www.maledatimes.com ፊልም፣ “ሰባተኛው ስነ-ጥበብ” - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፊልም፣ “ሰባተኛው ስነ-ጥበብ”

By   /   September 21, 2012  /   Comments Off on ፊልም፣ “ሰባተኛው ስነ-ጥበብ”

    Print       Email
0 0
Read Time:31 Minute, 19 Second
በሰሎሞን ተሠማ ጂ. (semnaworeq)
የአንድ ሀገር ህዝብ በጦር ሜዳ ግንባር የመጣበትን ወራሪ ጠላት መክቶ በድል አድራጊነት ቢወጣ ባለድል መሆኑ እሙን ነው፡፡ ድሉ በወታደራዊው ጦርነት የመጨረሻውን ትግል አድርጎ ለማሸነፉ ምስክር ነው፡፡ በባህሉና በማንነቱ በኩል ግን የሚመገበው፣ የሚለብሰውና የሚነጋገርበት ዘዬ፣ ወራሪዎቹ ትተውት የሄዱትን ርዝራዥ ብኂል ነው፡፡ ጦርነቱ ብርቱ ብርቱ የጦር አበጋዞችን እንጂ፣ ቆራጥ የባህል ጠበቆችን ወይም ስለባህልና ስለሥነ-ጥበብ ተምረው የተዘጋጁ ኃይሎችን (ልሂቃን) ስላላዘጋጀ፣ ከፍ ያለ የጥበባዊ ሽንፈት ይከተላል፡፡ የባዕዳንን ርዝራዥ ባህል በሲኒማና በመዝናኛ ውጤቶች እየተመገበ የሚያድግ ወጣት እንደምን አድርጎ የራሱን ታሪክ ሊተርክ ይችላል? እንዴትስ የራሱን እሴቶች ዋጋ ሊሰጥ ይችላል? ስለሆነም ወጣቱ  የውንብድናና የወላባነትን ባህሪ ብሂሉ ያደርገዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ፣ የቬትናም፣ የላቲን አሜሪካንና የበርካታ የመካከለኛው ምስራቅ አገር ሕዝቦች የጦር ሜዳ ወራሪዎቻቸውን በወኔ ቢመክቱም ቅሉ፣ የወረራቸውን የምዕራባዊያን ባህል ማሸነፍ አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም፣ ኤድዋርድ ሳይድ፣ Orientalismበተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ እንዳተተው፣ “መሪዎቹና ሕዝቡ ሙሉ ኃይላቸውን ጦርነቱ ላይ አድርገውት ስለቆዩ፤ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውንና ማንነታቸውን በዝንጓዔና በቀልበ-ቢስነትም ስለሚዘነጉት ነው” ይላል፡፡
 
ኢትዮጵያዊያንም የአድዋንና የአምስቱን ዓመት የፀረ-ወረራ ትግል ካካሄዱ በኋላ ታሪካቸውንና ባህላቸውን እንዲዘነጉ የጣሊያን ወራሪዎችም ሆኑ ቆንስላዎቹ ያልተቆጠበ ጥረት አድርገዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሥርግው ኃብለ ሥላሴ “ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ፣ የአዲሱ ሥልጣኔ መስራች” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት “የመጀመሪያው የሲኒማ ቤት በአንድ የፈረንሳይ ተወላጅ በ1890ዎቹ ተከፍቶ የነበረ ቢሆንም ቅሉ፣ በዚያን ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩት የውጭ አገር ሰዎች ቁጥር መጠነኛ ስለነበረ፣ ያሉትም ሲኒማ ለማየት ስላልፈለጉ፣ ኢትዮጵያዊያኑም ቶሎ ስላልለመዱ ኪሳራ ላይ ወደቀ፡፡ የሲኒማ ቤቱ ባለቤትም ይህ ንግድ እንደማያዋጣው ስላወቀ መሣሪያውን ለኢጣሊያው ሚኒስትር ቺኮዲኮሳ ሸጠለት” (ገጽ 444)፡፡ ቺኮዲኮሳም የሲኒማ ማሳያውን፣ አፄ ሚኒሊክ ለአዲስ ግኝት የነበራቸውን ጉጉት ስለሚያውቅ ገጸ በረከት አቀረበላቸው፡፡ በደስታም ተቀበሉት፡፡ አንድ የአርመን ተወላጅ እያንቀሳቀሰው ለብዙ ጊዜ ንጉሱና ንግስቲቱ ሲኒማ ሲያዩ ከቆዩ በኋላ በድንገት ተሰናከለ፡፡ አውቶሞቢል ይዞ የመጣው እንድሊዛዊው ቤንትሌይ ጠግኖት እንደገና መታየቱ ቀጠለ (ፕ/ር ሥርግው፤ ገጽ 444)፡፡
በ1902 ዓ.ም የመጀመሪያው ሲኒማ ቤት ቴድሮስ አደባባይ አጠገብ “ፓቲ” የሚሰኘው ሲሆን (የዛሬው ሜጋ አምፊ ቴያትር ያለበት ቦታ ላይ) የተከፈተ ሲሆን ያቋቋሙትም ሁለቱ ወንድማማቾች ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን የፈረንሳይ ተወላጆች ቢሆኑ፣ የጣሊያን ዜግነት ነበራቸው፡፡ ሕዝቡም ሲኒማ ቤቱን “የሰይጣን ቤት” እያለ ነበር የሚጠራው፡፡ ከ1908 እስከ 1926 ዓ.ም ድረስም አምስት ሲኒማ ቤቶች ተከፍተው ሲኒማ ያሳዩ ነበር፡፡ የኢጣሊያ ወራሪዎች ወደአዲስ አበባ ሲገቡ ከሰይጣን ቤት በስተቀር ሁሉም ሲኒማ ቤቶች ተቃጠሉ (የፊልም ማዳበሪያና መቆጣጠሪያ ዋና ክፍል፣ ገጽ 4-7)፡፡
ሆኖም ወራሪው ኃይል የሲኒማን ጠንከራ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያነቱንና ኃይሉን ስለተረዳ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቃጠሉትን ሲኒማ ቤቶች አድሶ፤ ሲኒማ ኢታሊያ (የዛሬው ሲኒማ ኢትዮጵያ ነው)፣ ሲኒማ አምፒር (አሁንም በቦታው ላይ አለ)፣ ሲኒማ ማርኮኒ (አሁን የብሔራዊ ቲያትር ሕንፃ ያረፈበት ቦታ ላይ ነበር)፣ ሲኒማ ቺንኮ ማጆ (አራት ኪሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሣይንስ ፋኩሊቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገኝ ነበር)፣ ሲኒማ ዲ መርካቶ (የዛሬው ራስ ቴያትር ነው)፣ ሲኒማ ዲፖላቮሮ (የተግባረ ዕድ ት/ቤት የፊት ለፊቱ ህንፃ ወስጥ) እና በድሬዳዋ ሲኒማ አምፒርና ሲኒማ ማጀስቲ የተባሉትን፤ በሐረር ሲኒማ ዲ ሮማን፣ በጅማና በጎንደር እንዲሁም በደሴ ሲኒማ ቤቶችን የወራሪ ኢጣሊያን ሹማምንትና ዜጎቻቸው ከፍተው ነበር (የፊልም ማዳበሪያና መቆጣጠሪያ ዋና ክፍል፣ ገጽ 4-7)፡፡
ከላይ የቀረቡት ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ፣ በአድዋና በሌሎችም የጦር ግንባሮች የተመከተው የወራሪ ኢጣሊያ ኃይል፣ የኢትዮጵያውያንን መንፈስና ወኔ ለማኮላሸት ሲኒማን እንደትልቅ የፕሮጋንዳ መሣሪያ ስለመጠቀሙ ነው፡፡ ታዳጊዎቹ ኢትዮጵያውያንም የራሳቸውን ታሪክ ሳያውቁ፣ የወራሪውን ኃይል ስልጣኔና ዕድገት ያለምንም ከልካይ እንዲጋቱ ተደረጉ፡፡ ስለሆነም፤ “ሀ፣ ራስህን እወቅ!” የሚለው መሪ-ቃል ተዘንግቶ “ለ፣ ሌሎችን አጥና! ሌሎችንም ምሰል!” ወደሚል አጓጉል ፈሊጥ አሽቆለቆለ፡፡ ይባስ ብሎም፣ “የሌሎችን ታሪክና ኪነ-ጥበብ ኮርጅ፣ የሌሎችንም ሥነ-ጥበብ ቅዳ!” ወደሚል አዘቅት ውስጥ ጅው ብሎ ገባ፡፡ ይኼው የመውጫው ጭላንጭል የጠፋቸው የፊልም ሰሪዎች በተለይ፣ የጥበብ ባለሙያዎች በጅምላ በሥመ-አርቲስትነት ጭለማ ውስጥ ገብተው ይደናበራሉ፡፡
                        ***************************************

የፊልም “ዘይቤ” ማለት የፊልምና የሲኒማ “ምንትነት”ን ለመበየን የሚውል ትርጓሜ ነው፡፡ “ፊልም” የተንቀሳቃሽ ምስሎች ሁሉ የወል ስያሜ ነው፡፡ ለብዙኃኑ፣ “ፊልም” ማለት የእንግሊዝኛውን ‘movie’ እንደማለት ነው፡፡ የእንግሊዝኛው ‘movie’ ልማዳዊ ባህልን እንጂ ጥበባዊነትን አይገልጽም፡፡ የፈረንሳይኛው ሲኒማ (cinema) ስርወ-ቃሉ እንደሚያመለክተው ከግሪክኛው ‘kineine’ ተንቀሳቃሽ ምስል or ‘to move’ ጋር የተወራረሰ ነው፡፡ ተንቀሳቃሽ ምስሎቹም ጥበባዊ ለሆነ ፋይዳ እስከዋሉና ጥበባዊነታቸውንም እስከጠበቁ ድረስ “ሲኒማ” ናቸው (Anatomy of Film, 2005: 1-2)፡፡

የሲኒማነት ደረጃ ላይ የደረሱ ፊልሞች ሊያሟላቸው የሚገባቸው አራት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ፣ የመተረክ ዕውቀትና ክህሎት ነው፡፡ ለመተረክ ደግሞ የራስን ታሪክ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው የራሱን ታሪክ ሳያውቅ አንደምን አድርጎ የሌሎችን ታሪክ ለመተረክ ይችላል? የራስን ታሪክ ማወቁ ሁለት ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በመጀመሪያ፣ በራስ ታሪክ ላይ እምነት ለማሳደር ማስቻሉ ነው፡፡ የራስን ታሪክ አውቆና አቀላጥፎ መተረክ የሚችል፣ የሌሎችም ታሪክ ለመተረክ ይችላል (ሃይሌ ገሪማ፣ 1996)፡፡ ቀጥሎም፣ የራስን ታሪክ ካለማወቅና ካለመተረክ የሚመነጩ ችግሮች ዞሮ ዞሮ ወደ ኩረጃና ወደ ጥራዝ-ነጠቅነት ስለሚከቱ ውጤቱ አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡
የሲኒማነት ደረጃ ላይ የደረሱ ፊልሞች በሁለተኛነት ሊያሟሉ የሚገባቸው ነጥብ አለ፤ እርሱም ብሔራዊ እውነትና ውበት እንዴት እንደሚሰምር መረዳት ነው፡፡ “እውነት” ሲባልም የከያኒው ውስጣዊ እምነትና አቋም ከከያኒው ውጫዊና ከባቢያዊ እውነታ ጋር የታረቀና ስምም እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ራሱ የማያምንበትን ነገር ለሌሎች መናገርም ሆነ፣ የሌሎችን እውነት ክዶ መሟገት ትርፉ ባዶ ልፈፋ ነው፡፡ ብሎም ለፕሮፓጋንዳና ለወቅታዊ ፍጆታ ሰልፈኛ ከመሆን አያድንም፡፡ መገናኛ ብዙኃን ዓባይ-ዓባይ እያሉ ሲያላዝኑ ሰምቶ፣ “ዓባይ” ወይም ናይል ብሎ መስገብገብ ትርፉ ባዶ ነው፡፡ ስለባህር በር ጉዳይ ወቅታዊ አጀንዳ ሲሆንም “የባህር በር” ብሎ መጣደፍ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ እነዚያን “ፊልሞች” ከጥቂት አመታት በኋላ ዞር ብሎም የሚያየው ተመልካች አይገኝም፡፡ የፊልም ሰሪውንም ለእውነት ያልቆመና ሸቃይ መሆኑን ያጋልጣል፡፡
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በስገብገብም የፊልም ስራውን በተለይ፣ የስነ-ጥበቡን ዘርፍ ባጠቃላይ ቅጥ የለሽ (Formless) ያደርገዋል፡፡ ከአርስቶትል ጀምሮ እስካሁን ድረስ የተነሡት የስነ-ውበት ሊቃውንት እንደሚያስገነዝቡት ከሆነ፣ ያለቅርጽ ምንም ዓይነት ውበት መግለጫ መንገድ የለም፡፡ “ሲያዩት ያላማረ….” የሚለው የሃገራችን አባባል ከንጽሕና ጋር ባቻ ሳይሆን ከቅርጽ ጋርም ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ ስለሆነም፣ ስነ-ውበትን መረዳትና ለኪነ-ጥበባዊ ስራውንም ተስማሚ ቅርጽ መስጠት የአንድ ከያኒ ግዴታው ነው፡፡ “የፊልም ይዘቱና የአቀራረብ ስልቱም ስነ-ጽሑፋዊ ነውና ቅርጽና ቅጥ ያስፈልገዋል፤” ይላል በርናርድ ዲክ Anatomy of Film በተባለው መጽሐፉ ውስጥ፣ ገጽ 254-6 ይመልከቱ)፡፡
በሦስተኛ ደረጃም፣ አንድ የፊልም ሠሪ ስለቋንቋውና በቋንቋው አማካይነት ሊያስተላልፈው ስለሚፈልገው እውነትና ውበት ትክክለኛ አቋም ሊኖረው ይገባል፡፡ የብዙኃኑን ሕይወትና አኗኗር ለማሳየት ተነስቶ የተንጣለለ የተውሦ ቪላና ፎቅ ቤት ውስጥ መንከላወስ የቋንቋ እጥረትን ያስከትላል፡፡ ስለሆን፣ ከያኒው ስለሚያውቀውና እየኖረበት ስላለው ሕያወት ቢተርክ ያዋጣዋል፡፡ እውነታውን በሚያውቀውና በገባው መልኩ ሌሎች እንዲያውቁትና እንዲገባቸው ለማድረግ ቋንቋና እውነታ እንደሰልባጅ አያጥረውም፡፡ የፈረደባቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮችና ፖለቲከኞች፣ ቀሳውስትና ባለጸጐች ላይ ፊጥ ከማለቱ በፊት የራሱን ኑሮና ሕይወት፣ ታሪክና እምነት መርምሮና ተፈላልጎ መጻፍ ከግልብነት ያድናል፡፡ የፕሮፌሰሩን የመነጽር አደራረግና አስተያየት ሳይመረምሩ፣ ወይም የኢንቨስተሩን ሚስት የመዋቢያ ቁሳቁስ አጠቃቀምና አኳኋን ሳያጠኑ፣ የአዛውንቱን የእጅና የፊት እንዲሁም የሰውነት እንቅስቃሴዎች ከነለዛቸው ሳይረዱና ሳያውቁ የተዋናዩ ላንቃና መንጋጋ ውስጥ ለመጠቅጠቅ መጀል አጉል ነው፡፡ የፊልም ሠሪ መጀመሪያውኑ ስለባለታሪኮቹ ማንነትና ስለሚናገሩት ቋንቋም በቅጡ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡
በአራተኛ ደረጃም፣ አንድ የፊልም ሠሪ የፈጠራቸው ገጸ-ባህሪያት ባለው ህብረሰብ፣ ባህል፣  ተፈጥሮና በስርዓቱ ጉድፎች ላይ የሚያምጽ መሆን አለበት፡፡ ዓመፁም ለበጎ ነው፡፡ ለለውጥ ነው፡፡ ወደ ለውጥ ነው፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ የማያቋርጥ የለውጥ ሂደትና ትግልም ነው፡፡ የለውጥ ትግሉና መፍጨርጨሩም ስልጣኔን ለማወጅ ነው፡፡ ሥልጣኔ፣ የብዙ እሴቶች ድምር ነው፡፡ ሰው ወደ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ሠላም፣ ፍቅር፣ እውነት፣ ነፃነትና ሌሎችም ረቂቅ እሴቶች ዝንት ዓለም ሲፍገመገም ይኖራል፡፡ በፊልም ወስጥ ያሉት ገጸ-ባህሪያትና ፊልሙም ሰብዓዊ ውበትንና እውነትን ለማምጣት ስለሚታገሉና ስለሚያምጹ ሰዎች መሆን ይገበዋል፡፡ ሲረገጡና ሲበደሉ፣ “በጄ!…..እሺ!….አሜን!….ወይም ተመስጌን!” የሚሉ ልፍስፍስ ባለታሪኮችን á‹­á‹ž የሚነሳ ፊልም ሠሪ ሁለት ግድፈቶችን ፈጽሟል፤ አንደኛ፣ የሰው ልጅ በለውጥ ጅረት ውስጥ ወደ ስልጣኔ የሚያደርገውን በውጣ ውረድ የተሞላ ትግልና፤ ሁለተኛም፣ ከያኒው ለሰብዓዊ ውበትና ክብርም ያለውን ዝቅተኛ ግንዛቤ ያሳያሉ፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸውን አራት ነጥቦች ቸለል ካልናቸው ወደብሔራዊ የፊልም ግብና ዓላማ መቼውንም አንደርስም፡፡ ዛሬ በተስፋና በጉጉት ለሰዓታት ፊልም ቤቶች ደጃፍ ላይ ተሰልፎ ለማየት የተነቃነቀው ተመልካቸም ደብዛው የጠፋል፡፡ የተመልካቹ ንቃተ-ሕሊናም እያደገና እየጎለበተ ነው፡፡ በTV-Africa ፋንታ፣ ደህና ደህና ፊልሞችን በተለያዩ Channels በማየት ላይ ነው፡፡ በተንቀሳቃሽ ምስሎች በኩል ንቃተ-ሕሊናው እያደገ ነው፡፡ ዓይኖቹንና ቀልቡን ከተንቀሳቃሽ ምስልና ከቴክኖሎጂ ጋር እያለማመደ ነው፡፡ አንድ ቀን፣ ዛሬ ላይ የተሠሩለትንና የተሠሩበትን “ነገሮች” አሽቀንጥሮ ይጥላቸዋል፡፡
***************************************
የአገራችን ፊልም ሞካሪና ሠሪ “ነን ባዮች” የፊልምንና የሲኒማቶግራፊን ዘይቤዎች በቅጡ ሳይረዱ፣ ድርጉስ ብለው ከገቡ በኋላ አጉል መንፈራገጥ ላይ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ በታኅሣሥ 2001 ዓ.ም እንደገለጸው፣ “ወደ ፊልም ድርጉስ ብለው የመጡት ወጣቶች በመምጣታቸው መበበረታታት አለባቸው፡፡ ሆኖም፣ ፊልምና ሲኒማቶግራፊ ከባድ ዋናተኛ መሆንንና የሲኒማ ቋንቋንም መልመድ የግድ ይፈልጋል፡፡ በተለይም ‘ከቋንቋው ጋር የእኔ ባህልና የምሠራው ፊልም ዘይቤ እንዴት ነው የሚዛመደው?’ ብሎ ፊልም ሠሪው ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡”
በአገራችን ለወጣቶች አእምሮ መደናበር አንዱ ዋና ምክንያት፣ ከውጭ እየተግበሰበሰ የሚገባው ዝባዝንኬ ፊልምና ስነ-ጥሑፍ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ጥሩ ቴአትር አቅርቦ ብዙ ተመልካች ያጣ አንድ ዝነኛ ደራሲ፣ “አዝናለሁ ከነቶም ክሮዝና ከነብራድ ቢት ጋር መወዳደር አልችልበትም!” ሲል ተደምጧል፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ነገር ግን ፈላጊ አለው ተብሎ ደግሞ የባሕር ማዶውን ዝባዝንኬና እንቶፈንቶ ዓይነት በኢትዮጵያችንና በኢጥዮጵዩውያንም ዘንድ እንዲስፋፋ አያስፈልግም፡፡ መፈቀድም የለበትም፡፡ ግባችን የሰብዓዊነትን ውበት የሚያሳምር፣ የአዲሲቱን ኢትዮጵያዊነት ባሕሪ የሚያጎለምስና የረቀቀ ሥነ-ጥበብ መሆን አለበት፡፡ “አዲሱን ኢትዮጵያዊነት” ሲባልም፣ ወደዕድገትና መሻሻል ለመገሥገሥ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊ፣ ማህበራዊና በሥነ-ጥበብ መስኮችም የሚዋትተውን ሕዝብ ውጣ ውረድ መስታወት ሆነው ማሳየት አለባቸው፡፡
ፊልምን ከመስታወት ጋር የሚያመሳስሉት ብዙ የማርክሲዝምን ፈለግ የሚያቀነቅኑ ሊቃውንት አሉ፡፡  “በፊት መስታወት አማካይነት አንድ ሰው መልኩን አይቶና መርምሮ ለማሳመር ይችላል፡፡ በፊልም አማካይነትም አንድ ሰው ወይም ሕዝብ መልኩን፣ መንፈሱን፣ ሞራሉንና በጠቅላላው አኗኗሩን ተመልክቶና ተመራምሮ፣ ስሕተቱን ለማረምና ኑሮውንም ለማቃናት ፊልም የዋጋ ድልድል አለው” ይላሉ፡፡ ለነዚህ ሊቃውንት ፊልም ከሰፊው ሕዝብ ጋር የመገናኛ ዘዴ (means of Communication) ነው፡፡
ይህ እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም ፊልም፤ የስነ-ጽሑፍን፣ የፎቶግራፊን፣ የሙዚቃንና የዳንስን፣ የቲያትርንና የሰርከሥን፣ የስዕልን፣ የምትሃትን (የአስማትን)ና የሌሎችንም ጥበባዊ ዘርፎች ባንድነት አዋሕዶ የያዘ በመሆኑ “ሰባተኛው ስነ-ጥበብ” ብለው የሚጠሩትም አልጠፉ (ሲን ኩቢት፣History of Ideas በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 327 ላይ እንደገለጸው) ነው፡፡ በተመልካቹም ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ግምት አለው፡፡ የፊልም ስራ ንግድን ብቻ ሳይሆን፣ ስነ-ጥበባዊ በሆነ አቀራረቡ ከዋነኛዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች መሃከልም አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም፣ “የፊልም ሠሪው ከባድ ሕዝባዊ ኃላፊነት ያለበት ነው” ይላሉ የማርክሲስት ፈለግ አቀንቃኝ ሊቃውንት፡፡
ያምሆነ ይህ፣ አንድ ብሔራዊ ፊልም፣ መመሥረቱና የፊልም ስራ ሙከራው መጀመሩ ምስጋናና መደፋፈር የሚገባው ቢሆንም፣ ቀጣዩቹ ፊልሞች አባት እንደሌለው ዲቃላ “…አባቷ ማነው?” ወይም ….የራሳችን የመረጃና የደሕንነት ቤት እንደሌለን ሁሉ “FBI” ማለቱ፣ ወይም የራሳችን የሚስጥርና የማዕከላዊ ድርጅት እንደሌለን ሁሉ “CIA” መሆኑ ያስተዛዝባል፡፡ ይባስ ብሎም እንደወረደ The Mechanic የሚለውን “ሜካኒኩ”፣ The Transporter የመለውን “ባለታክሲው፣ ቅብርጥሱ” ማለቱ፣ የፊልም ሥነ-ጥበባችን አንዳችም ብሔራዊ ግብና ዓላማ የሌለው “ድቅል” መሆኑን ያሳብቃል፡፡ (ይኼ ሁሉ ሃተታ የቀረበው ወደ ፊልሞቹ ይዘትና መልዕክት ገና ሳንገባ ነው፡፡ ወደዚህ ጉዳይ ላይ በቀጣዮቹ ጽሑፎቼ ተራ በተራ እመለስባቸዋለሁ፡፡)
ብሔራዊ ግብና ዓላማ ያለው ፊልም ስለመደርጀቱ ጉዳይ ተስፋዬና እምነቴ በታዳጊ ወጣቶቹ ላይ ነው፡፡ እውቀትንና ብሔራዊ ስሜትን ከጥበባዊነት ጋር አጣምረው ዕፁብ-ድንቅ ፊልሞችን እንደሚያሳዩን  የጸና ዕምነት አለኝ፡፡ የፊልም ቋንቋን ከቲያትራዊ ቋንቋና ትወና ለይተው ያወቁ፣ የራሳቸውን ታሪክና ባህል በትክክል የተረዱ፣ ታሪክን መተረክ የሚችሉ፣ እውነትንና ውበት አጣምረው መመርመር የሚችሉ፣ የሚናገሩትን ቋንቋና የባለ-ታሪኮቹንም ቋንቋ በደንብ ያወቁ፤ ብሎም ለሰብዓዊ ክብርና ውበት ዕቁብ ያላቸው ወጣቶች ወደመድረኩ በድንገት ብቅ እንደሚሉ አልጠራጠርም፡፡ እንደሻንበል አበበ ቢቂላ በባዶ እግራቸው ሮጠው ታሪክ የሚሰሩ የፊልም ስነ-ጥበብ ባለድሎችን በቅርቡ እናገኛለን፡፡ (የዚያ ሰው ይበለን!!!)
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 21, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 21, 2012 @ 4:12 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar