የኢትዮጵይያ የወቅቱ ኣምባገነናዊ መንግስት ( የወያኔ ሰርእት) በ23 ኣመታት የግፍና የጭቆና ኣገዛዝ ህዝቡ ላይ አሰቃቂ በደሎችን ፈጽሟል። ኣረመኔ የወያኔ ባለስልጥናት የኢትዮጵያን ኣኩሪ ታሪክ በመደምሰስ አጅግ ኣሳፋሪና ኣንገት ኣስደፊ የድህነት የአንግልት የዘረኝነት አንዲሁም የኣምባገነናዊነት ታሪክ በኣገሪቷ ላይ አየሰሩ ሁለት ኣስር ኣመታትን ኣሳልፈዋል።
በታሪካችን አያሌ ፈተናዎች ገጥመውናል።
ብዙም ጊዜ ታግለን ጥለናቸዋል፣በተለይ ዛሬ በደረስንበት ሁሉ አንገታችንን ከክብር ጋር ቀና አድርገን መሬት ለመርገጥ ድፍረትን የሚሰጡ ገናና ታሪኮች አሉን።ከአክሱም ከላሊበላ ከጎንደር ስልጣኔዎችና የገዳ ዲሞክራሲና ከሌሎች አያሌ የታሪካችን አምዶች ተርታ ልጠቅሰው የሚገባኝ ሌላው ሁነኛ የታሪካችን አምድ ለጥርኝ አፈራችን እንኩዋን የመሰሰት የአይበገሬነት ታሪካችነ ነው።እኛ ባናወሳው ጣሊያኖች ግብጾች ቱርኮችና ሌሎችም የተፋለሙአቸውን አጫጭር ቀጫጭንና ጠያይም እሳት የሚተፉ አይኖች ያሏዋቸው ጀግኖች አባቶቻችን ሳይወዱ በግድ ይዘክሩዋቸዋል።ታዲያ አባቶቻችን የሃገር ፍቅራቸውን መሰረት ምን እንደሆነ ሊጠየቁ ቢችሉና ቢነሱልንም መታደል ነበረ።
አባቶቻቸው ያስረከቡቸውን አገር ከእነክብሩ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የመኖራቸው አንዱ ትርጉም አድርገው ይወስዱት ነበረ።ከእነሱ በፊት ለነበረው ትውልድ ያላቸውን ውለታና በእቅፋቸው ለሚገኘው ትውልድ ያላቸውን ፍቅርና ራእይ የሚገልጹት ለራሳቸው እንኩዋን ባለመሳሳትና ለሃገር ክብርና ነጻነት ተሰውተው ዘመናቸውን ማሳረግ እንደ ትልቅ የተሳካ ፍጻሜ ይቆጥሩት ነበር።
የታሪክና የትውልድ ትርጓሜንም በሚገባ ይረዱት ነበር ብዬ አስባለሁ።
ከሁሉ በላይ ግን እትብታቸው ለተቀበረበት በኋላም እነእርሱ ላሸለቡበት ምድር ለተነፈሱት አየር ለተጠለሉበት ሰማይ ለሚጠሩበት የሃገር ስም ለሚወክሉት ባንዲራ አገራቸውን ለመጠበቅ ተገን ለሆናቸው ጋራና ሸንተረሮች እና ሌሎች አገራዊ እሴቶች ትልቅ ፍቅርና አክብሮት ነበራቸው፥ መስዋትነቱንም በሚፈለገው ደረጃ የተወጡት ከዚህ አንጻር ይመስለኛል።
በአሁኑ ዘመን ኢትዮጵያዊ ትውልድ አንገት የሚያስደፋው አምባገነኖች የአባቶቻችን የመስዋትነት ውሎዎች የሚያረክስ ፍጹም ኢትዮጵያዊ ስሜት የተለየውና ታሪካችንን የሚያንቋሽሹ የክህደት ተግባር መፈጸማቸው ነው።ለዚህም ውለታቸው ራሳቸውን ስልጣን ሸልመው ያቆሸሹት ታሪክ ተጠሪዎች ነን ብለው አይናቸውን በጨው ታጥበው በጫንቃችን ላይ ተፈናጠውብናል።
የኢትዮጵያ ህዝብ የሃገሩን የዳር ድንበር ወደኋላ የሚል ባይሆንም አብዛኛው የዓለም ህዝብ የነጻነት ጮራ በሚሞቅበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰማያችንን ከወትሮው የከፋ የጭቆና ጥቁር ደመና ጋርዶታል።ክቡር በሆነው መብቱ ተጠቅሞ መሪዎቹን መምረጥ አይችልም፣ድምጹን የማስጠበቅ መብት የለውም፣ከጠየቀ ይወነጀላል፣መብት ይገባኛል ካለ ይገደላል።የእሱ መብት መሞት ነው፣የአምባገነን ገዢው መንግስት ወያኔ መብት ደግሞ መግደል ነው።ከደመና ከሚዘንበው የአምባገነኖች ጥይት እየተበላ በየማጀቱ ድምጽ አውጥቶ ለማልቀስ እንኩዋን ነጻነት የለውም እየሞተም ስለሞቱ የመናገር ነጻነት የለውም።ይልቅስ እየሞተ ስለህይወቱ ስለልማቱና ከልማቱም ስለተገኘው ፈንጠዝያ በባዱ አንጀቱ እንዲጨፍር ይገደዳል።የትያትሩ ፈቃድ አልባ ገጸባህሪ ነው፣እንደተጠየቀውም ይፈጽመዋል።
አሁን ያለው የወያኔ ስርዓት በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ከፈጸማቸው አያሌ በደሎች ውስጥ ምንአልባት ከፍተኛው የኢትዮጵያን ህዝብ ለመለያየት አፌሴላዊ በሆነ መንገድ የተከተለው እጅግ ዘረኛና ከፋፋይ የሆነው ስሌቱ ነው፣ለዘመናት በደምና በስጋ የተገመደው የኢትዮጵያዊያን አንድነት ሆኖ እንጂ በሌሎች አንዳንድ አገሮች ላይ የተፈጸመ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ተበታትነን በቀረን ነበር።ያም ሆኖ አገዛዙ በኢትዮጵያ በህዝቡዋ ላይ ያደረሰው በደል ሰንበር አሁን ጉልህ ሆኖ ይታያል።በወያኔ አገዛዝ ዘመናት ውስጥ ከ34 ጊዜ በላይ ኢትዮጵያውያን ዘር ቆጥረው ሰይፍ ተማዘዋል ደም ተፋሰዋል፣ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም በወያኔ ስርዓት የተፈጠረው ወጣት አንዱ ከአንዱ ጋር እንዳይግባባ ብሎም አንድ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ማህበረሰብ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ደባ ተሰርቷል።እየተሰራም ይገኛል።የዚህ ሁሉ ስሌትና የደም ግብር ማጠንጠኛው መሪዎቻችንን ስልጣን ላይ አውሎ ማሳደር እንደሆነ ክፉ ተግባራቸው ሁነኛ ምስክር ነው።
ጥቂቶች ደግሞ ከኑሮ ጋር በሚገጥሙት ግብግብ የኢህአዲግ አባል በመሆን የእለት ኑሮአቸውን ማሸነፍ ይፈልጋሉ። አባል ይሆናሉ፣ ኢህአዲጋዊ ተልእኮ ይቀበላሉ፣ይፈጽማሉ ለውለታቸው ዋጋ ይከፈላቸዋል፣ህዝብ እንዲረግጡ ይታዘዛሉ፣እንደታዘዙት ያደርጋሉ፣ከገዛ ህሊናቸው ጋራ ጥዋትና ማታ ፍሊሚያ ይገጥማሉ።ነገሩ ውስብስብ ነው።ያለ ትምህርት ደረጃቸውና ያለአቅማቸው ስልጣን ይደራረብባቸዋል፣ከህዝብና ከህሊናቸው ጋር ተቃቅረዋል፣ለህሊናቸው ቢሸነፉ ሽብርተኛ ተብለው ይታሰራሉ ወይም ከሃገር ይሰደዳሉ።ወደ ህዝብ ቢወርዱ ከህዝብ ጋር ደም ተቃብተዋል፣ በሰላም መኖር ቢችሉ እንኩዋን የኢህአዲግ አባል በመሆን የደፈኑት ጉሮሮ እንደገና ጦም ሊያድር ነው።
ኢህአዲግ የሚሰጣቸውን የጭቆና ተልዕኮ እየፈጸሙ ከህሊና ጋር ጥዋትና ማታ እየተሟገቱ መኖር የመኖር ተልኮዕቸው ሆኑዋል።ይህ የብዙ ኢህአዲግ የሚመስሉ ወጣቶች ህይወት ነው። በዚህ ሁኔታ ነው አግዛዙ በህዝብ ላይ ጭቆናን አንግሶ የቀጠለው።እነእርሱም ከህሊናቸው ሙግት መዳን ይፈልጋሉ።እነእርሱም ነጻነት ይናፍቃቸዋል፣አገዛዙን መገላገል የሁልጊዜም ህልማቸው ነው።ነገር ግን እንዴት የሚለው ጥያቄ ያስጨንቃቸዋል።
የፍትህ ስርዓቱ መቀለጃ ከመሆኑ የተነሳ ህዝቡ ከፈጣሪ በቀር የሚተማመንበት አንዳች ነገር እንደሌለው እርግጥ ነው።እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ነጻነት አልባ ህይወት እየኖሩ የሚደርስባቸውንና የሚሰማቸውን እንኩዋን በድፍረት አለመናገርን እንደ ብህልነት ወስደውታል።
የወያኔ አግዛዝ በሃገራችንና በህዝባችን ላይ የፈጸማቸው በደሎች ሁልግዜም የሚያመን ቁስል ነው።ፈውሱም መታገል ነው።የኢትዮጵያ ህዝብ በተደጋጋሚ ወራሪዎችን ተፋልሞ አስደማሚ ታሪክ ሰርቷል።ከገዢዎቹም ጋር ግብ ግብ ገጥሞ ጥሏዋቸው ያውቃል።መዘውሩን ግን በእጁ ጨብጦ እስከወዲያኛው የነጻነቱ ባለቤት ለመሆን እስከአሁን አልቻለም። ከእዚህ ሁሉ የጭቆናና የአፈና ዶፍ በሃላ የኢትዮጵያ ህዝብ ማቁን ጥሎ ትቢያውን አራግፎ እንደሚነሳ ለአፍታም አንጠራጠር።እስክአሁን ያላቆምነውን ከቅርሶቻችን በላይ የላቀውን ታላቅ ሀውልት በአንድነት እናቆማለን። የነጻነታችን የአንድነታችን የእኩልነትና የወንድማማታችን ምልክት እንዲሁም የደም የአጥንታችን ተምሳሌት በሆነው ባንዲራችን የተገነባችው ኢትዮጵያ ሃገራችን ጥላ ስር ለመሰባሰብ እንድንችል ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥል።
በአቤኔዘር ኣህመድ
ከጀርመን
Average Rating