”ፕሮፌሰር መስፍንን ለቀቅ” ለሚለው ለአቶ አንተነህ መርዕድ ጽሁፍ መልስ፣ ቁ. 1
ከጣሰው አንተነህ ከስዊድን (tasewanete@gmail.com)
ዛሬ ኦክቶበር 8/2014 ምሳ ሰዓት ላይ አንድ ጓደኛዬ ደውሎ ”ፕሮፌሰር መስፍንን ለቀቅ” የሚለውን ጽሁፍ አንብቤው እንደሆን ጠየቀኝ። ይህ ሰው በፕሮፌሰር መስፍን ማንነት ላይ ይቅርታ ጠይቄው ስለነበር ”ቢጤህ የጻፈውን እየው” ለማልት ማሾፉ ነበር። ለፕሮፌሰር መስፍን ከወጣትነት በተለይም የትግራይ ብሄረተኞች ስልጣን ላይ ሊመጡ አጥቢያ ጀምሮ በየአደባባዩ ድምጼን ከፍ አድርጌና በጽሁፍ ጠበቃ ሆኜ ቆሜላቸዋለሁ። ሆኖም አልፎ አልፎ በሚጽፉትና በሚናገሩት ብደነግጥም የራሴን ቅን ትርጉም እየፈጠርሁለት እራሴን ሸንግዬ ስኖር በሸገር ሬዲዮ ጣቢያ ያደረጉትን ቃለ መጠየቅ ደጋግሜ ካዳመጥሁ በሗላ ግን በቅርብ የማገኛቸውን ወዳጆቼን ስለ ፕሮፌሰር መስፍን ቀደም ሲል የነበረኝ መረዳታ የተሰሳተ እንደነበር ገልጬ ይቅርታ ጠይቄአለሁ።
”ፕሮፌሰር መስፍንን ለቀቅ” የሚለው የአቶ አንተነህ መርዕድ ጽሁፍ ማስተላለፍ የፈለገው ምን እንደሆን ከመገመት ያለፈ ባላውቅም ከራሴ መረዳት፤
1ኛ/ አቶ አንተነህ ፕሮፌሰር መስፍንን ካለማወቅ በየዋህነት የጻፉት
2ኛ/ ፕሮፌሰር መስፍንን በማወቅ፤ ግን አቶ አንተነህ ስለሳቸው መናገር ፈርተው የፕሮፌሰሩን ማንነት የሚያውቁ ግለሰቦች ፕሮፌሰሩን በማጋለጥ ከነማስረጃቸው እንዲመጡ ለመጋበዝ
3ኛ/ ከ23 ዓመት በሗላ በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ዘመቻ የሚያጋልጥ ሞረሽ ወገኔ የሚባል ሲቪክ ድርጅት ተፈጥሮ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በካናዳና በአውስትራሊያ በተጠናከረ መልክ ከመደራጀቱ ተጨማሪ አባሎቹና ደጋፊዎቹ ግልጽ ያለመሆናቸው በህዝብ መካከል የፈጠረው መጠራጠር አስደንግጧቸው፤
4ኛ/ ወይም የፕሮፌሰር መስፍንን ቃል ልጠቀምና ”ልፋጭ አንጋጣጮች” እንደሚሏቸው የሞረሽ ወገኔን ሊቀመንበር በመስደብ ከትግራይና ከሌሎች አክራሪ ብሄረተኞች በልፋጭ አንጋጣጭነት
5ኛ/ ወይስ አቶ አንተነህ እንዳሉት ፕሮፌሰር መስፍን ጃጅተዋል እና ክደዋል መባላቸው አስቆጥቷቸው፣ ከሆነስ ለምን የሞረሽን ሊቀመንበር መዝለፍ ተፈለገ?
ለሁሉም አቶ አንተነህ አስቆጣኝ ያሉትን ”ጃጄ እና ከዳ” ለዛሬ ጽሁፌ በመንደርደሪያነት ልውሰድ፣ የአቶ አንተነህን ጽሁፍ ከማንበቤ ቢያንስ ከ10 ቀን በፊት ”ሞረሽ ወገኔ የባህል ማህበር በስዊድን” በ 24/10/2014 ”በአርባ ጉጉ እና አካባቢው በአማራው ህዝብ ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል መካድ አይቻልም” ሲል ባወጣው ጽሁፍ ለምን እንዳልቀጠለ ጠይቄአቸው፤ በአንድ አካባቢ በተፈጸመ ዘር ማጥፋትና በአንድ ሰው ንግግር ማተኮሩ በጊዜው በተከሰተብን የጊዜ እጥረት ላይ በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል እየተከታተሉ የማጋለጫ ጊዜያችንን ከመሻማቱም ተጨማሪ በተለይ በግለሰብ ላይ የማተኮር ፍላጎት እንደሌላቸውና ጉዳዩን ለግለሰቦች እንደተውት ነግረውኝ፤ እኔንም አሳምነውኝ፤ ስለፕሮፌሰር መስፍን ያለኝን ቅሬታ እኔም እንደነሱ ቸላ ብዬ ትቸው ነበር።
ፕሮፌሰር መስፍንን ለነቀፋ የዳረጋቸው በተከታታይ በሸገር ሬዲዮ ጣቢያ የሰጡት ቃለ መጠየቅ ነው። በዚህ ቃለ መጠየቅ አንዳንድ እሳቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ”እናንተ የምታደንቁትን ሰው የተደበቀ መልኩን በጨረፍታ ያሳየ ቃለ መጠይቅ ነው” ሲሉ ሌሎች ደግሞ ”መስፍን ቀባሪ አጣ፣ የአውስትራሊያ ጉዞውም ለመስፍን ነፍስ ለመዝራት ነው” ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ ቃለ መጠየቁን በደንብ ሳያዳምጡና ፕሮፌሰሩን ሳይከታተሉዋቸው ቀርተው ሊሆን ይችላል አሁንም ቢሆን ለፕሮፌሰር መስፍን የላቀ አክብሮት አላቸው። ሆኖም ከፕሮፌሰሩ ወገን ሆኘ ሳየው ያን ቃለ መጠየቅ ባላደረጉ ኖሮ እላለሁ። ለኔ ግን፣ ቃለ መጠየቁ ባይኖር ኖር ፕሮፌሰሩን ሳላውቃቸው እቀር ነበር ብዬ በዚህ የፕሮፌሰሩን ማንነት በጨረፍታም ቢሆን ባስደመጠን ቃለ መጠየቅ እደሰታለሁ።
ፕሮፌሰር መስፍንን አንዳንዶቹ እንደሚያደንቋቸው፣ እንደሚሸልሟቸው፣ እንደሚጽፉላቸው ሳይሆን ከቃለ መጠየቁ በሗላ ያ የሰጠናቸው ክብርና ካባ ተገፎ እርቃናቸውን የቆሞ ናቸው የሚል መረዳት አለኝ። ከእንግዲህ በሗላ በቁም እያሉም ሆነ ከዚህ ዐላም እንደማነኛውም ሰው ከተለዩ በሗላ ታሪክ የሚያስታውሳቸው ከዚህ በፊት ከነበራቸው ስምና ክብር በተቃራኒው መሆኑን በተከታታይ ለማውጣት በማስበው ጽሁፍ ለማሳዬት እሞክራለሁ። በዚህም ጽሁፌ አቶ አንተነህ መርዕድ ከቻሉ በውይይቱ ቢካፈሉ አንባቢ በነቃፊና በደጋፊ መካከል በሚደረግ ውይይት አንባቢም ሆነ እኔና አቶ አንተነህ የምንማረው ነገር ይኖራል የሚል ግምት አለኝ።
ፕሮፌሰር መስፍን ከመለሰ ዜናዊ ጋር ባደረጉት የቴሌቪዥን ውይይት ”አማራ የለም” ሲሉ ውነታቸውን ነው ብዬ በአደባባይና በጽሁፍ ነቃፊዎቻቸውን ተሟግቻለሁ። ምክንያቱም፣ በዚያን ጊዜ የሳቸው አማራ የለም የገባኝ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ነው ከሚል የግል እምነቴ በመነሳት የራሴን ትርጉም በመስጠት ነበር።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት በጦርነትም ሆነ በህዝብ መፍለስ ባደረገው ከቦታ ቦታ መዘዋወር አንድነቱን በመፍጠሩ ዛሬ ህዝብን እያጋጩ በስልጣን ላይ ለመቀመጥ ካልሆነ በቀር የኢትዮጵያን ህዝብ አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ቆቱ፣ ከንባታ፣ ሀዲያ ወዘተ ብሎ መለየት አይቻልም። ሌላው ቀርቶ ዛሬ ትግሬዎች ነን ብለው ስለሚኮፈሱ ትግሬዎች አንድ የታሪክ ተመራማሪ ”ትግሬዎች፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በሰሜን በኩል ሀገርን ከውጭ ወራሪ ለመከላከል ባደረገው ዘመቻና ጦርነት ስንት ነፍጠኛ በናቶቻቸው ጭን እንዳለፈ አያውቁም” እንዳሉት፣ የዛሬ የትግራይ ብሄረተኝነት አክራሪዎች እናቶቻቸውን እንጂ አባቶቻቸውን የሚያውቁ አይመስለኝም። ለዚህም ነው መለሰ ዜናዊ ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር ባደረገው ውይይት አማራ የለም ሲሉ የተቃውሞ ምልክት፣ አሁን ካድኸኝ አይነት ነገር ያሳየው። ታዲያ ያን የቴሌቪዥን ውይይት ዛሬ ጋ ሆኜ ሳዬው፣ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን ህዝብ እንደኔ አንድ ህዝብ ነው ብለው ከማመን ሳይሆን እሳቸው ካላቸው ስር የሰደደ የአማራ ህዝብ ጥላቻ አስበው፣ አልመውና አቅደው የሰጡት መልስ ይመስለኛል። ይሄንን ጥላቻቸውን ከራሳቸው ንግግርና ጽሁፍ በቀጣይ ጽሁፎቼ ለማሳየት እሞክራለሁ። በዚህ የቴሌቪዠን ውይይት አድናቂያቸው አቶ አንተነህ መርዕድ ያለተረዱት የመሰለኝ፣ ይህ ውይይት ከመደረጉ በፊት ፕሮፌሰር መስፍን ከመለሰና ከኢሳያስ ጋር ተወያይተውና ተማምነው፣ መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብለው አምነውና ደግፈውት እንዲሁም የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው ስለነበር፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውይይት እንዲሆን የተፈለገው ፕሮፌሰር መስፍንን የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሚያከብራቸው መለስ ዜናዊን የኢትዮጵያ ህዝብ በሳቸው መልክ እንዲያየው የተቀነባበረ ቲያትር መሆኑንና፣ ፕሮፌሰር መስፍን ከመለሰ ዜናዊ ጋር ያላቸው ወዳጅነትና መግባባት ለህዝብ ለማሳየት መሆኑን አቶ አንተነህ የተረዱት አይመስለኝምና በድጋሚ ቃለ መጠየቁን እንዲያዳምጡት እጠይቃለሁ።
ከላይ እንዳልሁት ለዛሬው አቶ አንተነህ ሁለት ወር አስበው፣ ከወዳጅና ከጓደኛ መክረው በድፍረት ለፕሮፌሰር መስፍን ጠበቃ ለመቆምና ለመጻፍ ያነሳሳቸው ፕሮፌሰር መስፍን ጃጁና ካዱ መባላቸው ነው። እኔ ጃጄ የሚለውን ቃል የምረዳው፣ አንድ ሰው በእድሜው መግፋት ምክንያት ነገሮችን መርሳት ጀመረ ማለት ሆኖ ነው። ይህ የመርሳት ነገር ደግሞ አሁን እንዲያውም አንድ ሰው በወጣትነት እድሜ ላይ እያለ የሚጠቃበት በሽታ ሆኖዋል። ታዲያ ሞረሽ ወገኔ ፕሮፌሰር መስፍንን ጃጁ ሲል ከስድብነቱ ይልቅ እንዲያውም በአንድ ህዝብ ላይ ክፋት አስቦ ነገር ከጀርባው ላዘለ ንግግራቸው በእድሜያቸው ምክንያት አድርጎ ህዝብ ይቅርታ እንዲደረግላቸው የሚጠይቅ ”ይቅርታ ልመና” ሆኖ ነው ያገኘሁት። ካዱ የሚለው ቃልም ቢሆን፣ አንድ ሰው በቃል፣ በጽሁፍና በድምጽ እንዲሁም የሰው ምስክር ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ ብዙ ሰው በሚያዳምጠው ራዲዮ አልሆነም፣ አልተደረገም፣ አልነበረም ብሎ ሲናገር ካደ ከማለት የተለየ ቃል እንዳለው አቶ አንተነህ አማራጩን አልሰጡንም። አንድ ሰው የሆነን አልሆነም፡ የተደረገን አልተደረገም፣ የተፈጸመን አልተፈጸመም ካለ፣ ካደ ይባላል። ሰውየውም ሌላ አዲስ ቃል ካልተፈጠረለት በቀር ከሀዲ ይባላል። ፕሮፌሰር መስፍን በቃለ መጠይቃቸው በአርባ ጉጉው የአማራውን ህዝብ እልቂት አልካዱም? ክህደታቸውስ ከሀዲ አያሰኛቸውም? ወይስ በአርባ ጉጉ አማራው የኢትዮጵያ ህዝብ ቤት ተዘግቶበት፣ ቤተክርስቲያንን ሙጥኝ ያለ ከነቤተክርስቲያኑ ተከቦ በሞርተር አልነደደም?
ፕሮፌሰር መስፍንን ከሀዲ ያሰኛቸው ንግግር በሸገር ሬዲዮ ጣቢያ የአርባ ጉጉን ጭፍጨፋ አስመልክቶ በተጠየቁት ጥያቄ ”በአርባ ጉጉ የሞተው ኦሮሞው ነው፡ አማራ የሚባል ህዝብ የለም” ማለታቸው ነው”
በዚህ ንግግራቸው ፕሮፌሰሩ፣ እስላም ኦሮሞዎች ክርስቲያን ኦሮሞዋችን ገደሉ፤ እስላም ኦሮሞዎች የክርስቲያን ኦሮሞዎችን ቤተ ክርስቲያን አቃጠሉ፤ ለማለት ይሆናል። ምክንያቱም በግንቦት ወር 1984 በኦህዲድ ሰራዊት፣ በጉልበት የደከሙና መሸሽ ያልቻሉ በቤታቸው እያሉ መንደሮች በላውንቸር ሲወድሙ፣ ሰውና ከብት እንዳይወጣና እንዳይሸሽ ሆኖ ከቤቱ ጋር አብሮ ነዶዋል፤ ወደ ቤተክርስቲያን ሸሽተው ቤተክርስቲያን አጥር ጊቢ የገቡ ህጻናት፣ እናቶችና አዛውንት እንዲሁም ካህናት መስቀል ይዘው እግዞ እያሉ አብረው ከነቤተ ክርስቲያናቸው እንዲነዱ ለሁሉም ወንጀሎች ትእዛዝ ሰጪና አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ሀሰን መሀመድ የኦህዲድ ተወካይ የመንግስት ምክር ቤት አባል በመሆናቸው፣ ፕሮፌሰሩ ሊሉን የፈለጉት አቶ ሀሰን መሀመድ እስላም በመሆናቸው እስላም ኦሮሞሞቹ ክርስቲያን ኦሮሞዎችን ገደሉ ከሆነ በቀጣይ ጽሁፌ ስለ አርባ ጉጉ እልቂት ሳነሳ ግልጽ የሚሆን ይመስለኛል።
በዚያው ቃለ መጠየቃቸው አማራ ማለት ክርስቲያን ማለት ነው ስለሚሉ፣ ክርስቲያን ኦሮሞ የለም? ለማለት ከሆነ በጊዜው በዋናነት ትእዛዝ ሰጪ የነበሩት ሰው ስለሀይማኖታቸው እርግጠኛ ባልሆንም አቶ ኩማ ደመቅሳ ክርስቲያን ይመስሉኛል። በአሩሲ ውስጥ ስላለው የኦሮሞ እስላሞችና ክርስቲያኖች ጉዳይ ከተነሳ ደግሞ የፕሮፌሰር መስፍን ንግግር ከጅዋር መሀመድ ንግግር ጋር የሚቀራረብና አንድ መልክት የሚያስተላልፍ ሆኖ እናገኘዋለን።
ፕሮፌሰሩ ”የወንድ በር መውጫ” በሚሉት ጽንሰሀሳባቸው እነማንን ነጻ ለማውጣት አስበው ነው? የሚለውም ሌላ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርብ ጉዳይ ነው። እንዲሁም ፕሮፌሰር መስፍን በአማራ ህዝብ ላይ ባላቸው ጥላቻ በአርባ ጉጉ በተደረገውን ጭፍጨፋ ተጠያቂ እንዳይኖር ለማድረግ ከሆነም፣ የሚያዛልቅ አይመስለኝም። ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖረው የአማራው ህዝብ ለመጨረሻ ጊዜ ”በቃ ብሎ” ሞረሽ ወገኔ የሚል ሲቪክ ድርጅት አቋቁሞ በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ዘመቻን በሚቻለው መንገድ ሁሉ ለመታገል የሚያደርገውን ትግል፣ የፕሮፌሰር መስፍን አድናቂ የሆኑት አቶ አንተነህ መርዕድ ድርጅቱን ከመንቀፍ አልፈው ድርጅቱ ሊቀ መንበር አድርጎ የመረጣቸውን ሰው መዝለፍ፣ በአማራው ህዝብ ላይ ለሚፈጸመው ግፍ ተባባሪነትን ከማሳየት ያለፈ ሆኖ አይታየኝም። በችኮላ ለተጻፈው ጽሁፌ ይቅርታ እየጠየቅሁ በሚቀጥለው ጽሁፌ እንገናኝ።
ይቀጥላል
ጣሰው አንተነህ፣ ከስዊድን (tasewanete@gmail.com)
Average Rating