www.maledatimes.com ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዉያን ብሄራዊ እርቅ ያስፈልጋል? - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዉያን ብሄራዊ እርቅ ያስፈልጋል?

By   /   October 20, 2014  /   Comments Off on ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዉያን ብሄራዊ እርቅ ያስፈልጋል?

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 54 Second

==============================
****** ሸንቁጥ አየለ (shenkutayele@yahoo.com ) ****

የኢትዮጵያ ህዝብ ዉህድ ህዝብ መሆኑን እና የጋራ ማንነት ያለዉ ህዝብ መሆኑን በቀደመዉ ጽሁፍ አስተዉለናል:: ዉህድነትና የጋራ ማንነት ግን የግድ ወደ አዎንታዊ የእርስ በእርስ መስተጋብር ብቻ ሊወስድ ይችላል የሚል አንደምታ ያለዉ ትንታኔ ላይ መቆም አይቻልም:: አንድ ህዝብ ዉህድ ሲሆን እና የጋራ ማንነት ሲኖረዉ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ መስተጋብራዊ ኩነቶች ከዚሁ ከጋራ መሰረቱና እሴቱ ሊመዘዙ ወይም ሊመነጩ እንደሚችሉ ማስተዋል ተገቢ ነዉ::

ከኢትዮጵያዉያን መስተጋብራዊ ዉህደትና የማንነት ተመሳሳይነት የመነጨ ነዉ ተብሎ የሚታመን የጋራ የሆነ የስነ መንግስት ጭብጥም በኢትዮጵያዉያን ማህበረሰቦች መሃከል በገሃድ ይስተዋላል:: ይሄዉም በጥንታዊዉ ኢትዮጵያዉያን ስነመንግስት ህሳቤ ዉስጥ እንዲህ የሚል ጥልቅ እሴት አለ:: መንግስት በሀይል ይያዛል:: መንግስትን የሚቀናቀኑትን የሚያርቃቸዉ ደግሞ ዱላና ሀይል ነዉ:: ከዚሁ ከጥንታዊዉ ህሳቤ ሲዛመት የመጣዉ የስነልቦና ጭብጥም አሁን ድረስ በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ልሂቃን ፖለቲከኞች እና ምሁራን መሀከል የረበበ ጭብጥ ሆኖ ይገኛል:: ምንግዜም ቢሆን ስነመንግስት ያለ ሀይል አይጸናም ብሎ የሚያምነዉ ኢትዮጵያዊ ቁጥር የዋዛ አይደለም::

ስነ መንግስት በሀይል እንደመያዟ መጠንም ዝም ተብሎ በዲሞክራሲና ምናምን በሚሉ ታሳቢዎች ተላልፋ ለሌ ቡድን የምትሰጥ ነገር አይደለችም የሚለዉ ኢትዮጵያዊ ብዙ ይመስላል:: ይህ ባህላዊ ጭብጥ አሁን በብዙ ኢትዮጵያዉያን ምሁራን: ፖለቲከኞች እና የስልጣን ደጋፊ ሀይሎች ዘንድ በገሃድ ሲወራ ይደመጣል:: ይሄዉ አባባል እዉነትም አሁንም በማህበረሰባችን ዉስጥ ጥልቅ ስር እንዳለዉ ለማወቅ ጥቂት ስነልቦናዊ ጥናቶችን እና የፖለቲካ ትንታኔዎችን ማድረግ በቂ ነዉ:: ሌላዉ ቀርቶ የሰለጠነ ስነልቦና እና ስነ ባህሪ አለን ብለዉ በሱፍ ታንቀዉ : በበርካታ የምዕራባዉያን ዲግሪ ተመርቀዉ በመድረክ ላይ የሚዉረገረጉት ኢትዮጵያዉያን ልሂቃን: ፖለቲከኞች እና ምሁራን (ስልጣኑን የጨበጡትም ሆኑ ተቃዋሚዎች) አንድ የጋራ እና ሀይለኛ የሆነ የስነልቦና መሰረት ላይ ቆመዋል::

ይሄዉም በጥንታዊዉ የኢትዮጵያዉያን ማህበረሰብ አስተሳሰብ ላይ የተንተራሰ ጭብጥን ያልለቀቀ እሤት ሆኖ ይገኛል:: ስነ መንግስት በሀይል ይጸናል የሚል የማይናወጽ ታሳቢ:: ይሄ እንግዲህ የጋራ የሆነ ከታሪካዊ እሴት የመነጭ ስነልቦናዊ ምህዳር ቢሆንም ግን ዞሮ ለዚህ ትዉልድ የርስ በእርስ መጠላለፊያና መጠላሊያ ሆኗል:: ሁሉ ስልጣንን ሲመኝ ለመጠፋፋት ሳያቅማማ አዉዳሚ የጥላቻ ስትራቴጅ ነደፋን ይከተላልና::

በዚህ የጥንታዊ የስነልቦና መሰረት እና የሰብዕና ተክለ አቋም ላይ የሶሻሊስታዊ የመደብ አመለካከት ሲደረብበት ደግሞ ለስልጣን የሚቀናቀኑ ሀይሎች ካላቸዉ አንድነት ይልቅ ያላቸዉን ልዩነት እየጎለጎሉ ኢትዮጵያዊው ማህበረሰብ እርስ በርሱ በጥርጣሬ እንዲናከስ ያላሰለሰ ሰበካ አከናዉነዋል:: እያከናወኑም ነዉ:: ይሄ ብቻ አይበቃም:: በዚሁ ላይ የብሄር/የጎሳ ልዩነት ሲደረብበት: በዚህ የልዩነት ከፍታም ላይ የዘመነ መሳፍንት ከዚህ ወንዝ እከሌ አሸፈ ከወዲያ ወንዝ ደግሞ እከሌ ተሸነፈ የሚለዉን ብሂል ሲደረትበት የልዩነት መሰረቱን እያጓነዉ ይመጣ::

ጥንታዊውያን ኢትዮጵያዉያን የመረረ የስልጣን ሽኩቻና ጸብ ዉስጥ ሲገቡ ቢያንስ በመንፈሳዊ አንድነታቸዉ ጥላቻቸዉ የሚረግብበትን ስልት ይቀምሩ ነበር:: ለዚህ ድንቅ ማሳያ ይሆን ዘንድ በአጼ ምኒልክና በአጼ ዮሐንስ መሃከል የተነሳዉ ጠንካራ የስልጣን ሽሚያ እንዴት በመንፈሳዊ ምክርና ወንድማማችነት ይለዝብ እንደነበረ ለማመሳከር ታሪክ ዘ ዳግማዊ ምኒሊክ (ከጸሃፌ ትዕዛዝ ገብረስላሴ) የሚለዉን ጥንታዊ መጽሀፍ ማንበቡ በቂ ግንዛቤ ይፈጥራል:: ሆኖም ዘመናዊ ትምህርት የቀሰመዉ ኢትዮጵያዊ ምሁር: ፖለቲከኛ እና ልሂቅ ሁሉ የመንፈሳዊ ጭብጡን በብዛት እያወለቀ ገደል የሰደደ ነዉና ሊግባባበት የሚችል አንድም የጋራ የሆነ መሰረት አጥቷል:: አይኑ ስልጣን እና የበላይነት ከማዬት ልቡም በቀልና ጥላቻን ከመስበክ ለቅጽበት እንኳን የሚተኛ አልሆነም::

በጥቅሉ ከላይ አጠር አጠር ተደርጎ የቀረበዉ የጋራ ዉህድ ህዝብነትነ የሚያሳይ ታሪካዊ መረጃ ሁሉ አሁን ላለዉ ኢትዮጵያዊ የአንድነትና የጋራ እሴት የሚያራምድበት እትብት ሆኖ ሲያስተሳስረዉ ወይም በጋራ ለመቆሚያ የሚሆን ማህቶት ሲሆነዉ አይስተዋልም:: እናም የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማ የተለያዩ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦችን ዉህድነት ወይም ልዩነት በርብሮ መተንተን ሳይሆን አሁን የጋራ ታሪክ አላቸዉ ብሎ ታሪክ በሚተርክልን ኢትዮጵያዉያን ልሂቃን : ፖለቲከኞችና ምሁራን መሃከል የተፈጠረዉን የስነልቦና ክፍተት እንዴት ሊጠገን እንደሚቻል መፍትሄ ማፈላለግ የሚያስችሉ ሀሳቦችን ማመላከት ነዉ::

የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄን ያህል ሰፊ የጋራ ጥንታዊና ታሪካዊ መሰረት ያለዉ ህዝብ ከሆነ ዛሬ የተለያዩ ማህበረሰቦችን በሚወክሉ ፖለቲከኞች እንዲሁም ምሁራን መሃከል ለምን የተፈራቀቀ ስነልቦናዊ ጭብጥ ሊኖር ቻለ? ይሄን የስነልቦና ክፍተት ያመጣዉ የስልጣን ጥያቄ ነዉ? የመደብ ልዩነት ነዉ? የቋንቋ ልዩነት ነዉ? አንዳንድ ተችዎች እንደሚሉትስ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ መሰረትና እሴት ሳይኖረዉ በዘፈቀደ ታሪክ የተጻፈለት ህዝብ ስለሆነ ነዉ? በአንድ ወቅት የተፈጠረ የአገዛዝ ስርዓት የፈጠረዉ ጥላቻና ልዩነት ነዉ? የዉጭ ሀይሎች ሆን ብለዉ በዘዴና በጥበብ የተለያዬ እሴትና መርዛማ ጥላቻን በልዩ ልዩ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰቦች መሃከል ስለዘሩ ነዉ? ነዉ ወይስ ምንድን ነዉ?

አሁን ያለዉ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን እና መሰረቱን አጥብቆ የጠላዉ ምን ቢገጥመዉ ነዉ? ለምሳሌ የጥንታዊት ኢትዮጵያ አካል የሆኑት: በታሪክ: በቋንቋ : በመልክ : በሀማኖትና በባህላዊ እሴት ከብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ጋር ቅርብና ጥብቅ ቁርኝት ያላቸዉ ኤርትራዉያን ለምን ያባቶቻቸዉ ታሪክ የሚባለውን ኢትዮጵያዊነት ለመካድ ጥቂት እንኳን አላቅማሙም? መሰረታዊ ችግሩ ምንድ ነዉ? ወይ ታሪኩ ዉሸት ነዉ ? ወይም በመሃል ከአባቶቻቸዉ ታሪክ እንዲነጠሉ ያስገደዳቸዉ ታላቅ ክስተት አለ? ለስልሳ አመት በሌላ መንግስት ስር ስለቆዩ ነዉ የሚለዉስ አሳማኝ ነዉ?

ስልሳ አመት በሌላ መንግስታት ስር ቆይተዉ ወደ መሰረታዊ ህዝባቸዉ የተቀላቀሉ ማህበረሰቦች በዓለም ላይ የሉም? በጭቆና አገዛዝ ስር ስለወደቁ ነዉ የሚለዉስ በቂ ምክንያት ነዉ? አንድ ህዝብ ጨቋኝ ወገን ከመሃሉ ስለወጣ ጠቅላላ ማንነቱን ለመካድ የሚያስችል በቂ ምክንያት ይኖረዋል? ኢትዮጵያዊ ከራሱ ጋር እንዲጣላ ያደረገዉ መሰረታዊ ጭብጥ ምንድን ነዉ? የተማረዉ/ ምሁር ተብዬዉ/ : ፖለቲከኛዉ በጥቅሉም ልሂቅ የሚባለዉና ማህበረሰቡን የመዘዉር አቅም ያለዉ ሃይል እርስ በርሱ የሚጠላላዉና ለመጠፋፋት ነገር የሚጎነጉነዉ እንደሚባለዉ አፍሪካዊ ድንቁርና አለቅ ብሎት ነዉ? ወይስ መሰረታዊ የማንነት ልዩነት ስላለዉ ነዉ?

ይሄ በአሁኒቷ ኢትዮጵያዉያን ልሂቃን መሃከል የተነሳዉ የእርስ በእርስ ጥላቻ በበርካታ መልክ ይገለጻል:: አንዱን ከስልጣን አባሮ ስልጣን መቆጣጠር እና አንዱ የሰራዉን ሙሉ ለሙሉ የመጥላት ብሎም የማዉደም ስነልቦና ቀላሉና ጥቂቱ ልዩነት ነዉ:: ዋናው እና አስፈሪዉ ልዩነት ግን አንዱን ወገን ፍጹም እንደ ባዕድና ወገን እንዳልሆነ በመፈረጅ የሚደረገዉ የርስ በርስ የመጠፋፋት የቤት ስራ ገና የተጀመረ ይመስላል እንጅ የበሰለም አይመስልም:: እናም ጥያቄ ያስነሳል:: ለምን ይሄ ሁሉ? ደግሞስ መፍትሄዉ ምንድነዉ የሚል ጥያቄ:: ነገሩ ግልጽ ነዉ:: የሚሻለዉም መፍትሄዉ ላይ ማጠንጠኑ ነዉ:: ወደ መፍትሄ ከመስፈንጠር በፊት ግን ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ወኪል ነን የሚሉ ምሁራን: ፖለቲከኞች እና ልሂቃን የሚያነሱትን የጥላቻ ጭብጥ በደንብ ነቅሶ ማዉጣቱ ተገቢ ቢሆንም በዚህ ጽሁፍ ሁሉን ነቅሶ ማዉጣት ስለማይቻል ለወደፊቱ በዚሁ ስራ ሊሰሩ የሚነሱ ሀይሎች በደንብ አድርገዉ ያንሰላስሉበት ዘንድ ለመደርደርሪያ የሚሆኑ ነጥቦቹን ነካክቼ ብቻ አልፋለሁ:: ከላይ እንደተባለዉ የጋራ ታሪክ ያለዉ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ አለ ብሎ ታሪካችን ትርክት ቢያቀርብም በአንድ ጽንፍ ተወርሬአለሁ : ቅኝ ተይዤአለሁ ብሎ የሚያምን ሀይል አለ::

በሌላ ጽንፍ እከሌ የሚባል ማህበረሰብ ሀገሬን ከሌላ አካባቢ መጥቶ አስለቅቆ ከያዘ ብኋላ እኔን መጤ ይለኛል ብሎ የሚያጉረመርም ሀይልም አለ:: በሌላ ፈርጅ ላይ ደግሞ ስጨቆን ስለኖርኩ አሁን ለመጨቆን እና ሌላዉን ለመቀጥቀጥ የኔ ተራ ሆኖ ተገኝቷል ብሎ የሚያስብ ሀይልም አለ:: እንዲሁም በአንድ ደርዝ ሀይማኖቴ ሲረገጥ ነበር ረጋጩም እክሌ ስለሆነ ቆይ ብቻ የሚል ቡድን አድፍጧል:: በሌላ መነጽር ሲቃኝ ደግሞ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ብቻ ነዉ የሚያስፈልጋት ሲል ስልጣን ከጨበጠዉ ሀይል ጋር አንገት ላንገት የሚተናነቅ ወገን አለ:: ስልጣኑን የጨበጠዉ ሀይልም ገና አርባና አምሳ አመት ይህችን ሀገር ሳልገዛ ማንም መንበረ ስልጣኑን ንክች አያደርጋትም ሲል አዋጅ አስነግሯል:: በሌላ ጎራም የብሄሬ/ የጎሳዬ ማንነት አሁን ተከበረ ብሎ በደስታ የሚመላለስ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ እንዳለ ሁሉ ከእዚሁ ጎን የጎሳዬ/ብሄሬ ማነትና መብት አሁን ተረገጧል/ተዋረዷል ሲል የሚያለቅስ ቡድን አድፍጧል::

ግማሹ በዉጭ ተሰዶ በሰዉ ሀገር በሀገር ፍቅር ሳይበላ ያለቅሳል:: ግማሹ ደግሞ በገንዛ ወንድሙ ላይ ያላግጣል:: ሌላዉ ቀርቶ ለአምሳና አርባ አመታት በፖለቲካ ርዕዮተ አለም ተለያይተዉ ኖረዉ አሁን ድረስ ሊጠፋፉ ያደቡቧት ሀገር ኢትዮጵያ ነች:: እንግዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች: ምሁራን እና ልሂቃን የሚባሉት በደንብ ተደርገዉ ከተተነተኑ ልዩነታቸዉ የሰማይና የምድር ያህል የሰፋ ሆኖ ይገኛል:: ከኢትዮጵያ ተነጥለዉ ነጻነትን የሚመኙ በርካታ ናቸዉ:: እንዲሁም አንዲት ኢትዮጵያን በህልማቸዉም በእዉናቸዉም ሊያገኟት የሚቃትቱ ሀይሎች በኢትዮጵያና ማዕቀፍ ዉስጥ ይመላለሳሉ::

ይሄን ጊዜ ነዉ እንግዲህ የብሄራዊ እርቅና የይቅርታ መንፈስ ለአንዲት ሀገር ብቸኛዉ ማጠንጠኛና መዉጫ ቀዳዳ ሆኖ የሚከሰተዉ:: ሀገራት በተለያዩ ምክንያት ማህበረሰባቸዉን የሚወክለዉ ምሁር: ልሂቅና ፖለቲከኛ ሲከፋፈልባቸዉ: እርስ በርሱ ሲባላባቸዉ: ሊጠፋፋ መቆራቆዝ ሲጀምር ወይም እርስ በርስ ተናክሶ መዉጫ ቀዳዳ ሲያጣ የብሄራዊ እርቅና የይቅርታ መንፈስ በሀገራቸዉ ህዝብና ማህበረሰብ ዘንድ ይረብ ዘንድ ደፋ ቀና ሲሉ ተስተዉለዋል:: የተሳካላቸዉ አሉ:: ሁሉም ወገን በቅንነት የሰሩት ተሳክቶላቸዋል:: ታጥቦ ጭቃ የሆነባቸዉ ሀገራትም አሉ::

የሆነ ሆኖ ለኢትዮጵያዉያን እና ለኢትዮጵያ በርካታ ተሞክሮ ሊያካፍሉ የሚችሉ (አንድም ከዉድቀታቸዉ ወይም ከዉጤታማነታቸዉ) አገራት ሞልተዋል:: ለምሳሌም ኩባ: አፍጋኒስታን: ደቡብ አፍሪካ: ሰሜን አዬርላንድ: ደቡባዊ ኮኔ: ኤልሳልቫዶር: ጉዋታማላ እና ሩዋንዳ ጥቂቶች ናቸዉ:: መረሳት የሌለበት ነገር በየሀገራቱ ያሉ ችግሮች ጥልቀታቸዉ የተለያዩ ቢሆን ዋናዉ ጉዳይ ግን አንድ ሀገር በምሁራኑ: በፖለቲከኞቹና በልሂቃኑ መሃከል ክፍፍልና ጥላቻ ሲረብበት ፈጽሞ ወደ ጥልቅ አዘቅት ከመግባቱ በፊት የብሄራዊ እርቅና የይቅርታ መንፈስ ጥሩ አማራጭ መሆኑን አለመርሳቱ ላይ ነዉ::

የብሄራዊ እርቅ: ይቅርታ እና ስምምነት ዘርፍ ብዙ ቢሆንም ሁለት ዋና ዋና ጭብጦችን ግን መዞ ማዉጣት ተገቢ ነዉ:: እነዚህም አሁን ማህበረሰቦችን በሚወክሉ ምሁራን እና ፖለቲከኞች መሃከል ለምን የተፈራቀቀና በአሉታዊ መንፈስ የታጠረ ስነልቦና ሊኖር ቻለ የሚለዉ ጥያቄ ነዉ:: ሁለተኛዉ ደግሞ ይሄን የስነልቦና ክፍተት እንዴት ነዉ ማቀራረብና የለዘበ አዎንታዊ መንፈስ መፍጠር የሚቻለዉ የሚለዉን ጥያቄ ማንሳት ነዉ:: ይሄ የተለያዩ ማህበረሰቦችን የሚወክሉ የፖለቲከኞችና የምሁራን ስነልቦና መንፈራቀቅ ብሎም አንዱ ለአንዱ አሉታዊ አቋም መያዝ መገለጫዉ ብዙና የሰፋ ቢሆንም ከላይ በስፋት ተገልጿል::

ሰብሰብ ተብሎ ሲገለጽ ግን በሀገራዊ የታሪክ ትርጉም ላይ አለመስማማትና መካሰስ: አጠቃላይ ፖለቲካዊ ጭብጥና ርዕዮት ላይ በተለያዬ ጽንፍ ላይ መቆም ብሎም ሲመች ለመጠፋፋት ማድባት: የእኛ ማህበረሰብ በዚያኛዉ ማህበረሰብ ተጨቁኗል ብሎ ማሰብና ይሄንኑ ለማሳመን ሰፊ ሰበካ ላይ መጠመድ: እንዲሁም አንዱ ወገን በአንዱ ላይ እንዲነሳ ያላሰለሰ ቅስቀሳና ሰበካ ማድረግ: ሌላዉ ቀርቶ አንድ ምሁር/ፖለቲከኛ ከሁለት የተለያዩ ማህበረሰቦች ተወልዶ እንኳን አንዱን ማህበረሰብ ለማስጠፋት አይኑን በጨዉ ታጥቦ መስራት: አንዱ ወገን በሌላዉ ወገን ላይ ፍጹም እምነት ማጣት ብሎም በአጠቃላይ የተነጣይነትና የተገንጣይነት መንፈስ በብዙ ማህበረሰቦች ዘንድ መርበብ ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ::

የብሄራዊ እርቅ እና ይቅርታ ብሎም ስምምነት ለማምጣት እስከዛሬ በአለም ላይ ልዩ ልዩ ሞዴሎች(ስልቶች) ተሞክረዋል:: ለመሆኑ እነዚህ የብሄራዊ እርቅና ስምምነት የተለያዩ ስልቶች ምን ምን ናቸዉ? ሆልይ አክረም የተባለ ተመራማሪ ለኩባ ብሄራዊ እርቅ የትኛዉ የብሄራዊ እርቅ ሞዴል(ስልትቅ) ይሰራል የሚለዉን ጭብጥ ለመፈተሽ ስድስት አይነት ስልቶችን እንደመረመረ እና ከስድስቱ ሞዴሎች ግን ለኩባ ተጨባጭ ሁኔታ የሚሰራ ሞዴሎች እንዳጣ ያስረዳል:: እያንዳንዱ የብሄራዊ እርቅ ሞዴል (ስልት) በአንዲት ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመርኩዞ ሊመረጥ አንደሚገባዉ የሚያብራሩ በርካታ ሰነዶች አሉ:: እያንዳንዱ ስልት የራሱ ተወንጫፊ ግብ ቢኖረዉም ጥቅል እና ዋና መሰረት አድርጎ የሚያንሰላስለዉ ግን በአንዲት አገር ዉስጥ ከጥላቻና ካለመተማመን የጸዳ ማህበረሰብ እኩልነትና ሰላም የሰፈነበት ማህበርሰብ ብሎም የነገዉ መሬት የተደላደለ እንዲሆንን እና የጋራ ህላዌዉ የሰመረለት ህዝብ ስለመፍጥር ነዉ:: እነዚህ ስደስት የብሄራዊ እርቅ ሞዴል (ስልት) የሚባሉትም :-
1.የተከፋፈሉና በጥላቻ የሚናጡ ወገኖች/ቡድኖች ተገናኝተዉ እንዲወያዩ ማድረግ ሂደትን እንደ ብሄራዊ እርቅ መግቢያ የሚወስድ ሞዴል (Literal meeting of opponents/divided groups; Frame process & model behavior)
2.የግጭት መንስኤ የሆኑ ከፋፋይ ማህበረሰባዊ/ባህላዊ እሴቶች እንዲደበዙ ብሎም እንዲጠፉ የሚያስችል የብሄራዊ እርቅ ሞዴል (Dissolution of conflicting identities e.g., class, race,religion, ideology)
3.የልዩ ልዩ ማህበረሰቦችን እሴቶች በማድነቅ የጋራ ህላዌ እና አብሮ መኖር ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችል የብሄራዊ እርቅ ሞዴል (Mutual coexistence of distinct groups; Act as broker/facilitator promoting tolerance of diversity)
4.ይቅርታና መጸጸትን መሰረት ያደረገ ሞራላዊ ወይም መንፈሳዊ የብሄራዊ እርቅ ሞዴል (Moral/religious—confess/forgive/repent)
5.በህግና በስርዓት ተረጋግጦ የሚጠበቅ የሰበአዊ መብትን መሰረት ያደረገ በህግ ታራቂ ማህበራዊ ስነባህሪ የብሄራዊ እርቅ ሞዴል ( Regulate social behavior via legislation of human rights Legal drafter/watchdog/whistle-blower)
6.የጋራ ሰላምን በመስበክና በማራመድ ማህበረሰብ ግንባታ ተኮር የሆነ (Community building; Promote trust-building, truth-telling, renewed interdependence & holistic view of society)

ከላይ እንደተባለዉ የኢትዮጵያ ጉዳይ እራሱን የቻለ የተለዬ መልክ ስላለዉ የትኛዉ ሞዴል የተሻለ እንደሆነ በደንብ መጠናት አለበት:: ለምሳሌ ከላይ ስሙን የጠቀስንዉ ተመራማሪ በፖለቲካ ርዕዮት አለም የተከፋፈለዉን የኩባን ፖለቲከኛና ምሁራን (በስደት ያለዉን እና በሃገር ቤት ያለዉን) ወደ ብሄራዊ እርቅ ለማምጣት የትኛዉ ሞዴል የተሻለ እንደሆነ ባደረገዉ ትንታኔና ጥናት መሰረት የደረሰበት ድምዳሜ ከላይ ከተጠቀሱት ሞዴሎች ዉስጥ የትኛዉም ሞዴል በአመርቂ ሁኔታ የችግሩን ስር ሊፈታዉ እንደማይችል አስምሮበታል::

ይሄም ማለት አንዲት ሀገር ወደ ብሄራዊ እርቅ ከመግባቷ በፊት በርካታ የሚሰሩ የጥናትና ትንታኔ ስራዎች አሉ ማለት ነዉ:: በየሀገራቱ ያሉት ሁኔታዎች በስፋትና በጥልቀት እንደመለያዬታቸዉ መጠን በደፈናዉ የአንድን ሀገር ተሞክሮ ሙሉ ለሙሉ ለመገልበጥ መንደርደር አስቸጋሪ እንደሆነም ያሳያል:: የሀገሩ አጠቃላይ የችግር ባህሪ መለያዬት እንዲሁም የሞዴሎቹ መለያዬት እንዳለ ይሁንና ዋናዉ መረሳት የሌለበት ጭብጥ ግን ለአንድ ማህበረሰብ የሚተማመን ልብ ግንባታ ብሎም በአዎንታዊነት የረበበ መንፈስ የሰፈነበት ማህበረሰብ መፍጠር ግን አማራጭ የሌለዉ የሁሉም ያገባኛል ባይ የቤት ስራ ነዉ::

እናም ጥያቄ እናስከትላለን:: ለምሆኑ በኢትዮጵያ ማን ከማን ጋር ነዉ የብሄራዊ እርቅና ስምምነት ማድረግ ያለበት? አሁን ባለዉ የኢትዮጵያ ሁኔታ እያንዳንዱ ግለሰብ ከራሱ ጋር ሳይቀር መታረቅ ያለበት ይመስላል:: በርካታ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ይነጫነጫል:: ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስ በርሳቸዉ ሊጠፋፉ አድብተዋልና እርስ በርሳቸዉ እርቅ ያስፈልጋቸዋል:: ሌላዉ ቀርቶ በአንድ ፓርቲ ዉስጥ ታቅፈዉ በአንድ አላማ ሲታገሉ የነበሩ አባላት በመላዉ አለምና በመላ ሀገሪቱ በጥላቻ ልዩነት እየተንፈቀፈቁ ነዉና እርቅ ያስፈልጋቸዋል:: ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ወካዮች: የሀይማኖት አባቶች: ስልጣኑን የጨበጡትና ተቀናቃኝ ሀይሎች: ምሁራን/ልሂቃን እራሳቸዉ: ትዉልድ እየቀረጸ ያለዉ የትምህርት ስርዓቱ ሳይቅር ከኢትዮጵያዊነት ጋር መታረቅ አለበት::

ልዩ ልዩ ማህበረሰቦች ባላቸዉ ታሪክና ታሪካዊ ታሳቢ ዙሪያ እንዲሁም በጥንታዊት ኢትዮጵያ ማንነት ዙሪያ ራሱ እርቅ ያስፈልጋል:: ከዚህ በተጨማሪም አሁን ስልጣን በጨበጠዉ ሀይል እየተመቱ ከስልጣን የሚባረሩትና ስልጣን ላይ ባለዉ ሀይል ላይ ጥርሳቸዉን የሚነክሱት ወገኖች ሁሉ እርቅና ሰላም ማዉረድ የስምምነት መንፈስ ዉስጥ መመላለስ ይጠበቅባቸዋል:: በቀደመዉ ዘመን በፖለቲካ ትግል ዉስጥ ገብተዉ በፓርቲ ተከፋፍለዉ የተጨፋጨፉ: በስልጣን ልዩነት የትናከሱ እንዲሁም በተንኮል የተበላሉ ሁሉ ብሄራዊ እርቅ ያስፈልጋቸዋል::

ደራሽ በሆነ ሀሳብ የተጠላሉ: የተገዳደሉ : የተገፋፉ: በጥርጣሬ ወጥመድ ዉስጥ የገቡ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ብሄራዊ እርቅ ሂደትና ሰላም ማዉረድ ያስፈልጋቸዋል:: በጥቅሉ በልዩ ልዩ ማህበራዊ ታሳቢዎች: ፖለቲካዊ ጭብጦችና የልዩነትና የጥላቻ መሰረትን በሚያራግቡ እሴቶች ዙሪያ ሁሉ እርቅና ይቅርታ ሰላምና ስምምነት መደረግ አለበት:: የሆነ ሆኖ ግን እነዚህ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በጥልቀትና በስፋት መጠናትና መዘርዘር አለባቸዉ:: ከላይ ከተጠቀሱትም ልዩ ልዩ የብሄራዊ እርቅ ሞዴሎች(ስልቶ) ዉስጥም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዉያን የትኞቹ አግባብነት እንዳላቸዉ ሰፊ ዉይይትና ጥናት መደረግ አለበት:: ብሄራዊ እርቅ: ይቅርታና ስምምነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ: ምሁራን: ፖለቲከኞች እና ልሂቃን በስፋትና በጥልቀት የሚሳተፉበት እንዲሆን ተደርጎ መዘጋጀት አለበት::

በጥቅል ብሄራዊ እርቅና ይቅርታ የጋራ ሀገር ግንባታ በጋራ ተሳትፎ ይሆን ዘንድ: የጋራ የሆኑትንም ሆነ የተናጠል የሆኑትን ሀገራዊ እሴቶች በጋራ የማክበር ባህል ግንባታ መርህ ይሆን ዘንድ: ያነሰ ወይም የበዛ ታሪክ ያለዉ ወገን የሚል ስነልቦና ከሀገሪቱ ይወገድ ዘንድ: የጠፋም የለማም የቀደመ ስራ ሁሉ የጋራ ታሪክ ብሎም የጋራ የእጅ ስራ ዉጤት መሆኑ ታዉቆ የአሁኒቷ ኢትዮጵያ የተፈጠረችዉ በሁሉ መስተጋብራዊ ሂደት ነዉ የሚል ስነልቦናል በኢትዮጵያዉያን ማህበረሰብ ዘንድ ይረብ ዘንድ ዛሬን በእርቅና በስምምነት ማበጃጀት ተገቢ ነዉ:: በጥቅሉ ለነገዉ ትዉልድ የተሻለ መደላድል የመፍጠር ሀላፊነት እና የማህበረሰብ የርስ በርስበስ ፍቅርና መተማመን በአንድ ትልቅ ታሳቢ ዉስጥ ገብቶ ብሄራዊ እርቅና ይቅርታ ቢደረግ የሁሉ ልብ የሚድንበት እና ወደ ሰበአዊ ልዕልና በጋራ መሸጋገር የሚያስችል ድልድይ በሀገር ይፈጠራል:: ትናት ጉም የዋጠዉ እዉነት ነዉ:: ዛሬ ግን ለዚህ ትዉልድ ዋና መሰረቱ ነዉ::

የነገ ትዉልድ ደግሞ በከፍታ መሰረት ላይ ሊቆም የሚችለዉ የዛሬ ትዉልድ በሚጥለዉ የብሄራዊ የእርቅና የስምምነት መንፈስ ላይ ተንተርሶ ነዉ:: እናም ባለ አዕምሮ የሆኑ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ በዚህ ዙሪያ ይተጉና ሳያሰልሱ ይሰሩ ዘንድ ይመከራሉ:: ስለ ትናቱ እዉነት : ወይም ስለ ዛሬ ጥላቻ መኖር ቁምነገር አይደለም:: ስለነገዉ ትዉልድ ሲባል ዛሬን በብሄራዊ እርቅ በይቅርታ ብሎም በስምምነት መንፈስ ማስጌጥ ግን ብቸኛዉ የዚህ ትዉልድ ባለ አዕምሮ ሀይላት ሁሉ ሊያንሰላስሉት የሚገባ አብሪ ሀሳብ ሊሆን ይገባል:: በልዩ ልዩ ምክንያት ከተለያዩ ማህበረሰቦች የፈለቁ ምሁራን: ፖለቲከኞችና ልሂቃን እንደ ትልቅ ግብ ያነገቡት የጥላቻ እሴት ይፈርስ ዘንድ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዉያን በብሄራዊ እርቅ: ይቅርታና ስምምነት ሂደት ዉስጥ ማለፋቸዉ የግድ ነዉ::

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on October 20, 2014
  • By:
  • Last Modified: October 20, 2014 @ 8:45 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar