ ነኝ ። ከዚያም በመፅሃፍ ድርጅትና በኩራዝ አሳታሚ ሰርተዋል ። ይህን ካልኩ በኋላ በቀጥታ ወደርስዎ ቃለ-ምልልስ ልምጣ ። የደራሲ በዓሉ ግርማ ባለቤት፣ ወ/ሮ አልማዝ አበራ፣ ‹‹…የካቲት 24 ቀን 1976 ዓ.ም. ቀን ላይ አስፋው ዳምጤ እቤት ስልክ ደወለ :: በዓሉ ቤት አልነበረምና፣ ስልኩን አንሥቼ ያነጋገርኩት እኔ ነበርኩ :: የእግዜር ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ፣ ‹… በዓሉ እንደመጣ እዚያ እቀጠሯችን ቦታ ባስቸኳይ እንድትመጣ ብሎሃል በዪልኝ …› ብሎ ስልኩን ዘጋ ::›› አቶ አስፋው ፡ የዚህ አጭር መልሱ “ሃሰት” ነው ። ብለዋል ። አበራ ለማ ከበአሉ ባለቤት ከወይዘሮ አልማዝ አገኘሁት ብሎ ካቀረበው ፅሁፍ ላይ ለእርስዎ ቃለ መጠይቅ መንደርደሪያ ሃሳብ ሆኖ የቀረበው ከፊሉ ብቻ ነው ። የአበራ ለማ ሙሉውን ምእራፍ ስናነብ ነው ፈታ ያለ ግንዛቤ የሚኖረን ። እንዲህ ይነበባል ፤ እጠቅሳለሁ፦ “….የካቲት 24 ቀን 1976 ዓ.ም. ቀን ላይ አስፋው ዳምጤ እቤት ስልክ ደወለ፡፡ በዓሉ ቤት አልነበረምና ስልኩን አነስቼ ያነጋገርኩት እኔ ነበርኩ፡፡ የእግዜር ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ’… በዓሉ እንደመጣ እዚያ እቀጠሯችን ቦታ ባስቸኳይ እንድትመጣ ብሎሃል በዪልኝ…’ ብሎ ስልኩን ዘጋ፡፡ በዓሉ ወደ አሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ወደ ቤት ሲመጣ መልእክቱን ነገርኩት፡፡ ወዲያው ሻወር ወስዶ ወጣና ለመሄድ ሲጣደፍ፣ ’እደጅ ውለህ መምጣትህ ነውና እባክህ ትንሽ እህል ብጤ ቀምሰህ ውጣ’ ብለው፤ ’አልችልም… ብርቱ ቀጠሮ አለንና ወደዚያው መፍጥን አለብኝ’ ብሎኝ ፈጥኖ ከቤት ወጣ::

” የጥቅሱ መጨረሻ ። መርምሮ ለሚያነብ ሰው የነገሩ ጭብጥ ያለው ወ/ሮ አልማዝ ከጠየቁትና አበራ ለማ ካቀረበው ከላይኛው ጥቅስ ጋር የተያያዘ ነው ። ወ/ሮ አልማዝ በስልክ መልእክት ከአቶ አስፋው ተቀብዬ ለባለቤቴ ነገርኩትና በመልእክቱ መሰረት ወደ ጓደኛው ወደ አቶ አስፋው ሄደ ነው የሚሉት ። አቶ አስፋው የሚሉት ደግሞ የለም ስልክ አልደወልኩም ፤ ቀጠሮም አላደረኩም ፤ ሆኖም ግን ያለቀጠሮ በዚያች የመጨረሻዋ ምሽት በአሉን አግኝቼዋለሁ ነው ። እዚህ ላይ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ይነሳል ። ይኸውም ወይዘሮ አልማዝ ከአቶ አስፋው ጋር ጠብም ወዳጅነትም ቅርርብም የላቸውም አቶ አስፋው ዳምጤ እንደነገሩን ።

ይህ ከሆነ ደግሞ ለምን ወይዘሮ አልማዝ እስካሁን ድረስ የምታውቀው ነገር አለና ንገረኝ ብለው አቶ አስፋውን ያስጨንቃሉ ፤ ለምን ሌሎቹን የበአሉ ጓደኞች አንደ አቶ አስፋው ሁሉ ጠይቀው አያውቁም ? ሌላው ደግሞ በመጨረሻዋ በአሉ በተሰወረባት ምሽት ፤ በአሉ ወደቤቱ ስላልተመለሰ ለወይዘሮ አልማዝ ከአስፋው ጋር አመሸሁ ብሎ አልነገራቸው ፤ ከእርስዎ ጋር ማምሸቱንስ ወ/ሮ አልማዝ እንዴት አወቁና ነው ወደቤትዎ የደወሉት ፤ ቀድመው ወደቤት ደውለው በወይዘሮ አልማዝ በኩል ለበአሉ ቀጠሮ ካልሰጡ ? አቶ አስፋው ወ/ሮ አልማዝ ወደቤቴ አልደወለችም ብለው ቢያስተባብሉም ጠዋት ላይ ወደስራዎ ደውለው እንደተነጋገሩ ደግሞ አልካዱም ። ወይዘሮ አልማዝ ባለቤቴ በአሉ ግርማ ማታ አልገባምና የምታውቀውን ንገረኝ ብለው ሲጠዩቅዎ “ አይቼዋለሁ ግን” ብየ የምለው ጠፋኝና ፤ የምለው ጠፋኝና ነው ያሉት ! ለምን የሚሉት ጠፋዎት ? አሁን የሚነግሩንን መገናኛችሁ አጠገብ ቆመን አንድ አንድ ብለን ተለያየን ብለው ለምን አልነገሯቸውም ለወ/ሮ አልማዝ ።

ይህን ብለዋቸው እስቲ ደግሞ ከሌሎች ሰዎች ላጣራ ብለው ቢሆን ኖሮ የተናገሩት እውነት ይመስል ነበር ። አንድ ሰው የሚለው የሚጠፋው አንድ የሚያውቀው ነገር ሲኖርና ለዚያ መልስ ሳይዘጋጅ ድንገት ጥያቄ ሲቀርብበት ነው ። ወዲያው የሚያስገድደው ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ የመዘጋጃ ጊዜ ለመግዛት ዘዴ ይቀይሳል ። አቶ አስፋው ለርስዎ ጊዜ መግዣ አድርገው የተጠቀሙበት “ አሁን አንድ ትልቅ ባለስልጣን ዘንድ ስለምሄድ እሱን ጠይቄ እነግርሻለሁ ብለው ዛሬ በህይወት የሌሉትን ሰው ለማ ጉተማን ምስክርነት መጥራት ነው ።

እስቲ ቆም ብለው ያስቡት ለራስዎም አልገረመዎትም ? ሌላው ወ/ አልማዝ የተናገሩትን ለማስተባበል ማስረጃ አድርገው የተጠቀሙበት የሬይደልፍ ኬ ሞልቬርን Reidulf K. Molvaerን ብላክ ላዮንስ Black Lions የተባለው መፅሃፍ ላይ ደራሲው በአሉ ግርማ በጠፋባት በዚያች ምሽት ያቀረበውን ትንተና ነው ። በአጭሩ መፅሃፉ ላይ እርስዎ በአሉን መጥተው ከቤቱ ወሰዱት አይነት አቀራረብ ስለሆነ አንዴ ስልክ ደውሎ ቀጠሮ ሰጠው ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቤቱ መጥቶ ወሰደው ተብሏልና አንዱን ይምረጡ ነው አባባልዎ ። መፅሃፉ ላይ እኮ ወ/ሮ አልማዝ እንደነገሩኝ ብሎ አልፃፈም ሞልቬር ፤ ስለዚህ ሞልቬር ይህን ነጥብ ከየትም ሊያገኘው ይችላል ። ሞልቤር ስህተት ፈፅሞ ከሆነ እንኳን ወ/ሮ አልማዝን ምርጪ አትምረጪ ሊያሰኛቸው አይችልም ።

መፅሃፉ ላይ ለወጣው ፅሁፍ ተጠያቂ መሆን ያለበት ሞልቬር ብቻ ነው ። ታዲያ እኮ ሞልቬር እዚያው ገፅ ላይና እዛው ፓራግራፍ ላይ የጠቀሳቸው ነጥቦች ነበሩ ፤ እርስዎ ሳያዩአቸው አልፈዋል ወይም ሆን ብለው ዘለዋቸዋል ። ሞልቬር እንዲህ ይላል እዚያ ላይ ፤ እርስዎ አቶ አስፋው በአሉ ከተሰወረባት ከመጨረሻዋ ቀን አስራ አምስት ቀን በፊት ነው በአሉን ያየሁት ብለው ለሌሎች ሰዎች ተናግረዋል ብሏል ። ይህም ወ/ሮ አልማዝ ከተናገሩትና ከሚሉት ጋር ባለመግጠሙ ሰዎች ደንቆቸዋል ሲል ፅፏል ፤ ይህን ነጥብ ይያዙ ። ቀጥሎም እንዲህ ይላል ሞልቬር (ስም ባይጠቅስም) ምንልባትም ይህ ጓደኛው ፤ ላደረገው አብዮታዊ አስተዋፅኦ መንግስታዊ ለሆነው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በዚያኑ ሰሞን ስልጣን ተሰጠው ፤ ብሏል ። ሞልቬር ብላክ ላዮንስ በሚለው መጽሃፉ ላይ ያስቀመጠው እንዲህ ይነበባል ገፅ 348 ፦ To other people he ( the friend ) said that he had not seen Be’alu for two weeks before he disappeared, and they were surprised to hear another story from Be’alu’s wife . Soon after the friend got ( perhaps as areward for his contribution to the revolutinary cause ) a high position with Kurraz , the government publishers. እዚህ ላይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ ። አበራ ለማ የሰዎች ስም አጠፋ የርስዎን የአቶ አስፋው ዳምጤን ጨምሮ እየተባለ ሲጠቀስ በየመጣጥፉ ላይ አንብቤ ነበር ።

የእርስዎም ብሶት አበራ ለማ ስሜን አጥፍቷል ነው ። ከዛሬ 17 አመታት በፊት በ1997 እ.አ.ኤ ሞልቬር ይህንኑ ፅፎት የለም እንዴ ያውም ዘላለማዊ ሆኖ በሚቀር መፅሃፍ ላይ ! ምነው አበራ ለማ እንዚህን መረጃዎች ሰብስቦ ሲፅፍ ድንቅ ሆነ ? አቶ አስፋው ሌላው ያሳዘነኝን ሳልገልፅልዎ ማለፍ አልፈልግም ።

ጋዜጠኛው ከአበራ ለማ ጋር ቅራኔ ነበራችሁ ? ብሎ ይጠይቅዎታል ። መሆን የነበረበት ከቮልቴር ጋር ቅራኔ ነበራችሁ ? ነው ። እርስዎም ሲመልሱ “ እኔ ከእርሱ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቻለሁ ብየ አስቤ አላውቅም ብለው ነበር ። ይህ የጨዋ መልስ በቂ ነበር ። በተረፈ ከዚያ አልፎ ከዛሬ 37 አመታት በፊት የተደረገን ስነፅሁፋዊ ክርክር ቂም በቀል አድርጎ ለማቅረብ መሞከርና በዚያ አስታኮ ስሙ ያልተጠቀሰ አስተማሪው እንዲህ ብሎ አለው ብሎ በማለት ሰውን በሾርኒ ለመስደብ መሞከር ትንሽነትን የሚያስይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ። በስነፅሁፍ ቅስሙ ቢሰበር ኖሮማ አበራ ለማ አሁን ይህን የመሰለ ኢንቬስቲጌቲቭ ስራ ባላቀረበልን ነበር ። በነገራችን ላይ አበራ ለማን ከፅሁፉ በስተቀር ጥቁር ይሁን ቀይ ሰልካካ ይሁን ኩርፋድ አላቀውም ። አስተያየቴ በሙሉ በአሉ ግርማን አስመልክቶ ከፃፈው ጋር የየያያዘ ነው ።

በርግጥ ሌሎች የግጥም ስራዎቹንም አውቃለሁ ቅስሙ አልተሰበረም ህያው ነው ለማለት ነው ። እውነቱን ለመናገር እርስዎን ቃለ-መጠይቅ ካደረገልዎ ጋዜጠኛ ነው የድርሰት ስራዎች እንዳሉዎትም የሰማሁት ። ልጅ ሆኜ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ነው መፅሕፍትን የማንበብ ልምድ የተጥናወተኝ ። ካነበብኳቸው ውስጥ አንዱ ርዕሱ “ከልታማዋ እህቴ” ይላል አሁን የዚህን መፅሃፍ ደራሲ ማን እንደ ደራሲ ቆጥሮ ያስታውሰዋል ! ወደ ወ/ሮ አልማዝ አበራ ልመለስ ። እኔ እንደገባኝ ከሆነ የወ/ሮ አልማዝ ጥያቄ አቶ አስፋው ባለቤቴን በአሉን ገድለዋል ፤ ወይም በግድያው ላይ እጃቸው አለበት አይደለም ። በኦሮማይ ምክንያት ህይወቱ እንዳለፈም ያውቃሉ ። የሳቸው ጥያቄ ግን አንድና አንድ ብቻ ነው ። የሟች ባለቤቴን የሞት መንገድ ፍለጋ ላይ ነኝ መዳረሻውን ላለፉት 30 አመታት እየፈለኩ ነው ። የዚያች መንገድ መግቢያ ቁልፍ አቶ አስፋው እርስዎ እጅ ላይ ይገኛልና ለፍትህ ብሎም ለህሊናዎ ሲሉ ይጠቁሙኝ ነው ። አቶ አስፋው ወ/ ሮ አልማዝ ልብ ውስጥ እንደማንኛውም ሰው ሊመላለስ የሚችለውን ስሜት ሊረዱት ይገባል ። የውድ ባለቤታቸውን ደብዛ እየፈለጉ ያሉ ናቸውና ። ቀያፋ ላዘዛቸው ሮማውያን ወታደሮች ጲላጦስ እየሱስን በግላጭ ጉንጩን ስሞ አሳልፎ ሰጥቶታል ብለው ቢያስቡስ ወ/ሮ አልማዝ ላይ ይፈረዳል ? አቶ አስፋው ሌላው ያሳዘነኝን ሳልገልፅልዎ ማለፍ አልፈልግም ። ወ/ሮ አልማዝ ላይ ለምን ጠየቀችኝ ከሚል ቅሬታ ተሰምቶዎታል ስለዚህም አቂመውባቸዋል ።

ወ/ሮ አልማዝ ጋር በስራ ምክንያት የሚያገናኛችሁና በዚህ ተቀይማኛለች በማለት ሊያቀርቡት የሚችሉት ምክንያት ሊኖር አልቻለም ። እና የሞተውን ባላቸውን በአሉን ሌላ ውሽማ ነበረችው በማለት የሴትነት ብቃታቸውን ለማዋርድ ሞከሩ ። ባልሻረ ቁስላቸው ላይ ጨው ነሰነሱበት ። ምን አይነት ጭካኔ ነው ! አዝናለሁ እንዲህ በማለቴ ፤ እንዲያውም ወራዳነት ነው ። የገባበትና አፅሙ እንኳ የት እንደወደቀ ያልታወቀ ሙት ወዳጁን አጽም ፤ ሰው እንዴት ይግጣል ። ቤተሰቡን ለማስቀየምስ ለምን ይቸኩላል ። ከራስዎ ጥያቄና መልስ ልነሳና ይህን ራስዎ የፈጠሩት መሆኑን ደግሞ ላስረዳዎ አቶ አስፋው ። ጠያቂው ጋዜጠኛ ቀድሞ የተዘጋጀበት በሚመስል መልኩ ከመሬት ተነስቶ አንድ ጥያቄ ያቀርብልዎታል ። በአሉ እርስዎጋ ከመድረሱ በፊት ይት ቆየ ብለው ነው የገመቱት ? ይልዎታል ። ከዚያ አስቀድመው እርስዎ ካላዘጋጁት በቀር የበአሉን መቆያ ቦታ ሐሳብ ከዬተ አመጣው ? የቃለ- መጠይቁን ቁራሽ እነሆ ፍቱን ፦ በአሉ እርሶ ጋ ከመድረሱ በፊት የት ቆየ ብለው ነበር የገመቱት ? አቶ አስፋው፦ጥቂት ቀደምብሎ እዚያው አካባቢ ወዳጅ እንደነበረው ተገንዝቤ ነበር ። ፍቱን፦ የማን ቤት ነው? አቶ አስፋው ፦ እሱን አልውቅም ። ፍቱን፦ወንድ ሴት? አቶ አስፋው ሴት ። ፍቱን፦ በዚያች እለት ምሽት እዚያ ቆይቶ ከተመለሰ በኋላ ነበር ከእርሶ ጋር የተገናኛችሁት ? አቶ አስፋው፦ እንደዚያ ነበር አመጣጡን ሳይ የገመትኩት ። ወዳጅ እንደነበረው ተገንዝቤ ነበር ። ተገንዝቤ ነበር የሚለውን ቃል መጠቀም የሚቻለው ለትምርት ለእውቀት ሲሆን ነው ። ውሽማ ነበረችው ለማለት ግንዛቤ አያሻውም አውቅ ነበር ነው የሚባለው ፤ ፈጠራዎን ግዝፈት ለመስጠት ግዙፍ ቃል ተጠቀሙ ። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ራስዎም የተናገሩትን እንዳላመኑበት ነው ። እዚያው ላይ ዝቅ እንበልና የማን ቤት ነው ? ሲል ይጠይቃል ጋዜጠኛው ።

አቶ አስፋው እሱን አላውቅም ሲሉ ይመልሳሉ ። ወንድ ሴት ይልዎታል ጋዜጠኛው ። የእርስዎ መልስ ደግሞ ሴት ይላል ። የማን ቤት መሆኑን ከላይ ሲጠቅሱ አልውቅም ካሉ በኋላ ፤እንዴት የሴት ቤት መሆኑን አወቁ ? እርስዎ ጋር ከመገናኘቱ በፊት ደግሞ ውሽማውጋ ቆይቶ ነው የመጣው ? ሲልዎ ጋዜጠኛው ፣ እንደዚያ ነበር አመጣጡን ሳይ የገመትኩት ይላሉ እርስዎ ። ለካ ግምት ነው የተረጋገጠ ማስረጃ የለዎትም ! ታዲያ በስድስት አረፍተ ነገሮች ወስጥ ሶስት የተለያዩ የተምታቱ ነገሮችን ማቅረብ ወ/ሮ አልማዝን ለመስደብ የተፈጠረ ቅጥፈት መሆኑን አያሳይም ? አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳ ፤ 1) በአሉ ግርማ ከወደአንዲት ሴት ቤት መምጣቱን ገመትኩ አሉ፡ 2) ኮማንደር ለማ ጉተማን ምስክርነት ጠሩ ፤በህይወት የሌለ ሰው ፡ 3) ስሙን ያልጠቀሱትን የአበራ ለማን መምህር ፤ እንዲህ ብሎ አለው አሉ ፡ 4) ወ/ሮ አልማዝ መስሪያ ቤትዎ ደውለው ሲያነጋግሩዎ የሚሉት ጠፋብዎ ፡ 5) አበራ ለማ በግጥሙ ምክንያት አደረገ ላሉት ክርክር ምስክር አድርገው አሁንም ያቀረቡት በህይወት የሌለውን ስብሃት ገ/እግዚአብሄርን ነው ። ከተደረገልዎ ቃለ-መጠይቅ ላይ ከሰጧቸው መልሶች የቱን ተቀብለን የቱን እንተው ፤ የትኛው እውነት የትኛው ሃሰት እንደሆነስ በምን እናረጋግጥ ? እስቲ እኔም እንደርስዎ ልገምት speculate ላድርግ በአሉ ግርማ ከሌላ ሴት ቤት መጣ ብየ ገመትኩ እንዳሉት ማለት ነው ። ከዚያ በፊት በደህናው ጊዜ በአሉ ከደሞዙ ሌላ በድርሰት ስራዎቹ የሚያገኘው ጠቀም ያለ ገንዘብ ነበረው ። እርስዎም ተቸግረው ከበአሉ ገንዘብ ተበድረው ነበር ።

ያን ገንዘብ ሊከፍሉት አልቻሉም ወይም አልፈለጉም ። በመጨረሻዋ እለት ላለፉት 6 ወራት ስራ ስላልነበረው የተበደረውን ገንዘብ ሊከፍለኝ ነው ብሎ ይሆን እንዴ ለወይዘሮ አልማዝ በሰጧቸው ቀጠሮ አማካይነት ከቀጠሮው ስፍራ የደረሰው ። በቃለ- መጠይቅዎም ላይ እኔና እሱን ብቻ የምትመለከት የግል ጉዳይ ነበረችን ብለዋል ከገንዘብ ብድር ጋር የተያያዘች ትሆን ? በአሉን ሰዋራ ስፍራ ድረስ በመውሰድ ለደርግ ሰዎች ማስረከብ እርስዎን ከገንዘብ እዳ ነጻ ሲያደርግዎ ፤ ደርግ ተረጋጋሁ ባለበት በዚያ ዘመን በኦሮማይ እርቃኑን ያስቀረውን የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣኑን በአሉን ያለግርግር እርስዎ ከወሰዱበት ስፍራ በቀላሉ ማፈን ችሏል ማለት ይሆን ? አቶ አስፋው ፤ አንድ ነገር እንዲያስቡ እፈልጋለሁ ። ላለፉት 30 አመታት የውድ ባለቤቴን መውደቂያ እፈልጋለሁ ብላ ያለድካም የምትተጋ አንድ ወይዘሮ በቤቷ ውስጥ ምን ያህል ፍቅር እንዳለ ማሳያ ናት ። ለባለቤቷም ሆነ ለራሷ የፍቅር ተምሳሌት ናት ። እንዲህ አይነት ሴት ደግሞ ለማይነጥፍ የቤት ውስጥ ፍቅር ምንጭ ናት ። እንደማናቸውም ድንቅ ደራስያን ሁሉ በአሉ ግርማም ከቤቱ ያገኘው የነበረው ፍቅር ለድርሰት ስራዎቹ ሁሉ ፅኑ መሰረት ሆኖት ለኛም ለአንባቢዎቹና ለአድናቂዎቹ የድርሰቶቹ ትሩፋት ደርሰውናል ። ለዛሬው በዚሁ ላብቃ ። ከአንበሳው ይብራ !

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on September 8, 2014
  • By:
  • Last Modified: September 8, 2014 @ 6:07 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar