www.maledatimes.com ሃና ማለት እኛ ነን! “we are Hana” by rahel gebregeziabher - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ሃና ማለት እኛ ነን! “we are Hana” by rahel gebregeziabher

By   /   November 19, 2014  /   Comments Off on ሃና ማለት እኛ ነን! “we are Hana” by rahel gebregeziabher

    Print       Email
0 0
Read Time:2 Minute, 19 Second

በመንገዳችን ሁሉ ዋስትና የሌለን፣ በኑሯችን ሁሉ ከለላ የሌለን ሃና ማለት እኛ ነን!! ሃና እድለኛ ሆና ስለፍትህ ተዘመረላት ስንት ሃናዎች ግን ያለፍህት ሞቱ፡፡ ስንት ሃናዎች ግን ህዝብ ሣያውቃቸው ተቀበሩ፡፡ ጉድ አንድ ሰሞን ነው ይላል ያገሬ ተረት ሁሌም አንድ አዲስ ነገር ሲፈጠር ጉድ ጉድ ከማለትና የአንድ ሰሞን ወሬ ሆኖ ከማለፍ የዘለለ የህዝብን ቁጣ ቀስቅሶና አሳምፆ መቀጣጫ የሚሆን ቅጣት ሲሰጥ በዘመኔ አላየሁም፡፡

ምን አልባት በዘመኔ ያየሁት ነገር ቢኖር የሰው ልጅ ያደርገዋል ከሚባለው በላይ ጭካኔን ነው፡፡ አንድ ሰሞን ሴቶች ላይ አሲድ ተደፋ ተብሎ ኡኡ ተባለ ምን አልባት ከሚላት የመጀመሪያዋ ሴት ላትሆን ትችላለች ግን እድለኛ ሆና ስለፍትህ ተዘመረላት አሲድ መድፋትም ብርቅ ነበርና ወሬው አገሩን ናኘው፡፡ ከዛ በሃላ ግን ብዙ ካሚላቶች በአሲድ ሲነዱ ማንም አላስታወሳቸውም ማንም አልዘመረላቸውም ምክንያቱን አሲድ መድፋት ብርቅ አይደለማ ለመድነውና ተውነው፡፡ አበራሽ አይኗ ወጣ ይሄም ብርቅ ነውና እድለኛ ሆና ተዘመረላት፣ ተንጫጫንላት ግን ከሷ የባሰ አካል ጉዳት ደርሶባቸው የተሰናከሉ፣ ከፍተኛ ጥቃት ደርሶባቸው የወደቁትን ማንም አላወቃቸውም ማንም አላስታወሳቸውም!! ምን አልባትም የአበራሽ አይን መውጣት ለሌሎች አምባገነን ወንዶች ትምህርት ሆኗቸው አይን ማውጣትም ይለመድ ይሆናል፡፡ የሃና መደፈርና ለሞት መብቃት ዜና ለኛ አዲሳችን አይደለም ጆሯችን እስኪደማ ነብስ ያላወቁ ህፃናት ተደፍረው ማለፋቸውን ሰምተናል፡፡

ዛሬ ስለሃና ፍህት ብንዘምርም ነገ እንረሣታለን ተረኛዋ ሃና ሌላ አሰቃቂ ድርጊት ተፈፅሞባት እስከምንዘምርላት፡፡ እንዲህ እላለሁ እኔ ሁሌም ዝማሬያችን ሃይል የለውም ሁሌም መዝሙራችን ህጉን አይንደውም፡፡ ምክንያቱም ከስሜት የመነጨ እንጂ ለፍትህ የቆመ ዝማሬ የለንምና፡፡ እኔ ስራዬ ሆኖ እናንተ ካወቃችኋት ሃና በላይ ብዙ ሃናዎችን አውቄያለሁ የሰው ልጅ ስንት ነብስ አለው? እንዴትስ ይሄንን ሁሉ ስቃይ መቋቋም ይችላል? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ከአእምሮ በላይ የሆነ አሰቃቂ ድርጊት የተፈፀመባቸውን ሴቶች አናግሬያለሁ፡፡ ይሄንን ፕሮግራም ስሰራ ወንዶች እንደአውሬ በሰንሰለት ታስረው ፍርግርግ ውስጥ መኖር ያለባቸው ፍጡሮች ናቸው የሚል እሳቤ ውስጥ ከቶኝ ነበር፡፡

ሴቶቹ ካረፉበት መጠለያ አናግሬያቸው ስወጣም በቀጥታ እናቴ ጋር ደውዬ ነበር ፈፅሞ እንደማላገባ ለመንገር ምክንያቱም ስሜቱ ከባድ ነበርና፡፡ ለ3 ተደፍራ ከነነብሷ ጉድጓድ ውስጥ የተቀበረችና ሙሉ አካላቷ ሽባ የሆነችን ሴት ኢንተርቪው ማድረግ፣ በገዛ አባቷ የተደፈረችን የ8 አመት ህፃን ማናገር፣ ከሰው እንዳልተፈጠሩ በደረሰባቸው አሰቃቂ ጥቃቶች ሰውን እንደአውሬ የሚሸሹ ድንጉጥ ነብሶችን ማየት…. የሚፈጥረውን ስሜት አልናገረውም፡፡ በየጓዳው ብዙ ሴቶች ያለፍትህ ተሰብረው ቀርተዋል፣ ብዙ ሴቶች ገመናቸው ተሸፍኖ ያለፍትህ መቃብር ወርደዋል፡፡ አደባባይ በወጣውም ድርጊት በሃዘን ልባችን ተነክቶ በስሜታዊነት ከመጮህ ውጭ ስለእውነት ብለን ለፍትሃቸው አልታገልንም፣ ጉዳቱ ያሣምመናል እንጂ የእኔነት ስሜት ፈጥሮብን ከጎናቸው አልቆምንም፡፡ የሴቶች ጥቃት አልፎ አልፎ በአደባባይ እንደምንሰማው በተወሰኑ ጊዜያቶች የሚፈፀሙ ድርጊቶች አይደሉም ሁሌም አሰቃቂ ጥቃቶች አሉ፣ ሁሌም ለጆሮ የሚከብዱ አዳዲስ ድርጊቶች ይፈፀማሉ፡፡

የሰው ልጅ የሚያድገው የሚሰለጥነው የጥቃቶችን አይነት ከፍ ለማድረግ እስኪመስል ድረስ በየጓዳ ጎድጓዳው ብዙ ታሪኮች አሉ አደባባይ መውጣት ያልቻሉ፣ ሰሚ ያላገኙ፣ ጩኸታቸውን የተቀሙ፡፡ ተማርንለት የምንለው ዘመን፣ የሴቶች እኩልነት፣ የሴቶች መብት ተከበረ የምንልበት ዘመን አልተማሩም ከምንላቸው አባቶቻችን የከፋ ጭካኔና ፍፁም ሰይጣናዊነት የሰፈነበት ሆኗል፡፡ ዛሬ ሃና አልፋለች ስለ ፍትኋም እየዘመርን ነው ሌሎች ሃናዎች ግን ነገም ያልፋሉ ምክንያቱም ጩኸታችን ስሜታዊ ነውና፣ ጩኸታችን ዛሬን አያልፍምና፡፡ እስኪ እንዲህ እናድርግ ፍትህ ለሃናን ግንቡ እስኪናድ ጮክ ብለን እንዘምረው፣ መዝሙራችንን እናጠንክረው፣ ድምፃችንን ከፍ እናድገው፣ ጩኸታችንን እናጉላው…. ፍትህ ለሃና! ፍትህ በየቤቱ ለጠፉ ሃናዎች! ፍትህ በየቤቱ በጥቃት ለተሰበሩ ሃናዎች! ፍትህ ለሰው ልጆች!….. ፍትህ… ፍትህ… ፍትህ…… please share on tweeter by #WEAREHANA Thanks Maleda Times Media Group

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on November 19, 2014
  • By:
  • Last Modified: November 19, 2014 @ 10:36 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar