www.maledatimes.com ናይ ፌስቡክ ተፃረፍቲ (የፌስ ቡክ ላይ ተሳዳቢዎች) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ናይ ፌስቡክ ተፃረፍቲ (የፌስ ቡክ ላይ ተሳዳቢዎች)

By   /   September 22, 2014  /   Comments Off on ናይ ፌስቡክ ተፃረፍቲ (የፌስ ቡክ ላይ ተሳዳቢዎች)

    Print       Email
0 0
Read Time:8 Minute, 4 Second

 

በታደሰ ብሩ

 

መንደርደሪያ

 

ፌስ ቡክ ላይ ህወሓትን (ወያኔን) የሚተች ጽሁፍ ሲወጣ ስድቦችን “በብርሃን ፍጥነት” የሚያዥጎደጉዱ ሃያ ያህል ሠራተኞች ሬድዋን ሁሴን ቢሮ ውስጥ መኖራቸውን ሰምቼ ነበር። ይህ ራሱ እየደነቀኝ እያለ ሰሞኑን ሌሎች ዜናዎች ተከታትለው መጡ።

 

በፌስ ቡክና መሰል ማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሚቀርቡበት ትችቶች ፈጣን የስድብ ምላሽ የሚሰጡለት 235 “ባለሙያ ተሳዳቢዎችን” ኢህአዴግ አሠልጥኖ ማስመረቁ ከግንቦት 27 ቀን 2006 ዓም የኢሳት ዜናሰማሁ። ዜናው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ኢሳት በነበረው መረጃ ሰልጣኞቹ 2, 350 የፊስ ቡክ፣ የቲውተር እና የብሎግ አካውንቶችን ከፍተዋል።

 

የኢሳት ዜና ከተሰማ ጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላ ደግሞ 300 ብሎገሮች ለተመሳሳይ ተግባር በባህር ዳር ሠልጥነው የመመረቃቸውን ዜና ሴቭ አዲና የተባለው የፌስ ቡክ ባልደረባዬ አጋራን። እሱ ባለው መረጃ መሠረት ደግሞ ሠልጣኞች 3 000 የፌስ ቡክ አካውንቶች ከፍተዋል።

 

ህወሓት ይህን ልምድ ከየት አመጣው? ይህ ነገር የት ያደርሰናል? ለዚህ ምላሻችን ምን መሆን ይኖርበታል? ይህ አጭር ጽሁፍ እነዚህ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያገለግሉ ውይይቶችን ለመቀስቀሻነት የሚረዱ ሀሳቦችን ይወረውራል።

 

የቻይና 50 ሣንቲም ፓርቲ

 

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በኦክቶበር 2004 አንድ የቻይና የክልል የሕዝብ አስተዳደር ቢሮ በማኅበራዊ ሚዲያ የደረሰበት ወቀሳ ለመቋቋም ከመንግሥት ጎን ወግነው የአፀፋ አስተያየቶችን የሚጽፉ ሠራተኞችን ቀጠረ። ይህም የተቀጣሪ የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳዳቢዎች ጅማሮ ሆነ። በአስተዳደሩ ላይ ወቀሳ ያቀርቡ የነበሩ ሰዎች በተራ ስድቦች ተሸማቀው ዝም ማለታቸውን የተመለከቱ ሌሎች የአስተዳደር ቢሮዎችን ይህ ልምድ ለእነሱም እንደሚጠቅም አስተዋሉ።

 

በ2005 (በእኛ አቆጣጠር 1997) የቻይና የትምህርት ሚኒስትር የኮሌጅ ጋዜጦችን ስልታዊ በሆነ መንገድ እንዲዘጉ አደረገ። ለምሳሌ ናንጅንግ ዩኒቨርስቲ ያትመው የነበረውን “Little Lily” የተባለው ተወዳጅ ጋዜጣ ታገደ። ተማሪዎች ተቃውሟቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች መግለጽ ጀመሩ። የዩኒቨርስቲዎች አስተዳዳሪዎች ካድሬ ተማሪዎችን እየፈለጉ አልያም ለገንዘብ ሲሉ የታዘዙትን ለመፈፀም ፈቃደኛ የሆኑ ተማሪዎችን እየመለመሉ በትርፍ ጊዜ ሠራተኝነት ቀጥሯቸው። የእነዚህ ቅጠረኞች ሥራ በማኅበራዊ ሚዲያ ዩኒቨስቲውን በመደገፍ ነፃ ህሊና ያላቸው ተማሪዎችን መፋለም ሆነ። እዚህም በስድቦችና ማስፈራሪያዎች ብዛት የተቃውሞ ድምጾችን ማዳከም ቻሉ። ከዚህ “ድል” በኋላ እያዳንዱ የትምህርት ተቋም የየራሱን ተሳዳቢ ቡድን ማደራጀት ጀመረ። የተቋም ስምን በተሳዳቢዎች መጠበቅ ራሱን የቻለ የሥራ ዘርፍ ሆነ።

 

በጃንዋሪ 2007 የቻይናው መሪ ሁ ጂንታኦ የቻንናን መልካም ገጽታ ለመገንባት “ጥራት ያላቸው በየድረገጹ አስተያየት ሰጭ ጓዶች” የመኖራቸው አስፈላጊነት ከተናገሩ በኋላ ይኸ “ሥራ” አገር አቀፍ እውቅና አገኘ። ከዚያ ወዲህ የቻይና የባህል ሚኒስትር የማኅበራዊ ሚዲያ “ኮሜንት” አድራጊዎችን በቋሚነት ማሰልጠንና ማሠማራት ጀመረ። በአሁኑ ሰዓት 300 000 የሚሆኑ “ኮሜንት አድራጊዎች” በቻይና የባህል ሚኒስትር ሥር እየሠሩ ይገኛሉ።

 

ከጥቂት “ከፍተኛ ካድሬ ተሳዳቢዎች” በስተቀር አብዛኛዎቹ ተቀጣሪዎች የሚከፈላቸው በሥራቸው መጠን ነው – ማለትም በፃፉት አሸማቃቂ ኮመንት ብዛት ነው። ታሪፉም ለአንድ ኮሜንት ግማሽ የን ነው። በዚህም ምክንያት ተረበኛው ሕዝብ የ50 ሳንቲም ፓርቲ (The 50 Cent Party) የሚል የወል መጠሪያ ሰጣቸው።

የቻይና የስድብ እድገት መዘዝ

 

አብዛኛዎቹ የ50 ሣንቲም ፓርቲ አባላት ክፍያቸው የሚታሰበው በኮመንት ብዛት ነው። በዚህም ምክንያት መንግሥትን የሚተቹ ጽሁፎች እንደወጡ በፍጥነት ይረባረባሉ። በአጭር ጊዜ ብዙ 50 ሳንቲሞን “ለመሸቀል” እንዲያመቻቸው አጫጭር አሸማቃቂ ስብዶችን ዘርዝረው ይዘው እንዳመጣላቸው ኮፒ ፔስት ማድረግ ልማዳቸው ሆነ። በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ግዜ በጽሁፉ ይዘት እና በባላ 50 ሣንቲሙ ኮሜንት መካከል ምንም ዝምድና የለም። ስድቦቻቸውም የተለመዱ ናቸው “ባለጌ”፣ “ከሃዲ”፣ “የታይዋን አሽከር”፣ “የታይዋን ተላላኪ” የታይዋን ሰላይ” የሚሉ እና የመሳሰሉ ስድቦች የተለመዱ ሆኑ። ባለ50 ሣንቲሞች የቻይናን ማኅበራዊ ሚዲያ አቆሸሹት።

 

ይህ ደግሞ በበርካታ ምክንያቶች እንደገና መንግሥትን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆነ።

 

ሀ)    “የ50 ሣንቲም ፓርቲ” የሚለው መጠሪያ በሰፊው ከተሰራጨ በኋላ ኮሜንቶቹ ማሸማቀቃቸው ቀረ። እንዲያውም የሶሻል ሚዲያ ፀሀፊዎች መሸማቀቃቸው ቀርቶ በ50 ሣንቲሞች ስድቦች መዝናናት ጀመሩ፣

ለ)    “የ50 ሣንቲም ፓርቲ አባል” መሆን ራሱ የሚያሸማቅቅ ነገር ሆነ፣

ሐ)   የታይዋን ስም በመጥፎም ቢሆን ደጋግሞ በተነሳ ቁጥር ታይዋንን የሚያስተዋወቅ፣ ቻይናዊያን የታይዋን ሥርዓት ናፋቂዎች እንዲሆኑ የሚያደርግ ነገር ሆነ፣

መ)   የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ከቻይና የልማት አቅጣጫዎች አንዱ ሆኖ እያለ የድረገጾችና የማኅበራዊ ሚዲያዎች መንግሥት በከፈለባቸው ስድቦች መቆሸሻቸው በረዥም ጊዜ የቻይናን ቢዝነስ እንደሚጎዳ ተረዱ።

 

በዚህም ምክንያት ለ50 ሣንቲም ፓርቲ አባላት ተግባር የሥነምግባር ደንብ ይውጣለት ተብሎ የሚከተሉትን ነጥቦች የያዘ ደንብ ወጣ። ይህ የስልጠና ሰነድ አፈልትልኮ ወጥቶ ተሰራጭቷል። ይዘቱም በአጭሩ የሚከተለው ነው።

 

  1. ትኩረታችሁ አሜሪካ ላይ ይሁን፤ ታይዋንን ናቋት፣ እንደሌለች ቁጠሯት፣
  2. የዲሞክራሲ ሃሳቦችን በቀጥታ አትቃወሙ፤ ይልቁንም “የቱ ዲሞክራሲ? ምን ዓይነት ዲሞክራሲ? የት አገር በተግባር ስለታየው ዲሞክራሲ ነው የምታወራው? … ወዘተ እያላችሁ አዋክቡ፣
  3. በዲሞክራሲ ስም ስለተነሱ ረብሻዎች፥ ስለሞቱ ሰዎች፣ ስለተፈናቀሉ ማኅበረሰቦች ማስረጃ በመዘርዘር ዲሞክራሲና ልማት አብረው እንደማይሄዱ የቅርብ ጊዜ ማስረጃዎችን በማንሳት አስረዱ፣
  4. አሜሪካና አውሮፓ በዓለም ዙሪያ ነውጦችን እያስነሱ የድሃ አገር ሕዝቦችን እርስ በርስ እንደሚያፋጁ ምሳሌ እየጠራችሁ ተከራከሩ፣
  5. ደም አፋሳሽ አብዮቶችን እያስታወሳችሁ፤ ምስሎችንም እየለጠፋችሁ ቻይና ውስጥ ነውጥ ቢነሳ የሚደርሰውን ውድመት በአንባቢያን አዕምሮ እንዲቀረጽ አድርጉ፣ እና
  6. የቻይናን ስኬቶች አወድሱ፤ ፈጣን ልማቷና ሰላሟን አድንቁ። የዓለም ኃያል አገር የመሆን ሕልሟን አጋሩ

 

እኔ እስከማውቀው ይህ አሁን ቻይና ያለችበት ሁኔታ ነው። የተሻለ መረጃ ያላቸው ወገኖቻችን ደግሞ የሚያውቁትን ያጋሩናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የቻይናን የውስጥ ፓለቲካ መከታተል ለአገራችን ጠቃሚ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ እወዳለሁ። ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ለማንበብ ለሚፈለግ ለምሳሌ ያህል በዚህ ዓረፍተ ነገር ያሉ ሊንኮችን ይጫን

 

ናይ ፌስ ቡክ ተፃረፍቲ

 

እነሆ ከቻይና ልምድ በመቅሰም ህወሓትም የፌስቡስ ተሰዳቢዎችን ቀጥሮልናል። አዲስ ክፍት የሥራ መደብ በመሆኑ በሚቀጥለው ጥቂት ወራት ውስጥ የእነዚህ ተሰዳቢዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን የሚጨምር ይመስለኛል። እኛም የስነልቦና ዝግጅት አድርገን ልንጠብቃቸው ግድ ይለናል።

 

እስካሁን ባለው ልምድ የኛዎቹ ናይ ፌስ ቡክ ተፃረፍቲ የቻይናዎቹ “አቻዎቻቸው” ሲነሱ በነበሩት ሁኔታ ነው ያሉት። እነዚህን ሰዎች “ኮተታሞች”፣ “ዝተታሞች” ብለው የሚጠሯቸው ባልደረቦች አሉኝ። የአዕምሮ ዝግመት ያለባቸው ስለሚመስል አባባላቸው እውነት አለው። የተለመዱ ስድቦችን ማዥጎድጎች እንጂ ደርዝ ይዘው መከራከር አይችሉም። ስድቦቻቸውም ያረጁና የተሰለቹ ናቸው። “ደደብ”፣ “አህያ”፣ “ጠባብ”፣ “ዘረኛ”፣ “ሻዕቢያ”፣ “የሻቢያ ቅጥረኛ” “የሻብያ ተላላኪ”፣ “አክራሪ”፣ እና በርካታ እዚህ ለመፃፍ የማይመቹ ቃላት ናቸው። በቆሻሻ ቃላት ማኅበራዊ ሚዲያውን በማቆሸሻቸው የፊስ ቡክ አካውንታቸውን የዘጉ ልባም ሰዎች መኖራቸውን አውቃለሁ። አብዛኛው ተጠቃሚ ግን ንቆ ትቷቸዋል።

