www.maledatimes.com ወጣቱ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት ምክንያት ከ10ኛ ፎቅ ተከስክሶ ሕይወቱ አለፈ በታምሩ ጽጌ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ወጣቱ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት ምክንያት ከ10ኛ ፎቅ ተከስክሶ ሕይወቱ አለፈ በታምሩ ጽጌ

By   /   September 23, 2012  /   1 Comment

    Print       Email
0 0
Read Time:12 Minute, 29 Second


ምንጭ(ሪፖርተር)

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈተ ሕይወትን ከሰማበት ዕለት ጀምሮ መሪር ሐዘን ውስጥ ገብቶ የነበረው ወንድወሰን ተስፋዬ የተባለ የ30 ዓመት ወጣት ከአሥረኛ ፎቅ ላይ ተከስክሶ ሕይወቱ ማለፉ ታወቀ፡፡
ወጣቱ ራሱ ተወርውሮ ሕይወቱ ያለፈው ነሐሴ 24 ቀን 2004 ዓ.ም. በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በቀድሞው ቀበሌ 02/03 በተለምዶ ወሎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው ሚና ሕንፃ ላይ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደል ወንጀል ምርመራ ዲቪዚዮን ለሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

ወጣቱ አሰፋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሚባል ድርጅት ውስጥ በሹፌርነት ተቀጥሮ የታሸጉ ምግቦችን እያዞረ ለሱፐር ማርኬቶችና ለተለያዩ የንግድ ተቋሞች ያከፋፍል ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሕልፈተ ሕይወት ከተሰማበት ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ “መኖር ምን ያደርጋል” በማለት ከሥራ ባልደረቦቹ ተለይቶና ለብቻው በመሆን አንዳንድ ጊዜም ያለቅስ እንደነበር ይሠራበት ከነበረው ድርጅት ባለቤት መስማቱን የገለጸው ፖሊስ፣ አሠሪውም የወጣቱ ሁኔታ ስላላማራቸው ለአራት ቀናት ዕረፍት ወስዶና ተረጋግቶ እንዲመለስ በመፍቀድ፣ የመኪና ቁልፍ ተረክበውት ወደ ቤቱ መሄዱንና በመጨረሻም ሕይወቱ ማለፉን መስማታቸውን ተናግሯል፡፡

ወጣቱ የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል አለመሆኑን፣ ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍቃሪ እንደነበርና እሳቸው በፓርላማም ይሁን በማንኛውም ቦታ ሆነው ንግግር ያደርጋሉ ከተባለ፣ ሥራውን ሁሉ ትቶ ሲያዳምጥ እንደሚቆይ ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡን የተናገረው ፖሊስ፣ ከሚና ሕንፃ አሥረኛ ፎቅ ላይ ተፈጥፍጦ ሕይወቱ ባለፈበት ዕለትም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሦስት ሃያ በሰላሳ የሚሆኑና አራት ትናንሽ ፎቶግራፎች ይዞ እንደነበር ጠቁሞ፣ ምስላቸው የታተመበት ቲሸርትም ለብሶ እንደነበር ገልጿል፡፡

ከፎቅ ላይ ተከስክሶ ሕይወቱ ማለፉ ለፖሊስ እንደተነገረ በአካባቢው የነበረ የፖሊስ ኃይል በደረሰበት ወቅት በወጣቱ ኪስ ውስጥ ከደብተር ላይ የተገነጠለችና እጥፍጥፍ ብላ ከተቀመጠች ወረቀት በስተቀር ምንም ዓይነት ማስረጃ እንዳልነበር የገለጸው ፖሊስ፣ ተጣጥፋ በተገኘችው ወረቀት ላይ ወጣቱ ኑዛዜውን አሳርፎ ማግኘቱን ተናግሯል፡፡

ራሱን ለማጥፋቱ ተጠያቂው ራሱ ብቻ መሆኑን፣ ከማንም ጋር ፀብም ሆነ ሌላ ችግር የሌለው መሆኑን፣ ከአለቃው ጋርም ፍቅር መሆኑን፣ በጣም ጥሩ ሰው መሆናቸውንና ሌሎችንም አድንቆ በጻፈባት በዚያች ወረቀት ላይ፣ ለሕይወቱ መጥፋት ምክንያትም ባለራዕዩ፣ ለወጣቱ በተለይ ሥራ ሌለው ትኩስ ኃይል እንዴት ሥራ መፍጠር እንደሚችል በተግባር ያሳዩ፣ ሁሉም የሰው ልጆች እኩል መሆናቸውንና በረሀብና በእርዛት የምትታወቅን አገር መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ባደረጉት ጥረት ከፍተኛ እመርታ ያሳዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ከሞቱ፣ “መኖር ለምን ያስፈልጋል” በማለት ራሱን በራሱ ለማጥፋት ወስኖ እንዳደረገው በዝርዝር በኑዛዜው ወረቀት ላይ ሰፍሮ ማግኘቱን ዲቪዚዮኑ አስረድቷል፡፡ ደብዳቤውንም እንድንመለከተው አድርጓል፡፡

ፖሊስ ወጣቱ ከጻፈው ደብዳቤ በስተቀር ስለ ወጣቱ ማንነት የሚያስረዳ ምንም ዓይነት መረጃ ስላላገኘ፣ የነበረው አማራጭ ደብዳቤውን ደጋግሞ ማንበብ ብቻ ነበር፡፡ ደብዳቤውን ደጋግሞ ያነበበው ፖሊስ “ባለውለታዬ ለሆነችው ሕይወት ሽፈራው” በሚል ስም ካሳንችስ አካባቢ ካለው አዋሽ ባንክ ከራሱ ሒሳብ 46‚100 ብር በማውጣት አየር ጤና በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሄድ የልጅቷ ሒሳብ ውስጥ ማስገባቱንና በድምሩ 54,980 ብር እንዳለ መጥቀሱን ተመለከተ፡፡ ፖሊስ ከደብዳቤው ላይ ያገኘውን ጠቋሚ መረጃ በመያዝ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ የባንኮች ሒሳብ መዝገብ ለማየት የሚያስችለውን ፈቃድ ከፍርድ ቤት በማውጣት፣ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (አየር ጤና ቅርንጫፍ) ሄዶ ሲያረጋግጥ፣ ወጣቱ ባለበት ቀን ሒሳብ ማስገባቱንና የጠቀሰውም የገንዘብ መጠን ትክክል መሆኑን ቢያረጋግጥም፣ ወጣቱ ሒሳብ ሲያስገባ የእሷን ስም፣ መለያ ቁጥርና የእሱን ፊርማ ከማስፈር ውጭ ምንም ማስረጃ እንዳልጻፈ ተረዳ፡፡

ፖሊስ ከባንኩ ያገኘውን የሕይወት ሽፈራውን አድራሻ ይዞ በባንክ ሒሳብ መዝገብ ላይ ያስመዘገባቸውን ቀበሌና የቤት ቁጥር ፍለጋ ሲሄድ ልጅቷ በተባለው ቤት ውስጥ ነዋሪ ሳትሆን፣ ወደ ውጭ (ዓረብ አገር) ስትሄድ የባንክ ሒሳብ ለመክፈት መታወቂያ ስለሚያስፈልጋት፣ በዚያ ቤት ቁጥር ማውጣቷንና በወቅቱ እንደሌለች ከቤቱ ባለቤቶች ተረዳ፡፡ ወንድወሰን ስለሚባል ልጅ የሚያውቁት ወይም የሰሙት ነገር እንዳለ ሲጠይቅ እንደሚያውቁትና ጓደኛዋ (እጮኛዋ) እንደሆነ አስረድተው ቤቱን እንዳሳዩት አስረድቷል፡፡

ፖሊስ ከረጅም ልፋት በኋላ የወጣቱን ቤት ሲያገኘው ሟች ከሦስት ወንድሞቹና አንድ እህቱ ጋር እንደሚኖር እናቱም በሕይወት እንዳሉ ካረጋገጠ በኋላ፣ የያዘውን ፎቶግራፍ ሲያሳያቸው ወንድማቸው መሆኑን ያረጋግጡለታል፡፡ የት እንዳለ ሲጠይቃቸው፣ ከአንድ ቀን በፊት እንደወጣና እንዳልተመለሰ ይገልጹለታል፡፡ ለግል ጉዳይ እንደሚፈለግ በመንገር ቤተሰቡን አረጋግቶ ነገር ግን ለጐረቤት በአደጋ ምክንያት ሕይወቱ ማለፉን በማስረዳት እንዲያረዷቸው አድርጐ መመለሱን ዲቪዚዮኑ አብራርቷል፡፡

የወጣቱ ቤተሰቦች አስከሬኑን ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በማውጣት የቀብር ሥርዓቱን ከፈጸሙ በኋላ፣ የሟች ወንድም ወደ ፖሊስ ጣቢያ መጥቶ እንደነበር የገለጸው ፖሊስ፣ ወጣቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍፁም የሆነ ፍቅር እንደነበረው፣ የመኝታ ቤቱ ሙሉ ግድግዳ በእሳቸው ፎቶግራፍ የተሸፈነ መሆኑን፣ ከፎቅ ራሱን ወርውሮ ሞተ በተባለበት ዕለት ጠዋት ከደብተር ላይ ወረቀት ገንጥሎ ሲጽፍ እንደነበር የገነጠለበትን ደብተር ይዞ በመምጣት ማረጋገጡን ፖሊስ ገልጿል፡፡
የወጣቱ ሕይወት ማለፍ ለምን እስከዛሬ እንደተደበቀ ፖሊስን ተጠይቆ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ድንገተኛ ሕልፈት ብዙዎችን ለመሪር ሐዘን የዳረገበት ወቅት እንደነበርና በዚህ ወቅት (ነሐሴ 24 ቀን 2004 ዓ.ም.) እንደዚህ ያለ ክስተት ይፋ ማድረግ ምናልባትም ሌሎችን ወደማይሆን መንገድ ሊመራ ይችላል በሚል ዝምታ መምረጡን አስረድቷል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on September 23, 2012
  • By:
  • Last Modified: September 23, 2012 @ 2:58 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

One thought on “ወጣቱ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት ምክንያት ከ10ኛ ፎቅ ተከስክሶ ሕይወቱ አለፈ በታምሩ ጽጌ

Comments are closed.

<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar