ሚሊ ሹርቤን እንደዋዛ!
በ2001 ዓ.ም. ይመስለኛል፤ በዘገባው የበሸቁ ጆሮውን ለመቁረጥ ያልሳሱለት አወዛጋቢው የስፖርት ጋዜጠኛ ዮፍታሔ ጸጋዬ (ፓፓ) በጨጓራ ህመም ሕይወቱ ያልፋል፡፡ ይህንን አስመልክቼ አውራምባ ታይምስ የስፖርት ገጽ ላይ ዮፍታሔን የሚዘክር ጽሑፍ ሰደድኩ፡፡ በወቅቱ ጋዜጣው በሚወጣበት ማክሰኞ ዕለት ማለዳ ከአልጋዬ ሳልወርድ የእጅ ስልኬን ስከፍት አንድ ጥሪ ደንደርድሮ መጣ፡፡ ደዋዩ ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹርቤ ነበር፡፡
‹‹ሚሊ ሹርቤ››
‹‹ሰላም ነው!››
‹‹አለን! እንዴት ነህ ባክህ?››
‹‹ስለ ዮፍታሔ የጻፍከውን አንብቤ እኮ ነው፡፡ በጣም ውስጥ ይነካል፡፡ ስላሰብከው (ስለዘከርከው) በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ‹እኔም ባልፍ ለካ የሚያስበኝ ወዳጅ አለኝ› እንድል አድርጎኛል (ሳቅ በሳቅ)››
‹‹ኧረ ጠላትህ! አያድርግብህ እንጂ…››
ብቻ ከዚህም አለፍንና ሞት እና ዮፍታዬ ላይ ያተኮሩ ‹ሀዘን ተኮር› ቃላት ተቀያየርን፡፡ እንደዚህ አይነት ክፍተት ካገኘሁ ከመቀለድ አልመለስም፡፡ ወሬያችንን በቀልድ አጅበን ለምስጋናው ምስጋና መልሼ ስልኩን ዘጋሁ፡፡
ትላንት በስደት አገር የሚገኘውን አሳዛኙን የሚሊ ሹርቤ ዜና እረፍት እንደሰማሁ በቶሎ በጭንቅላቴ የመጣው ይህ የስልክ ልውውጣችን ነበር፡፡ ‹‹ለካ እኔም ባልፍ የሚያስበኝ ወዳጅ አለኝ እንድል አድርጎኛል፡፡›› በጆሮዬ ሞላ፡፡ ሚሊን ከመዘከር በላይ የሚገባው ትሁት፣ ቅንና መረጃ አነፍናፊ (በተለይ የጥበብ መረጃዎች) ጋዜጠኛ ነበር፡፡
ከሚሊ ጋር በአካል የተዋወቅነው ጐግል ጋዜጣ ቢሮ ነበር፤ በ2000 ዓ.ም አጋማሽ ላይ፡፡ ቢሮ ሲመጣ የብዙዎችንን ጽሑፍ የተመለከቱ አበረታች እና አነቃቂ አስተያየቶችን ያጎርፈዋል፡፡ በጋዜጣዋ ኪነ ጥበብ አምድ ላይ ኮንትሪብዩት ያደርግ ነበር፡፡ ዜናዎችንም ያቀብላል፡፡ የብዙዎችን ትኩረት ይስብ የነበረውን የቴዲ አፍሮን የችሎት ዘገባ የመጀመሪያ ሰሞን ውሎ እየተቀያየርን እንሠራም ነበር፡፡ የሚሊ ችሎት ዘገባው ታዲያ ድራማዊ ለዛን የተላበሰ ነበር፡፡ ‹‹የጠዋቷ ፀሐይ መጣሁ መጣሁ በሚለው ዝናብ ደመና ተከልላለች፡፡ ልባቸው እንኳን ዝናብ ሞት የማይበግራቸው የሚመስሉ ወጣቶች ወደ ችሎት ለመግባት አቆብቁበዋል፡፡ … በሰዉ ልብ ላይ የነገሰው ቴዲ አፍሮ ሰማያዊ ሙሉ ልብስ፣ በጥቁር ቢትልስ ለብሶ፣ ዘመናዊ መነጽሩን ሰክቶ ወደ ችሎት ሲገባ ታዳሚው ትኩረቱን ሁሉ ወደ እሱ አድርጎ በተመስጦ ፈዘዘ…›› የወቅቱን ይህ መሰል የችሎት ዘገባዎችን ያስለመደው እሱ ይመስለኛል፡፡
ለጽሑፎች የሚሰጣቸውም ርዕሶቹ የኅትመት ውጤቱን ዓይቶ ለማለፍ የሚያስችሉ አይደሉም፤ ‹‹ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የተሸጋገረው የቤተ ክህነት ጉባዔ አነጋጋሪ ውሳኔዎችን አሳለፈ›› ዓይነት፡፡ የቤተ ክህነት የውስጥ ምንጮች ስለነበሩትም አወዛጋቢ ጉዳዮችን በማፈንዳት ይታወቃል፡፡ በጋሻው ደሳለኝን ጨምሮ ብዙ የሃይማኖት ከባቢ ሰዎች ለሚሊ ካልሆነ ቃለ ምልልስ ለመስጠት እምቢተኛ እንደነበሩ አስታውሳለሁ፤ ፍቅራቸው ሳይዘልቅ ቀረ እንጂ፡፡ አንተ ደውለህ አታክቶህ ተስፋ የቆረጥክበትን ሰው ሚሊ ቃለ ምልልስ አድርጎ ሙሉ ጉዳዩን ይዞ ከተፍ ይልልሀል፡፡
የበርካታ አቀንቃኞችን ሥራቸው እንዲተዋወቅና ዛሬ ላይ ለደረሱበት ደረጃ ሚሊ መወጣጫ መሰላል ሆኗቸዋል፡፡ አንዴ ማዲንጎ ይመስለኛል ‹‹ሚሊ በየጋዜጣው እና በየመጽሔቱ እንግዳ በማድረግ ከሕዝቡ ጋር እንድንተዋወቅ ለምታደርገው ያልተቋረጠ ጥረት በጣም አመሰግንሀለሁ›› ያለውን አሰምቶን ያውቃል፡፡ ዋና ፕሮሞተር ሆኖ አብርሃም (ሻላዬ)ን ከፍ ያደረገው ሹርቤው ነው፡፡ በቃ! ብዙዎች የጥበብ ሰዎች እንዲተዋወቁ እና እንዲታወቁ ብዙ ለፍቷል፡፡ እነዚሁ የጥበብ ሰዎች መስመራቸው ካልጣመውም ከፊት ገጽ የሚነሳ፣ ፊታቸውን በንዴት የሚያቀላ ግለ አስተያየቱን አስፍሮ ይገስጻቸዋል፡፡
ብዙ ወዳጆቻችን በአባቱ ስም ላይ ‹ው›ን ለጥፈው ‹ሹርቤው› የሚሉት ሚሊ መጨናነቅ አያውቅም፡፡ ሁሌም ዘና፣ ፈታ ነው፡፡ ኪሱ ሞቅ ካለ ለአዲስ አበባ ጊዜ አይሰጣትም፤ ተሰናብቷት ወደ ሀዋሳ ሸከተፍ ይላል፡፡ የቤት ሥራውን ሣይሰራ ስለሚዘገይ ማተሚያ ቤት መግቢያ በተቃረበ ጊዜ ሁሌም በውጥረት እንደተሞላ ነው፡፡
የሚሊን ያህል የሙያ ጓደኞቻቸውን ጽሑፍ ተመልክተው አነቃቃቂ እና አበረታች አስተያየቶችን ለመስጠት የማይነፍጉ የአንድ ጣትን አንጓ የሚሞሉ ጋዜጠኞች እንዳሉ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ መልካም አሳቢም ነው፤ ቢሆን ‹ሸጋ ነው› የሚለውን የሚጠቁም፣ በወዳጆቹ ስኬት የሚደሰት ሰው፡፡
በኢትኦፕ መጽሔት፣ መንገድ አምድ ላይ (እነዚያ ‹‹አላሙዲን ታውቃቸዋለህ?›› ሲባሉ ‹‹አዎ የኢትዮጵያ መሪ አይደለ!›› የሚሉ ሰዎችን መንገድ ላይ እያፈለገ አዝናንቶናል) በሜዲካል፣ ጐግል፣ ሮያል መጽሔትና በወራት በፊት በስደት በጢያራ ከአገር እስከወጣበት ጊዜ ድረስ የራሱ በነበረችው ማራኪ መጽሔት ላይ መሥራቱም ይታወቃል፡፡ ለቁጥር የሚከብዱ ቃለ ምልልሶችን ሠርቷል፡፡
ዋ! ሚሊ! ነፍስህ በገነት ትሁና!
ሚሊሻ ዜና ዕረፍትህን ኤሊያስ ገብሩ በስልኬ ሲልክልኝ ክው ብዬ ቀርቻለሁ፡፡ እነዚህን ኳሊቲዎችህን ላንተው ለራስህ ሳልነግርህ የቀረሁ ቢሆን ኖሮ ሀዘኔ ይበልጥ በበረታ ነበር፡፡ መልካም አሳቢ፣ ተባባሪና ጥሩ ወዳጅ ነበርክ፡፡ ‹እኔም ባልፍ ለካ የሚያስበኝ ወዳጅ አለኝ› ያልከኝን ያህል እንዳልሆንኩ ይታወቀኛል፡፡ ወድጄ እንዳይመስልህ ደንጋጤ ውጦኝ ነው፡፡ ቃላት ስደገፋቸው እየከዱ ሰነፉብኝም እንጂ ከዚህም በላይ ስላንተ ምስክርነት በሰጠሁ ነበር፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ድምጽህን ቪኦኤ ላይ ሰምቼ ‹‹ወደ ማይቀረው ሄደ›› ሲባል እንዴት ልመን?፡፡ በወሬህ መሀል የምትሰነቅራት ‹‹Sure›› ጆሮዬ ላይ ታቃጭላለች፡፡ አንተ ትሁት ልጅ! የምርርርርረርርርር አሪፍ ወዳጄ ነበርክ! ምን ያባላል ታዲያ ነፍስህ በገነት ትሁና! ዋ! ሚሊ ሹርቤ!!!
Average Rating