 

ወደፊት ግን እንዲህ አይቀጥልም።

 

የሰለጠኑት ናይ ፌስ ቡክ ተፃረፍቲ ወደ “ፍልሚያ ሜዳ” የሚገቡት ከተሻሻለ ስትራቴጂ ጋር ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። አሁንም ከቻይና ልምድ በመነሳት ምን ዓይነት ስትራቴጄ ይዘው እንደሚገቡ አስቀድመን መገመት እንችላለን። የራሳችን ግምት ለመስጠት ወያኔ በእርግጥ የሚፈራቸውን ነገሮች ማወቅ ይኖርብናል። እኔ እራሴን በደብረ ጽዮን ጭንቅላት ውስጥ አስገብቼ ሳስብ ያገኘሁት የሚከተለውን ነው።

 

  1. በአገር ውስጥ
  1. ከአገር በቀል ኃይሎች የወያኔ ቀዳሚ ሥጋት ያረፈው ግንቦት 7 ላይ ነው። ወያኔ ግንቦት 7 የድርጅት መዋቅሬን ሰርጎ ገብቷል ብሎ ያምናል። ስለግንቦት 7 ያለው ጥቂቱ መረጃ አስልቶና አሰላስሎ የሚራመድ ድርጅት እንደሆነ ይነግረዋል፤ ይህ ደግሞ ይበልጥ ያስፈራዋል። ትምህርትና ቴክኖሎጂ ባለበት ቦታ ሁሉ ግንቦት 7 አለ ብሎ ያምናል። በዚህ ፍርሃት ምክንያትም በልበሙሉነት የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ በግንቦት 7 አባልነት ይጠረጥራል።
  2. በሁለተኛ ደረጃ የሚፈራው ኃይል ኦብነግን ነው። ኦጋዴን የሚንቀሳቀሰው ለቁጥጥር በማያመች ቦታ ነው። የሶማሊያ ሁኔታም ለአብነግ አመቺ ነው። ኦብነግ ድርጅታዊ ጥንካሬውን ካጎለበተ ፈታኝ ኃይል ሊሆን እንደሚችል ይገባዋል።
  3. በሶስተኛ ደረጃ የሚመጣው የሙስሊሞች እንቅስቃሴን ነው። የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ከቁጥጥሬ ሊወጣ ይችላል ኢህአዴግንም ሊከፋፍለው ይችላል ብሎ ይሰጋል። የሙስሊም አክቲቪስቶች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እውቀት ከፍተኛነት ስጋቱን አባብሶታል።
  4. በአራተኛ ደረጃ የሚመጣው በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ናቸው። It’s the economy stupid እንዲሉ የድንጋይ ካቦችም ሆኑ “የተቀቀሉ” ቁጥሮች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለበትን አሳዛኝ ሁኔታ መደበቅ አልቻሉም። ህጋዊ ፓርቲዎች እመዳፉ ውስጥ እንዳሉ ቢያውቅም በየቦታው የሚታዩ የሥርዓቱ መበስበሶችን ተጠቅመው ድንገት ሊያፈተልኩብኝ ይችሉ ይሆናል ብሎ ይሰጋል።
  5. አምስተኛ ደረጃ የወያኔ ስጋት ኢህአዴግ ነው። የተማከለ አመራር እጦትና መረን የለቀቀው ሙስና የኢህአዴግ ድርጅቶችን እንዳይበታትናቸው ወያኔ ይሰጋል። የኦነግ መንፈስ በኦህዴድ ውስጥ አለ የሚለው ስጋት ወያኔን ምቾት የሚነሳ ነገር ነው።

 

  1. በውጭ ግኑኝነት
  1. ወያኔ ከሁሉም በላይ የሚፈራው የውጭ ጠላት ሻዕቢያን ነው፤ ሻዕቢያን በጦር ኃይል ማሸነፍ እንደማይችል ያውቀዋል።
  2. ሁለተኛው አቢይ የወያኔ የውጭ ስጋት አልሸባብ ነው። መለስ በግብተኛነት የገባበት ድጥ፣ ማጥ ሆኖበታል።
  3. ሶስተኛው ስጋት ያለው ደቡብ ሱዳን ነው። ይህ ገና በግልጽ ያለየለት ቢሆንም እረፍት የሚነሳ ነገር ነው፡
  4. አራተኛውና የመጨረሻው ስጋት ግብጽ ነው። አባይ ለብዙ ሺህ ዓመታት ለኢትዮጵያ ነገሥታት “ረዥም ጦር ባይወጉበት ያስፈራሩበት” ዓይነት ነበር። አቅም ባይኖርም “አባይን እገድባለሁ” ለኢትዮጵያ መሪዎች ማስፈራሪያ ነበር። ያ የዘመናት ማስፈራሪያ ባላዋቂ እጅ ተነካና ግብጽ ሥጋት ሆነች። ለጊዜው ሁለቱም አገሮች ከዛቻ የማያልፉ በመሆኑ ግልጽ ስጋት የለም። ወደፊት ግን ግብጽ ብቻ ሳትሆን ግድቡ ራሱ የስጋት ምንጭ ሊሆን ይችላል።

 

የተመራቂ ናይ ፌስ ቡክ ተፃረፍቲ ስትራቴጂዎች

 

አሁን አንባቢዎቼ የተመራቂ “ናይ ፌስ ቡክ ተፃረፍቲ” ስትራቴጂዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችል መገመት ይችላሉ ብዬ አምናሉ። ተራ ስድቦችን ቀንሰው ተቀርቋሪና ሩቅ አሳቢ መስለው ለመቅረብ ይሞክራሉ። ግን የፈለገውን ያህል ቢጥሩ ተፈጥሯቸው ስለማይፈቅድላቸው እጅግም መለወጥ አይችሉም። እነሱ ሳይሳደቡ ማውራትም ሆነ መፃፍ አይችሉበትም፤ እኛም እነሱን ለይተን ለማወቅ ጊዜ አይፈጅብንም። በስጋት ደረጃቸው ቅደም ተከተል ከላይ የቀረበውን ዝርዝር ገልጠው፤ የላዩን ታች የታቹን ላይ አድርገው ነው “ሜዳ” የሚገቡት። ዋና ዋናዎቹን ስትራቴጂዎችን ብቻ ላንሳ።

 

  1. አዳዲሶቹ ናይ ፌስ ቡክ ተፃረፍቲ ስለሻዕቢያ ብዙ እንዳይጽፉ መመሪያ ይሰጣቸዋል። ሆኖም አንዳንዴ – በነገር መሃል – ሻዕቢያን አናንቀው በፈለጉበት ቀንና ሰዓት ከአዲግራትና ዛላንበሳ በሚልኩት ፓሊስና ሚሊሽያ ሊያሸንፉት የሚችሉ ደካማ ኃይል አስመስለው ያቀርቡታል።
  2. የአዳዲሶቹ ተፃረፍቲ “ታርጌት” ጠላት አገር ግብጽ ይሆናል። በሽፍንፍንም በአጠቃላይ አረቦች ተነስተውብናል የሚል ስውር መልዕክት ለማስተላለፍ መጣራቸው አይቀርም። ግልጽ ስጋት ባይኖርም ግብጽ ላይ ያቅራራሉ፣ ይፎክራሉ።
  3. ግንቦት 7፣ ኢሳት፣ ሻዕቢያንና ግብጽን አሳክረው ያቀርባሉ።
  4. የሚቀጥለው ዓመት ምርጫ ትልቅ ስጋት ይዞ እንደሚመጣ አድርገው ማውራታቸው አይቀርም።
  5. ስለ ኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ ሲያነሱ ሆነ ብለው ከአልሸባብ፣ አልቃይዳ እና ቦኮ ሃራም ጋር እያያዘው ይሆናል።
  6. አሁኑ ኢቲቪ በርትቶ እየሠራባቸው ያሉት “በአብዮቶች የማስፈራራት ስልት” ተጠናክሮ ይቀጥላል። ሊቢያ፣ ግብጽ፣ ሶሪያ፣ ዩክሬን በማስፈራሪያነት የሚነሱ አገሮች ይሆናሉ።
  7. በምግብ ራሳችን ችለናል፤ መካከለኛ ገቢ አላቸው አገሮች ምድብ ደርሰናል፤ አድገናል፤ አምሮብናል … የሚሉ ጉራዎች ተፋፍመው ይቀጥላሉ።

 

አዳዲስ ተመራቂዎችን እንዴት እንቀበላቸው

 

ይህ ጽሁፍ ከአቀባበል ዝግጅቶቻችን አንዱ ነው። ከመምጣታቸው በፊት ምን ይዘው ለመጣት እንደተዘጋጁ፤ ምን ዓይነቱ ስልጠና እንደተሰጣቸው የምናውቅ መሆኑ ማወቃቸው አዲሱ ሥራቸውን በመሸማቀቅ እንጂምሩት ያደርጋቸዋል። እንደሁኔታው የሚለዋወጥ ሁኖ ሶሻል ሚዲያ (በተለይም ፌስ ቡክ) የምንጠቀም ሰዎች የሚከተሉትን መርሆዎች በሥራ ላይ ብናውል ይበጃል ብዬ አምናለሁ።

 

  1. ሶሻል ሚዲያን በተለይም ፌስቡክን ለእነሱ አለመቀቅ፤ በሚሰጧቸው አስተያየቶች በመሳቀቅ ፋንታ መዝናናት።
  2. ናይ ፌስ ቡክ ተፃረፍቲዎችን ማስነወር፤ “ሥራቸው” ምን ያህል አዋራጅ እንደሆነ መንገር፤ እነሱን በማብሸቅ መዝናናት።
  3. ከእነሱም መካከል ልባሞች አይጠፉምና ምስጥራዊ ግኑኝነት መመሥረት ሆኖም በቀላሉ አለማመን።
  4. የሚታወቁበትን መንገድ፣ ዘይቤዎቻቸውን፣ ስልቶቻቸውን እየተከታተሉ ማጋለጥ።
  5. የሚተማመኑ ወዳጆች የውስጥ ክበብ እና ለእውነት የቀረበው እውነታ (Virtual reality) እውነት እንዲሆን መጣር፤ ለምሳሌ በፌስ ቡክ የተዋወቁና በተወሰኑ መጠንም ቢሆን የሚተማመኑ ወዳጆች ከፌስ ቡክ ውጭ በሌሎች ሚዲያዎች የሚገናኙበት መንገድ መፍጠር።
  6. በነፃነት ማሰብ የጀመሩ ወጣቶች የፈጠራ አቅም አስገራሚ ነው፤ ናይ ፌስ ቡክ ተፃረፍቲዎች ላይ መሳለቂያ የፈጠራ ዘዴዎችን መጠቀም።
  7. በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ወያኔን የሚተቹ ጽሁፎን የሚጽፉ ወገኖቻችን ለዚህ ተግባር በስማቸው በተከፈቱ አካውንቶች ፈጽሞ አለመጠቀም ። ይህ በብዙዎች የሚታወቅ ቢሆንም ማንሳቱ ይጠቅማል።

 

እንደማሳረጊያ

 

እኔ፣ እንኳንስ በሳይበር ትግል ውስብስብ የሆኑ የሰላማዊ ትግል ስልቶችን ተጠቅመንም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ የሥርዓት ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብዬ አላስብም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ጉልበት መጠቀም የማይቀር እዳ ነው ብዬ አምናለሁ። ያም ሆኖ ግን ሁሉም ሰው በጉልበቱ መስክ አይሳተፍምና እያንዳንዱ እንደፍላጎቱና አቅሙ ለትግሉ የሚያበረክተው ነገር አለ። ትግሉ የሚካሄደው በሁሉም ቦታዎች ነው።

 

በተለያዩ መስኮች በሚደረጉ ትግሎች መካከል ያሉ ግኑኝነቶች ለጊዜው በግልጽ ላይታይ ይችላሉ። በመካከላቸው ያለው ከፍተኛ መደጋገፍ ግን በግልጽ የሚታይበት ጊዜ ይመጣል። በየተየሰለፍንበት ሜዳ ወያኔን ማሸነፍ ዓላማችን አድረገን መነሳት ይኖርብናል። ናይ ፌስ ቡክ ተፃረፍቲዎች ዝም ሊያሰኙን በፍጹም አይገባም።

አስተያየት ካለዎት tkersmo@gmail.com

 

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on September 22, 2014
  • By:
  • Last Modified: September 22, 2014 @ 10:19 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar