www.maledatimes.com ጨለማው ሰው - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ጨለማው ሰው

By   /   September 21, 2012  /   Comments Off on ጨለማው ሰው

    Print       Email
0 0
Read Time:19 Minute, 17 Second

ጨለማው  ሰው

Dark man

በርካታ የኢትዮጵያውያን ድረ ገጾች (ኢንተርኔቶች) አሉ፣ በርካታ የኢትዮጵያውያን የፓልቶክ መነጋገሪያ ክፍሎች (ፓልቶክ ሩምስ) አሉ፣ በርካታ የኢትዮጵያውያን ሬዲዮ ጣቢያዎችና ጋዜጦች አሉ።  የድረገጾቹን አዘጋጆች እናውቃቸዋለን – እዚያ ላይ አስተያየትና መጣጥፍ የሚያቀርቡትን ብዙዎቹን ግን አናውቃቸውም። ብዙዎቹን የፓልቶክ ውይይት ክፍል አስተዳዳሪዎች (አድሚንስ) እናውቃቸዋለን – እዚያ ላይ መጥተው የሚያወሩትንና አስተያየት የሚሰጡትን ብዙዎቹን ግን አናውቃቅቸውም። ብዙዎቹን የኢትዮጵያውያን ሬዲዮ ጣቢያ አዘጋጆች እናውቃቸዋለን-  እዚያ ላይ እየደወሉ “የትግል መመሪያ” የሚሰጡትን ብዙዎቹን ግን አናውቃቸውም። ብዙ ኢትዮጵያውያን የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ናቸው – ፌስ ቡክ ላይ የለጠፉትን እንጂ ፣ እውነተኛ ማንነታቸውን የብዙዎቹን አናውቅም። የለጠፉትን ፎቶ ፣ እነሱ ናቸው ብለን እናምናለን እንጂ፣ በርግጥ እነሱ መሆናቸውን ምለን መናገር አንችልም። መመሪያ ሲሰጡ እናያለን እንጂ ማን እንደሆኑ አናውቃቸውም።

 

እነዚህ ሳይታወቁ የሚናገሩ፣ ሳይታወቁ አስተያየት የሚስጡ፣ ማንነታቸው የማይታወቅ ማብራሪያ ሰጪዎችና ትግል መሪዎች፣ “ምሁራን” እና “ተንታኞች” ፣ “ሰባኪያን” እና “ዲያቆኖች” ፣ “ሃይለኛ ተቃዋሚዎች” እና “ሃይለኛ ደጋፊዎች” ፣ “አባዎች” እና “ሼኮች” በርግጥ እነማን ናቸው? እነሱ እንደሚሉት አባዎቹም አባዎች፣ ሼኮቹም በርግጥ ሼኮች መሆናቸውን በምን እናውቃለን?

 

በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ስለ አገራቸውም ሆነ ስለ መላው ዓለም ሁኔታ፣ ስለ ፖሊቲካውም ይሁን ስለኢኮኖሚው መረጃ ይፈልጋሉ። በሚነሱ ርዕሶች ላይ እየተነተኑ ማብራሪያ የሚሰጡ ባለሙያዎች ይፈልጋሉ። ይህን የሚፈልጉትን ነገር በአግባቡ ስለማግኘታቸው ትክክለኛ ማረጋገጫው ምንድነው?

 

አንዳንድ የመረጃ መረቦች (ኢንተርኔትና መጽሄቶች/ጋዜጦች) ጽሁፍ የሚልኩላቸውን ሰዎች በትክክል ያውቋቸዋል? ዶክተር እገሌ ነኝ ብሎ “ስለ ካንሰር” ማብራሪያ የሚሰጥ አንዱ ቢመጣ፣ ብዙዎቹ መገናኛዎቻችን ፣ ጸሃፊው በርግጥ ዶክተር መሆኑን ለማረጋገጥ ምን ያህል ይሞክራሉ? ይልቁንም ፣ እነሱም በዶክተር እገሌ ብለው ያቀርቡታል፣ እኛም “ኦ! አንድ ዶክተር እንዲህ ብሎ ጻፈ እኮ” ብለን እንቀባበለዋለን።

 

በየኢንተርኔቱ በተለያየ ስም የማይጻፍ ጽሁፍ እና ትንተና የለም። አንዳንዶቹ የኛን መንገድ ተከተሉ፣ እንዲህ ካላደረጋቸሁ እንዲህ ናችሁ ብለው በድፍረት ሲጽፉ ይታያል። የሌለ ነገርም ፈጥረው “እንዲህ ሆነ እኮ” ብለው ዋው! እንድንል ያደርጉናል። እኛም ኢንተርኔት ላይ፣ ሬዲዮ ላይ ፣ ፓልቶክ ላይ አንድ የማይታወቅ “የጨለማ ሰው” ያለውን ይዘን “እንዲህ ተባለ እኮ” ብለን እናስተጋባለን።

 

ትክክለኛ ጸሃፊዎች በቅድሚያ ራሳቸውን ማስተዋወቅ አለባቸው። የፖሊቲካ ትንታኔ ሲሰጡ ፣ እናምናቸው ዘንድ ቀድመው የት እንደተማሩ፣ በየትኛው ትግል እንዳለፉ፣ ለሚሰጡት ትንታኔ መረጃቸው ምን እንደሆነ ፣ እነሱን አምነን ሃሳባቸውን እንጋራ ዘንድ ማንነታቸውን ሊያሳውቁን ይገባል። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የጻፉትን ስናይ፣ ስለምናውቃቸው – ብንስማማም ባንስማማም- በትኩረት እናነበዋለን። አቶ እገሌ ፣ ወይም ዶክተር ወይም ፕሮፌሰር እገሌ በሚል ስም ብቻ፣ ማን እንደሆነ እኛም ያላወቅነው ፣ እሱም ያላሳወቀን ሰው የጻፈውን ጽሁፍ ግን እንዴት ብለን ልናነብና ልንቀበል እንችላለን? ዶክተርነቱን እና ፕሮፌሰርነቱን እንዲሁ ከስሙ ፊት ለጥፎት ይሁን አይሁን በምን እናውቃለን? ጽሁፉን የሚያስተናግዱለት መገናኛ ዘዴዎችም ማንነቱን ቢያሳውቁን የበለጠ ለመተማመን [ወይም ላለመተማመን] ይጠቅመን ነበር። በርግጥ “እውነት ያለ” ሰው መሆኑን እንኳን እንድናውቅ ምንም የሚደረግ ጥረት የለም።

 

ስለ ሃይማኖትም የሚጽፍ፣ ስለ ማህበራዊ ጉዳዮች ትንታኔ የሚሰጥም፣ ራሱን በአጭሩ ማስተዋወቅ አለበት። ለጽሁፉ ባለቤትነቱን መውሰድ አለበት። በብዛት የሚታየው ግን ማንም ሰው በፈለገው ስም ፣ የፈለገውን ትንታኔ ሲሰጥ ነው። ማንም ሰው በፈለገው ስም የፈለገውን ሲያሞግስና ያልፈለገውን ሲያጥላላ ነው። አንድ ሰው ለሚያምንበት ጽሁፍ ሃላፊነቱን መውሰድ አለበት። መልስ እንኳን ለመስጠት ሰውየው ራሱን የደበቀ “የጨለማው ሰው” ከሆነ አስቸጋሪ ነው።

 

ነገሮች የሚተራመሱት በነዚሁ “የጨለማው ሰዎች” ይመስለኛል። ደጋፊ ሳይሆኑ ደጋፊ፣ ተቃዋሚ ሳይሆኑ ተቃዋሚ፣ ቄስ ሳይሆኑ ቄስ፣ ሼክ ሳይሆኑ ሼክ፣ ዲያቆን ሳይሆኑ ዲያቆን ሆነው የፈለጉትን እየጻፉ ያተራምሳሉ። እኛም ደግሞ አንድ ምንም የማናውቀው ሰው ኢንተርኔት ላይ የሆነ ነገር ከጻፈ “እንደ ሰበር ዜና” ወስደን “እንዲህ ተባለ እኮ!!” ስንል አናሟሙቃለን። ፌስ ቡክ ላይ ማንም ሊጽፍ ይችላል፣ ለኢንተርኔት ሚዲያዎች ማንም ጽሁፍ ሊልክ ይችላል፣ በሬዲዮ ላይ ማንም ደውሎ የፈለገውን ሊናገር ይችል ይሆናል። ማን እንደሆነ የማይታወቅ ሰው በግል ወይም በድርጅት ወይም በማህበር ደረጃ ሃላፊነት ያልተወሰደበት ጽሁፍ እንዴት የኛን ሃሳብ ሊለውጥ ይችላል?

 

በእምነትም ደረጃ እኮ ብናየው አንዱ ተነስቶ “አባ እገሌ ነኝ” ብሎ የቤተክርስቲያኗ ያልሆነ ትምህርት ሊጽፍ ወይም ሊናገር ይችላል። እንዴት የማናውቀው “አባ” የጻፈውን ይዘን እንተራመሳለን? ጸሃፊውን እኮ የግድ በግል ባናውቀው፣ ቢያንስ በጽሁፉ መጨረሻ “እገሌ ነኝ፣ እዚህ እዚህ ቦታ ተምሬያለሁ፣ አሁን እዚህ ቦታ እያገለገልኩ ነው” ብሎ በሶሶት መስመር እንድናውቀው ሊያደርግ ይገባል። ያን ጊዜ ለጻፈው ጽሁፍ ተጠያቂነት ስለሚኖርበት፣ ቢያንስ ዕምነቱ ካልሆነ ቦታ ገብቶ ከማተራመስ ሊቆጠብ ይችላል። የሚያስተናግዱት መገናኛ ብዙሃንም ይህንን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ።

 

በፖሊቲካውም እንዲሁ ነው። በፖሊቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ሆኖ፣ በወኔና በስሜት የሚጽፍ ወይም የሚናገር ሰው ብዙ ነው። በየኢንተርኔቱ ላይ ያለው የትንታኔ ብዛት ለጉድ ነው። ግን ጸሃፊው ማነው? ራሱን ካላስተዋወቀን፣ ለጻፈው ጽሁፍ ዋጋ እንሰጠው ዘንድ በጥቂቱ ስለራሱ ካልነገረን እንዴት ብለን ነው ጽሁፉን አንብበን ሆ! ልንል የምንችለው?  – ከዚህ በፊት እዚህ እዚህ ቦታ ሰርቻለሁ፣ አሁን እዚህ ቦታ በመስራት ላይ ነኝ – በፖሊቲካ ጉዳዮች  የዚህን ያህል ጊዜ ተሳትፎ ነበረኝ – አለኝ” ብሎ ራሱን ለምን አያስተዋውቀንም? መልስ ለመስጠትም እኮ ጸሃፊውን ማወቅ ያስፈልጋል። አንዳንዶች ትግሉ የሚጠይቀው ይህንን ነው፣ እንዲህ አድርጉ፣ እነ እገሌ የታባታቸው ፣ እነሱን እንዳትከተሉ፣ እነ እገሌ (ስም እየጠራ) ፣ የዚህ ድርጅት አባሎች ናቸው .. የታባታቸው … የሚል “ጸሃፊ” ያጋጥመናል። ጥሩ .. ግን አንተ ማነህ?

 

በውጭ አገር በፖሊቲካውም ፣ በማህበራዊ ኑሮውም፣ በመንፈሳዊ ቦታውም፣ በሌላውም ህብረት እንዳይኖርና በጋራ ጥሩና ውጤት ያለው ሥራ እንዳይሰራ አንዱ እንቅፋት “የጨለማ ሰዎች” መብዛት ነው። ለአንዱ ያገዙ መስለው ሌላውን እያወገዙ፣ በሌላ ስም ደግሞ ያወገዙትን መልሰው እየካቡ፣ ትንሽ የተሻለ ሰው ብቅ ሲል ፣ እንደለመዱት ታርጋ እየለጠፉ ስም በማጥፋት ፣ እንዲሁ እያተራመሱ የሚኖሩት እነዚሁ የጨለማ ሰዎች ናቸው።  አሁን አንዱን የኢትዮጵያውያን ኢንተርኔት (ድረገጽ) ብትከፍቱ፣ ወይም አንዱ የኢትዮጵያውያን ፓልቶክ ክፍል ብትገቡ፣ የማታወቁት ሰው [ራሱን ለማስተዋወቅም ያልደፈረ ሰው] በሆነ ስም “እገሌ ነኝ” ብሎ የጻፈውን ታገኛላችሁ፣ ወይም ሲያወራ ትሰማላችሁ። የማናውቀው ሰው ለሚያወራውና ለሚጽፈው ለምን እንጨነቃለን?

 

በግል ስም እንዲሁ አስተያየት መስጠት፣ ወይም አንዱ በጻፈው ላይ ትችት መሰንዘር ይችላል። ግን ትልቅ ትንታኔና የሌላን ድርጅትና ግለሰብ ስም እየጠሩ፣ “ተነስ! ታጠቅ” የሚል ሰው ካለ .. በቅድሚያ አንተ ማነህ? የሚል ጥያቄ ልናስከትል ግድ ነው።

 

ማንም ሰው ፌስቡክ ላይ ሊጽፍ ይችላል – በጣም ቀላል ነው። ማንም ሰው ለድረገጾች መጻፍ ይችላል – በጣም ቀላል ነው፣ ማንም ሰው ሬዲዮኖች ላይ ደውሎ የፈለገውን ሊል ይችላል – እሱም ቀላል ነው። ማንም ሰው ወረቀት ላይ በታይፕ ጽፎ በየቦታው ሊበትን ይችላል – ይህም ቀላል ነው።  እኛ ግን ልክ ቢቢሲ ላይ እንደተወራ፣ ወይም ቪ ኦ ኤ ላይ እንደተገረ ዜና ቆጥረን – እንዲህ ተባለኮ! ብለን ልናካብድ አይገባም። በእንደዚህ ዓይነት አልባሌ ወሬዎች ህብረታችን ላልቷል፣ ርስ በርስ በአይነ ቁራኛ የምንተያይ ሆነናል፣ ወደ ፊት መሄድ አልቻልንም። ሰው መልስ እንዳይሰጠው ራሱን ከደበቀ ምንም ቢል ፣ የሚለው ሁሉ ሃሜት ነው። ያልሆኑትን ሆነው፣ የማይደግፉትን ደጋፊ መስለው፣ የማይቃወሙትን ተቃዋሚ መስለው፣ የማያምኑትን አማኝ መስለው፣ ራሳቸውን ላገር ተቆርቋሪ አስመስለው የሚፈልጉትን ሲያወድሱ፣ የማይፈልጉትን ደግሞ ሲያጥላሉና ስም ሲያጠፉ የሚገኙት እነዚሁ የጨለማው ሰዎች ናቸው። ለነሱም ከጨለማ ለመውጣት ልብ ይስጣቸው – ለኛም በየቦታው የምንሰማውና የምናነበው – አንዱ ተነስቶ በጻፈው ጽሁፍ- ከመደናበር እና ከመደነጋገጥ ይሰውረን። ከሁሉም በላይ ግን የዜና አውታሮቻችን፣ ሰዎች በግል የሚጠሏቸውን የሚረግሙባቸው፣ የሚወዷቸውን የሚያወድሱባቸው የግል መጠቀሚያ እንዳይሆኑ የራሳቸውን ጥረት እንዲያደርጉ እግዜር ይርዳቸው። ሚስጥራዊ ሆነው እንኳን የግድ አንባቢው ማንነታቸውን ማወቅ ባይኖርበት፣ ቢያንስ አዘጋጆቹ ወይም አቅራቢዎቹ ሊያውቋቸው (ማወቃቸውንም ሊነግሩን) ያስፈልጋል። መልካም አዲስ ዓመት።

_____________

ጸሃፊው አቶ ቴዎድሮስ ኃይሌ፣ በአትላንታ ከተማ ነዋሪና የድንቅ መጽሔት ዋና አዘጋጅ፣ የአድማስ ሬዲዮም አዘጋጅ ናቸው። ጸሃፊውን ለማግኘት በ dinqmagazine@gmail.com መጠቀም ይቻላል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 21, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 21, 2012 @ 7:13 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar