የማለዳ ወግ … ከሊባኖስ እስከ ሳውዲ ፣ ሌላ የደም እንባ እንዳናነባ !
* የተዘጋው የአረብ ሀገር ጉዞ ይጀመር ይሆን?
እለተ አርብ ጥቅምት 14 ቀን 2007 ይላል የቀን መቁጠሪያው ። በጠዋቱ ተነስቸ መብተክተክ ይዣለሁ ፣ መነሻየ ከሳምንት በፊት በሃገረ ሊባኖስ መዲና ቤሩት ስሟን ለደህነንነት ስል የማልገልጻት ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሰራተኛ በግድያ ወንጀል ተጠርጥራ ባለችበት ሁኔታ በነፍሰ ገዳይነት ውንጀላ መክሻሸፍ አስመልክቶ አዳዲስ መረጃን ለወዳጆቸ ለእናንተ ለማቀበል ነው ። ብዙም ሳልቆይ ቤሩት የመረጃ ምንጭ ወዳጆቸ ስልክ ደወልኩ … መረጃውን ሰባሰብኩ ፣ የኢትዮጵያ ቆንስል ጀኔራል መስሪያ ቤት ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተለው እንደሆነ ሰማሁ ፣ ዘብጥያ ውስጥ ያለችው እህት ስላለችበት ሁኔታ ቤሩት የሚገኘው የኢትዮጵ ቆንስል መ/ቤት ሊባኖስ ላሉ ተቆርቋሪ ዜጎቹ እንኳ መረጃ ለማቀበል ተቆጥቧል። እንደ ምክንያት ያቀረበው ” በፍርድ ቤት ያለ ጉዳይ ስለሆነ ምንም አይነት መረጃ መስጠት አይቻልም! ” የሚል ነው ። እዚህ ላይ ግራ ተጋብቻለሁ… ከሳሽ በመገናኛ ብዙሃን የናኘው ወደ ኋላ የተወላከፈ መረጃ ሆኖ የተገኘው መረጃ ባይሳካለትና ቢከሽፍበትም በፍርድ ቤት ያለ ጉዳይን ዘክዝኮ የወነጀላትን እህት ከሳሽ ህግ መጣሱን በመረጃ አስደግፎ መብቷን ማስጠበቅና መከላከል አይቻል ይሆን? ለፍርድ ቤት አቅርቦ የዋስ መብቷን ማስከበር የማይሞከርበትን መንገድ ምንድን ነው ? ይህን እየተደረገ ነው ወይ ? ብለን ሰውኛ ጥያቄ ብንጠይቅ መልሱ ጉዳዩ በፍርድ ከመያያዙ ጋር ታኮ መመለስ አንችልም የሚል ምላሽ መሰጠቱ ግራ ቢያጋባኝ አትገረሙ … ከዚሁ ጋር አሳሳቢው “ተከሳሽ እህት በምርመራ ተገዳ መግደሏን ልታምን ትችላለች!” የሚለው ስጋት እያንዣበበ መሆኑም ይጠቀሳል። ፍርዱ የሚሰጠው በአረብ ምድር በሊባኖስ ሰማይ ስር በመሆኑ በቆንሰሏ በር ተጎትታ ስትደበደብ የተመለከትናት እና የህሊናችን የማትጠፋ ቁስል የሆነችው የአለም ደቻሳ በአዕምሯችን ለታተመ ዜጎች የዚህች እህት መጨረሻ ያሳስበናል …
ይህንና ያንን ሳስብ ሳሰላስል ደጎስ ያለ መረጃ እስኪገኝ ስደቱን ተከትሎ ለከፋው ስማችን ምንጩን አውጥቸ አወረድኩት …. ከዚያ ሁሉ በፊት ግን “የአረብ ሃገሩ የተዘጋ መንገድ ሊከፈት ነው!” የሚል ሰሞነኛ የሹክሹክታ መረጃና የቱጃር የቪዛ ደላሎች ሳውዲ መድረስን ዜና ሰምቻለሁና እሱን ነካክቸው ላልፍ ፣ ከዚህ በፊት በኮንትራት ሰራተኞች አበሳ ዙሪያ ያጋጠመኝን አወሳስቸ ላልፍ ከራሴ ጋር ተስማማሁና ወጌን ጀመርኩት …
ከያዝነው ወር በፊት ጀምሮ “ወደ አረብ ሃገራት የተዘጋው የኮንትራት ቪዛ ይከፈታል !” የሚል መረጃ በሰፊው በመሰራጨት ላይ ነው ። እኔም የሚሆነው የሚናገሩት ባይሆንም ኢምሬት ላይ በጉዳዩ መግለጫ የሰጡት ፕሬዘደነት ዶር ሙላትና የኢምሬት አምባሳድር የተዘጋውን የአረብ መንገድ ለመክፈት ገና ህግ መመሪያ እየወጣ መሆኑን ፣ ከሃገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ከሁሉ አስቀድሞ እንደሚከወን ማሳሰባቸውን እንጅ መንገዱ ይከፈታል የሚል መረጃ አለመኖሩን በመረጃ ማስረጃ ለማስረዳት መሞከሬ ባይቀርም የእኔ መረጃ የከሸፈ መሆኑን ወዳጆች እየነገሩኝ ነው ፣ እነርሱ እውነት ነው ላሉት ማስረጃ ጭብጥ የሚሉትም አላቸው ። ይህም በቪዛው ንግድ ተሰማርተው ከገጠር እስከ ከተማ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰራተኛን ለሳውዲ ” ገበያ” ያቀረቡት ባለ ኤጀንሲ ደላላሉች ጅዳና ሪያድ መምጣት መጀመራቸው ነው ። እርግጥ ነው ከምንም ተነስተው ዛሬ “አንቱ “የተባሉና ጠባቂ የሚያስፈልገው ንብረት አላቸው የሚባሉት ወጣትና ጎልማሳ ኢትዮጵያውያን ደላሎችና የቪዛ ነጋዴዎች በጅዳና ሪያድ ከተሞች በአድርባዮች ታጅበው ሲንሸራሸሩ ተመልክቻለሁ … ሁሉንም መኮነን ባይቻል በአብዛኛው ደላሎቸደና አዘዋዋሪ ነጋዴዎች ለገንዘብ ሲሉ ምንም የማያውቁ እህቶቻችን ከየገጠሩ እየሰበሰቡ በየአረብ ሃገሩ ሲበትኗቸው የት እንዳሉ ያሉበትን ሁኔታ እንኳ ማወቅ የማይፈልጉ መሆናቸውን አውቃለሁ ። ሰራተኞች ተበደልን ብለው ስልክ ሲደውሉላቸው ስልካቸውን አያነሱም ። እኒህ ናቸው ሌላ ዜጋን አሁንም ወደ መከራው አለም ለመላክ በከተማችን ገብተው የመንገዱን መከፈት የሚጠባበቁት …መቸም ባለ ጸጎች ናቸውና ስላካበቱት መዋዕለ ንዋይ ጓጉቸ የቀናሁ እንዳያስመሰል በሚል ብዙ ከማለት መቆጠቡን እመርጣለሁ ። ይህን ስል ስማችን ለመጉደፉ ምክንያቶቸን በአጭሩ ፣ የግፍ በደሉን ቀማሽ እህቶች የሰማሁትን ምስክርነት በጨረፍታ መመልከቱ ግድ ይለኛል።
ድሮ ድሮ በማይባል የሩቅ ዘመን ትዝታ ሃበሻ በሚል የምንታወቀው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን ጨምሮ በአረቦች ዘንድ እንከበር ፣ እንታመን ፣ እንወደድ ነበር ። ይህን ወቅት ድንጋይ ዳቦ የነበረበት ዘመን አይደለም ። … እኔም “ኩራት ክብር እየቀረ ነው !” በሚባልበት የጊዜ ጫፍ የዛሬ 20 አመት ገደማ ሳውዲ መጥቸ በአረብ ሃገር ተንደላቀው በክብር የኖሩት ጎደለብን ብለው “ቀረ ፣ እየጠፋ ነው! “።ያሉትን የሃበሻ ክብርና ሞገስ ደርሸበታለሁ ። አሁን አሁን ግን እንጃ …አመኔታውና ክብሩ እየሸሸን መሄዱ ይሰማኛል። ሳንታመን ፣ ሳንከበር እንዳንከርምን የባጀነውም ያለ ምክንያት አይደለም ። አዎ በሚሊዮን የሚቆጥር ስደተኛ የህግ ሽፋን በተሰጠውና ህግ በማያውቀው ህገ ወጥ መንገድ ተሽሎክሉከው በቦሌም ፣ በባሌም ፣ በሞያሌም ፣ በጅቡቲና ሶማሊያም ወደ ከፋው የስደት ቀጠና ሲያቀኑ ነገር ተበላሽቷል። ስለማላውቀው የአፍሪካ ሃገር የከፋ ስደት መናገር ባልችልም ስለ አረቡ ሃገር ስደተኛ መናገር አይገደኝም ።
… ቀን ወጣለት የተባለው ያልሰመረለት የሃገሬ ገበሬ ልጆችን ፣ የኑሮ ውድነት ጣሪያ ነክቶ ፣ የእለት ጉርሱን አግኝቶ መኖር አቅቶት በችጋር የሚደቆሰው ከተሜ ፣ በአንድ ጀንበር የተለወጡት እያማመሉ ያለውን ጥሎ ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ የተሰደደው ቀቢጸ ተስፈኛ ፣ በአረብ ሃገር የሚላኩ የተሳሳቱ መረጃዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ አረብ ሃገር ተሰደዋል። “ከገጠር እስከ ከተማ መንገዶች ተሰርተው ፎቆች ተገጥግጠው ፣ በየአመቱ የምታድግ የምትመነደገው ሃገር ” ተብሎ ለእድገቷ ምስክር የሚጣቀስላት ሃገር ዜጎች በግፍ ወደ አረብ ሃገር መሰደድ መጀመራችን ስማችን ማክፋት መጀመሩና ነሩ ሁሉ ሲያበለሻሸው በአይኔ በብሌኑ ተመልክቻለሁ። አምስትና ስድስት አመታት በፊተ በስማችን መክፋት መበለሻሸት ዙሪያ ሲነሳ ከዚህ ቀደም የሚጠቀሱ ምክንያቶች ጥቂት ሃበሾቸ የተሰማሩባች ህገ ወጥ ስራዎች መጠጥ መሸጥ ፣ ዝሙት እና የመሳሰሉት ናቸው ይባል ነበር ። … ይህ ደግሞ የአረቦች ህገ ወጥ ምርት አቅርቦቱን ተጠቃሚ መሆን ፣ በገዥነት ፣ በተባባሪና በድጋፍ ሰጭነት ይሰራ የነበረው ስማችን ካስከፋው ስራ አረቦችን ቂም አስቋጠሮ ስማችን አጉድፎ በአደጋ የጣለን ከኮንተራት ስራው ቅበላው ጋር የመጣው የነፍስ ማጥፋት ውንጀላ ነው ። ይህ በኢትዮጵያውያን የኮንትራት ሰራተኞች ተፈጸመ የተባለው ወንጀል እየሰፋ መጣ ተብሎ በአደባባይ ስማችን እየተነሳ ሲወገዝ ፣ ጉብል እድሜያቸው ከሃያ የማይዘሉ የኮንትራት ሰራተኛ እህቶች “ገዳይ” ተብለው የገደሉበትን ምክንያት በአረብ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን ሲናገሩት ሰምተናል ። ይህም ስማችን ቅስማችን ሰብሮታል … በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንደጨው ተበትነዋልና ስማችን አሳፋሪ ሆኖ እስካሁን ቀጥሏል።
ለዚህ ሁሉ ምክንያት ከሃገር ቤት ከወላጅ ጀምሮ እስከ ደላላ ፣ ከደላላ እስከ ሃላፊነታቸውን መወጣት የገደዳቸው የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ናቸው የሚል እምነት አለኝ ። በዋናነት ደግሞ ከኢትዮጵያውያ በህጋዊ መንገድ ወደ ሳውዲና ወደ ቀሩት አረብ ሃገራት መላክ ሲጀመር በሃገራት መካከል በተደረገ ስምምነትን መሰረት ያደረገ አለመሆኑ፣ ከስልጠና ጀምሮ እስከ ስራ ስምሪት በቂ ስልጠናው ቀርቶ በሚደርሱቸው አረብ ሃገራት ያሉ ኢንባሲዎችና ቆንስሎች በሙያው በተካኑ ዲፕሎማቶች አለመመደብና በቂ ዝግጅት ያለመደረጉ አሁን ለተጋረጥንበት ጣጣ አደጋ አብቅቶናል። ይህ በዋንኛነት በእጅጉ እንደጎዳን ፣ እናድስ እንገንባ የምንለውን ስማችን እንዳከፋው ፣ እንደጎዳው አሰረገጦ የመናገር አቅሙ አለኝ …
የዘሃራ ውጋት …
ጊዜው በአዲሱ የፈረንጆች 2012 አሮጌው የፈረንጆች አመት ሊሰናበት ሲያስገመግም አዲሱ አመት 2013 ሊመጣ የቀሩት ሁለት ቀናት ብቻ ናቸው ፡፡ የጅዳ የሰሞኑ አየር ደስ የሚል ሆኗል ፡፡ ሙቀት ወበቅ የሚሉት ነገር ከጠፋ ሰነባብቷል ! አንዳንድ ቀን ግን አመል ሆኖበት ነው መሰል አልፎ አልፎ ሙቀቱ ብቅ ብሎ ጥልቅ ማለቱን ግን አልተወውም . . . ያማታው ብርድ ግን አይጣል ነው . . . ! ጂዳ ቆንስል ግቢ አዲስ በተሰራችው የኮንትራት ሰራተኞች መጠለያ ከታጨቁት እህቶች አንዳንዶቹን ከጎናቸው በርከክ ብየ አዳምጣለሁ፡፡ ሲለኝ ደግሞ ፎቶ ለመረጃ አነሳለሁ. . . ዘሃራ የተባለች እህት ቀልቤን ጨምድዳዋለች ! ይህች ከ15 አመት እድሜዋ የማትዘልለው ጉብል በኮንትራት መጥታና ከአንድ ክፍል ለአራት ቀናት ያለ ምግብና ውሃ በመዘጋቷ በማታውቀው ሃገር ቤቱ ሲከፈትላት ሾልካ ጠፍታለች ፡፡ ያልታደለችው ዘሃራ ግን ሳታስበውና ሳታልመው በሰው አውሬዎች እጅ ወደቀች . . . ሊደፍሩ ለሁለት ሲያንገላቷት የተጎዳው ጀርባዋ አላስቀምጥ አላስተኛ ብሎ እንዳስቸገራት የተረዳሁት ስታናግረኝ ከአንዱ ጎን ወደ ሌላኛው ጎን ለመገላበጥ ስትሞክር ነበር . . ፣ ዘሃራን ደጋግሜ መደፈር አለመደፈሯን ስጠይቃት “አልደፈሩኝም አረ !” ስትል ክብ ፊቷን ከስክሳና እንደ ማፈር እያለች አንገቷን ደፍታ ደጋግማ መለሰችልኝ ! ዘሃራን በኒያ ባለችኝ ጎረምሶች ጡንቻ ተይዛና ተደብድባ ወገቧ ሲሰበር ከመደፈር እንዴት እንደተረፈች ለመገመትና ለማመን አልዋጥልህ አለኝ ! ደግሞ እኮ ጎረምሳ ለምመስለው ለእኔስ ቢሆን እንዴት መደፈሯት ትነግረኛለች? አልኩና በውስጤ ይህንን ጥያቄ ከመደጋገም ራሴን ቆጠብኩ . . . ከትንሿ ልጅ ከዘሃራ ጋር በነበረኝ ቆይታ ስሜቴ ክፉኛ ተጎድቷል !
ዛሬ ዘሃራ ሃገር ቤት ናት ” ብድሬን አልከ ፈልኩምና የወላጆቸን ፊት አላይም !” ማለቷን አስብና ይጨንቀኛል በመንፈስ እታመማናለሁ ፣ አዎ ዘሃራ ህይወቷ እንደ አካሏ መናጋቱን ዘልቆ አውቃለሁና ፣ ብዙ ለጋ ዘሃራዎችን አይቻለሁ ፣ እህ ብየ አድምጫለሁና የውስጥ ህመሜን እኔ ነኝ የማውቀው …ዛሬ ዘሃራ መሰሎችዋ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ግን እንጃ …
የሪያዱ ወዳጀ ልብን የሚሰብር መልዕክት . .
በሪያድ መንፉሃ ተብሎ በሚጠራውና በባህር የመጡ ሃበሾች እርስ በርሳቸው በሰላ ቢላዋ በሚወጋጉበት መንደር በተለያዩ ቀናት በአስገድዶ መድፈር ባሰሪዎቻቸውና በቤተሰቦቻቸው የተጠቁ እህቶችን ተጥለው መገኘታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ እህቶችን አግኝተው ያስጠጓቸው ኢትዮጵያውያንን በስልክ አግኝቻቸው ብዙ መረጃን ሰጥተውኛል፡፡ በአብዛኛው እየተደፈሩ የሚመጡ የኮንትራት ሰራተኞች ቁጥር ከፋ ያለ መሆኑ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ከአንድ ወዳጀ ከዚህ በፊት አንድ የደረሰኝ አሳዛኝ መልዕክት የኮንትራት ሰራተኞች ሁኔታ እየከፋ መሄድ ድፍንፍን አድርጎም ቢሆን ያስረዳል ባይ ነኝ! የምሬት መልዕክቱን ዛሬም ደግሜ እንዳለች አውርጃታለሁና ተመልከቷት !
” ወዳጄ ሲራክ ከትላንት ወዲያ ሪያድ ውስጥ ኣንዲት እድሜዋ 19 የሚጠጋት ሴት ልጅ ኣሰሪዎቿ ዑለያ በሚባለው አካባቢ ያለ ምንም ፓስፖርት ወይም ኢቃማ ልብሷን በ ፌስታል አስይዘው ከመኪና አውርደው ጥለዋት ሄዱ። ስታለቅስ አግኝቼ የመጣው ይምጣ ቤቴ ወሰድኳት ። ደሞዝ ተከፍሏት ኣያውቅም ፣ ስራውንም በደምብ ኣለመደችም፣ በጣም ደንግጣለች፣ ዝምታ ወጧታል። የጣሏት ከፊሎቿ እንደሆኑ እና ከመጣች 3 ወሯ እንደሆናት ነገረችኝ።ደቡብ ወሎ ፣ ወግዲ ከሚባል ገጠር ሸህ ሁሴን በሚባል ደላላ ኣማካኝነት ከእህቷ እና ሌሎች 5 ሳዱላዎች ጋር ዕድሜዋን 25 ኣድርገው ወደ ሳውዲ እንዳመጧቸው እና እህቷ የት እንዳለች እንደማታውቅ ነገረችኝ። ዜግነቴን ጠላሁት። የት ልሂድ ከዚህ በላይ ፣እዚህ አገር መኖር አልፈልግም። ዜግነቴን ጠላሁት…” ነበር ያለኝ !
የኮንትራት ሰራተኞችን አበሳ ዘክዝኬ በምስል መረጃ ባቀርበው ደስ ባለኝ ፣ ግን ምስሎቹን ለመለጠፍና ግፉን ለማሳየት ልቤ ቢቆርጥም ፣ ሰብዕናን ላለማሸማቀቅ ስል ብቻ የምስል መረጃውን ልዘለው ግድ ብሎኛል፣ ስማችን ከፍቷል ብሎ በስሱ ስለስም መጨነቅ ለእኔ ቀልድ ነው ፣ የሚሰራው ታስቦና ተጠንቶ ስላልሆነ ፣ መብታችን የሚያስጠበቅልን ስለጠፋ ፣ ከስም በላይ ሰብዕናችን መርከስ ይዟልና ግፍ እየተፈጸብን ነው ፣ ለዚህ ማሳያ በሃገረ ሊባኖስ እየሆነ ያለውን በጥልቀት መመልከቱ ይበቃል፣ ለዚህ ማሳያ በሳውዲ የጅዳ ቆንስልና እና በሪያድ ኢንባሲ መጠለያ ያለፉትንና አሁን ድረስ ያሉትን ግፉዕ ዜጎች በደል ሰምተናል ፣ እየሰማን ነው ! ዜጎች ሰብአዊ መብታቸው ሲደፈጠጥና የተስማሙበት ኮንትራት ውል ተጣሰብን የሚሉ እህቶቸን ድምጽ ማሰማት ለእኔ ነፍሴ የፈቀደው ስራ ነው ፣ የመንግስት ዲፕላማቶች ቀዳሚ ስራ ነጋ ጠባ ለምንጠይቀው የዜጎች መብት ጥበቃ ቆሞ ወገናዊነትን ለህዝብ ለማሳየት መሞከር ነው ! የሚፈለገው የሚያወራ ሳይሆን የሚሰራ ነውና …የመንግስት ተወካዮች በህግና በስርአት የመጡ ዜጎችን መብት ማስከበር አለባቸው ! የቪዛ ውል ማስፈጸሚያ ገንዘብ እየሰበሰቡ ባጸደቁት የኮንትራት የስራ ውል ላይ የተጻፉት ስምምነቶች የመከታተልና የማስፈጸም ሃላፊነት አለባቸው! ፍትህ ሲጎድል ተከራክረው ሊያስከብሩልን ይገባል ! … ከዚህ በፊት መብታቸው ተጥሶ ተሸፋፍኖ እንደተላኩት ጉዳተኞች ወደ ሃገር ቤት ለማሳፈር የሚደረገውን ጥረት ጎን ለጎን የተገፊዎችን በደል ፍትህ ሊፈለግለት ይጋባል ፣ ይህ ግን በአብዛኛው አይደረግም ፣ በዚህ ረገድ እማኝነቱን ከባለቤቶቹ “እህ” ብየ ሰምቻለሁና እነግራችኋለሁ ! የተጎዱት ከተደፋባቸው የመከራ ህይዎትና ከእድሜ አለመብሰል አንጻር ” ወደ ሃገራችን እንግባ ! ከቤተሰቦቻችን ቀላቅሉን !” ማለታቸው ደጋፊ ማጣትና ስጋት እንጅ ያልተበደሉ ሆነው ፍትህን ሽሽት አይደለም !
መንግስት ይህ ሁሉ እየተነገረው የሚሰማ አይመስልም።ከአመት በፊት ወደ አረብ ሃገራት የተዘጋው መንገድ ደላላዎቹን ወደ ሊባኖስ ኩዌትና ኳታር የሚያሸጋግር ስራቸውን እንዳልገደበው አውቃለሁ። ከቀናት በፊት ሊባኖስና ቃጣር በተዘዋዋሪ መንገድ የገቡ ኢትዮጵያውያን አጋጥመውኛል ። ይህም ሁሉ ሆኖ ከኢትዮጵያ መንግስት አስቀድመው የሳውዲ መንግስት ያገደው ከኢትዮጵያን ሰራተኛ የማስማጣት እገዳ በኢትዮጵያ መንግስት ብቻ እገዳው ስለተነሳ ሰራተኛን ወደ ሳውዲ ማስገባቱ ይሰምራል ባልልም የአረብ ሃገሩ መንገድ ምንም ባልተሰራበት ሁኔታ መታሰቡ በራሱ ያማል ። አልተሰራም የምለው በጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት በኩል ያለውን ነባራዊ አቅም አውቃለሁና ነው ፣ ጅዳ ያለ ቋሚ ዲፕሎማት በተጠባባቂው ባለስልጣን መመራት ከጀመረች መንፈቅ ማለፉን ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖም አያውቁም አልልም ፣ ብቻ መንግስት ጀሮ ሰጥቶ ሊሰማን ይገባል ! … አባቶች ” አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ !” እንደሚሉት ሆኖ ሌላ እንባ እንዳናነባ …!
ቸር ያሰማል !
ነቢዩ ሲራክ
Average Rating